ለሰው ልጅ ከሚያስፈልጉ መሰረታዊ ነገሮች አንዱ ልብስ ነው፡፡ የሰው ልጅ ልብስ መልበስ ሰብዓዊ ሞራላዊና መንፈሳዊ ግዴታው ነው፡፡ አዳምና ሔዋንን ዕጸ በለስ አትብሉ የተባለውን ትዕዛዝ በመጣሳቸው ዕርቃናቸውን እንዲቀሩ መደረጋቸው ይታወቃል፡፡ ይህ በመሆኑም እርስ በርሳቸው ተፋፈሩ፡፡ የበለስ ቅጠል ሰፍተው ለራሳቸው ግልድም አደረጉ፤ በኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ እንደሰፈረው፡፡ ልብስ ገበናችንን የምንሸፍንበት ብቻ አይደለም፤ የምናጌጥበት፣ ጤንነታችንን የምንጠብቅበት ባህላችንን እምነታችንን የምናሳይበት ነው፡፡ ልብስ አምራችና ሰፊዎችስ ልብስን እንዴት ይመለከቱታል፡፡ ስለተለያዩ የልብስ ፋሽኖችስ ምን ይላሉ፡፡
አቶ ኃይሉ ረታ ወደ ቦሌ ክፍለ ከተማ ጃክሮስ በሚባል አካባቢ በአዲስ ኃይል ጋርመንት ድርጅት በጨርቃ ጨርቅ ልብስ ስፌት ውስጥ ይሠራሉ፤ሥራውን የጀመሩት ሁለት ሆነው ሲሆን ወደ ስድስት ዓመት ሆኗቸዋል፡፡
መንግሥት ለሥራቸው ሼድ በመስጠት ድጋፍ እንዳደረገላቸው የሚናገሩት አቶ ኃይሉ፣ የጥበቃ አልባሳትን ጨምሮ የቡቲክ፣ የአለቀላቸው ልብሶች፣ ሸሚዝ፣ ኮት የመሳሰሉትን እየሠሩና እያመረቱ ይተዳደራሉ፡፡ ምርቶቻቸውን በኮልፌና በመርካቶ ገበያዎች ለአከፋፋዮች እንደሚሰጡ የጠቆሙት አቶ ኃይሉ በሥራቸው 45 የልብስ ስፌት ባለሙያዎችን ይተዳደራሉ፡፡
በአዲስ ኃይል ጋርመንት ድርጅት የወንዶችንም የሴቶችንም በተለይ ቀሚስ በየጊዜው የተለያየ ዲዛይን ስለሚመጣ የበለጠ ይሰራሉ፤ ዲዛይን ራሳቸውም እንደሚያወጡ የሚናገሩት አቶ ኃይሉ ከመረጃ መረብ ( internet) እና ሰዎች የለበሱትን በማየት የራሳቸውን ደግሞ አክለው አሰማምረው እንደሚሠሩ ጠቁመዋል፡፡
ዲዛይን ተከትለን አልባሳቱን ስናመርት ገበያና ደንበኞች እናገኛለን ፤በጅምላ የሚወስዱ ነጋዴዎች ይወስዱታል፡፡ ዲዛይኑን የወደዱት ካሉ በብዛት እንዲሰፋላቸው በድጋሚ ይጠይቃሉ፤እናም ፋሽን በብዛት የሚከተልና ዕውቅና የሚሰጥ ባይኖርም፤ የሰፋናቸውን ልብሶች በጅምላ በተደጋጋሚ አሰፍተው ሲወስዱት ገበያውን ማግኘታቸውን በማስተዋል እኛ እንደ ፋሽን እናስበዋለን፡፡ ገበያው ሲሳሳ ደግሞ ሌላ ዲዛይን እንደ አማራጭ እናያለን፤በተለይ በሴቶች አልባሳት ማለት ነው፡፡
ብዙ ልብሶች ከውጪ አልቆላቸው የሚመጡ ናቸው፤ እኛ የውጪ ልብሶች ለመፎካከር የሚያስችል አቅም ባይኖረንም ሀገር ውስጥ ልብሶችን ሰፍተን የበለጠ ለመሸጥ የግብአት እጥረት ያጋጥመናል የሚሉት አቶ ሀይሉ፣ ትልቁ ችግራችን ጥሬ ዕቃ ላይ ነው ይላሉ፡፡
