ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ስለ ዛፍ መትከል ሰሞኑን ለህዝብ እንደራሴዎች እንደተናገሩት ‹‹ዛፍ መትከል በሂደት ወደ ሀገር በቀል፣ ከዚያ ወደ ፍራፍሬ ከዚያ አካባቢ ተስማሚ የሆነውን እየመረጡ መሄድ አስፈላጊ ቢሆንም በጥቅሉ ዛፍ መትከል በጣም ጠቃሚ ነው። ቦንጋ፣ ሚዛን፣ ሸካ ብንሄድ ከየትኛው የኢትዮጵያ አካባቢ ያነሰ እንጂ የተሻለ መሰረት ልማት የለም፤ የተለየ ፋብሪካ የለም። ግን ሸካ መንገድ ባይኖርም አይራብም። ከጫካ ማር፣ ኮረሪማ ይለቅማል። ጫካ በራሱ ተጨማሪ ነገር ሳይኖረውም እንዳንራብ ያደርጋል። ከብቶቻችን በደንብ ይመገባሉ ወተት እናገኛለን፤ ዝናብ ስለሚዘንብ መሬት አይደርቅም። ዛፍ መትከል ጥቅሙ ወደ ሸካ ስንሄድ ይገባናል። የምርጫ ጉዳይ ሊኖር ይችላል። ሙዝ አልበላም ቆጮ አልበልም ሊባል ይችላል፤ ግን መራብ የለም። ዛፍ መትከል በሳይንስ ከሚነገረው ተጨማሪ ኢትዮጵያን በእጅጉ ይጠቅማል። ለቱሪዝም በጣም ከፍተኛ ትርጉም አለው። ዛፍ መትከል ባህላችን ሆኖ መቀጠል አለበት። ዘንድሮ ያለው ነገር ደስ ይላል፣ በመሆኑም መቀጠል አለበት። ይህን በማድረግ ብዙ ነገር መቀየር ያስችላል።›› ሲሉ እንደ ሀገር የአረንጓዴ አሻራን ፋይዳ አስረድተዋል።
በተመሳሳይ መንገድ የሀገሪቱ ውስጥ የሚስተዋለውን የዋጋ ግሽበት ለማቃለል ዘርፈ ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል። በተለይም ደግሞ አለም ላይ ያለው አጠቃላይ ያለው ግሽበት ያመጣው ጫና ኢትዮጵያንም እየተፈታተነ መሆኑን አብራርተዋል። መንግስት ይህን በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ወስዶ ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ ይሆናል። ጥረት አድርገናል የሚል ሳይሆን ጥረት ውጤት እንዲያመጣ ሰፋፊ ሥራዎች መሠራት አለባቸው። በመሆኑም ማክሮ ኢኮኖሚውን ማረጋጋት ላይ ብዙ መሰራት እንዳለበት ተናግረዋል።
በሌላ ጎኑ ደግሞ ኢትዮጵያ የጀመረቻቸው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሞች በብዙ መንገድ ፋይዳቸው የጎላ እንደሆነ እየተነገረ ነው። በተለይም ደግሞ የምጣኔ ሃብት መነቃቃትን በመፍጠርና የስራ ዕድል በማብዛት ዓይነተኛ ሚና አለው። በዚያው ልክ ግን ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ የሚገባ ጉዳይ ስለመሆኑም በተደጋጋሚ ይነሳል።
ዶክተር ዳዊት ሃዩሶ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት ትምህርት ክፍል መምህር ናቸው። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በስፋት እያካሄደች ያለው አረንጓዴ አሻራ ማኖር እንቅስቃሴ ሀገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ትርጉም ያለው ሲሆን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ፋይዳም እንዳለው ይናገራሉ። በሌላ ጎኑ ደግሞ የአረንጓዴ አሻራ መኖር ስራን የሚፈታተኑ በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውን በመጠቆም በህግ ምላሽ ማግኘት ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉም ያመለክታሉ። ከዚህም በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት እንደ ሀገር ለሚስተዋለው የዋጋ ግሽበት መፍትሄ ማበጀት እንደሚገባ እና ለዚህም የተመረጡ አሰራሮች ስለመኖራቸው ይጠቁማሉ። በተጨማሪም ኢትዮጵያ የምትከተለው የኢኮኖሚ ሪፎርም ከረጅም እና አጭር ጊዜ አኳያ ፋይዳው በሚገባ መተንተን እንዳለበት ይጠቁማሉ። የዛሬ እንግዳችን ናቸው መልካም ቆይታ።
አዲስ ዘመን፡– አረንጓዴ አሻራ የረጅምና አጭር ጊዜ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ምንድን ነው?
