የኢትዮጵያን ቱባ ባህልና ወግ የሚያንፀባርቁ፣ በውብ አገርኛ ቃላት በተከሸኑ “ጉንጉንና የወዲያነሽ” በተሰኙ ዘመን ተሻጋሪ መጽሃፋቸው ይታወቃሉ። ትውልዳቸው ከሰሜን ሸዋ ማጀቴ በምትባል አካባቢ ነው። ከ33 ዓመት በላይ ከፍተኛ ክብር በሚሰጠው የመምህርነት ሙያ አገልግለዋል። ማስተማርን ብሎም “መምህር” የሚለውን መጠሪያ እጅግ አድርገው ይወዱታል።
በተማሪዎቻቸውና በድርሰቶቻቸው ብቻ ሳይገደቡ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍለ ሀገሮች እየተዘዋወሩ የማንበብን ጠቀሜታ አስተምረዋል። ከሰሞኑ በአርትስ የቴሌቪዥን መስኮት “እረኛዬ” በሚል ተከታታይ ድራማ በትወናው ብቅ ብለው በአዲስ መልክ ከጥበብ አፍቃሪው ጋር ተገናኝተዋል። ይህ ስራቸው በበርካቶች ተወዶላቸዋል። የዛሬው የአዲስ ዘመን “የዝነኞች የእረፍት ውሎ እንግዳችን” መምህርና ደራሲ ኃይለመለኮት መዋእል!
“እረኛዬ”ና ጋሼ ኃይለመለኮት
ምንም እንኳን በጥበቡ ዓለም በድርሰቱና ማንበብ ባህል እንዲሆን በሚያደርጉት ጥረት ይታወቁ እንጂ አንጋፋው መምህር ለኢትዮጵያ የሲኒማ ኢንዱስትሪ እንግዳ ናቸው። አንድ እለት ግን ይህን እውነታ ቀይራ በቅርቡ “እረኛዬ” በሚል ተከታታይ ድራማ ላይ እንድናያቸው ምክንያት ሆናለች። ለመሆኑ በዚህ ፍጥነት የተመልካች ቀልብን የሳበው ድራማ ላይ እንዴት ሊሳተፉ ቻሉ?
የእረኛዬ ተከታታይ ድራማ ደራሲዎች አዜብ ወርቁ፣ ቅድስት ይልማና ቤዛ ሃይሉ ናቸው። በአጋጣሚ ጋሼ ኃይለመለኮት ጋር ከአንደኛዋ ደራሲ አዜብ ወርቁ ጋር ይቀራረባሉ። ድራማው ላይ የአባትነት ሚናን እንዲወክሉ ለዚህም በመምህርነት ከ33 ዓመታት በላይ ማስተማራቸውና እድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ መሆኑና የአካባቢውን ባህልና ወግ ጠንቅቀው በማወቃቸው ገጸባህሪውን ወክለው ለመጫወት ትክክለኛ ተመራጭ መሆናቸውን ትነግራቸዋለች። ይሁን እንጂ ለሲኒማው ዓለም አዲስ
በመሆናቸው ጥያቄውን ለመቀበል ተቸግረው ነበር። የእሷ ጉትጎታና ማሳመን ታክሎበት ግን በድራማው በመጨረሻ ተሳተፉ።
ቆይታ ከተዋንያኑ ጋር“አብሬያቸው የሰራኋቸው እውቅ ተዋንያን የሚደንቅ ችሎታ አላቸው” የሚሉት መምህሩና ደራሲው ኃይለመለኮት ድራማው የፊልም ስራ አድካሚ መሆኑን የተገነዘቡበት እንደሆነ ይናገራሉ። ታሪክ ቀመስ የአገር ውስጥ እና የውጭ ፊልሞችን የማየት ልምድ ቢኖራቸውም ምን ያህል እንደሚደከምበት ያዩት ግን በ” እረኛዬ” ፊልም ላይ በነበራቸው ተሳትፎ ነው። የእርሳቸው ገጸባህሪ በመጀመሪያ ክፍል ላይ ያበቃ ሲሆን ወደፊት ምን እንደሚፈጠር እንደማያውቁ ይናገራሉ። ሆኖም “የእኔ ተሳትፎ ትንሽ ነው። ለዚህ ክብር ያበቁኝ እነሱ ናቸው ሊመሰገኑ ይገባል” በማለት ይገልጻሉ። ወደፊት በዚህ ፊልም ላይ የሚኖራቸውን ተሳትፎ አሁን ላይ ሆነው ለመገመት እንደሚቸገሩ ገልጸዋል።
ጋሼ ኃይለመለኮት ደራሲዎቹም ሆነ ፊልሙን የሰሩት በአጠቃላይ በጥናት ላይ ተመስርተው እንደሰሩት ይናገራሉ። በተለይ ድርሰቱ ህብረተሰቡን ጠንቅቆ ያወቀ፣ ሊያስተምር፣ ሊያርምና ቱባውን ባህል ሊያሳይ እንደሚችል ታልሞና ታቅዶ የተሰራበት እንደሆነ ይመሰክራሉ። የመረጡት የትእይንት ቦታም እንዲሁ ሳቢና ትክክለኛ መሆኑን ይገልፃሉ። በአጠቃላይ ጭብጡ፣ የተመረጠው አካባቢና ተፈጥሯዊ መልክአ ምድሩ ተገቢነት ያለው መሆኑን በአንድ ቃል ሲገልጹት “በጣም ረክቻለሁ” በማለት ይደመድማሉ።
