እአአ በ2015 ናይጄራዊያን የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ለመምረጥ ሲዘጋጁ ሁለት ምርጫ ነበራቸው፡፡ የመጀመሪያው ጉድላክ ጆናታን የአገሪቱ መሪ የነበሩና አስተዳደራቸው በሙስና የሚታማ፤ ሁለተኛው ደግሞ በዘረኛ አስተሳሰብና አምባገነንነት የሚታወቁ ሙሀመድ ቡሀሪ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ናይጄሪያዊያን ቡሀሪን መርጠዋል፡፡ ቡሀሪ የለውጥ ዴሞክራት መሪ እንደሆኑና ከአገሪቱ ሙስናን እንደሚያጠፉ ቃል በመግባታቸው ሊመረጡ ችለዋል፡፡
ከምርጫው በኋላ ጆናታን በቡሀሪ መሸነፋቸውን አምነው የፕሬዚዳንትነቱን መንበር ለቀቁ፡፡ ቡሀሪ በአገሪቱ ዴሞክራሲን በማስፈን በሰላማዊ መንገድ ስልጣናቸውን ከተረከቡ በኋላ ፊታቸውን ወደ ሙስና መዋጋት ላይ አተኮሩ፡፡ በዚህም የብዙ ናይጄራዊያንን ትኩረት ስበዋል፡፡ የናይጄሪያ ዜጎች ቀጣይ በሚደረጉ ምርጫዎች ያለማንም ጫና የፈለጉትን መምረጥ እንደሚችሉ ተስፋ ጣሉ፡፡
ነገር ግን ከጥቂት አመታት በኋላ ናይጄራዊያን ድጋሚ ምርጫ ለማድረግ ተዘጋጅተዋል፡፡ በምርጫው ናጄራዊያን ከባድ ፈተና ተጋርጦባቸዋል፡፡ በአሁኑ ምርጫ የራሳቸውን ዝና ለማስጠበቅ ስልጣናቸውን በተጠቀሙት መሃመድ ቡሀሪና የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ከነበሩት አቲኩ አቡበከር ጋር ይፎካከራሉ፡፡ አቲኩ አቡበከር የምርጫ ቅስቀሳቸው ሙስና ፈፅመዋል በሚል ወሬ በተደጋጋሚ ተስተጓጉሏል፡፡
አልጀዚራ ባወጣው ዘገባ በቡሀሪ የፕሬዚዳንትነት ዘመን ከፍተኛ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ ቡሀሪ ባሸነፉ ማግስት በሙስና የተጨማለቁ የመንግስት ሰራኞችን በማሰራቸው ከፍተኛ አድናቆት አግኝተው ነበር፡፡ በተጨማሪም ስልጣን ላይ ከወጡ በወሩ የቀድሞ የአገሪቱን ብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ሻምቦ ዳሱኪን እንዲታሰር አድርገዋል፡፡ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪው የቦኮሀራምን የመሳሪያ ማከማቻ ለማጥቃት ሁለት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር ያለአግባብ እንዲወጣ አድርገዋል በሚል ክስ ተመስርቶባቸው ነበር፡፡
ህዝቡ በአዲሱ ፕሬዚዳንት ችሎታ በመተማመኑ አብዛኛው ሰው አዲሱ አስተዳደር ችግሮችን መፍታት ይችላል የሚል እምነት አድሮበት ነበር፡፡ በነዳጅ ላይ የተደረገው ጭማሪ በአገሪቱ ሁከት የፈጠረ ቢሆንም አብዛኛው ነዋሪ ጭማሪው በመደረጉ የተስማማ ሲሆን ከጭማሪው በሚገኘው ገቢ ኢኮኖሚው ያድጋል የሚል እምነት ነበራቸው፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ነገሮች መለዋወጥ ጀመሩ፡፡
የቡሀሪ አስተዳደር ችግር ለመገለጥ ብዙ ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ የፀረ ሙስና ትግሉ በዋነኝነት ተቃዋሚዎቻቸውን ለማጥቃት የተጠቀሙበት መሆኑ ተገለጠ፡፡ አዲሱ ፕሬዚዳንት ከራሳቸው አስተዳደር ውስጥም ባብችሪ ላዋል እና የገንዘብ ሚኒስትርና የፌደሬሽኑ ጸሀፊ ኬሚ አዴሶን የተለያዩ የተቃዋሚ አመራሮችን በሙስና ሰበብ እንዲታሰሩ አድርገዋል፡፡ ታሳሪዎቹ ገዥውን ፓርቲ ለማጥቃት አስበዋል በሚል በሙስና ሰበብ እንዲታሰሩ የተደረጉ ናቸው፡፡