ዶክተር ዳዊት፡– ይህን በተለያየ መንገድ ማየት ያስፈልጋል። አረንጓዴ አሻራ አንደኛው ፋይዳው አካባቢው በመጠበቅ የአካባቢ ምርታማነት በመጨመር የግብርና ምርታማናት እንዲጎለብት ያደርጋል። ይህ ማለት ዘርፈ ብዙ አስተዋፅኦ አለው። አፈር ለምነት ተጠበቀ ማለት ግብርና ላይ በጎ አስተዋፅ አለው። በአረንጓዴ አሻራ ዛፎች የሚተከሉት የሥነ ምህዳርን ጤናማነት ለመጠበቅ ብቻ ሳይሆን አንዳንዶቹ ገበያ ተኮር በመሆናቸው ነው። ለምሳሌ በደቡብ ብሄር፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የጫካ ቡና እየተተከለ ነው። በኦሮሚያ ክልልም ይህ በሰፊው ይስተዋላል። ይህ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ አልፈው ገበያ ተኮር በመሆናቸው ወደ ውጭ በመላክ ገቢ የሚገኝበት ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን አቮካዶ እና ሌሎች ፍራፍሬዎች በስፋት እየተተከሉ ነው። ይህም በምግብ ዋስትና በማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት ትልቅ ፋይዳ አለው።
አዲስ ዘመን፡– በገበያው የተጠቃሚነት ዓይን ሲመዘንስ?
ዶክተር ዳዊት፡– በገበያው ዓይን ስናይ ደግሞ ኢትዮጵያ ከአምስት እና አስር ዓመት በኋላ ከፍተኛ ደንና የደን ውጤቶች እንደሚኖራት ይጠበቃል። ይህ ማለት ደግሞ ወደ ውጭ ምርቶችን ለመላክ ዕድል የሚሰጥ ሲሆን ከፍ ያለ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ያስችላል። ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡትን የሚቀንስ በመሆኑም ሚናው ትልቅ ነው። የደን ውጤቶችን በሀገር ውስጥ መተካት ሚናው ቀላል አይደለም። ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎችም እንዲፋፉ ሚናው የጎላ ነው። በተለይም የጣውላ ኢንዱስትሪ ከፍ ያለ ጥቅም አለው። በመሆኑም የእንጨት ኢንዱስትሪው ከፍ ካለ የገበያ ትስስሩ የማደግና ኢኮኖሚ ጠቃሜታው ከፍ ያለ ይሆናል።
በአሁኑ ወቅት የአረንጓዴ ኢኮኖሚን ብዙ ሀገራት እያከናወኑ ነው። በአየር ፀባይ መቀያየር የተነሳ ታዳጊ ሀገራት ጂ.ዲ.ፒ በዓመቱ በ0 ነጥብ 05 በመቶ እየቀነሰ ነው። በመሆኑም መሰል የአረንጓዴ ልማት ችግሮችን ለመከላከልና ኢኮኖሚውን የተረጋጋ ከማድረግ አኳያ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል። አልፎም ኢትዮጵያ ውስጥ ግብርና ምርት የተመሰረተው በዝናብ ነው። ዝናብ ወጣ ገባ በሆነ ወቅት የምግብ እጥረት ይከሰታል። በተለይም ከተማ አካባቢ የምግብ ነክ ነገሮች ከፍተኛ ግሽበት ይስተዋላል። ስለዚህ እነዚህንም ለመቀነስና ግሽበትን ለማስተካከል ደን መትከል ሚናው ቀላል አይደለም።
አዲስ ዘመን፡– አሁን ባለው ሁኔታ አረንጓዴ አሻራ ማኖር በሚለው ዘመቻ ላይ ፈተናዎች የሚሆኑት ምንድን ናቸው?
