አቶ ጌታቸው ንጉሴ በትግራይ ብልጽግና ፓርቲ የሚዲያና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊና በጊዜያዊ አስተዳደሩ የዋና ስራ አስፈጻሚ አማካሪ ናቸው። እኛም በወቅታዊ የትግራይ ሁኔታ እንዲሁም በጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራርነታቸው ወቅት ስላስተዋሏቸው ነገሮች ቆይታን አድርገናል፤ መልካም ቆይታ።
አዲስ ዘመን ፦ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በስራ ላይ በነበረባቸው ስምንት ወራት የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት ምን ነበሩ?
አቶ ጌታቸው፦ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ ወደ ትግራይ ከሄደ በኋላ የተለያዩ ኃላፊነቶችን ሲወጣ ነበር ። ከነዚህም መካከል በጁንታው እኩይ ተግባር ተስተጓጉለው የነበሩ መሠረተ ልማቶች ስራቸውን እንዲጀምሩ የማድረግ እንዲሁም አስተዳደራዊ መዋቅሩ ፈርሶ ስለነበርና ከፖሊስ ጀምሮ ሌሎች አገልግሎት ሰጪ የመንግሥት ተቋማት ሠራተኞች በስራ ገበታቸው ላይ ስላልነበሩ ይህንን መልሶ የማደራጀት ስራ በመስራትና ለዚህ ስልጣንና ኃላፊነት የሚጠቅሙ ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ ያሉ መዋቅሮችን ማዘጋጀት እንዲሁም ሰዎችን የመመደብ ስራ ተሰርቷል ።
ከምዕራባዊ ዞንና ከአምስት ደቡባዊ ዞን ወረዳዎች ውጪ በሌሎቹ የትግራይ አካባቢዎች መዋቅሩ መልሶ የተደራጀበት ሁኔታ ነው ያለው። በሌላ በኩልም በክልሉ ላይ ከ 10 ሺ በላይ እስረኞች ከማረሚያ ቤቶች ከመለቀቃቸው እንዲሁም ፖሊስና ሌሎች የጸጥታ መዋቅሩ አካላት ካለመኖራቸው የተነሳ ደፍርሶ የነበረውን ሰላምና ጸጥታ ወደ ቦታው ለመመለስና ህዝቡ በሰላም ወደ ቀድሞ ኑሮው እንዲመለስ ለማድረግ ሰፊ ስራዎች ተሰርተዋል።
ከጥቅምት 24 በኋላ በተጀመረው የህግ ማስከበር ዘመቻም የተለያዩ መሠረተ ልማቶች የወደሙበት ሁኔታ መኖሩ ይታወሳል። ከዛም በላይ ደግሞ እንደ ባንክ ያሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ስራቸውን በአግባቡ ማከናወን ባለመቻላቸውና በመዘጋታቸው ደሀውም ሀብታሙም ተረጂ የሆነበት ሁኔታ ስለነበር አብዛኛው ነዋሪ ችግር ውስጥ ነበር። እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች ሰብዓዊ ድጋፎች እንዲደርሳቸው የማድረግ ስራዎች እየተከናወኑም ነበር።
በተጨማሪም የመንግሥት አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ ቆመው የነበረ በመሆኑ እነሱ ወደ ስራ እንዲመለሱ ለማድረግና ህብረተሰቡም የሚፈልገውን አገልግሎት እንዲያገኝ ከማድረግ አንጻርም በርካታ ስራዎች ተከናውነው ነበር። በጠቅላላው ጊዜያዊ አስተዳደሩ እነዚህን ተግባራት አከናውኖ ክልሉ እየተረጋጋ በሄደ ቁጥርም ህብረተሰቡ ቀና ብሎ ስራውን ኑሮውን በተረጋጋ መምራት ሲጀምር በመረጠው አስተዳደር እንዲተዳደር ምርጫ የማድረግና ለዛም ዝግጁ እንዲሆን ስራዎች እየተሰሩ ባሉበት ሁኔታ ነው እንግዲህ መከላከያ ሠራዊቱም ክልሉን ለቆ የወጣውና ክልሉም ዳግም ወደ ችግር ውስጥ የገባው።
አዲስ ዘመን ፦ በዚህ ሂደት ያጋጠሙ መሠረታዊ ችግሮች ምን ነበሩ? እንዴትስ ፈታችኋቸው?
