አቶ ፈቃዱ ጸጋዬ ይባላሉ:: በአይነስውርነታቸው ያጋጠማቸው በርካታ ፈተናዎች ቢኖሩም እነዚህን ፈተናዎች በብዙ ትግልና ውጣውረድ ተሻግረው ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ህግ እስከመሆን የደረሱ ናቸው:: ከዚህ በፊትም ቢሆን የተለያዩ ቦታዎች ላይ በሀላፊነት ጭምር ተቀምጠው በፍትሁ ዘርፍ የተቻላቸውን አበርክተዋል:: በተለይም በሥራዎቻቸው ከስህተት የጸዳ ስራ በመስራት ብዙዎች የሚጠቅሷቸው ናቸው:: ከዚህ በተጓዳኝ ለአይነስውራን ተሟጋች በመሆን ብዙዎች የአካል ጉዳተኞች ችግር እንዲፈታ ያደረጉም ናቸው:: እናም ከዚህ የህይወት ተሞክሯቸው ብዙ የሚያጋሩት ነገር አላቸውና ለዛሬ የ‹‹ ህይወት ገጽታ›› አምድ እንግዳችን አድርገናቸዋል:: ተማሩባቸው ስንልም ጋበዝናችሁ::
አይነስውሩ በሶ ሸክሻኪ
በ1972 ዓ.ም ነው ይህችን አለም የተቀላቀሉት:: ተወልደው ያደጉት ደግሞ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ጢጆና ዲገሉ ወረዳ ነው:: እስከ አምስት ዓመታቸው ዓይናማ ሆነው ከስድስት አመት በኋላ ግን በአይነስውርነት የልጅነት ጊዜያቸውን በቦታው አሳልፈዋል:: በዚህም ብዙ የልጅነት ጊዜያቸውን ያስታውሱበታል:: በእርግጥ አይነስውር ከሆኑ በኋላ በውጣውረድ የተሞላ ህይወትን እንዲያሳልፉ ሆነዋል:: ከቤተሰብ እስከ እኩዮቻቸው የሚደርስባቸው ነገር በቀላሉ የሚቋቋሙት አልነበረም:: አትችልም ባይነቱ የገነነባቸው፤ እንዳይማሩ እንቅፋት የበዛባቸው፤ በሰው ጫንቃ ላይ ዘላለም መኖር አለባቸው ተብሎ የተፈረደባቸው ነበሩም:: ግን ጠንካራ በመሆናቸው ተወጥተውታል:: በተጨማሪ የአባታቸውና እናታቸው እንዲሁም የአዳሪ ትምህርት ቤቱ ሞግዚቶችና መምህሮቻቸው ተስፋ ሰጪነት ወደኋላ እንዳይሉ አድርጓቸዋል:: ቀጣይ የተሻለ ነገር እንዳለ እንዲያዩም አስችሏቸዋል::
ለእንግዳችን አይነስውር መሆን ሁለት መላምቶች ምክንያት እንደሆኑ ቤተሰቦቻቸው ያምናሉ:: እነዚህም የመጀመሪያው የሰው ዓይን ነው የሚል ሲሆን፤ የገበሬ ልጅ በመሆናቸው በደቦ አጨዳ ተከናውኖ ሲያልቅ በአካባቢው ዘንድ እንደተለመደው በቤት ውስጥ ድግስ ተደግሷል:: መብል መጠጡ ከጨዋታው ጋር ተጧጡፏል:: በዚህ ጊዜም እንግዳችን እናታቸው እግር እግር ስር እያሉ አዲስ ቀይ ልብስ ለብሰው ሁሉንም በሚማርኩበት ሁኔታ ይቦርቃሉ:: ስለዚህም ይህ ሁኔታ አይን ውስጥ እንዲገቡና እንዲታመሙ አድርጓቸዋል ይላሉ::
ሌላውና ሁለተኛ ምክንያታቸው ደግሞ አባት ስድስት ሰዓት ላይ ውድማ ጤፍ እየወቁ ባለታሪካችንን በነጭ ጋቢ ጠቅልለው እስኪጨርሱ አስቀመጧቸው:: ሲያጠናቅቁም ወደ ቤት አስገቧቸው:: ግን የጠበቁት ልጅ አልነበረም የጠበቃቸው:: ዓይኑ ቢጫ የሆነና ማየት የተሳነውን ልጅ ነው ያገኙት:: ስለዚህም ተለክፎ ነው አሉ:: ይህ ሁለቱ መላምት ደግሞ ከህክምና ይልቅ ጸበል አስመረጣቸው:: ነገር ግን የፈለጉትን ምላሽ ሊያገኙ አልቻሉም:: ከዚህ ብሶም ህክምና ቢወስዷቸውም የተሰጣቸው ምላሽ ከዚህ የተለየ አለመሆኑ እጅጉን አሳዘናቸው:: ነገር ግን ህክምናው ጋር መሄዳቸው የተለየ ተስፋ ሰጥቷቸው እንደነበር ያስታውሳሉ:: ይህም ለልጃቸው ቀጣይ ህይወት የሚሆን ምክረሀሳብ አግኝተዋል:: የአይነስውራን ትምህርት ቤት የት እንዳለ፤ መማር እንደሚችሉ ሀኪሞቹ ለአባታቸው በሚገባ አስረድተዋቸው ነበርና ልጃቸውን ከዚህ በኋላ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ላልተረዱ ወላጆችም የት መሄድ እንዳለባቸው የምስራች አግኝተውበታል:: ስለዚህም መማር እንዲችሉ ሆነዋል::
