አባታቸው አርሶ አደር ፀጋ ቱፋ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በያያ ጉለሌ ወረዳ በኖኖና ጮመሪ ቀበሌ ነዋሪዎች በትጉህ አርሶ አደርነታቸው ይታወቃሉ። በማሳቸው ከእህል ጀምሮ የማያመርቱት ምርት ዓይነት አልነበረም። በደን ልማት ሙያውም ተክነውበታል። ዛሬ እርሳቸው የወረሱት አልሚነትም የአባታቸው መለያ ነበር። አባታቸው ተሞክሯቸውን በወረዳው በማስፋትም አብዝተው ይጠቀሳሉ። በአካባቢው ከሰብል ልማት ጀምሮ በጥራጥሬው፣ በአትክልትና ፍራፍሬው፣ በከብትና ዓሣ እርባታ፣ እንዲሁም በንብ ማነብ ይታወቃሉ።
ሴት አርሶ አደር ብዙ ፀጋ የአባታቸውን ተሞክሮ ወርሰው ስርዓተ-ምግብ ተኮር ግብርና ልማትን በጓሮ በመተግበር በአባታቸው እግር ተተክተዋል። በሩብ ሄክታር መሬት ላይ ጓሯቸው ሁሉንም የግብርና ዓይነቶች በመተግበር ለአካባቢው አርአያ ሆነዋል። በሁለት ሺ ብር የጀመሩት ልማት በሦስት ዓመት ውስጥ ካፈሩት 10 ከብቶች፣ 13 በጎች፣ አንድ አህያ እና የማይንቀሳቀስ ንብረታቸው ውጪ በጥሬው 200 ሺህ ብር መቆጠብ በመቻላቸው የዋንጫና ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል።
የቀለም ትምህርት ቀስመው ፊደል ለመቁጠር ባይታደሉም ተፈጥሮ ብልሃትን ችራቸዋለች። የተነገራቸውን አይረሱም፤ ያዩትን በፍጥነት ይተገብራሉ። ሴትነታቸውም ሆነ ወደ ጎልማሳነት እየተሻገረ ያለው ዕድሜያቸው አያሳሳቸውም። ጊዚያቸውን በዋዛ ፈዛዛ አያሳልፉም። ከ24 ሰዓታቱ የአንድ ቀን ውሏቸው አብዛኛውን የሚያሳልፉት በሥራ ነው። በተለይ በጋ ላይ የሦስተኛ ክፍል ተማሪ ወንድ ልጃቸውና የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ሴት ልጆቻቸውን ስንቅ ቋጥረው ወደ ትምህርት ቤት መሸኘት የአርሶ አደር ብዙ ቀዳሚ ተግባራቸው ነው። በተለይ ትልቁ ልጃቸው ዘግይቶ ትምህርት ቤት በመግባቱ ቢቆጩም፤ ሴት ልጃቸው ዕድሜዋ ለትምህርት ከመድረሱ ፈጥነው በማስገባታቸው ደስ እየተሰኙ ፊታቸውን ወደ ዕለት ሥራቸው ያዞራሉ።
ከቤታቸው ጀምሮ ያለው የግቢያቸው አጥር ንጹህ ነው።አትክልቱ ይኮተኮታል፣ አረሙ ይነቀላል፣ ኮምፖስቱ (የተፈጥሮ ማዳበሪያው) ይዘጋጃል። ዘር ከመዝራታቸው በፊት በሬ ጠምደውና ደጋግመው ማሳ የሚያርሱበትም ጊዜ ቀላል አይደለም። ብዙ ሥራዎችን በአንድ ጊዜና በፍጥነት የማከናወን ተሰጥኦ አላቸው። እንጀራ እየጋገሩ ወጥ ይሰራሉ፤ ልብስ ያጥቡና ቤት ያፀዳሉ፤ ፈትል ይፈትሉና ዳንቴል ይሰራሉ። ተፈጥሮ በቸረቻቸው ብልሃት ከተማረው በላይ ማሰብ፣ መሥራትና በተሻለ ሁኔታ መኖር መቻላቸውን በአንደበታቸው ይናገራሉ።