አቶ ጌታቸው፦ አዎ እነዚህን ስራዎች ስናከናውን በርካታ ችግሮች አጋጥመውናል ። ከችግሮቹም መካከል በተለይም የሰብዓዊ ድጋፍ ስራዎች በሚሰሩበት አካባቢ በቅንነት የሚያገለግሉ አካላት እንዳሉ ሁሉ በዘረፋ የተሰማሩ ከአመራር ጀምሮ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ያሉ ሰዎች ነበሩ። በሌላ በኩልም የክልሉን ጸጥታ ለማስጠበቅ ስራዎች በሚሰሩበት ወቅት የጸጥታ ሀይሉን መልሰን ለማቋቋም በማሰብ ሰዎች መልምለንና አጫጭር ስልጠናዎችን ሰጥተን ወደ ስራው ብናስገባም አንዳንዶቹ የተሰጣቸውን መሳሪያ ይዘው በረሀ መግባት፤ ሌሎቹ ደግሞ መሳሪያ ታጥቀው ቤታቸው ቁጭ በማለት ተገቢውን አገልግሎት አለመስጠት እንዲሁም መሳሪያዎችን መሸጥ የታዩ ከባድ ችግሮች ነበሩ።
አብዛኛው ህብረተሰብ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር ምንም ችግር የሌለበት ቢሆንም በአንጻሩ ግን ስጋቶች ነበሩበት። ስጋቶቹም ህወሓት ተመልሶ ይመጣና እኛም ቤተሰባችንም ችግር ውስጥ እንገባለን በሚል መንፈስ ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ሙሉ እምነት አለመስጠትና በሙሉ ልባቸው በስራዎች ላይ አለመሳተፍ ነበር።
የህወሓት የውስጥና የውጭ ኃይሎችም ያለ የሌለ አቅማቸውን አጠናክረው በሚሰሩት ፕሮፖጋንዳ ህዝቡ አስተዳደሩን በሙሉ ልቡ እንዳያምን ሆኗል፤ ይህም ለስራው ከፍተኛ ጫናን ያሳደረም ነገር ነው። በሌላ በኩልም በምናደርገው ስብሰባዎችና ሌሎች ስራዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ እንቅፋት ሆኖ የነበረው በተለይም ቀደም ብሎ በትግራይ ክልል ይተዳደሩ የነበሩት እንደ ምዕራብ ትግራይና ደቡባዊ ዞን አምስት ወረዳዎች በጊዜያዊ አስተዳደሩ ስር አለመሆናቸው ህዝቡ መሬታችንን አሳልፋችሁ ሰጣችሁብን በሚል ከፍተኛ ጥያቄና ቅሬታ መኖሩም ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ከፍተኛ ፈተና ሆኖበት ቆይቷል።
ሌላው አንዳንድ የኤርትራ ሠራዊቶች በህዝቡ ላይ የሚያደርሱት በደል ህዝቡን በጣም ቅር ያሰኘው ከመሆኑም በላይ እነዚህን በደሎቻችንን ማስቆም ካልቻላችሁ ምኑን መራችሁን? በሚልና እንዴት ከእናንተ ጋር እንቀጥላለን? ይሉም ነበር። ይህም ቢሆን ግን በተለይም ወደ መጨረሻው አካባቢ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከፌዴራል መንግሥት ጋር እየተነጋገረ ችግሮች ቀስ በቀስ እየተፈቱ አካሄዱም መልክ እየያዘ የመጣበት ሁኔታ ነበር።
በሌላ በኩልም በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ የነበሩ አመራሮች አንድ የመሆን ከፍተኛ የሆነ ችግር ነበረባቸው፤ ይህ ደግሞ ዋናው ምክንያት አስተዳደሩ ከአንድ ፓርቲ የተውጣጣ አለመሆኑ ሲሆን በሀሳብ ያለመግባባትና ክፍተቶች እንዲኖሩ አድርጓል። በአንድ ፓርቲ ስም እየተሰራ ቢሆንም መንግሥት የሚሰጠውን ሰብዓዊ ድጋፎች ህብረተሰቡ ጋር እንዳይደርስ ከማድረግ ጀምሮ ፌደራል መንግሥት ምንም እያደረገላችሁ አይደለም፤ እየረዷችሁ ያሉት ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ብቻ ናቸው፤ በማለት በመንግሥትና በህዝቡ መካከል ክፍተት እንዲፈጠር የማድረግ ስራም ሲሰራ ነበር።
አዲስ ዘመን ፦ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ችግሮቹን አሸንፎ ለመውጣት ያደረገው ጥረት ምን ያህል ነበር?
