ታላቁ ፈላስፋ ፕሌቶ “ሪፐብሊክ” በተሰኘው ተወዳጅ የፍልስፍና መፅሃፉ ላይ በገፀ ባህሪነት የነደፈውን አርስቶትልን ተጠቅሞ ስለ “ደስታና ደስተኝነት” ሲያብራራ “ደስታ የሕይወት ሥነ ምግባራዊ ግብ ወይም ገጽታ እንደሆነ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ደስተኛ ሰው ደግሞ እነዚህን ሁሉ በአንድነት የያዘ መሆን አለበት” ብሏል፡፡ ስነ ምግባር ያለው እርሱ በተመሳሳይ ደስተኛና ከዛም የሚገኝ እርካታን የተጎናፀፈ መሆኑን ያስረዳናል።
ይህን መነሻ አርገን ነገሮችን በጥልቀት ለመመልከት ከሞከርን ቀሪው ዓለማዊ ቁስ፣ ሃብትና ዝና የሰውን ልጅ ደስተኛ የማረግ አቅሙ ከላይ ካነሳናቸው ውስጣዊ ምክንያቶች ቀጥሎ የሚቀመጥ ነው። የዛሬው ርዕሰ ጉዳያችንን በደስታና በምንነቱ ላይ ካረግን ዘንዳ እስቲ በሚከተለው አስተማሪ ታሪክ ላይ ተመስርተን “የደስተኝነትን” ትርጉም ለመፈለግ እንሞክር።
በአንድ የክረምት ወቅት አያቴ “እውቀት የህይወት ስንቅ” ይሆነኝ ዘንድ በተለመደው ብልሃቱ ያጫወተኝ አንድ ጉዳይ እዚህ ላይ መጠቀስ እፈልጋለሁ፡፡ ሶስት ወንድማማቾች በጫካ አጠገብ በሚገኝ ጎጆ ውስጥ ይኖሩ ነበር፡፡ ሁሉም ቅን እና ታታሪ ናቸው። በየቀኑ እንጨት ለመልቀም ወደ ጫካ ይጓዛሉ ፡፡ እንጨቱንም ጥሩ ዋጋ በሚያስገኝበት ገበያ ወስደው ይሸጡት ነበር፡፡ ህይወታቸውን በዚህ መልኩ ይመራሉ፡፡
ወንድማማቾቹ ሁል ጊዜም ለሰው የሚያዝኑ ስነ ምግባር ያላቸው ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ቁሳዊ በሆነ መልኩ ለራሳቸው ጥሩ ቢኖሩም ደስተኛ አልነበሩም፡፡ አንድ ቀን የለቀሙትን እንጨት ተሸክመው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ አንድ የእድሜ ባለጸጋ እናት በጆንያ ከባድ እቃ ተሸክመው ሲሄዱ ተመለከቱ፡፡ የእቃው ክብደት እኚህ እናት ክፉኛ አጎንብሰዋል፡፡ ወንድማማቾቹ ወዲያውኑ ወደ ድሃዋ ሴት ቀርበው ጆንያውን እስከ ቤታቸው እስከ ቤታቸው ለማድረስ ድረስ ተቀበሏቸው፡፡
ሶስቱም በየተራ ጆንያውን ተሸክመው ሴትየዋ ቤት ሲደርሱ በጣም ደክሟቸዋል፡፡ እኚህ እናት ድሃና ደካማ ቢመስሉም ተራ ሰው አልነበሩም፤ አስማታዊ ኃይል ነበራቸው፡፡ ወንድማማቾቹ ግን ይሄን አያውቁም። ሴትዬዋ በወንድማማቾቹ ሰው ወዳድነት በመደሰታቸው እንደ ሽልማት ለእነሱ ምን ብታደርግቸው እንደሚፈልጉ ጠየቋቸው፡፡
