አሁን ያለንበት ዘመን የፕሮጀክት ነውና በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን በ19 50 ዎቹ በሰኔና በሀምሌ ወራት ታትመው ከወጡት ዘገባዎች መካከል አብዛኞቹ በፕሮጀክት ጥናትና ፕሮጀክቶች ላይ ያተኮሩ ናቸውና ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡ መልካም ንባብ
የጣና ሐይቅ ልማት ጥናት
አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የቴክኒካዊ እርዳታ ቦርድና የአሜሪካ መንግሥት የኢኮኖሚክስ ልማት ምድብ 1 300,000 የኢትዮጵያ ብር የጣናን ሐይቅ አካባቢ የኢኮኖሚክ ልማት ማስፋፊያ ይሆን ዘንድ ተስማምተውበታል፡፡
በዚህ ወጪ ገንዘብ ባሕር ዳር ላይ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎትና የውሃ ማጣሪያና ማደያ አገልግሎት ይቋቋምበታል፡፡ በጎጃምና በበጌምድር ጠቅላይ ግዛቶች በባሕር ዳርና በጎርጎራ አካባቢ ላይ የእርሻ ሥራ ማሻሻያ አገልግሎት ጣቢያዎች ይቋቋማሉ፡፡የትምህርት መስጫ አገልግሎቶችም በመርዓዊና በጭልጋ አካባቢ ይስፋፋሉ።
እነኚህ እቅዶች ከሀገሪቱ የልማት ፕሮግራም ክፍል ሲሆኑ፤ የእርሻና የእንስሳት አጠባበቅ ቴክኒክ ጣቢያዎችን የትምህርት መስጫ ድርጅቶችንና እንዲሁም በመንግሥቱ ግዛት ውስጥ ራቅ ባሉ አካባቢዎች የሚገኙ ገበሬዎችም ሆኑ ዕቃ ሠሪዎች በብዙ ያመርቱ ዘንድ ለማድረግ የጤና ጥበቃ አገልግሎቶች መንገዶች ውሃና የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎቶችን ለማቋቋም ሲሉ የኢኮኖሚክና ቴክኒካዊ ቦርድና የአሜሪካ የተራድኦ መሥሪያ ቤት በመተባበር ያወጡዋቸው ድርጅቶች ናቸው፡፡
ባህር ዳር የሚቋቋመው የኤሌክትሪክ ኃይል ሁለት ባለ 60 ኪሎዋት (ኃይል አስተጋቢ) ዲናሞ ያሉት ይሆናል።
የኤሌክትሪክ ኃይል አስፈላጊነት እያደገ ሲሄድ ላንዳንድ ጊዜ የሚሠራበት ለመጠባበቂያ የሚቀመጠው ዲናሞ በሥራ ላይ ይውላል፡፡የውሃ ማጣሪያውና ማደያው አገልግሎት የህዝብ ጤና ጥበቃ እንደሚያደርገው ሁሉ ከጉድጓድ ውሃ የሚጎትት መሣሪያ የመድኃኒት መርጫ መሣሪያና የውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳ ተበጅቶለት ባሕር ዳር ለምግብና ለመጠጥ የሚሆን ውሃ እንድታገኝ አስችሏታል፡፡
በጋሞ ጎፋ ጠቅላይ ግዛት የእርሻ ሥራ ማሻሻያ አገልግሎት ጣቢያን ለማቋቋምና የወደፊቱም የጠቅላይ ግዛቱን ልማት እቅድ የሚመሠረትባቸውን ሁለት ታላላቅ ጥናቶች ለማከናወን 1000000 የኢትዮጵያ ብር ወጪ እንዲሆን የኢኮኖሚክና ቴክኒካዊ ዕርዳታ ቦርድና የአሜሪካ መንግሥት ተስማምተውበታል፡፡
የእርሻ ሥራ ማሻሻያ አገልግሎት ጣቢያ አርባምንጭ ላይ ይቋቋማል፡፡ሆኖም የግጦሽ ቦታዎችንና የጫካ ዛፎች ችግኞች የሚበቅሉባቸው መሬቶች ለመወሰን በቦይ የአፈሩን ፍሬያማነትና ውሃን በቦይ እያጠጡ የሚታረስ መሬት መሆኑን ከመሬቱ የተፈጥሮ ሀብት ጋር በማወዳደር ለመበየን ለከብትም ሆነ ለሰው በቂ ውሃ ያለው መሆኑንና በመሬት ላይም ሆነ በወሃ የመገናኛ አገልግሎት በቀላሉ ለመከናወን የሚቻል መሆኑን ለማወቅ አስቀድሞ አንድ ጥናት ይደረጋል፡፡
(ሐምሌ 25 ቀን 19/51 ከወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ)
የአዋሽ ጣቢያ ከ2 አመት በኋላ ኤሌክትሪክ መስጠት ይጀመራል
አዲስ አበባ፡- የአዋሽ ሁለተኛና ሶስተኛ የኤሌክትሪክ ሀይል ጣቢያ ጠቅላላ ስራ ሲትራና ኦስትሪያ ቮይት ለተባሉት የኢንተርናሽናል ኩባንያዎች በጨረታ በአሸናፊነት እንደተሰጣቸው ከኤሌክትሪክ መብራትና ሀይል ባለስልጣን የተገኘው ዜና ገልጧል፡፡ ሁለቱ ከባንያዎች የሚያከናውኑት ስራ 27 ሚሊየን 150 ሺ ብር እንደሚፈጅ ታውቋል፡፡