አቶ ጌታቸው፦ በእርዳታ ዙሪያ የሚያጭበረብሩ ችግር የሚፈጥሩ እስከ ቀበሌ ድረስ ያሉ አካላት የሚጠየቁበትን ሁኔታ የማደራጀት ስራ እየሰራን ነበር። በዚህ ላይ ህብረተሰቡ እራሱ እየጠቆመና መረጃ እያደራጀ መሳተፍ ጀምሮ የነበረ ሲሆን በዚህም እስከ 16 ቤተሰብ ድረስ አስመዝግበው የሚጠቀሙ አካላት ተገኝተዋል። በዚህ ስራ ላይም ቀጥተኛ ተሳትፎን ያደረጉ አመራሮችንም ከቦታቸው እንዲነሱ ተደርጓል።
በሌላ በኩልም አንዳንድ ፖሊሶች የተሰጣቸውን መሳሪያ ይዘው ወደበረሃ የሚቀላቀሉ ወይንም ደግሞ የሚሸጡም ነበሩና ይህ ደግሞ የህብረተሰቡን ጸጥታ ከማስጠበቅ አንጻር ጫናው ከፍተኛ በመሆኑ ይህንን ለማስተካከል ወጣቶች በራሳቸው ተደራጅተው የአካባቢያቸውን ጸጥታ እንዲጠብቁ ተደርጓል።
ዋናው ትኩረታችንን ያደረግነው ግን በፖለቲካዊ ስራው ላይ ሳይሆን ህዝቡን ከችግር ማውጣት ሰብዓዊ ድጋፎችን በተገቢው መንገድ ማዳረስ ላይ ነበር። ይህንን ስናደርግ የጥፋት ቡድኑ በጣም ትልቅ ችግር ሲፈጥር ነበር፤ ከዚህም መካከል በፖለቲካው ውስጥ የሌሉ ሰዎችን የመግደል የማፈን የማሰቃየት ተግባራት ነበሩ፤ ሁኔታው ጊዜያዊ አስተዳደሩ በራሱ ተማምኖ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በአግባቡና በስርዓቱ እንዳይወጣ አድርጎታል።
ብዙ ሰዎች ሞተዋል ፤ ባልሞቱትም ላይ ቢሆን ከፍተኛ የሆነ ስነ ልቦናዊ ጫና እንዲፈጠርባቸው ሆኗል፤ ይህም ቢሆን ግን የጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮች እራሳቸውን መስዋዕት እስከማድረግ የደረሰ የስራ ቁርጠኝነት ነበራቸው። በሌላ ጎን ደግሞ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ህዝቡ ሲገደል የተለያዩ ችግሮች ሲደርሱበት አጥፊዎችን ተከታትሎ ለመጠየቅ ያለመቻል ችግሮች ነበሩ ፤ይህንን ያደረገው ከከተማ ወጥቶ የትም መንቀሳቀስ አለመቻሉ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮች ከአምስት የተለያዩ ፓርቲዎች የተውጣጡ መሆናቸው በውስጡ የአንድነት ስሜት እንዲጠፋና ሁሉም በየፊናው የሚመስለውን እንዲሰራ ውጤቱ ግን ምንም እንዲሆን አድርጎታል።
አዲስ ዘመን ፦በቅርቡ ባካሄዳችሁት ግምገማ የለያችኋቸው ጠንካራና ደካማ ጎኖች ምን ነበሩ? በተለይም ደካማ ጎኖቹ መንስኤያቸው ምን ነበር?
አቶ ጌታቸው፦ የተለየ ያነሳነው ነገር የለም ። ነገር ግን አዲስ አበባ ከመጣን በኋላ የነበሩብንን ጠንካራና ደካማ ጎኖች በደንብ የለየ ግምገማ አድርገናል። በዚህም ከላይ የገለጽኳቸው ቸግሮች እንዳሉ ተማምነናል። እዚህ ላይ ግን ለመጨመር ያህል ጊዜያዊ አስተዳደሩ በስራ ላይ በነበረበት ወቅት ይፈጠሩ ለነበሩ የህግ ጥሰቶች ተገቢና አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ እንዲሁም አጥፊን በቶሎ ተጠያቂ ማድረግ ላይ ከፍተኛ ክፍተት እንደነበር ተነጋግረናል።
በወቅቱ አመራር ሆነውም ይሁን ሳይሆኑ በማጭበርበር በስርቆት በጠቅላላው ህዝቡን ሲበድሉ የነበሩ አካላትን ለመጠየቅ አልተቻለም። ለዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ የፍትህ ተቋማት በአግባቡ ተከፍተው ስራቸውን እያከናወኑ አለመሆኑ ነበር።
በተለይም የጸጥታው መዋቅር ላይ ያሉ አመራሮች ከፍተኛ የሆነ ችግር ይፈጥሩ ነበር። ህብረተሰቡ ከወጣቱ ጋር ተባብሮ ሌቦች እንኳን ሲይዝ እነሱ ተደራድረው የመፍታት፣ የመከላከያን ልብስ እየለበሱ ህዝቡን በማሸበር ስራ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ሲያዙ አንድና ሁለት ቀን አስሮ መፍታትና የመሳሰሉትን እኩይ ተግባራት ሲፈጽሙ ነበር ፤ይህ ደግሞ የጸጥታው ሁኔታ እንዳይጠናከር ህብረተሰቡም በአመራሩ ላይ እምነት እንዲያጣና መጥፎውን አማራጭ እንዲናፍቅ አድርገውታል። ይህ በግምገማችን በደንብ ያየነውና በወቅቱ ምንም እንኳን መዳኘትና መጠየቅ ያልተቻለ ቢሆንም አሁንም አዲስ አበባ አመራሩን ተቀላቅለው የመጡ በተግባሩ ላይ ሲሳተፉ የነበሩ አመራሮች እንዲጠየቁ እንደሚደረግም ተግባብተናል።
ሌላው በግምገማችን ያነሳነው የጊዜያዊ አስተዳደሩ ግማሽ ያህል ካቢኔ መቀሌ ቀርቷል፤ ይህ ትልቅ ሀይል ለመቅረቱ ዋናው ምክንያት ቀድሞውንም ከህወሓት ጋር ሲሰሩ የነበሩ በመሆናቸው ነው። በመሆኑም እነዚህ ተላላኪዎች የፈጠሩት ችግር እዚህ እንዳደረሰን በመነጋገር በእነሱ ላይ አሉ የሚባሉ መረጃዎች ሁሉ ተዘጋጅተው ቅጣታቸውን የሚያገኙበት መንገድ ቢፈጠር መልካም እንደሆነ ተነጋግረን ተማምነናል።
አዲስ ዘመን ፦ የመከላከያ ሠራዊት ክልሉን ለቆ ለመውጣቱ በመንግሥት በኩል እንደ ምክንያት ከቀረቡ ነገሮች መካከል አንዱ ህዝቡ ለሠራዊቱ ደጀን አልሆነም የሚል ነውና እንደው እናንተ ህዝቡ ደጀን እንዲሆን ለምን አልሰራችሁም?
