ተ ባባሪ ፕሮፌሰር ትልቅሰው ተሾመ ይባላሉ። በዓይን ህክምናው ዘርፍ በተለይም በሬቲና ላይ በኢትዮጵያ ቀዶ ህክምና እንዲጀመር ያደረጉ ናቸው። የሬቲና ቀዶህክምና ማዕከል በኢትዮጵያ እንዲከፈት አድርገዋልም። በዚህና በርከት ባሉ ሥራዎቻቸው በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ሽልማቶችን አግኝተዋል።
ከእነዚህ ውስጥ የቅርቡን መጥቀስ ቢያስፈልግ በአለም አቀፍ ደረጃ በአሜሪካ በዓይን ሀኪሞች ማህበር ያልተዘመረለት ባለሙያ ተብለው ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ሽልማቱ የሚበረከተው ለአሜሪካዊያንና አሜሪካዊ ላልሆኑ አባል የዓይን ሀኪሞች ሲሆን፤ በአብዛኛው አውሮፓ ውስጥ የሚኖሩ ከ10ሺ ያልበለጡ አባላት ባሉበት ውስጥ እርሳቸው ተመርጠው እውቅናው ተችሯቸዋል። እኛም ለዛሬ የ‹‹ህይወት ገጽታ›› አምድ እንግዳችን አድርገናቸዋልና ከህይወታቸው ተማሩ ስንል ጋበዝናችሁ።
ልጅነት
ተወልደው ያደጉት እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነው። ቤተሰቡ በቤት ኪራይ ስለነበር የሚኖረው እድገታቸው በአንድ ሰፈር አልተወሰነም። በዚህም እትብታቸው የተቀበረበት መሀል ካሳንቺስን በመተው አራትኪሎ ከዚያም ቀበና ኮከበጽብሃ አካባቢ እያሉ ነበር የልጅነት ጊዜያቸውን ያሳለፉት። በዚህም በእያንዳንዱ ቦታ ላይ የተለያየ ትዝታ አላቸው። የሁሉም ግን እንደ ቀበናው እንደማይሆን ይናገራሉ። ምክንያቱም አብዛኛው የልጅነት ጊዜያቸው ያለፈው በዚሁ ሰፈር ነው። ከዚያ በተጨማሪም ይህ ቦታ ለልጆች ልዩ ስሜት የሚሰጥበት መዝናኛ ስፍራዎችን አቅፏል።
ከሰፈሩ ወደ ታች ሲወርዱ 15 ሜዳን ያገኛሉ። እንደፈለጋቸው ቦርቀው ተጫውተው ወደ ቤታቸው መመለስ ይችላሉ። ከዚያው ከሰፈራቸው ብዙ ሳይርቁም ብዙዎችን የእድገት ማማ ላይ ያደረሰው ጃንሜዳም አለ፤ በዚያም እንደፈለጋቸው ኳስ ይጫወታሉ። በእርግጥ እንግዳችን ከጨዋታ ይልቅ ትልልቆቹ ሲጫወቱ ማየት ይመስጣቸዋል። ለዚህም ቢሆን የተሻለ አማራጭ ስለሰጣቸው ሰፈሩን በጣም እንደሚወዱትና ልዩ ትዝታ የፈጠረባቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።
በባህሪያቸው ብዙ ማንበብ የሚወዱና ከሰው ጋር በፍቅር ማሳለፍ የሚወዱ ናቸው። ታዛዥነትም ቢሆን መለያቸው ነው። እንደ ልጅ ረብሸው ሳይሆን ዝምተኛ ሆነው ሳይጣሉ ነበር የሚጫወቱት። ይህ ደግሞ በልጆች ሁሉ ተወዳጅ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።