አካባቢያቸውንና ቤተሰቦቻቸውን እንዲሁም ጓደኞቻቸውን እያዩ ያሳለፉት እስከ አምስት ዓመታቸው ድረስ ብቻ የሆነው ባለታሪካችን፤ በእነዚህ ጊዜያት የማይጠፋ ትዝታዎች እንደነበሯቸው ያወሳሉ:: በተለይም ከብት እያገዱ ከጓደኞቻቸው ጋር የሚያሳልፉት ጊዜ ልዩ እንደነበር አይረሱትም:: አይነስውር ከሆኑም በኋላ ቢጨመርበትም እንቁጣጣሽ፣ መስቀልና ቡሄ ለእርሳቸው የልዩ ትዝታ በዓላት እንደነበሩም ይናገራሉ:: በእነዚህ ጊዜያት የሚያደርጉት ነገር ልጅነታቸውን ጣፋጭ ካደረጉት መካከል ዋነኞቹ መሆናቸውንም ያነሳሉ:: ጭፈራው፣ የማህበረሰቡ ልዩ ስጦታና ምርቃት እንዲሁም የተለያየ ባህላዊ ጨዋታው ልዩ ስሜት ይሰጣቸው ነበር:: ልምላሜና ተስፋ የሚያዩበት ጊዜም ስለሆነ በጉጉት ይጠብቁት እንደነበር አጫውተውናል::
ሌላው የልጅነት ትዝታቸው በሰፈራ ምክንያት ያጋጠማቸው ነው:: ከትውልድ ቀያቸው ለቀው በሄዱበት ጊዜ ልጅ ሆነው የጠፉበትን የማይረሱት ነው:: ለዚህ ምክንያቱ የቤተሰብ የእርሻ ቦታ በተወለዱበት አካባቢ ስለነበር ቤተሰባቸውን ተከትለው ለመሄድ ተሰባስበው ሲጓዙ አቅጣጫው ጠፍቶባቸው ሌላ መንደር ውስጥ መግባታቸው ሲሆን፤ በስንት ፍለጋ ነበርም የተገኙት:: እናም ይህንን ጊዜ መቼም አይረሱትም::
አቶ ፈቃዱ በባህሪያቸው እልኸኛ ሲሆኑ በፍጹም እርሳቸው ያሉት ካልሆነ የማይቀበሉ ናቸው:: ኑሮና ትምህርት የገራው እልህ አይነት አይደለም ያለባቸው:: ይሆናል ካሉ ይሆናል ነው:: በዚህም የማይችሉትን ሁሉ ለማድረግ ይሞክሩ እንደነበር አይረሳቸውም:: ይህ ባህሪያቸው ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እስከሚያጠናቅቁም አብሯቸው ያደገ እንደሆነ ያስረዳሉ:: በተለይም በጉልበት ምክንያት ማንም ማንንም መንካት የለበትም ብለው የሚያስቡ ናቸው:: ይህ አይገባህምን በምንም መንገድ አይቀበሉም:: ተሸናፊነት የሚባል ነገር በእርሳቸው ዘንድ ቦታ የለውም::
እንግዳችን ይህ ባህሪያቸው ቢኖርም ቤተሰብን በማገዝ ግን የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጉ ነበር:: በአካባቢው የሚሰሩ ሥራዎችን በሙሉም በአቅማቸው ልክ ያከናውናሉ:: እንደውም አይነስውር ሆነው ሳለ እንኳን የራሳቸውን ምግብ ማለትም ለትምህርት ሌላ ቦታ ሄደው ስለሚማሩ በሶና ቅንጬ ሲዘጋጅ እርሳቸው ብዙውን ነገር ይሰሩ ነበር:: ከእነዚህ መካከልም መፈተግ በዋናነት የእርሳቸው ስራ ነው:: ጌሾ መውቀጥና ሌሎች የድግስ ሥራዎችንም ይሰራሉ:: ይህ እንዴት ይሆናል ላላችሁ ሰዎች በልምድ ያዳበሩት ሥራ ስለሆነ ነው:: በአዳሪ ትምህርት ቤት እያሉም ያልለመዱት ሥራ የለም:: በዚህም የራሳቸውን አትክልትና ፍራፍሬዎች ከሌሎቹ ለይተው ይንከባከቡ ነበር:: የምግብ ሥራም ለእርሳቸው ብርቅ አይደለም::
አይነስውርነትና ትምህርት
ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ጀምሮ ብዙ ውጣውረድ የበዛበትን ጉዞ ነበር ያደረጉት:: በተለይም አይችልም፣ አይመዘገብም፣ አይማርም፣ ከእኛ መራቅ የለበትም፣ ምን ሊሆን ይችላል፣ ማን ይመግበዋልና መሰል ምክንያቶች ለፈተናው መንስኤ ነበሩ:: በዚህም ከቤተሰብ መጣላት እስከ ቤተሰብ መለየት የሚደርሱ ጊዜያትን አሳልፈዋል:: ትምህርት ቤት እስኪገቡ ድረስም ውጤታማ ይሆናል ብሎ የሚያስብ ሰው በጣም ጥቂት ነበር:: አባታቸው የተነገሩትን ነገር ስለያዙ እድሜያቸው ለትምህርት ይድረስን ይጠብቃሉ እንጂ ሌሎች ግን ከዚህ የተለየ አቋም ነበር የነበራቸው:: እነርሱ የሚያስቡት እስከ ዘለቄታው እንዴት እያገዝነው ይኖራልን፤ ማን ጋር ይቀመጣልን ነው::
ትምህርት ቤት አባት ይዘውም ሲሄዱም ቢሆን እህቶቻቸው ጭምር ተጣልተዋቸዋል:: እናታቸውን ጨምሮ ይዘዋቸው ለመጥፋት የሞከሩም እንደነበሩ አይረሱትም:: ምክንያቱም አይመለስም ፣ሊጥልብን ነው ብለው ያምናሉ:: እናም በሀይል እርምጃ ተደርጎባቸው ትምህርት ቤት መግባት ቻሉ እንጂ ዛሬን እንዲህ ባሉበት ሁኔታ አያዩትም ነበር::
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸው ማለትም ሻሸመኔ የካቶሊክ አይነስውራን ትምህርት ቤት ለእርሳቸው ባለውለታቸው ነው:: ምንም እንኳን በትምህርት ቤቱ እስከ ስድስተኛ ክፍል ብቻ ቢቆዩም የትናንት ተስፋ መሰነቂያቸው የዛሬው ውጤታቸው መሰረት ሆኖ ነበር ያለፈው:: ምክንያቱም በዚህ አዳሪ ትምህርት ቤት መምህሮቻቸው ደናግላን ሲሆኑ፤ የህይወት ክህሎትን በደንብ እንዲማሩ አድርገዋቸዋል:: የእንቅስቃሴ ትምህርትንም ቢሆን እንዲሁ ለአይነስውር በሚሆን መልኩ አስተምረዋቸዋል:: በተለይም ነጭ በትራቸውን ይዘው ብቻቸውን እንዴት መንቀሳቀስ እንደሚችሉ ተገቢውን ትምህርት ያገኙበት ነበር::
ከዚህ በተጓዳኝ ብቻ፣ ከሰዎች ጋር መኖርንም ቢሆን በሚገባ የተለማመዱበትና በህይወት ጭምር የተማሩበትም ነው:: ከሁሉም በላይ ስለቀጣይ ሁኔታቸው በሚገባ ያወቁበት የቀለም ብቻ ሳይሆን ወርቅ የሆነ የህይወት ቤታቸውም ነው:: የውስጥንም የውጪንም አካባቢ በደንብ እንዲለዩና ሌሎች ስሜቶቻቸው ስለሚሰሩ እነርሱን መጠቀም ላይም ብዙ ስንቅ አሲዟቸዋል:: የሚገጥሟቸውን ፈተናዎችም እንዴት እንደሚያልፉ በሥራ ጭምር ደግፈው አስ ተምረዋቸዋል::
መለስተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት እድለኛ ሆነው በቅርብ ርቀት ሰባተኛና ስምንተኛ ክፍል በመከፈቱ ከቤተሰባቸው ብዙም ሳይርቁ አክስታቸው ጋር በመሆን ጢጆ መለስተኛ አንደኛ ደረጃ ትምህርትቤት ተምረዋል:: ይህ ትምህርት ቤት ብዙ የሚለዩ ነገሮች ያዩበት ነው:: ምክንያቱም እስከስድስት ባሉት የትምህርት ክፍሎች ውስጥ ቆይታቸውም ሆነ ትምህርታቸው ከአይነስውራን ጋር ብቻ ነው:: አሁን ግን ከአይናማው እኩል በአካቶ ተደባልቀው መማር ጀምረዋል:: ስለዚህም ብሬላቸውን ተጠቅመው አዲሱን የተሰጣቸውን ትምህርት የሚጀምሩበት የህይወት ጉዞ ላይ ደርሰዋል:: ጉዟቸው በፈተና የተሞላ ቢሆንም ያልወደቁት ለዚህ እንደሆነም ይናገራሉ::
በዚህ ትምህርት ቤት በትምህርታቸው በጣም ጎበዝ ተማሪ ናቸው:: መምህራንም በጣም ይወዷቸዋል:: እንደውም ዓይናማ ጓደኞቻቸው ጭምር በትምህርት ስለሚበልጧቸው እርስ በእርስ መተጋገዛቸው አዋጪ እንደሆነ አምነው ያግዟቸው እንደነበር ያስታውሳሉ:: ይህ ደግሞ የበለጠ ያበረታቸውና ችግሮቻቸውን ወደጎን በመተው ትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩ እድል የሰጣቸው እንደሆነ ያነሳሉ::