አቶ ጌታቸው፦ የትግራይ ህዝብ ለመከላከያ ሠራዊት ደጀን ነው፤ ነገር ግን ህብረተሰቡ ተረጋግቶ ስራውን እንዳይሰራ ተማሪዎች በአግባቡ በትምህርት ገበታቸው ላይ እንዳይገኙ አርሶ አደሩ የግብርና ስራውን እንዳያከናውን የሚፈጠሩ ችግሮች ነበሩ። ይህ ነው የሚያስማማን፤ ይህንን ያልኩበት ዋናው ምክንያት ደግሞ አርሶ አደሩ ሞፈር ቀንበሩን ተሸክሞ ወደ ስራ ሲወጣ የሚያስፈራራው አካል አለ። እየፈሩና ስጋት ውስጥ ሆነው ደግሞ ስራቸውን በአግባቡ ማከናወን አይችሉም። በተመሳሳይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ መንገድ ላይ እየተጠበቁ ዛቻና ማስፈራሪያ የሚደርስባቸው ከሆነ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት በመላካቸው ብቻ ቆይ ጠብቁ የሚባሉ ከሆነ የንግድ ተቋማት አገልግሎት እንዳይሰጡ ማንም ከጫካ እየወጣና ውስጥ ባሉ ተላላኪዎቹ አማካይነት የሚያሸብር ከሆነ በየት በኩል ደጀንነቱን ማረጋገጥ ይችላል። በዚህ ምክንያት ህብረተሰቡ ምንም አላጠፋም ነው የምንለው? በመሆኑም ህብረተሰቡ “ ህወሓት ተመልሶ ይመጣል፤ ያን ጊዜ የት እንደምትገቡ እናያለን” እየተባለ ነበር፤ በመሆኑም በህዝቡ ላይም መፍረድ በጣም ይከብዳል።
ነገር ግን ጥፋት አለ ከተባለ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ይህንን ማስቆም ባለመቻሉ ላይ ነው ። ህዝቡ ለመከላከያ ሠራዊቱ ደጀን ላለመሆን ያደረገው ነገር የለም። በመሆኑም ጊዜያዊ አስተዳደሩ በሚያስፈራሩት አካላት ላይ አልሰራም፤ የሚለው ትክክል ነው።
እነዚህ የጥፋት ኃይሎችና ጀሌዎቻቸው ምንም እንኳን የጊዜያዊ አስተዳደሩ አካል ቢሆኑም ፖለቲካ አንሰራም በማለት ማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ እርዳታ አከፋፋይ በመምሰል ሌሎች እኩይ ተግባራትን ሲሰሩ ነበር። ይህ ደግሞ ካቢኔው ላይ ያሉ አባላት ብቻ ሳይሆን እስከ ወረዳና ቀበሌ ድረስ የሚወርድ ችግር ነው።
በመሆኑም የህወሓትን ኔትዎርክ መበጣጠስ በጣም አዳጋች መሆኑ ነው ለዚህ ሁሉ ችግር የዳረገን እንጂ የትግራይ ህዝብ ለመከላከያ ሠራዊት ደጀን መሆን ስላልፈለገ አይደለም።
አዲስ ዘመን ፦ በሌላ በኩል ደግሞ መከላከያው ክልሉን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ እናንተ አመራሮቹ አዲስ አበባ እንድትቀመጡ ሆኗል፤ በዚህ መካከል አንዳንድ አመራሮች በጣም ችግር ላይ ነን በማለት ቅሬታ ሲያሰሙ ነበር፤ ይህ እንዴት ሆነ? እርስዎስ በዚህ ላይ ያልዎት ሃሳብ ምንድን ነው? መሠረታዊ መፍትሔውስ ምን ሆነ?
