በአገራችን በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት ብዙ ንብረት ወድሟል፣ የሰው ህይወት ጠፍቷል:: መፈናቀሉም እንዲሁ ብዙ ነው:: በተለይ በትግራይ ያለው ሁኔታ ደግሞ የከፋ እንደሆነ ይታወቃል:: ይህንን ተከትሎም የዲያስፖራ የሰላም ጓድ አባላት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተዘዋውረው ሁኔታውን ጎብኝተዋል:: ማገዝ ያለባቸውንም እያደረጉ ይገኛሉ:: በዚህም በሰሞኑ ቆይታቸው ዙሪያና በአንዳንድ አገራዊ ወቅታዊ ሁኔታዎች ዙሪያ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር:: በወቅቱ ከተሳተፉትና የሰላም ጓዱ አባል ከሆኑት አስር አለቃ አትሌት በላይነህ ዲንሳሞ ጋር በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ አጠር ያለ ቆይታ አድርገናል:: የተመለከቱትንና መሆን ያለበትንም በብዙ መልኩ ስለነገሩን እንደሚከተለው አቅርበናል::
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ህዝብ እርስዎን የሚያውቆት በአትሌትነትዎ ነው፤ ከሩጫው በኋላ ደግሞ ለብዙ ዓመታት ድምጽዎ ጠፍቶ ቆይተዋልና በቅድሚያ ለአንባቢዎቻችን ስለራስዎ ጥቂት ይግለጹልንና ቃለምልልሳችንን በዚህ እንጀምር::
አትሌት በላይነህ፡- የተወለድኩት በድሮው አጠራር ሲዳሞ ክፍለ አገር ሲዳማ አውራጃ በሸበዲኖ አውራጃ ነው:: በዚህ አካባቢ ስኖርም ሆነ ከዚህ ከወጣሁ በኋላ ከሩጫ በላይ የሆኑ ስራዎችን አከናውናለሁ:: ለአብነት በቀበሌ ደረጃ የስፖርት ሊቀመንበርና አሰልጣኝ የሆንኩበት በዋናነት ይጠቀሳል:: በአትሌቲክሱ ዘርፍ የዓለምን ሪከርድ ከሰበርኩ 32 ዓመት ሆኖኛል:: ከአበበ ቢቂላ በስተቀር በዓለም ሪከርድ ታሪክ ማንም ባልተመዘገበበት ሰዓትና የአበበም ሪከርድ ነጮች ከወሰዱት 23 ዓመታት ከቆየ በኋላ የመጣሁ በመሆኔ ብዙዎች ያውቁኛል:: ይህ የሆነው ደግሞ በአትሌቲክስ ፌደሬሽን ከታቀፍኩ በኋላ ነበር::
የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሁኜ ሳለሁ የሲዳሞ ክፍለ አገር ገበሬዎች ስፖርት ማህበር በ 1974 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይደረግ የነበረውን የሲዳሞ ገበሬዎች ስፖርት ማህበርን በመወከል ግማሽ ማራቶንና 10 ሺህ ሜትር በመሮጥ ከብዙ ጉምቱ አትሌቶችና አሰልጣኞች ብዙ ልምድ ቀስሜ መመለሴና ኑሮዬ አዲስ አበባ መሆን እንዳለበት ማመን መቻሌ ይህንን እድል እንዳገኝ አድርጎኛል:: መጀመሪያ ፖሊስ ሰራዊት ውስጥ መቀጠሬም እንዲሁ ትልቅ አስተዋጽጾ ያደረገልኝ ጉዳይ ነው:: በ1976 ዓ.ም ለገዳዴ ማሰልጠኛ ገብቼም ጥሩ እውቀትም አቅምም ማግኘቴ ለዛሬ ማንነቴ ትልቅ ዋጋ ነበረው::