እንደ አቶ ሀይሉ ገለጻ፤ ጥሬ ዕቃ ለማግኘት በጣም ከባድ ነው፤ከውጪ ጨርቅ የሚያስመጡም እያስመጡ አለመሆኑም አንዱ ችግር ነው፡፡ የሚያመጡትም ዋጋቸው ውድ እየሆነ ነው፡፡ በብዛት የውጪ አስመጪዎችም ያለቀላቸው ልብሶች ያስመጣሉ ያም ሥራችን ላይ ተፅዕኖ አለው፤ ለመወዳደርም ከባድ ነው፡፡ መንግሥት የሀገር ውስጡን አምራች በመደገፍና በማበረታታት ተወዳዳሪ ማድረግ አለበት፡፡ ሰው ልብሶቻችንን እንደ አማራጭ እየመረጣቸው መሆኑን ጠቅሰው፣ ሥራት ፍላጎታችን ግን ከባድ እየሆነ ነው ሲሉ ያመለክታሉ፡፡
የሀገር ውስጥ የተለያዩ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች፤ምርቶቻቸውን ለነጋዴዎች ስለሚሸጡ በቀላሉ ምርቶቻቸው አይደርሷቸውም፤ ምርቶቻቸውን በቀጥታ ለተጠቀሚ አይሰጡም፡፡ በዱከም ኢንዱስትሪ ፓርክ ቻይናዎች ያመርታሉ፤ ባብዛኛው ለነጋዴዎች ነው የሚሸጡት፡፡ ስለዚህ፤ከፋብሪካ የማግኘት ዕድላችን በጣም ጠባብ ነው፡፡ ከነጋዴው ላይ መልሰን ገዝተን ፤እነሱም ጥሬ ዕቃ የለም ብለው በእጥፍ ጨምረው ስለሚሸጡ የመሥራት ፍላጎታችን ከባድ እየሆነ ነው፡፡
በዚህ አይነት ሁኔታ እያመረቱ ከውጪ ከሚያስመጡት ጋር መወዳደሩ ከባድ መሆኑን ጠቅሰው፣ አንደኛ እነሱ ያለቀ ምርት ነው ይዘው የሚመጡት ፤ ሁለተኛ እኛ እናመርታለን ብንልም ጥሬ ዕቃ ስለማናገኝ ከባድ ሆኖብናል ሲሉ ያብራራሉ፡፡
ፋሽን እኛ ሀገር ገና ነው፤ ፋሽን ተከታይም ብዙ የለም። ሰው የወደደውን ገበያ የሚስበውን ዓይተን ደጋግመን እናመርታለን፤ሰው ሲወደው ለራሳችን ፋሽን ነው ብለን እናስባለን እንጂ ከውጪ ካሉት ጋር ሲተያይ ገና ጅማሮ ላይ ነን፡፡ የምንሠራው የቅብብሎሽ ሥራ ስለሆነ አንድ ፋሽን ይወጣል፤ ከ20 እስከ 30 ሺ ልብስ ይሠራና ፤ከዚያ ደግሞ ሌላ ፋሽን ይወጣል፡፡ ለፋሽን ብለን በተለየ የምንሠራው የለም፤ ገበያው ሲቀበለው ግን ፋሽን ብለን እናስበዋለን ሲሉ ያብራራሉ፡፡
በመንግሥት በኩል የብድር አቅርቦት ጨርቅ የምናገኝበትን ሁኔታ ቢያመቻችና ሀገር ውስጥ ካሉ ጨርቅ ፋብሪካዎች ጋር ትስስር የምንፈጥርበትን መንገድ ቢያመቻችልን መልካም ነው ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡
አቶ ጌትነት ዘመድ አገኘሁ በደብረ ብርሃን ከተማ ነው የሚኖሩት፡፡ በጨርቃ ጨርቅ ልብስ ስፌት ሙያ የተሠማሩ ሲሆን፣ በሥራቸው 30 የሚደርሱ ባለሙያዎች ይሠራሉ፡፡ የተለያዩ አልባሳትን እንደሚያመርቱ የሚናገሩት አቶ ጌትነት፣ በተለይ ደግሞ የሴቶች ሙሉ ቀሚስና ጉርድ ቀሚስ በልዩ ልዩ ዲዛይን እንደሚያመርቱ አስታውቀዋል። ‹‹ፋሽን ብለን የምናመርተው ባይኖርም፣ በልዩ ልዩ ቅርጽና ዲዛይን እንዲሁም ቀለማት ያሉት አልባሳት በገበያ ላይ ያላቸውን ተቀባይነት በማየት እናመርታለን ሲሉ ያስረዳሉ።
አቶ ጌትነት ዘመድ አገኘሁ በአዲስ ዲዛይንና ቀለም አልባሳቱን አምርተው በደብረ ብርሃንና በአቅራቢያው በሚገኙ ከተሞች ያከፋፍላሉ፡፡ በገበያ ላይ ያለውን ተፈላጊነት በማስተዋል እንደ ፋሽን በተደጋጋሚ የሚያመርቱት መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡
የዘርፉ የጥሬ ዕቃ አቅርቦት እጥረት ለሥራቸው ተግዳሮት እንደሆነባቸው አቶ ጌትንም ይጠቁማሉ። መንግሥት ለሥራው ድጋፍ በመስጠትና የግብአት እጥረት ተወግዶ አምርተን አትራፊ የምንሆንበት መንገድ ቢያመቻች ልዩ ልዩ ዲዛይን ያላቸውን ልብሶች በማምረት ተወዳዳሪ መሆን እንችላለን ሲሉ ያመለክታሉ፡፡
የሀገር ውስጥ ባለሙያና ገበያ የበለጠ ተወዳዳሪ ለመሆን እንደሚረዳቸው ይገልጻሉ፡፡ የጨርቃ ጨርቅ ሥራው ትልቁ ማነቆ የሆነብን የጥሬ ዕቃ አቅርቦት እጥረት ነው ሲሉም አጽንኦት ሰጥተው ይገልጻሉ፡፡ ያለቀላቸው ልብሶችም ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ ጫናው እንደሚበረታ፤ በገበያው ተወዳዳሪ ለመሆን ግን ጨርቅ ለማግኘት እንደሚቸገሩ ይገልጻሉ፡፡
በአዲስ አበባ መርካቶ ገበያ ያገኘሁዋቸው ወይዘሪት አመለወርቅ ሚደቅሳ ለሴቶች የሚሆኑ የተለያዩ በሀገር ውስጥ የተሰፉ ቀሚሶች እንደሚገኙ ትናገራለች። ቀለሙንና ዲዛይኑን በማየት መርጣ እንደምትገዛ ትናገራለች፡፡
‹‹የውጪ ልብሶችን የሚያስንቁ ዲዛይኖች ገበያ ውስጥ አሉ ፤ግን አምራቾቹ አይታወቁም ፤የሀገር ውስጥ እንደሆኑ ግን አውቃለሁ ትላለች፡፡ አንዳንዴም ጨርቅ ገዝታ በመርካቶ በራስዋ ምርጫና ዲዛይን እንደምታሰፋ የምትናገረው ወይዘሪት ቀለመወርቅ፣ የወንዶች ልብሶችን የሚያመርቱ ዕውቅና ያላቸው የሀገር ውስጥ ድርጅቶች እንዳሉም ጠቅሳለች፡፡ በእንስት ልብስ ስፌት ዝነኛ የሆኑ አምራቾች ድማጻቸው እንደማይሰማ ጠቁማ፤ ራሳቸውንና ሥራቸውን ቢያስተዋውቁ ገበያ እንደሚያኙ ተናግራለች።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 19/2013