
የኢንዱስትሪ ከተማ ተብላ ትታወቃለች። ቆነጃጅት ብቻ ሳይሆኑ ስብዕናቸው ያማረ ደጋግ ዜጎች ያሉባት የፍቅር ከተማ ናት። የሁሉም ሐይማኖት ዕምነት ተከታይ ተቻችሎና ተሳስቦ የሚኖርባት መሆኗ ልዩ ያደርጋታል ኮምቦልቻን። አየር ንብረቷ ለጤና ተስማሚ ሲሆን ከፍተኛ ዓመታዊ የሙቀት መጠኗ 26 ነጥብ 1 ዝቅተኛው ደግሞ 5 ነጥብ 8 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ይደርሳል። ዓመታዊ አማካኝ የዝናብ መጠኗም 1 ሺህ 248 ሚሊ ሜትር እንደሚደርስ መረጃዎች ያመላክታሉ።
በከተማ አስተዳደሩ ባሉ ቀበሌዎች 8 ነጥብ 05 በመቶ ደጋ፣ 74 ነጥብ 86 በመቶ ወይና ደጋ፣ 17 ነጥብ 09 ቆላ ነው። ከተማዋ ከባህር ጠለል በላይ በ1 ሺህ 857 ሜትር ከፍታ ላይ ትገኛለች። ከተማዋ በ1928 በጣሊያን ወረራ ወቅት እንደተቆረቆረች ይነገርላታል።
የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ኢንጅነር ከማል መሐመድ እንደሚናገሩት፤ ኮምቦልቻ ከተማ በአሁኑ ወቅት ያላት የቆዳ ስፋት 124 ነጥብ 5 ስኩየር ኪሎ ሜትር ነው። ከ253 ሺህ ህዝብ በላይ ይኖርባታል። በተቆረቆረችበት ወቅት በአካባቢው የነበረው አብዛኛው ነዋሪ ይተዳደር የነበረው በግብርና ሥራ ነበር። አሁንም በስድስት ገጠር ቀበሌዎች የሚኖረው 22 በመቶ የሚሆነው የከተማዋ ነዋሪ በግብርና ስራ የሚተዳደር ነው።
ሆኖም ያኔም ቢሆን ለዛሬው የኢንዱስትሪ ማዕከልነቷ የየራሳቸውን አስተዋጽኦ በማድረግ መሰረት የጣሉና ሞቅ ደመቅ የሚያደርጓት የተወሰኑ ነጋዴዎች እንደነበሯት ይነገራል። አሁን የነጋዴዎቹ ቁጥር ሰፍቷል። ይህም ለከተማው ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። በአሁኑ ወቅት ከከተማው ነዋሪ ቀላል የማይባል ቁጥር ያለው በተለያዩ ፋብሪካዎች ተቀጥሮ የሚሰራ ነው።
እየተስፋፋ ካለው ግዙፍ የኢንዱስትሪ ፓርክ በተጨማሪ አራት የኢንዱስትሪ ዞኖች ያሏት መሆኑን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ኢንጅነር ከማል ይገልጻሉ። የኢንዱስትሪ ዞኖቿ በ558 ነጥብ 1046 ሄክታር መሬት ላይ ያረፉ ናቸው። ከ1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።
በከተማዋ በሚገኘው በተንጣለለ ሥፍራ ላይ ካረፉት ኢንዱስትሪዎች መካከልም ለ6 ሺህ 182 ዜጎች የስራ ዕድል የፈጠሩ 33 ኢንዱስትሪዎች ከተማዋን ለማሳደግ በሚያችስችል ከፍተኛ የሥራ ግስጋሴ ላይ ናቸው። ወደ ምርት ማምረት ገብተዋል።
በአጠቃላይ በትግበራ ደረጃ ያሉትን 31 ኢንዱስትሪዎችና በቅድመ – ትግበራ ላይ የሚገኙትን 143 ኢንዱስትሪዎች ጨምሮ 195 ኢንዱስትሪዎች በዘርፉ ወሳኝ ሚና ለመጫወት ደፋ ቀና እያሉ ይገኛሉ። ከነዚህ በተጨማሪም የሐርቡ አዲስ ኢንዱስትሪ መንደርም ተመስርቶ ለባለሀብቶች መሬት የማስተላለፍ ሥራ መጀመሩንም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ኢንጅነር ከማል አብራርተውልናል።
በኮምቦልቻ መሬት ወስደው ግንባታ ያልጀመሩ 82 ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውን ኢንጂነር ከማል አልሸሸጉም። እንዲሁም በግንባታ ላይ ያሉና ግንባታቸው ሙሉ በሙሉ ያልተጠናቀቁ ኢንዱስትሪዎች ብዛት 28 መሆኑን ጠቅሰዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ሌላው ከሚታወቅባት መካከል ቅርሶች አንዱ ነው። ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ከሰጡን ምላሽ አራት ዋና ዋና ቅርሶች እንዳሏት ነው የተረዳነው። ዋነኛውና ቅርሷ በከተማዋ ውስጥ የሚገኘው መጀት የእስልምና ሀይማኖት መዳረሻ ቦታ ነው። ሌላውና ሁለተኛው ዛውዮች የእስልምና ሀይማኖት መዳረሻ ቦታ ሲሆን ሦስተኛው ቅርሷ ልጎ ጊዮርጊስ አንድነት ገዳም እና አራተኛውና የመጨረሻው ቅርሷ በከተማዋ ቀበሌ 06 ውስጥ የሚገኘው ደራ ቅዱስ ቶማስ ቤተክርስቲያን ነው።