አንደኛው ፈጠን ብሎም “እኛ ደስተኞች አይደለንም፣ ይህ ለእኛ ትልቁ የስጋት መንስኤ ሆኗል” ሲል መለሰላቸው። እኚህ እናት ወንድማምቾቹን ምን ደስተኛ እንደሚያደርጋቸው ጠየቋቸው፡፡ ከሶስቱ ወንድማማቾች ታላቅ የሆነው “የሚያምር ግሩም መኖሪያ ቤት ከብዙ አገልጋዮች ጋር ባገኝደስተኛ ያደርገኛል። ከዚህ በላይ የምፈልገው ነገር የለም›› ይላቸዋል፡፡ ከታናናሾቹ አንዱ ደግሞ “ብዙ ምርት የሚሰጥ ትልቅ እርሻ ቢኖረኝ ደስተኛ ያደርገኛል፡፡ ያኔ ሳልጨነቅ ሀብታም መሆን እችላለሁ” ሲል ምኞቱን ተናገረ፡፡
ሶስተኛውና የመጨረሻው ደግሞ “ቆንጆ ሚስት ቢኖረኝ ደስተኛ እሆናለሁ፡፡ ወደ ቤት ስሄድ ትንሽዬ ፊቷ ያበራልኛል፤ እናም ጭንቀቴን እንድረሳ ያደርገኛል” በማለት ፍላጎቱን ገለጸ፡፡ አዛውንቷም “ጥሩ ነው። እንደ እኔ ያለ ምስኪን አቅመቢስ በመርዳታችሁ ብቻ ይህ ሁሉ ይገባችሁዋል፡፡ ወደ ቤታችሁ ሂዱ፣ እያንዳንዳችሁም እንደምትመኙት በትክክል እዛ ስትደርሱ ሆኖ ታገኙታላችሁ” በማለት አሰናበቷቸው።
ወንድማማቾቹ ስለ ሴትየዋ ሀይል ስለማያውቁ ሁኔታው አስገረማቸው፡፡ ትንሽ አረፍ ብለው ወደ ቤታቸው ተመለሱ፡፡ ከጎጆአቸው አጠገብም ሲደርሱም በአገልጋዮች ጥበቃ የሚደረግለት አንድ ግዙፍ መኖሪያ ቤት ተመለከቱ! ይሄን አይነት ቤት ማግኘት የተመኘው ታላቅዬው ነበር። ልክ በሩ ዘንድ ሲደርስ ሰራተኞቹ አቀባበል አርገው ወደ ውስጥ አስገቡት፡፡
ከእዚህ ትልቅ ቤት በተወሰነ ርቀት ላይ ደግሞ የእርሻ መሬት ታየ፡፡ በአካባቢው የነበረው አርሶ አደር መጥቶ የእርሻ ቦታው የሁለተኛው ልጅ መሆኑን አስታወቀ። በተመሳሳይ ሁኔታም ወዲያውኑም አንዲት ቆንጆ ልጃገረድ ወደ ሶስተኛው ልጅ ቀረበች እና ሚስቱ መሆኗን ነገረችው፡፡ ሁሉም በዚህ አዲስ የለውጥ ሂደት በደስታ ግራ ተጋቡ፡፡ ዕድለኛ እየተደሰቱ አዲሱን የአኗኗር ዘይቤ መላመድ ጀመሩ፡፡
በዚህ አይነት ሁኔታ አንድ ዓመት አሳለፉ፡፡ አሁን ሁኔታው የተለየ እየሆነ መጣባቸው፡፡ ታላቅየው የባለ ትልቁ ግቢ ቤት ባለቤት መሆን ይሰለቸው ጀመር፡፡ እሱ ሰነፍ ስለነበረ አገልጋዮቹ ያን ትልቅ ቤት በአግባቡ እንዲንከባከቡ አይቆጣጠርም፡፡ የእርሻ የታደለው ወንድሙ ደግሞ ከመሬቱ ጎን ለጎን ጥሩ ቤት ቢያሰራም መሬቱን በሚገባ ማረስ እና በወቅቱ በዘር መሸፈን ከባድ ሆኖ ያገኘዋል፡፡ ሶስተኛውም ልጅ ቆንጆዋ ሚስቱ እያፈቀረችው ብትመጣም እሱ ግን ምንም ደስታ ሊያገኝባት ሳይችል ይቀራል፡፡
