ቂም ይዞ ጸሎት፤ ሳል ይዞ ስርቆት እንዲሉ፤ ሱዳን ማንነቷን ወደኋላ ደብቃ የኢፌዴሪ መንግስትን በሽብርተኛነት ከተፈረጀው ህወሓት ጋር ላደራደር ማለቷ ከሰሞኑ ተሰምቷል።ሱዳን ኢትዮጵያ የተዳከመች በመሰላት ጊዜ አድብታና አድፍጣ የኢትዮጵያን መሬት ለመውረር ጉርብትናውም ሆነ የኢትዮጵያ ውለታ ውል አላላትም።ይህ ሳያሳፍራት ደግሞ የኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እኩይ ተግባሩን ከግምት ውስጥ በማስገባት ጁንታውን በሽብርተኝነት መፈረጁ የአደባባይ ምስጢር ሆኖ ሳለ ላሸማግል በሚል ተፍ ተፍ ለማለት ማስቧ በእጅጉም አስደምሟል።ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ አዲስ ዘመን በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲ መምህር ከሆኑት ከአቶ እንዳለ ንጉሴ ጋር ቆይታ አድርጎ ያገኘውን መረጃ እንደሚከተለው አሰናድቶታል።መልካም ንባብ ይሁንልዎ።
አዲስ ዘመን፡- በአሁን ወቅት ሽብርተኛው ጁንታን እንደፈለገው የሚያሽከረክረው የምዕራቡ ዓለምና አሜሪካ ስለመሆናቸው በግልጽ እየታየ ያለ ነው፤ ኢትዮጵያን በዚህ ልክ ለመረበሽ ምክንያታቸው ምንድን ነው?
አቶ እንዳለ፡- ዋናው ከጁንታው ጋር ተያይዞ እና ከምዕራባውያን ጋር ያለው ግንኙነት ምንድን ነው ቢባል ኢትዮጵያ በነጻነት የኖረች እና ለሌሎችም ምሳሌ የሆነች አገር መሆኗ ነው።ይህን ምሳሌነቷን በቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ለሚመራው ዓለም በተለይ ለምዕራቡ ዓለም የሚዋጥለት አይደለም።ይህን ለማጥፋትና ለማደብዘዝ ባለፉት 40 ዓመታት ብዙ ተሰርቷል።ይህ ስራ በተለያየ መልኩ ሊመጣ ይችላል። ለምሳሌ የተማሪ ንቅናቄ በይው ሌላም ልትይ ትችያለሽ፤ በብዙ መንገድ የመጣ ነው፤ ኢትዮጵያን አዳክሞ እና ከፋፍሎ ሁለተኛ እንዳትነሳና የዓለም ምልክት እንዳትሆን የማድረግ ፖሊሲ ተነድፎ ተግባራዊ ሲደረግ ነው የቆየው።
ለዚህ ደግሞ ሁለት አካላት ኃላፊነት ወስደው ነበር። አንዷ ግብጽ ነች፤ አሁንም ድረስ የሚመራው በቅኝ ግዛት አፈጻጸም ነው።እንደመንግስት ሲታሰብ ግብጻውያን ሉዓላዊነታቸውን አላረጋገጡም።የዴሞክራሲያቸው ባለቤት አይደሉም።የብሄራዊ ጥቅማቸውም ባለቤት አይደሉም።አሁንም ድረስ የግብጽ መንግስት በቀይ ባህርና በአረቡ ዓለም የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ወኪል ነው።ይከፋፍላል፤ ያጣላል፤ ያገዳድላል።ለዚህ ስራው ደግሞ ገንዘብ ከምዕራባውያኑ ያገኛል።
በኢትዮጵያ አካባቢ ደግሞ ሲመጣ ለዚህ ወኪል ሆኖ እንዲያገለግል የተቋቋመው ይህ መንፈስ ልጅ የሆነው የጁንታው ቡድን ነው።ጁንታ የመንፈስ ልጃቸው ሲሆን፣ ራሳቸው ወልደውና በመንፈስ አሳድገው፤ ገንዘብ ሰጥተውና አቅጣጫ ሰጥተው ኢትዮጵያ ላይ የጫኑት ቡድን ነው።በጤናማ አካሄድ ቢሆን ይህ ቡድን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመጣበት ምንም እድል የለውም።ምክንያቱም ይህ ሁኔታ ኢትዮጵያን አይመጥንምና ነው።
