
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ አበባ፦ እስከአሁን የትግራይ ክልልን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ ከታረሰው 11 ሚሊዮን ሄክታር ማሳ ውስጥ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታሩ በትራክተር መታረሱን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ለማ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት ፣በ2013/14 መኸር ምርት ዘመን 12 ነጥብ 78 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማረስና 374 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዷል።
የትግራይ ክልልን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ ከታረሰው 11 ሚሊዮን ሄክታር ማሳ ውስጥ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታሩ በትራክተር መታረሱን አስታውቀዋል።ይህም የሀገሪቱን 91 በመቶ ምርት የሚሸፍን እንደሆነ ገልጸዋል።
ክልሎች ለአርሶ አደሩ ወቅቱን የጠበቀ ግብዓት በማቅረብ፣ በመንግሥትና በግል ባንኮች ትራክተር መግዣ ብድር በማመቻቸትና ትራክተሩን በወቅቱ ተደራሽ በማድረግ ፤የአርሶ አደሩ ትራክተርን እና መሰል ቴክኖሎጂ እንዲጠቀም የሚያስችል ንቃተ ህሊናውን የማሳደግ ሥራዎችን መሥራታቸውን ጠቁመዋል።
በምርት ዘመኑ አርሶ አደሩ የረጅም ጊዜ ሰብሎች የዘራበት ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰው፣ በምርት ዘመኑ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በእነዚሁ ሰብሎች የተሸፈነበት ሁኔታ መኖሩን አመልክተዋል።
የአርሶ አደሩ የግብዓት ፍላጎት በዓይነትና በመጠን በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፣ ካለፈው ዓመት መኸር ምርት ዘመን ጋር ሲነፃፀርም የ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ጭማሪ ማሳየቱን ጠቁመዋል።
በምርት ዘመኑ የታቀደውን 374 ሚሊዮን ኩንታል አጠቃላይ ምርት ማግኘት የሚቻለው አርሶ አደሩ የተሻለ ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር፣ የአስተራረስ ዘዴ ሲጠቀም የማሳ እንክብካቤ ሲያደርግ ፣በአረምና ተባይ ቁጥጥር ያለውን አቅሙን አሟጦ ሲተገብርና ሰብሉን በጊዜ ሲሰበስብ መሆኑንም አመልክተዋል።
የዘንድሮ ክረምት ሁኔታ ለመኸሩ ሰብል በ10 ቀን ዘግይቶ የገባ ቢሆንም ተፅዕኖ እንደሌለው የጠቆሙት አቶ ኢሳያስ፣ በበልጉ ምርት ላይ ተፅዕኖ እንዳለውና በተለይ ሐምሌና ነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ በልጉ ለተወሰነ ቀሪ የመኸሩ ምርት መሬት መልቀቅ በሚኖርበት ሁኔታ ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳድር መሰጋቱን አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12 ቀን 2013 ዓ.ም