በእዚህ የተነሳም ሁሉም ወደ ቀድሞው ሃዘናቸው ተመልሱ፡፡ መቆዘም ጀመሩ፡፡ ሶስቱም አንድ ቀን ይሰበሰቡና በጉዳዩ ላይ ለአሮጊቷ ጥያቄ ለማቅረብ ይወስናሉ፡፡ “እኚህ እናት አስማታዊ ሀይሎች አሏቸው፤ በዚህም ህልሞቻችንን ወደ እውነት ቀይረውልናል። በተመኘነው ልክ ደስተኛ መሆን ስለቻልን አሁንም የእሳቸውን እርዳታ መፈለግ አለብን፡፡ ደስታ የማግኛ ሚስጥሩን ሊነግሩን የሚችሉት እሳቸው ናቸው” በማለት ተስማሙ፡፡
ወደ አሮጊቷ ይሄዳሉ፤ እሳቸው ጥደው ወጥ እየሰሩ ያገኙዋቸዋል፡፡ ወንድማማቾቹ ተራ በተራ ሰላምታ ከሰጧቸው መጀመሪያ ደስተኛ እንደነበሩ አሁን አሁን ደግሞ ደስተኛ መሆን እንዳልቻሉ ገለጹላቸው፡፡ የሆነውንም ሁሉንም በዝርዝር አስረዷት።
‹‹እናታችን እባክዎትን ደስተኛ መሆን የምንችለው እንዴት ቢሆን ነው ይንገሩን” በማለት ተማፀኗቸው። አሮጊቷ “ደህና” ካሉ በኋላ መልሱን ይነግሯቸው ጀመር። ‹‹ ሁሉም ነገር በገዛ እጃችሁ ውስጥ ነው ያለው። እያንዳንዳችሁ ምኞታችሁ ሲፈፀም እና ሲሳካላችሁ ደስተኛ ነበራችሁ፡፡ ሆኖም ፣ ደስታ በጣም አስፈላጊ ነገር ቢሆንም ያለ እርካታ እስከመረሻው በጭራሽ አይቆይም። ደስታን የሚያጠፋው በተሰጣችሁ ነገር መርካት አለመቻል ነው። እርካታን መማር ከቻላችሁ ብቻ እውነት በደስታ ለብዙ ጊዜያት መኖር ትችላላችሁ” አሏቸው።
በዚህ ጊዜ ሁሉም ስህተታቸውን ተገንዝበው ወደ ቤታቸው ተመለሱ፡፡ በአንድ ወቅት ይመኙ የነበሩትን ሁሉ በማግኘታቸው ምን ያህል ዕድለኞች እንደሆኑ አሰቡ፡፡ ትልቅ የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሆነው ታላቅየው የሆነውን ሁሉ እያመሰገነ መኖር ጀመረ፡፡ ሁለተኛውም ጥሩ ምርት ለማግኘት እርሻውን በትጋት ማረስ ውስጥ ገባ፡፡ ሶስተኛውና የመጨረሻውም ቆንጆ ሚስቱ ቤት ውስጥ የምትሰራውንና ለእሱ ያላትን ፍቅር ማድነቅ ተማረ፡፡ ደስታ እና እርካታ ጎን ለጎን እንደነበሩ ማሰብ ውስጥ ገቡ፡፡ ወንድማማቾቹ በረከቶቻቸውን እንደ ቀላል መመልከቱን ተው፡፡ ከዚያ በኋላ በደስታ ኖረዋል። እኛስ በእጃችን ውስጥ ያለውን አስተውለን አመስግነንና ረክተን ይሆን?
እንዳለ ከበደ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2013