እርግጥ ነው ከቅርብ ግዜ ወዲህ በእኛና በአሜሪካ “አሊስ” የምትላቸው ተባባሪዎቿ መካከል መካረር ይታያል። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ሌላ ሳይሆን ለእኛ ለሀበሾቹ የማንነትና ሉአላዊነት ጉዳይ በመሆኑ ነው።
በእርግጥ ለዘመናት “ስትጣራ አቤት”፣ “ስትልክ ወዴት”ን የለመደችው አሜሪካ አሁን ላይ “ለምን?” የሚል የማንነት፣ ምክንያታዊነት፣ ዲሞክራሲያዊነት ወዘተ ጥያቄ ሲነሳ ብትበረግግ፣ በርግጋም ለማስበርገግ ብትሞክር ምንም የሚገርምም ሆነ የሚደንቅ ነገር የለውም። የዚህም ምክንያቱ ይታወቃልና ነው የማይገርመው፤ የማይደንቀውም።
አሜሪካ አብዝታ እተማመንበታለሁ፣ እመካበታለሁ፣ የአለም ቤዛ ነው፣ ዋልታና ማገር ነው ወዘተረፈ በማለት የምታመፃድቀው አንድ ትልቅ ሰነዷ ቢኖር “የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ”ዋ ሲሆን እሱንም ቢሆን ለማስፈፀም የምትጠቀመው “አዋጭ” ዘዴዋ ሀይልና መሳሪያ ነው።
እውነቱ ግን እንደሱ አይደለም፤ እውነቱ ከሁለት አመት በፊት የሩሲያው ፑቲን በሚገባት ቋንቋ የነገሯት ሲሆን እሱም “የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ እንጂ ማነው የአለም ውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ያደረገው?” የሚለው ነው።
ምንም ጥርጥር የለውም፤ ፑቲን ያሉትን አለመቀበል ሊሆን የሚችል ነገር አይደለም። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ እንጂ የሌላ የማንም ሊሆን አይችልም። ሆኖም እንደ አሜሪካውያን አባባል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የአለም የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መሆን ከቻለ የሌላው የማይሆንበት ምንም ጉዳይ የለምና አሜሪካ “የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ”ዋን እንደ አንድ የመጨቆኛ መሳሪያ አላደረገችውም ብሎ ሙግት መግጠም ውሃ ሊቋጥር የሚችል መከራከሪያ ሀሳብ አይደለም።
የውጪ ጉዳይ ፖሊሲዬ ነው ብሎ እዛ ማዶ ሄዶ አገር ማፍረስ፣ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲዬ ነው በማለት ምንም አይነት የድንበርም ሆነ ሌላ ግንኙነት እንኳን በሌለበት የሰው አገር መንግስት መገልበጥና መሪ መለወጥ፣ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲዬ ነው በሚል ፍፁም ከዘመኑ ጋር በማይሄድ አስተሳሰብና ዲፕሎማሲያዊ አሰራር አይን ያወጣ ጣልቃ ገብነት … ሄዶ ሄዶ ከእነዛ ማንነታቸው ከተደፈረው፣ አገራቸው ከተተራመሰው፣ መንግስታቸው ከተገለበውና አሻንጉሊት መንግስት ከተቋቋመባቸው አገራት ጋር ማላተሙ የማይቀር ብቻ ሳይሆን እውን የሚሆንና ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው።
እርግጥ ነው አንዴ እራሷን “የአለም ፖሊስ”፣ “የሰብአዊ መብት ጠበቃ”፣ የተራቡትን አልባሽ፣ የታረዙትንም አጉራሽ አድርጋ እራሷን ከፍታው ላይ አስቀምጣለች። ይህ ማንም አገር ሊያደርገው የሚገባ፣ አገርንና ህዝብን ከፍ የማድረግ ተግባር ነውና የሚደነቅ ነው። ይህ ሊሆን የሚገባው ግን የሌላውን አገር ማንነትና ሉአላዊነት እስካልነካ ድረስ እንጂ የሌላውን መብት እስኪጨፈልቅ ድረስ ሊፈቀድለት አይገባም።
የፑቲንን “የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ እንጂ ማነው የአለም ውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ያደረገው?”ን ስንጠቅስ በአድናቂ ፑቲንነት አይደለም፤ ፑቲንን ስንጠቅስ በተያያዥ የሚታወሱን ጉዳዮች ስላሉ ነው። ይህም ማለት አሜሪካ ብድግ እያለች ያሻትን ታደርግ ዘንድ “የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዬ …” የምትለው እንደሚፈቅድላት ታውጅ እንጂ፣ እያልን ያለነው አለም የምትመራው ወይም አለምን ሊገዛ የሚገባው አለም አቀፍ ህግጋት እንጂ በአንድ አገር ነጠላ ሕግ አይደለም ነው።
