በትግራይ ሲካሄድ የቆየውን የህግ ማስበር ዘመቻ ተከትሎ የበርካታ ዜጎች ህይወት አልፏል፤ በርካቶችም ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። ከዚህም ባሻገር በአካባቢው በሚደረገው የህግ ማስከበር ዘመቻ ዜጎች ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች መዳረጋቸው እሙን ነው። በተለይ ጦርነት በሰው ልጆች ላይ ከሚያደርሰው የስነልቦና ቀውስ አንጻር ብዙዎች ለአእምሮ ህመም ሊዳረጉ እንደሚችሉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። በተለይ የአሸባሪው የህወሓት ቡድኖች ህጻናትን በጦርነት በማሰለፍና ሰላማዊ ዜጎችን ከግጭት ፊትለፊት በመማገድ እነዚህ ህብረተሰብ ክፍሎች የግጭትን አስከፊነት በግንባር እንዲጋፈጡ በማድረግ ለተለያዩ ማህበራዊ ቀውሶች እንደሚዳረጉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። እኛም ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት የዘርፉን ባለሙያ አነጋግረናል።
እንግዳችን ዶክተር ዳዊት ወንድማገኝ ይባላሉ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥቁር አንበሳ የህክምና ሳይንስ ኮሌጅ ኃላፊ ናቸው። ከዚህም ባሻገር ‹‹ቤት የመቱ ሀሳቦች›› በሚል ርዕስ የግጥም መድብል ያሳተሙ ሲሆን፤ ‹‹አለመኖር›› በሚል በአእምሮ ጤና ላይ ያተኮረ የልብወለድ ድርሰትም ለህትመት አብቅተዋል። የዚሁ ቀጣይ ክፍል የሆነው ‹‹አለማወቅ›› የተሰኘ ድርሰታቸውም ለህትመት ተሰናድቷል። ከእንግዳችን ጋር በአዕምሮ ህክምና ዙሪያ እንዲሁም በሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ውይይት አድርገናል፤እንደሚከተለው ተሰናድቷል።
አዲስ ዘመን ፡- በሀገሪቱ የተወሰኑ አካባቢዎች የዜጎች መፈናቀልና ጦርነት አለ፤ ይሄን ተከትሎ የሚመጣ የአዕምሮ እክል ምን እንደሚመስል ይንገሩንና ውይይታችንን እንጀምር?
ዶክተር ዳዊት፡- ልክ ነሽ፤ ከጦርነትና ግጭቶች ጋር ተያይዞ በሰዎች ላይ ብዙ ጊዜ የአዕምሮ እክሎች ሲያጋጥሙ ይስተዋላል። ከዚያ በፊት ግን የአዕምሮ እክል ስንል ምን ማለታችን ነው? አንድ ሰው አዕምሮው ደህና ነው የምንለው መቼ ነው? የሚለውን ነው ማንሳት ያለብን። አንድ ሰው አዕምሮው ደህና ነው የምንለው ያለውን ሀሳብ፣ ስሜትና ፍላጎት አንድ ላይ አዋቅሮ ከሌሎችና ከአካባቢው ጋር ማንኛውንም አይነት ሥራ እየሰራ ማድረግ የሚጠበቅበትን እያደረገ በደህንነት መኖር ሲችል ነው። ሁለተኛ ደግሞ ችግሮች ሲኖሩበት እሱን መቋቋም ሲችል ነው። ስለዚህ ሀሳቤ ሰላም ነው፤ ችግር የለም ስል ፍላጎቴ ይሄንን ብነግድና ባተርፍ፤ ባጠና እና ብማር ቢሆን ሥራዬን ሰራሁ ማለት ነው። ከዚያ ደግሞ የሚወጣውን በጎ ስሜት አስተናግዳለሁ፤ ስለዚህ የሚገጥመኝም ችግር በሥራ ሆነ በትምህርት አልፈዋለሁ። ሀሳቤ ሰላም አይደለም፤ በማንኛውም ሰዓት ችግር ሊመጣብኝ ይችላል፤ የምበላው የምጠጣው የለኝም፤ የማድርበት የለኝም ከሆነ ደግሞ ሁኔታዎቹ በተቃራኒው ይሆናሉ። ፍርሀት እና ስጋት ይሆናል፤ የለመድኩትን ሰርቼ ልኑር፣ ተምሬ ልደግ የሚለው ነገር ሁሉ ይቋረጣል ማለት ነው። በዚያ ምክንያት የሚኖረኝ ፍላጎት አስተሳሰብ ሁሉ ጤናማ ወደአልሆነ መንገድ ይሄዳል። የሚያጋጥሙኝን ነገሮች ደግሞ ባለፈው መቋቋም ከምችለው በላይ መቋቋም የምችለው ይሆናል። ምናልባት አሁን እኔና አንቺ ያለንበት ሁኔታ በሰላም ስለምንኖር ጠዋት እንወጣለን። ምናልባት ትልቁ በጣም የሚያስቸግረን ነገር ትራንስፖርት ተሰልፎ መጠበቅ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ እሱን ወይ ተሰልፌ ወይም በጠዋት ወጥቼ አልያም የሆነ ዘዴ ፈጥሬ ብቻ በአንድ መልክ እወጣዋለሁ። ሰላም ባይሆን ግን መውጣት፣ መሄድ፣ መኖር አልችልም። በዚህ ምክንያት ከባድ ወደሆነ የአእምሮ ጭንቀት፣ መዛባት እና መረበሽ ሊያጋጥመኝ ይችላል።
አዲስ ዘመን ፡– በዚህ ወቅት በተለየ ሁኔታ ተጋላጭ የሚሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች አሉ?