ከአባታቸው በወረሱት ልምድ ጓሯቸውን ማልማት የዕለት ተዕለት ሥራቸው ነው። ልማቱን ለአየር ብክለትና ለአፈር መሸርሸር ከሚያጋልጠው ዛፍ ተከላ ጀምረዋል። ዛፉም እግረ መንገዱን ለጥላና ለማገዶነት አገልግሏቸዋል። የጊቢያቸው ዙሪያ በቆርቆሮ አጥር ቢከለልም ግራር፤ ወይራ፣ ቅንጭብ፣ ለከብት መኖነት የሚያገለግሉትን ጨምሮ ረጃጅም ቁመት ባላቸው በሀገር በቀል ዛፎችም የተከበበ ነው። በከተማ ካላቸው የሚያከራዩት ቤት ባሻገር መኖሪያ ቤታቸው አሰራሩ ከአዲስ አበባ ከተማ 126 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ ገጠር ቀበሌ ሳይሆን መሀል ከተማ የተገነባ የሚመስል እጅግ ዘመናዊና ውብ ነው።
ቀበሌያቸው የ24 ሰዓት የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ መሆኑ ደግሞ ለቤቱ የሚመጥን ዘመናዊ የቤት ዕቃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። በተለይ ከተንቀሳቃሽ የእጅ ስልካቸው በተጨማሪ የገበያ መረጃ የሚያገኙባቸውና በእረፍት ሰዓታቸው ከነልጆቻቸው በሙዚቃ፣ በተለያዩ ፊልሞችና ድራማዎች ዘና እያሉ በሚያሳልፉባቸው የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ተሟልተዋል። ወደ ጊቢ ከመዘለቁ በፊት ዓይንን ወርወር ሲያደርጉ ገና ጣራ ላይ የሚታየው ዲሽ ዕቃዎቹ ለዚህ ተግባር መዋላቸውን ያረጋግጣል። አርሶ አደሯ ደጋግመው እንደሚናገሩት ይህ ሁሉ ተግተው የልማት ሥራ በመስራታቸው የተገኘ ሲሳይ ነው።
ሲሳዩን ካስገኙት ከመኖሪያ ቤታቸው በስተጓሮ የሚለማው የቀይና ነጭ ሽንኩርት ተክል በብዛት ይገኝበታል። ጥቅል ጎመን፣ የሀበሻ ጎመን፣ ቀይ ስር፣ ድንች፣ ካሮት፣ ቃሪያ በርበሬ፣ ጌሾ ከዚሁ ጋር ተሰድረው ይስተዋላሉ። ጤና አዳሙ፣ በሶብላው፣ የጥብስ ቅጠሉ (አዝመሪኖ) እና በቫይታሚን የበለፀገ ድንች ስኳር አለ። ግቢያቸው ባይበዙም ለቤት ውስጥ ፍጆታ በመዋል በየዕለቱ ስድስቱን የምግብ ዓይነቶችን ያሟላ ‹‹ገበታ አደምቅበታለሁ›› በሚሏቸው በፓፓያና አቡካዶ ታጅቧል። ውበቱ ውጡ ውጡ ከማይለውና አልባብ፤ አልባብ ከሚሸተው ከዚሁ ፀአዳ ግቢያቸው ውስጥ የአሣ እርባታም ያከናውናሉ። የአሣ ኩሬውን በአቅራቢያቸው ከሚገኘው ጮመሪ ከተሰኘው ወንዝ ውሀ ጠልፈው ወደ ጊቢያቸው በማስገባት ነው። ውሃው ጥሩና ንፁህ ሲሆን ጥራቱን የበለጠ ለማጠናከር በሚያስችል ኬሚካልም ታክሟል። በኩሬው ላይ አሣው በቀላሉ የዶሮ ኩሱን እንዲመገብ በማስቻልም የዶሮ ቤት ገንብተዋል። በዶሮ ኩስና በዓሳ እዳሪ ንጥረ ነገር የበለፀገውን የኩሬ ውሃም ለአትክልቶችና ፍራፍሬዎች ልማት ይውላል። የወተት ላምና ለፍጆታ የሚውል ዶሮ በማርባት እንቁላልም ያገኛሉ። በግቢያቸው ከሚገኝ አትክልትና ፍራፍሬ ባሻገር መኖሪያ ቤታቸውን ለማስዋብና ለማድመቅ የበቀሉትን የሚያማምሩ ጽጌሬዳ አበቦች ቀስመው ማር የሚያመርቱ ንቦችን በ15 ዘመናዊ ቀፎዎች በመታገዝ ያነባሉ።
