አሸባሪው ህወሓት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ስፍር ቁጥር የሌለውን በደል አድርሷል። ዛሬም ከእኩል ተግባሩ አልተላቀቀም፤ እንዲያውም ባስ ብሎ ለይቶለታል። በሥልጣን ላይ በነበረበት 27 ዓመታት በህዝብና በአገር ላይ የሰራው በደል አልበቃው ብሎ እታገልለታለሁ የሚለውን የትግራይ ህዝብን ዛሬም ድረስ ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለው ይገኛል። በዚህም ሳቢያ ህዝቡን ለከፋ ስቃይና ረሃብ አጋልጦታል። ህዝቡን ለረሃብ መዳረጉ ሳያንስ የዕርዳታ ድርጅቶች እንዳይገቡ ከማድረግ ባሻገር፤ ለህጻናት የተላከውን አልሚ ምግብ ከአፋቸው ነጥቆ ለራሱም አድርጎታል።
እንደሚታወሰው መንግሥት በትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታ ወደሚፈለገው ቦታ እንዲደርስ፣ አርሶ አደሩ በክረምቱ ወራት ወደ እርሻው እንዲገባ እንዲሁም ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ መኖሪያ ቀያቸው እንዲመለሱ እና ምናልባትም ከአሸባሪው ቡድን መካከል ወደ ሠላም መንገድ መምጣት የሚሻ አካል ካለም ዕድል ተሰጥቶ እንደነበር አይዘነጋም ። ነገሩን አርቆ ያሰበው መንግሥትም ክልሉ በልማት ወደኋላ እንዳይቀር፤ አርሶ አደሩም ተረጋግቶ የእርሻ ሥራው ላይ ትኩረት እንዲያደርግ የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነትም አድርጓል።ነገር ግን አሸባሪው የህወሓት ጁንታ ዕድሉን አልተጠቀመበትም።
አሸባሪው ቡድን እና እኩይ ተከታዮቹ ይህንን የመንግሥት ውሳኔ እንደ መልካም አጋጣሚ ቆጠሩት። በአንድ በኩል ‹መንግሥት ህዝቡን ለማስራብ ነው ውሳኔውን ያሳለፈው› እያሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ‹መንግሥት ተሸንፎ ነው› ሲሉ የሀሰት ወሬያቸውን በራሳቸው አንደበት እና በተከፋይ ቃል አቀባዮቻቸው እንዲሁም አሸባሪው የሚደግፉ አንዳንድ የውጭ አገር ‹የስም› ለጋሽ ድርጅት ጋር ለክፉ ሥራ በማበር ወሬውን በስፋት ለማንሸራሸር ሲደክሙ ተስተውሏል።
መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ከማድረጉ በፊት በመቀሌ 400 ሺህ ኩንታል የእርዳታ እህል፣ 2ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት፣ 14 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ፣ 536 ኩንታል በላይ ማዳበሪያ፣ ከ37 ሺህ በላይ ኩንታል ምርጥ ዘር ገዝቶ ለህዝቡ ደህንነት ሲባል አስቀምጦ እንደ ነበር ይታወሳል። መታረስ ከሚችለው መሬት 70 በመቶው እንዲታረስ ተደርጓል። ከነዚህ በተጨማሪም ከ10 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ምግብ፣ 664 ቶን ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁስ ከ47 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ በአጋር አካላት በኩል ወደ መቀሌ መግባቱ ይታወቃል።
ከተናጥል የተኩስ አቁም ስምምነቱ በኋላ ቢሆን መንግሥት መንገዶችን በማመቻቸት፤ የእርዳታ አቅርቦት እንዳይቋረጥ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመሆን በጋራ ሰርቷል። እስከ ነሐሴ 5 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ብቻ ወደ ትግራይ ክልል የምግብ ዕርዳታን ይዘው የገቡ የጭነት መኪናዎች 277 ደርሰዋል። በተቃራኒው አጥፊው ቡድኑ ግን ባሳለፍነው የሐምሌ ወር ላይ በአፋር በኩል ወደ ትግራይ ክልል ምግብና ምግብ ነክ ያልሆነ ሰብዓዊ እርዳታ ጭነው የሚጓጓዙ 189 ከባድ ተሽከርካሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ የሽብር ጥቃት ፈጽሞ የእርዳታ መስመሩ እንዲዘጋ አድርጓል። እርዳታ አድራሾቹ ተሽከርካሪዎች ለመቆም መገደዳቸውንም የግድ ማስታወስ ያስፈልጋል።
