በሀገራችን የኮቪድ ስርጭት እየቀነሰ ይመስላል፡፡ የጤና ሚኒስቴር እለታዊ የኮቪድ መረጃ እንደሚያመለክተውም ስርጭቱ እየተስፋፋ ነው የሚያስኝ ሁኔታ የለም፡፡ አንድ ሰሞንም ለጥቂት ቀናት በበሽታው የሞተ እንዳልነበረም ሳስታውስ ስርጭቱ እየቀነሰ መሆኑን ታሰበኝ፡፡
እንዲህ ዓይነቱን ለውጥ በተለይ በኮቪድ ሣቢያ ሰው ያልሞተበትን ቀን ፈረንጆች ምን ያህል እንደተደሰቱበት መገናኛ ብዙሃን አጋርተውን ተመልክተነዋል፡፡ በርግጥም በአንድ ጀንበር እምስትና ስድስት ሺህ ሰዎች ይሞቱ ከነበረበት ሁኔታ ምንም የማይሞትበት ደረጃ ላይ መድረስ ትልቅ ድል ነውና ፈንጠዝያው ትክክል ነው፡፡
ከዚህ አኳያ እኛም ሀገር በአንድ ቀን ከሠላሳ በላይ ዜጎች ይሞቱ የነበረበት ሁኔታ አንድም ሰው ያልሞተበት ሁኔታ ላይ ሲደረስ፣ ሁለትና ሦስት ሰዎች ወደሚሞቱበት ሁኔታ ዝቅ ማለት ሲቻል ትልቅ ሥኬት ነው፡፡
ይህ ማለት ግን በሽታውን ከመከላከል መቆጠብ ያስፈልጋል ማለት አይደለም፡፡ ዓለም አቀፍ የበሽታው ሥርጭት መቀነስ ሁኔታም ይህንን አያመለክትም፡፡ በሽታው በባህሪው ሄደ ሲሉት የሚመጣ፣ ባህሪውን የሚቀያይር ነውና ከመከላከል መታቀብ አያዋጣም፡፡
ለዚህም ነው የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና የጤና ሚኒስቴር ለአፍታ እንኳ ከአጠገቡ አልተነሱም፡፡ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ ማድረጉን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት እያሳሰቡ ናቸው፡፡ በየጊዜው የበሽታው ሥርጭት ያለበትን ሁኔታ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ይገመግማሉ። አዳዲስ መመሪያዎችን በማውጣትም ህብረተሰቡ የመከላከል ሥራውን እንዲያጠናክር የሚያስችሉ አሠራሮችን እየቀየሱ ይገኛሉ፡፡
ከዚህ አኳያ በአዲስ አበባ በሽታውን ለመከላከል እየተወሰደ ያለው ርምጃ ጥሩ የሚያሰኝ ነው፡፡ መሥሪያ ቤቶች ሠራተኞቻቸው ማስክ እንዲያደርጉ ያስገድዳሉ፡፡
አሁን ትንሽ መላላት ቢታይም አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ማስክ ላላደረገ ተገልጋይ አገልግሎት አይሰጡም፡፡ ማስከ ያላረገ ወደ ግቢያቸው ሕንጻቸው አያስገቡም፡፡
ማስክ ሣያደርጉ ትራንስፓርት ላይ መሣፈር ክልክል ነው። ታክሲዎች፣ የከተማ አውቶብሶች፣ ሌሎች ተሸከርካሪዎች ውስጥ የሚጠቀምም እንዲሁ ማስክ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ አሽከርካሪዎች ተሣፋሪ ሲያስገቡ ማስክ መደረግ አለመደረጉን ይቆጣጠራሉ፡፡ እዚህ ላይ መኪና ሣያንቀሳቀስሱ በፊት ማስክ ያላደረገ መኖር አለመኖሩን የሚከታተለው የትራንስፖርት ተቆጣጣሪው አካልም እነሱም ሊመሠገኑ ይገባል፡፡ ቅጣት ፈርተውም ቢሆን በቁጥጥሩ ጠንክረዋል፤ ለነገሩ በሽታው እንጂ ቅጣቱ አልነበረም መፈራት የነበረበት፡፡ ውጤት እስካስገኘ ድረስ ቀን እስኪያልፍ ይሁን ግዴለም፡፡