አቶ ጌታቸው፦ አብዛኛው የጊዜያዊ አስተዳደር አባላት አዲስ አበባ ላይ የነበረንን ስራ ነው ትተን ህዝብ እናገለግላለን ብለን ወደ ትግራይ የሄድነው፤ ትግራይ ውስጥ ሆነው ደግሞ ጊዜያዊ አስተዳደሩን ተቀላቅለው የሚሰሩም ነበሩ። በመሆኑም ተኩስ አቁም ታውጆ ወደ አዲስ አበባ በምንመጣበት ጊዜ መንግሥት ጊዮን ሆቴል እንድናርፍ ሁኔታዎችን አመቻችቶልናል፤ ከዛ በኋላ ግን ቀድሞ ስንሰራበት ወደነበረው ስራችን እንድንመለስ ነው የተባለው፤ ለዚህ ደግሞ አስፈላጊው ትብብር እንዲደረግ ነበር የታዘዘው፤ ነገር ግን ጊዜያዊና ቋሚ የሆነ የስራ ሁኔታን መለየት ባለመቻል ትንሽ መንገራገጮች ነበሩ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ቀድሞውንም ትግራይ ላይ ሲሰሩ የነበሩ አመራሮች አሁን ወደ ክልሉ ሄደው መስራት ስለማይችሉ አዲስ አበባ ባሉ መስሪያ ቤቶች በሚችሉት ወይም በሚመጥናቸው የሙያ መስክ ተመድበው እራሳቸውን የሚያስተዳድሩበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት፤ ይህ እስከሚሆን ድረስ ግን መንግሥት ዝም ብሎ አልጣላቸውም።መጀመሪያ ላይ መደናገጦች ስለነበሩ አንዳንዶች አዲስ አበባን ባያውቋትም እንኳን ቤተሰባቸውን ይዘው የመጡም ስላሉ ቦታው ተገኝቶ ወደስራ እስከሚመለሱ ድረስ እንዳይቸገሩ ደሞዛቸው እንዲከፈላቸው እየተደረገ ነው። ይህም አሁን ላይ ሁኔታውን በመጠኑም ቢሆን አሻሽሎታል።
ሰላም ሚኒስትርም ስልጠናዎችን እየሰጠ አንዳንድ ድጋፎችን ለማድረግም ዝግጁ መሆኑን እየገለጸም ሲሆን አሁን ላይ ችግሩ ተቃሏል።
አዲስ ዘመን፦ ይህንን ያህል ዝግጁነቱ ካለ ታዲያ አመራሮቹ ከምን ተነስተው ነው ችግር ላይ ወድቀናል ያሉት?
አቶ ጌታቸው፦ አሁን በትክክለኛ መዋቅር ውስጥ ያሉ ሰዎች ይህንን ቅሬታ ያሰማሉ ብዬ አላስብም። ምክንያቱም አሁን ደመወዝ እየተከፈለ ያለው በጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ የስራ ድርሻ ኖሯቸው ደብዳቤ ደርሷቸው እየሰሩ ላሉ አካላት ብቻ ነው። ነገር ግን ከዚህ መዋቅር ውጪ ሆነው ጊዜያዊ አስተዳደሩን በመደገፍ ሲሰሩ የነበሩ አካላት ግን ይህንን ማግኘት ስለማይችሉ ተቸግረዋል።
አዲስ ዘመን ፦በአሁኑ ወቅት በትግራይ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ እንዴት ትገመግሙታላችሁ? በምንስ ሁኔታ ትከታተሉታላችሁ?