የፖሊስ ሰራዊት አገርአቀፍ ውድድር በሚደረግበት ጊዜም 10 ሺና 21 ኪሎ ሜትር ሦስተኛ ወጥቼ ስንመረቅ አስር አለቅነት ማዕረግ ተሰጥቶኝ በ 1977 ዓ.ም ትምህርቴን ማጠናቀቅ መቻሌም ብርታቴ ነበር:: ለስድስት ወር ያህልም አዲስ አበባ ፖሊስ ወንጀል መከላከል ላይ ከሰራሁ በኋላ በውጤቴ የተነሳ ወደ ኦሜድላ እንድዛወርና ስፖርት ዋና ጉዳዬ እንዲሆን ተደረገ:: ይህ ደግሞ የበለጠ ስፖርትን እንድወደውና የኑሮ መሰረቴ እንዲሆን አደረገው:: በተለይ በዚህ ጊዜ የአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ማራቶን ላይ ሳይፈቀድልኝ ሮጬ 13ኛ ደረጃን ይዜ 2 ሰዓት 28 ደቂቃ መግባቴ ብዙዎቹ ተስፋ እንዲጥሉብኝ አድርጓቸዋል:: እኔም ብሆን ወኔዬን እንዳሰባስብ ያገዘኝ ጊዜ ነው:: የብሔራዊ ቡድን አባል እንድሆንም የተደረገው ከዚህ በኋላ ነው::
ከአምስት ወር ልምምድ በኋላ ለሦስት አገራት አገርን ወክለው የሚሮጡ አትሌቶች ሲመረጡ ሰንዳፋ መስመር ላይ 30 ኪሎ ሜትር በቀን ይሮጥ ነበርና ያንን እያደረኩ ቆየሁ:: በፍጻሜውም ሰባተኛ በመውጣቴ አገሬን ወክዬ ቶኪዮ ላይ እንድወዳደር እድል ተሰጠኝ:: 2 ሰዓት ከ8 ደቂቃ ከ09 ሰከንድ በመግባት ሁለተኛ በመውጣት አዲስ ሰዓት ኢትዮጵያ እንድታስመዘግብ አድርጌያለሁ:: በ23 ዓመቴ የ23 ዓመት ታሪክ መመለስ ችያለሁ:: ሪከርድ የሰበርኩትና በቋሚነት ዓለም የያዘው በ80 ዓ.ም ሲሆን፤ ሆላንድ አምስተርዳም ከተማ ውስጥ ነው:: 2 ሰዓት ከ06 ደቂቃ ከ50 ሰከንድ የገባሁበትም ነበር::
አዲስ ዘመን፡– በንግግርዎት ላይ አገሬን የመጎብኘት እድል አላገኘሁም:: አሁን ነው እድል የተሰጠኝ ሲሉ ነበር:: ይህ ምን ማለት ነው፤ ለምን እንዳይጎበኙ ሆኑ ?
አትሌት በላይነህ፡– የከለከለኝ ነገር የለም:: ራሴ ሆን ብዬ ጊዜ አለመስጠቴና ለልምምድ ብዙ ሰዓት ከመስጠቴ የተነሳ አልተሳካልኝም:: ጊዜው ወደ ዝግጅቱ ብቻ ያደላ ስለነበርም ትምህርቴን እንኳን ከዘጠነኛ ክፍል ነው ያቋረጥኩት:: በሩጫ ምክንያት ብዙ አገሮችን የማየት እድሉ ገጠመኝ እንጂ ለጉብኝት የምሰጠው ጊዜ አልነበረም:: በተለይ ደረጃዬ ከፍ እያለ መምጣቱ ደግሞ አገሬ ውስጥ የመሮጥና አገሬን የማየቱን ሁኔታ ስላጠበበው በደንብ እንዳላውቃት ሆኛለሁ:: እንዳልጎበኛትም አድርጎኛል::
አሁን ባለው መልካም አጋጣሚ ባይባልም በተፈጠሩ መፈናቀሎች ምክንያት ብዙ ቦታዎችን ለማየት ችያለሁ:: እስከ ኮንሶ ድረስ ያሉ ቦታዎችን የመጎብኘት እድል እንዳገኝ ሆኛለሁ:: ባለፈው ዓመት ልጆቼን ጭምር በመያዝም የአገራችን ታሪካዊ ክፍል የሆነውን ሰሜንም በስፋት የማየት አጋጣሚውን አግኝቻለሁ::
አዲስ ዘመን፡- ብዙ ጊዜ ውጭ አገር አሳልፈዋል:: አሁንም ኑሮዎት በዚያ ነው:: ከአገርዎ ውጭ ሌላ አገር ለምን መረጡ፤ ምክንያቱስ ምን ነበር?
