ከአፄ ኃይለሥላሴ ጀምሮ የህዝብ እንደራሴ ሆነው ህዝባቸውን አገልግለዋል። በደርግ ደግሞ የጠቅላይ ፍርድቤት ዳኛ ሆነው በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሰርተዋል። ከ20 አመት በላይ በዳኝነት ቢያገለግሉም ህወሓት በዘረጋው ሀገር አፍራሽ የአስተዳደር መዋቅር ባደረጉት የሰላ ትችት ያለጡረታ ከስራ አሰናብቷቸዋል። ከዚያ በኋላ ያለጡረታ እስከ 2009 ዓ.ም በግላቸው በጥብቅና ሰርተዋል። በአሁኑ ወቀት የሀገር ሽማግሌ፣ የኢትዮ – ሱዳን የድንበር ኮሚቴ እንዲሁም የወሰንና ማንነት ኮሚሽን አባል ሆነው በሀገር ሽማግሌነት እያገለገሉ ይገኛሉ።
የዛሬው የወቅታዊ አምድ እንግዳችን አቶ ባዩ በዛብህ ናቸው። የዝግጅት ክፍላችንም ከእኚህ ባለሙያ ጋር በኢትዮ- ሱዳንና በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ቆይታ አድርጓል፤ መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- በሀገሪቱ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ እንዴት ይመለከቱታል?
አቶ ባዩ፡- በሀገራችን ያለው ሁኔታ ከ2010 ጀምሮ የለውጥ መንግስት መምጣቱን ተከትሎ ህወሓት የፈጠረው ጥቁር ጠባሳ የማይረሳ መጥፎ ታሪክ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን በተፈጠረው ስንጥር ሱዳን ሉአላዊነታችንን ተዳፍራ የምትገኝበት ወቅት ነው። መንግስት እየወሰደ ባለው የህግ ማስከበር ዘመቻም ፈረሳቸው ህወሓት የሆኑ ምዕራባውያን ትኩሳት የተፈጠረበት ወቅት ላይ እንገኛለን።
አዲስ ዘመን፡- ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር ጥሳ መሬት የወረረችበት መንገድን ከምን የመነጨ ነው? የሱዳንና የኢትዮጵያን ህዝቦች የቆየ ትስስር አያጎድፍም?
አቶ ባዩ፡- የሱዳን የመሬት ይገባኛል ጥያቄ ከቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ጀምሮ የተነሳና ሁለቱም ሀገሮች በጋራ ለመፍታት ስምምነት ላይ የደረሱበት መንገድ ነበር። ነገር ግን ሱዳን አሁን ያደረገችው ወረራ ‹‹ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል›› እንደሚባለው ጥቅምት 24 አሸባሪው ህወሓት የሀገር ደጀን በሆነው መከላከያ ሰራዊት ላይ ባደረሰው ጥቃት መንግስት ወደ ህግ ማስከበር ሲዞር ክፍተቱን በመጠቀም ያደረጉት ወረራ ነው። ሱዳን በድንበሩ ጉዳይ ካሁን በፊት ስታነሳው የነበረው ክርክር በቀድሞው አፍሪካ አንድነት ድርጅት የቀኝ ግዛት የሀገራት ድንበር ወሰን እንዲጸና የተወሰነውን መነሻ በማድረግ ነው።
ሱዳን በእንግሊዝ ዘአንግሎ ኢጅብሻን (Anglo Egyptian) በሚል ከሱዳን እስከ አሌክሳንደሪያ በቅኝ ግዛት ውስጥ ነበረች። በዚህ ወቅት ሜጀር ጐይን የሚባል የእንግሊዝ የጦር መሃንዲስ ወታደር የኮሎኒያል ባውንደሪ ብለው ያመሩት መስመር ወሰናችን ነው ይላሉ። በኢትዮ – ሱዳን ባውንደሪ መሃከል ያለው የጐይን መስመር ስለሆነ በዚህ የሱዳን ወሰን ይጠበቅልኝ ነው። ኢትዮጵያ ደግሞ አይደለም፤ የጐይን መስመር የሚሰራ በቅኝ ግዛት ስር ወድቀው ለነበሩ አገሮች እንጂ እንደ ኢትዮጵያ ነጻ ሆና ለኖረች ሀገር አይደለም። ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግስት ምንም ተሳታፊ ባልነበረበት ጐይን ይሂድበት አይሂድበት ባልተረጋገጠበት በጎይን መስመር ብቻ የኢትዮ – ሱዳን ድንበር አይወሰንም የሚል ጠንካራ አቋም አላት። ሱዳን የምታነሳውና እያደረገችው ያለው ተግባር የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ግንኙነት የማይመጥንና ሊያሻክር የሚችል ነው።
አዲስ ዘመን፡- የድንበር ወሰኑ ከውዝግብ እንዲወጣ ወሰኑ በምን መልኩ መካለል አለበት ብለው ያስባሉ?
