የሰው ልጅ ጥንካሬዎችና መገለጫዎች በርካታ ናቸው። ዛሬ ለመኖር ምቹ የሆነች ዓለም ማግኘት የቻልነው በብዙ ጥረት ነው። ግለሰቦች የማሰላሰልና የመፍጠር አቅማቸውን ተጠቅመው ተዓምር እንድናይ አስችለውናል። ዘመናዊነት፣ ቀላል ህይወት፣ ሕግና ሥርዓት የዓለም ሁሉ ገዢ በሆነው የሰው ልጅ እውቀትና ጥበብ የተፈጠሩ ናቸው።
ቁሳዊ ከሆነው ሥልጣኔ በላይ ደግሞ የሰላ አእምሮ ባለቤት የምንሆንበትን “የማሰብ ነፃነት” የምንጎናፀፍበትን ጥበባዊ ክንዋኔ እያሳደግን እንድንመጣ የጥቂቶች የመፍጠር ችሎታ ልዩ ቦታ ነበረው ። አሁንም እንደዛው። ታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ “ሰው በመብል ብቻ አይኖርም። በእግዚአብሔር ቃልም ጭምር እንጂ” እንደሚለው ሁሉ፤ ሰው በቁሳዊ ነገሮች ብቻ ታጥሮ ከመኖር በላይ “የማሰላሰል፣ ስሜቱን የመግለፅ፣ ነፃነቱን የማሳየት እንዲሁም በቀላሉ ለመረዳት የሚያስቸግሩ ስሜቶቹን በጥበብ የመግለፅ ኃይል አለው። እነዚህ ሁሉ ለመኖሩ ዋንኛ ዋልታዎች እንደሆኑ እንረዳለን።
በዚህ ጊዜ ነው ጥበብ የሚገለፅባቸው ጥበበኞች የሚያሹን። ሶስተኛው አይናቸውን ተጠቅመው ከኛ እይታ ውጪ የሆኑ ጉዳዮችን፣ በሥነ ፅሁፍ፣ በትወና፣ በሥነ ጥበብና በሌሎች ጥበባዊ ዘርፎች አስውበውና አሰማምረው ለአእምሯችን ምግብ የሚያሰናዱልን ጥበበኞች ናቸው። እኛም ከማእዱ ከመካፈላችን ባሻገር ይህን የማድረግ አቅም ያላቸው ባለተሰጦዎችን እናከብራለን፣ አድናቆታችንን እንለግሳለን። ያኔ ጥበበኛውም አመስጋኝ ሲያገኝ የበለጠ እንዲተጋና ለሌላ ተጨማሪ መልካም አላማ እንዲነሳሳ ይረዳዋል። ከምስጋና ሌላ የምናከብረውን የሰራን ሰው መሸለም ንፉግ አለመሆናችንን የሚያሳይ ነው። በተለይ በጥበቡ ዓለም ያለ አንድ ባለተሰጦ በቁስና በንዋይ እውቅና ከምንሰጠው ይልቅ የሰራውን ሥራ ብንመለከትና ለዚያም ያለንን ልዩ ክብር በአደባባይ መግለፅ ብንችል ለእርሱ ከምንም በላይየእርካታ ምንጩ ይሆናል። ያኔ ጥበበኛም ሆነ ጥበብ በቁመታቸው ልክ ተከብረዋል ለማለት እንደፍራለን።
“ሽልማት ለጥበብ”
ዛሬ ስለ ጥበብና ጥበበኛን ስለማክበር ብዙ ያልነው ያለምክንያት አይደለም። ከሰሞኑ ይህንኑ ሃሳባችንን የሚደግፍ ዝግጅት ተሰናድቶ እዛው ላይ የመካፈል እድል ገጥሞን ነበር። የዚያ “የሰላ ሃሳብና” የጠራ “ማሰላሰል” እንዲኖረን በጥበብ ሥራዎቻቸው ለሚያግዙን አርቲስቶች፣ በሥነ ፅሁፍ፣ በሙዚቃ፣ ውዝዋዜ፣ ቲያትርና ፊልም እንዲሁም በሥነ ጥበብ ዘርፍ ላይ ለሚገኙ ባለሙያዎች እውቅና የሰጠ መድረክ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና በዘርፉ ማህበራት ትብብር ሽልማት በማዘጋጀት የማመስገን አላማ የነበረው ነው።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር “ሽልማት ለጥበብ” በሚል መሪ ቃል ከዘርፉ ማህበራት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የእውቅናና የሽልማት መርሐ ግብር ለባህልና ጥበብ ባለሙያው ሽልማት ማበርከትና እውቅና መስጠት አገር ውለታዋን እንደማትረሳ ማሳያ መሆኑን አዘጋጆቹ በመሰናዶው ላይ ገልፀዋል።