አትሌት በላይነህ፡– በአገር ደረጃ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ብዙ ችግሮች ነበሩ:: በተለይ የፖሊስ ሰራዊት ውስጥ ስለነበርኩና ያም ስለፈረሰ በአገር ውስጥ መቆየቱ ትልቅ ፈተና እንደሚሆንብኝ አምኛለሁ:: ተቋማት በሙሉ ስጋት ውስጥ ነበሩ:: ዘራፊም ጭምር ተበራክቶ ነበር:: እንደውም ብር አምጣ እያሉ ያስፈራሩኝ የነበሩም እንደነበሩ አስታውሳለሁ:: ቤቴም በቦንብ ጋይቷል:: ስለዚህም በዚህ ችግር ውስጥ አገር ውስጥ መቆየቱ ፈታኝ ነበርና ወደ ጃፓን አቀናን:: ነገር ግን በጃፓንም የመሬት መንቀጥቀጥ በመነሳቱ ወደ አገር ተመልሰን ነበር:: ሆኖም ብዙ ሳንቆይ ወደ አሜሪካ ለውድድር ስሄድ ልጆቼ እንዲማሩ በማሰብ እዚያ የምኖርበትን ነገር አመቻቸሁ::
አሁን በአሜሪካ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እያሰለጠንኩና አገሬ በምትፈልገኝም በኩል እየተሳተፍኩ ኑሮዬን እየመራሁ እገኛለሁ:: ግን አንድ ነገር መረሳት የለበትም:: ከአገር በላይ ማንም እንደማይሆን:: አማራጮችን አግኝቶ መሄድና አገርን መተው የተለያዩ ናቸው:: ስለዚህም አገሬን ሳይሆን የተውኩት አማራጮችን ለመጠቀም ነው የሄድኩት:: አገሬ ሁሌም ከእኔ ጋር ናት:: በፈለገችኝ ጊዜም ለእርሷ አለሁ::
አዲስ ዘመን፡– የቶኪዮ ኦሎምፒክን እንዴት አዩት?
አትሌት በላይነህ፡– ይህ ኦሎምፒክ 2020 የሚደረግ ነበር:: ሆኖም በኮሮና ምክንያት እንዲራዘም ሆኗል:: ነገር ግን ስያሜው አልተቀየረም:: የ2020 ኦሎምፒክ በሚል ነው የተዘጋጀው:: ኦሎምፒክ የሚካሄደው ሁል ጊዜ ሙሉ ዓመት ላይ ነው:: በመሆኑም የዘንድሮው በሙሉ ዓመቱ ተሰይሟል:: ይህ ኦሎምፒክ እንደ ባለፉት ዓመታት የሞቀ ሊሆን አይችልም:: ምክንያቱም አጠቃላይ ጎብኚዎች በዚህ ዝግጅት ላይ ነጻ በሆነ መልኩ እንዲገቡ አልተደረገም:: ደህንነት ስለሚቀድም:: ስለዚህም ወሳኝ ሰዎችና ስፖርተኞች ብቻ ናቸው እንዲገኙ የተፈቀደው:: ይሁንና እነዚህ ሁኔታዎች ባሉበትም ቢሆን አትሌቶቻችን ከምንም ጊዜ በተሻለ መልኩ የተዘጋጁበት ጊዜ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል:: ለስምንት ወር ያህልም ዝግጅት አድርገዋል::
በአሰልጣኝነትም ሆነ በሰልጣኝነት ለኦሎምፒክ ዝግጅት ስናደርግ ይህንን ያህል ጊዜ ተሰጥቶ አያውቅም:: ስለዚህም የአየር ሁኔታው ጥሩ ከሆነ አትሌቶቻችን ባደረጉት በቂ ዝግጅት የተሻለ ውጤት ያመጣሉ ብዬ አስባለሁም:: ሙሉ ግምት ለመስጠት አሰልጣኝም ሆነ አብሬያቸው አልነበርኩምና አልችልም::
አዲስ ዘመን፡- የእርስዎ ቤት በቦንብ ሲመታ ዋና መሪው ማን ነበር?ፖለቲካዊ ተጽዕኖስ አለው ብለው ያምናሉ?
አትሌት በላይነህ፡- በዚህ ጉዳይ ላይ ይህ ነው የምልበት ነገር የለም:: ምክንያቱም እርግጠኛ አይደለሁም:: ነገር ግን በጊዜው የጸጥታ ችግር እንደነበር እሙን ነው:: ስለዚህም ከሌሊቱ ሁለት ሰዓት ላይ በቦንብ ተመታ:: ሁላችንም ቤት ውስጥ ነበርን:: ነገር ግን የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖ ምንም ሳንሆን ወጥተናል:: ይህ የሆነው ደግሞ በቀጥታ ቤቱ ላይ ቦንቡ አለማረፉ ነው:: ጊቢ ውስጥ ያለው መናፈሻ በጽዶቹ አማካኝነት ሃይሉን በመውሰዳቸው ቤቱ ላይ የደረሰው ፍንጥርጣሪው ነው:: በዚህም መዳን ችለናል:: ይሁን እንጂ ቤቱም ሆነ በጊቢው ውስጥ የሚገኝ ንብረት ግን ምንም አልተረፈም:: ሚኒባስ መኪናችን ሳይቀር አመድ ሆኗል::
በሰዓቱ ወዴትም የሚኬድበት ስላልነበር በፈራረሰ ቤት ውስጥ ቁጭ ብለን ያለቀስነውን መቼም አልረሳውም:: ምክንያቱም እንኳን ተረፋችሁ የሚል እንኳን አልነበረም:: ሁለት አመራሮች መጥተው ስለ ቦንቡ ሁኔታ አወሩ እንጂ ምንም አይነት የመፍትሄ አቅጣጫ አላመላከቱንም ነበር:: ምንም አይነት አማራጭ አልሰጡንም:: ይልቁንም የነበረው ቦታ ሁሉ ተወስዷል:: በነበረችኝ ብር ነው ሌላ ቦታ ገዝቼ ቤት እንኳን የሰራሁት::
አዲስ ዘመን፡– ህወሓት ሲገባ ጀምሮ በአገር ላይ እስካሁን ድረስ ባደረሰው ችግር ምክንያት በአሸባሪነት እንዲፈረጅ አድርጎታል:: እናንተ እንደ ሰላም ጓድ በዲያስፖራው በኩል ወደ አገር ተመልሳችሁ የኢትዮጵያን እውነታ ወደ ዓለም ለማድረስ እየተጓዛችሁ እንደሆነ ይታወቃል:: የእስካሁኑ ጉዟችሁ ምን ይመስላል? እውነታውንስ ካያችሁት አንጻር እንዴት ይገመግሙታል?