ዶክተር ዳዊት፡– በአንድ በኩል እየተከልን ስንሄድ ተፈጥሮን መጠበቅ ነው። በሆነ ወቅት ከፍተኛ ደን ነበር። ግን ነገሮችን አጣጥሞ መሄዱ ላይ ፈተና አለ። ነገር ግን ደን ሆነው ጥምቅ በሚገባ መስጠት ደረጃ ላይ ሳይደርሱ እየተቆረጡ ነው። በአሁኑ ወቅት የሚተከሉ እጆች እንጂ የሚቆርጡ እጆች ላይ የተሰራው ሥራ በጣም አነስተኛ ነው።
ሌላው የጣውላ ንግድ ህግ አልተበጀለትም። ኮንትሮባንድ ነጋዴዎች በገጠር እየተንቀሳቀሱ ጥቅማቸውን ከመጠበቅ አኳያ ብቻ ደን እየተጨፈጨፈ ነው። ይህ ህግ ሊበጅለት ይገባል። በአጠቃላይ የችግኝ ተከላ፣ ቆረጣ እና ጣውላ ንግድ በህግ ሊመራ ይገባል። ሰው ችግኝ የመትከል መብት እንዳለው ሁሉ ዛፍ የመቁረጥ መብቱም በህግ ሊመራ ይገባል። ይህ ካልሆነ የሚቆረጠው እየበዛ የሚተከለውም በሚፈለገው ደረጃ ሳይሆን እየተመናመነ ይሄዳል።
በአሁኑ ወቅት የችግኝ ተከላ እየተከናወነ ያለው በዘመቻ እየሆነ ነው። ይህ አካሄድ ጥቅም ቢኖረውም ችግኝ መትከልና መንከባከብ በግለሰቦች እና በሀገር ደረጃ ባህል መደረግ አለበት። ከዘመቻ ባላፈ በዕቅድና በሳይንሣዊ አሰራር መደገፍ አለበት። በርካታ ችግኞችም በየጊዜው መተከል አለባቸው። ይህ በቀላሉ መታየት የለበትም። አሁን ያለው የዘመቻ ሥራ በራሱ ትኩረት ሊሰጠውና ወደ ህጋዊ መስመር ገብቶ መሥራት ይገባል። በዚህ አግባብ ያልተመራ ከሆነ ዘርፉ ላይ የሚወጣው ጉልበትና የሚገኘው ጥቅም ላይመጣጠን ይችላል።
አዲስ ዘመን፡– ከአረንጓዴ አሻራ ጎን ለጎን መንግስት የጀመራቸው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሞች አሉ። እነዚህ ፋይዳቸው ምንድን ነው?
ዶክተር ዳዊት፡– አዎንታዊ ጥቅሙን ስንመለከት አጠቃላይ በኢትዮጵያ ደረጃ ፕራይቬታዜሽን ለማየት የማክሮ ኢኮኖሚውን ማየት ይገባል። የማክሮ ኢኮኖሚ አመላካች ከሆኑት አንዱ የኑሮ ውድነት አንዱ የማክሮ ኢኮኖሚ መሳያ ነው። ሌላው የውጭ እና ሀገር ውስጥ ንግድ ሚዛን አለመጣጣም አንዱ የማክሮ ንግድ ማሳያ ነው። በተለይም ከፍተኛ ውጭ ምንዛሪ የሚጠይቀውየሸቀጣሸቀጥ ግዥ ይህን ያመለከታል። የውጭ ምንዛሪ ጨመረ ማለት ግሽበት ጨመረ ማለት ነው። ወደ ውጭ የምንልከው ሦስት ቢሊዮን ዶላር ሲሆን የምናስገባገው 16 ቢሊዮን ዶላር ነው። ይህ በከፍተኛ ደረጃ ያልተመታጠነ ስለሆነ ብዙ ስራ የሚጠይቅ ነው። ከፍተኛ ተፅዕኖ እየፈጠረ ነው። አብዛኛው ሸቀጥ ከውጭ የሚገባ በመሆኑም በኢትዮጵያ የኑሮ ሁኔታ ችግር ፈጥሯ። ይህ አካሄድ ኢንቨስትመንት አያበረታታም።
ስለዚህ እነዚህ ነገሮችን መፍትሄ ማፈላለግ አስፈላጊ ነው። ፕራይቬት ሴክተር ከመንግስት ጋር ሲነፃፀር በዋጋም በአሰራር እና ኢንቨስትመንት በማካሄድም የተሻለ ነው ተብሎ ይታሰባል። በመሆኑ ፕራይቬታዜሽን ማድረግ ይመከራል። ይህም የንግድ ሚዛን ለመጠበቅ ያግዛል። የውጭ ምንዛሪ በቀላሉ ለማግኘት ያስችላል። ሚዛኑን የጠበቀ ንግድ ሊኖርም ይችላል። በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ መንግስት ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል። የንግድ ሚዛን መጠበቅ ብሎም ግሽበትን ለመቆጣጠር ፋይዳ አለው። እነዚህ ነገሮች ግን በአጭር ጊዜ የሚኖሩ ጥቅሞች ናቸው።
አዲስ ዘመን፡– ፕራይቬታይዜሽን በረጅም ጊዜ የሚኖረው ትርጉምስ ምንድን ነው?