እየተባለ ያለው፣ ኢትዮጵያም እየወተወተችና ከራሴ ላይ ውረዱ እያለች ያለችው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የአፍሪካ ህብረትን የመሳሰሉ አህጉር አቀፍና አለም አቀፍ ተቋሟት አሉ። እነዚህ ተቋማት ደግሞ በአባል አገራቱ ያፀደቋቸው አለም አቀፍ ህጎች አሏቸው። በመሆኑም አለም ልትመራ የሚገባው በእነዚህ ህግጋት እንጂ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አይደለም ነው።
አሁን ያለንበት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊም ይሁን ማህበራዊ ሁኔታ ጥሩ አይደለም፤ ወይም የደፈራረሰ ነው። ለመደፈራረሱ ቀዳሚው ምክንያት የራሳችን የሽብር ቡድን ህወሃት ይሁን እንጂ ግራም ነፈሰ ቀኝ እየተካሄደብን ያለው ጦርነት የውክልና ጦርነት ነው። የጦርነቱም ወሰን ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ እየተካሄደ ያለ የሚመስለን ካለን ተሳስተናል። ጦርነቱም ይሁን ግጭቱ፤ ወይም የውክልና ጦርነቱ ከኢትዮጵያም ባለፈ ቀጠናውን (ቀንዱን) ያካለለና እሱንም የማተራመስ ስትራቴጂን መሰረት ያደረገ ነው። በመሆኑም ከባድና ውስብስብ ነው።
የዚህን ከባድና ውስብስብ ሁኔታ (ቀውስ) በበላይነት እየመራች ያለችው ደግሞ (ምንም ሳንሸዋወድ መነጋገር ካለብን ታላቋና የአለም ፖሊስ ነኝ ባይዋ አሜሪካ ነች። ለዚህ ማረጋገጫችን ደግሞ እንደ ውሀ ቀጂ ወደ ቀጠናው ከሚመላለሰው የአሜሪካ ቱባ ቱባ ልኡካን ቡድን በተጨማሪ አንቶኒ ብሊንከን እዛው ዋሽንግተን ሆነው በማንኛውም መንገድ፣ እጃችን ላይ ባለው ሁሉ አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን ማለታቸውና እያደረጉትም መሆኑ ነው።
“ፍላጎታችንን ለሟሟላት ይረዱናል” በሚል ለዘመናት ሲጠሉት የነበረውን የህወሃት ቡድን ዛሬ ላይ የተጠናከረ ድጋፍ በማድረግ የውክልና ጦርነቱ ፊታውራሪ ያደረጉት ቀጠናውን፣ በተለይም ቀይ ባህርንና አካባቢውን (የንግድና ሌሎች ጉዳዮች መተላለፊያ በሩን) ከቁጥጥራቸው ስር ላለማስወጣትና ለዚህም የሚያደርጉትን የሞት ሽረት ትግል እንዲጋፈጥላቸው፤ ከሱ ጀርባ በመሆንም ፑፔት መንግስት ለመመስረት መሆኑን ማወቅ፣ ደጋግሞም ላላወቀ ማሳወቅ ተገቢ ይሆናል።
በርእሳችን “ከራሳችን ላይ ካልወረዱ አንወርድም” ስንል ያለ ምክንያት ሳይሆን እየወጋን ያለው የሽብር ቡድኑ ብቻ ሳይሆን ከጀርባው የተሰለፈው “የአለም ፖሊሰ” ነኝ ባዩ ቡድን፤ እየተካሄደ ያለውም የውክልና ጦርነት፤ እየተሰጠ ያለው ፍርድም ፍርደ ገምድልነት የተጠናወተው ነውና ያ ይቁም፤ ያ ካልቆመ ኢትዮጵያ መፍረስ የለባትምና እንዳትፈርስ ሁሉም ዘብ የመቆም ግዴታውን ይወጣል።
ገና ለገና ኢትዮጵያ ያለችው ቀንዱን በተቆጣጠረው መልክአ-ምድርዊ (ጂኦፖለቲክስ የሚሉት) አካባቢ ነውና መፍረስ አለባት? የለባትም። ገና ለገና ኢትዮጵያ ፊቷን ወደ ልማት በመመለስ የተፈጥሮ ሀብቷን መጠቀም ጀምራለችና መጥፋት አለባት? የለባትም። ገና ለገና አንድን በሙስና ናላው የዞረን ቡድን ራዕይ ባለው መሪ በመተካቷ እንዴት ትፍረስ ይባላል? አሁን ጥያቄው “ስለዚህ ምን ይሁን?” የሚለው ሲሆን፤ የመጀመሪያው መልስ “ተዉን” ነው፤ ቀጥሎ “ሁሉንም እንዳመጣጡ ለመመለስ እንገደዳለንና ጊዜ ይፈታዋል” የሚል ሲሆን ለዚህም ይሄው እንደሚታየው ሁሉም ለእናት አገሩ ዘብ ቆሟል።
በአጠቃላይ፣ ያለንበት ወቅት ከባድ፣ አስቸጋሪ ብቻም ሳይሆን የተወሳሰበ ውስብስብ፤ የተቆላለፈ ቁልፍልፍ ነው፤ በተለይም በራሷ ውላጆች ለምትሰቃየው ኢትዮጵያ። ከኢትዮጵያም ባለፈ ለቀጠናው ብቻም ሳይሆን ለአጠቃላይ አፍሪካም የሚተርፍ ጦስን ይዞ ነው ጊዜው እየፈተነን የሚገኘው። ይህ ብቻም ሳይሆን አሜሪካ በቀጠናው ለዘመናት የተከለችው መርዝ የሚነቀልበት፣ የቆፈረችው ጉድጓድ የሚደፈንበት፤ የዘረጋችው መረብ የሚበጣጠስበት ወዘተረፈ ወቅት ነውና ከዚሁ አኳያ ሁሉም እራሱን ሊያዘጋጅ ይገባል። ለአበሻም “ዘጠኝ ሞት መጣ ቢለው፣ አንዱን ግባ በለው” የሚለው መፈክሩ ሊሆን፤ በክርክሩም “ከራሳችን ላይ ካልወረዱ አንወርድም” ማለት ይገባል እያልን በዚሁ እናብቃ።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 16 ቀን 2013 ዓ.ም