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ከቤተሰብ ርቀው እንዲማሩ የሆነበት ሲሆን፤ በአቅራቢያቸው ባለመኖሩ የተነሳ እንደእርሳቸው አይነስውር ከሆነ ጓደኛቸው ጋር ተከራይተው ነው የተማሩት:: አሰላ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርቱን ተከታትለዋልም:: ከዘጠነኛ እስከ 12ኛ ክፍልም በትምህርት ቤቱ ቆይታን አድርገዋል:: በዚህ ቆይታቸውም ሰው እንጂ እንደ አዲስ ፍጡር የሚያየው ከአዳሪ ትምህርት ቤት የወጣ ተማሪ ምንም የሚቸግረው ነገር የለም፤ ለእርሱ ህይወት አዲስ አይሆንበትም:: ነገር ግን ፈተና የለም ማለት ግን አይቻልም ይላሉ:: ምክንያታቸውን ሲያነሱም አስራሁለተኛ ክፍልን አጠናቀው የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት አምጥተው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቅለው የገጠማቸውን ፈተና በመጥቀስ ነው::
የመጀመሪያ ዓመትን ያሳለፉት ከግብዓቱ በላይ ጓደኛቸው ውጤት ስላልመጣለት አብሯቸው ባለመኖሩ በጭንቀት ነበር ያሳለፉት:: አራት ዓመታትን ሲያሳልፉ መተጋገዛቸው ሀይላቸው ነበርና መቼም ቢሆን የተለየ ሁኔታ ይገጥመኛል አላሉም:: ሆኖም ዩኒቨርሲቲውን ሲቀላቀሉ ግን አዲስ ሰው አዲስ ህይወት አዲስ አካባቢን ብቻቸውን መልመድ እንዳለባቸው ዱብዳ ሆነባቸው:: ስለዚህም ምንም እንኳን በትምህርታቸው ጎበዝ ቢሆኑም ይህንን መቋቋም አቅቷቸው እንደነበር ያስታውሳሉ:: እንደውም ሳይካትሪስት ሳይቀር ያያቸው እንደነበርና ብዙ መድሀኒት ተሰጥቷቸው በቀላሉ ወደ ትምህርት ትኩረታቸው ለመግባት እንደተቸገሩ ይናገራሉ::
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ፈተናዎችን አሳልፈዋል:: የመጀመሪያው ጭንቀት ሲሆን፤ በቀን እስከ አምስት ጊዜ ክሊኒክ ይሄዱ ነበር:: በራሳቸው ጊዜም ነው ይህንን ችግራቸውን የፈቱት:: ምክንያቱም በጊዜው የባሰ ጭንቀት እንጂ የተለየ መረጋጋት ውስጥ አልገቡም ነበር:: እናም ወዴት እየሄዱ እንደሆነ ራሳቸውን ጠይቀው ምላሹ በጥናትና መሰል ተግባራት ራስን ባተሌ ማድረግ እንደሆነ አሳመኑት:: ወደ ተግባር ገቡና ጥያቄያቸውና መልሳቸው እንደተገናኘ ተረዱ::
ሌላውና ሁለተኛው ደግሞ የግብዓት ጉዳይ ሲሆን፤ ብዙ የተፈተኑበት እንደነበር አይረሱትም:: በተለይም በፈታኝና አንባቢ በኩል በጣም ተቸግረው ነበር:: ከሌላው ተማሪ ሁለት ሶስት እጥፍ መልፋትን የሚጠይቅም እንደነበር ያስታውሳሉ:: ምክንያቱም ለምሳሌ ዓይናማው የወሰደውን ማስታወሻ ወስዶ በብሬል ወይም በካሴት መገልበጥና ማንበብ አንዱ ነው:: እርሳቸው ደግሞ በካሴት ሰምቶ መያዝ ደግሞ አይሆንላቸውም:: እንደውም ትንሽ ሰምቼ እንቅልፌ ይመጣል ነው የሚሉት:: ስለዚህም አማራጫው በብሬል ማስገልበጥ ሲሆን፤ ይህም በክፍያ ነው:: በዚያ ላይ የህግ ትምህርት ማጣቀሻዎችና ኮዶቹ በብሬል ስለማይገኙ ለማንበብ እጅግ ካባድ ነው:: ስለዚህም አንዱ ምርጫቸው የሚሰጠውን ማስታወሻ መከታተል አልያም ከአይናማው ጋር ሆኖ እያነበበልን ማጥናት ነው:: ይህ ሁሉ ቢሆን እንኳን ሌላ ተጨማሪ ፈተና የማይቀርበት ነው:: ይህም ፈተና ሲመጣ የሚያነብ ፍለጋ አንዱ ራስ ምታት ነው:: በግቢ ህይወት በጣም ከማልረሳው መጥፎ ትዝታ አንዱ ይህ ነውም ይላሉ::
