ታሪክ ተመልሶ ሲታይ አንድም ለመማሪያ በዚያውም ዛሬ የተገኘንበትን በብዙ ማሳያ ነውና ከትውስታ ገፃችን ላይ ፈላልገን አስረጂ መዛግብትን አገላብጠን ትላንት የሆነውን ዛሬ ላይ እንድትመለከቱት ከዓመት በፊት በዚህ ሳምንት የሆነውን አንድ ታላቅ ክስተት ዛሬ ይዘን ቀርበናል፡፡ ይህን የዓለም ሚዲያዎች ጭምር በስፋት ያወሩለትን ክስተት እነሆ ብለናል፡፡
ልክ የዛሬ ዓመት በዚህ ሳምንት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ታላቅ ብስራት የተበሰረበት፣ የዘመናት ቁጭት ወደ ተስፋ ተለውጦ ኢትዮጵያውያን ጅማሬያቸው ማበብ የጀመረበት ታሪካዊ ቀን ነበር፡፡ እኛም ሁነቱን ለአንባቢያን በዚህ መልክ ዳሰስነው፡፡ በድንገት ተሰምቶ ብዙ ሚሊዮኖችን ያስፈነደቀ በአንፃሩ ደግሞ እቅዱ ተግባራዊ እንዳይሆን ከጅምሩ ብዙ ያሴሩ የነበሩ የኢትዮጵያ ጠላቶችን ያስደነገጠ ልዩ ቀን፡፡
የወቅቱ የኢትዮጵያውያን ታላቅ ጉዳይ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን መሳካቱን እጅግ የሚናፍቁት፣ መጠናቀቁን እጅግ የሚፈልጉት ትልቅ ጉዳይ፡፡ የአንድነታቸው ማሰሪያ የአብሮነታቸው ማህተም የወደፊት የመልማት እቅድና ጥረታቸው ማሳያ የሆነው የህዳሴ ግድብ፡፡
ቀኑ ሐምሌ 15 ቀን 2012 ዓ.ም ልክ የዛሬ ዓመት በዚህ ሳምንት የታላቁ የኢትዮጵያ ግድብ በተመለከተ አንድ ታላቅ ዜና ተሰማ፡፡ ብዙዎች ሳይጠብቁት በድንገት የተነገረው የብስራት ዜና፤ በደቂቃዎች ውስጥ የዓለም መገናኛ ብዙኃን ተቀባበሉት፤ ኢትዮጵያውያንም በሰሙት እጅጉን ተደሰቱ፤ ፈነደቁም፡፡
በዚህ ሳምንት የተነገረው ዜና “ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ወደ ታሪካዊ ምዕራፍ በመሸጋገር ለመጀመሪያ ዙር የታቀደለትን 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ሙሉ ለሙሉ መያዙ ተነገረ ።” የሚል ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን ለውጥን አልመው ለለውጣቸው መሰረት ይሆናቸው ዘንድ የጀመሩት ታላቅ ፕሮጀክት የመጀመሪያና ወሳኝ ምዕራፉ በድል መጠናቀቁን ሲሰሙ ለዚያውም ገና ነው በሚሉበት ወቅት ስለነበር ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ ከምዕራብ መነሻ እስከ ምስራቅ ጠረፍ በደስታ የእንኳን ደስ ያለን መልዕክት ተለዋወጡ፡፡
ታላላቅ የዓለም መገናኛ ብዙኃን ከኢትዮጵያ የሰሙትን ዜና ለዓለም ደጋግመው አሰሙ፡፡ ኢትዮጵያ በጥረትዋ የታላቁን ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር ውሃ ሙሌት ማሳካቷን በልሳኖቻቸው ለሚሰማቸው ሁሉ ሹክ አሉ፡፡ በተለይም ቢቢሲ፣ አልጀዚራ፣ ሲኤንኤን፣ አጃንስፍራንስ ፕሬስ፣ ሲሲቲቪ፣ ኒዮርክ ታይምስ እና ሌሎች አለማቀፍ መገናኛ ብዙኃን በግድቡ ሙሌት ዜና የኢትዮጵያውያን ደስ መሰኘትና የግብጾች መከፋት በስፋት ሲዘግቡ ዋሉ፡፡
