ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አቶ በፍርዴ ጥላሁን ይባላሉ። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በህግ ትምህርት ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ተመርቀዋል። ከዚያም በተለያዩ አካባቢዎች ተመድበው ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል። በተለይም ደግሞ ግጭቶች ሲከሰቱ በነበሩባቸው አካባቢዎች ሁኔታዎችን ተመልክተው በህግ ዓይን እልባት እንዲያገኙ ሠርተዋል። በኦሮሚያ ክልል ቡኖ በደሌ ዞን ቦርቻ ወረዳ አቃቤ ህግ፣ በኦሮሚያ ክልል ቡኖ በደሌ ዞን ደዴሳ ወረዳ አቃቤ ህግ፣ ፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የቡራዩ ከተማ ወረዳ አቃቤ ህግ፣ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ቶሌ ወረዳ አቃቤ ህግ፣ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን የቀርሳ ማሊማ ወረዳ አቃቤ ህግ ሆነው ሙያዊ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ጠበቃ ሆነው በመሥራት ላይ ናቸው።
በዛሬው እትማችን በተለያዩ ወቅቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ይስተዋሉ የነበሩ ግጭቶችና፣ አሁናዊ ሁኔታ፣ የግጭቶች መሰረታዊ መነሻ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ ወይስ ኢኮኖሚያዊ አንድምታዎችና መፍትሄዎች፣ የሁኔታዎችን ከመሰረታዊ የዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር አኳያ ምን መሆን አለበት በሚለው ላይ ሰፊ ትንታኔ ሰጥተዋል። ሀገሪቱ ውስጥ እየሆኑ ባሉ ነገሮች በዓለም አቀፍ ህጎችና መርሆዎች አንፃርም ኢትዮጵያ እየሄደችበት ያለውን መንገድ በመጠቆም ሙያዊ ሃሳብ ሰጥተዋል። ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ሁኔታ መብቷ ለማስከበር የምታደርገው ጥረት ምን መሆን አለበት በሚሉት ላይም በህግ ባለሙያው ሃሳብ ተዳሰዋል። መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- በተለያዩ ወቅቶች በኢትዮ ጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ይስተዋሉ የነበሩ ግጭቶች ባለፉት ሦስት ዓመታት ለምን እየተባባሱ ሄዱ? የግጭቱ ተዋናዮችስ ለምን ተበራከቱ?
አቶ በፍርዴ፡- ይህን ጉዳይ ሰፋ አድርጎ ማየት አስፈላጊ ነው። እኔ እንደሚገባኝ የሀገራችን የሁልጊዜ ችግር ፖለተካ ነው። በአንድ በኩል እኛ በቅኝ ገዥዎች ያልተንበረከክን ያልተበረዘ ማንነታችን ይዘን ያለን ኩሩ ህዝቦችና ነጻ ሀገር ስላለን እንኮራለን። ይህ መልካም ገጽታችን ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ብዙ ክፍለ ዘመናትን ከኛ ጋር የዘለቀ የፖለቲካ ችግር አለ። የፖለቲካ ችግር አለመስተካከል ብዙ ችግሮችን ያስከትላል። ድህነት፣ መሃይምነት፣ ፍትሃዊ የሃብት ተጠቃሚነት ችግር፣ የኢኮኖሚ ጥገኝነት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖ ፈጣሪ ያለመሆን እና የውስብስብ ማህበራዊ ችግሮች ሁሉ ምንጭ ፖለቲካ ነው። የሀገር ሉዓላዊነትና ነጻነት በምንም መልኩ ድርድር ውስጥ አይገባም። ነገር ግን ህዝቦቿዋን ዳቦ መመገብ ያልቻለች ሀገር ሁሌ ፈተና ውስጥ ናት።