‹‹የኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎችና የመሰረተ ልማት መሟላት ለከተማው ህዝብ አጠቃላይ እንቅስቃሴም ሆነ ለኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ትልቅ ሚና እንዳለው ይታወቃል። አስተዳደሩ ከዚህ አኳያ ብዙ ሥራዎችን ሰርቷል›› ሲሉ በከተማዋ የኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎችን አስመልክተው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ኢንጅነር ከማል ጠቅሰዋል።
የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር መላውን የከተማዋን ህዝቦች ተጠቃሚ ለማድረግና ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት ከጊዜ ወደ ጊዜ አዳጊ የሆነ እንቅስቃሴ እያደረገ የመጣበት ሁኔታ አለ። ይሄ እንቅስቃሴ በተለይ ለከተማዋ ወጣቶች ሰፋፊ የሥራ ዕድሎችን የሚፈጥር ነው። ከዚህም በተጨማሪ በፌደራል መንግስት በጀት የተሰራው ሙሉ በሙሉ ወደ ምርት ሲገባ በሁለት ፈረቃ እስከ 13ሺህ ለሚደርሱ ዜጎች የስራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ መጠበቁንም አብራርተዋል።ለነዚህ ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው ዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጠረው በጨርቃ ጨርቅ ዘርፎች መሆኑንም ጠቅሰዋል። እዚህ መስክ ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ ግብይትን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ሲሆን ለአብነትም የለማ ኢንዱስትሪ ፓርክ በከተማዋ ምርጥ የኢንቨስትመንት አካባቢ ላይ አልሚዎችን ተቀብሎ በመስራት ላይ መገኘቱን ነግረውናል።
አስተማማኝ የኤሌክትሪክ፣ የውሃና የቴሌኮም አገልግሎት መኖሩ፣ ከተማዋ ለጅቡቲ ወደብ ቅርብ መሆኗ፣ ዘመናዊ የአውሮፕላን ማረፊያና የደረቅ ወደብ አገልግሎት መኖሩ፣ አዋሽ ኮምቦልቻ ወልዲያና መቀሌን የሚያካልል የባቡር ጣቢያና ወርክሾፕ በከተማዋ መገኘቱ ለኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው ኮምቦልቻን ምቹ ከሚያደርጋት አንዱ መሆኑን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ይናገራሉ።
የፌደራል ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በከተማዋ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ከፍቶ እየሰራ መሆኑ፣ በርካታ አገልግሎቶችን የሚሰጡ የመንግስት የልማት ድርጅቶችና የመንግስትና የግል የፋይናንስ ተቋማት መኖራቸው፣ ከተማዋ በፌደራልና በክልል መንግስት ልዩ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገላት መሆኑ ሌላው ለኢንቨስትመንት መልካም አጋጣሚ የሆነ የኮምቦልቻ ዕድል መሆኑን ያብራራሉ። በቂ የተማረና የሠለጠነ የሠው ኃይል መኖሩ ታታሪና ትጉህ ሠራተኛ በበቂ ሁኔታ ማግኘት የሚቻል መሆኑ፣ ኗሪዎቿ እንግዳ ተቀባይ፣ ሰው አክባሪና የመቻቻል ባህል ባለቤት መሆናቸው፣ ለኢንደስትሪዎች ግብዓት የሚሆኑ የሠው ኃይል የሚያሰለጥኑ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የቴክኖሎጂ ተቋምና ኮሌጅ መኖራቸውና ከእነዚህ ተቋማት የሚወጡት ምሩቃን በቅርበት ኢንዱስትሪዎችን እየጎበኙና በተግባር እየቃኙ የሚወጡ መሆኑ ከተማዋ ለኢንቨስትመንት የተመቸ ሁኔታ እንዳላት ሁነኛ ማረጋገጫዎች ናቸው ሲሉም ተቀዳሚ ከንቲባው ይናገራሉ።
