ምሽት ላይ አዲስ ሩጫዋ ይበረክታል፡፡ ሠራተኛው ከዋለበት ሥራ ወደቤቱ ይቻኮላል፡፡ መንገዶች በእግረኞች ይሞላሉ፡፡ ያኔ የአዲስ አበባ ዋና ዋና መንገዶች በሰዎች ኮቴ ይጨናነቃሉ፡፡ ሜክሲኮ በተለምዶ ቡናና ሻይ አካባቢ ምሽት ላይ የመንገደኞች መጨናነቅ ከሚበረክትባቸው የመዲናዋ መንገዶች አንዱ ነው፡፡ ለመንገዱ መጨናነቅ ምክንያት እዚህ ቦታ የእግረኛው መብዛት ብቻ አይደለም፡፡ የእግረኞች መመላለሻ መንገድ ላይ ምሽቱን እየተራወጡ ለመንገደኞች አልባሳት፣ ጫማዎች፣ የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁስና ዓይነተ ብዙ መገልገያ ዕቃዎች የሚሸጡ ነጋዴዎች ናቸው፡፡
ደንብ አስከባሪዎች ሕገወጥ የሚሏቸው ነጋዴዎቹ ከደንብ አስከባሪዎች ጋር እየተሽሎኮሎኩ የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን አላፊ አግዳሚውን ያቀረቡትን ዕቃ ይገዛ ዘንድ ይወተውታሉ፡፡ «አላየን አልሰማን እንዳትሉ፤ በአንዱ ዋጋ 2 ጫማ፣ አስገራሚ የሽንኩርት መክተፊያ ነፃ በሚባል ዋጋ፣ ካልሲ በአስር አስር ብር..» መንገዱ ላይ ተዘውትረው ከሚሰሙ ድምፆች መሀከል ተደጋግመው የሚደመጡ ናቸው፡፡
የመንገደኛ መተላለፊያ መንገድ ላይ ተርታውን ባነጠፉት ሸራ ዘርግተው ለመንገደኛው የይግዙን ጥሪ የሚያቀርቡት የመንገድ ላይ ነጋዴዎቹ ደንብ አስከባሪዎቹ ሲመጡ ዕቃቸውን ሰብስበው ይሮጣሉ፡፡
ሀብታሙ እዚህ አካባቢ ምሽቱን ማሳለፍ ከጀመረ ሁለት ዓመቱ ነው፡፡ ነገር ግን እስካሁን በሁለት እግሩ መቆም የተሳነው ከችግር ያልተላቀቀ በፈተና ተሞልቶ ኑሮውን የሚገፋ ለውጥን በውስጡ ሁሌም የሚናፍቅ ወጣት ነው፡፡ ቀን ላይ ከመርካቶ ያገኘውን ዕቃ እየገዛ ምሽት ላይ በተለያዩ አካባቢዎች እየተዘዋወረ ይሸጣል፡፡ ከደንብ አስከባሪዎች ጋር ድብብቆሽ እየተጫወተ የቤተሰቡን የዕለት ጉርስ ለመሸፈን ይተጋል፡፡
ከዓመታት በፊት በአንድ የመንግሥት መስሪያ ቤት ተቀጥሮ የሚሰራ ጥሩ ደመወዝ ተከፋይ የመንግሥት ሠራተኛ ነበር፡፡ በሥራው ታታሪና ታማኝ ከሰዎች ጋር በመግባባትም የሚደርስበት አልነበረም፡፡ ለሥራው ታማኝ መሆኑ በቡድን አጋሮቹ ጥርስ ውስጥ እንዲገባ አደረገው፡፡ ለሥራው በጉርሻ መልክ እንዲቀበል ከደንበኞች የሚቀርብለት ጥያቄ «ደመወዜ ይበቃኛል፤ አመሰግናለሁ» ሆነ መልሱ፡፡
