ጉበት ከደም ውስጥ መርዛማ ነገሮችን የሚያጣራ ከመሆኑም ባሻገር ቢያንስ ቢያንስ 500 የሚሆኑ ሌሎች አስፈላጊ ተግባራትን ያከናውናል። ሄፒታይተስ ወይም የጉበት ብግነት የአንድን ሰው ጤንነት በእጅጉ ሊጎዳ የሚችለው በዚህ ምክንያት ነው። ሄፒታይተስ አልኮል አብዝቶ በመጠጣት ወይም መርዛማ ለሆኑ ነገሮች በመጋለጥ ሳቢያ ሊመጣ ይችላል። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ ለሄፒታይተስ መንስኤ የሚሆኑት ቫይረሶች ናቸው።
በተሐዋሲ አማካኝነት ጉበት ላይ ጉዳት የሚያደርሰው እና በህክምናው ቫይራል ሄፒታይተስ የሚባለው የጉበት በሽታ በመላው ዓለም 325 ሚሊዮን ሰዎችን መያዙን የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል። በተለይ ሄፒታይተስ ቢ እና ሲ የሚባለው የበሽታው አይነት ሳይታወቅ ለረዥም ጊዜ በሰውነት ተደብቆ ሕይወት ሊቀጥፍ የሚችል በመሆኑ ፤ ድምፅ አልባው ገዳይ በመባል ይታወቃል።
ሄፒታይተስ ቢ ቫይረስ በየዓመቱ ቢያንስ 600 ሺህ ሰዎችን ይገድላል፤ ይህም በወባ ምክንያት ከሚሞቱ ሰዎች ጋር ይተካከላል። ከሁለት ቢሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ማለትም ከዓለም ሕዝብ አንድ ሦስተኛ ገደማ የሚሆኑት በሄፒታይተስ ቢ ቫይረስ የተጠቁ ሲሆን አብዛኞቹ በወራት ጊዜ ውስጥ ከበሽታው ድነዋል። ይሁን እንጂ በሽታው በመላው ዓለም 325 ሚሊየን ሰዎችን ላይ ስር ከመስደዱ ባሻገር፤ በየዓመቱ 1,3 ሚሊየን ሕዝብ እየገደለ ይገኛል። ለዚህ ደግሞ ከ10 ሰዎች ስምንቱ ተገቢውን ምርመራ እና ህክምና ማግኘት ባለመቻላቸው መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ።
በሽታው በከፍተኛ ደረጃ በኤስያ እና ከሰሀራ በታች ባሉ ሀገራት የሚታይ ነው:: የበሽታው ስርጭት ከአምስት እስከ ሃያ በመቶ ሲሆን፤ የበሽታው ዝቅተኛ ስርጭት ደግሞ በአሜሪካንና በምዕራብ አውሮፓ ሲሆን፤ የበሽታ ስርጭቱ ከዜሮ ነጥብ አንድ እስከ ዜሮ ነጥብ አምስት ይደርሳል::
በሀገራችን በሽታው በስፋት ተሰራጭቶ ከሚገኝባቸው ሀገራት መሀከል አንዷ መሆኗን በ2017 እ.ኤ.አ የተሰራ የዳሰሳ ጥናት ያመለክታል::
ሳይንቲስቶች ሄፒታይተስ አምጪ የሆኑ አምስት ቫይረሶችን መለየት የቻሉ ሲሆን ቢያንስ ሌሎች ሦስት ዓይነት ቫይረሶችም ሊኖሩ እንደሚችሉ ያምናሉ። በተለያዩ ኬሚካሎች አማካኝነት የጉበት ሴሎችን በመጉዳት ወደ ካንሰርነት የሚቀየር በሽታ መሆኑን ባለሙያዎች የሚናገሩለት የሄፒታይተስ በሽታ፤ከቲቪ ቀጥሎ ገዳይ ሲሆን ፤በተለይም ሄፒታይተስ ቢ እና ሲ በተበከለ ደም፤ ልቅ በሆነ የግብረ ስጋ ግንኙነት እንዲሁም በወሊድ ጊዜ ከእናት ወደ ልጅ ሊተላለፍ የሚችል በሽታ በመሆኑ ደም ልገሳ ላይ ልዩ ጥንቃቄ ተደርጎ መሰራት ያለበት ስለመሆኑ ያነሳሉ።
በተጨማሪም ሄፒታይተስ ቢ በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ በሽታ ነው:: ከኤች አይቪ ጋር ሲወዳደር ሃምሳ ከመቶ በላይ እጥፍ ነው:: በኤች አይቪ በተበከለ መርፌ አንድ ሰው ቢወጋ በቫይረሱ የመያዝ ዕድሉ ዜሮ ነጥብ ሦስት ከመቶ ሲሆን ፤ በሄፒታይተስ ቢ ከሆነ ግን ከስድስት እስከ ሠላሳ ከመቶ የሚደርስ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ:: በከፍተኛ ሁኔታ ገዳይ ለሚባለው በሽታ ተጋላጭ የሆኑት የኅብረተሰብ ክፍሎች ከበርካታ ሰዎች ጋር ልቅ የፆታ ግንኙነት የሚያደርጉ፣ በጣም የታመመ የቤተሰብ አባል ያላቸው ቤተሰቦች፣ ቫይረሱ ያለበት የትዳር አጋር ያለው ሰው፣ የጤና ባለሞያዎች፣ በጤና ችግር ምክንያት በተደጋጋሚ ደም የሚለገሳቸው ህሙማን ናቸው።