መገናኛ ብዙኃኑ የኢትዮጵያውያን ፀንቶ ለግድቡ ያልተቆጠበ ጥረት ማድረግንና ለስኬትም መብቃት አወደሱ፡፡ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ምዕራፍ ውሃ ሙሌት መከናወኑን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥትና የኢትዮጵያ ዜጎች በከፍተኛ ሁኔታ ደስታቸውን ሲገልጹ ግብጽ ግን በነገሮች አካሄድ ምንም ደስተኛ እንዳልሆነች በብዙ ዘገቡ ፡፡
በእርግጥ የታችኛው ተፋሰስ አገራትና ከእነሱ ጋር በጥቅም የተሳሰሩ አንዳንድ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን እድገት አለመፈለጋቸውን በህዳሴው ግድብ ላይ በነበራቸው አቋም ሲያመላክቱና ኢትዮጵያም ስራውን በተሳካ መልኩ እንዳታከናውን የተለያዩ አሉታዊ ጥረቶች ሲያደርጉም ቆይተዋል፡፡
በመጨረሻም ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት ማጠናቀቋን ይፋ የማድረግዋን ዜና ሲሰሙ ተቃወሙ፤ በዚህ አላበቁም፤ የተለያዩ አሉታዊ አጀንዳዎች ያነገቡ ተቃውሞዎች ማውጣታቸውን ቀጠሉ፡፡ በተለይ ግብፅ የህዳሴ ግድብን የውሀ ሙሌት ኢትዮጵያ ያለታችኛው ተፋሰስ አገራት ፍቃድ ማከናወኗ እጅጉን ቁጭት ውስጥ ገብታም ነበር፡፡ ያኔ ልክ እንደዛሬም “እስኪ እኔ ሳልፈቅድ አድርጉና” የሚለው የግብፅ ፉከራና ኢትዮጵያ በራስዋ ተፈጥሯዊ ሀብት የመልማት ዕቅድዋ ማንም ሊያስቆማት የማይችል አቋሟ መሆኑን ደጋግማ ስትገልፅም ነበር፡፡
ግድቡ በውሃ ሙሉ ለሙሉ ሲሞላ ውሃ በአንድ ሺ 874 ስኲየር ኪሎሜትር ስፋት ላይ ይንጣለላል፤ በ4 ዙር በአጠቃላይ 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሀ መያዝም ይችላል፡፡ ግድቡ የዛሬ ዓመት ልክ በዚህ ሳምንት የመጀመሪያው ዙር ውሀ ሞልቷል የተባለውን ያህል ኢትዮጵያውያን ዘንድሮም ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት በጉጉት ሲጠባበቁ ቆይተዋል፡፡ ዋንኛ ጉዳያቸው ልማትና ለውጥ ነውና ዛሬም ሁለተኛው ዙር የውሀው ሙሌት መጠናቀቅ አሰፍስፈን በታላቅ አገራዊ ስሜት የመጠበቃችን ያህል የሚያስቀድሙት ምንም የለም፡፡
በእርግጥ ያኔ የህዳሴው ግድብ የመጀመሪያው ዙር የውሀ ሙሌት መጠናቀቁ ሲነገር ብዙዎቻችን የደስታ ሲቃ ውስጥ ነበርን፡፡ ታዲያ በዚያ ታሪካዊ ሳምንት ኢትዮጵያውያንን ያስደሰተው ዜና ካበሰሩት ውስጥ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ታሪካዊ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት ይገኝበታል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ውስጥ የህዳሴው ግድብ የመጀመሪያ ዙር ሙሌት መሳካት የእንኳን ደስ ያላችሁ መልካም ምኞት መግለጫ ጋር ግድቡን የተመለከቱ አጠቃላይ ሁኔታዎችን የሚያመላክት ነበርና ይህን ታሪካዊ መልዕክት በዚህ የታሪክ ትውስታ ጽሁፍ ማካተት ወደድን፡፡
