ኃይለማርያም ወንድሙ
የቆዳ ኢንዱስትሪ በኢትዮጵያ አንድ ምእተ ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረና በአገራችን አንጋፋ ከሚባሉት ኢንዱስትሪዎች ቀዳሚ ነው። የኢትዮጵያው ብሔሮች በባህላዊ መንገዶች ቆዳን ለበርካታ አገልግሎት ይጠቀሙበት ነበር። ጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ትልካቸው ከነበሩት መካከል ቆዳን ጨምሮ ዝባድ፣ የዝሆን በግንባር ቀደምነት እንደሚጠቀሱ ሰነዶች ያስረዳሉ።
ከቅርብ ግዜ ወዲህም ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት ዜጎች በርካታ የቆዳ ኢንዱስትሪዎች ተመስርተዋል፤ በማይክሮ እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ በተወሰነ መነሻ ካፒታል ተደራጅተው እየሠሩ ነው። ከቆዳ ልማት ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት ያገኘነው መረጃ እንደሚያስረዳው በአገሪቱ 400 የሚጠጉ ማይክሮ እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ቡድኖች ተደራጅተው የቆዳ ውጤቶችን በማምረት ላይ ይገኛሉ። እኛም የቆዳ ጫማዎች አልባሳት ምን ይመስላሉ በሚል በኢንተርፕራይዝ ተደራጅተው የሚሠሩትን አነጋግረን ነበር።
በደቡብ ክልል ከአዲስ አበባ መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ባለችው ቡዒ ከተማ የሚሠሩት አቶ ግሩም ድንቅ በቆዳና ቆዳ ውጤቶች ሥራ 25 ዓመት እንደቆዩ ይናገራሉ። አዲስ አበባ ይሠሩ እንደነበርና በኋላ ወደ ክልል ገባሁ ይላሉ። ሙያውን በልምድ ያገኙ ሲሆን ቀስ በቀስ አቅማቸውን አሳደጉ። በዚህም በፒያሳ ጆይ ሌዘር በባለሙያነት የሠሩ ሲሆን ሥራ አስኪያጅ ሆነውም አገልግለዋል። ቀጥሎ በመርካቶ ዳሎል የቆዳ ውጤቶች መደብርም በሥራ አስኪያጅነት ሠርተዋል።
ልምዳቸውን አጎልብተው አቅም ፈጥረው በቡኢ ከተማ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ሥራ ከጀመሩ አምስት ዓመት እንደሆናቸው ይናገራሉ። ዋና ሥራችን የቆዳ ጃኬት ነው የሚሉት አቶ ግሩም ድንቅ ፤ ቀበቶ፣ የሴት ቦርሣና ሳምሶናይት የሚባል ትልቅ ቦርሣ፤ ጫማዎችን ይሠራሉ። በክረምቱ የቆዳ ጃኬት የሚሸጥበት ወቅት ነው፤ ተፈላጊ ነው።
“በፊት ቆዳ ጃኬት በስስ ገበር ይሠራ ስለነበር በጋ በጋ ይሞቃል ክረምት ሲሆን የመቀዝቀዝ ጸባይ አለው” የሚሉት አቶ ግሩም እሳቸው የክረምቱን ቅዝቃዜ ሙቀት በሚፈጥር ፈር ገበር የቆዳውን ጃኬት እየሠሩ እንደሚሸጡ ተናግረዋል። ጃኬቱ ያሞቃል በተጨማሪም ዝናብ ይከላከላል። ውሃ ስለማያስገባ የቆዳ ጃኬት በክረምት ወራት እንደፋሽን በገበያ በጣም ተፈላጊነት አለው ይላሉ። ለቆዳ ሥራ የሚሆኑ ግብአቶች ግን በጣም እየተወደደ ነው፤ ቁሶቹ በብዛት ከውጪ ስለሚገቡ አንድ የቆዳ ጃኬት ወደ 3ሺ ገደማ እየሄደ ስለሆነ ከዕሴት ታክስ ጋር 3ሺ 500 ነው የሚጠጋው፤ በዛ ነው እየሠራን ያለነው። በክረምት አየሩ በአብዛኛው ቀዝቃዛ እና ዝናባማ ስለሆነ ቆዳ ተመራጭ ነው። ዝናብም ሲሆን ቢያንስ ከወገባቸው በላይ ዝናብ ሳይነካቸው ኩልል ብሎ ይወርዳል።
ከሁለት ዓመት ወዲህ ለቆዳው ምርት የሚሆን የግብአት እጥረትና ለተመረቱትም ቆዳዎች የገበያ እጦት ተግዳሮት እንደሆነባቸው አቶ ግሩም ድንቅ ይናገራሉ። ግብአት አለማግኘት ማለት ለሚመረቱ ቆዳ ውጤቶች ችግር ነው። የሚመጡትም ቆዳዎች ለሀገር ውስጥ ተብለው ደረጃቸው የወረዱ ናቸው። ጥራት ያለው ቆዳ ወደ ውጪ የሚላክ ነው። ኤክስፖርት ደረጃ ያለውን ቆዳ አናገኘውም።