እነዚህ በጨረታ አሸናፊነት የያዙት ኩባንያዎች ሰኔ ፩ ቀን ፲፱፶፮ አ.ም ስራውን ለመጀመርና ለማጠናቀቅ የሚያስችላቸውን ውለታ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ መብራትና ሀይል ባለስልጣን ጋር ተፈራርመዋል፡፡
የሲትራ ኩባንያ የሚሰራቸው ሁለት የውሃ ማገጃ ግድቦች ሁለት የውሃ ማሽቆልቆያ ቦዮች ፣ሁለት የውሃ ሀይል መስጫ ጣቢያ ቤቶች ሲሆን፣ የሚከፈለው ገንዘብ 25 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር ነው፡፡ የቮይስ ኩባንያ ስራም በሁለቱም የሀይል መስጫ ጣቢያዎች አራቱን ተርባይኖች መገጣጠምና መትከል ነው፡፡
ለዚሁ ስራም የሚከፈለው ገንዘብ 2ሚሊየን 150 ሺ ብር ነው፡፡ ማናቸውም ስራ ከተጠናቀቀ በኋላ የመጀመሪያው ተርባይን በ፲፱፶፰ አ.ም ኤሌክትሪክ መስጠት ሲጀምር ሁለተኛው በዚሁ አመት መጨረሻ እንደሚጀምር ይታመናል፡፡ ሶስተኛውና አራተኛው በ፲፱፶፱ አ.ም እና በ፲፱፷ አ.ም ተከታትለው በአገልግሎት ላይ እንደሚውሉ ተረጋግጧል፡፡
እነዚህም ተርባይኖች እያንዳንዳቸው 22 ሺ የፈረስ ጉልበት ሀይል ሲኖራቸው በጠቅላላው 92 ሺ የፈረስ ጉልበት ኤሌክትሪክ ሀይል ሊሰጡ ይችላሉ፡፡
እንደዚሁም የጀነሬቶችና የትራንስፎርመሮች ዋጋ ውለታ በዚሁ ሳምንት ውስጥ እንደሚፈረም ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ መብራትና ሀይል ባለስልጣን ማስታወቂያ ክፍል የደረሰን ዜና ያመለክታል፡፡
ይህ የአዋሽ የሁለተኛና የሶስተኛ ኤሌክትሪክ ሀይል ጣቢያ ስራ ለአለም የኢንተርናሽናል ተጫራቾች ቀድም ብሎ መሰጠቱ ሲታወስ፣ እስከ አሁን ድረስ የሂሳቡና የቴክኒክ ጠቅላላው ጥናት ሲጠናቀቅ መቆየቱን ለመረዳት ችለናል፡፡
የሲቪል መሀንዲሱን ስራ በጨረታ አሸናፊ የሆነው ሲትል የፈረንሳይ አገር ኩባንያ ነው፡፡
ሰኔ 3 ቀን 1956
የተበላሹ የምግብ ሸቀጦች በምርምራ ተያዙ
በአዲስ አበባ ከተማ የጽዳት ክፍል መ/ቤት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጎዳና በሚገኙት ሱቆች ውስጥ ባደረገው ምርመራ ከአንድ ሺህ በላይ የሚሆኑ ሸቀጣ ሸቀጦች በመጥፎ ሁኔታ ተመርዘው የበሰበሱ መሆናቸውን ተረድቷል ሲል የማዘጋጃ ቤት ማስታወቂያ ክፍል አስታውቋል፡፡
እነዚህ የምግብ ሸቀጦች ሰርዲን፣ ከረሜላ፣ ልዩ ልዩ በቆርቆሮ ታሽገው የሚሸጡ ፍሬዎች፣ ቸኮሌቶችና የእንግሊዝ ጨው ከመሆናቸውም በቀር ፤ለኤግዚቪት ሸቀጦቹ በፅዳት ክፍል መሥሪያ ቤት የሚገኙ መሆናቸው ታውቋል፡፡
የዚህ ጉዳይ ተመርምሮ ከተጣራ በኋላ የተያዙት የምግብ ሸቀጦች ከመጣላቸውም በቀር የሸቀጦቹ ባለቤቶች በጤና ጥበቃ ሕግ አስፈላጊው ቅጣት እንደሚወሰድባቸው ታውቋል፡፡
በማናቸውም የምግብ ሸቀጥ የሚነግድ ነጋዴ ጥቅም ማግኘቱን ብቻ ሳይከታተል የሚሸጠው ምግብ ለሕዝብ ጤና ተስማሚ መሆኑንም እየተቆጣጠረ ለጤና ጠንቅ የሚያመጡትን ማስወገድ ትክክለኛ ዓላማ ሲሆን ፤በዚህ ዓይነት በማቆየትና በልዩ ልዩ ምክንያቶች የተመረዙትን የምግብ ሸቀጦች በመነገድ መጠቀም በሕዝብ ጤና ላይ ከፍ ያለ ጉዳት የሚያስከትል እንደ መሆኑ መጠን፤ በነጋዴውም ላይ የሚወሰደው የቅጣት ርምጃ ጥብቅ በመሆኑ ፤ነጋዴዎች ቀደም ብለው ሊጠነቀቁ ይገባል ሲል የማዘጋጃ ቤት ማስታወቂያ ክፍል ይገልጻል፡፡
(ሐምሌ 5 ቀን 1955 ዓ.ም ከወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ በፊት ገጹ የዘገበው ዜና)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 19/2013