ዜናው በተሰማበት ዕለት የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ለኢትዮጵያውያን ያስተላለፉት ታሪካዊ መልዕክት መካከል ለትውስታ የሚከተለው የሚከተለውን እንመልከት፡፡
“የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ሕዝቦች፤ ዛሬ አገራችን በላቀ ጉጉት የምትጠብቀውን ብስራት የምትሰማበት ዕለት ነው። የዓመታት ልፋታችን ወሳኝ ምዕራፍ ላይ የደረሰበት፣ የህዳሴው ግድባችን የመጀመሪያ ዙር የውኃ ሙሌት የተጠናቀቀበት ታሪካዊ ዕለት ነው። በጋራ ጥረታችን ግድባችንን እዚህ ደረጃ ስላደረስነው መላው የአገራችን ሕዝቦች እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እወዳለሁ።
‹‹ በዚህ ዕለት እኛ ኢትዮጵያውያን ዳግም አገር ተኮር ስራ ሰርቶ እንዴት ማሳካት እንደሚቻል አውቀናል፤ ሰርቶ አንድ ምዕራፍ ላይ መድረስ የሚያስገኘውን ደስታ በድጋሚ ማጣጣም ጀምረናል። ይበልጥ የሚያስደስተው ማንም ባልተማመነብን ወቅት በራሳችን አቅም ላይ ዕምነት ኖሮን ማሳካት በመቻላችን ነው። አንዳንዶች ሕዳሴው ግድብ ላይ ሙጭጭ ማለታችን ምስጢሩ አይገባቸውም። የታችኛው የዓባይ ተፋሰስ አገራትን ለመጉዳት አልመን የነደፍነው ተንኮል ይመስላቸው ይሆናል፤ እውነታው ግን ያ አይደለም።
‹‹ሕዳሴ ግድባችን የዚህ ትውልድ መለያ ማኅተም፣ ሰርቶ የማሳካት ትእምርት ነው። የዘመናት ቁጭታችን መልስ ማግኘት መጀመሩን የምናበስርበት ፋና ነው። አንገታችንን ሊያስደፉ ሲከጅሉ ለነበሩት ሁሉ የጫኑብንን የድህነትና የኋላቀርነት ሸክም ወዲያ
ልናሽቀነጥር መቁረጣችንን ጮክ ብለን የምንናገርበት ድምጻችን ነው። እንግዲህ ”ግድባችን” በሁለት እግራችን መቆም እንደማይሳነን፣ ወደ ከፍታው ለማቅናት የመታጠፊያ ነጥባችን መሆኑን ዓለም በትክክል ይረዳል ብዬ እገምታለሁ። ››ሲሉ በእለቱ ተናግረዋል፡፡
‹‹እነሆ እንደተናገርነው ማንንም ሳናስቸግርና ማንንም ሳንጎዳ ባቀድነው ልክ የመጀመሪያውን ዙር ውኃ ሞልተናል። መስከረምን ጨምሮ፣ ክረምቱ ገና ሁለት ወር ተኩል ይቀረዋል። የዝናቡ መጠንም እየጨመረ ነው። እኛም ፈጣሪ ረድቶን ከታቀደለት ጊዜ ቀድሞ የግድቡ ውኃ ሞልቶ መፍሰስ ጀምሯል። ግድባችን እንኳንስ ጉዳት ይቅርና በተቃራኒው ለታችኛው ተፋሰስ አገሮች ጥቅም ሊያስገኝ እንደሚችል የተናገርነውም አሁን በተግባር ይረጋገጣል። ስንገነባውም ሆነ ወደፊት ስናስተዳድረው ግብጽና ሱዳንን የመጥቀም እንጂ የመጉዳት ሀሳብ በእኛ ዘንድ ፈጽሞ የለም። ሁለቱም አገሮች የሚያገኙት ውኃ ሳይቀንስ የመጀመሪያውን ሙሌት ማጠናቀቃችን ለዚህ የተግባር ማሳያ ነው። ብለዋል፡፡
ውድ ኢትዮጵያውያን፤ ይሄ እኛ ያየነውን ግድብ ለማየት፣ የሰማነውን የግድቡን ዜና ለመስማት፣ በመዋጮው ላይ ለመሳተፍ ብዙ ትውልዶችና ብዙ መሪዎች ተመኝተው ነበር፤ ዳሩ ግን አልቻሉም ። እኛ እዚህ ዘመን ደርሰን ዓባይ ከዘፈንና ከማስፈራሪያነት አልፎ፣ ማንንም ሳይጎዳ ተገድቦ፣ ግድቡም ውኃ ይዞ ለማየት በቃን ። ይሄን ያዩ አይኖቻችንና ብስራቱን የሰሙ ጆሮዎቻችን ምንኛ ዕድለኞች ናቸው?
