የዘንድሮው ክረምት ብርዱ ከበድ ያለ ነው። የብርዱ ክብደት አንዳንዶችን በንቃት እና በትጋት አቃፊ እንዲፈልጉ አያረጋቸውም ተብሎ አይገመትም። እርግጥ ብርዱ አንዘፍዝፏቸው አቃፊ እየፈለጉ ያሉት በዋነኝነት ላጤዎች እንደሆኑ የታወቀ ነው።
ባለትዳሮች ወይም ወላጆችንም ብርዱ እያንዘፈዘፋቸው ነው። ከላጤዎቹ ባይብስ። ብርድ ብርድ ያሰኛቸው ግን አየሩ ብቻ አይደለም፤ አየሩ ወቅቱን ጠብቆ የመጣ ስለሆነ በዘዴ ይይዙታል። ብርድ ብርድ ያላቸው ልጆቻቸውን በግል ትምህርት ቤት የሚያስተምሩትን ነው፤ ብርዱ ደግሞ የትምህርት ቤት ክፍያ ጭማሪ ጉዳይ ነው።
አምና በኮቪድ ምክንያት ክፍያ ላለመጨመር ተስማምተው የነበሩት የግል ትምህርት ቤቶች የዘንድሮው የትምህርት ዘመን ገና በወጉ ሳይጠናቀቅ አጀንዳቸው የክፍያ ጭማሪ ሆኗል አሉ። አሁን በወላጆቹ እና ትምህርት ቤቶቹ አካባቢ የሚዞረው መረጃም ይሄው ጉዳይ ነው። ወላጆች በእጅጉ ፈርተዋል። ግራ የገባቸውም ጥቂት አይደሉም።
እዚህ ላይ ትምህርት ቤቶቹን በኮሮና ወቅት ስለፈጸሙት ሃላፊነት የሚሰማው ተግባር ሳላመሰግን አላልፍም። ከኮሮና ጋር ተያይዞ ለወራት መዘጋታቸውን ተከትሎ ክፍያ ቆሞ በነበረ ጊዜ ጥቂት የማይባሉት የግል ትምህርት ቤቶች የህልውና አደጋ ተጋርጦባቸው ነበር። የተቋማቱ ህልውና የቀጠለው መንግስት አቅጣጫ ማስቀመጡን ተከትሎ ከወላጅ ኮሚቴዎች ጋር በተደረገ ምክከር ነው ማለት ይቻላል።
አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ አሁን ሊደረግ የታሰበው ጭማሪ ትንሹ 20 በመቶ ገደማ ይመስላል። አብዛኛው ጭማሪ ከዚያ በላይ ነው ይባላል። አንዳንዶቹማ በቁጭት የአምናውንም ጭማሪ ጭምር ታሳቢ ያረገ ጭማሪ የሚያደርጉ ይመስላሉ ሲሉ ሰምቻለሁ።
ትምህርት ቤቶቹ ለምን ይህን ያህል ጭማሪ ሲባሉ “መምህራን ደሞዝ ይጨመርልን እያሉ ናቸው›› ይላሉ፤
ምሁራኑ በበኩላቸው “እኛ ምን እናርግ ኑሮ ተወደደ” እያሉ ናቸው። ኑሮን አስወደዱ የተባሉት ነጋዴዎች ቢጠየቁ ደግሞ “እኛ ምን እናርግ የልጆቻችን ትምህርት ቤት ጨመረ” ሊሉ ይችላሉ።
ትምህርት ቤቶቹ በድጋሚ ሲጠየቁ “የትምህርት ቤት ህንጻ ኪራይም ጨምሮብናል” ሲሉ ያብራራሉ። አከራዮች ሲጠየቁ “እኛ ምን እናርግ ኑሮ ሰማይ ነካ” ይላሉ። ኑሮን ሰማይ አስነኩ የተባሉት ነጋዴዎች በድጋሚ ሲጠየቁ “እኛስ ምን እናርግ ፤እቃ ተወደደ” ሲሉ ይመልሳሉ። እቃ አስወደዱ የሚባሉት ሲጠየቁ “ምን እናርግ ዶላር ጠፋ” ይላሉ። ዶላሩን የያዘው መንግስት ሲጠየቅ “እኔ ምን ላርግ ስግብግብ ነጋዴዎች ዶላሩን በጥቁር ገበያ እየሰበሰቡ ባንክ ውስጥ አልገባ አለ” ይላሉ። መንገዱ ሁሉ መውጫ የሌለው አዙሪት ነው።