አቶ ባዩ፡- የኢትዮ – ሱዳን ድንበር መወሰን ያለበት በሁለቱም ሀገር አዋቂዎች፣ በተለይም በኢትዮጵያ የጠረፍ ጠባቂዎች፣ በነበሩት ስለድንበሩ ጠንቅቀው በሚያውቁ ሰዎች አማካኝነት ነው። ኢትዮጵያ ግዛቷን አስጠብቃ በነበረችበት ወቅት የሱዳን መንግስት የሚባል አልነበረም። በወቅቱ ሱዳን በድርቡሽ ማሀዲስት እና በሌሎች የጎሳ ቀበሌዎች ስትተዳደር ነው የነበረው።
ስለዚህ ኢትዮጵያ ከሀቋ ውጭ የማንንም ሀገር ሉአላዊነት መንካት አትፈልግም። ነገር ግን የኢትዮጵያ ጠላቶች ሱዳንን በገዙበት ወቅት ጐይን አስምሬዋለሁ ያለው የውሸት መስመር በኢትዮጵያ ላይ እሾህ ለመትከል አስቦ ነው። ጎይን አሰመረው ከሚባለው መስመር ፊት የኢትዮጵያ ወሰን ከሰላ፣ ገዳሪፍ፣ ቶማክ ነው። እነዚህ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የተውለበለበባቸው ቦታዎች ናቸው። በአጼ ሚኒሊክ ዘመነ መንግስት ጐይን ራሱ ድንበሩን አሰመርኩት ባለው ማስታወሻ ሲጽፍና ካርታውን ሲሰራ “ለመሬት አቀማመጥ አይመቸኝም ብዬ ከኢትዮጵያ ግዛት ገብቻለሁ” የሚል ከማስታወሻው ግርጌ ላይ አስፍሯል። ስለዚህ ሱዳኖች በመረጃና በታሪክ ላይ መሰረት አድርገው ለሰላማዊ ድርድር መቅረብ ብቸኛው መፍትሔ ነው ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለመሆኑ በሱዳን በኩል የሚነሳው የድንበር ይገባኛል ጥያቄው የጎይን መስመር ብቻ ነው ብለው ያምናሉ?
አቶ ባዩ፡- አላምንም። አሁን የብዙ ሀገሮችን ጉዳይ ተጭና ለመፈፀም እየሰራች ነው። ያለው ሁኔታ የሱዳን የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ከጎይን መስመር ያለፈ ነው። ምክንያቱም እስካሁን ጥያቄውን ማንሳት እንጂ ገፍታ ለችግሩ መፍትሔ እንዲሰጠው ጠይቃ አታውቅም። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ተገዳ የገባችበት የህግ ማስከበር ላይ ትኩረት በሰጠችበት ወቀት ከፍተቱን በመጠቀም ለመውረር ያደረገችው ሙከራ ነው። በሌላ በኩል ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ግብጽ በመካከለኛው ምስራቅና በአረቡ አለም የአሜሪካ ጉዳይ አስፈጻሚ ናት።
ስለሆነም ማንም እንደሚያውቀው ሁለቱም ሀገሮች ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ ገንብታ እንዳታጠናቅቅ የጭቃ እሾህ ሆነው የግድቡ ግንባታ እንዲስተጓጎል ለማድረግ ነው። ስለዚህ አሜሪካም ለሱዳን አንቺ በኢትዮጵያ ላይ ይህን ስታደርጊ ማዕቀብ ይነሳልሻል እና ሌሎች እርዳታዎችን ታገኛለሽ የሚል ተልእኮ ተሰጥቷታል። በዚህ መነሻ ባልፈለጉትና የሱዳንን ህዝብ በማይጠቅም መንገድ እየተጓዙ ይገኛሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ በ1902 አፀ ምኒልክ በጎይን መስመር ተስማምተዋል የሚባል አንድ ሪከርድ አለ። በዚህ ላይ በተነሳው ክርክር በቀዳማዊ ኃለሥላሴ ዘመነ መንግስት በኢትዮጵያ በኩል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ከተማ ይፍሩ እና ዶክተር ምናሴ ኃይሌ ከሱዳን መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መንሱር ካሊድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት(memorandum of understanding) ተፈራርመዋል። የ1902 የአጼ ምኒልክ ስምምነት የሚባለው ሁለቱም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አከራካሪ መሆኑን አምነውበት በ1972 እ.ኤ.አ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት በሁለቱም ሀገሮች ባሉ አዋቂዎች ወሰኑ እንዲከለል የስምምነት ፊርማ ተፈርሟል። ይህ ውሳኔ ከተወሰነ በኋላ በ2007 ዓ.ም በተደረሰው ስምምነት መሰረት የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ኮሚሽን ተቋቁሞ ተከልሏል። ይህ መካለል በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ ሰነዱ ተቀምጦ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡- ሱዳን የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ መኖሩን እያወቀች ያልተገባ ጥያቄ ይዛ መቅረቧ ምንን ያመላክታል?