ዶክተር ዳዊት፡– ይህ እነዚህን ትልልቅ ኩባያዎችን የሚገዙት የውጭ ሀገር ስለሚሆኑ የሀገር ኢኮኖሚ ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል። ከፍተኛ ቀጣሪ ራሳቸው ይሆናሉ። ከፍተኛ የገንዘብ ክምችት ስለሚኖራቸውም መንግስት የሚያወጣቸውን ፖሊሲዎች በገንዘብ ኃይል እና አቅም ተፅዕኖ ይፈጥራሉ። መንግስት ላይ ጫና በመፍጠርም ከህዝብ ውሳኔ በላይ የራሳቸውን መንግስት በገንዘብ አቅም ሊያመጡ ይችላሉ። ስለዚህ በሀገር ሉዓላዊነት ላይ ጉዳት ያመጣል። ሀገር በቀል በሆኑ ድርጅችም ከውድድር ውጭ ያደርጓቸዋል። በተለይም በኢትዮጵያ ውስጥ ባለሃብቶች ገና በማደግ ላይ ስለሆኑ ጉዳት አለው። ኢኮኖሚውም በጥቂት ባለሃብቶች እንዲሽከረከር ያደርጉታል። በአውሮፓ እና በአሜሪካ እየታየ ያለው ይህ ነው። አንድ ከመቶ የሚሆነው ህዝብ በያዘውና ባካበተው ሃብት ነው ሰፊ ህዝብ የሚዘወረው። ይህ በረጅም ጊዜ የሚኖረው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑም በሚገባ ማሰብ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡– እነዚህ ችግሮች እንዳይከሠቱ ሪፎርሙ እንዴት መከናወን አለበት?
ዶክተር ዳዊት፡– መጀመሪያ ፕራይቬታይዝ የሚደረጉትን ተቋማት ቅደም ተከተል መጠበቅ ነው። ከዚያ ደግሞ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችን ሚዛን መጠበቅ ያስፈልጋል። የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች የተሻለ አቅም እንዲፈጥሩ ማድረግ ይገባል። ቀስ በቀስ ፋይዳዎች እየታዩና እየተገመገሙ ከሀገር ጥቅም አንፃር ወደ መስመር መግባት ያስፈልጋል።
ፕራይቬታይዜሽን በአንድ ቅፅበት የሚከናወን ባለመሆኑም ከዓለም ነበራዊ ሁኔታዎች ጋር በማነፃፀርና በማገናዘብ በጥንቃቄ መራመድ ይገባል። መንግስትም የሁኔታዎችን ሚዛን የሚጠበቅበት ህግ ማውጣት አለበት። ከሁሉም ቀድሞ ህግ መርቀቅ አለበት። ይህ ካልሆነ በውጭ ሀገራትና ካምፓኒዎች ስር መውደቅ ይመጣል።
በአሁኑ ወቅት ፕራይቬታይዜሽን አስገድዶ እየገባብን ነው። ከ10 ዓመት በፊት ቢጀመር ኖሮ ይህ አይከሰትም። አሁን ወደዚህ መግባታችን ወደን ሳይሆን ተገደን ነው። አሁን ያሉትን ችግሮች እንደሁኔታው እየተረዳን የተወሰኑ ዓመታት መቀጠል አለበት ቢባል ደግሞ የፖለቲካ መናጋት ሊያመጣ ይችላል። የአሴት ግምገማ እና ስቴክ ማርከትም መሰራት አለበት።
አዲስ ዘመን፡–የአሴት ግምገማ እና ስቴክ ገበያም ምን ማለት ነው?
