መቼም እንደዚህ ጊዜ አስገራሚ ጊዜ ያለ አይመስለኝም፡፡ ባንዳው በሙሉ በይፋ በአደባባይ የተገለጠበት ዘመን ይህ ነው፡፡ ጠላቶቻችን የተደበቀ ጠላትነታቸው በአደባባይ የተገለጠበት ወቅት ነው። ባላንጣዎቻችን አጋጣሚውን ተጠቅመው እኛን ጠልፈው ለመጣል የተረባረቡበት ጊዜ ይህ ነው፡፡ ግን ደግሞ በዚያው ልክ አዳዲስ ጀግኖች የተወለዱበት ወቅትም ይህ ነው፡፡ ይህ ወቅት ኢትዮጵያ ማህጸነ ለምለም ለምን እንደተባለች የታየበት ወቅት ነው ብንል ማጋነን አይሆንም፡፡ የሚሰሙት ጀብዶች የሚደንቁ ናቸው፡፡ ከጀግኖቹ እስኪ ዝናቸው በመገናኛ ብዙሃን እና በነጋዜጠኛ አንሙት አብርሀም የተዘገበላቸውን የተወሰኑትን ጀግኖች እናስታውስ እስኪ፡፡
የመጀመሪያው ጀግና አረጋዊው ሀሰን ከረሙ ናቸው፡፡ አንዳንዱ አካባቢ በወሬ እየተፈታ ሲፈረጥጥ ሽርጥ ለባሹ ጀግና ግን እግራቸውንም አላነሱ፡፡ምን አሉ መሰላችሁ «ማንም ቀዬውን ለቆ እንዳይወጣ!!!… ህዝቤን ከተማ ልኬ በበሽታ አላስጨርስም። እዝሁ ጥይቱ ይብላን… ወንዱም እንዳትሸሽ… የህዝብህን መከራ ሳናይ እንሙት … ሲሆን አላህ አለን እናሸንፋለን!!! ዛሬ ሐራ እናደርሳታለን!!!…»….ይሄው እሰከዛሬ ጠላትን እያበራዩ ከተማቸውን እና ህዝባቸውን ጠብቀው አሉልህ፡፡
ደሞ ሌላ ጀግና አለልህ ፤ ከሰሜን ሸዋ አንኮበር በተጠባባቂ ሚሊሻነት የዘመተው አቶ አለሙ ላቀ ታሪካዊ ጠላትን ከሚፋለሙት መካከል ነው።አስር ጎራሽ መሣሪያውን ታጥቆ ፣ አራት ልጆቹንና ቤተሰቦቹን ሳይነግር ተደብቆ ዘመቻውን ተቀላቀለ ፤ ከዋጃ እስከ ደብረ-ዘቢጥም ከጠላት ጋር ተፋለመ። በዚህ ፍልሚያ ግን ጥይት አለቀበት።ይሄኔ ታዲያ አልሸሸም ፤ ይልቁንም በእሱ አቅጣጫ የነበረ የጠላት ወታደርን ጥይት ሳይተኩስበት ፈጥኖ በድንጋይ መትቶ ሙሉ ትጥቁን ቀማው እንጂ። ሲመጣ በተጠባባቂነት የሚኒሻ ተዋጊ ቢሆንም አሁን የማረከውን መሣሪያ ይዞ ከመከላከያና አማራ ልዩ ኃይል ጋር እየተዋጋ ነው። ሲመጣ የለበሰውን የሲቪል ልብስም አሁን ቀይሮ በሙሉ ወታደራዊ ቁመና ጠላትን የሚቀጠቅጥ ቆራጥ ነው።
ከበርካቶቹ ወዶ ዘማቾች መካከል አንድ ሞረሽ አርሶ አደር የክተት ዘመቻውን የተቀላቀለው “ጥልቆ” በመባል የሚታወቀውን ባህላዊ መሣሪያ ይዞ ነበር።ሞረሹ አርሶ አደር ስናይፐር ከታጠቀ አንድ የጁንታ ወታደር ጋር ፊት ለፊት ተጋፈጠ። አንገቱን በጥልቆ ብሎ ስናይፐሩን ማረከ። ጀብደኛው አርሶ አደር የማረከውን የጦር መሳሪያ “እኔ ገበሬ ነኝ ከትክሻየ የሚወጣው የገበሬ እቃ እንጅ መትረዬስ አይደለም፣ እኔ የምውለው ከበሮቼ ከእነ’ሰንጎ ከእነ’ኮራ ጋር ነው። ይህንን መሣሪያ እንኩ” ብሎ ለፀጥታ ኃይሉ አስረክቧል።”አባት እርሰዎ ትክክል ነዎት ቢሆንም ይህ ለእርሰዎ ልጆች ለአካባቢው ነዋሪ ልጅ ለበርካታ ዜጎች አስተማሪ የታሪክ ስንቅ ነው። ስናይፐሩን እሽ እንቀበለዎት ይህን ክላሽ እነሆ ለፈጸሙት ገድል ምስክር ነው።” ብሎ ሸልሟቸዋል።