ባለፉት አምስትና ስድስት ሺ ዓመታት ያሉ ኢትዮጵያውያን በሉዓላዊነታቸው ላይ አይደራደሩም። ብዝሃነትን በማስተናገድ ረገድ ወደር የላቸውም። አድዋን የመሰለ ድል ያስመዘገቡ፣ በዚያድባሬም ሆነ በሁለተኛው ዓለም ጦርነት፣ አሁንም ቢሆን ጁንታውን ጭምር ያሸነፈ የብዝሃ አንድነት ያላት አገር ያለች ናት ኢትዮጵያ።ስለዚህ አሁን ይህንን ጉዳይ እንዲያፈርስና እንዲከፋፍል በጣም ዝቅተኛ በሆነው በዘረኝነት መንፈስ ኢትዮጵያውያን እንዲሰክሩና እርስ በእርሳቸው እንዲገዳደሉ አቅጣጫና ገንዘብ እየሰጠ የነበረ ይኸው ቡድን።በጥቅሉ የእነርሱ የመንፈስ ልጃቸው ነው ማለት ነው የሚቻለው። ስለዚህ ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያውያን የሚመጥን አልነበረምና ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከዳር ታግለው ይህን ጁንታ በ15 ቀን ግብዓተ መሬቱን አረጋገጡለት።አሸባሪው ህወሓት የፖለቲካ ሞቱ ተረጋግጧል።
አሁን መጀመሪያ ምዕራባውያኑ ገንዘብ ሰጥተነዋል። መሳሪያ ሰጥተነዋል።የመረጃም ድጋፍ እያደረግንለት ነው።ስለዚህ የሚገዳደረው አካል አይኑር ብለው የኢትዮጵያውያንን ኢትዮጵያዊነት አያውቁምና ሲሸነፍ ደነገጡ። በአሁን ወቅት መነሳት የማይቻለውንና ድጋሚ ሊመጣ የማይችለውን ቡድን እንደለመዱትና ብዙ አገር ላይ እንዳደረጉት ሁሉ ድጋሚ በመንፈስ ሊያመጡት ፈለጉ። በእርዳታ ሰበብና በፕሮፓጋዳ ሰበብ እሱን መልሰው ማምጣት ነው ጽኑ ፍላጎታቸው።
በአሁን ወቅት እንዲህ አይነት ነገር ኢትዮጵያዊያን ማስተናገድ አይችሉም።የለውጡ ዋናው ምክንያት የሉዓላዊነትና የአንድነት ጉዳይ ነው።ለለውጡም ዋጋ የተከፈለበት ምክንያት አብሮ የመኖር ጉዳይ ነው።ስለዚህ እነርሱ እያደረጉት ያለው እንቅስቃሴ ከኢትዮጵያውያን ፍላጎት በተጻራሪ የሆነውን ጉዳይ ነው።
ይሁንና ለእነርሱ አስተሳሰብና ፍላጎት ልክ ናቸው።የምዕራባውያኑ ሚዲያ በራሱ የተቋቋመው ይህን የቅኝ ግዛትን አስተሳሰብ ለማስቀጠልና ከፍ ለማድረግ ነው እንጂ እንደሚናገሩት የጋዜጠኝነቱን መርሆ ተከትለው የሚሰሩ አይደለም።ሁሉ ውሸት ነው ማለት ያስደፍራል። ዞሮ ዞሮ በሳይንሱ ፕሮፓጋንዳ የምታቋቁሚው ሌላ አገር ላይ ነው።የሌላውን አገር ሐሳብ ለመስለብ ነው የምትሰራው።ስለዚህ ቢቢሲም ሆነ ሌላው የሚሰራው የፕሮፓጋንዳን ስራ ነው።የአሜሪካ ድምጽም የፕሮፓጋዳ ማሸን ነው። የጀርመኑም ቢሆን እንዲሁ ነው።ለአገራቸው ጉዳይ ልክ ናቸው። የሚሰሩት የአገራቸውን ብሄራዊ ጥቅም ከፍ ለማድረግ ነው፤ እኛም እንዲሁ ነው ለጥቅማችን የሰራነው። ስለዚህ ፕሮፓጋንዳው ከሽፎ ቡድኑም ተሸነፈ።
በመሆኑም በእርዳታ ሰበብ፤ ያውም ሌላው ዘንድ የማይሰጡትን እርዳታ ማለት ነው፤ ለምሳሌ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው እንደ ሊቢያም ሆነ ሶሪያ ወይም ሌላ ቦታ እያለ፤ ነገር ግን ወደእዛ ስፍራ አልሄዱም።እዚህ ግን ምዕራባውያውኑ የመንፈስ ልጃቸው ድጋሚ እድል አግኝቶ ከዳነ በሚል እንክብካቤ ሊያደርጉለት ፈልገዋል።እርዳታ እንሰጣለን ብለው ከመጡ በኋላ እርዳታው እንዲደርስ ያደረጉት እንኳ እዛ ክልል ላለውና ለተጎዳው የህብረተሰብ ክፍል አይደለም።ለጁንታው ቡድን ነው እስከመጨረሻው ድረስ ሄደው የቴክኒክ ድጋፍና የእርዳታው አቅርቦት እንዲሰጠው ያደረጉት።በዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ በእርዳታ የሚዋጋ ቡድን እንደገና እንዲያንሰራራ ለማድረግ የሞከሩት።የት አገር ነው የእርዳታ ስንዴ እየተቀበለ ውጊያ የሚያካሂደው፤ ፕሮፓጋንዳ የሚያካሂደው፤ ይህን በኢትዮጵያ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ሲያደርጉት ነው የተስተዋለው።