ይህ ችግር ነው እንግዲህ ከዓለም ህዝቦች ወደ ኋላ እያስቀረን ያለው። እስቲ እንመልከት የኛ ዜጎች በአሜሪካን ሀገር እንደ ሀገራቸው ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ተጠብቆላቸው ወልደው ከብረው ሃብት አፍርተው በሠላም ይኖራሉ። እኛ ግን በገዛ ሀገራችን አንዱ ለአንዱ ስጋት ሆኖ በሰቀቀን እንኖራለን። አሜሪካ እንደ ሀገር የኛን ያህል ረጅም ታሪክ የላትም። ነገር ግን ዛሬ አሜሪካ የዓለም ፖለቲካ ዘዋሪ ናት። እኛ ግን ዛሬም እንጠላለፋን፤ ዛሬም እንለምናለን። አሜሪካዊያን ከሰው ልጅ የተለዩ ዘሮች አይደሉም።
ከሥልጣኔ አንጻር ቀዳሚ ህዝቦች ነበርን። ዛሬ የአክሱም ሀውልት፣ የፋሲለደስ ቤተመንግስት፤ የላሊበላ ውቅር ዓብያተ ክርስትያናት የጀጎል ግንብ ወዘተ ይታዝቡናል። በዴሞክራሲም ቀዳሚ ነበርን። የገዳ ሥርዓትን የመሰለ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር በእጃችን ይዘን ከምዕራባዊያን ባዕድ ሥርዓት ላይ እንንጠለጠላለን። በሀገራችን የተለመደው መጥፎና የዕድገት ካንሰር የሆነው መጠላለፍ እና ምቀኝነት አለ። የመደናነቅን ባህል ከቶውንም የለንም። አዲስ የሚነሳ መንግስት ያለፈውን እየረገመ፤ እሱ የሰራውን እያጠፋ ደግሞ የራሱን ሰርቶ ሳይጨርስ ሌላው ተነስቶ ያጠፈዋል። እንዲህ በዔሊ ፍጥነት እየገነባን እሱኑ ሳንጨርስ እያፈረሰን 21ኛው ክፍለ ዘመን ገብተናል።
ከታሪክ አንጻር ኢትዮጵያ እንደ ማንኛውም የዓለም ሀገራት ብዙ በጎና መጥፎ ታሪኮች አሏት። መሆን የነበረበት ያለፈውን መልካም ገጽታ ይበልጥ እያጠናከረን፤ መጥፎውን በውይይት እያስተካከለን በይቅርታ መሻገር ሲገባን ያለፈ ትውልድ ሰርቶ ባለፈው ታሪክ አንዳችን አንዳችንን ተጠያቂ እያደረገን ይሄው መጠላለፋችንን በአዲስ መልክ አጠናክረን ቀጥለንበታል። አሁንም ዓለም በፍጥነት ወደ ሥልጣኔ ስትገሰግስ እኛ ደግሞ በፍጥነት በተቃራኒው መጓዛቸን ነው። በሌላ በኩል የዕምነት ተቋማት ጥሩ ሀገር ወዳድና ሞራል ያለው ዜጋን በመፍጠር ለጠንካራ ሀገር ግንባታ የሚያደርጉት አስተዋጽኦ የማይለካ ነው። ነገር ግን አሁን እያየን ያለነው ይህንን አይደለም። የሃይማኖት ተቋማት እንደቀደሞው የሞራል ምንጭ መሆናቸው ያጠራጥኛል።
አዲስ ዘመን፡- መነሻ ምክንያቶቹ ምንድን ናቸው ማለት እንችላለን?
አቶ በፍርዴ፡- በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን በበርካታ ቦታዎች የሚከሰተው ግጭት መፈናቀል ሁለት መነሻ ምክንያቶች አሉት። ውጫዊና ውስጣዊ። ውስጣዊው ያው ከላይ የገለጽኩት የተለመደ የመጠላለፍ ሴራ ነው። የጥቂት ቡድኖችን የኢኮኖሚ ወይም የፖለቲካ ጥቅም ለማስጠበቅ ንጹሃን የሚሞቱባት፣ የሚፈናቀሉባት፣ የሚሰቃዩበት፣ ብዙዎች ዕድሜ ልካቸውን ያፈሩት መተዳደሪያ ንብረትና አለን የሚሉትን ቅሪት በቅጽበት አመድ የሚሆንበት አዲስ ቁማር ነው የተጀመረው። እኔ ግን በጣም የሚገርመኝ በህዝብ ሞትና መፈናቀል የሚያዘው ሥልጣን የሚገኘው ሃብት ምን ያህል ምቾት ይሰጣል?
ትንሽ በትምህርት በዕውቀቱ ገፋ ያላደረገና የፖለቲካ ቁማሩን በቅጡ የማይረዱ የተወሰኑ የወጣቱ ክፍል በቁማርተኞቹ መርዛማ ስብከት ተጠልፎ በራሱ ወገን ላይ ይጨክናል፤ የሀገሩን ንብረት ያቃጥላል። ይህ አካሄድ በየትኛውም መንገድና መመዘኛ አግባብ አይደለም። ‹‹እኔ ከሞትኩ ሳርዶ አይብቀል›› አባዜ መቆም አለበት።
አዲስ ዘመን፡- እነዚህ ውስጣዊ ግጭቶች በተበራከቱ ቁጥር የውጭ ጫናዎችም በዚያው ልክ መበራከታቸው ምን ያሳያል?