እዚያ መስሪያ ቤት ይህ አልተለመደም፡፡ ለዓመታት ሠራተኞች የተሰጣቸውን አደራ ከመወጣት ይልቅ ከደንበኞች ጋር እየተመሳጠሩ መንግሥትና ሕዝብ የሚዘርፉበት ሙስና እጅግ የተንሰራፋበት ነበርና የሀብታሙ ታማኝ መሆን በሌሎች ባልደረቦቹ አልተወደደም፡፡ ባልደረቦቹ የሚሰሩትን ሕገ ወጥ ሥራና ያላግባብ ጥቅምን የግል የማድረግ ተግባር በሚያይበት ጊዜ ፊት ለፊት መጋፈጡን ቀጠለ፡፡
በተደጋጋሚ ለአለቆቹ ጉዳዩን ቢያስረዳም ፈፅሞ ከዚያ ተግባራቸው ሊያስቆማቸው አልቻለም፡፡ ይባስ ብሎ ውሎ ሲያድር የመስሪያ ቤቱ አስተዳዳሪ ዋንኛ ተዋናይ መሆኑን ሲያውቅ ተስፋ ቆረጠ፡፡ ሀብታሙ አገሩን ወዳድ ነበርና ጉዳዩን በቀላሉ አላለፈውም፡፡ ከተቋሙ ውጪ ያለና ሙስና ላይ በሚሰራ ተቋም የድርጅቱ ብልሹ አሠራር ይስተካከል ዘንድ ጥቆማ ሰጠ፡፡ ይህን ደግሞ የተቋሙ አንዳንድ ሠራተኞችና ኃላፊዎች ሰምተው ቀደሙት፡፡
ጥቆማ የደረሰው መስሪያ ቤት ተቋሙ ላይ አለ ስለተባለውና ስለተንሰራፋው ሙስና ምንም ማስረጃ ማግኘት ተሳነው፡፡ ከዚያ በኋላ ለሀብታሙ በተቋሙ ኃላፊዎችና አንዳንድ ሠራተኞች ወጥመድ ተዘጋጀለት፡፡ በሚፈርምባቸው ደረሰኞችና ወረቀቶች ላይ ቀድመው ባቀዱት እቅድ መሠረት ስህተት እንዲሰራ አመቻቹለት፡፡ ሀብታሙም በተጠመደለት ወጥመድ ከመውደቅ አላመለጠም፡፡ በዚህ የሰነድ ማጭበርበር በሚል ወንጀል በመስሪያ ቤቱ ተከሶ ተፈረደበትና ለሁለት ዓመታት ታስሮ ብዙ የስቃይ ጊዜ እስር ቤት ውስጥ አሳለፈ፡፡
በሥራ ላይ እያለ ያገባትና የወለዳቸው ሁለት ልጆቹ እሱ ይጦራቸው በነበሩ ወላጆቹ እጅ ወደቁ፡፡ ባለቤትና ልጆቹ በችግር ዓመታት አሳለፉ፡፡ በተለይ ልጆቹ ይማሩበት ከነበረው የግል ትምህርት ቤት በገንዘብ ማጣት ምክንያት ትምህርታቸው ተቋረጠ፡፡ ሀብታሙ ከእስራቱ ከፍ ባለ በቤተሰቡ ችግር ውስጥ መውደቅ ቅስሙ ተሰበረ፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ ከእስር ሲፈታ ማህደሩ በሸር የተበላሸበት ሀብታሙ ሌላ የመንግሥትም የግልም መስሪያ ቤት የማንኳኳት ዕድሉ ተበላሸ፡፡ ተቀጥሮ የመስራት ዕድሉን አጣ፡፡
ከእስር ቤት እንደወጣ ቶሎ ሥራ ማግኘት ባለመቻሉ ብዙ ተጎዳ፡፡ ዓለም ፊቷ ያዞረችበት ዕድለ ቢስ ሰው መሆኑን አመነ፡፡ ዓለም ለታማኞችና ለእውነተኞች ቦታ የሌላት መሆኑንና ከዚያ ይልቅ ለአስመሳይና ወንጀሎኞች ምቹ የሆነች መሰለው፡፡ ለ3 ወራት ያህል በቀን ሠራተኝነት ሲሰራ ቆይቶ ባገኛት አነስተኛ ብር አሁን እየተራወጠ የሚሰራውን የመንገድ ላይ ንግድ ጀመረ፡፡ በሕገወጦች ይሰራው የነበረው ሕጋዊ ሥራ ሕገወጥ ሥራ ላይ እንዲሰማራ ግድ ሆነበት፡፡