በዚህ ስቃይ እንባ አውጥተው ያለቀሱባቸው ቀናቶች ጥቂት እንደነበሩም ያነሳሉ:: ፈተናውን መዘጋጀትና አለመዘጋጀት አንዱ ሆኖ ፈታኝ ማግኘትም ይጨመራል:: እናም በፈታኝ ብቻ ምንም እንኳን ጎበዝ ተማሪ ብትሆኝ ልትወድቂና ውጤትሽ ሊበላሽ ይችላል:: ተስፋ መቁረጥማ ብዙ ጊዜ ያጋጥማል ነው ያሉን::
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ብሬል ኮሌክሽን የሚባል ክፍል ቢኖርም ከልቦለድ ያለፈ መጽሀፍ የለበትም የሚሉት እንግዳችን፤ ብዙውን ዓመት በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዳልቆዩ ያነሳሉ:: ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ሁለተኛ ደረጃ በሚማሩበት ጊዜ በጣም ጎበዝ የእንግሊዝኛ መምህራቸው ልጅ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ስለነበር እርሳቸው እስኪመረቁ ድረስ ፈታኛቸውና አንባቢያቸው ሆኖ ማገልገሉ ነው:: በተመሳሳይ የባቾቻቸው መደጋገፍ፣ የእነርሱ ጉብዝናና ዓይናማው የሚፈልጋቸው አይነት ሰዎች መሆናቸው ለዛሬ ድላቸው እንዳበቃቸው ይናገራሉ::
ከመግባታቸው በፊት መሆንና መማር የሚፈልጉት የታሪክ ትምህርት መምህር ሲሆን፤ ለዚህ ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ የታሪክ መምህራቸው ብዙ ጫና አሳርፎባቸው ነበር:: ይህንንም ጫና በሁለት መልኩ ያዩታል:: በአወንታዊና በአሉታዊ:: በአሉታዊ ያዩት መምህር መሆን የለብህም የሚለው ግፊት ነው:: እርሳቸው የጎደለባቸው ነገር ይኖራል ብለው በመገመታቸው የተፈጠረ ነው:: ሌላው አወንታዊ ጎን ደግሞ መምህር መሆን የለብህም ያሏቸው በጣም ጎበዝ ስለሆኑ ተሰጥኦህን የሚመጥን ትምህርት መማር አለብህ ብለው ስለፈለጉ ነው የሚል ነው:: ስለዚህም የታሪክ መምህር መሆናቸውን ትተው ፍላጎታቸውን በመምህራቸው ፍላጎት ተክተው የህግ ትምህርት መስክን መረጡ:: በተጨማሪ ለአይነስውራን የሚቀርቡ የትምህርት መስኮች ውስን መሆናቸውና የተሻለው ስወጣ የሚያበላኝ፣ ቶሎ ልቀጠርበት የምችለው የቱ ነው ሲሉም መስኩ ህግ ላይ በማረፉ ትምህርቱን መርጠው በአግባቡ ተከታትለውም የመጀመሪያ ድግሪያቸውን እንዲይዙበት ሆነዋል::
ከሁለት ዓመት የሥራ ላይ ቆይታ በኋላ በሰብአዊ መብት ዙሪያ ለመማር የሞከሩት ባለታሪካችን፤ በሁለት ምክንያት ትምህርቱን እንዲያቋርጡ ሆነዋል:: የመጀመሪያው የትምህርት መስኩ ቀላል ነው በመባሉና ከስራ ጋር ለማስኬድ አይከብድም ብለው ያመኑበት በመሆኑ ሳይፈልጉ የመረጡት ነው:: ስለዚህም በግዳጅ የሚማሩ አይነት ነበር የሚሰማቸውና ብዙም መቀጠላቸውን አልፈለጉትም:: ሌላው ደግሞ 45 ቀን ያለምንም ማቋረጥ ስልጠና መውሰድ አለባችሁ ተብለው ከአዲስ አበባ በመውጣታቸው ለወር ያህል ትምህርቱን ሳይከታተሉት ቀሩ:: ስለዚህም ዊዝድሮ ሳያደርጉ አቋረጡት:: በዚያውም ሳይማሩ እስካሁን ቆዩ:: ስለዚህም ከልምድ በተጨማሪ የተለያዩ ስልጠናዎችና የልምድ ልውውጦችን በማድረግ ነው ክህሎታቸውን ያዳበሩት:: አዳዲስ መረጃዎችንም ቢሆን በማንበብ ራሳቸውን በእውቀት ያበለጽጋሉ::
አይነስውሩ ጠቅላይ አቃቢህግ