የአርሶ አደር ብዙ ትልቁ የገቢ ምንጭ አትክልት ቢሆንም ጤፍም ያለማሉ። ገቢም ያገኙበታል። በዘንድሮ የመኽር ምርት ዘመንም ዩሪያና ዳፕን ጨምሮ እራሳቸው ያዘጋጁትን የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) በመጠቀም ማሳቸውን ደጋግመው አርሰው በቅርቡ በጤፍ ሸፍነውታል። ከዚሁ ጎን ያለው በቆሎ እሸት እየደረሰ ነው። እያንዳንዱ ውጤት የራሳቸው ትጋትና ጥንካሬ መሆኑን መካድ እንደማይቻልም በራስ በመተማመን ይናገራሉ። የቀበሌው የኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ድጋፍ እንዳለበትም ይጠቁማሉ።
ልማቱን የሚያከናውኑበት ማሳቸው በተፈጥሮው ለም ቢሆንም የሰብል ልማቱ ባለሙያ በሰብል ልማት፣ የእንስሳቱ ባለሙያ፣ በእንስሳት ልማቱ፣ የተፈጥሮ ሀብቱ ባለሙያ በተፈጥሮ ሀብቱ የሚሰጧቸው ምክር የበለጠ ውጤታማ እንዳደረጋቸው ይጠቁማሉ። በመስመር ከሚጠቀሙት ከጤፍ ዘር አዘራር ጀምሮ ኮምፖስት ዝግጅቱንና ኩትኳቶውን የሚያከናውኑት ከነዚሁ ባለሙያዎች ባገኙት ትምህርት ታግዘው መሆኑንም አርሶ አደር ብዙ አስረድተውናል።
የፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ፤ እንዲሁም መፀዳጃ በዘመናዊ መልኩ ገንብተው እንዲጠቀሙ ከማድረግ ጀምሮ፤ አራርቆ ለመውለድና የአመጋገብ ስርዓታቸውን በተመጣጠነ ምግብና በቫይታሚን የበለፀገ ለማድረግ በአካባቢው ከተመደቡ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ትምህርት ማግኘታቸውንም አጫውተውናል። በዚህም የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ጤና መጠበቅ፤ የአኗኗር ዘይቢያቸውንም ማዘመን ችለዋል። ማንበብና መፃፍ የሚያስችል ትምህርት ባያገኙም የሚያመርቷቸውን ምርቶች ለገበያ ከማቅረብ ጋር ተያይዞ በተለያየ መንገድ ትምህርት ያገኛሉ። መሸጫ ዋጋን በእጅ ስልካቸው፤ በሬዲዮና ቴሌቪዥን ያገኛሉ። በተለይ በእጅ ስልካቸው መረጃ ለማግኘት የሚያስችላቸውን ዕውቀትና ቁጥሮችን መለየት ትንሿ ልጃቸው አስተምራቸዋለች። ምርታቸውን ለገበያ በሚያቀርቡበት ጊዜም ከሸማች ጋር የሚገበያዩት በአእምሯቸው በማሰብ (በማስላት) ነው።
በዚህ መንገድ በሳምንት ቅዳሜ፣ ማክሰኞና ሐሙስ 10 ኪሎ ሜትር ተጉዘው በሚገኙት የገበያ ቦታዎች ምርታቸውን ያቀርባሉ። ጤፍን ጨምሮ አትክልት፤ በተለይም ሽንኩርት በስፋት ይሸጣሉ። ዓሣም በፍሬ በመቸርቸር ጭምር የሚያቀርቡ ሲሆን የአንዱ ዋጋም 40 ብር ይደርሳል። በዚህ ዋጋ በአንድ ቀን ገበያ ውሎ ከ40 እስከ መቶ ዓሣ የሚሸጡበት ጊዜ አለ።ዓሣው በገበያ እጅግ ተፈላጊ በመሆኑ የሚሸጠው ፈጥኖ ነው። ዓሣና አትክልትን በአካባቢያቸው ላሉ አንዳንድ ባለ ሆቴሎችም ያቀርባሉ። ለአብነትም በላይ የተሰኘው ሆቴል ይጠቀሳል። ማር፣ እንቁላል ዶሮና ሌሎች ምርቶችንም ለገበያ ያቀርባሉ። ዳጎስ ያለ ገቢም ያገኛሉ። ወርሃዊ ገቢያቸው እንዳይነጥፍ ተከታታይነት ያለው ምርት የሚያመርቱ መሆኑንም አጫውተውናል።