አቶ ባዩ፡- ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት የአሜሪካ፣ እንግሊዝና የግብጽ ፈረስ ከመሆን ውጭ ሌላ ምንም መሰረታዊ ጥያቄ የሚያስነሳ እና ወረራ ለመፈፀም የሚያስችል ጥያቄ የለም። የጎይን መስመር እኮ አከራካሪ መሆኑ ሁለቱም ሀገሮች አምነውበት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው በኩል ስምምነት ላይ ደርሰውበታል።
አዲስ ዘመን፡- ሱዳን ከሰላም አማራጭ ይልቅ አሁን በጉልበት ወረራ ፈጽማለች የወሰኑ ጉዳይ በጉልበት የሚቋጭ ነው ብለው ያስባሉ?
አቶ ባዩ፡- በጉልበት መፈታት እንደማይችል እንኳን ሱዳን ይቅርና የእኩይ አላማ ጠንሳሿ አሜሪካም ጠንቅቃ ታውቀዋለች። ስለዚህ የወሰኑ ጉዳይ በሁለቱ መንግስታት የሁለትዮሽ ውይይት ስምምነት የሚፈታ እንጂ በጦርነትና በጉልበት የሚፈታ አይደለም። ጦርነቱ በሁለቱም ሀገሮች ጥፋት ከማስከተል በስተቀር ጥቅም ስለሌለው በውይይትና በድርድር መፍታትና ከደም መፋሰስ መራቅ ይገባል። እነሱ የጎይን መስመር ካነሱ እኛም የቶደሉክን ዘመን የገዳሪፍና የከሰላን አስተዳደር መጠየቅ እንችላለን።
ነገር ግን አሁን ሱዳን እየሄደችበት ያለው መንገድ ግብጽንና አሜሪካን ለማስደሰት እና በራሷ ውስጥ ያለውን የውስጥ ችግር ለመፍታት የምታደርገው መፍጨርጨር ነው። ሱዳን የራሷንም የውስጥ ችግር ለመፍታት የድንበሩን ጉዳይ እንደ አንድ ማስታገሻ እየወሰደች ነው። እንደሚታወቀው በሱዳን የሲቪል አገዛዝና የወታደራዊ አገዛዝ አለ። ሀምዶክ የሚመሩት የሲቪሉ አገዛዝ የኢትዮጵያን አቋም ይደግፋል። የአልቡራሃን ወታደራዊ ክንፍ ደግሞ እነ ግብጽን ለማስደሰት ይጥራል። ነገር ግን የኢትዮጵያ አቋም ልክ እንደ ህዳሴው ግድብ እንወያይ በድርድር እንፍታ፤ የጋራ ጥቅማችን ይጠበቅ የሚል ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በድርድር ላይ የተመሰረተ ሁለቱንም ሀገሮች አሸናፊ የሚያደርግ አቋም መያዟን ወደ ጎን የሚተውበት ሁኔታ ምክንያቱ ምንድን ነው?