በህዳሴው ግድብ ስም የግል ጥቅማቸውን ሲያሳድዱ የነበሩ ጥቂቶች የመኖራቸውን ያህል ግድቡ እውን እንዲሆን ብዙዎች ለፍተዋል፤ ሳይሰስቱ ጉልበታቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ ጊዜና ዕውቀታቸውን ሰውተዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከምንም በላይ አይተኬ ሕይወታቸውን ለሕዳሴው የገበሩለትም እንዳሉ ጠቅሰዋል። በተከፈለው ዋጋ እነሆ የዘመናት ሕልማችን እውን ሆኗል። ዛሬ የምንወቃቀስበት ጊዜ ሳይሆን የምንመሰጋገንበት ዕለት ነው ሲሉም አብራርተዋል።
ግድቡን ያቀዱ አመራሮች፣ ፕሮጀክቱን ሲያስተዳድሩ የነበሩ መሪዎች፣ ሌት ተቀን በግድቡ ስራ ተሰማርተው የደከሙ ሰራተኞች፣ በየመድረኩ ኢትዮጵያን ወክለው ስለግድቡ ሲደራደሩ የነበሩ የቁርጥ ቀን ልጆች ይሄን ዕለት እንድናይ አድርገዋል። ከዕለት ጉርሳቸው ቀንሰው መዋጮ ያዋጡ ዜጎቻችን እና በዕውቀታቸው ሲያግዙ የነበሩ ባለሙያዎችን ስም እንዘርዝር ብንል ቀናት ይፈጃል።
እንዲሁ በአጠቃላይ የቀድሞዎቹን ጠቅላይ ሚኒስትሮች እና በግድቡ ግንባታ ሂደት ላይ ቀጥተኛም ተዘዋዋሪም ተሳትፎ የነበራቸውን አካላት በሙሉ፣
በዲፕሎማሲውም መስክ ከፍተኛ ተጋድሎ ያደረጉትን ጭምር ከልብ ሳላመሰግን አላልፍም። እኛ እንደ አገር የመውቀስና የመኮነን እንጂ የምስጋና ባህል በመጠኑ ይጎድለናል። ትልቁ ወንዛችን ዓባይ ራሱ የዘመናት ወቀሳችን ሰለባ ነበር ። በርግጥ ወቀሳው ያለምክንያት አልነበረም፤ እኛን ትቶ ሌሎችን ሲጠቅም ኖሯል። ከእንግዲህ ዓባይም ለእናት ሀገሩ መልካም አስተዋጽኦ ለማበርከት ከጫፍ ደርሷልና አፍ አውጥተን ልናመሰግነው ግድ ይለናል ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን ዓባይን በተመለከተ ሲመኙ ከኖሩበት ረዥም ዘመን አንጻር፣ የህዳሴው ግድብ ቢያንስ የዛሬ ሁለት መቶ አመት መገደብ ነበረበት። መሪዎቻችንና ሕዝባችን ፍላጎት ነበራቸው። ሁኔታዎች ግን አልሰመሩላቸውም። እኛ ግን እነርሱ ያሰቡትን አደረግነው፤ የተመኙትን አየነው፤ የናፈቁትን አሳካነው።
ድል ያስፈነድቃል። በድል ላይ እየፈነደቁ ተንጠልጥሎ መቅረት ግን ሁለት ጉዳት አለው። አንድም የተያዘውን ድል ያስነጥቃል፤ አንድም ለሌላ ቀጣይ ድል በር ይዘጋል። ለዚህ ደግሞ ሁነኛ መፍትሄው ያገኙትን ድል አድንቆና አመስግኖ፤ ነገር ግን እርሱን ተሻግሮ ማለፍ ነው። ልክ ደረጃ እንደሚወጣ ሰው። የደረስንበትን የደረጃ እርከን ለቅቀን ወደ ቀጣዩ የደረጃ እርከን ካልወጣን፣ ወደ ኋላ መመለሳችን አይቀሬ ነው። ወደ ከፍታ መጓዝ የሚቻለው ከሚናፍቁት የደረጃ እርከን ለመድረስ በመጓዝ፤ ሲደርሱበት ደግሞ እርሱን ትቶ ወደቀጣዩ በማለፍ ነው። ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ሰሞኑንም ኢትዮጵያውያን ወሳኝ ምዕራፍ የተባለው የሁለተኛውን ግድብ ውሀ ሙሌትም ፈጽመዋል፡፡ አገሪቱ በእርግጥ ዛሬ በዚህ ሁሉ ስኬት ውስጥ እልህ አስጨራሽ መሰናክልና ጫናዎች በታችኛው ተፋሰስ አገራትና ከእነሱ ጋር በጥቅም በተሳሰሩ መንግሥታት ሲደርስባት ቆይቷል። ነገር ግን ኢትዮጵያ በእነዚህ ኃይላት የምትረታ አልነበረችምና ጉዞዋን ቀጥላለች። በጠንካራ አገራዊ ስሜት የቆሙ ኢትዮጵያውያን በሚያደርጉት ጥረት ታላላቅ ውጤቶችና ስኬቶችን ተጎናፅፋለች፡፡
ኢትዮጵያውን በዓለምአቀፍ መድረኮች ጭምር የአፍሪካውያን ጉዳይ በአፍሪካ በሚል አቋም በህዳሴው ግድብ ላይ የሚደረገው ድርድርም ሆነ ስምምነት በባለቤቶቹ ብቻ እንዲወሰን ታግለው መርታት ችለዋል። ነገ ከነገ ወዲያ ደግሞ በሚሰሙት የድል ዜናዎች ታጅቦ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ሁሌም አሸናፊ ይሆናል። ግድቡም በታሰበው መልክ ተሳክቶ እውን ይሆናል። እኛም የሆነ ዘመን ላይ ቆመን ኢትዮጵያ የህዳሴው ግድብ ግንባታዋን አጠናቃ ኃይል ማምረት ጀመረች የሚለውን ዜና እንዘግባለን፡፡ እስከዚያው ቸር ያቆየን፤ አበቃሁ፡፡
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2013