አቶ ጌታቸው፦ የትግራይ ህዝብ ህወሓት እስካለ ድረስ ከችግር ይወጣል ማለት ከባድ ነው። ሁሌም ቢሆን ህዝቡን ለከፍተኛ ችግር የሚዳርገው ህወሓት ነው። ህዝቡ እስከ አሁን ከኖረበት በባሰ አሰቃቂ ችግር ላይ ነው። ይህ ደግም በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው። በነገራችን ላይ ህወሓት ክልሉንም አገርንም ለረጅም ዓመት ያስተዳደረበት ሁኔታ ቢኖርም ለትግራይ ህዝብ የሚጠጣው ውሃ እንኳን በአግባቡ ማቅረብ ያልቻለ ድርጅት ነው። ጭካኔያቸውን እንግዲህ በዚህን ያህል ደረጃ መገመት ይቻላል።
ነገር ግን ለትግራይ ህዝብ እኔ ነኝ የማስብለት በማለት ህጻናትን እናቶችን ወደ ጦር ግንባር እየላከ ነገ ባለስልጣን እሆናለሁ በሚል ቀቢጸ ተስፋ እየኖረ ነው። አሁን አይደለም ከቀደመው ጊዜ ጀምሮ ወጣቱ ከእሱ ውጪ እንዳያስብ ስራ እንዳይሰራ ተምሮ ራሱን እንዳይችልና እንዳይለውጥ በማድረግ አፍኖ ይዞት ነበር ፤ አሁን ደግሞ ሁሉም ነገር ዝግትግት ሲልበት ወጣቱ ወዶ ሳይሆን አማራጭ አጥቶ ይልሰው ይቀምሰው ተቸግሮ የእናት የአባቶቹን ስቃይና የቁም ሞት ላለማየት በመሻት በገፍ ወደጦር ግንባር በመሄድ ላይ ነው።
በመሆኑም የፌዴራል መንግሥት ከዚህ አረመኔ ከስልጣኑ ውጪ ምንም ከማያውቅና ከማይፈልግ የጁንታ ቡድን በፍጥነት ሊያድነው ይገባል ። አለም አቀፉ ህብረተሰብም የጥቅም አጋራቸው የሆነውን የጁንታ ቡድን እየደገፉም ቢሆን መንግሥትና እኛም ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ እኩይ ተግባሩን በማጋለጥ እነሱም እንዲገነዘቡ በማድረግ ብሎም እንደ አገር የእነሱን ጫና ተቋቁመን ይህንን አስቸጋሪ ጊዜ ማለፍ ይገባናል።
የትግራይ ህዝብ በሀብቱ በንብረቱ ማዘዝ ልጆቹን አስተምሮ ለወግ ማዕረግ ማብቃት አይደለም ሌላው ክልል የሚተነፍሰውን ንጹህ አየር እንኳን እንዳይተነፍስ ታፍኖ የኖረ ህዝብ ነው። በመሆኑም ከአሸናፊነትና ከተሸናፊነት የስሜት አስተሳሰብ ወጥተን ሰላማችንን ለማምጣት ህዝቡን ያስቀደመ ስራ ቢሰራ ጥሩ ነው ።
የትግራይ ህዝብ በምንም ዓይነት መንገድ ከኢትዮጵያ ህዝብ መነጠል አይፈልግም።ይህ ሀሳብ የጥቂት ስልጣን ወዳድ ስግብግቦች አጀንዳ ብቻ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ለዚህ አጀንዳ ማስፈጸሚያ ህጻናት የእሳት ማብረጃ እየሆኑ ነው፤ ይህ የሚሆነው ደግሞ በፍቃደኝነት ሳይሆን በግዳጅ ነው።
ወጣቱ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር ተቀራርቦ ሰርቶ ክልሉንና ራሱን እንዳይለውጥ ህወሓት ተመልሶ ይመጣል፤ ያን ጊዜ ደግሞ ወየውላችሁ እየተባሉ ነበር፤ አሁን ደግሞ አላልናችሁም ወደማለት ተሂዷል፤ በመሆኑም ህዝቡ ወትሮም ቢሆን ተቸግሮና ተጨንቆ እንጂ ለመከላከያ ሠራዊት ደጀን መሆን ስላልፈለገ መሆኑ ታውቆ አሁንም የበለጠ ሰላም እንዲያገኝ ይህንን ጁንታ ቡድን ከላዩ ላይ ለመንቀል የተጠናከረ ስራ መሰራት አለበት።
በሌላ በኩልም አሁን ላይ የጁንታው ቡድን የዘረጋው ስትራቴጂ ትግራይ ላይ ብቻ የሚያበቃ ባለመሆኑና መላው አገሪቱን ማተራመስ መሆኑን በመረዳት ከምንም በላይ ለሰላማችን ቅድሚያ በመስጠት ህዝቡ የሚረጋጋበትንና ወደቀድሞ ኑሮው የሚመለስበትን መንገድ መፈለግም ከመንግስት ብሎም ከሁላችንም የሚጠበቅ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ በአሁኑ ወቅት ጊዜያዊ አስተዳደሩ ተግባርና ኃላፊነቱን በምን መልኩ እየተወጣ ይገኛል? ክልሉንስ እያስተዳደራችሁት ነው ማለት ይቻላል?
አቶ ጌታቸው፦ ጽህፈት ቤቱ አለ፤ ነገር ግን በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ ስራዎችን ሲያከናውኑ የነበሩት አብዛኞቹ ሰዎች ስራ የላቸውም።የሚያስተዳድሩትም ነገር የለም። ለምሳሌ የትግራይ ቢሮ ኃላፊዎች የሚመሩት ቢሮ የለም ፤የዞን አስተዳዳሪም እንዲሁም የሚያስተዳድረው ዞን የለውም። የወረዳ ኃላፊውም በተመሳሳይ፤ በመሆኑም ይህ በሌለበት ሁኔታ የዞን አልያም የወረዳ አስተዳዳሪ ተብሎ አዲስ አበባ ላይ ቁጭ ማለት ተገቢም ባለመሆኑ ወደ ቀድሞ ስራቸው ተመልሰው ስራቸውን እንዲሰሩ ሆኗል።
እንደ ጊዜያዊ አስተዳደር ግን ጽህፈት ቤቱ አለ በቀጣይም የሚመጡ ነገሮችን እያየን የምንሰራቸውን ስራዎች እናያለን ። ነገር ግን በስሩ የነበረው የአመራር መዋቅር ጊዜያዊም ስለነበር አሁን ላይ ፈርሷል ማለት ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ጽህፈት ቤቱ ካለ የትግራይን ወቅታዊ ሁኔታ የምትከታተሉበት መንገድስ ይኖር ይሆን ?