ዶክተር ዳዊት፡– የአንድ ድርጅት የሚለካው ባለው ንብረት ብቻ ሳይሆን ባለው አሴት ጭምር ነው። ድርጅቱ ከመሸጡ በፊት እያንዳንዱ እሴት ተቆጥሮ ወደ ገንዘብ መቀየር አለበት። ንብረትና ገንዘብ ብቻ ሳይሆን የድርጅት መልካም ሥም ትልቅ ድርሻ አለው። ይህ ካልሆነ የሚሸጠው ድርጅት ከገበያ ዋጋ በታች ወይንም በላይ ሊተመን ይችላል። በዚህ ውስጥ ደግሞ ድርጅቶች የተሸጡ ቢሆኑ እንኳን ሼር እና ቦንድ የሚሸጥበት ገበያም መፈጠር አለበት።
አዲስ ዘመን፡– ኢትዮ–ቴሌኮምን ጨምሮ ፕራይቬታይዝ የሚደረጉት በሀገር ውስጥ ባለሃብት መመራት አለባቸው የሚሉ አካላት አሉ። እርስዎ ምን ይላሉ?
ዶክተር ዳዊት፡– ሀገር ውስጥ ባለሃብት መግዛት አለበት መባሉ ክፋት የለውም። ግን ለምን ፕራይቬታዜሽን አስፈላጊ ብሎ መጠየቅ ይገባል። ወደዚህ መስመር ስንገባ አንዱ ነገር የውጭ ምንዛሪ እጥረት ነው። የሀገር ውስጥ ባለሃብት እነዚህን ሜጋ ድርጅቶች የሚገዛበት ዶላር የለውም። ቢኖረውም ሀገር ውስጥ የተፈጠረ ባለሃብት እዚህ ደረጃ አልደረሱም። እነዚህ ድርጅቶችን መግዛት ብዙ እውቀትና ክህሎት የሚጠይቅ ሲሆን ለዚህ ዓለም አቀፍ ድርጅት ያስፈልጋል። ይሁንና ነገሮችን በሀገር ውስጥ ዕድል መጠቀም ይቻላል ወይ የሚሉትን አማራጮች ሁሉ ማየትና መገምገም አስፈላጊ ነው።
አዲስ ዘመን፡– የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል የሚል ሃሳብ አለ። እርስዎ ምን ይላሉ?
ዶክተር ዳዊት፡– የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች እጅ ቢገባም የተወሰነ ለውጥ እንጂ ማክሮ ኢኮኖሚውን እድገት በሚገባው ደረጃ በማስኬድና የንግድ ሚዛን በመጠበቅ ለውጥ ያመጣሉ፤ ግን በጣም ጥቂት ነው። የኢትዮጵያ ትልቁ ችግር የንግድ ሚዛን አለመጣጣም ነው። ስለዚህ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ይህን ችግር በቀላሉ ሊፈቱ አይችሉም። ነገር ግን በውጭ ሀገር ያሉ ኢትዮጵውያንና ትውልደ ኢትዮጵውያን በዚህ ዕድል እንዲጠቀሙ ማድረግ ይቻላል። ይህ የሀገር ሉዓላዊነትን ለመጠበቅና ጥቅም ለማስከበር የተሻለ ፋይዳ አለው ተብሎ ይታመናል።
አዲስ ዘመን፡– ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚፈጠረው ኢኮኖሚያዊ ትስስር እና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ዕድል ቢሰጣቸው ሁኔታዎች አይረጋጋም?