ተሰጦ፣ ችሎታና ልምድ በሚያስፈልገው የፊልም ስራ ላይ በነጮቹ አባባል “ያረጀ ውሻን አዲስ ስልት አታስተምርም” ስለሚባል እኔም በትወናው ዓለም ላይ ድጋሚ አልመለስም የሚሉት ጋሼ ኃይለመለኮት በሌሎች የሲኒማ ስራዎች ላይ መሳተፍ እንደማይፈልጉ በጨዋታና በቀልድ እያዋዙ ለዝግጅት ክፍላችን ገልጸውልናል። በእረኛዬ ላይ ያላቸው ተሳትፎም “ለስሟ መጠሪያ ቁና ሰፋች” ከሚለው አገራዊ አባባል እንደማይዘል ገልጸው ወዳጆቻቸው ከዚህ የዘለለ እንዳይጠብቁ ይገልጻሉ። ምንም እንኳን በፊልሙ ላይበነበራቸው ሚና ከፍተኛ ተወዳጅነት ቢያገኙም እርሳቸው ግን “የኔ ድርሻ ትንሽ ነው” ይላሉ”
ጋሼ ኃይለመለኮት- ተወዳጅ የኢትዮጵያ ክፍሎች መምህርና ደራሲ መሆናቸው ኢትዮጵያን በደንብ ለማወቅ አስችሏቸዋል። ከአፋርና ከቤኒሻንጉል በስተቀር ሁሉኑም የሀገሪቱን አካባቢዎች ተዘዋውረው ተመልክተዋል። በተለይ ከደራሲያን ማህበርና ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቤተመዛግብትና ቤተ መጻሃፍት ኤጀንሲ ጋር “በጥበብ ጉዞና” “ማንበብን ባህል ለማድረግ” በሚሰሩ ስራዎች ላይ ልምዳቸውን ከማካፈል አኳያ ጉልህ አስተዋፆኦ አበርክተዋል። ከዚህ መነሻ ሰሜን፣ ደቡብ፣ ደቡብ ምእራብ፣ ምስራቅ ኢትዮጵያ የሚገኙ ባህላዊ፣ የታሪክና የቅርስ ሀብቶች የማየት እድሉን አግኝተዋል።
“ኢትዮጵያ ሁለመናዋ የሚጎበኝ ነው” የሚሉት ጋሼ ኃይለመለኮት፤ በኢትዮጵያውያን መታየት ከሚገባቸው መሃል አክሱም፣ አል ነጃሺ፣ገረአልታ፣ ግሸን ማሪያም፣ ላሊበላ፣የአጼ ፋሲል ቤተመንግስት ፣ አባይ፣ ጣና፣ የደቡብ ምእራብ የተፈጥሮና ባህላዊ ውበት፣ የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ፣ ሃረር፣ ድሬዳዋ፣ አፋር (ዳሎልና ሌሎች መልክአምድራዊ ውበቶቹ) ሁሉም ህብረተሰብ ሊጎበኛቸው እንደሚገባ ይጠቁማሉ። በተለይ በአዲስ አበባ ታሪካዊ ህንጻዎች ሃይማኖታዊ ስፍራዎችና እጅግ በርካታ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ የመስህብ ቦታዎች መኖራቸውን ይናገራሉ።
ህብረተሰቡም በአካባቢው የሚገኘውን ሀብት አውቆና ተረድቶ ጥበቃ ማድረግ ይኖርበታል የሚል ምልክታ አላቸው። በተለይ መንግስት ለነዚህ ቅርሶች ጥበቃ ማድረግ የማይችል ከሆነ “በታሪክ ላይ ወንጀል መስራት ነው” በማለት ከዚህ ቀደም ለተሰሩ ስህተቶችም መንግስት ይቅርታ መጠየቅ ይኖርበታል የሚል አቋም አላቸው።
የመምህሩ የመዝናኛ መንገድረጅሙን ህይወታቸውን ያሳለፉት በመምህርነት ነው። እነዚህ ጊዜያት በእርሳቸው ዘንድ እጅግ ልዩ ስሜት የሚፈጥሩና ከምንም በላይ የሚያስደስቷቸው ናቸው።
“ደራሲ” ከሚለው ይልቅ “መምህር ኃይለመለኮት” ተብለው ቢጠሩ የበለጠ ይደሰታሉ። ከአርትኦትና ከድርሰት ስራ ለጥቂት ሰዓትም ሆነ ቀናት ማረፍ ሲሹ አንዱ ልምዳቸው የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሙዚቃዎችን በመስማት ነው። ምንም እንኳን ማንበብ ዋንኛው ስራቸው ቢሆንም የሚዝናኑበትና እረፍት የሚሰጣቸው ጭምር ነው።
መምህር ኃይለመለኮት ማህበራዊ ህይወት ላይ በመሳተፍ ይታወቃሉ። ካላቸው ጊዜ ቆጥበው ከቤተሰብ ጎረቤትና ጓደኛ ጋር መጫወት፣ መረዳዳት፣ መልካምም ሆነ ክፉ ጊዜን መጋራት ይወዳሉ። ከዚህ ባሻገር በስእል አውደ ርእይ ይገኛሉ። የቀድሞ ተማሪዎቻቸውን ሲያገኙ ወደር የሌለው ደስታ ይሰማቸዋል። ስላሳለፉት ዘመንና ስለኢትዮጵያ ታሪክ በሚያገኙት ውስን ሰዓት መጫወት “መንፈሳቸውን የሚያድስ” በኢትዮጵያዊ ማንነታቸው እንዲኮሩ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸውልናል። በመጨረሻም መምህር ኃይለመለኮት “ከስጋት ነፃ የሆነች ኢትጵያ እንድትኖር እመኛለሁ” በማለት ሁሉም ለሰላምና ለአንድነት እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል። ሰላም!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2013