አቶ በፍርዴ፡- ከውጭ የሚመጣው መሰል ፈተና በዋናነት በውስጣችን ያለውን መከፋፈል በማየት ነው። ሌላው የህዳሴ ግድባችን ወሳኝ የግንባታ ምዕራፍ ላይ በመድረሱ የኢትዮጵያን መልማት እንደ ብሔራዊ ሥጋታቸው የሚመለከቱና ተባባሪዎቻቸው በሚያደርጉላቸው ድጋፍ ነው። እውነታው ግን ዕድገታችን እንዲቀጭጭ ያደርጉት ይሆናል እንጂ ኢትዮጵያን ማፍረስ ግን አይችሉም። የውስጥ ባንዳዎችም የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ በራሳቸው ጊዜ ይጠፋሉ። ባንዳዎች በእያንዳንዱ የኢትዮጵያ ፈተና ዘመናት አሉ። ከሁኔታዎች በመነሳትም በቀጣይም ሊኖሩ እንደሚችሉ መገመት አይከብድም። ነገር ግን እነርሱ ይጠፋሉ ኢትዮጵያ ትቀጥላለች።
በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ላይ ፈተና የበዛው ከመቼውም ጊዜ በላይ በራሷ የተፈጥሮ ሃብት ለመጠቀም ከጫፍ የደረሰችበት ጊዜ ላይ ስለሆነች ነው። ይህን ህልሟን ካሳካች በፍጥነት ከኃያላን ተርታ እንደምትሰለፍ ስለሚያውቁ ተረባርበው ወደኋላ ሊመልሷት ይፈልጋሉ። ይህ ብቻ አይደለም አንዳንድ ሀገሮች ኢትዮጵያ እስካሁን በታሪክ ነጻነቷን አስከብራ ስለቆየችና ድንበሯን ስላላስደፈረች በዚህ ብቻ የሚመቅኑዋት ይመስለኛል። ይህም በመሆኑ በተቻለ መጠን ችግሮችን በጥንቃቄ መመከት ይገባል። መንግስት አሁን የጀመራቸው ጥረቶች የሚበረታታ እና የሚደገፉ ናቸው። ሆኖም በዓለም አቀፍ ህግና እውቀት የተደራጁ መረጃዎችና ማስረጃዎችን በሚገባ መያዝና እውነታውን ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብና ዲፕሎማቶች ማሳወቁ ብዙ ሊሠራበት ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- የምናስተውላቸው ግጭቶች መሰረታዊ መነሻ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ ወይስ ኢኮኖሚያዊ?
አቶ በፍርዴ፡- በሦስተኛ ዓለም (Third World) ውስጥ ሆነህ ሁሉም ነገር ኋላ ቀር ነው። የሦስተኛው ዓለም ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ሁኔታ የሀገራቱ የዜጎቻቸው ንቃት ላይ የተመሰረተ ነው። ይህ ደግሞ በፖለቲካ ይመራል። ለምሳሌ የአፍሪካ መንግስታት ፖለቲካ የሰለጠነ አይደለም። በአብዛኛው በመጠላለፍ ላይ የተመሰረተ ነው። አብዛኞቹ የአፍሪካ መሪዎች ወይም የፖለቲካ ድርጅቶች ከስልጣን የሚነሱት በህዝቦቻቸው በሚናሳባቸው ነውጥ ወይም እርጅና ተጭኗው አሊያም ደግሞ እስከወዲኛው ሲያሸልቡ ብቻ ነው። ስለዚህ አብዛኛውን የሥልጣን ዘመናቸውን የሚጨርሱት የሥልጣን ወንበራቸውን በመጠበቅና በመንከባከብ ነው። ህዝቦች እንዲማሩና ሀገራቸውን እንዲያለሙ የሚደረገው ጥረት እምብዛም ነው።
የአንድ ሀገር ዜጎች በዘመናዊ ትምህርት አለመበልጸግ ከውስብስብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ችግሮች እንዳይወጣ ያደርጋል። ወደ ሀገራችን ሁኔታ ስንመጣ በሀገር ወይም በንጹሃን ዜጎች ኪሳራ ለፖለቲካ ትርፍ የሚሰሩ የሀገር ጠላቶችና የደም ነጋዴዎች ቀን ከሌሊት ይሰራሉ።