ዶክተር ዳዊት፡– አሉ፤ በተለይ ደግሞ በተፈጥሮ ወይም በእድገታቸው ሁኔታ ተጋላጭነታቸው ከፍተኛ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች አሉ። ለምሳሌ አንድ ነገር ቢመጣና ሮጦ ማምለጥ ቢኖርብን ወጣች ሊያልጡ ይችላሉ። ስለዚህ አረጋውያን ባላቸው የእድሜ ወሰን፣ የቦታ ቁርኝት አንጻር እነሱ ላይ የሚኖረው ጫና ከባድ ይሆናል። አንድ ቦታ ላይ 50 እና 60 ዓመት ከኖርሽበት በኋላ ድንገት ብድግ ብሎ መሄድ ቀላል አይደለም። ማንም ሰው ማንነቱ ከቦታ ጋር የተያያዘ ነው፤ ‹‹እኔ ነኝ›› የምለው ነገር ከቦታ ጋር በጣም ይያያዛል። ‹‹እኔ›› የሚለውን ነገር ቀርጸው የሚኖሩት እና ረጅም ዓመት ከኖሩበት ቦታ አረጋውያን እዛ ያሉ ወዳጆቻቸው፣ የሃይማኖት መሪዎቻቸው እና ተቋሞቻቸውን ሁሉ ይይዛል። ከቦታ ጋር ያለን ቁርኝት በጣም ትልቅ ነው ፤ በዚህ ምክንያት መፈናቀልም ሆነ ከአንድ ቦታ መሄድ ለአረጋውያን በጣም ከባድ ነው። አንዳንዴ በዚህ ምክንያት አልሄድም የመጣው ይምጣ ብለው ለአካላዊ አደጋ ሊጋለጡ ይችላሉ።
በሌላ ጊዜ ደግሞ ወተው ሊሂድም ቢሉ ከለመዱት ማህበራዊ ህይወት ተገንጥለው ትርጉም ባጣ መልኩ የአኗኗር አቅማቸውን አጥተው ለችግር ይጋለጣሉ። ከአረጋውያን የጀመርኩት ሆን ብዬ ነው፤ ምክንያቱም ሁልጊዜ ስለአረጋውያን ስለማናነሳ ነው። ግን በጣም ተጠቂ የሚሆኑት ኋላም የሚቀሩት አረጋውያን ናቸው። ህፃናት ሁለተኛ ናቸው፤ በእድገት ደረጃቸው ምክንያት በራሳቸው ወስነው ለመኖር የማይችሉበት የእድገት ደረጃዎች ስላሉ በሰላም የሚኖሩት አካባቢያቸው፣ ወላጅ፣ ሰፈር እና ትምህርት ቤት እነዚህ አራቱ ነገሮች አንድ ላይ ሆነው ነው የልጆችን እድገት የሚወስኑት። ትምህርት ቤት የለም፤ የሰፈር ልጆች የሉም፤ ቤተሰብ ይበታተናል፤ ወላጆች አብረው ላይሆኑ ይችላሉ። እነዚህ ሁሉ ነገሮች ተሸፍነው በደህንነት ይኖር የነበረ ልጅ በድንገት ከኖረበት ሲወጣ ከለላ የሆነለት ነገር ሁሉ በአንዴ ይጠፋና እራቁቱን ይቀራል። ይሄን ማሰብ ያለብን የዛን ያህል ነው፤ የተወለደ ልጅ ራቁቱን ብንተወው ሰውነቱ ቀዝቅዞ ይሞታል። ከዚያ ግን ቤተሰብ እና ሌሎች ሽፋኖች ድንገት በጦርነት በመፈናቀል ሲጠፉ ልጆች በጣም ግራ ይገባቸውና ለከፍተኛ ጭንቀት ይጋለጣሉ።
