የተወለደው ጎንደር ውስጥ ነው፡፡ ነገር ግን እትብቱ የተቀበረባትን ጎንደር ትቶ በወላጆቹ እቅፍ ውስጥ እንዳለ ጎንደርን የተሠበናበታት ገና የ6 ወር ጨቅላ ሣለ ነው፡፡
ማረፊያው ከአዲስ አበባ 50 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኘው ሌላኛዋ አንጋፋ ከተማ አዲስ አለም ነበረች። በታሪካዊቷ ከተማ የልጅነት ዕድሜውን ያሣለፈው ረዳት ፕ/ር ነቢዩ ባዬ ከአንደኛ እስከ 6ኛ ክፍል ያለውን ትምህርቱን በታላቁ ሊቅ አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ ሥም በተሠየመው ትምህርት ቤት ነው የተከታተለው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ እስከ 9ኛ ክፍል ያለውን ትምህርቱን በዚያው በአዲስ አለም አንደኛ እና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሯል፡፡
ከዚያ በኋላ ግን አዲስ አለምን ተሠናብቶ አዲስ አበባ መሀል ፒያሣ ላይ ከተመ፡፡ ከዚያ ወዲህ ያለው ትምህርቱንም በእቴጌ መነን ትምህርት ቤት ቀጠለ፡፡ በትምህርት አቀባበሉ ቀልጣፋ የነበረው ነቢዩ የከፍተኛ ትምህርት ውጤት አስመዝግቦም ከእቴጌ መነን ጋር ጎረቤት ወደሆነው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገባ፡፡
በትወና ሕይወቱ ብዙ እውቅናን ያተረፈው ነቢዩ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲገባ የትምህርት ምርጫው ያደረገው ቴአትርን ነበር፡፡ ይህ የነቢዩ ምርጫ ግን በሙሉ ድምጽ የፀደቀ አልነበረም፡፡ ራሱ ነቢዩ ተዋናይ መሆን ይፈልጋል፡፡
ገና በልጅነቱ የመጀመሪውን የትወና ዕድል የሰጡት የእንግሊዝኛ መምህር የነበሩት አባቱ ባዬ ንጋቱም የልጃቸውን ፍላጎት ይደግፋሉ፡፡ እናት ግን ከዚህ የተለየ ምኞት ነበራቸው፡፡ ልጃቸው ሕግ ተምሮ እሣት የላሠ ጠበቃ አሊያም ፍትሀዊ ዳኛ ቢሆን ነበር ምኞታቸው፡፡ በርግጥም አይፈረድባቸውም፡፡ ”በዚያን ጊዜ ቴአትር እማራለሁ ብሎ መምረጥ የሚያስገርም፤ የሚያስወቅስ፤ ቤተሠብም ጋር ጥያቄ የሚያስቀርብ ነበር” ይላል ነቢዩ፡፡ የሆነ ሆኖ ነቢዩ የቴአትር ተማሪ ሆነ፡፡
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ የቴአትር ትምህርቱን ሲጀምርም እነዚህ የልጅነት እና የአፍላነት የኪነ ጥበብ ተሞክሮዎቹ አግዘውት ካለው ፈጣን የትምህርት አቀባበል ጋር ተዳምሮ ትምህርቱን በማዕረግ ተመራቂነት አጠናቀቀ። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም እፈልግሀለሁ እዚሁ ቆይ አለው። በተማረበት ዩኒቨርሲቲ ማስተማር ጀመረ፡፡ ከረዳት መምህርነት የጀመረው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርነት በተለያዩ ሀላፊነቶች ቀጥሎ እስከ ዩኒቨርሰቲው ሴኔት አባልነት መጓዝ ቻለ፡፡
በዚያ ጊዜ ውስጥም ግን ከመድረክ መራቅ ያልፈለገው ነቢዩ በጎን ትወናውንም ያካሂድ ነበር፡፡ ገና ተማሪ እያለ የተወነው የመጀመሪያ ሥራው ‹‹አማጭ›› የሚል ሲሆን፤ የመተወን ዕድል ያጋጠመውም ከታላላቆቹ ደበሽ ተመሥገን፣ አለምፀሐይ በቀለ እና አዳነች ወ/ገብርኤል ጋር ነበር፡፡
ትወናው በአንድ ጎን እየሄደ በዩኒቨርሲቱ መምህር እና የትምህርት ክፍለ ዲን በነበረ ጊዜ በርካታ ሥራዎችን ሠራ፤ ከነዚህም መካከል ታሪካዊው የዩኒቨርሲቲው ባህል ማዕከል በድጋሚ እንዲነቃቃ፣ የቴአትር ትምህርት በማስተርስ ደረጃ እንዲሰጥ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው የክብር ዶክትሬት የሚሰጥበት ሕግ ሲረቀቅ መሣተፍ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በቴአትር ቤት ባለው ቆይታ በቴአትር ምሩቅ በሆነ ተዋንያን እና በተሰጥኦ ብቻ በሚተውኑ ተዋንያን መካከል ያለውን ክፍተት ለመሙላት የቴአትር ትምህርት በማታ መርሀ ግብር እንዲጀመር በማድረግ ብዙ አንጋፋ ተዋንያን ተምረው ራሣቸውን ብቁ እንዲያደርጉ የነበረው ሽኩቻ እንዲቀርም ጥረት አድርጓል፡፡