በመጨረሻም ቡሀሪ ከስድስት ወራት ቆይታ በኋላ ካቢኒያቸውን አቋቋሙ፡፡ ካቢኒያቸው ከራሳቸው ጎሳ የሚበዛበት ሲሆን ይሄ አወቃቀራቸው ናይጄራዊያንን ጥርጣሬ ውስጥ አስገብቷቸዋል፡፡ ከዚህ በላይ ደግሞ ፕሬዚዳንቱ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ያረጋጋሉ ተብለው ሲጠበቁ በአገሪቱ የሚገኙ አምራች ድርጅቶች እንዲዘጉ በመደረጉ የስራ አጥ ቁጥር ከፍተኛ እንዲሆን አድርጓል፡፡
በሌላ በኩል የቡሀሪ ጤንነት ጉዳይ ጥያቄ ያስነሳ ሲሆን ፕሬዚዳንቱ በቢሮ ቆይታቸው 103 ቀናትን በእንግሊዝ በህክምና አሳልፈዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ፕሬዚዳንቱ እድለኛ እንዳልሆኑ በማሳያነት የቀረበ ሲሆን የ76 ዓመት አዛውንቱ በአሁኑ ወቅት ብዙ ነገር እየዘነጉ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ የፓርቲያቸውን አርማ በአግባቡ አለመስቀልና ስልጣን የያዙበትን ቀን መቀላቀል ተስተውሎባቸዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ የተደናገሩ፣ ስልጣን የሌላቸው፣ ትክክለኛው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት አይደሉም ወደሚል ግምት አስገብቷቸዋል፡፡ እአአ ታህሳስ 2018 ባለቤታቸው ዶክተር አሺያ የቡሀሪ ፕሬዚዳንትነት መጠለፉን በመናገራቸው የህዝቡን ጥርጣሬ እውነት ወደ መሆኑ ሄዶ ነበር፡፡
ዴሞክራሲያዊ በሆነ የትግል መንገድ የመጡ እንደ ቡሀሪ አይነት መሪዎች በተለያዩ ጉዳዮች ውድቀት ሲያመጡ ለሁለተኛ ጊዜ አልተመረጡም ነበር፡፡ ነገር ግን ናይጄሪውያን ከማያውቁት መላክ የሚያውቁት ሰይጣን ይሻላል በሚለው ተረት መሰረት ቡሀሪ ለፕሬዚዳንትነት እንዲወዳደሩ ድጋፍ ሰጥተዋል፡፡ በምርጫው የቡሀሪ ተፎካካሪ የሆኑት የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት አቲኩ አቡብከር ከህዝቡ ድምፅ ሊያገኙ የሚችሉበትን መንገድ እየፈለጉ ይገኛሉ፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አቲኩ አቡበከር ለፖለቲካ እራሳቸውን የሰጡና የሚስቡ ናቸው ሲሉ ቡሀሪ ግን ለፖለቲካ የሚሆኑ አይደሉም ሲሉ ተችተዋል፡፡ ትራምፕ በሰጡት ቃለመጠይቅ በአገሪቱ በምርጫ ወቅት ግጭት እንዳይከሰት የመንግስትን አቅም በማሳደግ በተለይ ለክልል አስተዳደሮች ስልጣን መሰጠት እንዳለበት ሀሳብ አቅርበዋል፡፡ እንደ ውጤታማ ንግድ ሰው አቡበከር ስልጣን ላይ ቢወጡ የአገሪቱን ኢኮኖሚ በማንቃት ስራ አጥነትን ሊቀንሱ እንደሚችሉም ትራምፕ ተናግረዋል፡፡