ይኼ ሁሉ ተደማምሮ የኮምቦልቻ ከተማን በአማራ ክልል ካሉት ከተሞች ደሴ፣ ባህር ዳርና ጎንደር ወደ ሪጅኦ ፖሊታን ከተማነት እንድታድግ ሆኗል። የአማራ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት ኮምቦልቻ ከተማን ወደ ትልቅ ከተማነት ደረጃ ሲያሳድጋት የሕዝብ ብዛቷ፣ ወጪን የመሸፈን አቅሟን፣ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታዋ እንዲሁም የሕዝብ አሠፋፈር ጥግግቷን ታሳቢ አድርጎ ነው። በተለይ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታዋ የጎላ መሆኑ ከኢጣሊያ ወረራ ጀምሮ የነበራትን አስተዋጽኦ ይጠቅሳሉ።
‹‹የከተሞች ልማት ለአንድ ሀገርም ሆነ ክልል ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጾ አለው›› ሲሉም ወደ ሪጅኦ ፓሊታን ከተማነት ማደጓ የኢንዱስትሪ ማዕከልነቷነት በአግባቡ እንድትወጣ ያስችላል። ኮምቦልቻ ወደ ትልቅ ከተማ ዕድገት ደረጃ መድረሷ የሠራተኛ ደመወዝን ጨምሮ ለሥራ ማስኬጃ የካፒታል በጀት የሚጠይቁ ሥራዎችን ወጪ ለመሸፈን ያስችላታል። ገቢ የመሰብሰብ አቅሟን ያጠናከራል። ያላትን የገቢ አማራጮች ሁሉ አሟጣ በመጠቀም የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ ያስችላታል። ይህም ሕዝቡ የሚያነሳቸውን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመስራት ያስችላል።
እንዲሁም ኢኮኖሚውን ያሳልጣል፤ የንግድ፣ የቱሪዝምን እንቅስቃሴ፣ የመንገድና ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን በአጠቃላይ የልማት እንቅስቃሴን ያፋጥናል። በአካባቢው የማኒፋክቸር ኢንዱስትሪዎችን መስፋፋት ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ የከተማው ነዋሪ ኑሮ የሚሻሻልበትን የከተማዋንና የክልሉ ኢኮኖሚ የሚያድግበትን ምቹ ሁኔታም በተገቢው መንገድ ይፈጥራል።
የማኒፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ከተስፋፉና ሕዝቡ በአካባቢው የሚኖር ከሆነ የሥራ ዕድል ፈጠራንም ያበረታታል። ከዚህም በላይ የሥራ ዕድሉ አሁን ከተፈጠረውና ካለበት ደረጃ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ያሳድጋል።
የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ብዙዎቹ ከተማዋ ወደ ሪጅኦ ፖሊታን ከተማነት ማደጓ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ማዕከል መሆኗ ለክልሉ ህዝብና ለሀገር ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርግና ሰፊ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ይናገራሉ። ከነዚህ መካከል ወይዘሮ ዝማምነሽ አሰፋ እንደሚሉት ኮምቦልቻ በኢንዱስትሪ ማዕከልነት የታወቀችና ለክልሉም ሆነ ለሀገራችን ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገች ናት። የቀድሞዎቹ ቀርተው ከቅርቦቹ እንኳን ኮምቦልቻ ኢንዱስትሪያል ፓርክን መጥቀስ ይቻላል። ከአዲስ አበባ በ375 ከክልሉ መዲና ባህር ዳር ደግሞ በ505 ኪሎ ሜትር ርቀት የምትገኘውን ኮምቦልቻን ለሪጅኦ ፓሊታን ከተማነት ካስመረጣት አንዱም ይኸው የኢንዱስትሪ ማዕከልነቷ ነው ብለው ያምናሉ።