ነገር ግን ስለሀገርና ፖለቲካ እምብዛም ለይተው የማያውቅ ዜጎች ሀሳባቸውን በመግዛት ለዘርፈ ብዙ ግጭቶች ምክንያት ይሆናሉ። ይገላሉ፤ ይሞታሉም። እኔ የሚገርመኝ ሰው ምን ዓይነት የዕውቀት ደረጃ ላይ ሆኖ ነው ለነዚህ ነጋዴዎች መሣሪያ ሆኖ እናት ሀገሩን የሚወጋት? ሌላ ሀገር አለው ወይ? ዋናው ነገር የሚሸጥ ነገር ያለው ሰው የሚገዛው ሰው ከሌለ እቃውን ይዞ ገበያ አይሄድም፤ ብሄድም ተሸክሞ ይመለሳል። ሰው ለኑሮው የሚጠቅመውን እቃ ብቻ እንደሚገዛ ሁሉ ሀገሩን የሚያፈርስ ሳይሆን ሀገሩን የሚገነባ ሀሳብ ብቻ መግዛት አለበት። እንደዚህ ቢሆን ኖሮ የት በደረሰን ነበር። ይህን አመለካከት የቀረጸው ባለፉት 30 ዓመታት የነበረ የፖለቲካ ቁማር ነው። የፖለቲካ ቁማሩ ደግሞ በመርዝ የተለወሰ የትምህርት ፖሊሲ ተጠቅሟል።
በእርግጥ ችግሮቻችንን በሚገባ እየተረዳን ይመስለኛል። ብዙ ዋጋ ከፍለንበታል፤ አሁንም እየከፈልንበት ይገኛል። መራመድ ከሚገባን እርምጃ በእጅጉ ወደ ኋላ ጎትቶናል። ይህ ሁሉ ፈተና ኢትዮጵያን የበለጠ እንዲያጠነክራት መሥራት ይጠበቅብናል። ለዚህ ሁሉ መፍትሔው መማር፣ መስራት፣ እንደ ሀገር ማሰብ፣ ፖለቲካውን ማስተካከል አንድነት ላይ መስራት ነው። በህግ ዓይን የሚታዩትንና በአግባቡ መዳኘት የሚገባቸውን ደግሞ በሚዛኑ ላይ ለፍርድ ማስቀመጥ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- በእነዚህ ግጭቶች የተነሳ በየጊዜው የሚወድመው ንብረት በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የሚኖረው አሉታዊ ተጽዕኖ በረጅም ጊዜ እና በአጭር ጊዜ ምን ሊሆን ይችላል?
አቶ በፍርዴ፡- ከኢኮኖሚ አንፃር የሚያመ ጣውን ተጽእኖ ለመገመት ኢኮኖሚስት መሆን አያስፈልግም። በአንድ አካባቢ ላይ የሚወድመው ንብረት ሶስት ጉዳቶችን ያስከትላል። የሚወድመው ንብረት ካለ ሃብት ቀንሰን የተገነባ ነው። መልሶ ለመገንባት ሌላ ሃብት ያስፈልጋል፤ ሌላ ልማት ማልማት ስንችል የተሰራውን አፍርሰን ስንሰራ ከባድ የኢኮኖሚ ጠባሳ ጥሎ ያልፋል።
ከአጭር ጊዜ አንጻር የሚያስከትለው ጉዳት ብዙ ሰራተኞች ከሥራ ገበታቸው ይፈናቀላሉ። እነዚህ ሰዎች ብዙ የሚያስተዳድሩት ቤተሰብ አላቸው፤ ስለዚህ ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን ስነልቦናዊ ችግርም ይደረስባቸዋል። ሌላ ሥራ ለማገኘትም ይቸገራሉ። ከረጅም ጊዜ አንጻር ደግሞ በግጭት ምክንያት ንብረቶች የወደሙባቸው አካባቢዎች ኢንቨስትመንት እንዳይስፋፋ ብቻ ሳይሆን የነበረውንም የሚያወድም ይሆናል። አዳዲስ ኢንቨስተሮች እንዳይመጡ ያደርጋል። ይህ በአንድ ላይ ተደምሮ ሀገሪቷን እጅግ በጣም ይጎዳታል ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- በህግ ዓይን ሲታይ ለዚህ ሁሉ ጥፋት ተጠያቂ የሚሆነው አካል ማነው?