በጠቅላይ ፍርድቤት ሥራ ያለው የተከላካይ ጠበቆች ጽህፈት ቤት ውስጥ ነበር የስራን ሀ ሁ የጀመሩት:: በእርግጥ ይህ ከመሆኑ በፊት ባህርዳር ዩኒቨርስቲ የህግ መምህራንን ከህግ ትምህርት ክፍሉ መጥቶ ይመለምል ነበርና ገና ሳይመረቁ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ሆነው ነበር:: ነገር ግን በሁለት ምክንያት አልገቡበትም:: የመጀመሪያው ማስተማር የሚችሉ አልመሰላቸውም:: ሁለተኛው ደግሞ ከአዲስ አበባ መውጣቱ ከባድ መስሎ ስለታያቸው ይህንን እድል ቢያልፉም ትተውታል:: እናም በረዳት ዳኝነት የተከላካይ ጠበቆች ጽህፈት ቤት ውስጥ እንዲገቡ ሆነዋል::
በተከላካይ ጠበቆች ጽህፈት ቤት ውስጥ ተወዳድረው ከገቡ በኋላ ‹‹አንተ ረዳት ዳኛ መሆን አትችልም:: ለአይነስውራን አልተፈቀደም›› እንደተባሉ ያጫወቱን እንግዳችን፤ ህግ ስለተማሩ ብዙ ተከራክረው እንደነበር ያስታውሳሉ:: ይሁን እንጂ የመጨረሻ የሄዱበት ቦታ ላይ ያገኙት ሰውም ቢሆን ይህንን ሊሽርላቸው አልቻለም:: ቢያምንበትም በመመሪያ ይሻራል እንጂ ቦታውን ብንሰጥህ ተጠያቂ እንሆናለን ብሎ ስሙን ረዳት ዳኛ ሥራቸው ደግሞ የተከላካይ ጠበቆች ሆኖ ለሁለት ዓመት ከሦስት ወር ዘለቀ:: ከዚያ ጉዟቸው ወደ ፍትህ ሚኒስቴር ሆነ:: በዚህ ሚኒስቴር መስሪያ ቤትም ከ1999ዓ.ም እስከ አሁን ስሙ ቀይሮ እስከመጣበት ድረስ በተለያዩ ዘርፎችና አመራር ቦታዎች ላይ መስራት ችለዋል::
መጀመሪያ ወደዚህ መስሪያቤት ሲዛወሩ አቃቤ ህግ ሆነው ለሁለት ዓመት ቆይተዋል:: ቀጥለው ደግሞ ልደታ ፍትህ ጽህፈት ቤት ምክትል ሀላፊ ሆነው ለሁለት ዓመት አገለገሉ:: እንዲሁም በየካ ክፍለከተማ ፍትህ ጽህፈት ቤት ዋና ሀላፊ ሆነው ለሦስት ዓመት ሰሩ:: ከዚያ በፌደራል ማዕከል የተደራጁ ወንጀሎችን የሚመራ ክፍል ነበርና የዚህ አስተባባሪ ሆነው አገለገሉ:: የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት ዳሬክተር በመሆንም ሰርተዋል:: ይህ የሆነውም አሁን ያለው አዲሱ ሀላፊነታቸው እስኪሰጣቸው ድረስ ነው:: አሁን ደግሞ ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ሆነው ይሰራሉ:: ስለዚህም ወደ 15 ዓመታት ያህል ከህግ ጉዳዮች ሳይወጡ በፍርድቤት ሥራ ላይ አገልግለዋልም::
ከቋሚ ቅጥረኝነት በተጓዳኝ የተለያዩ ቦታዎች ላይም በሀላፊነት ሰርተዋል:: ለዚህም በሀላፊነት የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ አይነስውራን ብሔራዊ ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ለስምንት ዓመታት ያገለገሉበት አንዱ ነው:: ሌላው የኢትዮጵያ አይነስውራን ብሔራዊ ማህበርና ሌሎች ድርጅቶች በጥምረት የመሰረቱት የልዩ ገንዘብ ድጋፍ ማይክሮ ፋይናንስ ውስጥ ማህበራቸውን ወክለው ለስምንት ዓመት ያገለገሉበት በዋናነት የሚጠቀስ ነው::
የህይወት ፍልስፍና
ለነገሮች አወንታዊ አስተሳሰብ መኖር የመጀመሪያው ነው:: በእያንዳንዱ ነገር የምችለውን ሁሉ ማድረግ አለብኝም የህይወት ፍልስፍናቸው ነው:: በእርሳቸው ቁጥጥርና በእርሳቸው ችሎታ የሚሆን ነገር ሁሉ መሆን አለበት ብለው የሚያምኑም ናቸው:: ሰው በመሆናቸው ብቻ የሚያደርጉት ነገር እንዲያመልጣቸው አይፈልጉም:: ከዚያ ውጪ የእርሳቸው ድርሻ እንዳልሆነ ያምናሉና ለፈጣሪ ሰጥተው መቀመጥ አቋማቸው፣ ፍልስፍናቸውም ነው::