ሌላው የኮምቦልቻ ከተማ 08 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሐምዛ ከድር እንደሚሉት፤ ኮምቦልቻ ከተማ ቀድሞ የኢንዱስትሪ ማዕከል ከመሆን ጋር በተያያዘ ሥልጣኔ ከሚገለፅባቸው የሀገራችን ኢትዮጵያ ከተሞች ዋነኛዋ ናት። ሆኖም ዕድገቷ እንዲህ እንደ ቀደምት ኢንዱስትሪና የንግድ ማዕከልነቷ አልነበረም። በእጅጉ አዝጋሚ ሆኖ ነው የኖረው። የነዋሪዎቿም ሕይወት ቢሆን ከከተማዋ ዕድገት ጉስቁልና የተለየ ታሪክ የለውም። በተለይ በሥራ ዕድል ፈጠራ የነበራት እንቅስቃሴ የተቀዛቀዘ ነበር። አሁንም የሚቀረው ቢሆንም ያኔ በተለይ የመንገድ፣ የመብራት፣ የውሃና የቴሌኮም አገልግሎቷ ተደራሽ አልነበረም። የመቻቻልና የፍቅር ተምሣሌት ከተማ ብትባልም ከሠላም እጦትና ከአገልግሎት አሰጣጥ መጓደል ጋር ተያይዞየመልካም አስተዳደር ችግሮችም ነበሩ። በዚህ የተነሳ ብዙ ወጣቶች ጥለዋት ወደ ዐረብ ሀገራት ይሰደዱ የነበረበትን ሁኔታ መጥቀሱ ጥሩ ማሳያ ነው ብለው ያምናሉ።
ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ ግን ይኼ ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣት ችሏል። በተለይ ባለፉት ሦስት የለውጥ ዓመታት ደግሞ የበለጠ ተሻሽሏል ማለት ይቻላል። ለወጣቱ በነባርም ሆነ በአዳዲስ ኢንዱስትሪ መስክ ሰፊ የሥራ ዕድል የተፈጠረበትን ሁኔታ አስተውለዋል። በንግድ የሚተዳደረው ህዝብ ቁጥሩ ጨምሯል። ይኼ ሁሉ ታሳቢ ሆኖ በምትገኝበት ክልል እንደ አሉት እህት ከተሞቿ ጎንደር፣ ባህር ዳርና ደሴ ሁሉ ወደ ሪጅኦ ፖሊታን ከተማነት ማደጓ ተገቢ መሆኑን ይገልጻሉ። ከተማዋ ወደ ሪጅኦ ፖሊታን ከተማነት የዕድገት ደረጃ ማግኘቷ በአቅራቢያዋ ካለው ከደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ጋር በቅንጅት እንድትሰራና የበለጠ ዕድገቷን እንድታፋጥንም ሰፊ በር ይከፍትላታል ይላሉ።
ወጣት እንዳለ ማሩ በከተማዋ 06 ቀበሌ ነዋሪ ነው። የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ተከታትሎ ያጠናቀቀው በኮምቦልቻ ሲሆን፤ ከትምህርቱ ጎን ለጎን በከተማዋ በንግድ ስራ የተሰማሩትን ወላጆቹን እያገዘ ነው። ሆኖም በከተማዋ አስተዳደር ከነበረ የመልካም አስተዳደር ችግር ጋር ተያይዘው በገጠሙት አንዳንድ ችግሮች ሳቢያ በዐረብ ሀገር ተሰዶ ለመቆየት ተገድዷል። ነገር ግን ባለፉት ሦስት የለውጥ ዓመታት በከተማዋ ከመልካም አስተዳደርም ሆነ ከሁለንተናዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ በታየው መሻሻል ከተሰደደበት ተመልሷል። እናም የአብዛኛው የከተማዋ ነዋሪ ቋሚ መተዳደሪያ ንግድ እንደመሆኑ እሱም የራሱ ንግድ ድርጅት በመክፈት እየሰራ ይገኛል።
ኮምቦልቻ በኢንዱስትሪ ማዕከልነት ቀደምት ብትሆንም እስካሁን የሚመጥናትን የከተማነት ደረጃ ሳታገኝ መቆየቷ ይቆጫት እንደነበር የገለፀችልን ደግሞ በኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ የምትሰራው ወጣት ፎዝያ አህመዲን ነች። ቢዘገይም አሁን ላይ የትልቅ ከተማነት ደረጃ መሰጠቷ አስደስቷታል። እሷን ጨምሮ ብዙ ወጣቶችን አብዝተው ለዕድገቷ እንዲተጉ አነሳስቷቸዋል።
በተለይ ወደ ሪጅኦ ፖሊታን ከተማነት ከማደጓ ጋር ተያይዞ የሚፈጠረው ከክፍለ ከተማ እስከ ቀበሌ አደረጃጀት ያካተተ የመንግስት መዋቅር በራሱ ለብዙ ነዋሪዎች ተጨማሪ የሥራ ዕድል የሚከፍትበት ዕድል ይሰጣል። የአምነት መዳረሻ ቦታን ጨምሮ በከተማዋ የሚገኙ ቅርሶችም በገቢ ምንጭነት ዕድገቷን የሚያፋጥኑበት ሁኔታ ይኖራል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የከተማውን ሕዝብ በማሳተፍ ኮምቦልቻ ለነዋሪዋ ደረጃዋን የሚመጥን አገልግሎት እንድትሰጥ ለማስቻልና አዲሱን አደረጃጀቷን ለማሳለጥ የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ በመመኘት ጽሑፋችንን ቋጨን።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 3/2013