ሐምሌ 12 ቀን 2013 ዓ.ም በኢንተር ኮንትኔንታል ሆቴል በተካሄደው የእውቅና መስጠት ሥነሥርዓት ላይ የጥበብ ሙያተኞች በውድድር መንፈስ ተነሳስተው ለወገንና ለአገር የሚጠቅም ስራ በመስራት ላበረከቱት አስተዋጽኦ እውቅናና ማበረታቻ እንዲያገኙ የሚደረግበት አሰራር ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ሲሰራ መቆየቱን ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ብዙነሽ መሠረት በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ገልጸዋል። ለዚህም መመሪያና መስፈርት በማዘጋጀት የባህል ዘርፍ የመንግሥት ተቋማትና ሌሎችንም በማሳተፍ ወደስራ እንደተገባ ጠቁመዋል።
ሽልማትና እውቅናውን በዋነኝነት የሰጡት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው እንደተናገሩት፤ በአገራዊ ጉዳይ ላይ ሙያቸውንና የጥበብ ተሰጧቸውን ተጠቅመው ውለታ የሰሩ ባለሙያዎችን ማመስገን ከምንም በላይ አስፈላጊ ነው፤ ወቅቱም ትክክለኛው ሰዓት ነው። ጥበብ አይንን ገላጭና ሕዝብን ከሕዝብ የማስተሳሰር ትልቅ ኃይል ያለው ከመሆኑ አኳያ ጥበበኛን በዚህ መንገድ ማክበር ይገባል ብለዋል።
ከሐረሪ ክልል አቶ በድሪ የሱፍ ሲማን፣ አቶ አቡበከር አብዱላሂ፣ አቶ ሲሳይ ታደሰ ከድሬዳዋ ፣ አቶ ሞቱማ አሰፋ ከኦሮሚያ፣ በሥነ ፅሁፍ፤ አቶ እያዩ ሲሳይ ሸቴ ከአማራ ክልል በስነ ጥበብ፣ አቶ ይልማ አበበ ከደቡብ በሙዚቃ ዘርፍ፣ አቶ አስራት ማርቆስ ከሲዳማ ክልል በሙዚቃ የክብር ሽልማትና እውቅና ተሰጥቷቸዋል።
በተመሳሳይም አቶ ተክለማሪያም ዘውዴ በግል ከሰዓሊያን ማህበር፣ ተሾመ አንዳርጋቸው ከቲያትር ባለሙያዎች ማህበር፣ ተስፋዬ ገብረማሪያም ከቲያትር፣ ቴዎድሮስ ካሳሁን ገርማሞ (ቴዲ አፍሮ) ከኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበር ድምፃዊ፣ ገዛኸኝ ብርቄ ከኢትዮጵያ ተወዛዋዦች ማህበር ውዝዋዜ፤ ፍቅርአዲስ ነቃጥበብ በድምፃዊያን ዘርፍ፣ አቤል ሙሉጌታ የዜማ ደራሲ፣ ሃብታሙ ቦጋለ በሙዚቃ ግጥም፣ ካሙዙ ካሳ በሙዚቃ አቀናባሪ ዘርፍ፣ ደስታ ደጀን በፋሽን ዲዛይን ዘርፍ የክብር ሽልማትና እውቅና የተሰጣቸው ናቸው ። ከእውቅናው ባሻገር በቦታው ተገኝተው ለነበሩ ተሸላሚዎች ካባ የማልበስ ስነስርዓት ተካሂዷል።
ከተሸላሚዎቹ መካከል አንዱ የሆነው ሰዓሊ ተክለማሪያም ዘውዴ ስለ ተሰጠው የእውቅና ሽልማት ላቀረብንለት ጥያቄ “ለአገሬ ባበረከትኩት ትንሽ ሙያዊ አስተዋፅዖ አገሬ በወኪሎቿ የህይወት ዘመን ሽልማት ሰጥታኛለች፤ ይሄም በቀሪ ዘመኔ ይበልጥ እንድተጋ ስንቅ ይሆነኛል” የሚል ምላሽ ሰጥቶናል።