ከትራንስፓርት ሲወረድ ከመሥሪያ ቤት ሲወጣ ያለው ሁኔታ ግን ያሣስባል፡፡ ውጪ ላይ አብዛኛው ሰው ማስክ አያደርግም፡፡ የሠለጠነ ሕዝብ በብዛት አለበት ተብሎ በሚታሰበው አዲስ አበባ ከተማ፡፡
ርቀትን መጠበቅ፣ ማስክ በአግባቡ ማድረግ የግድ ሆኖ ሣለ ይህን በአግባቡ ሲፈፀም የማይታይባቸው በርካታ መድረኮችንም እያየን ነው፡፡ ሠርጉ፣ መልሱ፣ ቅልቅሉ፣ ለቅሶው፣ ወዘተ…ኮቪድን የዘነጉ ሆነዋል፡፡
አሁን ወቅቱ የምረቃ ነው፡፡ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎቻቸውን እያስመረቁ ናቸው፡፡ ብዙዎቹ ምረቃውን በስታዲየሞች ማድረጋቸው ለመከላከል ሥራው ይጠቅማል። እዚያም ቢሆን ግን ማስክ ማድረግ መዘንጋት የለበትም፡፡ በየመገናኛ ብዙሃኑ የሚታዩ ምሥሎች ግን መከላከሉ የተዘነጋ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ ተመሳሳይ ምረቃዎች በአፀደ ሕጻናት፣ በብሄራዊ ፈተና ወሣጆች ዘንድም ስለሚካሄድ የመከላከል ሥራው ቤት ውስጥ ጭምር መዘንጋት አይኖርበትም፡፡ የኮቪድ መከላከል ሥራ አንዴ ምረቃችንን እንጨርስ ተብሎ የሚቆይ አይደለም፡፡
ቀደም ሲል ከምርጫ ጋር ተያይዞ የድጋፍ ሠልፎች ይካሄዱ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት በመላ ሀገሪቱ እጀግ በርካታሕዝብ የተገኘባቸው ሠላማዊ ሠልፎች እየተካሄዱ ናቸው። እነዚህም ላይ በመገናኛ ብዙሃን ከሚቀርቡ ምሥሎች መረዳት እንደሚቻለው የኮቪድ መከላከል ወዴት ነህ የሚያሰኝ ሁኔታ በሥፋት ታይቷል፡፡
ርግጥ ነው መድረኮቹ በይደር የሚቆዩ ዓይነት አይደሉም፤ የሀገር ፍቅር ሥሜት የተገለፀባቸውና የሕዝብ ሥሜት ገንፍሎ የወጣባቸው ናቸው፡፡ የሀገር እና የሕዝብ ሕልውና ለአደጋ ሲጋለጥ በየቤቱ ተቀምጦ መመልከት አይሆንም፡፡ ችግሮቹን በጋራ ለመከላከል አብሮ መምከር፣ አንድ ቃል መናገር ያስፈልጋል፡፡ መድረኮቹ ለወዳጅም ለጠላትም ሲባል መደረግ አለባቸው፡፡
ይህ እንዲሆን ሲፈለግ ግን ኮቪድ መከላከሉም ሀገራዊ አጀንዳ ነውና ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹን መድረኮች የሚያስተባብሩ አካላትም ለኮቪድ መከላከሉ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት አለባቸው፡፡ ሠልፍ የሚወጣ በሙሉ ማስክ ማድረግ እንዳለበት ማሳሰብ፤ አርጎ ካልመጣ አለማስተናገድ ያስፈልጋል፡፡ በቀጣይም ተመሳሳይ መድረኮች እንደሚኖሩ ይጠበቃልና በዚህ መልኩ ቢቃኝ ጥሩ ነው፡፡