በመቀጠል ደግሞ ሴቶች አሉ፤ ሴቶች በተፈጥሮና በተለያዩ ምክንያቶች ለችግር ተጋላጭ ናቸው። ሀገር ሰላም ሆነም፤ አልሆነም ብዙ የቤተሰብ ኃላፊነቶች ሴቶች ላይ ያርፋሉ። ስለዚህ እናት ልጇን ትታ የመሄድና ሮጣ የማምለጥ እድሏ በጣም አነስተኛ ነው። በቀሚሷም ቢሆን ከልላ ትደብቀዋለች። ስለዚህ ለጥቃት ይጋለጣሉ ሴቶች። ሁለተኛ ልጇን ብቻ ሳይሆን ወላጆቿንም ትታ ለመሄድ እንደዚሁ አስቸጋሪ ስለሚሆን አደጋ ባለበት ቦታ የመቆየት ችግር ይገጥማቸዋል። በተጨማሪም ብዙ ጊዜ በኛ ሀገር ባለው የቤተሰብ አወቃቀር እናቶች የኢኮኖሚ ጥገኛ ናቸው። በመሰረቱ ጥገኝነት እራሱ ችግር ነው፤ ግን ደግሞ ተመፅዋች ያደርጋቸዋል። ይህም ደግሞ ለችግር ተጋላጭነታቸውን ይጨምራል።
በሌላ በኩልም የቆየና የሚታወቅ ህመም ያለባቸው ሰዎች በግጭትና በመፈናቀል ምክንያት ከፍተኛ የአዕምሮ እክል የሚደርስባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው። ለምሳሌ መጀመሪያውኑ የአዕምሮ ህመም ያለባቸው ሰዎች እንደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ሲገቡ ችግሩ የባሰ ይሆናል። ሌላም አካላዊ ህመም ያለባቸው ለምሳሌ የስኳር ፣ ደምግፊት፣ ኤች.አይ.ቪ፣ ካንሰር ያሉና በየቀኑ መድኃኒት የሚያስፈልጋቸው በሽተኞች ህክምናቸው ይቋረጣል። በነገራችን ላይ ይሄ በጣም ትልቅ የሆነ የማህበረሰብ ቀውስ የሚፈጥር በመሆኑ ያንን በደንብ መረዳት ያስፈልጋል።
ሁልጊዜም ቢሆን ጦርነት ጦሱ ይህ ነው፤ አሁን ለምሳሌ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ማድረጉ በጣም ጥሩ ነገር ነው። እኔ እንደግለሰብም ሆነ እንደአዕምሮ ሐኪም ተኩስ አቁሙን እደግፈዋለሁ። ምክንያቱም በተተኮሰ ቁጥር በየትኛውም ወገን የሚሞት ሰው አለ። ስለዚህ ተኩስ ማቆም በጣም ጥሩ ነገር ነው። ይሁንና አንደኛው ወገን ስለሚወክለው ህዝብ ምንም ሳይጨነቅ ካልተጋጠምን ሲል በግሌ የጦርነቱን ጥቅም መረዳት ይቸግረኛል። ዞሮ ዞሮ ጦርነት በከፍተኛ ሁኔታ የመኖር ህልውናን አደጋ ላይ ስለሚጥል ለአእምሮ ህመም መጋለጥ ያን ያህል የሚደንቅ አይደለም።
አዲስ ዘመን ፡– ለተፈናቀሉ ወገኖች የቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ሁሉ ለተፈጠረባቸው የስነልቦና ቀውስ ትኩረት ተሰቶት የሚደረግላቸው ህክምና ምን ይመስላል?