ይብላኝ ለደሞዝተኛው፤ 30 ቀናት ጠብቆ አንዲት ደሞዝ ለሚበላው። እሱ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ አይችልም፤ ደሞዙ ባለበት የቆመ ነው። ገቢው አንዲት ስንዝር ከፍ ሳትል ወጪው 42 ኪ.ሜ ሮጦ ጨርሷል፤ ማራቶን።
ልጆቹን በግል ትምህርት ቤት የሚያስተምረው የመንግስት ሰራተኛም የትምህርት ቤት ክፍያ ጭማሪውን ምክክር መርዶ ሰምቶታል። ይህ ጭማሪ በሁለት ወይም በሶስት ልጅ ከተሰላ ነገሩ ኡ…ኡ…ኡ… ኡ ያስብላል። ይሄን ደግሞ ከጤፍ ዋጋ መጨመር፤ ከእንቁላል ዋጋ መናር፤ ከዘይት በገበያ ተፈልጎ አለመገኘት፤ ከስጋ የቅንጦት ምግብ መሆን ወዘተ…ጋር ደማምረው ሲያሰሉት አለም በቃኝ የሚያስብል ይሆናል።
ገና እኮ ደግሞ የቤት ኪራይ ጭማሪም አለ። የወሩን ስትከፍል አከራይህ ፈገግ ብለው ይጠብቁሃል። ”ያለወትሮአቸው ፈገግታ ያበዙት ምን አግኝተው ነው” ስትል ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ 400 ብር እንደተጨመረብህ ያረዱሃል። ምክንያቱስ? ምክንያቱማ የልጆች የትምህርት ቤት ክፍያ መጨመሩ ነዋ። አልጨምርም ማለት አይደለም ካንገራገርክ በዚህ ክረምት ሌላ ቤት ፍለጋ ይጠብቅሃል። እሱ ደግሞ የሚሆን አይደለም። እሺ ካልክ የወጪ መዝገብህ ከአቅምህ በላይ ሊሆን ነው። እንዲሁ እየተወዛገብክ እዳህን ተረክበህ ትመለሳለህ። በዚህ ተናደህ ብስጭትህን ለማብረድ አንድ ሁለት ልበል ብትል እንኳን የድራፍት ዋጋም ጨምሯል። እንግዲህ የት ታኮርፍ?
እንግዲህ ከወጪዎችህ የአንዱ የትምህርት ቤት ክፍያ መጨመር ነው የቀረውን የጭማሪ ናዳ የሚስከትልብህ። እና ምን ተሻለ? ተያይዘን ኑሮአችንን ሲኦል ከምናደርገው ትንሽ ብንተሳሰብ እና ጭማሪውን በልክ ብናደርገው ነው የሚሻለው።
እውነቱን ለመናገር የግል ትምህርት ቤቶች ጭማሪ ሙሉ ለሙሉ ህገወጥ ነው ማለት አይቻልም። ለምሳሌ የቤት ኪራያቸው በ10ሺ፣ የመምህራን ደሞዝ በ25 ሺ የትምህርት ግብአቶች ወጪ በ15ሺ ሊጨምር ይችላል። ችግሩ ያለው ይሄ ጭማሪ ወደ ወላጅ የሚያከፋፍሉበት መንገድ ላይ ነው። 50ሺ ብር ጭማሪ ቢያጋጥማቸው እነሱ ግን በእያንዳንዱ ወላጅ ላይ የሚያደርጉት ጭማሪ ቢደመር ከ100ሺ በላይ ይሆናል። ታዲያ ይሄ አግባብ ነው? በፍጹም።
አንዱ አንዱ እያየ ይጨምራል፤ የተወሰኑት ደግሞ ብር መጨመር ትምህርት ቤቱን ምርጥ ትምህርት ቤት ያስመስልልናል ብለው የሚያምኑ ናቸው። ብቻ በዚያም አለ በዚህ የዋጋ ጭማሪ አድርገናል ለማለት ምክንያት አያጡም። የትምህርት ቤቶቹ ጭማሪ የገበያ ግርግር ለሌባ ያመቻል እንደሚሉት እንዳይሆን እሰጋለሁ። በዚህ አጋጣሚ የህዝቡን ኪስ ለማራቆት የሚሰማሩት።