አቶ ባዩ፡- ሱዳን አሁን ለግብጽና ለአሜሪካ ባላት የታዛዥነት ሚና ሁለቱን ሀገሮች ለማስደሰት ጉዳይ አስፈፃሚ ሆና መምጣቷ እውነታውን ለመቀበል ስለከበዳት ነው። የሰላም ጥሪ እየቀረበላት ሀሳቡን ወደ ጎን በመተው የኢትዮጵያን ሉአላዊነት መዳፈር ትልቅ ስህተት ነው። የሱዳን ሩጫ በሀገራቸው የተፈጠረውን የውስጥ ችግር ለመፍታት ለህዝቡ መሬት አስመልሰንልሃል በማለት የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በመንዛት የውስጥ ችግራቸውን ለማረጋጋት ጭምር እየተጠቀሙበት ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ሱዳን የተጓዘችበት መንገድ አይሆንም እያለ ነው። ምክንያቱም በመወያየትና ከዚህ በፊት በተጀመረው መንገድ መፈታት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- ሱዳን ወደ ሰላማዊ ድርድር ለመምጣት ያልፈለገችበት ምክንያት ምንድን ነው ይላሉ?
አቶ ባዩ፡- ሱዳን እያደረገችው ያለው በግብጽ ተጽዕኖ ስር ስለወደቀች ነው። ግብጽ እንደሚታወቀው አሜሪካ እና በሌላው ሀገር እንኳን በአፍሪካ በመካከለኛው ምስራቅ ባላት ሚና ከፍተኛውን እርዳታና ድጋፍ የሚያገኝ የግብጽ መንግስት ነው። በትንሹ 30 ቢሊዮን ዶላር ግብጽ ከአሜሪካ ታገኛለች። አሜሪካ ለግብጽ ይህን ያክል መዋዕለ ንዋይ ስታፈስ ለጽድቅ ሳይሆን ለራሷ ብሔራዊ ጥቅም በማሰብ ነው። ለምሳሌ ዶናልድ ትራምፕ በህዳሴው ግድብ ለግብጽ በመወገን ለኢትዮጵያ 127 ሚሊዮን ዶላር አገድኩ ሲሉ በ30 ቢሊዮን ዶላር እና በ127 ሚሊዮን መካከል ያለው ልዩነት ሲታይ በሁለታችን መካከል ያለውን የፍቅርና የጥቅም ግንኙነት ማየት በቂ ነው። ስለሆነም ግብጽ በአሜሪካ በሚደረግላት ድጋፍ ለሱዳን ትለግሳለች። በዚህም የኢትዮጵያን እውነታ አምኖ ለመቀበል ተቸግረዋል። ኢትዮጵያ በድርድር መረጃና ማስረጃ በመያዝ ኑ ስትል የይዞታ ማስረጃና የታሪክ ማስረጃ ይዛ ነው። ይህን ለመነጋገር የኢትዮጵያ መንግስት ለተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ለአፍሪካ ህብረት አቤቱታ አቅርቧል። ምክንያቱም የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች አብረው የሚያርሱ በመሆናቸው የሚለያቸው ነገር የለም። ግጭቱ ሁለቱን ሀገሮችን ከመጉዳት ውጭ ምንም ጥቅም ባለመኖሩ ሱዳንም ካሁን በፊት የሰራችው ተግባር ጸጽቷት ወደሰላሙ መንገድ ትመለሳለች ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ህወሓት ከማዕከላዊ መንግስትነት በህዝብ ተገፍቶ ወደ መቀሌ ከገባ በኋላ ሰላማዊ አማራጮችን ወደ ጎን ትቶ በኃይል ወደ ስልጣን ለመመለስ የመከላከያ ሰራዊትን ያጠቃበትን ሁኔታ እንዴት ይገልጹታል?