ነገር ግን አቡበከር እነዚህ ጥሩ ስራዎቻቸው በጣም በከፍተኛ የሙስና ቅሌቶች ተሸፍነውባቸዋል፡፡ ይህ የሙስና ቅሌትም ለሚያደርጉት የፕሬዝዳንትነት ውድድር እንቅፋት ሆኖባቸዋል፡፡ እአአ 2014 ላይ በሰጡት ቃለመጠይቅ ህዝቡ በተሳሳተ መንገድ እንዲረዳቸው ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ስህተታቸውንም ለማረም ዝግጁ መሆናቸውን በመጥቀስ፤ የህዝቡ አስተሳሰብ የተቀየረው ምክትል ፕሬዚዳንት በነበሩበት ወቅት በሰሩት ስህተት መሆኑን አምነዋል፡፡ አቡበከር በሙስና ስራ ውስጥ የተሰማሩት ከወጣትነት እድሜያቸው ጀምረው በተለይ የግብር ሰብሳቢ ሰራተኛ ከሆኑበት ቀን አንስቶ እስካሁን በታክስ ማጭበርበር እስከተከሰሱበት ድረስ በሙስና ተጠርጥረው አያውቁም፡፡
አቡበከር እአአ 2009 የአሜሪካ የፓርላማ አባል በጉቦ በተጠረጠረበት ወቅት ቁልፍ ሰው ነበሩ፡፡ በፍርዱ ወቅት አቃቤ ህጉ እንዳለው አቡበከር የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዚዳንት ቤተሰቡን ለመጥቀም ሲል ከአገሪቱ ገንዘብ እንዳይወጣ በማድረግ ዊልያም ጄፈርሰን ከተባለ ግለሰብ ጋር የቴሌኮሚኒኬሽን ስራ ኮንትራት ያለአግባብ ወስደዋል ሲል ከሷቸዋል፡፡ እአአ 2010 ላይ የአሜሪካ ሴኔት አቡበከር ከአገሪቱ የነዳጅ ዘይት ገቢ ላይ አስር ሚሊዮን ዶላር ወስደው በውጭ በማስቀመጥ ሙስና ውስጥ ከገቡ ባለስልጣናት ቅድሚያ ምሳሌ ናቸው ሲል ተናግሮ ነበር፡፡
ከሙስና ቅሌቱ በላይ የተቃዋሚው እጩ ተወዳዳሪ በከባድ ሙስና የተጠረጠሩ ናቸው በሚል ህዝቡ በቅስቀሳ ወቅት እንዳይሳተፍ የሚደረገው ዘመቻ መበራከቱ ነው፡፡ ግባንጋ ዳንኤል የቀድሞ የክልል አስተዳዳሪ የነበረና አሁን የአቡበከር ቅስቀሳ ቡድን መሪ ሲሆን በአሁን ወቅት በሙስና ተጠርጥሮ በፍርድ ላይ ይገኛል፡፡ የአገሪቱ የሴኔት ፕሬዚዳንት የሆኑት ቡኮላ ሳራኪ በአቡበከር ጉዳይ ላይ ባለፈው ወር በሰጡት አስተያየት፤ አቡበከር በናይጄሪያ የሚገኙ የማፊያ ቡድኖች ድጋፍ የሚደረግለትና በሚኖርባት ካዋራ የሚገኙ ሀብታሞችን ለማስደሰት የሚሰራና በብዙ የሙስና ወንጀሎች የሚፈለግ ሰው ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በግልፅ ቋንቋ ቡሀሪም ሆነ አቡበከር ናይጄሪያ ለማትወጣው ችግር የሚዳርጉ ሰዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን የተለያዩ አማራጮች ባሉበት ወቅት በተለይ አክቲቪስት ኦማይሌሶዎሬ፣ የኢኮኖሚ ባለሙያዎቹ ኪንግስሊ ሞግሀሉና ቶፔ ፋሱአ በሚደረገው ምርጫ ሊከሰቱ ይችላሉ የሚል ግምት ተሰጥቷል፡፡ ናይጄራዊያን ለአዲስ ሰዎች እድል መስጠት የሚገባቸው ሲሆን አሁን አገሪቱ ላለችበት ችግር አማራጭ ያመጣል የሚል ግምት ተሰጥቷል፡፡ ነገር ግን አዳዲስና ልምድ የሌላቸው ተወዳዳሪዎች ቢገቡ በተወሰነ መንገድ መራጩን ህዝብ ሀሳብ ለማስቀየር የሚያግዝ ሲሆን እንደ ቡሀሪና አቡበከር ያሉ የፖለቲካ ሰዎችን ለማስወገድ ያግዛል፡፡
እንደ አልጀዚራ ዘገባ የናይጄሪያ ዴሞክራሲ ስለመውደቁ ምርጫውን ማየት ይቻላል፡፡ ማንም ያሸንፍ ማ አሸናፊነቱ የናይጄራዊያን አይደለም፡፡ ነገር ግን አሸናፊ የሚሆነው ፖለቲካውና የስልጣን ጥመኞች ብቻ ናቸው፡፡ የናይጄሪያ ህዝቦች በሚመርጡት ሰው ማሸነፍ የሚችሉት ዝቅተኛ አደገኝነት ያለውን ሰው ሳይሆን አደገኛ የተባለ ውሳኔ ከሰጡ ውጤታማ ይሆናሉ፡፡ በዚህም አማራጭ ያለው የፖለቲካ ምህዳር መገንባት ይችላሉ፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 18/2011
መርድ ክፍሉ