በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወነ ያለው ሦስተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የህዝብ ንቅናቄን የፈጠረ መሆኑ ይታወቃል። በመሬት ላይ ብቻ ሳይሆን ህንፃዎችንም በአረንጓዴ በማስዋብ ለሥራና ለኑሮ ምቹ ለማድረግ አበረታች የሆኑ ጥረቶችን እያየን ነው። የአረንጓዴ ልማቱ በዚህ ከቀጠለ ኢትዮጵያን አረንጓዴ የማልበሱ ግብ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይሳካል። የዛፍ ችግኝ የመትከሉ ባህልም ይጎለብታል። እንዲህ ያለው መልካም የሆነ እንቅስቃሴ በዓላማ ሲተገበር ደግሞ ውጤታማነቱ ከፍ ይላል። የቱሪዝም መዳረሻዎችን ታሳቢ ያደረገ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ማከናወን ከዓላማዎቹ አንዱ ነው። መስህብ ከሆኑት ባህል፣ ታሪክ፣ ቅርሶችና ሌሎችም ፀጋዎች ጋር አረንጓዴ ልማቱ ሲጠናከር የቱሪስት መስህብነቱን ለመጨመር አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ይሆናል።
አረንጓዴ አሻራና የቱሪዝም ኢንዱስትሪው የማይነጣጠሉ የአንድ ሣንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። እስካሁን ባለው ተሞክሮ ከአረንጓዴ ልማቱ ይልቅ ጎልቶ የሚነገረው ስለዱር እንስሳትና ሌሎች መዝናኛዎች ነው። ይህ ደግሞ በቱሪዝም መዳረሻ የአረንጓዴ ልማቱን የተዘነጋ ያስመስለዋል። ከዚህ አንፃር በዘርፉ ላይ የሚገኙ ተቋማት ቀደም ሲል በነበሩ የአረንጓዴ ልማትም ሆነ ባለፉት ሁለት ዙሮች፣ አሁን ደግሞ በሦስተኛው ዙር እየተካሄደ ያለውን አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ማዕከል ባደረገ እየተከናወነ ስላለው ተግባር እንዲህ ቃኝተናል።
የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሽ ግርማ ‹‹ዕፅዋቶችም እንደ አንድ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ግብዓት በመሆናቸው የቱሪስት መስህብ ናቸው። እንደብርቅዬ የዱር እንስሳት ሁሉ በኢትዮጵያ ብርቅዬ የሆኑ የዕፅዋት ዓይነቶች ይገኛሉ። ለአብነትም በሌሎች ሀገራት የሌሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኙ እንደ ጅብራ ያሉ ዕፅዋቶችን ወይንም ዛፎችን መጥቀስ ይቻላል። ጎብኝዎች በተለይም ከተለያዩ የዓለም ክፍል የሚመጡት ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኙ ሀገር በቀል ዛፎችን እንደ አንድ መስህብ ነው በአድናቆት የሚያዩዋቸው። በመሆኑም የአረንጓዴ ልማት ሥራ ከቱሪዝም ኢንዱስትሪው ጋር ከፍተኛ ቁርኝት አለው። የማይነጣጠሉ ተግባራት ናቸው። ጉዳዩ ስለዛፍ ወይም ከዛፍ ጋር ተያይዞ ስለሚገኘው ጥቅም ብቻ ሳይሆን በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ውስጥ ስላለው አስተዋጽኦም ጭምር ነው›› በማለት አስረድተዋል።
እንደ አቶ ስለሺ ገለጻ፣ የዛፍ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ልዩ ትርጉም አለው። አዕዋፋት የሚያርፉትም ሆነ መኖሪያቸውን የሚሰሩት በዛፎች ላይ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ከ860 በላይ ዝርያ ያላቸው አዕዋፋት የሚገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል ወደ 28 የሚሆኑት አዕዋፋት ብርቅዬ ናቸው። ከሌሎች ዓለማት በስደት ብዛት ያላቸው አዕዋፋት ይመጣሉ። በስደት የሚመጡ አዕዋፋት