አትሌት በላይነህ፡– እዚህ በመምጣታችን ብቻ ሳይሆን በነበርኩበት ጊዜም ማለትም ከ17 ዓመት በፊት አገሬ ነበርኩና የሚሰራውን አሻጥር በደንብ አውቀዋለሁ:: የፖሊስ መኮንን በመሆኔም ሁሉ ቦታ ይመለከተኛል:: ስለዚህም ግምገማዎች ላይ እሳተፋለሁም:: በመሆኑም የሚሰራውን ነገር በሙሉ የማየቱ አጋጣሚ በስፋት አለኝ:: ገና ኢህአዴግ ከመግባቱ ጀምሮ እያንዳንዱ ነገር ከእኔ የተደበቀም ነው ለማለት እቸገራለሁ:: እናም የሚሰራው ሥራ ኢፍትሀዊ እንደሆነ መመስከር እችላለሁ::
ፍትሀዊ ያልሆኑ ነገሮች በዝተው ሲታዩ አንዳንዴ እስከመጋፈጥ የደረስኩባቸው ጊዜዎች ብዙ እንደነበሩ አስታውሳለሁ:: በእርግጥ ጊዜው እውነት መናገር የማይፈለግበት ጊዜ ነው:: ይሁን እንጂ መጠን ሲያልፍ ከአቅም በላይ ይሆናልና እንደእኔው ብዙዎች ደፍረው ይናገሩ ነበር:: ኢትዮጵያዊነታቸው ያሸነፋቸው ሁሉ ተቃውሟቸውን ያሰሙም ነበር:: ለእኔም ኢትዮጵያዊነት እያንዳንዱ ነገር በፍትሀዊነት ሲከወን ማየት ነውና ከመታገል ወደኋላ አልልም ነበር:: ኢትዮጵያዊነት አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀይ ባንዲራዋ በአትሌቱም አካባቢ ጎላ ብሎ እንዲታይ መፈለግን ያነገበ ነው:: ይሁን እንጂ ብዙዎች የተደሰቱበት ጊዜ አልነበረም:: ምክንያቱም ጥቅም ይቀራል:: እውነት ጎልቶ ውሸት ይኮመሽሻል:: እናም በእኔ ላይ ብዙ ተጽዕኖዎች ይደረጉብኝ ነበር::
አትሌትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ስለሆንኩ እንጂ ከዚህም በላይ ከፍተኛ ችግር ይደርስብኝ እንደነበር አስባለሁ:: ያልገለጽኳቸው ብዙ ነገሮችም በህይወቴ ላይ ደርሰዋል:: ለምሳሌ እነርሱ ሲገቡ ከሚኒስትሮች ጋር በመከላከያ ተይዤ ታስሬያለሁ:: ይህ የሆነው ደግሞ ዋና ተልዕኳቸው ስለነበር ነው:: የአገር ባንዲራ እያለ የሚጮህ አይፈለግም፣ እኔ እንድያዝበት የሆነው ምክንያት ይህ ነው:: ሆኖም መሸፈኛው ሌላ ሆኖ ብዙ ችግር ይደርስብኝ ነበር:: በህይወቴ ላይ ጭምር ብዙ ነገሮች መጥተዋል:: ነገር ግን የእግዚአብሔር ጥበቃ አይሎ ልለቀቅ ችያለሁ:: ይህ የሆነው ደግሞ አገር በመውደዴ ብቻ ነው::
በግምገማ ደረጃ ሲወራ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በእኩል በማየት አድርጉ ነው:: ነገር ግን በሥራ ከዚህ የተለየ ማድረግ ነው የሚፈቀደው:: አድርጉ የተባለውን የሚያደርግ ሁሉ ተጠያቂ ይሆናል:: በተለይም አገር ወዳድ ሰው በብዙ ነገር ይፈተናል:: ሆኖም ማንም ሰው ቢሆን መቼም ቢሆን ከእውነት ሊያፈነግጥ አይገባም:: እኔም ማንም ቢመጣ እውነትን እንጂ በውሸት ልራመድ አልፈልግም:: እውነትን ይዞ ለተሰለፈው አካል እደግፋለሁ:: እውነትን መደገፍ ደግሞ ፖለቲካ ወይም መንግስትን መደገፍ እንዳልሆነ ሁሉም ሊረዳው ይገባል::
