የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከባህልና ጥበባት ዘርፍ ማኀበራት ጋር በመተባበር “ሽልማት ለጥበብ” በሚል መሪ ቃል አገር አቀፍ የእውቅናና ሽልማት ስነ ስርዓት ሰኔ 29 ቀን 2013ዓ.ም እንደሚካሄድ አስታውቆ ነበር:: ይሁን እንጂ በተለያዩ ተደራራቢ ስራዎች ምክንያት የሽልማት ሥነ ስርዓቱ ወደ ሐምሌ 10 ቀን 2013 ዓ.ም እንደተቀየረ በተመሳሳይ በመገናኛ ብዙሃንና በማህበራዊ ድረ ገፆች ይፋ አድርጓል።
ይህ የሽልማት ስነስርዓት በሃምሌ 10 አመሻሽ ላይ በወዳጅነት አደባባይ እንዲደረግ መወሰኑንም ሰምተናል:: ይህን በማስመልከት የዝግጅት ክፍላችንም ከዚህ ቀደም የነበሩ የሽልማት አሰጣጦችን፣ መልካምና ደካማ ጎኖችን በዚሁ በዘመን ጥበብ አምድ ላይ በማንሳት በቅርብ ቀናት የሚደረገው የእውቅና አሰጣጥ ስነስርዓት ሊደፍናቸው የሚገቡ ሽንቁሮችንና መጠናከር ያለባቸው መልካም ጎኖችን ለማንሳት ወደናል።
ቅድመ ታሪክ
በአገራችን የጥበብ ሽልማት ታሪክ የመጀመሪያው የሽልማት ድርጅት ሃምሌ 1 ቀን 1955ዓ.ም የተመሰረተው የአጼ ኃይለስላሴ የሽልማት ድርጅት ነበር:: የመጀመሪያውን የኪነጥበብ ባለሙያዎች ሽልማት ለባለሙያዎቹ የሰጠው ይሄው ድርጅት ነው። የሽልማት ድርጅቱ በንጉሱ የግል ሀብት የተቋቋመ በመሆኑ የገንዘብ ችግር እንዳልነበረበት ይነገራል። አብዮቱ እስከ ፈነዳበት 1966ዓ.ም ድረስም በስነፅሁፍና በስእል መስክ አስር ባለሙያዎችን በመሸለም ተጉዟል።
ለሽልማት ድርጅቱ በወቅቱ እንደ ችግር የተጠቀሰው ሁሉንም የጥበብ ዘርፎች አላካተተም የሚለው ነበር። ድርጅቱ በተለያዩ አስተዳደራዊ ችግሮች ምክንያት የታሰበውን ያህል ባይሰራም፣ እስከ ስርአቱ ውድቀት ድረስ ጉዞው አልተገታም። ለባለሙያዎቹ የተደረገው ሽልማት የጥበቡ ዘርፍ ባለሙያዎች ተበረታተው ለአገራቸው የስነፅሁፍ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከት እንዲችሉ ማድረጉ በወቅቱ ይገለጽ ነበር። ለአብነትም ለኢትዮጵያ ዘመናዊ የሥነ-ጥበብ ዕድገት አርአያ በመሆኑ በ1958 ዓ.ም የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የሽልማት ድርጅት የአገሪቱን ከፍተኛና ዓለም አቀፋዊ የሥነ ጥበብ ሽልማት በአድናቆት የተቀበለው ሰዓሊ ገብረክርስቶስ ደስታን ለማስታወስ እንችላለን።
ሰአሊ ገብረ ክርስቶስ ደስታ እንደ መምህርነቱም ከ1955 ዓ.ም እስከ 1967 ዓ.ም ድረስ ባሉት 12 ዓመታት ውስጥ ዛሬ ለሀገሪቱ አንቱ የተሰኙ እና ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸውን ሠዓልያን አፍርቷል:: ‹‹ሞዴል አርቲስትና መምህር›› በመሆኑም በ1963 እና 1964 ዓ.ም ከወቅቱ የትምህርትና የሥነ ጥበብ ሚኒስቴር እንዲሁም ከአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ጽሕፈት ቤት የዓመቱ ምርጥ መምህር ተብሎ ተሰይሟል:: በ1969 ዓ.ም የዕድገት በህብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ ለፈፀመው ታላቅ የማስተባበር ተግባርም ከዘመቻው መምሪያ የወርቅ ሜዳልያም ተሸልሟል::
ከ24 አመታት በኋላ የተቋቋመው አገር አቀፍ የስነ ጥበባትና መገናኛ ብዙሀን የሽልማት ድርጅት ጠንካራ የሚባል የባላደራ ቦርድ አባላትን ይዞ ነበር ስራውን የጀመረው። በስነ ጥበብና በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ተሰማርተው የላቀ የፈጠራ ስራ የሚያቀርቡ ተቋማትንና ግለሰቦችን በየሙያው ዘርፋቸው በማወዳደር ለማበረታታና ለመሸለም እንዲሁም ስነ ምግባርን የተላበሱ ጠንካራ ተተኪዎችን ማፍራት የሚሉ አበይት አላማዎችን ይዞ ነበር የተቋቋመው።