ስለዚህ እያደረጉት ያለው ድጋፍ ለሰብዓዊነት አይደለም። ለሰብዓዊነት ቢሆን ኖሮ ይህ ቡድን እኮ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል መፈናቀልን አስከትሏል። በዚህም ትልቅ ጉዳት አስከትሏል። ይህ ሁሉ መከራና ፈተና ሲገጥምና ቡድኑ እንዲያ ሲያደርግ እነርሱ በወቅቱ የት ነበሩ።አሁንስ ቢሆን መቼ ነው እኩል የሰጡት።አማራ ክልል ብቻ ከ200 ሺህ ዜጋ በላይ ተፈናቅሏል። በአፋርም እንዲሁ ነው።ኦሮሚያ ውስጥ ደግሞ ከሚሊዮን በላይ ዜጋ ሲፈናቀል እነርሱ ከወደዬት ነበሩ።
ስለሆነም አሁን ይህን የሚያደርጉት የጁንታው ቡድን ይድን ይሆንን በሚል በጣም የደነዘዘ ሐሳብ ነው። ምክንያቱም ልክ እንደ ጁንታው አይነት ቡድን ሰዎች እንዲገዳደሉ የሚያደርግ እርስ በእርስ እንዲተራረዱ የሚያደርግ አይነት ቡድን እነርሱ ከየት ያመጣሉ፤ ማምጣት አይችሉም። ስለዚህ በዛ ምክንያት እጅግ ተናደዋል። ይህ አንዱ የተበሳጩበት ጉዳይ ነው።ሁለተኛው በአሳፋሪ ሁኔታ የተበሳጩበት ጉዳይ ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ እንድትሞላ ብሎም ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ እንድታካሄድ አልፈለጉም ነበር።
ነገር ግን ይህንንም ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌትም ሆነ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያውያን ናቸውና በተግባር አሳዩአቸው። ይህ እንዲህ ከሆነ ደግሞ ነገ ምን ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ይከብዳቸዋል። በዚህ ልክና እንዲህ የተቋቋመ መንግስት ብሄራዊ ጥቅሙን ለማስጠበቅ የልብ የልብ አለውና ይህን ደግሞ እነርሱ ማየትም መስማትም አይፈልጉም።
ደካማ እና ሽባ መንግስት፤ እንዲሁም ሲጠሩት አቤት እያለ የሚሮጥ መንግስት ነው የሚፈልጉት።ያውም ደግሞ ምንም አይነት የኢትዮጵያዊነት ስሜት የሌለውን መንግስት ነው የሚሹት። ይሁንና እንደእርሱ አይነት መንግስት ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ስለሌለ ጫና ለማድረግ ሲሞክሩ ማየትም መስማት እምብዛም አይገርምም።
ምክንያቱም አንደኛ የዓለም ጂኦፖለቲክስ አሁን ተቀይሯል።ስለሆነም ኢትዮጵያ ብዙ ምርጫ አላት።ስለዚህ አሁን እነርሱ ፖሊሲያቸውን ማስተካከል ሲገባቸው በኢትዮጵያ ወጪ ያንን ማድረግ ይፈልጋሉ።ኢትዮጵያ ከዚህኛው መንግስት ወይም ከዚያኛው መንግስት መሆን አለባት ማለት በአሁን ወቅት አይመለከታቸውም።እንዲያውም ኢትዮጵያ በነጻነት የኖረች አገር በመሆኗ ከሁሉም ጋር ነው መስራት ያለባት።በአሁን ወቅት ወደቅኝ አገዛዝ አስተሳሰብ ሊመሯት አይገባም።እነርሱ አሁን የጠሉት ይህንን ነው።በመሆኑም ማስተካከል ያለባቸው ራሳቸውን ነው።
ሌላው የራሳቸው የውስጥ ችግር ነው።በአሁን ሰዓት ምዕራባውያኑ ውስጣቸው ላይ ብዙ ችግር አለ፤ የኢኮኖሚ ችግር፣ የመከፋፈል ችግር፣ ከዓለም ጋር መወዳደር ያለመቻልም ችግር አለባቸው።ይህ አይነት ችግር ስላለ አሁን እኛ ላይ ጫና ለማድረግ ቢሞክሩ አይገርምም፤ ይህን ሲያደርጉ ደግሞ የመጀመሪያቸውም አይደለም።ኢትዮጵያ በታሪኳ ጫናዎች ይገጥሟታል።በዓድዋ ጊዜ ችግር ገጥሟት ስታሸነፍ ግን በማግስቱ ነው የተፈራረሙት።በዚያድባሬም ቢሆን እንደዚያ ያደረጉት ወዲያኑ ነው።በሁለተኛው የዓለም ጦርነትም እንዲሁ ነው።
አሁንም ቢሆን እኛ የሚጠበቅብን የጁንታውንና የእነርሱን ሐሳብ ማሸነፍ ብቻ ነው።ስናሸንፍ የሚመጡት ወዲያኑ ነው።የቅኝ ግዛት አስተሳሰብን ስታሸንፊው ከአንቺ ጎን መጥተው ለጥ ሰጥ ብለው ይሰራሉ። ስለዚህ መንገዳገድ አያስፈልግም።በብዙ ፈብርከው ብዙ ማድረግ ይችላሉ፤ ነገር ግን ለእነርሱ የውሸት ፕሮፓጋንዳ እድል መስጠት በፍጹም አያስፈልግም።
