
አዲስ አበባ፡- ሽብርተኛው ቡድን ህወሓት ለትልቋ ኢትዮጵያ ቀርቶ የእኔ ለሚለው ክልል ህዝብ ቅንጣት ያህል አዘኔታ እንደሌለው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ኦባንግ ሜቶ ገለጹ። በ21ኛው ክፍለ ዘመን በብሄር መደራጀት ውርደትም ፣እርግማንም እንደሆነ ጠቆሙ ።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ኦባንግ፣ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፣ አንድ የሚያደርገን ብሄራችን ወይም ቋንቋችን ወይም ደግሞ መልካችን አይደለም፤ አንድ የሚያደርገን ኢትዮጵያ የምትባል ምድራችን ናት። ትልቁን ማንነት እያፈረስን ትንሹን ማንነት ፍለጋ አንድከም።
ሽብርተኛው ህወሓት ለትልቋ ኢትዮጵያ ቀርቶ የእኔ ለሚለው ክልል ህዝብ ቅንጣት ያህል አዘኔታ የለውም። እነርሱ አዘጋጅተው የሰነዱት ህገ መንግስት ማንነትን፣ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ብሎ በሶስት ከፋፍሎ የፈረጀ ነው፤ ህገ መንግስቱ በተለይ የሚያጎላው አገራዊ፣ ህዝባዊና ኢትዮጵያዊነትን ሳይሆን ብሄር ተኮርነትን ነው ብለዋል።
አሸባሪው ህወሓት እያሰቃየ ያለው ተራውን ህዝብ ነው። ይህን ሁሉ ያደረገው የብሄር ፖለቲካው ነው፤ የብሄር ፖለቲካ ደግሞ ኋላቀር አካሄድ ከመሆኑም በላይ መርዝ ነው። የብሄር ፖለቲካ ሌላውን ዓለምም ያልጠቀመ ነው። በብሄር የተደራጀ አገር እርስ በእርስ መባላቱና በመጨረሻም መፍረሱ እንደማይቀር አመልክተዋል።
እነርሱ የአካባቢውን ህብረተሰብ መነገጃ እያደረጉ ነው። ለዚህ ማሳያ ደግሞ የእኔ የሚሉትን አካላት ከጎኔ ካልቆማችሁ እጨርሳችኋል የሚል ነው። ያለእኔ መንገድ ሌላ መንገድ የለም የሚል ነው። የእነርሱ ፍላጎት እኔ እስከተጠቀምኩ ጊዜ ድረስ ስለሌላው አያገባኝም ነው። ይህ ደግሞ የኋላቀርነት የፖለቲካ አካሄድ ነው ብለዋል።
ይህ የጽንፈኝነት ፖለቲካ ነው። በእንዲህ አይነቱ የፖለቲካ አካሄድ በመጨረሻ ሰዎች ይጎዳሉ። በተለይ እነሱ የሚጠቀሙበት የፖለቲካ ስልት የማስፈራራት ነው፤ የሚያስፈራሩት ደግሞ እኛ ከሌለን እናንተም የላችሁም በሚል ነው። ይህ አይነቱ ፖለቲካ ደግሞ ከቡድንተኝነት፣ ከሆዳምነትና ከጽንፈኝነት ጋር ተያይዞ የመጣ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ለዚህ ሁሉ ችግር እየማገደን ያለው ብሄር ተኮሩ ህገ መንግስት፣ የዘረኝነትና የጽንፈኝነት እንዲሁም የሆዳምነት ፖለቲካው ነው። ይህን ሁሉ ጠጥተን ሰከርን፤ እንደሰከርን እንኳን ማመን አቃተን ያሉት አቶ ኦባንግ፣ የእኛ ትልቁ ጠላት የራሳችን አስተሳሰብና ቀና አለመሆናችን ነው። ስለዚህም የተንኮል፣ የቁማር፣ የኋላቀርና የበላይነት ፖለቲካ ከአገራችን ካልወጣ ቀጣይነታችን በራሱ ጥያቄ ውስጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የትግራይ ህዝብ ኢትዮጵያዊ ነው። እስካሁን የኖረውም ከኢትዮጵያውያን ወንድሞቹና እህቶቹ ጋር ነው። አሸባሪው ህወሓት ከመጣ 27 ዓመቱ ነው። በተለያየ እንቅስቃሴው ከአርባ ዓመት በላይ አስቆጥሯል። አንዳንዶች ስለትግራይ ህዝብ ሲነሳ ህዝቡ መቀሌ ብቻ ላይ ይመስለዋል። ህዝቡ ግን በየትኛውም የኢትዮጵያ ጫፍ እንዳለ መረዳት ይገባል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ችግር ስለመኖሩ መረዳት ያስፈልጋል። ሌሎች በፖለቲካው ውስጥ የሌሉ ሰዎች ለዚህ ችግር መፍትሄ ማምጣት የሚችሉበት ጊዜ ቢኖር አሁን ነው። ለዚህ ችግር ፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም ሊንቀሳቀሱ ይገባል ያሉት አቶ ኦባንግ፣ የአማራ፣ የትግራይ፣ የአሮሞ፣ የወላይታ፣ የጉራጌ ህዝብ ከሚል አስተሳሰብ መውጣትና ስለኢትዮጵያ መነጋገር መቻል አለብን። እኛ ከዚህ አይነት አነጋገር በላይ ነን። እኛ የዚህኛው ወይም የዚያኛው ሳንሆን የሰው ልጆች ነን። ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ነን ብለዋል።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 5/2013