አቶ ባዩ፡- አሁን የደረሰበትን ደረጃ ለማየት አፈጣጠሩን መመልከት ይገባል። ህወሓት ገና በ1968 ትህነግ ተብሎ ትግራይ ውስጥ ሲፈለፈል ሰላም ፈላጊ ሳይሆን ሁከት ፈጣሪ ሆኖ ነው የተወለደው። በወቅቱ ቡድኑ ሲመሰረት ባልበሰለ አስተሳሰባቸውና ጭንቅላታቸው ሀገር የማፍረስ የሴራ ጉንጉናቸውን ያስቀመጡት መንገድ ነው። በወጣትነት ስሜት ብዙ የተሳሳተ አስተሳሰብ ይመጣል። ነገር ግን ህወሓት ሴራውን ከጎነጎነ በኋላ ሀገርን የመበተን እኩይ አለማ ነው ይዞ የተጓዘው።
ትህነግ የትግራይ ነጻ አውጭ ግንባር ነው። ይህን አቋቁመው እስካሉ ድረስ ሌላውን ህዝብ በስር አድርገው በጎጥ፣ በዘርና በሐይማኖት በመከፋፈል እንዲጋጭ በማድረግ ኢትዮጵያን በበላይነት ሊገዙ፤ ሊበዘብዙ ነው። ይህ እኩይ ተግባራቸው ካልተሳካ ደግሞ የትግራይን ነጻ መሬት ለመከለልና የትግራይን መንግስት ለማቋቋም ነው። አሁን ከስልጣን ከተገፉ በኋላ በግልጽ እየሰሩ ያሉት ይህንኑ እኩይ ሴራቸውን ለመፈፀም ነው። ይህ ድርጊት ራሳቸው በሳሉት ካርታ የኢትዮጵያ ህዝብ ሳይጠየቅ፣ የአካባቢው ህዝብ ሳይጠይቁ ፓርላማ ላይ ሳይቀርብ 27 አመት ሲገዙ ከዚህ ወዲህ የትግራይ ነው ብለው በዚህ የበጌ ምድርና ሰሜን ጠቅላይ ግዛት፣ የነበረውን ወልቃይትን፣ ጠገዴን፣ ጠለምትን እንዲሁም የወሎ ግዛት የነበረውን ራያ አዘቦን ወደ ትግራይ ከልለው ለሙን መሬት ወስደው ታላቋን ትግራይ ለመመስረትና ሀገር ለማፍረስ የሰሩት ሴራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ታላቋን ትግራይ መመስረት ብቻ ነበር አላማቸው?
አቶ ባዩ፡- አይደለም። ኢትዮጵያን ከአለም ካርታ አጠፋለሁ ብላ መጥታ የነበረችውን የጣሊያን ሀሳብ ለመፈፀም ህዝቡን ቋንቋውን ለያይተው 85 ቋንቋ የሚናገር ኢትዮጵያዊ አበጅተው፣ በኃይማኖት ከፋፍለው፣ በሀሰት ትርክት በስርዓተ ትምህርት ቀርፀው፣ አማራ እንዲህ አድርጓል የሚል መርዝ በመርጨት፤ ሀገር የማፍረስ ተግባር ፈጽመዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን ክልል ብለው የተለያየ የቋንቋ ክልል አጥር አበጅተው አንዱ ወደ ሌላው ተሻግሮ እንዳይሄድ ሀገር ለማፍረስ ጥረት አድርገዋል።
ለምሳሌ አማራ በሚባለው ክልል በምንም ሁኔታ ሊለያይ የማይችል ህዝብ ቅማንትና አማራ በማለት አጥር እንዲበጅ ዘሩም ግንዱም አንድ የሆነውን ህብረተሰብ በርስቱ ጊዜ ያልተጋደለውን እነሱ እንዲጋደል አድርገዋል። ዛሬ በቋንቋ የተፈጠረው የግጭት መዓት የወረደው ህወሓት በፈጠረው አጥርና ሀገር የማፍረስ ሴራ ነው። ይህን ነገር ያደረጉት ኢትዮጵያን ከመሰረቱ ሊያፈርሱ ስለተነሱ ነው። ጥቅምት 24 በመከላከያ ሰራዊት ላይ ያደረሱት ጥቃትም ገና ከጅምሩ ይዘውት ያደጉት ሀገር የመበተን አላማቸውን ለማሳካት ነው።
አዲስ ዘመን፡- የመከላከያ ሰራዊቱን ለማጥቃት የሄዱበትን የጥፋት መንገድ እንዴት ይገለጻል? ህዝቡ የሰጠውን ምላሽስ?