አቶ ጌታቸው፦ እኛ እኮ አሁን ትግራይ ውስጥ ላለው ህዝብ ብቻ አይደለም የምንጨነቀው፤ ለምሳሌ አሁን ላይ ከትግራይ ክልል ተፈናቅለው በአፋር፣ ወልዲያና በጎንደር አካባቢዎች ላይ ያሉ በርካታ ህዝቦች አሉ፤ የእነሱ ጉዳይም ይመለከተናልና፤ እነሱንም እንከታተላለን ። አዲስ አበባ ላይም ያሉ ትግራዋይን በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ የመከታተል ስራዎች ይሰራሉ።
አዲስ ዘመን፦ በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ የትግራይ ተወላጆች እየታሰሩ ንብረታቸው እንዳይንቀሳቀስ እየታገደ በተለይም ንግድ ቤቶች እየተዘጉ ነው የሚል ክስ በመንግሥት ላይ እየቀረበ ነውና እንደው ይህንን እንደ ፓርቲ ብሎም እንደ ጊዜያዊ አስተዳደር አመራር እንዴት ያዩታል ? ለህዝቡስ ግልጽ መሆን ያለበት ነገር ምንድን ነው?
አቶ ጌታቸው፦ አዲስ አበባም ሆነ ከአገር ውጪ ሆነው የጁንታውን ቡድን አጀንዳ የሚያስፈጽሙ አሉ። እነዚህ ሰዎች ደግም አሸባሪ ተብሎ ከተፈረጀ አካል ጋር እንደዚህ አይነት ተግባር ላይ መሳተፍ አለባቸው ብዬ አላስብም። ምክንያቱም እየሰሩ ያሉት ነገር ወንጀል በመሆኑ፤ እነዚህ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ሊነገራቸው ይገባል። የማይስተካከሉ ከሆነ ግን በህግ መጠየቁ አግባብነት ያለው ስራ ነው። ነገር ግን ከጥፋት ቡድኑ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ሰዎች ላይ የሚደርስ ነገር ካለ ጥፋት በመሆኑ ሊታረም ይገባል። ነገር ግን በትክክል የጥፋት ቡድኑን ሲያግዙ ችግር ሲፈጥሩ የተገኙ አካላት መጠየቅ አለባቸው። በዚህም ምንም ድርድር ሊኖር አይገባም።
ሆኖም ምንም ጥፋት ሳይኖረው የታሰረ ሰው ካለ ተጣርቶ ሊፈታ ይገባል፤ በተመሳሳይ ድርጅታቸው የተዘጉ አካላትም የጁንታውን አላማ ሲያስፈጽሙ በገንዘብና በተለያዩ ነገሮች ሲያግዙ የነበሩ ከሆነ ቢዘጋባቸውም በህግ መጠየቃቸውም አግባብነት ያለው ጉዳይ ነው። ነገር ግን እዚህም ላይ ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ ያስፈልጋል።
“ አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ” እንዳይሆን የሚያጣራው አካል በፍጹም ቅንነትና ታማኝነት አጥፊን ከጥሩ መለየት አለበት። ትግራዋይም ሆኖ ምንም ነገር ውስጥ የሌለበት ሰው በሰላም ወጥቶ ገብቶ በልበ ሙሉነት ስራውን አከናውኖ አገር ከእርሱ የምትፈልገውን ከፍሎ መኖር መቻል አለበት። ኢትዮጵያ የአንድ ብሔር ወይንም የጥቂት ሰዎች ሳትሆን የሁላችንም ናት እስከ ዛሬ የመጣንበት የበላይና የበታችነት አካሄድ እንዲሁም የባለጊዜነት ጉዳይ እዚህ ችግር ውስጥ እንዳስገባን ተረድተን ከዚህ አስተሳሰብ ሙሉ በሙሉ ተላቀን ሁሉም በእኩልና በነጻነት የሚንቀሳቀስበት ሰርቶ የሚበላበት አገር ማቆየት ደግሞ የሁላችንም ኃላፊነት ነው።
አዲስ ዘመን፦ ጁንታው በአሁኑ ወቅት ህጻናትን ለጦርነት እየመለመለ እያሳተፈ ነው፤ ይህ እንደው ከባህርይው ብሎም ከዓለም አቀፍ ህጎች አንጻር እንዴት ያዩታል?