እርሳቸው ማድረግ ያለባቸውን እያደረጉ ሳሉ ብዙዎች ባይቀበሉትም እስከሚቀበሉት ድረስ ደጋግመው ማድረግም ፍልስፍናቸው ነው:: “ጠብ ላይል” የሚባልን ነገር አይቀበሉትም:: ምክንያቱም እኔ የህሊና ወቀሳ ውስጥ መግባት የለብኝም ብለው ያምናሉ:: ሰዎች ምን ለማለት ፈልገው ነው የሚሉት ነገር እንዳይኖርባቸው አድርገው መንቀሳቀስም የህይወት መርሀቸው ነው::
አይነስውርነትና ድሉ
አካል ጉዳተኝነት በአብዛኛው ከድህነት ጋር የሚያያዝ ነው:: ለዚህም ባላደጉት አገራትና ባደጉት አገራት መካከል ሰፊ ልዩነት መኖሩ አንዱ ማሳያ ነው:: ባደጉት አገራት አይነስውርነት በብዛት የሚፈጠረው በእድሜ ምክንያት ሲሆን፤ አንዳንድ ጊዜ ከስኳር በሽታ ጋር በተያያዘ ሊያጋጥም ይችላል:: እንደ እኛ አገር ባሉት ላይ ደግሞ ከንጽህና ጉድለት ጭምር ይህ ነገር ይመጣል:: ስለዚህም ከድህነትና ካለመማር ጋር የሚመጣ ከሆነ ፈተናው ከባድ ነው:: በእነዚህ አገራት ውስጥ ህይወት በራሱ ፈታኝ ነው:: ከዚያ ባሻገር አይነስውር ላይ ሲሆን ደግሞ ተጨማሪ ፈተና ነው:: ስለዚህም ህይወትን የሚያሸንፍ በጣም ጠንካራ የሆነና የተለየ ፍጡር ስለሆነ ሳይሆን ምቹ ሁኔታ የተፈጠረለትና ያንን እድል ጊዜ ሳይሰጥ የተጠቀመ ነው ይላሉ::
የአካል ጉዳተኞች የመጀመሪያ ፈተናቸው የሚሆነው በተለይም ከትምህርት ጋር በተገናኘ እድል ማግኘት ነው:: ለዚህም ከአራት ዓመት በፊት የወጣ መረጃ እንደሚያሳየው በአካል ጉዳተኛ ደረጃ መማር ካለባቸው ውስጥ የትምህርት እድል ያገኙት አራት በመቶ ናቸው:: ከዚያም አለፍ ሲባል ደግሞ ከግብዓት እስከ ኑሮ ድረስ ተስፋ አስቆራጭ ነገር ሊገጥምም ይችላል:: ስለሆነም አራቱ ውስጥም ገብቶ ሌሎች ፈተናዎችን መቋቋም ካልተቻለ መቼም ውጤታማ መሆን አይታሰብም::
አይነስውራን መማር ይችላሉ የሚል ማህበረሰብ ጥቂት ነው፤ የሚማሩበት አዳሪ ትምህርት ቤትም ጭምር ቁጥሩ በጣም ያንሳል:: ከዚህ ጎን ለጎን የአካቶ ትምህርት እንኳን ለመማር የሚያስችል ሙሉ ነገር ያለበት ትምህርት ቤትም የለም:: በዚህም አለመማር ለእነርሱ ልምድ እንደሆነ ይናገራሉ:: እርሳቸው በነዚህ ነገሮች ብዙም አልተፈተኑም:: ይህ ሲባል ግን ችግር አልገጠማቸውም ማለት አይደለም:: ጾም ማደርን ጭምር ያውቁታል:: ይሁን እንጂ የሚደረጉላቸው ድጋፎችና የሚሰጧቸው እድሎች እንዳይወድቁ አግዟቸዋል:: እናም አይነስውራን የብዙዎችን መልካም ፈቃድ ከአይናማው ይበልጥ ይፈልጋሉ፤ ከትምህርት ፈተና ሲወጡም ለስራ ቅጥር ይችላል አይችልም ውስጥም ስለሚገቡ እድል ከሁሉም ሰው ሊያገኙ ይገባል ይላሉም::
አይነስውራንም በግል የሚጠበቅባቸው ነገር እንዳለ ሊገነዘቡ ይገባል:: በተለይም መቻልን ማሳየት በሁሉም ዘርፍ ፈተናቸውን የሚያሸንፉበት ድላቸው ነው:: ምክንያቱም አይናማው ሲሳሳትና አይነስውር ሲሳሳት እኩል አይፈረጅም:: አይነስውሩ ድሮም እነርሱ ሲባል ዓይናማው ተሳስቶ ነው ይባላል:: ስለዚህም ስራዎችን ሲሰሩ ከስህተት ነጻ አድርገውና ተጠንቅቀው መሆን እንዳለበትም ይመክራሉ:: ለአንድ ስራ ብዙ ማሰብ እንዳለባቸውም ያስገነዝባሉ:: በተደጋጋሚ ካለመሳሳትም ነው ውጤታማና ተኣማኒነት የሚመጣውና ይህንን ገንዘብ ማድረግ እንደሚገባቸው ያነሳሉ::