አቶ ባዩ፡– መከላከያን ሲያጠቁ መነሻቸው ‹‹የሚጠባ ጥጃ ሲይዙት ያጓጉራል›› እንደሚባለው እነሱ ብቻችን ኢትዮጵያን ካልጠባናት፣ ካላፈረስናት፣ በሰላም አንቀመጥም ብለው ነው። ጥፋታቸው አፈጣጠራቸውም ለጥፋት ስለሆነ ከዝንብ ማር እንደማይጠበቅ ሁሉ ከህወሓትም መልካም ተግባር የማይታሰብ ነው። እነሱ ሊያፈርሷት የተነሱባትን ሀገር የኢትዮጵያ አምላክ ህዝቡን ከተፈበረከው የመለያየት አጥር በተቃራኒው አቁሞ ፀረ ወያኔ ሆኖ በአንድነት ተሰልፏል። የህዝቡ አንድነት ኢትዮጵያ በፈጣሪዋ የታመነች ሀገር በመሆኗ እና የህዝቡ ኢትዮጵያዊነት ስሜት የአድዋውን ታሪክ ዳግም ያሳየ ነው።
በዚህ ሁለትና ሶስት ወር ውስጥ እየታየ ያለው በኢትዮጵያዊ አንድነት የደመቀ ህዝባዊ ማዕበል አይደለም ለአሸባሪዎች የኢትዮጵያን ውድቀት ለሚመኙ ምዕራባውያን ትልቅ መልስ ነው። የህወሓት ስብስብ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከውጭ ጠላቶቻችን ተልዕኮ የተቀበለ የማይማርና የማይለወጥ የግፈኞች ጥርቅም ነው። የትግራይ ህዝብ ድሮም አሁንም በጠገዴና ወልቃይት ያርሳል፣ በፊት ትግሬነት፣ ኦሮሞነት፣ አማራነት፣ ሳይሆን የሚያስፈልገው ኢትዮጵያዊነት ነበር።
ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ በየትኛውም የሀገሪቱ ጫፍ ማልማት የሚችልበት ሁኔታ ነበር። ይህ ቡድን ግን ህዝቡን ከዚህ ሁሉ ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነት ነጥቆት ቆይቷል።
በፊት እኮ እንኳን እኛ ኢትዮጵያውያን ሀሰን የሚባል የናይጀሪያ ተወላጅ ሁመራ ውስጥ ሰፊ እርሻ ነበረው። የትግራይ ገበሬዎች ወልቃይት፣ ሁመራ ጠገዴ የእነሱ እርሻ ነበር። ወያኔ ግን ይህን ሁሉ በክልል ሲያጥረው አማራም ከዚህ ወዲህ ይውጣ፣ ኦሮሞም ከዚህ ወዲህ ይውጣ፣ ሌላውም ከዚህ ወዲህ ይውጣ ብሎ ሁሉንም አጥር ሰርቶ አፈራርሶ ለመቅበር የሰራው ሰይጣናዊ ተግባር ነው። አጥሩን ሲያበጁ እኩይ አስተሳሰብ እንጂ ለትግራይ ህዝብም አስበው አይደለም።
የህወሓት ሀገር የመበተን ሴራ በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ እየከሸፈ ነው። ህወሓት ራሱ ጎንጉኖ ራሱ በለኮሰው እሳት እየተለበለበ ነው። ካሁን በኋላ ቢንፈራገጥ እንጂ አይራገጥም። ሴራውን ህዝቡ ተረድቶታል። ጥንትም እየለያዩ ህዝብና ህዝብ እያጋጩ እነሱ የሀገር ሀብት ይዘርፋሉ።
ኢትዮጵያን የማፍረስ ሴራ ሲጠነሰስ ለማፍረስ የተጠቀመበት አንዱን ከአንዱ በማጋጨት ነበር። የአዋጭነት ጥናት ያካሄደው በቋንቋ በኃይማኖት፣ በዘር በመግባት ነበር። የአኖሌን ሀውልት ሳይቀር በማቆም ወንድምና ወንድም አብረው እንዳይኖሩ ሀገር ፈርሳ እንድትቀር የሰራው አሁን ላይ በሀገር መከላከያ ላይ ባስከተለው ጥቃት ኢትዮጵያውያን ዋጋውን እየሰጡት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ህወሓት ህዝቡን በዘር፣ በጎሳ፣ በኃማኖት አጥር መስራቱ እንደሀገር ያስከተለው ውድቀትና ኪሳራ ምንድን ነው?