ሥር የሰደደ የሄፒታይተስ ቢ ቫይረስ ያለባቸው ሰዎች ገና ከጅምሩ ተገቢውን ሕክምና ካገኙ በጉበታቸው ላይ የሚደርሰውን ከባድ ጉዳት ማስቀረት ይችላሉ። ይሁን እንጂ ሄፒታይተስ ቢ ቫይረስ ለዚሁ ተብሎ በሚደረግ ልዩ የደም ምርመራ ካልሆነ በስተቀር ሊታወቅ ስለማይችል አብዛኞቹ ሰዎች በበሽታው እንደተያዙ እንኳ አያውቁም።
በተለምዶ የሚደረገው የጉበት ምርመራ እንኳ የበሽታውን ምልክት ላያሳይ ይችላል። በመሆኑም ሄፒታይተስ ቢ ቫይረስ ያለምንም ማስጠንቀቂያ ለከፋ ጉዳት የሚዳርግ ድምጽ አልባ ገዳይ በሽታ ሊሆን ይችላል። በአንድ ሰው ላይ ግልጽ የሆኑ የሕመም ምልክቶች የሚታዩት በቫይረሱ ከተያዘ ከአሥርተ ዓመታት በኋላ ሊሆን ይችላል። በዚህ ወቅት ግን ሕመሙ ተባብሶ ስሮሲስ የተባለ የጉበት በሽታ ወይም ካንሰር ወደ መሆን ደረጃ ሊደርስ ይችላል። እነዚህ በሽታዎች የሄፒታይተስ ቢ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ ከሚገኝባቸው አራት ሰዎች መካከል የአንዱን ሕይወት ያጠፋሉ።
የአለም ጤና ድርጅት እንደሚመክረው፤ በሽታውን አስቀድሞ መከላከልም ሆነ ታክሞ መዳን የሚቻል ሲሆን ፤ በሽታውን በሁለት ዓይነት መንገድ መከላከል ይቻላል። የመጀመሪያው የተፈጥሮ መከላከያ ሲሆን፤ በሽታው ሲከሰት ሰውነታችን የተፈጥሮ መከላከያ በማመንጨት ራሱን የሚያድንበት ነው::
በዚህ ዓይነት መንገድ የዳኑ ሰዎች ቫይረሱ ከሰውነታቸው ከጠፋ በድጋሚ ለበሽታው አይጋለጡም:: አርቴፊሻሉ መከላከያ ደግሞ በክትባት መልክ የሚሰጥ ነው:: ይህም “ፓሲቭ (passive)” እና “አክቲቭ (Active)” ተብለው ይጠራሉ:: የፓሲቭ ህክምና ፀረ ህዋሱ በአንቲ ቦዲ መልክ ተዘጋጅቶ ይሰጣል። አክቲቩ ደግሞ ክትባቱን ከተከተበ በኋላ በደም ውስጥ አንቲ ቦዲ እንዲፈጠር ያደርጋል:: የሄፒታይቲስ ቢ ክትባት በአብዛኛው ጊዜ የሚሰጠው 3 ጊዜ ሲሆን በስድስት ወራት ውስጥ መጠናቀቅ ይኖርበታል::
ክትባቱ የሚሰጠው ለእርጉዝ ሴቶች በሙሉ፣ ለሚወለዱ ህጻናት በሙሉ፣ የረጂም ጊዜ ሄፒታይተስ ቢ የተያዘ/የተያዘች ባል/ሚስት ያላት/ያለው ሰው፣ በቅርቡ ተመርምሮ በግብረ ስጋ ግንኙነት የሚመጡ በሽታዎች /STDs/ እንዳለው የተገለጸለት ሰው፣ የህክምና ባለሙያዎች በተለይም መርፌ ጋር ንክኪ ያላቸው፣ ስራቸው ከሰው ደም ጋር ንክኪ ያላቸው ሰዎች ናቸው። በመሆኑም ሃገራት ለዚህ በሽታ የሚደረገውን ምርመራም ሆነ ህክምና በጤና አገልግሎት ማዕቀፋቸው በማካተት ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ድርጅቱ ያስገነዝባል። በተጨማሪም ያልተከተቡ ሕፃናት በሽታውን ለመከላከል የተዘጋጀውን ክትባት በመከተብ በከፍተኛ ሁኔታ ስርጭቱ እየጨመረ የመጣውን የጉበት በሽታ መቆጣጠር እንደሚገባ ያመላክታል።
በኢትዮጵያ የሄፒታይተስ ቫይረስን ለመቆጣጠርና ለመከላከል እንደ ሀገር የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች የምርመራና እና የህክምና አገልግሎት ማስፋት እንዲሁም የሄፒታይተስ ቢ ክትባት ከመሰረታዊ የክትባት መርሀ ግብር ጋር በማቀናጀት ለህፃናት እየተሰጠ ይገኛል። በተጨማሪም ሕፃናት እንደተወለዱ የሚሰጥ ክትባት ለመጀመር እንቅስቃሴ መጀመሩን ለማወቅ ተችሏል:: ነገር ግን በባለሙያዎች በኩል የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት ተገቢ እንደሆነ የሚነሳ ሲሆን፤ የሄፒታይተስ በሽታ መተላለፊያ መንገዱን አውቆ እራሱን ከበሽታው መጠበቅ የሚያስችል ግንዛቤ መፍጠር የሚጠይቅ መሆኑን ይናገራሉ።
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 24/2013