የቤተሰቡ የመጀመሪያ ልጅ በመሆናቸው በቤት ውስጥ ብዙ ድርሻዎች ያሉባቸው ነበሩ። ታናናሾቻቸው ጭምር የእርሳቸው ሥራ ነበሩ። አባትና እናት ተለያይተው በመኖራቸው የተነሳ እንደታላቅነታቸው ልጆቹን መንከባከብ የእርሳቸው ሀላፊነት ነበር። በእርግጥ አባት ቤቱ ሙሉ እንዲሆን ይለፋሉ። በተለያዩ ሙያዎች ውስጥ ገብተው ይሰሩ ነበር። ለአብነትም ሆቴል ከፍቶ መስራት፤ መነገድና ይህ ሳያዋጣ ሲቀር ደግሞ መልሶ ደሞዝተኛ መሆን በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። ስለዚህም አባት የሥራ ጫናቸው የበዛ ነበር። ከዚህ የተነሳም ለእንግዳችን በቤት ውስጥ የሚሰራው ሁሉ የእርሳቸው ድርሻ ነበር። በዚህ ግን አንድም ቀን ተማረው አያውቁም። እንደውም ደስተኛ ሆነው ነበር ጊዜያቸውን ያሳለፉት።
ተባባሪ ፕሮፌሰር፤ ከልጅነታቸው አልረሳውም የሚሉት ልጅነቱ ራሱን ነው። ልጅነት ተመልሶ አይመጣም እንጂ ብዙ ስንቆች የሚሰነቅበት ነበር። አብሮ መብላቱ፣ በፍቅር አብሮ መጫወቱ፣ መታዘዙ ሁሉ ነገሩ የሚናፈቅና ተመልሶ በመጣ የሚያስብል ነው። ለነገ ህይወት ጭምር መንገድ የሚያቀና ማን እንደልጅነት አለ ሲሉ ይጠይቃሉም። ወሰን የሌለበት አክብሮቱ፣ መነፋፈቁ ሁሉ ነገር ዋጋ ያለውና የሚናፈቅ ነው። መቦረቁና በበዓላት ልዩነት ሳይኖር ሁሉንም በእኩል ደረጃ ማስተናገዱም ልዩ ጣዕም ያለው ነው። ለዚህም ነው ማንኛውም ሰው ልጅነቱን ሲጠየቅ ዳግም ቢመጣ እያለ የሚመኘው። ግን አንድ ነገር አለ። ልጅነት ሲነሳ እንደ አገር አንድ እንሆናለን። ሁሉም ወደኋላ መልሶን መልካሙን ነገር እንድናስታውስ ያደርገናል። ይህ ነገሩም ዛሬም ቢሆን ተናፋቂ አድርጎታል ይላሉ።
የዓይን ፍቅርን በትምህርት
የትምህርት ሀሁ የተጀመረው ከመኖሪያ ቤታቸው ብዙም ባራቀው ኪዳነምህረት የሚሽነሪ ትምህርት ቤት ነው። በዚህ ትምህርት ቤት እስከ ስምንተኛ ክፍል መማር ችለዋል። ከዚያ ቀጣዩን ትምህርት ለመማር በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ገቡ። ይሁን እንጂ ዘጠነኛ ክፍልን ብቻ ነበር እዚህ መማር የቻሉት። ሌሎቹን ክፍሎች የቀጠሉት የተሻለ ትምህር ለመማር በአባታቸው አማካኝነት ወደ አዳማ ተጉዘው ባያብል አካዳሚ በተባለ የአዳሪ ትምህርት ቤት ነው። በዚህም ቢሆን አስረኛና አስራ አንደኛ ክፍልን ብቻ ነው መማር የቻሉት። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የደርግ መንግስት ትምህርት ቤቱ ከሀይማኖት ትምህርት አልራቀም በሚል በመዝጋቱ ነው። ስለዚህም እንግዳችን ከዚያ ትምህርቱን አቋርጠው ዳግም ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ ሆኑ።
አዲስ አበባ ከተመለሱ በኋላም በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ገብተው አስራ ሁለተኛ ክፍልን ማጠናቀቅ ችለዋል። በወቅቱ በማህበረሰቡም ሆነ በተማሪዎች ዘንድ ጥሩ ግምት የሚሰጠውና ጎበዝ ተማሪ የሚገባበት ትምህርት ክፍል ምህንድስና እና ህክምና ነበር። በመሆኑም እርሳቸው በሂሳብና በፊዚክስ ልዩ ብቃት ያላቸው በመሆኑ ምርጫቸውን ምህንድስና ለማድረግ ወሰኑ። ነገር ግን ፎርም ሲሞሉ ሌሎች የትምህርት መስኮችም ይካተቱ ስለነበር የመረጡት ሳይደርሳቸው ህክምና ላይ እንዲያርፉ ሆኑ። በእርግጥ ይህም ቢሆን አልተከፉበትም። ክብደቱ እንዳለ ሆኖ ወደውት ተምረውታል።