በብዙ አገር ይህ አካሄዳቸው ታውቋል።ራሳቸው ፈጥረው ራሳቸው አደጋ የሚያደርሱበት ጊዜ ስላለ ነው።ስለዚህም እኔ ይህን ጫና አልለውም።ኢትዮጵያ
በትክከለኛ መንገድ መሄዷን ማረጋገጣቸው ነው እንጂ ኢትዮጵያ እንዳለፉት አርባ ዓመታት ብትደክም ኖሮ ስለኢትዮጵያም አያወሩም ነበር።እንዲያውም እርዳታው ይጨመር ነበር።ከዚህ ባሻገር ሌላ ሌላውም ነገር ይደርግልን ነበር።
አዲስ ዘመን፡- በአሁን ወቅት በትግራይ ክልል ድጋፍ በማድረጉ ረገድ በኢትዮጵያ በኩል የሚደረግ የምግብ እርዳታ እያለ በሱዳን በኩል ሌላ ኮሪደር ተከፍቶ ይድረስላቸው መባሉ ምንን ነው የሚያሳየው? ከቀናት በፊትም በኢትዮጵያ የተገኙት የእርዳታ ድርጅቱ ሃላፊ ሳማንታ ፓወር በቆይታቸው ከሐሳባቸው የተስተዋለውን ጉዳይ እንዴት አዩት?
አቶ እንዳለ፡- በነገራችን ላይ ኃላፊዋ ሳማንታ ፓወር ድጋፍ በሱዳን በኩል ይደረግ አላሉም።ነገር ግን ሐሳቡ አለ።ሳማንታ ፓወር በእርግጥም ይህንን ሊሉም አይችሉም።አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ይህ ቡድን ውስጥ ያለ ቡድን ነው።ውስጥ ላይ ማስተካከያ እየተደረገበት ያለ ቡድን ነው።ስለዚህ ይህ የኢትዮጵያ የሉዓላዊነት ጉዳይ ነው።
ሉዓላዊነት ማለት ደግሞ በውጭና በውስጥ ጉዳይ ላይ መወሰን ማለት ነው።እነሱን በውስጥ ጉዳያችን አያገባቸውም።ሳማንታ ፓወርም ቢሆኑ ከተሰጣቸው ስልጣን ውጪ ከዚህ ከጁንታው ቡድን ጋር ለመስራት የፈለጉ ናቸው።ከጁንታው ቡድን ጋርም ግንኙነት ያላቸው ስለሆኑ ማለት ነው።እርሳቸው የአንድ እርዳታ ድርጅት ኃላፊ ናቸው።የአንድ የእርዳታ ድርጅት ኃላፊ ከሆኑ ደግሞ ማውራት ያለባቸው ስለእርዳታ ድርጅታቸው ብቻ ነው መሆን የነበረበት።ስለጁንታው ቡድን ማውራት መብታቸው አይደለም፤ በዲፕሎማሲውም አካሄድ የሚፈቀድም አይደለም።አልፈው ቢያወሩም ውጤት የሚያመጡ አይደለም።ይህን አካሄዳቸውን በሌሎች አገሮች ስለለመዱ በኢትዮጵያ ላይ ያንን ማድረግ ግን አልቻሉም።በመሆኑም ነው ልካቸውን አውቀው የሄዱት ማለት ይቻላል።በዚህ ጉዳይ ማንም እድሉን አልሰጣቸውም።
ይህ እድል ስልተሰጣቸው እኛን በሱዳን ክፈቱ፤ ወይም ደግሞ በዚህኛው ክፈቱ የሚል ነገር ቢመጣ በኢትዮጵያ ጉዳይ ማንም አያገባውም።እስካሁን ድረስም አብዛኛውን እርዳታ የሚችለው የኢትዮጵያ መንግስት ነው።እነርሱ በትንሹ ሰጥተው ነው በብዙ የሚጮሁት።
በሌላ በኩል ደግሞ እነርሱ በነጻ የሚሰጡት እርዳታ የለም።በእያንዳንዷ በሚያወጡት ነገር መቀበል የሚፈልጉት በእጥፍ ነው።ስለዚህ እውነት እርዳታ የሚሰጡ ከሆነ መጥተው ከማዕከላዊ መንግስቱ ጋር ተነጋግረው ለሁሉም እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው አካላት መስጠት ነው።አይ ይህ አይሆንም የሚሉ ከሆነ ደግሞ ይዘው መሄድ ነው።
በእነርሱ እርዳታ ያደገ አገር የለም፤ ኢትዮጵያ ደግሞ እርዳታውን ማቅረብ አላቃታትም።እነርሱ በግድ መጥተን እንስጥ በማለታቸው ሰው ብዥታ ውስጥ እንዳይገባ እስኪ ይምጡና ይስጡ በሚል ነው የኢትዮጵያ እሽታ።እርዳታ ማቅረቡ ከኢትዮጵያ አቅምም ቁጥጥርም በላይ ሆኖ አይደለም።በዚህኛ ሰው ይግባ ወይም በዛኛው ይግባ በሚል የሚጠይቁበት ሳይንስም ሞራልም የለም።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ መንግስት በሽብርተኝነት ከተፈረጀው ጁንታ ጋር መንግስት ድርድር ያደርግ ዘንድ በሱዳን በኩል ጥያቄ ቀርቧል፤ አሜሪካም የዚህ ሐሳብ ደጋፊ ናት፤ ነገር ግን ሱዳን ይህንን ማሰቧ መሬታችንን ወራለችና ቂም ይዞ ጸሎት አይነት አይሆንባትም?