ዶክተር ዳዊት፡– ሁልጊዜ ማስተዋል ያለብን ነገር እንዲህ ቁጭ ብለን ስንነጋገርና መሬት ላይ ያለው ነገር አንድ አይነት አይደለም። መሰረታዊ ነገሩ እነዚህ የተፈናቀሉትም ሰዎች የመኖር መብት አላቸው። ስለዚህ የተፈናቀለው ሰው ቀድሞ የነበረበት ቦታ በተወሰነ መልክ የተለመደ የሚመስለውን አኗኗር መልሶ መገንባት ያስፈልጋል። ስለዚህ ቤት ፣ ልብስ እና ምግብ ያስፈልጋል። ይሄ ከተሟላ በኋላ ደግሞ እንግዲህ የጤና እና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች ሊያገኝ ይገባል። ሰው ተፈናቅሎ የሚሄድባቸው ቦታዎች ለመኖር የሚመረጡ አይደሉም። ስለዚህ አካባቢውን ለመኖር የሚመች ከማድረግ ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ትኩረቶች ይፈልጋል።
ይህ በሚሆንበት ጊዜ ፊትለፊት ለማይታዩ ነገሮች ትኩረት ለመስጠት ያስቸግራል። ለምሳሌ ራቁታቸውን የሄዱ ልጆች ካሉ ልብስ እሰጣለሁ፤ እነዚህ ሁሉ ልጆች ግን ጨንቋቸው እንቅልፍ የማይተኙ ቢሆኑ ግን ለመረዳት ያስቸግራል። ጥቃት እና መደፈር አይታይም፤ እነዚህ የዝምታ ወረርሽኞች ይሆናሉ። በነገራችን ላይ በተፈናቀለውም ሆነ ጦርነት ውስጥም ባለው ማህበረሰብ ውስጥ የዝምታ ወረርሽኞች አሉ። ግን ፊት ለፊት አናየቸውም፤ በመሆኑም በትኩረት የመስራት እድላችን አነስተኛ ነው። ግን ሁሌም የምንዘነጋው በአንጻሩ የሰው ልጅ ምን ያህል ችግርን የመቋቋም አቅም ያለው ፍጡር መሆኑን ደግሞ እንረሳዋለን። ስለዚህ አብዛኞቹ ሰዎች ጥቃትም ደርሶባቸው መሰረታዊ ነገራቸው ከተሟላ ይመለሳል። የደረሰባቸውን ችግር አልፈው ዳግመኛ ለመኖር መታገል ይጀምራሉ። በቁጥር ትንሽ ቢሆኑም ግን የተወሰኑት የኛን ቀጥታ ትኩረት ለህመማቸው የሚፈልጉ አሉ። እነሱን መምረጥ ደግሞ በሂደት የሚስተካከል ነገር ነው።
አዲስ ዘመን ፡– በሀገሪቱ በቅርብ ጊዜያት ህፃናት በጦርነቱ በቀጥታ በወታደርነት ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ፤ ይሄ በታዳጊዎቹ ላይ ምን አይነት ተጽዕኖ ይኖረዋል?
ዶክተር ዳዊት፡– እንዳልሽው ብዙ ጥናቶች የሚያሳዩት ይህንኑ ነው። ሲጀመር ህፃናትን ለጦርነት መጠቀም ወንጀል ነው። ምንም የሚሸፋፈን ነገር አይደለም፤ ህጻናትን ጦርነት ውስጥ በቀጥታ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ ይቅርና በጦርነት ውስጥ ሳይታሰብ ጥቃት እንዲደርስባቸው ማድረግ ወንጀል ነው። እነዚህ ህፃናት ከሚያሳልፉት ህይወት ወተው ወደፊት ማገገምና ወደነበሩበት የልጅነት ሰነልቦና መመለስ ከባድ ይሆንባቸዋል። እንደምታውቂው በእኛ ሀገር እነዚህን ህፃናት አሁን እንኳን አውጥተን እንዲያገግሙ እናድርጋቸው ብንል እንኳን እነሱን ለማገገም የሚያስችል ስርዓት