በአብዛኛው አብጃታ ሻላ አካባቢ ይገኛሉ። አዕዋፋትን ብቻ ለማየት የሚመጡ ቱሪስቶች በመኖራቸው የአዕዋፋት ቱሪዝምን ማሳደግ የሚቻለው የዛፍ ችግኝን በብዛት በመትከልና ተንከባክቦ በማሳደግ በአጠቃላይ አረንጓዴ ልማቱን በማጠናከር ነው። የዛፍ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ጫካ እንዲፈጠርም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። ይህ ደግሞ ከቱሪዝም አንጻር ሲቃኝ በጫካው ውስጥ የሚገኙ የዱር እንስሳት በቂ የሆነ ምግብና መጠለያ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። የዱር እንስሳቱን የቱሪዝም መስህብ በማድረግ ተጠቃሚ መሆን የሚቻለው ለእነርሱ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ሲቻል ነው። አረንጓዴ ልማቱ ተፈጥሮ ተኮር ለሆነው ቱሪዝም እጅግ ጠቃሚ በመሆኑ ኢትዮጵያ ቱሪዝም ልዩ ትኩረት በመስጠት በራሱና ከሌሎች ተቋማት ጋርም በመሆን ይንቀሳቀሳል። ድርጅቱ ጎን ለጎን ተፈጥሮን የመጠበቅ ባህል እንዲዳብር በተለያዩ የማስተዋወቅ ዘዴዎች ግንዛቤ በመፍጠርም ሚናውን ይወጣል።
ቱሪዝም ኢትዮጵያ ድርጅት ባለፉትም ሆነ አሁን እየተከናወነ ባለው የዛፍ ችግኝ ተከላ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው እንደ አንድ ግብአት (ፕሮዳክት) ተወስዶ በስፋት በመከናወን ላይ ይገኛል። ከዚህ አንፃር ቱሪዝም ኢትዮጵያ ድርጅት በሦስተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በመልካ ቆጥሬ፣ በአርሲ ተራሮች፣ ወንዶ ገነት ላይ የዛፍ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አከናውኗል። በተጨማሪም በአስጎብኝነት፣ በሆቴልና መስተንግዶ የተሰማሩ፣ የቱሪዝም ባለሙያዎችና በአጠቃላይ በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ውስጥ ያለውን ማህበረሰብ በማነቃቃትና በማሳተፍ ድርጅታቸው በእንጦጦ፣ በየካ ተራራ በቅንጅት ካከናወናቸው ተግባራት መካከል ይጠቀሳል። በቀሪው ጊዜያቶችም ዋና ዋና በሆኑ የቱሪዝም መዳረሻዎች የዛፍ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ይከናወናል።
አቶ ስለሺ እንዳስረዱት፤ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከመጀመሩ በፊት ድርጅታቸው ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሆን ላልይበላ ላይ የማደጎ የዛፍ ችግኞችን ተክሏል። የተተከሉት ችግኞች ዛፍ እንዲሆኑ ክትትልና እንክብካቤ ያስፈልጋቸዋል።በመሆኑም ባለቤት እንዲኖራቸው ልክ ልጅ በማደጎ እንደሚሰጠው ሁሉ ነው ችግኞችም ለእንክብካቤ ለአካባቢው ማህበረሰብ የተሰጡት። ይህ አንዱ የሆነው የማሳያ ሥራ የራሱ የሆነ ፕሮጀክት ያለው ሲሆን፤ ይህ በፕሮጀክት ደረጃ በላልይበላ ውስጥ እየተከናወነ ያለው የማደጎ የዛፍ ችግኝ ተከላ ዓላማ ዓለምን ከአየር ንብረት ለውጥ መታደግን ማዕከል ያደረገ ነው። ቱሪስቱ ችግኝ እንዲተክል ሲደረግ እንደ አንድ የቱሪስት መስህብ ሆኖ ጥቅም ያስገኛል።
በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ የተከለው የዛፍ ችግኝ የአየር ንብረት መዛባትን በመጠበቅ እርሱ በሚኖርበት ሀገርም ጭምር ፋይዳው የጎላ መሆኑን እንዲገነዘብ ያስችለዋል። በአካባቢው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ወይም አስተሳሰቡ ወደ ቱሪስት መስህብነት መቀየሩ ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት በመፍጠር ልማቱ የጋራ እንዲሆን ያስችላል። ቱሪስቶችን በማሳተፍ በላልይበላ ላይ እየተከናወነ ያለው የችግኝ ተከላ ፕሮጀክት ሥፍራ ላይ የዓለም ካርታ ምልክት ተደርጓል። እያንዳንዱ ቱሪስትም ችግኝ ሲተክል የመጣበትን አካባቢ በሚወክል ካርታ ሥፍራ ነው የዛፍ ችግኝ የሚተክለው። ፕሮጀክቱ መተግበር ከጀመረ አንድ ዓመት ሲሆን፤ ተጠናክሮ ይቀጥላል። የቱሪዝም እንቅስቃሴው ወቅታዊ ቢሆንም ቋሚ ቱሪስቶች በመኖራቸው አሻራቸውን በማኖር ላይ ይገኛሉ።
የላልይበላን ፕሮጀክት በጋራ ሆኖ በማጠናከር ሚና ያለው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርም ውጤት የታየበት ተሞክሮ እንደሆነ የሚኒስቴሩ የኮሙኒኬሽን ጉዳች ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ጌታቸው ይናገራሉ።
እንደ አቶ ዓለማየሁ ገለጻ፤ ችግኙን የሚተክለው ሰው ለእንክብካቤው የሚውል ገንዘብ ለመመደብ ቃል ይገባል። ቃል እየገቡ ድጋፍ ከሚያደርጉ ሰዎች ገንዘቡ የሚሰበሰብ ሲሆን፤ ለአንድ ችግኝ እስከ 50 ዶላር ክፍያ ይፈፀማል። በዚሁ መሠረትም ባለፈው ዓመት እስከ ሁለት ሚሊየን ብር ድረስ ለእንክብካቤው ቃል ተገብቷል። በድጋፍ የሚገኘው ገንዘብ የተተከሉትን የዛፍ ችግኞች በኃላፊነት ለሚንከባከቡ ክፍያና ለችግኙ አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች ይውላል። ይኼ ችግኝ የሚተክለውንም ችግኞችን ለሚንከባከበውም በጋራ ተሳታፊ የሚያደርግና ለውጤትም የሚያበቃ ነው። የዚህ ተሞክሮውም ጥሩ በሚባል ደረጃ ላይ ይገኛል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በተመሳሳይ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ማዕከል አድርጎ በሦስቱም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እየተሳተፈ መሆኑን የተናገሩት አቶ አለማየሁ አዲስ አበባ ከተማ ገላን ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በ2011 ዓ.ም የተከናወነውንና የተገኘውን ለውጥም ለአብነት ጠቅሰዋል። በገላን አካባቢ ሰባት ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በተከናወነው በዛፍ ችግኝ አረንጓዴ የማልበስ ሥራ ለአካባቢ ጥሩ ገጽታ መፍጠር ተችሏል። ለአካባቢው ነዋሪም መናፈሻ ሆኖ በማገልገል ጥቅም እየሰጠ ይገኛል። እንዲህ ያሉ ተሞክሮዎች እንዲሰፉ ሚኒስቴሩ ጥረቱን አጠናክሯል።
በሦስተኛው ዙር ኢትዮጵያን እናልብሳት አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሐምሌ አንድ ቀን 2013 ዓ.ም በቅርቡ በእሣት ቃጠሎ አደጋ ከፍተኛ ጉዳት በነበረው በአማራ ክልል ሠሜን ሸዋ ውስጥ በሚገኘው ወፍ ዋሻ ደን ውስጥ ሀገር በቀል የዛፍ ችግኞች በመትከል ከጉዳቱ እንዲያገግም የማድረግ ተግባር ተከናውኗል።
ሚኒስቴሩ የዛፍ ችግኝ ተከላ ያከናወነበት ወፍ ዋሻ ደን 16 ሺህ 925 ነጥብ 5 ሄክታር የቆዳ ስፋት እንዳለው፣ በውስጡም የተለያዩ የዱር እንስሳት፣ ብርቅዬ አዕዋፋትና ዕፅዋት እንዲሁም አንኮበር ሴረን የተባለች በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ በወፍ ዋሻ ደን ውስጥ የምትገኝ አዕዋፍ መኖሯን፣ ከዱር እንስሳትም ጭላዳና ዝንጀሮ፣ የምኒልክ ዱኩላ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኘውን ጅብራ ጨምሮ የተለያዩ ሀገር በቀል ዕፅዋቶች መገኛም እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ወፍ ዋሻ ደን የእሣት ቃጠሎ በደረሰበት ወቅትም ቃጠሎው ለቀናት ሣይቆም ከፍተኛ ጉዳት ደርሶ እንደነበር ይታወሳል። ዕድሜ ጠገብና ታሪክ ያላቸው እንዲህ ያሉ የተፈጥሮ የቱሪስት መስህቦች ተገቢው ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባም መዘንጋት የለበትም።ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም ከዚህ አንጻር ያደረገው እንቅስቃሴ ያስመሰግነዋል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በዚህ የተከላ ወቅት ቀደም ሲል የተከላቸውን የዛፍ ችግኞችን እግረ መንገዱንም በመጎብኘት አዲስ ተከላዎችን እንደሚያከናውን የተናገሩት አቶ አለማየሁ ችግኝ ተከላ ካከናወኑባቸው መዳረሻዎች አንዱ በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቶ ኦዳ ወረዳ ኦዲ እና ዝቋላ ተራራ ይጠቀሳሉ። መልማት አለባቸው ተብለው የሚታሰቡ መዳረሻዎችን ወይም መዝናኛዎችን ሁሉ በተለያየ ዘርፍ ላይ የሚገኙትን ባለሙያዎችና ተቋማት በማስተባበር ሚኒስቴሩ ተግባሩን የሚያጠናክር ሲሆን፤ ከፕሮግራሞቹም ኮይሻ አንዱ ተከላ የሚከናወንበት ሥፍራ መሆኑን አቶ አለማየሁ ይናገራሉ።
እንደእርሳቸው ገለጻ፤ የሚኒስቴሩ የዛፍ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ማጠቃለያ የሚሆነው በላልይበላ ላይ የተጀመረው የዛፍ ችግኝ ማደጎ ሞዴል ፕሮጀክት ማስቀጠል ይሆናል።የአረንጓዴ ልማቱ በመዳረሻ ቦታዎች መጠናከሩ የቱሪስቱን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑ ግንዛቤ ውስጥ ገብቶ ሁሉም ለልማቱ እንዲነሳሳ አቶ አለማየሁ ጥሪ አቅርበዋል።
ጥሩ የቱሪስት መስህብ ሊሆኑ የሚችሉ ነገር ግን ትኩረት ባለማግኘታቸውና ባለመልማታቸው ሀገራዊ ጥቅም ሳይስገኙ የቆዩ ጥብቅ ደኖችና የተፈጥሮ መስህቦች በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድ አነሳሽነት በመልማት ላይ ይገኛሉ። አሁን ትኩረት አግኝተው እየለሙ እንዳሉት ሁሉ በአዲስ አበባ ከተማ ኦሮሚያ ልዩ ዞን፣ ሆለታ ወልመራ ወረዳ ውስጥ የሚገኘው ሠበታ መናገሻ ሱባም ቢለማ መዳረሻ ሊሆን እንደሚችል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ ወቅት ሀሳብ ማቅረባቸው ይታወሳል። ዕድሜ ጠገብ የሆነው ይህ ደን በኢኮኖሚው ውስጥ አሁን እያበረከተ ካለው አስተዋጽኦ በተጨማሪ ለቱሪዝም መዳረሻ ሆኖ ጥቅም እንዲሰጥ ቢደረግ ደግሞ ፋይዳው ከፍ ይላል።
የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የደን ባለሙያ አቶ ዮናስ ክፍሌም ይኼንኑ በማጠናከር በሰጡት አስተያየት የተፈጥሮ ሀብቱ በሥፋት የሚገኘው በክልሎች በመሆኑ ክልሎች ትኩረት ሰጥተው የአረንጓዴ ልማቱ እንዲጠናከር መሥራት ይኖርባቸዋል ብለዋል። የዛፍ ችግኝ ተከላው በዓላማ ሲከናወን ደግሞ ውጤታማ ይሆናል። በመሆኑም ችግኞች የትና መቼ፣ ምን ዓይነት ዝርያ እና ለየትኛው አካባቢ የሚሉት ተለይተው እንዲከናወኑ ግንዛቤ እየፈጠሩ መሄድ፣ የዘርፉ ባለሙያዎችም እገዛ በማድረግ የጋራ የሆነ ሥራ ሊሰሩ ይገባል። ኮሚሽኑ ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ ኃላፊነቱን ይወጣል ብለዋል። አረንጓዴ አሻራን በመተግበር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን በመወጣት አጠናክረው ከቀጠሉ የቱሪስት መዳረሻዎችን በአረንጓዴ የማልማቱ ሥራ ውጤታማ ይሆናል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2013