ቦርዱ ከተቋቋመ ከአምስት ወራት በኋላ በታህሳስ 1991ዓ.ም ነበር የመጀመሪያዎቹን ተሽላሚዎች መርጦ ለመሸለም የበቃው። በወቅቱ የተሸለሙት ባለሙያዎች ስምንቱ ከስነ ጥበብ ዘርፍ ሲሆኑ፣ አንዱ ከመገናኛ ብዙሀን ዘርፍ እንደነበር ይታወሳል። ከተሸላሚዎቹ ውስጥ አምስቱ መላ ህይወታቸውን በጥበብ ውስጥ በማሳለፋቸው የህይወት ዘመን ተሸላሚዎች ተብለዋል፤ አራቱ የረጅም ዘመን አገልግሎት ተሸላሚ ነበሩ። በወቅቱ የመተዳደሪያ ደንብ ላይ ከህይወት ዘመን እና ከረጅም ዘመን አገልግሎት የሽልማት አይነቶች ሌላ ወቅታዊና ዓመታዊ ሽልማቶችን እንደሚሰጥም ተገልፆ ነበር።
የቅርብ ጊዜ ትዝታዎች
አሁንም ከረጅም ዓመታት በኋላ በመንግስት ደረጃ ለኪነጥበብ ባለሙያዎች ሽልማት ለመስጠት ሽርጉዱ የተጀመረው ደግሞ በ2006 ዓ.ም ነበር። ሽልማቱን የተዘጋጀው በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በሀገር አቀፍ የሙያ ማህበራት ጋር ቅንጅት ነው። አላማውም ኪነጥበብን ለማበረታታት በስዕል፣ በሙዚቃ፣ በፊልም እና በስነጹሁፍ ዘርፎች ላይ ትኩረቱን አድርጎ ነበር።
በአገራችን የኪነጥበብ ባለሙያዎችን ለማበረታታት የሽልማት ድርጅቶች በተለያዩ ወቅቶች ተቋቁመዋል። የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የሽልማት ድርጅት በቆየባቸው ጊዜያት አንጋፋ ባለሙያዎችን በመሸለምና በማበረታታት በኩል ከፍተኛ ሚና እንደነበረው አይካድም። በወቅቱ የነበረው የሽልማት ድርጅት በዋንጫና በምስክር ወረቀት ብቻ የሚሸኝ አልነበረም። የገንዘብ ምንዛሪ ከፍተኛ የሚባል ሽልማት ይበረከትላቸው ነበር ። ለአጭር ጊዜ ብልጭ ብሎ ድርግም ያለው የመገናኛ ብዙኃንና የኪነጥበብ ባለሙያዎች የሽልማት ድርጅትም ቢሆን በአጭር ዕድሜው በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚሰጠው እውቅና በተጨማሪ ተሸላሚዎቹን የሚያበረታታ የገንዘብ ሽልማትም ተካቶበት እንደ ነበር አይዘነጋም።
ምን ቢደረግ ይሻላል?
ዛሬ በአገራችን ጠንካራና የተቀናጀ የሽልማት ድርጅት አለመኖሩ አይካድም። ባለመኖሩም ምክንያት የተለያዩ ፊልም ሰሪዎች ከዋና ሥራቸው በተጓዳኝ ሸላሚ ለመሆን በቅተዋል። ይህ ደግሞ በራሱ የአመለካከት ክፍተቶችን ይፈጥራል። ምክንያቱም የሽልማት ድርጅቶች ገለልተኛ ቢሆኑ ይመረጣልና።
ያም ሆነ ይህ በአሁኑ ወቅት ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሆኑ ባይታወቅም በተለያዩ የኪነጥበብ ዘርፎች የሚሸልሙ ድርጅቶች መኖራቸው ይታወቃል። በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት የተደረገው የህይወት ዘመን ሽልማትም ለእዚህ በአብነት ይጠቀሳል። ይህም ቢሆን በጊዜው ከአካታችነት ጋር በተያያዘ በርካታ ቅሬታዎች ሲነሱበት ነበር።
መንግሥት በተለያዩ ዘመናት እንደነበሩት አገር አቀፍ የሽልማት ድርጅቶች ኃላፊነቱን ወስዶ ከሐሜት ነፃ የሆነ የሽልማት ድርጅት እንዲቋቋም ግፊት ማድረግ ይኖርበታል የሚሉ አስተያየቶች ከየአቅጣጫው መነሳት ከጀመሩ ቆይቷል። ሃሳቡ እውን ሲሆን ያኔ ሁሉንም የኪነጥበብ ባለሙያዎች ያሳተፈ፣ ከአድሎና ከቡድናዊነት መንፈስ የፀዳ የሽልማት ድርጅት ሊፈጠር ይችላል። ካልሆነ ግን አንዳንድ ግለሰቦችና ተቋማት እየተነሱ የሚያዘጋጁት ሽልማት የራሳቸውን ተጠቃሚነት ከማጉላት ባለፈ ለባለሙያው የሚኖረው ፋይዳ ያን ያህል የጎላ ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም።
በመጨረሻም የፊታችን ሀምሌ አስር ይካሄዳል ተብሎ ቀን የተቆረጠለት “ሽልማት ለጥበብ” በኪነጥበብ ባለሙያዎችና አፍቃሪዎች ዘንድ በጉጉት ይጠበቃል። የሰራ ሲሸለም ለመስራት የሚያስብ ተስፋ እንደሚሰንቅ ሁሉ ለጥረቱ እውቅና የሚሰጠው የጥበብ አድባር ደግሞ ከነበረው የተሻለ ለመስራት መነሳሳቱ አይቀርም። ከዚህ መነሻ ባለሙያዎች እጀ ሰባራ ነን ብለው እንዳያስቡና ተስፋ እንዳይቆርጡ “እውቅና የሚሰጥበት መስፈርት እጅግ የበረታ ጥንቃቄ እንዲሆን የዝግጅት ክፍላችን ለማሳሰብ ይወዳል። ሰላም!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 4/2013