አቶ እንዳለ፡- በመጀመሪያ ደረጃ የውስጥ ጉዳይ ድርድር የሚያስፈልገው ነገር አይደለም።ህግ ነው የምታስከበሪው።ውስጥ ለውስጥ ትወያያለሽ።ከዚህ ውጭ ከዜጎችሽ ጋር ድርድር አይደለም የምታደርጊው።ከዜጎችሽ ጋር ውይይት ነው የምታደርጊው።ምን ይሻላል፤ እንዴትስ ይደረጋል የሚል ውይይት እንጂ ውስጥ ካለ ቡድን ጋር ሌላ አካል ገብቶ ላደራድር የሚልበት ምንም አይነት ሳይንሳዊ አካሄድም የለም።
ስለዚህ ምዕራባውያኑም ቢሆኑ በሌላ አገር መፈትፈት ስለለመዱ በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ መግባት ፈለጉ፤ ይህ ግን በተባበሩት መንግስታት ቻርተር ህግ የተከለከለ ነው።ሉዓላዊነት ማለት እኮ በውስጥ ጉዳይም ሆነ በውጭ ጉዳይ ጭምር የመወሰን ነጻነት ማለት ነው።በሌላ መልኩ የተባበሩት መንግስታት ሁለተኛው አንቀጽ የሚለው በአገሮች የውስጥ ጉዳይ መግባት ክልክል ነው ይላል።ይህ መርህ የማይከበር ከሆነ ደግሞ የተባበሩት መንግስታት ራሱ ይፈርሳል ማለት ነው።
ስለዚህ አሁን ሱዳን ለማወያየት የምትጠይቅበት ምንም ምክንያት የለም።መልስም የለም።ምንም አይነት ሞራልም የላትም።ሱዳን እንዲያውም ከቻለች ለሶስት ቦታ የተከፈለውን ማንነቷ ወደአንድ በማምጣት ራሷን አረጋግታ መንቀሳቀስ ነው የሚገባት።ለሱዳን በአሁኑ ሰዓት አንደኛ የሲቪሉ መንግስት አለ፤ ሁለተኛ ከወታደራዊ መንግስቱ የተገነጠለው ልዩ ኃይሉ አለ፤ ሶስተኛ ደግሞ ወታደራዊው ክንፍ አለ።ሱዳን በዚህ መልኩ ለሶስት ተከፍላ አንድ ጉዳይ እንኳ መናገር ያልቻለች አገር ናት።ብሄራዊ ጥቅሟን ማስከበር አልቻለችም።ይህን ጉዳዩዋን መሬት ለማስያዝ በሂደት ላይ ናት።
ከግብጽ ጋር የሄደና ያበረ አገር ሰላም አያገኝም።የመንንም፣ ሶሪያንም ሆነ ሊቢያን ማየት ይቻላል።በአንድ ወቅት ሶሪያና ግብጽ እኮ አንድ መንግስት ሁሉ መስርተው ነበር።ስለዚህ የሱዳን ችግር የራሷ የውስጥ ችግር ነው።እንኳን ለማወያየት አይደለም ራሷ እስከ ዛሬ ከነጻነቷ ማግስት ጀምሮ የተረጋጋ መንግስት መመስረት አልቻለችም።
ሌላው ደግሞ ይህ የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ነው፤ ማንም ሊያወያይ አያስፈልገውም።ላደራድር ብሎ ነገር የሚያስፈልግ አይደለም።የውስጥ ጉዳያችን ነው ትወያያለሽ፤ ህጋዊ የሆነ አካል ደግሞ መስመር ይይዛል።ህገ ወጥ እሆናለሁ ካለ ደግሞ ያው ነው።
ሱዳን ተልካ ነው።መከፋፈል ስራቸው ስለሆነ ይህን ይህን ጠይቂልን ብለው ነው የላኳት።እኛ ከሱዳን ጋር እንደመልካም ጎረቤት ተሳስበን መኖር እንፈልጋለን።ሱዳናውያኑ ወንድሞቻችን ናቸው።የሱዳን ህዝብ ከኢትዮጵያውያኑ ጋር እስካሁን ወዳጅ ነው።የሱዳን ህዝብ የሱዳን የተለያዩ ክንፎች የሚሰሩትን ስራ አይደግፈውም።ተቃውሞውንም ለመግለጽ በየጊዜው ሰልፍ እያካሄደ ነው።
ኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል ጁንታው ባደረገው ጥፋት ወደህግ ማስከበሩ ስራ ስትገባ ነው ሱዳን ደግሞ ድንበሩን መውረሩ የተሰማው።ይህ የሚያሳየው ምን ያህል በቅኝ ግዛት አስተሳሰብ እንደሚመሩ ነው።ሱዳን የኢጋድ ሊቀመንበር ሆና ሳለ ነው የኢትዮጵያን መሬት የወረረችውና ይህቺ አገር በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ገብታ ልታወያይ አትችልም።
ሱዳን፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ ባልተናነሰ እንደሚጠቅማት እያወቀች ነው በቅኝ ግዛት አስተሳሰብ የተመራችው።ወደግብጽ ስትመጪ ደግሞ አልሲሲ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር ሆነው የአፍሪካ ህብረት የእኛን ጉዳይ ማወያየት የለበትም፤ አቅምም የለውም እያሉ ፈረንጆቹ ዘንድ ሄጄ ካልወድኩ ነው ያሉት።ስለዚህ የእነዚህን አገሮች አካሄድ ጤነኛ ነው ብለን አንወስደውም።
ጤነኛው አካሄድ የኢትዮጵያ ጉዳይ የውስጥ ጉዳይዋ ነው፤ ስለዚህ በውስጥ ጉዳይዋ ማንም መግባት የለበትም።ራሷ ነች መፍታት ያለባትም፤ ለዚህ ደግሞ አቅሙም አላት።በአሁን ሰዓት ሱዳን፣ በኢትዮጵያ ያለውን አምባሳደር ጠርቼያለሁ ስትል ተደምጣለች።አምባሳደሩን የጠራችበት በሁለት ምክንያት ሊሆን ይችላል፤ አንደኛው ሱዳናውያን ለሶስት ስለተከፈሉ ይህ ተጠራ የተባለው በኢትዮጵያ የሱዳን አምባሳደር የትኛው ጎተራ ውስጥ እንዳለ የሚታወቅ ነገር የለምና ስለዚህ እሱን ለማጣራትና የውስጥ ጉዳያቸውን ለመፈተሸ ሊሆን ይችላል።
ሁለተኛው ደግሞ ፖሊሲዋን ለማስተካከል ሊሆን ይችላል።ምክንያቱም አሁን እየሄደችበት ያለው ፖሊሲ ትክክል አይደለም።ወይ ታባብሰዋለች፤ አሊያም ደግሞ የተሻለ ለመንደፍ ሊሆን ይችላል፡፤ ስለዚህ በእነዚህ ሁለት ምክንያት ነው ሊሆን የሚችለው፡፤ ከሁለቱ ውጪ እምብዛም ሊያፈነግጥም አይችልም።
እኛ ደግሞ በመልካም የምትመጣ ከሆነ እንቀበላታለን።በመጥፎ የምትንቀሳቀስ ከሆነ ደግሞ ከዚህ ቀደም ሱዳን መንግስት እንድትሆን ወዳጅነት አሳይተናል።ብሎም እንድትረጋጋም ጭምር አድርገናል።አይ እንዳሻኝ እሄዳለሁ የምትል ከሆነ እኛ በዚህ ሰዓት ብዙውን የቤት ስራችንን ጨርሰናል።የህዳሴ ግድባችንን ሞልተናል።ምርጫውንም በሰላም አካሂደናል።
ስለሆነም ሱዳን ከእንግዲህ በኋላ ከኢትዮጵያ ጋር ባትሆን የምትወድቀው ራሷ ነች።ከግብጽ ጋር ሄዶ ያለፈለት አገር የለም።ሱዳንም የበለጠ ነው የምትከፋፈለው።ስለዚህ ኢትዮጵያ እስካሁን በዲፕሎማሲው ረገድ ላጠፋችው ጥፋት በዲፕሎማሲ መንገድ እየጠበቀቻት ነው።ይህ ደግሞ ትልቅነት ነው።ባይሆነ ጥፋቷን ማስተካከል ነው እንጂ የሌለ አጀንዳ ፈጥራ ላወያይ ነው፤ ላደራድር ነው ማለቷ የማይመስል ነገር ነው።እሱ ውሸት ነው፤ ሌላው ቢቀር ማስመሰል እንኳን አልቻለበትም።ማወያየት የሚያስችላት አሳማኝ ምክንያት የላትም።በኢትዮጵያ መንግስት በኩል አይቻልም ከተባለች የሚያናድዳት ምንም ነገር መኖር አልነበረበትም።