አልፈጠርንም። ስለዚህ በጣም ከፍተኛ ለሆነ የስነልቦና ቀውስ የሚጋለጡ ነው የሚሆነው። ተመልሰው ወደ ትምህርት ቤት ገብተው እንደሌሎች እኩዮቻቸው መሆን አይችሉም። ያ ማለት የእድገት እድላቸውን አሳጥተናቸዋል ማለት ነው። ተምረው አንድ ቦታ የመድረስ እድላቸውን ነፍገናቸዋል። ለመማርም ሆነ ለሌላም ሥራ ማህበራዊ ተሳትፎ የሚያገኙበትን የወደፊት እድል ተነጥቀዋል። ስለዚህ በወደፊት ማንነታቸው ላይ ትልቅ ጫና ነው የሚፈጥረው። ይሄ በጣም በመሰረታዊ ደረጃ ህፃናትን በጦርነት ተሳታፊ ማድረግ ትልቅ ወንጀል ነው የሚባለው ለዚያም ነው ። አንድ ጊዜ በውጊያ አውድ ላይ የተሳተፈ ታዳጊ ተመልሶ ከማህበረሰብ ጋር ለማቀላቀል ቢቻል እያንዳንዱ ህጻን ልጅ ግን በውስጡ ይዞት የሚኖረው ስቃይና ሰቆቃ ለመረዳት በጣም አዳጋች ነው የሚሆነው።
ህፃናትን ጦርነት ውስጥ የሚያሳትፉ አካላት መረዳት ማወቅ ያለባቸው ነገር ፤ የፖለቲካም ሆነ ሌላ ፍላጎት ሁሉም ሰው ሊኖረው ይችላል፤ ግን ህፃናትን በዚህ ውስጥ በማስገባታችን፤ ይዘገይ ይሆናል እንጂ የምንቀበለው የራሳችን የሆነ የአዕምሮና የስነልቦና ቅጣት ይኖረዋል። ምክንያቱም እኔ አሁን ህፃን ልጅን ሰው ግደል ብዬ አዝዤው ምንም ሳይሰማኝ ሰላማዊ ኑሮ መኖር አልችልም። በህፃኑ ላይ ያደረኩትን ነገር ለራሴ ምንም አድርጌ ባስረዳው ራሴን ይቅር ልለው አልችልም። በአጠቃላይ ጉዳቱ በሁሉም ዙሪያ በመሆኑ ይህንን በአግባቡ ማስተዋል ያስፈልጋል። ‹‹ስለዓለም ያገባናል›› የሚሉ አካላት በሙሉ በጠቅላላ ይሄንን ጉዳይ ትኩረት ሊሰጡት ይገባል። የህፃናት ጦርነት ውስጥ መግባት በተለይ በአፍሪካ በጣም የተለመደ ነው። በሴራሊዮን፣ በኮንጎ እና በርዋንዳ እናውቃለን፤ ውጤቱንም አይተናል፤ ከዚህ ውስጥ ሲወጡ ምን አይነት ማህበረሰብ እንዳተረፉ፤ ምን አይነት ሀገር ሆነው እንደቀሩም እናውቃለን። በእኛ ማህበረሰብ ደግሞ ይሄ ማህበራዊ አወቃቀር ሲታይ እንደሌሎቹ አይደለም። ከእንደዚህ አይነት ሁኔታ ለማገገም በጣም ይቸግረናል። ምክንያቱም ያለን የሃይማኖት የባህል ትስስር ከሌሎች የተለየ ነው፤ ልጅ እኮ በአርባ ዓመቱም ከእናት ከአባቱ ጋር ነው የሚኖረው። ስለልጅ ያለን ነገር ያን ያህል ነው። ልጄ የምንለውን አቅፈን ደግፈን የመያዝ ሁኔታችን በጣም ከፍ ያለ ነው። ከዚህኛው አመለካከት ተነስተን ይሄንኑ ልጅ ወስደን በህፃንነቱ ጦረኛ ማድረግ በጣም ሩቅ ስለሆነ ችግሩን ማስታረቁ ከባድ ማህበራዊ ሥራ ይፈልጋል።
አዲስ ዘመን ፡– የዓለም መንግሥታት ሆኑ ግብረሰናይ ድርጅቶች በሌላ ዓለም ክፍል ተመሳሳይ ድርጊት ሲፈጸም ሲያወግዙ እናውቃለን፤ አሁን ግን እንዳላየ ዝም ይላሉ፤ እንዲያውም የተወሰኑ አካሎች እንደህዝባዊ መገለጫነት እያቀረቡት ነው። ተቋማትም ሆኑ ግለሰቦች ለተመሳሳይ ጉዳይ እንዴት የተለያየ መመዘኛ ሊኖራቸው ይችላል?