አርሶ አደር ብዙ ደጃቸውም እጃቸውም ሙሉ ሲሆን ምርታቸውን ወደ ገበያ የሚያጓጉዙበት አንድ አይሱዙ መኪናም አላቸው። በመኪናው ለገበያ የሚቀርበውን ምርት አውራጅና ጫኝ ሆነው የሚሰሩበትም ጊዜ ቀላል አይደለም። በአጠቃላይ አርሶ አደሯ ለአካባቢው ነዋሪዎች አርአያ መሆን ችለዋል።
ሴት አርሶ አደር ጊዛይ ኩምሳ አርሶ አደር ብዙን አርአያ አድርገው የእርሻ ሥራቸውን ከሚያከናውኑ የአካባቢው ነዋሪ አርሶ አደሮች አንዷ ናቸው። ‹‹ግቢዋም ሆነ ማሣዋ ለእኛ ሰርቶ ማሳያ ተሞክሮ መቅሰሚያ ነው›› ሲሉም በፈገግታ ይገልፃሉ። ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ እሳቸው ከዚህ በቀሰሙት ልምድ በሰው ያሳርሱ የነበረውን ማሳቸውን እራሳቸው ወደ ማረስ መግባታቸውንም ይናገራሉ። ከእርሻ በተጨማሪ በጓሯቸው ባለው ባዶ ቦታ አትክልት ወደ ማልማትም ገብተዋል። አሁን ላይ ከዶሮ ጀምሮ እንስሳት ወደ ማርባትም እየተሸጋገሩ ይገኛሉ። በሥራው አርሶ አደሯ ከራሳቸው አልፈው ተርፈው እሳቸውንም በጉልበትም፤ በምክርም እንደሚያግዟቸው ጠቅሰው ምርታቸውን ወደ ገበያ ለማውጣትም መኪናቸውን እንደሚጠቀሙ አጫውተውናል።
አርሶ አደር ሀብታሙ ግርማም እንዲሁ የአርሶ አደር ብዙ ጎረቤት ናቸው። ‹‹ብዙ ለሴቶች ብቻ ሳይሆን ለእኛም ለአካባቢው ወንድ አርሶ አደሮች አርአያችን ናት›› ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። በአካባቢው በመኸር የምርት ዘመን ጤፍ ብቻ ያመርቱ እንደነበር ያስታውሳሉ።ገቢያቸውም በዓመት አንድ ጊዜ በሚያመርቱት ጤፍ የተወሰነ ነበር።በመሆኑም ከነቤተሰባቸው ዓመቱን የሚዘልቁበት ገንዘብ እያጠራቸው ሲቸገሩ ኖረዋል። ለዘር እንኳን የሚሆን ገንዘብ አጥተው ያውቃሉ። አሁን ግን ከቀለብ አልፈው ለገበያ እያቀረቡ ይገኛሉ። ከአርሶ አደር ብዙ ጋር የቅርብ ጎረቤታሞች በመሆናቸው በቡናውም፤ በዓውድ ዓመቱም ሲገናኙ ተጨማሪ የልማት ሥራዎች እንዲሰሩ ይጎተጉቷቸው ነበር። ሆኖም ‹‹በእጅ ያለ ወርቅ አያደምቅ›› እንዲሉት ተረት ሆኖባቸው ምክራቸውን አልተቀበሉትም። ለውጣቸውን እያዩ እንኳን ስቀው ያሳልፉታል።