አቶ በፍርዴ፡- ለዚህ ችግር ተጠያቂ አንድ አካል ብቻ ነው ለማለት ይከብዳል። ለችግሩ መከሰት ብዙ አካላት ምክንያት እንደሆኑ ሁሉ ለመፍትሔውም እንደዛው ነው። ህገወጥ አስተሳሳብና ትርክት የሚነዙ ሚዲያዎች፣ የፖለቲካ ነጋዴዎች፣ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ አንዳንድ ግለሰቦች እና አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች ቢያንስ ከህሊና ከተጠያቂነት አያመልጡም።
በሌላ ጎኑ ደግሞ ስናያው ላለፉት ሰላሳ ዓመታት የመጣንበት የፖለቲካ ትርክት እና ትርክቱን በዋናነት የልዩነት ምንጭች አድርገው ሲመሩ የነበሩ አካላት ትልቅ ሚና ነበራቸው። በዚህ የመሪነት ሚና ውስጥ የሀገር አንድነትን አደጋ ላይ የሚጥል፤ ጥርጣሬን በሰፊው የሚያጭርና ለኢትዮጵያ ህልውና አደጋ እንዲሆን የተሠራ ነው። ይህም ከህግም ከሞራል ተጠያቂነት የሚያመልጥ አይሆንም።
አዲስ ዘመን፡- እየተፈፀመ ያለው ግድያ ከሽብርተኝነት፣ ሰብዓዊ መብት ጥሰት እና ከመሰረታዊ የዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር አኳያ በዓለም አቀፍ መርሆዎች አንፃር እንዴት ይመዘናል?
አቶ በፍርዴ፡- እኔ በእነዚሀ ድርጊቶች ያልተጣሰ ህግ አለ ብዬ አላስብም። ከሁሉም በላይ የህሊና ህግ ተጥሷል። የአንድ ሰው ገዥው ህሊናው ነው። ህሊናው ያልገዛው ሰው ከእንስሳት አኗኗር የተለየ ኑሮ አይኖርም። እንደዚህ ዓይነት ብዙ ግለሰቦች ደግሞ ማህበረሰብን ይፈጥራሉ፤ ኪሣራውም በዚያው ልክ ከፍ ይላል ማለት ነው። አሁን ባለው የሀገራችን ህገ መንግስት ዓለም አቀፍ ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶች ተካቷል። ነገር ግን በተደጋጋሚ ሲጣሱ ቆይቷል። መንግስት የዜጎችን ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን የማክበርና የማስከበር ግዴታ አለበት። ሆኖም የዜጎች ትብብር ካልታከለበት መንግስት ብቻውን አይወጣውም።
አዲስ ዘመን፡- በየጊዜው በሚስተዋሉ ግጭቶች የህገመንግስቱ የትኞቹ አንቀፆችና መብቶች ተሸራርፈዋል ብለው ያስባሉ?
አቶ በፍርዴ፡- የሰው ልጆች መብት ትርጉሙና ይዘቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ በትርጉሙና በይዘቱ እየተሻሻለ የሚሄድ ነው። ለምሳሌ ሰብዓዊ መብትና ዲሞክራሲያዊ መብት ተብሎ ሊከፈል ይችላል። ሰብዓዊ መብት ማለት ማንም የማይሰጥህ ማንም የማይወስድብህ ሰው በመሆንህ ብቻ በተፈጥሮ የተጎናፀፍካቸው ዩኒቨርሳል ወይም በየትኛውም የዓለማችን ጫፍ ተመሳሳይ የሆኑ በየማይቀነሱና የማይጨመሩ ናቸው። ለምሳሌ በህይወት የመኖር፤ የአካል ደህነትና የነጻነት መብት፤ ሀሳብን የመግለጽ ነጻነት መብቶችን መጥቀስ ይቻላል።
ዲሞክራሲያዊ መብቶች ደግሞ በፖለቲካ የመሳተፍ መብት ማለትም የመምረጥና የመመረጥ መብት፤ ህግ ስወጣ የመሳተፍ የመሣሳሉትን ያካትታል። እነዚህ መብቶች አንድ እንድ ጊዜ Civil Rights and Political Rights ተብለው ይጠራሉ። (በሌላ በኩል ደግሞ First Generation Rights, Second Generation Rights, Third Generation Rights እና Fourh Generation Rights) ተብለውም ይጠራሉ።
እነዚህ መብቶች ከሞላ ጎደል በህገ መንግስታችን ውስጥ ተካተዋልል። ይህ አንቀጽ ያኛው አንቀጽ ተጥሷል ብሎ መዘርዘሩ ብዙም አይጠቅምም። በፖለቲካ ለውጥ ላይ ያለች ሀገር ውስጥ ብዙ ችግር ይፈጠራል፤ ተፈጥሯልም። ፖለቲካው ባልተረጋጋበት ሁኔታ ውስጥ ብዙ የህግ ጥሰቶች እንደሚከሰቱ ቢጠበቅም ሰብዓዊ መብቶች ግን የትም ሆነ በምንም ሁኔታ ውስጥ መጣስ የለባቸውም።
አዲስ ዘመን፡- ለእነዚህ የመብት ጥሰቶች ማካካሻው ምን ሊሆን ይችላል?