ዶክተር ዳዊት፡– ዓለም እንደዚህ ነው። ሁሌ መርሳት የሌለብን ነገር የዓለም መንግሥታት የምንላቸው ሀገራት ፈጣሪ አይደሉም። ከነሱ ፍትህን መጠበቅ የለብንም። እነሱ በዋናነት የሚጨነቁት አጀንዳቸውን እንዴት አድርገው እንደሚያስፈፅሙ ነው። ስለዚህ የዓለም መንግሥታት የምንላቸው ሀገራት በአብዛኛው እነሱ የሚፈልጉት አጀንዳ ይኖራል፤ ያንን ወደፊት የሚወስድላቸው ነገር ሁሉ ይገፉበታል። እነዚህ ሀገራት አይናቸው እያየ እንዳላየ የሚሆኑት በዚህ ምክንያት ነው። ይህ ሲባል ግን ከእነዚህ አካላት ጋር ፊት ለፊት መጋፈጥ እንደሌለብን እሙን ነው። ተፅዕኖውን ግን በትክክል ማሳወቅ መቻል ያስፈልጋል። በተጨማሪም ይህንኑ የሚመጥን የሚድያ ሥራ መስራት ይገባናል። በጣም ትልልቅ ጋዜጦች ላይ ይሄ እንደጀብዱ ሲፃፍ ‹‹ይሄ ስህተት ነው›› ብሎ ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም መፍጠር መቻል አለብን። መግጠም ያለብን በዛ ደረጃ ነው፤ የሞራልና የስነ-ምግባር መከራከሪያ ይዘን ‹‹ልክ አይደለም›› የሚለው አያስኬደንም፤ ምክንያቱም በዓለም ላይ ብዙ ልክ ያልሆኑ ነገሮች አሉ። በዚህ ረገድ በጣም የዋህነት ይታይብናል። ከየዋህነት ስንወጣ ደግሞ ኃይለኛ እንሆናለን። ‹‹እኛን ማን ይነካናል፤ ስለኛ ምን አገባቸው?›› ብሎ መጮህ አይደለም የሚያስፈልገው። ይልቁኑ ግን ይህንን የሚመጥን ትርክት ጎን ለጎን አብሮ መፍጠር ይገባል። ምክንያቱም እኛ አቤት ማለት ያለብን ለተራ ህዝብ ነው፤ አንድ የምንስተው ነገር እሱን ነው።
እነዚህ ሀብታም መንግሥታት ለህዝባቸው ፍላጎት ተገዢ ናቸው። አፍሪካ ውስጥ ስትመጪ ደግሞ ለህዝቡ ፍላጎት ተገዢ የሆነ መንግሥት ማግኘት ሊቸግር ይችላል። እነሱ ግን እንደዚህ አይደሉም። ስለዚህ በሚድያ መድረስ የምንችለው ህዝቡ ጋር ነው። ለምሳሌ አንድን ሀገር ወስደን መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ እያራመደ ያለው ፖሊሲ ትክክል አይደለም። ትክክል ያልሆነበት ምክንያት ደግሞ ይሄ ነው። እውነታውን ማሳወቅና አቤት ማለት አለብን። ያለበለዚያ ግን ‹‹ ለምድነው እንደዚህ አይነት ነገር የምታደርጉት?›› ብሎ መጠየቁ ብቻ ውጤት አያመጣም። ይሁንና መመዘኛው ፍትሃዊ አለመሆኑን በተጨባጭ ማስረጃ ማሳየትና ማጋለጥ ይገባል።
ይህም ማለት ኃያላን ሀገራት መንግሥታት ስለሚፈሩ የራሳቸውን ህዝብ ፍላጎት እንኳን ቢኖራቸው እንደመንግሥት ከህዝቡ ፍላጎት ጋር በጣም የሚጋጭ ነገር ሊያደርጉ አይችሉም። ለምሳሌ ህፃናትን ጦርነት ውስጥ ማሳተፍ ወንጀል ነው። ማንም መንግሥት እንዳላየ ሊያልፍ አይችልም፤ የሀገሬው ህዝብ ምን እያደረግህ ነው? ብሎ የመጠየቅ መብት አለው። ስለዚህ ብዙ የውይይት መድረኮች አያለሁ ፤ ትልቅ የተባሉ ሰዎች እርስ በእርስ እንዲህ ስንባባል እንውላለን፤ ግን ይሄን የምንለውን ነገር ለእኛ አይደለም መባባል ያለብን። ከዚህ አንፃር አሁን ከሀገር ውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ማድረግ ያለባቸው ነገር ከጎናቸው ላለ ለዛ ሀገር ዜጋ ይሄንን ማስረዳት ነው። እያንዳንዱን ሰው ወስዶ ማለት ነው። በሚድያ ውስጥ ደግሞ ይህን ትርክት ውስጥ አስገብቶ ሰዎች እንዲያውቁት ማድረግ ያስፈልጋል። ያ እዛ ያሉ መንግሥታትን ጫና ውስጥ ይከታቸውና በኛ መንግሥት ላይ የሚያደርጉትን ጫና እንዲቀንሱና አመለካከታቸውን እንዲያጤኑት ያስገድዳቸዋል።
አዲስ ዘመን፡– እንደ ሀገር አማኝ እና ስነምግባር፣ ያለን ህዝቦች ነን እንላለን፤ግን በተቃራኒው ከሃይማታዊ አስተምህሮ የወጣ ጭካኔ የተሞላባቸው ድርጊቶች ሲፈፀሙ ይስተዋላል። ይህ ከምን የመነጨ ነው ብለው ያምናሉ?