አቶ ጌታቸው፦ ህወሓት ለስልጣንና ለስልጣን ብቻ የሚኖር ፓርቲ ነው፤ አገር ፣ሰላም፣ፍቅር፣ ሰብዓዊነት የሚባሉ ነገሮች ሁሉ ለእሱ ምንም ቦታ የላቸውም ። በየትኛውም መንገድ በምንም አጋጣሚ ብቻ ያጣትን ስልጣን ማግኘት ነው የሚፈልገው፤ ህጻናት ጦር ሜዳ ሄዱ እናቶች ሞቱ አዛውንቶች ተራቡ ያ የእሱ ጉዳይ አይደለም። ባለፉት ዓመታትም ቢሆን እኮ በስልጣኑ የመጡበትን ሲያስር፣ ሲያሰቃይ፣ ሲያሳድድ፣ ሲገድል ነው የኖረው፤ አሁንም እየሰራ ያለው ስራ ተመሳሳይ ነው።
አልደገፉኝም ያላቸውን አሁን እንኳን በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ ስራ ሲሰሩ የነበሩ ሰዎችን ቤተሰቦች በነፍሳቸው እየተጫወተ እያሸማቀቀ ሁለተኛ ዜጋ የሆኑ ያህል እንዲሰማቸው እያደረገ ነው። ጁንታው ለስልጣኑ ሲል ሙሉ የትግራይን ህዝብ በአንድ ጀምበር ቢያጠፋ ራሱ ደስ የሚለው አረመኔ ቡድን ነው።
ትግራይ ውስጥ ሌላ ተፎካካሪ ፓርቲ አማራጭ ሆኖ መቅረብ እንደማይችል ያውቃል ፤ የፖለቲካ አማራጭ እንደሌለም እንደዛው በመሆኑም ህዝቡን ከኔ ውጪ ከማንም ጋር አትሆኑም ብሎ ነው የያዛቸው ፤ በዚህም መሠረት ነው እናቶች ህጻናት አረጋውያን ሳይቀሩ ወደ ጦርነት ግቡ እየተባሉ ያሉት፤ ይህ ደግሞ እንደ ዜጋ በጣም ያማል፤ መሆንም አልነበረበትም ፤ ነገር ግን የጁንታ ቡድን እያደረገው ነው።
የፌዴራል መንግሥትም ለህዝቡ ሲል ሰላም የሚገኝበትን አማራጭ መፈለግ ካልሆነ ግን መወሰድ ያለበትን እርምጃ ጊዜ ሳይሰጥ ወስዶ ሰላም ማምጣት ይገባዋል። ይህ የማይሆን ከሆነ ደግሞ ብዙ ህዝብ እያለቀ ነው ወደፊትም የሚያልቅ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፦ እኔ ጨርሻለሁ እርስዎ ቀረ የሚሉት ሃሳብ ካለ?
አቶ ጌታቸው፦ በአገር ውስጥም በውጭም ያሉ ትግራዋያን በእኛ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ህዝባችን ማለቅ የለበትም በማለት ቆም ብለው ሊያስቡ ይገባል። እከሌ አሸነፈ ይህንን ተቆጣጠሩ እያሉ ህዝብን ግራ ማጋባት አይጠቅምም። ይልቁንም ችግሮች ወደ ሰላማዊ መንገድ የሚያመሩበትን ሁኔታ ማመቻቸትና ለዛ መንቀሳቀሱ ይጠቅማል ብዬ አስባለሁ። ችግር የሚፈጥሩ አካላትንም ለህግ አሳልፎ መስጠቱ ጥሩ አካሄድ ነው። ይህንን ማድረግ ከቻልን ሰላም ይሆናል፣ ህብረተሰቡም እየተረጋጋ ይሄዳል።
በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ ልቡ ማመን ያለበት የህወሓት የጥፋት ቡድንና የትግራይ ህዝብ የተለያዩ መሆናቸውን ነው። በመሆኑም በየአካባቢው ያሉ የትግራይ ተወላጆች አስፈለጊው ሁሉ እንክብካቤ ሊደረግላቸው ይገባል። ስራቸውንም ያለምንም ስጋት ሊሰሩ ይገባል። ነገር ግን የጥፋት ቡድኑን በመደገፍ ስራ ላይ የተሰማሩ ሲገኙ አሳልፎ ለህግ መስጠቱ በጣም ተገቢ ነው። ይህንን ማድረግ ከቻልን የትግራይ ህዝብ ራሱ ማነው ችግር የሚፈጥረው፣ ለአካባቢው ሰላም ጠንቅ የሆነው የቱ አካል ነው፣ የሚለውን የሚጠቁም ይሆናል።
የትግራይ ህዝብ አሁንም ቢሆን በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር የመነጠልና የመገንጠል አስተሳሰብን የሚጸየፍ ህብረተሰብ ነው። ከሁሉም ብሔሮች ጋር ተዋዶና ተፋቅሮ መኖር የሚፈልግ ህብረተሰብ መሆኑን መላው ህዝብ ሊያውቀውና ሊረዳው ይገባል ።
አዲስ ዘመን ፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ ጌታቸው ፦ እኔም አመሰግናለሁ
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 4/2013