ጥቂት ወደ ኋላ
በአገራችን የጥበብ ሽልማት ታሪክ የመጀመሪያው የሽልማት ድርጅት ሐምሌ 1 ቀን 1955 ዓ.ም የተመሰረተው የአጼ ኃይለስላሴ የሽልማት ድርጅት ነበር:: የመጀመሪያውን የኪነጥበብ ባለሙያዎች ሽልማት ለባለሙያዎቹ የሰጠው ይሄው ድርጅት ነው። የሽልማት ድርጅቱ በንጉሱ የግል ሀብት የተቋቋመ በመሆኑ የገንዘብ ችግር እንዳልነበረበት ይነገራል። አብዮቱ እስከ ፈነዳበት 1966 ዓ.ም ድረስም በሥነፅሁፍና በስዕል መስክ አስር ባለሙያዎችን በመሸለም ተጉዟል።
ሰዓሊ ገብረ ክርስቶስ ደስታ አንዱ ተሸላሚ ነበር ። ሰዓሊ ገብረ ክርስቶስ እንደ መምህርነቱም ከ1955 ዓ.ም እስከ 1967 ዓ.ም ድረስ ባሉት 12 ዓመታት ውስጥ ዛሬ ለአገሪቱ አንቱ የተሰኙ እና ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸውን ሠዓልያን አፍርቷል:: ‹‹ሞዴል አርቲስትና መምህር›› በመሆኑም በ1963 እና 1964 ዓ.ም ከወቅቱ የትምህርትና የሥነ ጥበብ ሚኒስቴር እንዲሁም ከአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ጽሕፈት ቤት የዓመቱ ምርጥ መምህር ተብሎ ተሰይሟል :: በ1969 ዓ.ም የዕድገት በህብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ ለፈፀመው ታላቅ የማስተባበር ተግባርም ከዘመቻው መምሪያ የወርቅ ሜዳልያም ተሸልሟል ::
ከ24 አመታት በኋላ የተቋቋመው አገር አቀፍ የስነ ጥበባትና መገናኛ ብዙኃን የሽልማት ድርጅት ጠንካራ የሚባል የባላደራ ቦርድ አባላትን ይዞ ነበር ስራውን የጀመረው። በሥነ ጥበብና በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ተሰማርተው የላቀ የፈጠራ ስራ የሚያቀርቡ ተቋማትንና ግለሰቦችን በየሙያው ዘርፋቸው በማወዳደር ለማበረታታና ለመሸለም እንዲሁም ሥነ ምግባርን የተላበሱ ጠንካራ ተተኪዎችን ማፍራት የሚሉ አበይት ዓላማዎችን ይዞ ነበር የተቋቋመው።
ቦርዱ ከተቋቋመ ከአምስት ወራት በኋላ በታህሳስ 1991 ዓ.ም ነበር የመጀመሪያዎቹን ተሽላሚዎች መርጦ ለመሸለም የበቃው። በወቅቱ የተሸለሙት ባለሙያዎች ስምንቱ ከስነ ጥበብ ዘርፍ ሲሆኑ፣ አንዱ ከመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ እንደነበር ይታወሳል። ከተሸላሚዎቹ ውስጥ አምስቱ መላ ህይወታቸውን በጥበብ ውስጥ በማሳለፋቸው የህይወት ዘመን ተሸላሚዎች ተብለዋል፤ አራቱ የረጅም ዘመን አገልግሎት ተሸላሚ ነበሩ። በወቅቱ የመተዳደሪያ ደንብ ላይ ከህይወት ዘመን እና ከረጅም ዘመን አገልግሎት የሽልማት አይነቶች ሌላ ወቅታዊና ዓመታዊ ሽልማቶችን እንደሚሰጥም ተገልፆ ነበር።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2013