ተደራራቢ ችግር አይነስውሩ ቢኖርበትም ይህም በመምህራኑ ጭምር ቢታወቅም ከዚህ የሚያወጣ ከስንት አንድ ነው:: ለፍቶ ባመጣው ውጤት እንኳን ተሰርቶለት እንጂ ሰርቶ አይደለም ነው የሚባለው:: በተመሳሳይ የቤት ስራ ሳይሰራ ቢቀር የሚሰራለት ጠፍቶ እንጂ ሳይሞላለት ችግር ገጥሞት ነው የሚልም አይኖርም:: ስለዚህም በተቻለ ሁሉ አይነስውር የሆነ ሰው ከሁሉም በልጦ መታየትን አበክሮ የሚሰራበት ጉዳይ ሊያደርገው ይገባልም ይላሉ:: በጊዜው መገኘት፣ በወቅቱ መስራት፣ እንደሚችሉ ሁልጊዜ ማሳየትም አለባቸው እምነታቸው ነው::
ገጠመኝ
ሁለተኛ ደረጃን ሲማሩ የሆነ ነው:: ሁለቱም አይነስውራን ሲሆኑ ምግባቸውን ሳይቀር ራሳቸው ያበስላሉ:: ይህ ሲሆን ደግሞ እንደዛሬው በኤሌክትሪክ ሳይሆን በቡታጋዝና በእንጨት ጭምር ነበር:: እናም በተደጋጋሚ የተለያዩ ነገሮች ገጥመዋቸው ያውቃል:: ከእነዚህ መካከል ግን ሁለቱን መቼም አይረሱትም:: የመጀመሪያው ቡታጋዙን ለኩሰው ሳያጠፉት ቤቱ ሊያያዝ ትንሽ ሲቀረው ሙቀቱን በማዳመጣቸው ለማጥፋት ይረባረቡ ጀመር:: ይሁን እንጂ በጊዜው ውሃ መስሏቸው ለማጥፊያነት የተጠቀሙት ጋዝ ሆኖ አገኙት:: በጣም ሲነድም በእሳቱ እየተለበለቡ የውሃ ጀሪካኑን ፈለጉ:: አገኙትናም ጨምረው አጠፉት:: ይህ ጊዜ አለማየት ምን ሊያደርስባቸው እንደነበር የማይረሳቸው ገጠመኝ ነው::
ሌላውና ሁለተኛው ገጠመኛቸው ከቅንጬ ጋር ባለመተዋወቃቸው የሆነው ነው:: ማለትም ቅንጬ እንዴት እንደሚሰራ ምን ያህል ለድስቱ በቂ እንደሆነ አያውቁም:: እናም በዛ አድርገው ይጥዳሉ:: መጀመሪያ ላይ ከድነውት ሲፈላና ሲፈስ ውሃው ነው ብለው ይከፍቱታል:: ነገር ግን እየሞላ እየሞላ መፍሰሱን ሳያቆም ሲቀር በእጃቸው ውሃ ነው አይደለም የሚለውን ለመለየት ይነኩታል:: በዚህን ጊዜ ሞልቶ የተረፈው ቅንጬ እጃቸውን ያቃጥላቸዋል:: ለማውጣትም ሆነ ለመቀነስ ተቸግረውም እንደነበር አይረሱትም:: በተለይ ግን መቀነሻ ስለሌላቸው ሳይበስል አውጥተው ከሚፈስ ብለው የተመገቡበትን ሁኔታ መቼም አይዘነጉትም::
መልዕክት
ለደስታ መቼም ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም:: ሁሌ የደስታ ምንጭን ፈልጎ የሚኖርበት ነው:: ለዚህ ደግሞ መጀመሪያው ሰዎች ሲደሰቱ ማየት ነውና ኢትዮጵያውያን የኖሩበትን ባህል ዳግም ማስጠራትና ለልጆቻቸው ማስተላለፍ ላይ መስራት አለባቸው:: በተለይም ብሔርተኝነት የሚለውን እሳቤ ከውስጣቸው አውጥተው አንድ ሆነው መቀጠልን መለማመድና መተግበር አለባቸው:: ምክንያቱም በብሔር መወለድ ፈልገውት የሚያገኙት ወይም ሳይፈልጉት የሚያስለቅቁት ቀለም አይደለም:: እናም ይህ መሆኑን አምኖ መከባበርን ማስቀደምና የራስን ደስታ መፍጠር የሁልጊዜ ተግባራችን ሊሆን ይገባል ይላሉ::
መቼም ቢሆን ትልቅ የሚያስብልን እድሜ ወይም የሥራ ልምድ ሳይሆን አስተሳሰብ ነው:: አስተሳሰብ ወርቅ ሀሳቦችን ያላብሳል፤ አስተሳሰብ ለሁሉ መልካምን የሚመኝ ሰው ያደርገናል፤ አሉታዊ እንኳን ቢሆን በአወንታዊ የምንመለከትበትን እድል ይሰጠናል:: አስተሳሰብ የእድል ምንጭ ፣ የደስታ በረከት ፣ የሀብት ግምጃ ቤት ነው:: ስለዚህም ሰዎች በዚህ ምድር ላይ በሚኖሩባት ጥቂት ጊዜ ምቾትን ከፈለጉ መልካም አሳቢ መሆንን ሊያስቀድሙ ይገባል:: በተለይም በዚህ ጊዜ ከመልካም አስተሳሰብ በላይ የሚያሻግርና ምቾትን የሚሰጥ ስለሌለ ሁላችንም ባህላችን እናድርገው ሲሉ ይመክራሉ::
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 4 ቀን 2013 ዓ.ም