ዶክተር ዳዊት፡– አይቃረንም፤ የአንድ ሰው የአንድ ማህበረሰብ የስነ-ምግባር መርህ ደረጃ የሚመሰረተው እንዳለው የደህንነት ሁኔታ ነው። ስለዚህ በተወሰነ መልክ የስነ-ምግባር ጠባቂ የምንለው በማህበረሰቡ ውስጥ ረጋ ብሎ የተቀመጠ፤ በሰላም ውስጥ ያለ የህብረተሰብ ክፍል ነው። ጦርነት ሲሆን ይሄ የተለመደው ማህበራዊ አወቃቀር ይፈርሳል፤ አነስተኛ ገቢ፣ ከፍተኛ ገቢ፣ መካከለኛ ገቢ የሚባል ነገር አይኖርም። ጦርነት ውስጥ ህግ እንጂ ሊገዛ የሚገባው ሞራል አይደለም። ለዚያ ነው ቁጭ ብለን ስናስብ እንዴት እንደዚህ ይሆናል? ወደሚል ጥያቄ ውስጥ የምንገባው። ምክንያቱም እኔና አንቺ ይህንን ስንነጋገር ቢሮ ውስጥ ቁጭ ብለን ነው፤ በአንፃራዊ ሁኔታ ሰላም ባለበት ቦታ ላይ ሆነን ነው ‹‹ልክ አይደለም›› ብለን የምንሞግተው። ይሁንና እኔና አንቺ ጦርነት መሀል ብንሆን አልያም እየተተኮሰብን ቢሆን እንደዛ ላናስብ እንችላለን። ልናስብ የሚገባን ነገር እንደአዋቂ ሰዎች ነው። ግን የፈለገ ቦታ ላይ ብንሆን የህግ ተጠያቂነት አለ። ህፃናትን ወደ ጦርነት ማስገባት ወንጀል ብቻ ሳይሆን በማህበረሰባችንም ነባር እሴት ነው። ከሁሉ በላይ ግን በህግ ተጠያቂነትን የሚያስከትል ነው ወደሚለው መሄድ አለብን። እንዳልሽው እነዚህ ሁኔታዎች እርስበርሳቸው የሚፋለሱ ይመስላሉ። ግን አይፋለሱም፤ ምክንያቱም እነዚያ ቀድሞ የነበሩ ማህበራዊ እሴቶች መዋቅራቸው ስለሚጠፋ የሞራል ጠባቂ አይኖርም። በስደት በጦርነት ላይ መስኪድ፣ ቤተክርስቲያን የለም፤ ሽማግሌ ሰው ‹‹አይዞአችሁ፤ ተው›› የሚል የለም። እነዚህ ሁሉ ጠባቂዎች ሲጠፉ ሰው እራሱ የፈለገውን ለማግኘትም ሆነ ምንም ነገር ለማድረግ ወደኋላ አይልም። ምክንያቱም ማህበራዊ ተቋማት፣ ስርዓት፣ መንግሥት የምንላቸው ባይኖሩ አንዳንድ በዚህ ላይ ያጠኑ ሰዎች የሚሉት ሰውን እንዲሁ ለተፈጥሮ ብንተወው መጨረሻው እርስ በርስ መበላላት ነው። ስርዓት ይዞን ነው እንጂ ስርዓቱ ሲፈርስ በአረመኔነት ከማንም ህዝብ የተለየን አይደለንም።
አዲስ ዘመን ፡– በሀገሪቱ በከተሞች አካባቢ አደንዛዥ እፅ እየተዘወተረ ነው፤ ጦርነት ላይም በአማፂያኑ ወገን ጥቅም ላይ እየዋለ ነው። ይህ ሁኔታ በህብረተሰቡ ላይ በዘላቂነት ምን አይነት ጉዳት ይኖረዋል?