በሌላ በኩል አስቀድሜ እንደጠቀስኩት ሱዳን በራሱ ወድቃ ሶስት ቦታ ተከፍላ እያለ ያልሆነ አጀንዳ ይዛ በየአገሩ መዞር የተወሰነ ቡድን ስለላኳት ነው።እዛና እዚህ መሮጥ ሱዳንን የበለጠ ገደል ውስጥ ነው የሚከታተሉት።ስለዚህ ኢትዮጵያውያን በዚህ ጉዳይ የሚያሰጋን አንዳች ነገር የለም።እኛ የያዝነው ትክክለኛውን መንገድ ነው።ያስቀደምነውም ዲፕሎማሲን ነው።
እንደተለመደው ባለፈው ሺህ ዓመታት እንዳደረግነውና የሱዳንን ህዝብ ስለምንፈልገው አካሄዳችን ዲፕሎማሲያዊ ነው።ሱዳንም ብትሆን ከኢትዮጵያ ጋር መስራት ነው የሚያዋጣትም የሚጠቅማትም። ባለመስራቷ ኢትዮጵያ ባትጎዳትም እንኳ ራሷ ትደክማለች።ምክንያቱም አሁን የኢትዮጵያን ድጋፍ የምትፈልግበት ጊዜ ነው።ግብጾች በባህሪያቸው የመደገፍ ባህል የላቸውም።ባህሪያቸው የመከፋፈልና የማዳከም ነው።ግብጾች እንኳን ለሌላው አገር ቀርቶ በራሳቸውም ላይ የሚያደርጉት ይህንኑ ልምዳቸውን ነው።
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ ወደአገራችን ብቅ ያሉት የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት ሃላፊ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይን ማግኘት አለመቻላቸው የዚህን ያህል አነጋጋሪ መሆን ነበረበት?
አቶ እንዳለ፡- እርሳቸው አስቀድሜ እንደገለጽኩት የአንድ እርዳታ ድርጅት አስተባባሪ ብቻ ናቸው፤ የእኛን ጠቅላይ ሚኒስትር ለማናገር የፕሮቶኮል ጉዳይም ቢሆን ስለማይፈቅድላቸው ነው ያላናገሯቸው።የመጡበት መንገድ ጤናማ ቢሆን ኖሮ መጀመሪያውኑ መምጣት የነበረባቸው ወደ አፍሪካ መዲና ነበር፤ ምንም እንኳ እርግጠኛ መሆን ባልችልም ተንኮል ለመስራት በሚል የቀሩ አይመስለኝም።
አሜሪካውያን እርዳታ የሚታወቅ ነው።በጥሬ ገንዘብ እንኳ የሚሰጡት ነገር የለም።በአይነትና በመሰል ነገር ነው ሰጠን የሚሉት።ከአንድ አሸባሪ ቡድን፤ ህጻናትን ለጦርነት ከሚማግድ ቡድን፤ በእናቶች ስም ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ጦርነት የከፈተ ቡድን ከእርሱ ጋር በራሱ መታየታቸው ለክብራቸው የሚመጥን አይደለም።ሱዳንም ብትሆን ጁንታው ልኳን ነው የሚያሳያት።ጁንታው የተቋቋመው ለማንም ጥቅም ሲል አይደለም።ለምዕራባውያኑ ለቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ጥቅም ሲባል ነው።ስለዚህ በማንም ላይ ከመተኮስ ወደኋላ የማይል ቡድን መሆኑን ማወቁ አግባብ ነው።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንዶች ከአሜሪካ ጋር ተቀያይሞ ብዙ ርቀት መሄድ አይቻልም ይላሉና እርስዎ ይህን እንዴት ይመለከቱታል?