ቅርብ ጊዜ በወጣ የኮቪድ መከላከያ መመሪያ መሠረት በከተማ አውቶብስ የሚጫነው ቁጥር እንደ ፊቱ ባይሆንም ገደብ ተጥሎበታል፡፡ በድጋፍ ሰጪ አውቶብሶች ቆሞ መሄድ ክልክል ነው፡፡ በአንበሣና ሸገር አውቶብሶች ቆሞ እንዲሄድ የሚፈቀደው ጥቂት ሰው ብቻ መሆን አለበት፡፡
ይህ ግን በአግባቡ እየተተገበረ አይደለም፡፡ በሀይገርም በሸገርም በአንበሣም ሰው በሰው ላይ እየተጫነ ነው። የሸገር አውቶብሶች በፊት በራቸው ተሣፋሪ አያስገቡም አያስወጡም። ከሾፌሩ ጀርባና ከትኬት ቆራጭ አካባቢ ሰው እንዲቀመጥም ሆነ እንዲቆም አይፈቀድም፡፡ ያንን አካባቢ ለኮቪድ መከላከል ጥሩ አድርገውታል፡፡ ችግሩ ያለው ግን የእነሱን ቀጠና ከኮቪድ እየተከላከሉ ሕዝቡን እየጠቀጠቁ መጫናቸው ላይ ነው፡፡ ወደኋላ ዞረው ተጠጋጉ ይላሉ፤ ያስገባሉ፡፡ ይህ መስተካከል አለበት፡፡
ማስክ ያደረገን ከተሜ በመመልከት ኮቪድን የከተማ በሽታ ያደረጋችሁ የክልል ሰዎች አመለካከታችሁን ቀይሩ፤ ማስክ የማትጠቀሙ ከተሜዎችም በየመሥሪያ ቤቱ በየትራንስፖርቱ ማስክ የሚጠቀሙ ስትመለከቱ በሽታው ያለው በየመሥሪያ ቤቱና ትራንስፖርቱ ላይ ነው አትሉም ተብሎ አይገመትም፡፡ እናንተም አመለካከታችሁን ቀይሩ ብያለሁ፡፡
እናስተውል፤ የቅርብ ጊዜ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ይህ በሽታ በሀገራችን ብቻ ከ4 ሺህ 360 በላይ ዜጎችን ሕይወት ቀጥፏል፡፡ በአጠቃላይ ከ278 ሺህ 230 በላይ ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ11 ሺህ 110 በላይ ሰዎች ቫይረሱ አለባቸው፡፡ በሽታው ውድ የሀገር ባለውለታዎችን ጭምር አልማረልንም፡፡ ነጥቆናል፡፡ ይህ አሀዝ በሽታው ምን ያህል አሳሳቢ ስለመሆኑ ይናገራል፡፡
እናም አውቆም ይሁን ሣያውቅ እነዚህ ሁኔታዎች እንዲደገሙ ማንም መፍቀድ የለበትም፡፡ የኮቪድ መከላከል ጉዳይ ለአፍታም ሊቀዛቀዝ አይገባውም፡፡ መከላከሉን እከሌ የሚተገብረው እከሌ የማይተገብረው አይደለም፡፡ ክትባት የወሰደ ጭምር የሚተገብረው ነው፡፡ ጥቂቶችን ብቻ ባስከተበች ሀገር መዘናጋት ዋጋ ያስከፍላል፡፡
ዓለም አቀፍ ሁኔታም ይሁን በኮቪድ ክፉኛ የተጎዱ ሀጎሮች ሁኔታ የሚያሣየው መዘናጋት ዋጋ እንደሚያስከፍል ነው፡፡ ከበሽታው ባህሪ አኳያ ሲታይ ኮቪድ አያገረሽም ተብሎ አይታሠብም፡፡ አሁን የያዝነውን የመከላከል ሥራ እያጠናከርን መሥራት ይኖርብናል፡፡
የጤና ሚኒስቴር በቅርቡ በሰጠው መረጃ በየጤና ጣቢያው የኮቪድ መመርመሪያዎች ዝግጁ ተደርገዋል። በአጭር ጊዜም ውጤት መንገር የሚቻልበት ሁኔታም ተፈጥሯል። ሥጋቱ ያለው ሰው ጤና ጣቢያዎቹ በመሄድ መመርመር ይችላል፡፡ በተለያዩ ሕዝባዊ መድረኮች፣ ምረቃዎችና ሕዝብ በሚበዛባቸው መድረኮች ላይ የተገኛችሁ ሁሉ ምርመራ ብታደርጉ ራሣችሁንም፣ ህብረተሰቡንም ሀገርንም መታደግ ትችላላችሁና አድርጉት!
ዘካርያስ ዶቢ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2013