አቶ በፍርዴ፡- በመሰረታዊነት መግባባት የሚያስፈልገው የሰው ልጆች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን የሚያስከትሉ ችግሮች ከመነሻውን ለማጥፋት አለያም ደግሞ መቀነስ ነው። በተቻለ መጠን ደግሞ ሁኔታዎችን ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መፍትሄ ለማምጣት መሥራት ነው። በተለይ ደግሞ በየትኛው የዓለም ጥግ ለድርድር የማይቀርበውን የሰው ልጆች የሰብዓዊ መብቶች እንዳሸራረፉ መትጋት ይፈልጋል። እነዚህ ሁሉ ለማክበርና ለማስከበር ጥረት ተደርጎ በተለያዩ ምክንያችና ከአቅም በላይ በሆኑ አሰራሮች ወይንም የፖለቲካ ውጥንቅጦች ያልተሳካ እንደሆነ ግን ለመብት ጥሰቶች እንደየሁኔታዎች ማካካሻ ይፈልጋል። ማካካሻው የዜጎችን መሰረታዊ መብቶች ጠብቆ ማስጠበቅና የተጎዱ ካሉ ደግሞ ወደ ነበሩበት ሁኔታ እንዲመለሱ ማድረግ ነው። ከዚህም በተጨማሪ በህገ መንግስቱ መመለስ እና መስተካከል ያለባቸው ሁኔታዎች ካሉ ደጋግሞ ማጤን ይፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ህገመንግስቱ ቢሻሻል ሊስተካከሉ የሚችሉ ችግሮች ይኖራሉ ብለው ያስባሉ፣ ከሆነስ አሁን ጊዜው ነው?
አቶ በፍርዴ፡- የሀገራችን ህገ መንግስት መሻሻሉ የማይቀር ነው። ለምሳሌ የክልሎች ቁጥር እየጨመረ ነው። ቢያንስ አሁን ባለው ሁኔታ የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ይሁንታ አግኝቶ የተደራጀ ነው። ይህ በራሱ አንድ ምክንያት ነው። ሌሎች ጉዳዮችም ይኖራሉ። ህገመንግስቱ እንዴት መሻሻል እንደሚችል በራሱ በህገ መንግስቱ ተቀምጧል። የመሻሻሉ ጊዜ ግን አሁን አይደለም። መጀመሪያ ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ተደርጎ በህዝብ የተመረጠ መንግስት ህገመንግስቱ በሚፈቅደው መንገድ ህዝቡን አወያይቶ ማሻሻል እንዳለበት አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ለማከናወን እና የህወሓት ደብዛ ለማጥፋት ዘመቻ በተጀመረበት በዚህ ወሳኝ ወቅት የግጭቶችና መፈራገጥ መስተዋላቸው ምን ያመለክታል?