አሁን ከተጠየቁት አንጻር ለማንሳት ያህል ያየሁትን፣ የሰማሁትን መሰረት አድርጌ ጥቂት ለማለት ልሞክር:: ባለሁበት ጊዜም የነበረውን ጭምር ማንሳት እወዳለሁ:: ህዝብ እስካሁን ለውጥ እስኪመጣ ድረስ እየጮኸ ፣ እያለቀሰ፣ እየሞተና እየታሰረ ነበር ያለው:: አሜሪካ ከሄድኩ በኋላ በተለያዩ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ ተሳትፌም በአገሬ የሚሆነውን ስቃወም ነበር:: ጥቁር እየለበስኩ ጭምር ለአገሬ ድምጼን ሳሰማ ነበር:: ለውጥ ከመጣ በኋላ መንግስት ያለፈው አልፏል በሰላም በፍቅር ወደ እርቅ እንምጣና አገራችንን እናሳድግ በማለት ብዙ ለፍቷል፤ ሰርቷልም::
የኢህአዴግ መንግስት ወይም ወያኔ ሰላም እንዲፈጠር አልፈለገም:: ለዚህም ማሳያው መንግስት አንድ ላይ እንስራ ብሎ በስንት ትግል ለመስማማት ሲሞክር እንቢ ማለቱ፣ የአገር ሽማግሌዎች ሳይቀር ተልከው ስምምነት እንዲደረግ መለመኑና እናቶችም ቢሆኑ መሬት ጭምር ተደፍተው ይህንን ሰቆቃ እናቁም ሲሏቸው አይሆንም ሆነ መልሳቸው:: ከዚህ በላይ እነዚህን በምን መንገድ ማሳመን ይቻላል? እንደ እኔ ምንም ምርጫ የማይሰጥ ጉዳይ ነበር:: እነርሱ የያዛቸው ትእቢት ነው:: ዓለምም ሆነ አገር የሚያውቀው እንቢተኝነት የተጠናወታቸው ናቸው:: ጦርነት ጭምር ከፍቶ የአገር ጠበቃ የሆነን መከላከያ መምታት ከትዕቢት ውጪ ምን ሊባል ይችላል?
ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ኢትዮጵያውያንን ለያውም አብሮ ጠጥቶና አብሮ በልቶ የኖረን ሊገል ይችላል? ለአገር የሚሞትን ራሳችን ነብሱን መንጠቅ ፣ ከቤተሰቡ ተነጥሎ ዘመናትን የኖረ እንዴት በጦር ይወጋል? ይህ እንደእኔ መግለጫ ቃላት የለውም:: የትም ዓለም ላይ ሆኖ የማያውቅ ድርጊትም ነው:: ልብ ሰባሪ ተግባርም ነው:: እኔ የምኖርበት አሜሪካ ለአንድ አፍታ መከላከያ ቢጠቃ አሜሪካ ዙሪያዋን ዘግታ ነው አድራጊውን የምትቀጠቅጠው:: እናም መከላከያን መውጋት ማለት የኢትዮጵያን ህዝብ መውጋት ማለት ነው:: መከላከያ ስላለ ነው ህዝቡ በሰላም ወጥቶ የሚገባው:: እርሱ ከሌለ ግን የማንም አሽከርና ምርኮኛ ወይም ነጻነት ያጡ ህዝቦች ሆነን እንኖራለን::
ኢትዮጵያ ነጻነቷን ጠብቃ ጦርነቱ ዓለም ማለትም ከአድዋ ጀምሮ ባሉት ድሎች የቆየችው እነዚህ አይነት አገር ወዳድ ሃይሎች ስላሏትና መከታ ስለሆኗት ነው:: ይሁን እንጂ ዛሬ ከራሳችን የወጡት አብረን በልተን፣ አብረን ኖረን ጠላት ሆነው እኛን መልሰው የሚወጉት ሰዎች እጅግ የሚያሳዝኑ ናቸው:: ኢትዮጵያዊ ናቸውም ለማለት እቸገራለሁ:: በእርግጥ የትግራይ ህዝብ ኢትዮጵያዊነቱን የሚያከብር ሰው እንደሆነ ጥርጥር የለኝም:: ነገር ግን ወያኔ የትግራይን ታሪክ ፣ የትግራይን ህዝብ የሚያሳፍር ተግባር ሰርቶ አሳፍሮታል:: አሸማቆታልም:: የአድዋን ታሪክ ጭምር ያስመሰከሩ አባቶችን ጭምር ነው ያዋረዱት::