ዶክተር ዳዊት፡– ከባድ ጉዳት ነው የሚኖረው፤ በተለይም ድሀ ሀገር ስትሆኚ ብዙ ችግር ይፈጥራል። ወጣቶችን ወደ አደንዛዥ እፅ የሚወስዷቸው ነገሮች ምንድናቸው? ብለን መጀመሪያ ከዛ መነሳት አለብን። ስለዚህ ተፈጥሯዊ ነገሮች አሉ፤ ወጣትነት ነገሮችን ለመመርመር ለማወቅ መፈለግ። ግን ዋናው ማህበራዊና ስነልቦናው ጉዳዮች ናቸው። ማህበራዊ ጉዳዩ ደግሞ ለምሳሌ ሥራ አጥነት የምንላቸው ተጋላጭነቱን ይጨምሩታል ማለት ነው። ስነልቦናዊ ነገሮች ደግሞ ብዙ ከማንነት ጋር የተያያዙ ናቸው። እነዚህ ሁሉ ይመጡና የወጣቶችን ተጋላጭነት ከፍ ያደርጉታል። በሁለተኛ ደረጃ በዓለም ላይ ባለፉት 20 እና 30 ዓመታት አደንዛዥ እፆች በተለያዩ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ስርዓት ቀውስን ለመግፋት ለመጠቀሚያነት እንደመሳሪያ መዋል ከጀመሩ ሰነባብተዋል።
በግሌ ለዚህ ጉዳይ ትኩረት አለመስጠታችን ይገርመኛል። በተለይ አሁን አሁን በሚድያ አደንዛዥ እፅ ሲባል እንሰማለን። በፖሊሲ ደረጃ ግን ከህፃናት ጀምረው ልጆች በትምህርት ቤት እንደ እድሜያቸው እየተማሩ መምጣት አለባቸው። ምክንያቱም በሚዲያ ብቻ ስላወራነው ልንከላከለው አንችልም። አሁንም ቢሆን በኛ ሀገር እየተሰራ ያለው ሥራ ከመከላከል የዘለለ አይደለም። ይህንን ስል ግለሰቦች የሉም ማለት አይደለም፤ ከችግሩ ስፋት አንፃር ግን የሚመጣጠን አይደለም። እዚያ ውስጥ የገቡ ሰዎች ደግሞ ጉዳት እንዳይደርስባቸው፤ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ካሉም እንዴት ያገግሙ ብሎ አቅዶ መስራት ይፈልጋል። ከዚያ ሁሉ በፊት ግን መከላከል ላይ ብናተኩር ብዙ ወጣቶችን መታደግ ይቻላል። ሌላው አውቀንም ሳናውቅም የምናበረታታበት ሁኔታ አለ።
አንቺ እንዳነሳሽው በተለያዩ አገራት ሆነ ብሎ አደንዛዥ እፅ አስጪሶ በጦርነት ውስጥ እንዲገቡ የሚደረግበት ሁኔታ እንዳለ እናውቃለን። በመሰረቱ ህፃን ልጅ መሳሪያ ይዞ እየሮጠ ለመሄድ በህፃን አእምሮ ብቻ መሆን የሚችል ነገር ነው ወይ የሚለው የሚያጠያይቀን ነገር ነው። ከዚህ አንፃር ይህ ጉዳይ እራሱን የቻለ በደንብ ማጣራት የሚፈልግ ነገር ሆኖ ሳለ፤ ስለዚህ አውቀን ልጆችን እንደዚህ እናስገባለን። ሳናውቅ ግን እናደርገዋለን፤ ይህም ማለት ለምሳሌ ማታ ላይ አራት ኪሎ ብንመጣ መደዳውን ትልልቅ ሰዎች በሰፋ ሁኔታ ሲጠጡ ነው የምናየው። መልዕክቱ ምንድነው? በዚህ ጋር የሚያልፍ የዩንቨርሲቲ ተማሪ ገንዘብ የሌለው ወጣት ልጅ፤ ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ብዙ ብር አውጥተው የሚያደርጉትን ሲያይ ምን ትሆናለህ እያልን ነው? እነዚህ በጣም መሰረታዊ ነገሮች ናቸው። ድግስ ስንደግስ እንደ ትልቅ የሀብትም፤ የእውቀትም ደረጃ መስፈሪያ የሚሆነው ስንት አይነት፣ ምን ያህል መጠጥ ጠረጴዛችን ላይ አርገናል ብለን ነው። ይህንን ስናደርግ ልጆች አሉ ወጣቶች ምንድነው የሚማሩት? በተቃራኒው የሰለጠኑት አገራት መንገድ ላይ መጠጥ ይዞ መሄድ አይቻልም። ይህንን ያደረጉት ሳናውቅ የምናበረታታው በጣም ብዙ ነገር አለ። ስለዚህ ስለአደንዛዥ እፅ ስናስብ አውቀንም ሆነ ሳናውቅ እምናደርገው አለ። ግን ሳናውቅ የምናደርገው ብዙዎችን እያበረታታ እንዳይሆን የሚል ስጋት አለኝ። አደንዛዥ እፅ ሲባል አሁን ጦርነት ውስጥ ተጠቅመዋል፤ አልተጠቀሙም የሚለው ነገር ሲመጣ እንደገና ትኩረታችንን ይስባል እንጂ በሌላው ጊዜ የሆኑ መጥፎ ልጆች የሚያደርጉት መጥፎ ነገር አድርገን እንወስደዋለን። ማህበራዊ ቀውስ ሊያመጣ የሚችል መሆኑን ግን እንዘነጋለን።
አዲስ ዘመን፡– ለነበረን ቆይታ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልና በአንባቢዎቼ ስም አመሰግናለሁ።
ዶክተር ዳዊት፡– እኔም አመሰግናለሁ።
ቤዛ እሸቱ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 7/2013