በትግራይ ህዝብ ስም የራሱን እና የውጭ አገር አለቆቹን አላማ ለማስፈጸም ደፋ ቀና ማለቱን የተያያዘው የጁንታው ቡድን አንዳንድ በእርዳታ ስም የተቋቋሙ ድርጅቶችም ከተቋቋሙለት አላማ በመውጣት፤ የአገርን ጥቅም በሚጻረር መልኩ በመንቀሳቀስ አይዞህ በርታ በማለት በሃሳብም በቁሳቁስም አግዘውታል። ይህ ክፉ ሥራቸው ታውቆም ለሦስት ወራት የታገዱ ሦስት የእርዳታ ድርጅቶችም እንደነበሩም ይታወቃል።
አገር ለማፍረስ ያልተሳካለት አሸባሪው ህወሓት የትግራይን እናቶችን እያስለቀሰ ፤ገና በታዳጊ ልጆች ከመዳፋቸው በመንጠቅ ሲሻው በአደንዛዥ እጽ እያደነዘዘ ‹መንግሥት በህልውናክ መጥቷል ተነስ።› እያለ መቼም የማያበራውን የሃሰት ትርክቱን በመንዛት ወደጦርነት እየማገዳቸው ሲሆን አሸባሪ ቡድኑን ግን ‹ትክክል አይደለህም፤ እየፈጸምክ ያለው ከባድ ወንጀል ነው ።›ብሎ ለመናገር የደፈረ በሰብዓዊ እርዳታ ስም የተቋቋመ ድርጅትም ይሁን ገለልተኛ ሚዲያ የለም ።ይባስ ብሎም ድርጅቶቹ በንጥረ ነገር የበለጸገውን የህጻናቱን አልሚ ምግብ ለአሸባሪው ጁንታ ቡድን በሥጦታ አበርክተውለታል። አሸባሪውም ህጻናቱን እያስራበ እርሱ ግን የገዛ አገሩ በባዕዳን በተሰጠው አልሚ ምግብ በመታገዝ ኃይልም ጉልበትም እያገኘ አገሩን እየወጋ ይገኛል።
ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማትም ዝምታን መምረ ጣቸውም ትልቅ ግፍ እና በደል ነው። ከሳምን ታት በፊት ኢትየጵያን ጨምሮ ምስራቅ አፍሪካን የጎበኙት የአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት ኃላፊ ሳማንታ ፓወር፤ በትግራይ ክልል ለተረጂዎች የቀረ በው ምግብ ሊያልቅ እንደሆነና መጋዘኖችም ባዶ እንደሆኑ በመግለጽ መንግሥትን ሲወቅሱ ምንም አላቅማሙም ነበር። ይህንን እንደተናገሩ ብዙም ሳይቆይ ለህጻናት እና ለእናቶች ይጠቅማቸዋል የተባለው ኃይልና ጉልበት የሚሰጠውን አልሚ ምግብ በአሸባሪው ህወሓት እጅ ተገኝቷል። ይህ እውነታ ሲደረስበትም ጁንታው እና እነ ሳማንታ የውሸት ካባቸውን እንዲከናነቡ አድርጓቸዋል።
ወደ ክልሉ አልሚ ምግቦችን ጨምሮ የተለያዮ ድጋፎች መላካቸው ይታወቃል። ታዲያ እርዳታውን የላኩት ድርጅቶች የተላከውን እርዳታ ለተረጂዎች መድረስ አለመድረሱን ማረጋገጥ ነበረባቸው፤ ይህንን ግን አልተገበሩትም።ስለዚህ አሸባሪውን እየቀለቡ ምግብ አለቀ መጋዘን ባዶ ሆነ ብሎ መውቀስም ተገቢ አይደለም።
መርጦ ዘጋቢ የሆኑት ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንም አሸባሪው ቡድን እና ግብረ አበሮቹ ጉልበት ሰጪ አልሚ ምግቦቹን ከተረጂ ህጻናት አፍ ነጥቀው ጁንታውን ብርታት እና ጉልበት ይሁንክ ብሎ መስጠቱ ሲነገር ተመልክተው ምንም አለማለታቸውም አሳፋሪ ተግባር ሆኖ ተመዝግቧል። የአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅትም (ዩኤስኤይድ) አልሚ ምግቦችን ለአሸባሪው ቡድን መስጠቱን እንደማይቀበለው ሆኖም ግን በአብዛኛው ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ላይ ታጣቂዎቹ (አሸባሪው ህወሓት) እርዳታ ከሚፈልጉ ሰዎች እንደሚሰርቁ ደርሼበታለሁ ሲል እውነታውን ለመደባበስ ሞክ ሯል።
አሸባሪውን ህወሓት መደምሰስ ጊዜ የሚሰ ጠው ጉዳይ አይደለም። ህብረተሰቡ የቻለውን ሁሉ በማድረግ ቡድኑን እኩይ ተግባር ማውገዝ ይገባል። ለጋሽ ድርጅቶቹ ለህዝብ አዛኝ በመመሰል በህዝብ ላይ አሳዛኝ በደል ሲፈጸሙ ዝምታን መምረጥም ከወዲሁ ካልታረመ ብዙ ዋጋ ያስከፍላል። እንዲህ ያለ ግፍ ሲፈጸም ሥራቸውን በማጋለጥ ፤ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስገንዘብም ያስፈልጋል። በሥራቸውም እንዲሸማቀቁ እንዲህ ያለ ተግባራቸውን እንዳይደ ግሙት ለማድረግ ጊዜው አሁን በመሆኑ ሁሉም የድርሻውን መወጣት ይጠበቅበታል።
እየሩስ ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 20 ቀን 2013 ዓ.ም