አቶ በፍርዴ፡- ሁለተኛው የህዳሴ ግድባችን ሙሌት በተሳካ ሁኔታ እንዲሞላ ከተፈለገ ኢትዮጵያን ሀገሬ ብሎ የሚያምን ሁሉ በጋራ መቆም አለበት። ይህ ትውልድ ዕድለኛ ነው። ከዓድዋ በላይ ነው ድሉ፤ የህዳሴ ግድባችን እንዳይሞላ ለማደናቀፍ የሚሰራ የውጭም ሆነ የውስጥ ባንዳ የ 110 ሚሊዬን የኢትዮጵያ ህዝብ የመኖርና ያለመኖር እጣ ፋንታ ላይ እንደ መወሰን ነው።
እባቡ ያው ጭንቅላቱ ተመቶ ሞቷል የሚያስብል ሁኔታ ላይ ቢሆንም ነፍሱ አልወጣችም። ስለዚህ ጭንቅላቱ የተመታ እባብ መሞቱ አይቀርም ግን ዝም ብሎ አይሞትም። የእባቡ መንፈራገጥ ብቻ ሳይሆን እባቡን በማከም አፈር ልሶ እንዲነሳ የሚያደርጉ ዘንዶዎችን በትኩረት መከታተል በጣም አስፈላጊ ነው። በዚህም የህወሓትን መመለስ የሚናፍቁና የኢትዮጵያን ዕድገት የሚቃሙት በጣም የሚታትሩበት ወቅት ነው። በተቻለቸው መጠን ሁሉ ዘግናኝ ድርጊቶች በመፈፀም ሥም የማጠልሸት ሥራ መሥራታቸው አይቀሬ ነው። ይህን ከግንዛቤ በማስገባት ሁላችንም እንደ ሀገር ማሰብና መቆም ይጠበቅብናል። ግድቡን ልንሞላ እየተዘጋጀን ይቅርና ዱሮም አይተኙልንም። እንዳናድግና እርስ በእርስ እንድንቆራቆዝ ሲያደርጉ ኖረዋል። ካደግን በቀጣናው ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገር ስለምንሆን፤ እኛ ስናድግ የፖለቲካ ጥቅሞቻችን ይነኩብናል ብለው ስለሚያስቡ ጭምርም ጫናዎች እንደሚበረቱ ማወቅ ይገባል። ይህን ሴራ በመረዳት መሥራትና ለሚመጣው ሁሉ መዘጋጀት ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ለሚስተዋሉ አጠቃላይ ሀገራዊ ችግሮች መፍትሄ ምንድን ነው?
አቶ በፍርዴ፡- ባለፈ ታሪክ መስማማት ባይቻል ታሪክን ለራሱ ለታሪክ በመተው ሊታረም የሚችለውን በማረም ካለፈው በጎ በጎውን በመውሰድ በጎ በጎውን ጨምረንበት እጅ ለእጅ ተያይዘን ወደፊት መጓዝ ይገባል። ለማንኛውም የኢትዮጵያ ችግር መፍትሔ የሚገኘው እኛ በኢትዮጵያውያን ብቻ መሆናችንን ማመን አለብን። ብሔራዊ መግባባት አድርገን በእኩልነት ተባብረን ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ ይጠበቅብናል። ይህ ደግሞ ከሁሉም ዜጎች ይጠበቃል።
ሌላው ያለምንም ቅድመ ሁኔታና ድርድር የህግ የበላይነት መከበር መቻል አለበት። ለዚህ ደግሞ መንግስትም ህዝብም መተባበር አለብን። የኑሮ ውድነትን የሚያባብሱ ችግሮችን ለይቶ ማስተካከያ ማድረግ ይገባል። የህዳሴ ግድቡን በተሻለ ፍጥነት አጠናቆ የጠላት ወጥመዶችን መበጣጠስም የወቅቱ መሰረታዊ ጉዳይ ነው። የውጭ ዲፕሎማሲ ረገድም ሰፊ ሥራ ስለሚጠይቀን በዚህ ላይ በትኩረት መስራት አለበት። በእነዚህ ነገሮች ላይ በደንብ ከተሰራ ከብዙ ችግሮች እንወጣለን። ካልሆነ እራሳቸው ስጋት ሆነው ሊቀጥሉ እንደሚችሉ መገመት ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ሙያዊ ሃሳብዎትን ስላከፈ ሉን በዝግጅት ክፍላችን ሥም አመሰግናለሁ።
አቶ በፍርዴ፡- እኔም አመሰግናለሁ። የሰው ልጆች ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲዊ መብቶች እንዲከበሩ ደግሞ ጠንክረን መስራት ይጠበቅብናል። ሁላችንም በአንድነት ቆመን ኢትዮጵያን ማሣደግ አለብን።
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 28/2013 ዓ.ም
ፎቶ-በሐዱሽ አብርሃ