ዛሬ ከ11 ሰዓት ጀምሮ እዚያ ቦታ ላይ ጥቂት ጥንድ ጫማዎችን በሸራ ዘርግቶ ቆሞ በዓይነቁራኛ ደንብ አስከባሪዎችን እየተከታተለ ለተላላፊው እንዲገዙት የማስተዋወቅ ሥራ ይሰራል፡፡ በመሀል ግን አንድ ግለሰብ በእጁ የያዘውን ጫማ ለመጠየቅ ተጠግቶ ያዋራው
ጀመር፡፡ ተነጋግረው ዋጋ ይነጋገሩ ጀመር ወዲያው አካባቢው ላይ ትርምስ ተፈጠረ፡፡ ደንብ አስከባሪዎች ድንገት አካባቢው ላይ ፈሰው ነጋዴዎቹ የያዙት ዕቃ መቀማት ጀመሩ፡፡ አንድ ደንብ አስከባሪ ሀብታሙ በዘረጋው ሸራ ላይ እግሩን ተክሎ ቆመ፡፡ ይሄኔ ሀብታሙ የተያዘበትን ለማስለቀቅ ትግል ጀመረ፡፡ ነገር ግን ተረታ፡፡ የደንብ አስከባሪው ባልደረቦች ቀርበው ተረባረቡበት፡፡ ይብስ ብሎ በዱላ ይነርቱት ጀመር፡፡ እጅ ሰጠ፡፡ ዕቃውን ይዘው እየሄዱ እሱ ደግሞ ከኋላ ይከተላቸው ጀመር፡፡
ተከትሏቸው የደንቦቹ ማረፊያና አነስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ድረስ ሄደ፡፡ የወሰዱበት ከመመለስ ይልቅ ይበልጥ ያጭቁት ጀመር፡፡ ይዘውበት ከሚሄዱት አንዱ «ዞር በል አንተ፤ በዚህ ዱላ ነው ማቀምስህ አታፍርም ሕገ ወጥ ሥራ እየሰራህ» ሀብታሙ ይሄኔ በንዴት ያጉተመትም ጀመር፡፡ «እኔ ሕገወጥ አይደለሁም ሕገወጥ ሥራ ላለመስራት ሕግን ላለመጣስ በጉልበቴ እየለፋሁ ያለሁ ሰው ነኝ፡፡ በፍፁም ሕገ ወጥ አይደለሁም ሲል ገለጻላቸው፡፡
ድብ አስከባሪዎቹ ግን በንግግሩ ይሳለቁበትና ያሾፉበት ጀመር፡፡ «ሀሀሀሀ ተው እንጂ እስኪ ንግድ ፍቃድህ ሃሀሃሃሀ» ብዙ ለመነ፤ ከቆየ እሱንም እንደሚያስሩት ነገሩት፡፡ በል ሂድ በሕገወጥ መንገድ የተገኘ ምንም በሕግ ጥላ ስር ነው የሚውለው አንሰጥህም» አሉት፡፡ ተስፋ ቆርጦ ሲወጣ በር ላይ እንድ ነገር ተመለከተ፡፡ እንደሱ ዕቃ ተወስዶበት ደንበኞች ጋር የቆመ በዓይኑ የሚያውቀው ወጣት ለደንቦች ብር ኪሳቸው ውስጥ ሲያደርግ ዕቃውን ሰጥተውት ሲሄድ፡፡ ይሄኔ ሀብታሙ እጅጉን እያዘነ እራሱን ጠየቀ፡፡ እንባ በተናነቀውና ተስፋ በቆረጠ ድምፀት ማነው ሕገ ወጡ እኔ? መልስ የመለሰለት ግን የለም፡፡ …ተፈፀመ
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሰኔ 18/2013