እኔ ፖለቲከኛም የፖለቲካ ደጋፊም አይደለሁም:: አንድ ንጹህ ኢገትዮጵያዊ አገሬን አጥብቄ የምወድ ግለሰብ ነኝ:: ስለዚህም ስለአገሬ ይመለከተኛል:: ሁሉም ኢትዮጵያዊ የአንድ ፖለቲካ ወይም መንግስት ደጋፊ መሆን ሳይጠበቅበት የአገሩ ጉዳይ ይመለከተዋልም:: ምክንያቱም ለፖለቲከኛ ብቻ የተሰጠ አገር የለም:: አገር የሁሉም የሚኖርባት ሰው ነች:: ስለዚህም ለአገሬ የሚለው አንድ ነገር ይኖረዋል:: እኔም ጸሐይ ፣ ሀሩር ውርጭ ሳልል ሮጬ የአገሬ ባንዲራ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ እፈልጋለሁ የምለው አገሬን ስለምወድና ስለ እርሷ ስለሚመለከተኝ ነው:: ሁሉም በሙያው ይህንን የሚያደርገውም ከዚህ የተለየ ነገር ኖሮት ነው የሚል እምነት የለኝም:: ሆኖም እንደ ወያኔ አይነቱ አገሬ ኢትዮጵያ እያለ አገሩን መልሶ የሚወጋ አገር ጠል አካል አላየሁም፤ አልሰማሁምም::
መሪ ሆኖ ተቀምጦ ብዙ ችግሮቿን ተጋርቶ ዋናውን አካል እኔ ካልመራሁ ብሎ መግደል እጅግ አሳፋሪና የወራዳ ተግባር ነው:: አጋጣሚ አላገኘም እንጂ እኛንም ገሎናል፣ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ዳድቶት ነበር:: ኢትዮጵያን እናፈርሳለን ሲልም ኢትዮጵያ አለመሆኑን ያረጋገጠ አካል ስለሆነ ከምድረገጽ ማጥፋት ያስፈልጋል:: ግን አንድ ነገር ማንሳት እፈልጋለሁ:: ወያኔ ኢትዮጵያ ትፍረስ እንዳለ ሁሉ የትግራይ ህዝብም ይህንን ይፈልጋልን? ካልፈለገ ዛሬ ከእርሱ ባርነት የሚወጣበትን መንገድ መቀየስ አለበት::
ይህ ሃይል በህግ የሚፈለግ ነው:: ወጣቶችንና በጣም ልብ የሚሰብረውን ህጻናትን እያሰለፈ ለጦርነት እየማገደ ነው:: ከሰሜን አሜሪካ የመጣው የሰላም ጓድ ሁሉ ዛሬም ነገም የትግራይ ህዝብ፣ አባቶች፣ ምሁራኖች ኢትዮጵያዊ ፍቅራቸው የጠነከረ ነው ብለን ስለምናምን እንዲያስቆሙት እንጠይቃለን:: ሰላም ወዳዱና ንጹሁ ህዝብ ከዚህ ችግር እንዲወጣም ጫና ማሳረፉ የህዝቡ ሃላፊነት ነውና አሁንም አልረፈደም እላለሁ:: እንደ ድሯችን በፍቅር የምንጓዝበትን መንገድ ጠርገን በህግ ተጠያቂ መሆን ያለባቸውን ለህግ አቅርበን መጓዝ እንድንችል ማድረግ ይኖርባቸዋል:: በጦርነት ማንም አይጠቀምም:: ከሁለቱም ወገን ኢትዮጵያዊ ነው የሚያልቀው::
አዲስ ዘመን፡– ለውጡ ሲመጣ በግልጽ የታየ ስደትና ሞት አለ ይባላል:: ይህ በሦስት ዓመታት የተጠነሰሰ ነው ወይስ ቀደም ብሎ የነበረ?