ዶክተር ዳዊት፡– ቀጣናዊ ውህደት አልተፈጠረም። ኢትዮጵያን ጨምሮ ጎረቤት ሀገራት የሚገበያዩት በዶላር ወይንም በውጭ ምንዛሪ ነው። በዚህም እነዚህ ሀገራት የተፈለገው ምንዛሪ በማምጣት የሚኖራቸው ሚና የጎላ አይደለም።
የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንት ከመጠን በላይም እንዳይሆን መጠንቀቅ ይገባል። ባለሃብቶች ትርፍ ብቻ በሚያጋብሱበት ላይ እንዳያተኩሩም መሠራት ያስፈልጋል። በሌላ በኩል እነዚህ አካላት እድሉ ቢሰጣቸው ኢትዮጵያ ፕራይቬታይዝ እያደረገች ባለው ሁኔታ ላይ የመሳተፍና ማስተዳደር አቅማቸው ያን ያክል አይደለም። ለምሳሌ ቴሌኮም በመሳሰሉት ላይ በከፍተኛ ደረጃ ኢንቨስት ለማድረግ አቅም የላቸውም። መሰል ኢንቨስትመንት በባህሪው ብዙ ኢንቨስት ተደርጎ በሂደት ጥቅሙ የሚገኝ ነው። ይህን ደግሞ የእኛ ሀገር ድርጅቶች አልተለማመዱትም። በሌላ ጎኑ የማስተዳደርና የሰው ኃይልንም በሚገባ በማሰማራት በኩል ያን ያክል ስኬታማ ናቸው ማለት አይቻልም።
አዲስ ዘመን፡– ፕራይቬታይዜሽንን በጥሩ ተሞክሮ የሄዱበት እና ወደ ተሻለ ደረጃ ያደጉ ተምሳሌት የሆኑ ሀገራት አሉ?
ዶክተር ዳዊት፡– አንዷ ሀገር ህንድ ናት። 1980ዎቹ መሰል ችግር ገጥሟቸው ነበር። የሀገሪቱ መሪ በወቅቱ የፋይናንስ እና የኢኮኖሚውን አካሄድ ያውቅ ነበር። በዚህ ጊዜ ሦስት ፖሊስ አወጣ። እነዚህም ግሎባላይዜሽን፣ ፕራይቬታይዜሽን እና ሊበራላይዜሽን በአንድ ወቅት ይፋ አደረገ። በዚህ የተነሳ የህንድ ኢኮኖሚ በአንዴ ወደ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ደረሰ። በአሁኑ ወቅት ህንድ የሀገር ውስጥ ብዙ ቢሊየነሮች አሏት። በፎርቢስ መጽሄትም በዓለም ላይ ቱጃሮች ከሚበዙባቸው ቀዳሚዎቹ ህንዳውያን እና ቻይና ባለሃብቶች ነው።
አርጀንቲናም በተመሳሳይ መንገድ አልፋለች። ችግር ውስጥ ገብተው በቀላሉ አልፈዋል። ነገር ግን የእነርሱ ይህን መሻገር ከፕራይቬታዜሽን የዘለለ ነው። ሊበራላይዜሽን አብረው ነው የቀመሩት። ግሎባላይዜሽንም ሌላው ጉዳይ ነው። የውጭ ካምፓኒዎችን በማስገባት በማገዝና የሀገር ውስጥን በማበረታታትም አብሮ ማስኬድ ነው። በአሁኑ ወቅት ግሎባላይዜሽን ሳይኖር ሊበራላዜሽንና ፕራይቬታዜሽን ሊኖር አይችልም። ሦስቱን አብረው አቻችለው በመሄዳቸው ተጠቃሚ ሆነዋል። ነገር ግን በእነዚህ ሀገራት የተፈጠረ ችግርም አለ። የድሃ ድሃ እና እጅግ የናጠጡ ሃብታሞችም እንዲፈጠሩ አድርጓል።
አዲስ ዘመን፡– በኢኮኖሚ ሪፎርም መጥፎ ታሪክ ያላቸው ሀገራትስ አሉ?