አቶ ባዩ፡- ያላስከተለው ምን አለ። እንደ ህወሓት የጥፋት አካሄድ የተረፍነው በፈጣሪ ምህረት ነው። እነሱ እኮ ደም እንዲፈስ ያላደረጉበት የኢትዮጵያ ምድር የለም። አንዱ በአንዱ ላይ እንዲዘምትበት፣ ከቀዬው እንዲፈናቀል፣ እንዲሰደድና እንዲሞት አድርገዋል። በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እነሱ እንቆረቆርለታለን ለሚሉት የትግራይ ህዝብ በኢፈርት ስም የሀገርን ሀብት ከማከማቸት በስተቀር ሌላ ምንም የሰሩት በጎ ተግባር የለም። አቶ ስብሃትም የኢፈርትን ያህል ሀብት ያለው ድርጅት አለም ላይ የለም ብሎ በአደባባይ ተናግሯል። እውነቱን ነው፣ ባይል ነበር የሚገርመው፤ ማን አለው የደሃን ሀገርና ህዝብ ንብረት 27 አመት ሲበዘብዝ ላይኖር ነው።
አሁንም እያደረጉት ያሉት ተግባር ለትግራይ ህዝብ አይጠቅምም። ምክንያቱም አሁን በያዙት ሁኔታ ቢቀጥሉ የትግራይ ህዝብ በኤርትራ ዝግ ነው፣ በኢትዮጵያ በኩልም ዝግ ነው፣ በጉልበት ከሱዳን ጋር ለመገናኘት ቢፈልጉም አይችሉም። ምክንያቱም ወልቃይት የበጌምድርና ሰሜን ጠቅላይ ግዛት አስተዳደር ነው። ህዝቡ ካሁን በኋላ እድሜ ልኩን ሲዋጋ ይኖራል እንጂ ወልቃይትና ጠለምት፣ ጠገዴ፣ ራያ ወደ ትግራይ የሚካለሉበት መንገድ የተዘጋ ፋይል ነው።
አዲስ ዘመን፡- ወልቃይት፣ ጠለምት፣ ራያ በቀድሞው የበጌምድርና ሰሜን ጠቅላይ ግዛት ከሆኑ ህወሓት በምን መልኩ ወደ ትግራይ እንዲካለሉ አደረገ?
አቶ ባዩ፡- ህወሓት ትግራይ ሲፈለፈል መቀሌ ውስጥ የጠቅላይ ፍርድቤት ዳኛ ሁኜ እያገለገልኩ ነበር። በወቅቱ ሲፈለፈሉ ለም መሬት የትኛው ቦታ ነው፣ ወደብ የምናገኘው በየት በኩል ነው ብለው አስበው እና አቅደው ሲነሱ እነዚህን ቦታዎች ወደ ትግራይ ማካለል እንዳለባቸው አስበው ነው። ከጫካ ወደ አራት ኪሎ እንደገቡ ታምራት ላይኔ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ፕሬዚዳንት ሆነው ጊዜያዊ አስተዳደር እንደነበሩ በጎንደር ተወላጆች የተቋቋመ የጎንደር ልማት ማህበር(ጎልማ) ሲጸድቅ መመሪያው የቀድሞውን የበጌምድርና ጠቅላይ ግዛትን አቅፎ የሚሰራ ሆኖ ሲመሰረት እንዲሻሻል ጠየቁ። ምክንያቱን ስንጠይቅ ለምንዘረጋው የአስተዳደር መዋቅር ስለሚያስቸግር ይሻሻል ብለው እስከማሰር ደርሰዋል። ይህም የጎንደርን መሬት ለመውሰድ ያሰቡት ነበር። በወቅቱም በጉልበት ተሳክቶላቸዋል። ዛሬ ላይ ግን የህወሓት ሴራ ከሽፏል። የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ሆኖ አሸባሪውን እና የሀገር ጠላት የሆነውን ቡድን መፈናፈኛ አሳጥቶታል።
ድሮም ቢሆን እየለያየ ህዝብና ህዝብ እንዲጋጭ በማድረግ ነጣጥለህ ግዛ ሲከተል ነበር። አንዱን ከአንዱ በማጋጨት፣ በቋንቋው፣ በኃይማኖቱ በእምነቱ በመግባት ነው። ለምሳሌ ወያኔ በኦሮሚያ ክልል የአኖሌ ሀውልትን ያሰራው የሀሰት መረጃ ላይ በመመስረት ሁለቱን ትልልቅ ህዝብ ለማለያየት ነው።
ማን ጡት ቆረጠ፣ መቼ እንዴት፣ የት የሚለውን ሳያገናዝብ ህዝብን ለማበጣበጥ የሰራው ሃውልት ነው። ታሪክ መረጃና ማስረጃ ይጠይቃል። ታሪክን ሲሚንቶ አቡክቶ አውጥቶ በመለጠፍ አይደለም። የታሪክ ሀቅ የሌለው የጡት ቁራጭ ማስቀመጥ የፈለጉት ሀገር ፈርሳ እንድትቀር ነው።
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪው ህወሓት በስልጣን ላይ በቆየበት ጊዜ ኢትዮጵያ እንድትፈርስ ሲሰራ ነበር፣ አሁንም እየሰራ ነው፤ ምን ለማግኘት ነው?