አትሌት በላይነህ፡– በፍጹም በሶስት ዓመታት ውስጥ የመጣ አይደለም:: ረጅም ዓመታት የወሰዱና በሴራ ፖለቲካ ጥንስሳቸው የፈላ ነው:: በሥራ ጭምር የተረጋገጡ ናቸው:: የእግዚአብሔር ቃል እንደሚለው ሰው የዘራውን ያጭዳል:: ስለዚህም አንድ ነገር ሊታይ የሚችለው ዘሩ ሳይሆን የበቀለው ነውና አሁን እያጨድንም ሆነ እያየን ያለነው የተዘራው በቅሎ ነው:: ክፉ ዘሩ ደግሞ ህዝቡን ነቅሎ በሚያጠላው ላይ የተመሰረተ ሲሆን፤ ብሔርተኝነትን በዋናነት ይዟል:: ከዚህ ቀደም ለጥቅም ብቻ የተማረው አካል ይከፋፈል ነበር:: ወያኔ ሲመጣ ግን የተለየ ክፉ ዘር በመዝራቱ ተከፋፍሎ የማያውቀው ህዝብ ተከፋፍሎ ውጣልኝ መባባል እንዲጀምር አደረገው::
አሁንም ቢሆን ከላይ በአለው አመራር ሳይሆን ኢትዮጵያ የቆመችው በአምላክ እገዛና መልካም በሚያስቡ ህዝቦቿ አማካኝነት ብቻ ነው:: የሃይማኖት አገር በመሆኗ ፈጣሪ ጠብቋት ነው:: ህዝቡ ዘንድ አሁንም መልካምነት እንዳለ ይሰማኛል:: ምክንያቱም ክፉ እንዳይነካ መጠባበቁ አለ:: ይሁንና ስልጣንና ጥቅማቸው የተነካባቸው እየተኙለት አይደለም::
አዲስ ዘመን፡– ኢትዮጵያ ህወሓትን አሸባሪ ብላ ፈርጃለች:: አሸባሪን የምትጸየፈው አገር አሜሪካ ግን የህወሓት ደጋፊ ስትሆን ይታያል:: ምክንያቷ ምንድነው ይላሉ? ኢትዮጵያ አልሸባብን በመዋጋት ጭምር ትልቅ አስተዋጽጾ እያላት መጫኗስ ለምን ይሆን?
አትሌት በላይነህ፡– ጥያቄው በጣም ተገቢነት ያለው ነው:: ሁላችንም እኛ እንደ ሰው የምናስበው አሜሪካ የዴሞክራሲ አገር ምሳሌ ነች ብለን ነው:: የአሜሪካ ህዝብ ትልቅ ህዝብ ነውም:: የት ነህ፣ ከየት መጣህ የማይባባልም ነው:: በህግ የሚኖሩ ህዝቦችም ናቸው:: በአገርነት ደረጃም አሜሪካ ትልቅ አገር ናት:: የቀደሙት መሪዎች እግዚአብሔርን የሚፈሩና የሚጸልዩ ነበሩ:: በብርና በደረሱበት ቴክኖሎጂ ሳይሆን በእግዚአብሔር የሚተማመኑ ናቸውም:: ይህ ደግሞ ታላቅነትን ሰጥቷቸው ከርሀብ ለሌሎች ደራሽ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል:: አሁን ግን ብዙ ነገሮች እየተበላሹ እንዳሉ ይሰማኛል:: በተለይም በመሪዎች ደረጃ::
አገሪቱ ትልቅ ብትሆንም መሪዎቿ ግን ትልቅ አልሆኑም:: በፖለቲካ ዲፕሎማሲ የወረደ አሰራር ላይ ይገኛሉም:: ለምሳሌ ጆባይደንን ስንመርጥ ምክንያት ነበረን:: ትራንፕ ከግብጽ ጋር አብሮ ኢትዮጵያን ያልሆነ ቦታ ላይ አስቀምጧታል:: በዚህም ዋሺንግተን ብቻ ያለው 300 ሺህ ኢትዮጵያዊ ትራንፕን እንዳይመርጥ ሆኗል:: ብስለት ማጣት፣ ጥበብ ማጣትና ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎችን በቅንነት አለመስራት ብዙ ነገሮችን የተሳሳተ ቦታ ላይ እንድናገኛቸው ያደርገናል:: በትራንፕ ላይ ውሳኔ ያስወሰደንም ይህ ነበር:: ባይደንም ሲመረጥ ዲሞክራት ይሆናል ብለን ነበር:: ነገር ግን ያልጠበቅነው እየሆነ ይገኛል:: አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያዳያን የተሳሳተውን ለመመለስ ተነስተዋል::
ዲሞክራትነት በምን የሚለውንም መለየት ያለብን ይመስለኛል:: ይህ ሥርዓት ሁላችንንም ያሳዘነና ልባችንን የሰበረ ነው:: 110 ሚሊዮን ህዝብን ትቶ ሽብርተኛ የተባለ ቡድንን መደገፍ አሳፋሪ ነው:: ለዘመናት ከኢትዮጵያ ጋር የነበረውን ዲፕሎማሲ ግንኙነት የሚያበላሽም ነው:: ጥቁር ነጥብም የጣለ ተግባር ከውነዋል:: ስለዚህም ኢትዮጵያ ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች በተግባር ወደፊት የምናሳያቸው ይሆናል:: ድህነታችን እንጂ ከአሜሪካ የምናንስበት ምንም ነገር የለም:: ነገ ደግሞ በብልጽግናው ዓለም ይህንንም መሻገር እንደምንችል በሚገባ የምናሳይበት ጊዜ እሩቅ አይደለም::