ህክምናውን ለመማር የገቡበት ዩኒቨርሲቲ ከትውልድ ቀያቸው ያልራቀው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው። በዩኒቨርሲቲ የህክምና ትምህርታቸውን አጠናቀዋል። ከምረቃ በኋላ በቀጥታ ወደ ሥራ የገቡት እንግዳችን፤ ከአራት ዓመት የሥራ ላይ ቆይታ በኋላም ዳግም ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመመለስ በህክምናው ዘርፍ በአይን ህክምና ስፔሻላይዜሽን በከፍተኛ ውጤት ተመርቀው በዚያው ቀሩ። ይህ ደግሞ ለሌላኛው ስፔሻሊቲና የተለያዩ ስልጠናዎች ምቹ ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል።
መማር ሁልጊዜ አዲስ ነገር ማግኘት ነው ብለው የሚያምኑት ባለታሪካችን፤ ቪትሬዮ-ሬቲና በሚባል የትምህርት መስክ ሰብ ስፔሻሊቲያቸውን ሰርተዋል። ከዚህ በተጓዳኝ የተለያዩ ስልጠናዎችን በተለያዩ አገራት በመዘዋወር ወስደዋል። በተለይም አውሮፓ ላይ ሰፋ ያሉ ስልጠናዎችን እንደወሰዱ አጫውተውናል። በሥራቸውም ቢሆን በየጊዜው እየተማሩ እንደሆነ ይናገራሉ።
ዓይን ለዓይናማው በሥራ
ሥራን በቅጥር የጀመሩት በህክምና ትምህርት ከተመረቁ በኋላ በሀረር ምስራቅ አርበኞች ሆስፒታል ውስጥ ነው። በዚህ ሆስፒታል በቆዩባቸው አራት ዓመታት ውስጥ አጠቃላይ ሀኪም በመሆን ሰርተዋል። ለማህበረሰቡም በቂ ግልጋሎት ሰጥተዋል። ለዓይን ህክምና ትምህርት ወደ አዲስ አበባ መጥተው የማዕረግ ተመራቂ መሆናቸው እና በዘርፉ ትምህርቱን የሚሰጥ በቂ መምህር ባለመኖሩ እዚያው ቀርተው እንዲሰሩ ተደርገዋል። ይህ ሥራቸው ደግሞ ዛሬም ድረስ የሚያከናውኑት ነው።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከጥቁር አምበሳ ሪፈራል ሆስፒታል በላይ ብዙ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት በምኒልክ ሆስፒታል ነው። ምክንያቱም ትምህርቱ ከንድፈ ሀሳቡ ይልቅ ተግባሩ ይበልጣልና ያንን ለማስተማር ምቹ የሆነው ምኒልክ ሆስፒታል ሆኖ በመመረጡ ነው። የሥራ ቦታቸው ግን በሁለቱም ሆስፒታሎች ነው። በመማር ማስተማሩ ሥራ እስከ ተባባሪ ፕሮፌሰርነት ደረጃ የደረሱት ባለታሪካችን፤ የተለያዩ የምርምር ተግባራትን ብቻቸውንና ከተለያዩ አጋሮቻቸው እንዲሁም ከተማሪዎቻቸው ጋር በመሆን ሰርተዋል።
እስከ አሁንም ከ10 በላይ ሥራዎችን በአለማቀፉ የምርምር መጽሔት ላይ አሳትመዋል። በማስተማሩ ዓለም በቆዩባቸው 20 ዓመታት ውስጥም ከ100 በላይ ተማሪዎችን አስተምረው አስመርቀዋል። በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችም በዘርፉ የሚማሩ ተማሪዎችን አማክረዋል።