ዶክተር ዳዊት፡– ከምስራቅ ኤዥያ በተለይም ባንኮክ ማየት ይቻላል። መቶ በመቶ ወደ ከተማ ተለውጣለች። በወቅቱ ከገጠማት ትልቅ ችግር መውጣት ችላለች። ነገር ግን ደግሞ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች መስራት የሚገባቸውን ሙሉ በሙሉ በውጭ ባለሃብቶች ተይዟል። ስለዚህ መንግስትና ህዝቧ በብዙ ካምፓኒዎች ፍላጎትና ቁጥጥር ሥር ወድቀዋል። በዚህም በሳይኮሎጂ ድሃ ሆነው በመሰረት ልማት ወይም ቴክኖሎጂ ሃብታም የሆኑ ናቸው። ጎረቤት ሀገር ኬኒያም ተመሳሳይ ሁኔታ ይስተዋላል። በትንሹ ከፍታ ብዙ ድርጅቶች የገቡባት ናት። ዜጎች ላይም የሳይኮሎጂ ጫና እያደረገ ነው። በዝምባብዌ በቀኝ ግዛት ወቅት የተጀመረ ቢሆንም አሁን ከዚያ አሰራር እየወጡ ነው። በዚህም ሃብት በጥቁር ዜጎች እጅ እንዲሆን አድርጋለች። ይሁንና ይህ ከፍተኛ ውግዘት አስከትሎባታል። መንግስታቸው ከባድ ውሳኔ ወስኖ ኢኮኖሚው ወደ ሀገር ውስጥ ባለሃብት እየተመለሰ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ምዕራባውያን በሚደረጉ ፖሊሲዎች ላይ በፍጥነት ጣልቃ መግባት የሚፈልጉት ለምንድን ነው?
ዶክተር ዳዊት፡– እነርሱ ደስተኛ የሚሆኑት በፖሊሲ ሪፎርም ነው። ከባለፈው መንግስት ጋር የነበረው ጭቅጭቅም የእኛ ካምፓኒ ይግቡ እያሉ ነው። እነዚህ ህልሞቻቸውን ለማሳካት ብዙ ይሠራሉ። የሚፈልጉት ፖሊሲ ከመጣ በጣም ደስተኛ ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥም የለውጡ መንግስትም ሲመጣ ከፍተኛ ገንዘብ የለቀቁት የፖሊሲ ሪፎርም ይደርጋል በሚል ትልቅ ተስፋ አድርገውና ትርፋቸውን በሰፊው አስልተው ነበር። የእነርሱ ድርጅቶች በየትኛው ሀገር ውስጥ ገብቶ በእጅ አዙር መጠምዘዝ እና ፍላጎታቸውን ማስከበር እንዳለበት ያምናሉ። ለእነርሱ የሚመቸውን ከማድረግ ወደ ኋላ አይሉም። በበርካታ ሀገራትም ሪፎርም ይደረግ ብለው የሚወተውቱት በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ስለሚያግዛቸው ነው። ይህ የማይሆን ከሆነ ደግሞ በተለያዩ መንገዶች ጫና ለማሳደር ይፈልጋሉ።
አዲስ ዘመን፡– ኢኮኖሚውን ሙሉ ለሙሉ ሊበራል ማድረግና ፕራይቬታይዜሽን በሰፊው መፍቀድ ለሀገር ሉዓላዊነት ሥጋት አይፈጥርም?
ዶክተር ዳዊት፡– በጣም ይፈጥራል፤ እየፈጠረም ነው። እጃቸው ረጅም ነው። አካሄዳቸው ሉዓላዊነት ላይም ጥያቄ ያስነሳል። የሚደረገው ሪፎርም የቅርብ ችግርን ከመሻገር አኳያ ትክክለኛ ውሳኔ ነው። በረጅም ጊዜ አኳያ ግን አደጋ አለው። በገዛ ሀገርህ ከዜጋ በላይ ዜጋ ይሆናሉ። እነሱ ቀጣሪ፣ ነባሩን ዜጋ ተቀጣሪ ያደርጋሉ። በሌላ ሀገር ፈላጭ ቆራጮች ይሆናሉ። በሂደት ደግሞ ሁሉንም ነገር የመቆጣጠር ዕድል ይሰጣቸዋል። ስለዚህ ለአጭር ጊዜ ችግር ተብሎ የረጅም ጊዜ ዕድል ፋንታ የመሸጥ ጉዳይ መሆኑም መታወቅ አለበት። በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያ እነዚህን ነገሮች በማመዛዘንና የረጅም ጊዜ ጥቅሟን አስልታ መሄድ ይጠበቅባታል።
አዲስ ዘመን፡– ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቆይታ ለሰጡን ሙያዊ ሃሳብ እናመስግናለን።
ዶክተር ዳዊት፡– እኔም እንግዳ ስላደረጋችሁኝ እና ሃሳቤን ስላካፈልኩ አመሰግናለሁ።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ሐምሌ 2/2013