ኢትዮጵያ ማንንም አትገፋም:: ገፍታም አታውቅም:: የሰው ድንበርም አትነካም:: ሌሎችን ትደግፋለችና ትንከባከባለች እንጂ:: ክብራቸው እንዳይነካም ከእርሷ መደረግ ያለበትን ሁሉ የምታደርግ አገር ነች:: በነጻነቷ ግን መደራደር አትችልም:: ምክንያቱም ዛሬ ድረስ የኖረችበት ታሪኳ ነው:: ለዚህች አገር ይህንን ሁሉ ጫና ማድረግና ማዕቀቦችን መጣል ምን እንደሚፈልጉ ለመረዳትም የሚያስቸግር ነው:: ምንም የገባን ነገርም የለም:: ቦታ የሌላቸው፣ መንግስት የሌላቸው ፣ የኢትዮጵያ ፓርላማ ሽብርተኛ ብሎ የፈረጀውን አካል መደገፍና ከእነርሱ ጋር መቆም እንደ ትልቅ አገርነቷ በጣም አሳፋሪ ተግባር ነው:: አሁንም የምለው በተለይም የባይደን መንግስት ደግመው ደጋግመው የኢትዮጵያን ጉዳይ ሊያስቡበት ይገባል ነው:: ዜግነት ቢኖረኝም አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምታደርገውን ፍትሀዊ ያልሆነ ነገር ልታቆም ይገባል የሚለውን ከመቃወም ወደ ኋላ አልልም::
አዲስ ዘመን፡– አሜሪካን ጨምሮ ሌሎች አገራት በኢትዮጵያ ላይ ተነስተዋል:: በተለይም ከህዳሴ ግድቡ ጋር ተያይዞ:: ይህንን ችግር ለመፍታት ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
አትሌት በላይነህ፡– ኢትዮጵያ በብዙ ችግር ውስጥ ሆና አሁንም ለማደግና ለመለወጥ እየሰራች ያለች አገር ነች:: ምድሪቷን በብዙ ነገር ለምለም ለማድረግም እየተጋች ነው:: ይህንን እንዳታደርግ ደግሞ ማንም ሊገድባት አይችልም:: ምክንያቱም ማደግ መብት ነው:: ይሁን እንጂ ይህ እንዳይሆን ብዙ አገራት እየፈተኗት ይገኛሉ:: እናም እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በዋናነት መደረግ አለበት የምለው ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ ኢትዮጵያዊነቱን ያጠንክር ነው:: ለዚህ ደግሞ አንድ ሆኖ መቆም ከምንም በላይ ያስፈልጋል::
ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተያይዞ ለህዳሴው እውን መሆን የሚሰራ ከሆነ፤ የአገርን ሰላም የሚያረጋግጥበትን መስመር ከያዘ ማንም ምንም አይነት ጫና ቢያደርግም ዳግማዊ አድዋ ሩቅ አይሆንም:: አምላክም ያግዘናል:: ኢትዮጵያዊ መሆናችንን ስናምን ኢትዮጵያን ከችግሮቿ ሁሉ ማላቀቅ እንችላለን:: አሁን አገራችን ያለባት ችግር የፖለቲካዊ ጥያቄ የምንጠይቅበት አይደለም:: ጥያቄው የማደግ፣ የሰላምና ኢትዮጵያን የመጠበቅ ጉዳይ ብቻ ነው:: እንደግለሰብ አሁን አገሬ ምን ያስፈልጋታል፣ ምንስ ማድረግ እችላለሁ ብሎ አስቦ ወደተግባር የሚገባበት ጊዜ ነው:: ስለሆነም ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ ለአገሩ የሚጠበቅበትን ማድረጉ ብቻ ነገሮችን ቀላል ያደርጋቸዋል::
አዲስ ዘመን፡– ስለሰጡን ማብራሪያ እጅግ አድርገን እናመሰግናለን::
አትሌት በላይነህ፡– እኔም አመሰግናለሁ፤ ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ::
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 27/2013