በጊሌ ታንክ ስለማረከው የአፋር ጀብደኛው ሁመድ ሆሪሶ ሰምተናል!! በአፋር ጋሊኮማ ግንባር የተሰለፈው የአፋር ልዩ ኃይል አባል የአስዶራው ተወላጅ ሁመድ ሆሪሶ የያዘው ክላሽንኮቭ መሳሪያ ጥይት ቢጨርስበት ጊሌውን አነሳ። ታንክ ላይ የነበረ የጠላት ካፒቴን ጀርባ ላይ በመከመር ጨበጣ በማድረግ ካፒቴኑን በያዘው ጊሌ በመቅላት ዘመናዊ ታንኩን መማረክ የቻለ ጀግና ነው።”በድንጋይ ኮለኔል ማራኪ” የሚባለው የጠላት ዘፈን አፋር ላይ “በጊሌ ታንክ ማራኪ” ተብሏልና ሰሚ የለውም።አፋር ጀግናውን አክብሯል ፣ የሁመድ ፎቶግራፍ ሠመራ ላይ አስር ሚሊዮን ብር ተሽጧል።
ከትሕነግ ወራሪ ላይ ክላሽ በከዘራ የማረከውን አርሶ አደር ንጉሴ አለኸኝ ጀግንነት እነሆ !! ነሐሴ 11 / 2013 የጠላት ወራሪዎች እንደለመዱት በጉና በጌምድር ወረዳ ከ30 በላይ ሆነው ይንቀሳቀሳሉ። ከመካከላቸው የፈረደበት አንዱ ጁንታ ደግሞ የርብ ወንዝን ብቻውን ተሻገረና ከንጉሴ ጋር ተገናኘ። ይሔ ወራሪም ንጉሴን “ አንት የአህያ ልጅ ምን እያደረክ ነው?” አለው። ጠላት ክላሽ ስለያዘ ባለከዘራ ግለሰብ አይደፍረኝም ብሎ ይሆናል መሳደቡ። ንጉሴም ከጓደኞቹ የራቀውን ጁንታ ጠጋ ብሎ በያዘው ከዘራ አንገቱን መታው። “ሲወድቅልኝ ኮሚሳር ክላሹን ነጥቄ ሮጥኩ” ይላል። የጁንታው ጓደኞች እንዳይደርሱበት የቀማውን ክላሽ እየተኮስ አመለጣቸው።”በከዘራ ኮሚሳር ማራኪ” በለህ ፃፍለት። እዚህ ጋር ጠምንጃ ማራኪውን ስናነሳ ቦንቡን መልሶ ቀበላቸውን የተከዜው መብረቅ ቦንብ አጉራሹ ዋና ሳጅን አስፋው ዘለቀ ማስታወስም ይገባናል፡፡ዋና ሳጅን አስፋው ከጠላት የተወረወረን ቦንብ መሬት ሳትደርስ ቀልቦ መልሶ ወርዋሪዎችን አጉርሶ የደመሰሰ ጀግና ነው።
6ቱን ገድሎ የተሠዋው የንፋስ መውጫው ጀግና አስር አለቃ ደመቀ ቀለሙ ሌላኛው ነው። ደመቀ ህወሓት ደብረዘቢጥ ደርሳ ውጊያ ስትጀምር በወኔና በእልህ ታግሎ የደብረ ዘቢጥ ምሽግ በጠላት ተሰብሮ ወደ ጋይንት ሲዘልቁ ግን ደመቀ ለክፉ ቀን ያስቀመጠውን ቦንብ ከቤቱ ይዞ ወጣና ጠላት ወደ ተሰበሰበበት ቦታ በመሔድ ጠላት ላይ ወረወረው። ወዲያው 6ቱ የጠላት አባላት ሲደመሰሱ ቀሪዎቹ ቆስለኛ ሆኑ። ደመቀም በዚያው ተሰዋ።
አስር አለቃ ደመቀ ተሰውቶ ጀግና የመሆኑን ያህል ጠላትን ረፍርፎ በኩራት ወደ ከተማ የገባውን ጀግናውን አቶ ጌጤ መኳንንት ማስታወስ ግድ ይላል፡፡ክምር ድንጋይ በስጋ ንግድ እና ሬስቶራንት ስራ ላይ ተሠማርቶ የነበረው አቶ ጌጤ መኳንንት ክምር ድንጋይን ተቆጣጥረው ንግድ ቤቱ ገብተው ምግብ እንዲያቀርብ ካስገደዱት የወራሪ ቡድን አባላት መካከል 11ዱን ወደሰማይ ቤት አሰናብቶ አባ ረፍርፍ የሚል ስም ይዞ በጀግና ወግ እየኖረ ነው፡፡
ሁሉም ጀግኖች ግን በጦር ሜዳ የዋሉ አይደሉም፡፡አንዳንዶቹ ጀግኖች ደግሞ በትዊተር ጦራቸውን እየመሩ የጠላትን የውሸት ብርጌድ አፈር ድሜ እያበሉት ነው፡፡ከነዚህም መሀከል ዋነኞች ጋዜጠኛ በላይ ማናየ እና የማህበረሰብ አንዊው ሱሌማን አብደላ ተጠቃሽ ናቸው፡፡እነዚህኞቹ ደግሞ የሚተኩሱት ተኩስ ኒውዮርክ እና ብራስልስ ድረስ የሚሰማ አንዳንዶችን በዋሽንግተን ጎዳና የሚያንከባልል ነው፡፡
ብቻ ምን ልበላችሁ ጀግና በየቦታው በየፈርጁ እየተወለደ ነው፡፡የባንዳው ሀይል ቀን በቅን እየተመናመነ የጀግናው ሀይል ቀን በቀን እየተበራከተ ዛሬ ላይ አዲስ ከተፎ ትውልድ ሀገሩን እያስጠራ ነው። እንግዲህ ከአይን ያውጣችሁ ከማለት ወዲያ ምን እንላለን
(አቤል ገ/ኪዳን)
አዲስ ዘመን ነሐሴ 30 ቀን 2013 ዓ.ም