በ1994 ዓ.ም የመጀመሪያ ዲግሪውን በቴአትር ያገኘው ረዳት ፕሮፌሰር ነቢዩ፣ ከዚያም በኋላ መማሩን ሣያቆም ሁለተኛ ዲግሪውን በሥነ ጽሁፍ ከዚያም ዶክትሬቱን በአፍሪካ ጥናት አጠናቋል፡፡ ገና የመጀመሪያ ዲግሪውን ሣይጨርስ በጀመረው ትወናው በጣም በርካታ ቴአትሮችን፣ የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን ድራማዎችን እንዲሁም ፊልሞችን ተውኗል፡፡
ከእያንዳንዱ ዘርፍ ታዋቂ የሆኑ አንዳንድ ሥራዎችን ብንጠቅስ እንኳን በቴአትሩ ነቢይ ዤሮን፣ በቴሌቪዥን ድራማ ዳና፣ በሬዲዩ ድራማ የቀን ቅኝት እንዲሁም በፊልም ጤዛን መጥቀስ እንችላለን፡፡
በተዋናይነት በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅ የሆኑ ሥራዎችን የሠራው ረዳት ፕ/ር ነቢዩ በምሁርነትም በርካታ ጥናታዊ ጽሁፎችን ያቀረበ ሲሆን፤ በአሠልጣኝነት እና በአማካሪነት እንዲሁም ዳኛ በመሆን ሠርቷል፡፡ በተወዳጁ የሰው ለሰው ድራማ ተዋንያንን እንዲሁም የየኛ ድራማ ተዋንያንን ዳኛ ሆኖ ተሠይሞ የመረጠው ረዳት ፕ/ር ነቢዩ ነበር፡፡ ከዚህም ባለፈ በአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ፣ በፍልውሀ አስተዳደር፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቴሌቪዥን እና ሌሎች ተቋማትም በቦርድ አባልነት እና መሪነት ሠርቷል፡፡
ሀገራዊው ለውጥ እንደመጣም የብሄራዊ ቴአትር ሥራ አሥኪያጅ ሆኖ ለወራት የሠራው ረዳት ፕ/ር ነቢዩ በኋላ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ባህል ኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ ሆኖ ተሹሞ ሠርቷል፤ በዚህ የአመራርነት ዘመኑ የፊልም ሣንሱር እንዲቀር፣ የኪነ ጥበብ መዋቅር እስከ ወረዳ እንዲደርስ፣ ሀገር ፍቅር ቴአትርና ባህል አዳራሽ እንዲሁም ራስ ቴአትር እንዲታደሱ እና አዳዲስ ግንባታዎች እንዲካሂዱ አድርጓል፡፡ የፒያሣው የአድዋ ማዕከል እንዲገነባ ግፊት ካደረጉት ሰዎች መካከል አንዱ የነበረም ሲሆን፣ ታሪካዊዎቹ ሠይጣን ቤት እና አንበሣ ፋርማሲ እንዳይፈርሱ ያደረግኩት ትግልም በሕይወቴ የምኮራበት ነው ይላል፡፡
ከወ/ሮ የሸዋዘርፍ አዛናው ግን ትዳር መሥርቶ አማናዊት፣ ቃናልኡል እና ኆኅተ የተባሉ ሦስት ልጆችን ያፈራ ሲሆን፤ በዘንድሮው ስድስተኛ ብሄራዊ ምርጫ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤትን ተቀላቅሏል፡፡ በዚህም መሠረት የመንግሥት ሕግ አውጪ አካል የሆነውን ክፍል በመቀላቀል የእናቱን ምኞት በሌላ መልኩም ቢሆን አሣክቶታል፡፡
ስለ እረፍት ቀን ውሎው የጠየቅነው ረዳት ፕ/ር ነቢዩ የሚኖረው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ የመምህራን መኖሪያ ውስጥ መሆኑን ገለፀልን፡፡ እዚያ ብዙ ጓደኞች እንዳሉትና ከነሱ ጋራ የእግር ጉዞ እንደሚያደርግ ይገልጻል፡፡ ‹‹ሠፈራችንን እንጎበኛለን፤ አየር እንቀበላለን፤ እንሣሣቃለን፤ እንጫወታለን፤ እንከራከራለን፤ ስለሀገራችን ሀሳብ እንለዋወጣለን፡፡›› ይላል፡፡
በተረፈ አንዳንዴ ረዥም መንገድ መንዳት፣ ሙዚቃ ማዳመጥም እወዳለሁ፡፡ መጽሀፍትም አነባለሁ፡፡ በዚህ መልኩ አሣልፈዋለሁ፡፡” ብሎናል፡፡ እሱ አይንገረን እንጂ የረዳት ፕ/ር ነቢዩ የፌስ ቡክ ገጽ እንደሚጠቁመው ከሆነም ረዳት ፕ/ር ነቢዩ የእሁድ ማለዳን ከልጆቻቸው ጋር ከቤተ ክርስቲያን የማይቀሩ መሆናቸውን ነው፡፡
በመጨረሻም ባስተላለፉት መልዕክት “እምነት፣ ተሥፋ፣ ፍቅር መሠረታዊ እሴቶች ናቸው፡፡ እምነት ወሣኝ ነገር ነው፡፡ ተስፋም እንዲሁ በሁሉ ነገር ላይ ያስፈልገናል። ሁሉም ግን ፍቅር ይበልጣል እና ሰውን ሁሉ መውደድ በጣም ደስ የሚለኝ እና አስፈላጊ የሆነ ነገር ነው፡፡” በማለት ፍቅርን አጠንክሮ መያዝ እንደሚገባ መክረዋል፡፡
አቤል ገብረኪዳን
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2013