አቶ እንዳለ፡- ምንም አይመጣም፤ ለምሳሌ ቱርክን ተመልከቺ፤ አሜሪካ ያልጣለችባት ማዕቀብ የለም።ታዲያ አሁን ስታስተውዪ ቱርክ ጠንካራ አገር መሆኑን ነው የምትረጂው።ራሺያም በተመሳሳይ ነው።እንዲያውም በብዙ እጥፍ አድጋና ጠንክራ ነው የታየቸው።ቻይናም እንዲሁ ነው።
ከአሜሪካ ጋር የተጋጨ ምናምን የሚባለው የእነርሱ ፕሮፓጋንዳ ነው።እንዲያውም እነርሱን መያዝ በርቀት ነው።ብዙ መቅረብም፤ ብዙም መራቅ አያስፈልግም።ስለዚህ ከአሜሪካ ጋር የሚባለው የትኛው የኢኮኖሚ እርዳታ እና የትኛው የልማት እርዳታ ሲሰጡ ነው።ኢትዮጵያ ውስጥስ የታሉ።ከማውራት የዘለለ አሜሪካውያን ገንብተውታል የሚባል ነገር የለም።እነርሱ የፈጠሩት ነገር ተረት ነው።
እኛ አሜሪካንን እንፈልጋታለን፤ ከአሜሪካ ጋርም መስራት እንፈልጋለን።ይህ የሚሆነው ግን የእኛንም ጥቅም ስትጠብቅ፤ እኛም የእርሷን ጥቅም እንጠብቅላታለን።አሜሪካ ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር የማትሰራ ከሆነ ጥቅሟን ማስጠበቅ አትችልም።ይህ በራሳቸው ጥናትም ይታወቃል።በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ጥናትም ይታወቃል።ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ነች።በአፍሪካ ምድር አካባቢ እንዲሁም በቀይ ባህር አካባቢ ኢትዮጵያን የመሰለ አገር የለም።
ስለዚህ አሜሪካ ሂጂ ብትያትም አትሄድም።ጸባይዋን አስተካክላ ነው ተመልሳ የምትመጣው።ስለዚህ ምንም የሚያስጋ ነገር የለም።በዲፕሎማሲው መንገድ በነጻ የሚሰጥ ምንም ነገር የለም።ኢትዮጵያ በአካባቢው በጣም አስፈላጊ አገር ነች።ይልቁኑም አሁን እንዲህ በጠነከረችበት ሰዓት ቀርቶ በጁንታው ጊዜ እንኳ ታስፈልጋለች ብለው አብረው ሰርተዋል።
ሱዳን ከአሜሪካ ጋር መስራት የዚያን ያህል አያዋጣትም።ለአሜሪካ ስትዪ የተሰጠሸን የቤት ስራ ሁሉ የምትሰሪ ከሆነ አሜሪካ ዞሮ ዞሮ የምትሰራው ለራሷ ነው።እንዴት ብሎ ነው ታዲያ ጥቅማችንን ልታስከብርልን የምትችለው።አሜሪካ እንዴት ነው የሱዳንን ጥቅም ልታስከብርላት የምትችለው።ሳማንታ ፓወር ሱዳን የገቡ ጊዜ የሱዳን ህዝብ በጣም ነው የተናደደው።ዴሞክራሲውም ሆነ መልካም አስተዳደሩ ሳይጀምር እርሳቸው ግን ተጀምሯል አሉ።ሰው ግን ለምን እንዲህ ይደረጋል በሚል ሰልፍ ነው የወጣው።ስለዚህ ሱዳን የተረጋጋ መንግስት ባለመመስረቷ ምክንያት አሁን ላይ የሚልካት የትኛውም አካል ነው።ማንም ነው የሚያዛት።የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ አፍሪካን በሙሉ ሲዞሩ ነው የሚታዩት።የየት አገር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናቸው እስኪባሉ ድረስ፤ የግብጽ ወይስ የሱዳን የሚለው ነገር እስኪያወዛግብ ድረስ ነው የሚዞሩት።የሚያቀርቡት ነገር ሁሉ ከግብጽ ብሄራዊ ጥቅም ጋር የሚጋጭ ነው።ስለዚህ አሁንም ኢትዮጵያን ላወያይ በሚል በድፍረት መናገር በራሱ ይህ የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ነው ብሎ ነው መመለስ ያለበት።ኢትዮጵያ ደግሞ ጉዳዩ አላቃታትም።ነገር ግን ይህ ሁሉ ትዕግስት ማሳየቷ ዜጎቿን ከመንከባከብ አንጻር ነው እንጂ ምንም ነገር ከአቅም በላይ ሆኖ አይደለም።ነገር ግን ለሁሉም ሰዓትና ጊዜ አለው።እነርሱ ስላሉ የሚደረግ ነገር የለም፤ ስላላሉ ደግሞ የሚቀር ነገር የለም።
የአሜሪካ ማዕቀብ እንዲያውም የበለጠ ጥንካሬ ነው የሚፈጥረው።የሚቀረው ነገር ቢኖር ስንዴ ነው።ከጸጥታ አኳያ ብትወስጂ ግን ሽብርተኝነትን ኢትዮጵያን ካልያዙ መዋጋት አይቻልም።በሱማሊያም ሆነ በሱዳን ገብተው አይቶታል።ስለሆነም ኢትዮጵያን መያዝ ለአሜሪካ ግዴታዋ ነው።ይህን አሜሪካ አሳምራ ታውቀዋለች።ደግሞም ታስተካክለዋለች ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡-ለሰጡኝ ማብራሪያ በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ እንዳለ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 6/2013