አቶ ባዩ፡- ኢትዮጵያ ምን እንዳደረገቻቸው አላውቅም። የትግራይ ተወላጆች የማይሰሩበት ጅማ፣ ወለጋ፣ አዲስ አበባ፣ ደቡብ፣ የት አለ። ፎቁ፣ ንግዱ፣ ፋብሪካው የማን ነው። ምን አልባት ኢትዮጵያ እንድትፈርስ ለሚፈልጉ የውጭ ኃይሎች ህልማቸው እንዲሳካ ተልእኮ ለመፈፀም ካልሆነ በስተቀር ለህዝባቸውም ኪሳራ ነው። የትግራይ ህዝብ ሰርቶ እንዳይበላ መከራ ነው ያወረዱበት። ቢገነጠሉ ምንድነው የሚያገኙት ወልቃይት ከሆነ የተዘጋ ፋይል ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለኢትዮጵያ አንድነት መጠናከር መፍትሔው ምን መሆን አለበት ይላሉ?
አቶ ባዩ፡- ዋናው መፍትሔው ትግሬ፣ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ጉራጌ፣ ወዘተ….. ሳንባባል 85 ብሔር ብሔረሰቦች ህዝቦች ብለው የከፈሉት ‹‹ህዝብ›› ተብሎ ኢትዮጵያዊነትን አንግሶ መኖር ብቻ ነው። የኢትዮጵያ ህዝቦች ሳይሆን ህዝብ ተብለን ልንጠራ ይገባል። ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ ህዝብ ሊባል ይገባል። የኢትዮጵያ ህዝብ መሆኑንም ድጋሚ አስመስክሯል። ሁሉም ኦሮሞ፣ አማራ ጉራጌ ሳይል በአንድነት ወደ ጠላቱ ዘምቶ አስመስክሯል።
አዲስ ዘመን፡- ለአሁኑ ትውልድ የሚያስተላልፉት መልዕክት ምንድነው?
አቶ ባዩ፡- ወጣቱ ከታሪክ አጥፊዎች ሳይሆን ከታሪክ ሰሪዎች መማር አለበት። የታሪክ አተላ ከሆኑት የጥፋት ቡድን የተማረውን የተዛባ ታሪክ ማረም አለበት። ከዛሬ ጀምሮ በኢትዮጵያዊነቱ እንዲደራጅ እና የኢትዮጵያ ህዝብ ልጅ መሆን አለበት። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ህዝብ በአድዋ፣ በኳቲት፣ ዶጋሊ በእነ ራስ አሉላ፣ አጼ ዮሃንስ፣ ፊታውራሪ ገበየሁ፣ ገረሱ ዱኪ፣ እነ ኡመር ሰመትር፣ ጃገማ ኬሎ እነ ራስ አበበ የጉበና ዳጪ የልጅ ልጅ የኢትዮጵያ ልጆች ጠላትን አሳፍረው የመለሱ ጀግኖች ልጆች መሆናቸውን ዳግም ማስመስከር አለባቸው። ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ኩራት መሆኗን ዳግም የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት።
የኢትዮጵያ ወጣት በዘር በጎሳ መከፋፈልን አውልቆ በመጣል በኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያዊ ህዝብ ሆኖ ለሀገር አንድነት መታገል ይጠበቅበታል።
የመገናኛ ብዙሃን ድርጅቶች የኢትዮጵያን አንድነት የሚያናግሩ፣ የሀሰት ታሪክ የማይጽፉ እውነተኛውን ታሪክ ለህዝብ አይንና ጆሮ በማድረስ የኢትዮጵያን አንድት ለማጠንከር ጠንክረው ሊሰሩ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉና በአንባቢያን ስም እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ።
አቶ ባዩ፡– እኔም አክብራችሁ ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ።
ሞገስ ተስፋ
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 1/2013