የሕንጻ ኪራይ ዋጋ መጨመርን እንደ ዋና ምክንያት የሚጠቅሱም አሉ። እሱ ምክንያት ሊሆን ይችላል፤ ዋናው ግን ላይሆን ይችላል፤ ምክንያቱም የራሳቸው ህንጻ ያላቸውም ከጭማሪው እጃቸውን ሲሰበስቡ አልታዩማ።
ደሞ ሌላ የሚያስገርመው ነገር የትምህርት ቤት ጭማሪ የሚያስከትለው ተቀጣጣይ የዋጋ ጭማሪ የትምህርት ቤት ክፍያ የጨመሩትንም ያስጨመሩትንም የሚጎዳ መሆኑ ነው። ለምሳሌ ለዋጋ ጭማሪው መንስኤ ሆኖ ሁሌ ከፊት ከሚቀርቡት ምክንያቶች አንዱ የመምህሩ ደሞዝ ነው። ከዚያ የዋጋ ጭማሪ ተደርጎ መምህሩ ደሞዙ ላይ ተጨማሪ 500 ወይ 700 ብር ገብቶለት ይሆናል። ነገር ግን የሱን ደሞዝ ከፋይ የሆኑት የቤት አከራዩ፤ ባለሱቁ፤ ባለ ምግብ ቤቱ ወዘተ.. እነሱ በምላሹ የዋጋ ጭማሪ ያደርጉና መምህሩ ኪስ የገባችው ሰባት መቶ ብር ገቢ ዘጠኝ መቶ ብር ወጪ ሆና ትሸኛለች።
ነገሩ አንደ ሀገራችን የብድር ጉዳይ ነው። ከአሜሪካ ወይም ከአውሮፓ 500 ሚሊየን ዶላር እንበደርና በተበደርነው ገንዘብ ከአሜሪካ ወይም ከአውሮፓ እቃ እንሸምትበታለን። በቀኝ እጅ የሰጡንን በግራ ይቀበሉናል። የሚተርፈን ስማችን እዳ መዝገባቸው ላይ መስፈሩ ይሆናል።
ይህ አዙሪት ነው፤ ጎበዝ መተሳሰብ ይኖርብናል፤ ነገሮች እንዴት እንዴት ሊሆኑ እንደሚችሉ አየን፤ ዋናው መልእክቴ እንተሳሰብ የሚል ነው።
የቤት ኪራይ፣ የመምህራን ደሞዝ ጭማሪ ያፈጠጡ እውነታዎች ሊሆኑ ይችላሉ። የግል ትምህርት ቤቶች ለጽድቅ እንደማይሰሩም እገነዘባለሁ፤ ማትረፍ አለባቸው፤ ይህን ሁሉ የማይረዳ ይኖራል ብዬ አልገምትም። ጭማሪው ግን ምክንያታዊ ይሁን፤ ስንጥቅ ትርፍ ፍለጋ አይሁን። እነሱን አብልጠው የሄዱትን ወላጆች ከግምት ያስገባ ይሁን፤ ባለፈው አመት ጭማሪ አለመደረጉ ብዙ ጉዳት እንዳስከተለ ይታሰባል፤ ይህን ጉዳት ሁሉ ማካካስ የሚቻለው በአንድ በዘንድሮ ብቻ አይደለም። ቀስ በቀስ ነው። አንድ ሰኔ የገደለውን አስር ሰኔ አያነሳውም አይደል የሚባለውስ።
ነጻ ገበያ በሚል ሽፋን እየተዘራረፍን አንዘልቅም። ይሉኝታን የመሰለ የሰብአዊነት ባህላችንን ባናጣው መልካም ነው። የሆነ ጊዜ ኤች አይ ቪ በተስፋፋበት ወቅት ታዋቂ ድምጻውያን አንድ ጥሩ ሙዚቃ ሰርተው ነበር። ከሷ ላይ አንዲት የተወሰኑ ስንኞችን ወስደን ለትምህርት ቤት ባለቤቶች እንጋብዛቸው
ክፉ ደጉን ያየን ነንና ጎረቤት
ያንተ ቤት ሲንኳኳ ይሰማል እኔ ቤት
የማንፈልገውን በራሳችን ደርሶ
ሌላው ላይ እንዲሆን አናርገው ጨርሶ
አቤል ገብረኪዳን
አዲስ ዘመን ሐምሌ 20/2013