የልማት ሠራተኞችንም ምክር ባለመስማት የእርሻና ዘር ወቅት እስኪደርስ ማሳዬ ይተንፍስ በማለት በዘመድ ጥየቃና ወዲያ ወዲህ በማለት ጊዚያቸውን ሲያባክኑ ኖረዋል። የግብርና ልማት ባለሙያዎችና አመራሮች የአርሶ አደሯን ማሳ ለቀበሌውና ለወረዳው አርሶ አደሮች ተሞክሮ መቅሰሚያ አድርገውት ሲያዩ እሳቸውም ባለቤታቸውም መንፈሳዊ ቅናት አደረባቸውና ተነሳሱ። ዓመቱን ሙሉ ገቢ በሚያስገኙ የልማት ሥራዎችም መሳተፍ ጀመሩ። ሽንኩርት አትክልትና ፍራፍሬን በማልማት ወደ ወተት ላም እርባታ ተሸጋገሩ። እንደ አርሶ አደር ብዙም ወቅቱን ጠብቀው በበልግ እርሻም ይሳተፋሉ። አሁን ላይ ከበልግ እርሻ አንስተው የመኸር እርሻ ሥራውን እያከናወኑ ይገኛሉ። በዓመት ውስጥ ሁለቴና ሦስት ጊዜ ያመርታሉ። ሁሉንም ምርቶቻቸውን ገበያ አውጥተው በመሸጣቸው የነበረባቸውን የገንዘብ ችግር መቅረፍና ዓመት ከዓመት የሚዘልቅም ቋሚ ገቢ ማግኘት ችለዋል።
ወጣት ደበሌ ኢቲቻ እሳቸው ቁጭ ማለት ስለማይወዱ ገበያ የሚቀርበውን ዕቃ ከመጫንና ከማውረድ ጀምሮ በየትኛውም ሥራ ቢሳተፉም እሱን ጨምሮ ለብዙ የአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ይናገራል። በተለይ የሰብሉም ሆነ የአትክልቱ ምርት በሚሰበሰብበት ወቅት ሥራው አያሌዎችን ያሳትፋል። እሱ የራሱ መሬትና ጥሪት ስለሌለው እራሱን ችሎ በእንዲህ ዓይነቱ ሥራ መሳተፍ አይችልም። ሆኖም አርሶ አደሯ በከፈቱት የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እየሆነ ይገኛል። ከቤተሰብ ጥገኝነት ተላቆም ራሱን ማስተዳደር ችሏል። በቅርቡ ከሚያገኘው ገቢ ከፍሎ በቆጠበው በአርሶ አደር ብዙ አበረታችነት በራሱ የልማት ሥራ ለመሰማራትም መንገድ ላይ ነው።
አርሶ አደር አጥናፉ ፀጋ የአርሶ አደር ብዙ ወንድም ናቸው። አርሶ አደሯ እየተሳተፉበት ያለው ሁለገብ የልማት ሥራ እንቅስቃሴ ከአባታቸው የወረሱት እንደሆነ ይናገራሉ። የአባታቸው ተሞክሮ በእህታቸው አማካኝነት ሰፍቶ ተወልደው ላደጉበት ለኖኖ ቀበሌና ለጉለሌ ወረዳ ሲተላለፍ በማየታቸው እጅግ ደስተኛ ናቸው። እህታቸው ዘመናዊ ትምህርት ባይማሩም በተፈጥሮ ብልህና ጠንካራ በመሆናቸው በልማቱ ከአባታቸው በበለጠ ስኬታማ መሆን መቻላቸውንም ይጠቅሳሉ። የተሻለ ኑሮ ከመኖር ባሻገር፤ ተከታታይነት ያለው ቋሚ ገቢ ማግኘትና ለክፉ ቀን የሚሆን ጥሪት መቋጠርም አስችሏቸዋል። ይህም በተፈጥሮ ከተቸራቸው ሩህሩህነት ጋር ተዳምሮ ዘርም ሆነ ገንዘብ የተቸገረን የአካባቢያቸውን አርሶ አደር እንዲረዱ አግዟቸዋል።
በእርግጥ ለሴት ልጆች እንዲህ ያለውን የልማት ሥራ በቤተሰብ ልምድ ለስኬት ማብቃት ከብዙ አቅጣጫ ሲመዘን ይከብዳል። በተለይ የሴትነት ኃላፊነት ሲደመርበት ጫናው ይበዛል። የሁለት ልጆች እናት ለሆኑት አርሶ አደር ብዙ ደግሞ እናትነት ሲታከልበት ካቀዱት ከማሰናከል አይመለስም። ሆኖም አርሶ አደሯ ሁሉንም አሸንፈው መውጣት ችለዋል። አርአያነታቸው የጎላ በመሆኑ ከዚህም ባለፈ ሊሰፋና ሊበረታታ ይገባል በማለት አበቃን።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 6/2013