ከአዲስ አበባ ንግድና ልማት ባለሙያዎችም ጋር ተነጋግረናል፤ በቀጣይ መሥራት እየቻሉ አቅም እያላቸው ብር ያጠራቸው ተስፋ ይኖራቸዋል ብለን እናስባለን። ኢንተርፕራይዞችን አደራጅተን ወደ ፋብሪካ እናሳድጋለን ብለውን የነበረ ቢሆንም እየሠራን እየጠበቅን ነው። መሥራት ግድ ስለሆነ መንግሥት ደገፈን አልደገፈንም እንሠራለን ይላሉ። “መንግሥት ሲያግዘን የበለጠ ውጤታማ እንሆናለን፤ ለወጣቶች የሥራ ዕድል አንፈጥራለን የገበያ ዕድል እናሰፋለን። መንግሥት ሥልጠና ሰጥቶናል የምንሠራበትንም ሼድ ሰጥቶናል እየሠራን ነው” በማለት የወደፊት እቅዳቸውን ይናገራሉ።
አቶ ግሩም “የወታደር ጫማ እንደሚመረት መደበኛ ጫማዎች ተፈላጊ እና ትርፋማ ስለሆነ፤ በጃኬት ከምናገኘው ትርፍ በጫማ የምናገኘው ትርፍ የበለጠ ነው” በማለት፤ ሰው በዓመት ቢያንስ አንድ ጫማ እንደሚገዛ፤ ቆዳ ጃኬት ግን በየዓመቱ እንደማይሸጥ፤ አንዴ ክረምቱን ገዝቶ ሦስት አራት ዓመት እንደሚለበስ ያነሳሉ። ጫማዎች ሞዴል ብቻ ነው እንጂ የሚቀያይሩት አይሸጥም ገንዘብ ይዞ ይቀመጣል ብለው አይሰጉም፤ ቆዳ ጃኬት ካልተሸጠ ገንዘብ ይዞ ሊቀመጥ እንደሚችልም ይገልፃሉ።
በአራዳ ማኑፋክቸሪንግ ግቢ “የናቹራል የጫማ ስቱዲዮ” መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቸሩ አሰፋ ናቸው። የተለያዩ ቆዳና የቆዳ ውጤቶችን ለሀገር ውስጥና ለውጪ ሀገር ገበያ ለማቅረብ ይጥራሉ። አቶ ቸሩ የቆዳ ልማት ኢንዱስትሪ ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት ያሠለጥኑ ነበር። ወደ ማምረቱ ከገቡ አራት ዓመት ሆኗቸዋል። በቆዳ ዘርፉ ውስጥ ከ15 ዓመት በላይ ልምድ እንዳላቸው ይናገራሉ።
የቆዳ ገበያው ከኮቪድ ወረራ በኋላ መቀዛቀዙን የሚናገሩት አቶ ቸሩ፤ የግብአት እጥረትና የዋጋ ንረትም መኖሩን ገልፀው ሆኖም በችግር ውስጥም ቢሆን እየሰሩ መሆኑን ይናገራሉ። አብዛኛውን ምርታቸውን ለሀገር ውስጥ ገበያ ለደንበኞቻቸው እንደሚያቀርቡ እነሱም በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ለቸርቻሪዎች እንደሚያከፋፍሉ ነግረውናል።
“ከዚህ በፊት አሜሪካ ላስቬጋስ ውስጥ ማጂክ ሾው በሚባል ምርቶቻችንን አቅርበን የተወሰኑ አንድ 12 ገዥዎች አግኝተን ነበረ። ናሙና ሰጥተን ብዙ ደረጃዎች ከሄድን በኋላ በኮቪድ ምክንያት ሲዘጋ ባለበት ቆመ። ጃፓንም እየሞከርን ነው፤ የተለያዩ ናሙናዎችን በማሳየት ገዥዎችን ለማግኘት ጥረት እያረግን ነው” በማለት፤ ቦርሳም አምርተው ለመላክ መሞከራቸውን የኮቪድ ችግርና የግብአት እጥረት ስላለ መግፋት እንዳልቻሉ ገልፀውልናል። በሥራ ልምዳቸው በክረምት ጉርድ ቡትስ ጫማዎችና ቆዳ ጃኬቶች እንደፋሽን ይሆናሉ ተፈላጊነታቸው ከፍ ይላል፤ ሲሉ ነግረውናል።
በአዲስ አበባ በጫም ንግድ ሥራ የሚተዳደሩ አቶ ግርማ ነጉማ የተባሉ እንደተናገሩት በክረምት ወቅት የወንዶችና የሴቶች ጉርድ ቡትስ ጫማዎች ገበያቸው ፋሽን ሆኖ እንደሚደራ ጠቁመዋል። ረጃጅም ጉልበት የሚደርሱ በጉርድ ቀሚስ የሚለበሱ የሴቶች ቡትስ ጫማዎች ገበያ እንዳላቸውና በብዛት ከውጪ ተመርተው የሚመጡ መሆናቸውንና በሀገር ውስጥ ሊመረቱ የሚችሉበትን መንገድ መምረጥ ተገቢ መሆኑን ነው የሚናገሩት።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ሀገራችን በእንስሳት ሃብት ከአፍሪካ ቀዳሚ ከዓለም ደግሞ አስረኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ይህ የጥሬ ቆዳና ሌጦ ዋጋ በከፊል ከተዘጋጁ ቆዳዎች ጋር ሲነፃፀር ዋጋው እስከ 60 በመቶ ያህል ብቻ ነው። በየቦታው በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ በተደራጁ ግለሰቦች የሚሠሩትን ሥራዎች የበለጠ ለማጠናከር መንግሥት የሚሰጠው ድጋፍ መቀጠል አለበት። እንደ ቆዳ ሀብታችን ቀዳሚነት ጥሬ ቆዳ ወደ ውጪ ከመላክ ዕሴት ጨምሮ ቆዳና የቆዳ ውጤቶችን መላክ፤ ከውጪ ከሚገቡ የቆዳ ምርቶችን ጋር ተወዳድረው ተመራጭ እንዲሆኑ ሊሰራ ይገባል ብለን እናምናለን። ሰላም!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12 ቀን 2013 ዓ.ም