ባለታሪካችን ከማስተማሩ ባሻገር በተለያዩ ሀላፊነቶች ላይ በውጪና በአገር ውስጥም የሰሯቸው በርካታ ሥራዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል የአውሮፓና የአፍሪካ የዓይን ሀኪሞች ማህበር አባል በመሆን መሳተፋቸው፣ የአፍሪካ ሬቲና ማህበር የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል በመሆን ማገልገላቸው፣ ለአንደኛው የአፍሪካ ሬቲና ማህበር ስብሰባ ኮሚቴ አባል ሆነው ብዙ ተግባራትን ማከወናቸውና የምስራቅ፣ መካከለኛው እና የደቡብ አፍሪካ የዓይን ሕክምና ኮሌጅ የሥርዓተ ትምህርት ግምገማ ኮሚቴ ሆነው ሙያዊ አሻራቸውን ማሳረፋቸው የሚጠቀሱ ናቸው።
የምስራቅ፣ መካከለኛው እና የደቡብ አፍሪካ የዓይን ሕክምና ኮሌጅ መጽሔት ዝግጅት ክፍል የኢዲቶሪያል ቦርድ ውስጥም ሰርተዋል። በሕንድና ኢትዮጵያ በዓይን ዙሪያ የሚታተሙ መጽሄቶችን ገምጋሚም በመሆን ብዙ ተግባራትን አከናውነዋል።
የኢትዮጵያ የዓይን ህክምና መጽሔት አዘጋጅ ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በህክምና ትምህርት ክፍሉ ውስጥ በሚገኘው የዓይን ህክምና ክፍል አስተባባሪ፤ በኢትዮጵያ የዓይን ህክምና ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት፤ የብሔራዊ የዓይን ባንክ የቦርድ አባልና ባላደራ ሆነው አገልግለዋል። በተመሳሳይ በዓይን ህክምና ክፍል ውስጥ የትምህርት መስኩ እንቅስቃሴዎች ኮሚቴ፣ የዓይን ህክምና ትምህርት ክፍል ሃላፊም ሆነው ሰርተዋል።
ቪትሮክቶሚ ቀዶ ህክምናን ያስተዋወቁ፤ የመጀመሪያው የሬቲና ቀዶ ህክምና አድራጊ፣ የሬቲና ቀዶ ህክምና ማዕከል በግል ደረጃ እንዲከፈት በር ከፋችም ናቸው። ማዕከሉ ብሩህ ቪዥን የዓይን ህክም ሲሆን፤ ከዛሬ አስር ዓመት በፊት የተከፈተ ነው። በእርግጥ ይህ ሥራ እንዲጀመር ምክንያት የሆናቸው በመንግስት ሆስፒታሎች ውስጥ ያለው ያልተሟላ አሰራር ነበር።
በተለይ ክፍተቶቹ ብዙዎችን ከፍተኛ ወጪ አውጥተው ወደ ውጪ አገር በመሄድ ህክምና እንዲያገኙ ያስገደደ መሆኑ እረፍት አልሰጣቸውም። በመሆኑም የእኛ ድርሻ ምን ይሁን ሲሉ ከሥራ አጋሮቻቸው ጋር በመሆን ተነሱ። ማዕከል ከፍቶ መስራት ደግሞ አማራጭ የሌለው ጉዳይ እንደሆነ አመኑ። ወደ ተግባር ቀየሩትናም ያለውን ክፍተት ለመሙላት ቻሉ። እንደውም ይህ ማዕከል ለኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያን ጭምር መድረስ የቻለ ሆኗል። ብዙ የአፍሪካ አገራት ታካሚዎች በህክምናው ጥራትና ዋጋ የተነሳ ወደዚህ መጥተው መታከም ችለዋል። ደስተኞችም ሆነው እንደሚመለሱ አጫውተውናል።
የመልካም እይታ ሜዲካል አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ውስጥ ሥራ አስኪያጅ፣ በእስቶክ ማንደቪል ሆስፒታል የቡድን መሪ፤ ዳድ የበጋ ትምህርት ቤት ወኪል፣ የኦርቢስ ፍላይንግ ዓይን ሆስፒታል ኮሚቴ ሊቀመንበርም ሆነው ማገልገላቸውም በግል ዘርፉ ካደረጉት አስተዋዕጾ ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ሌላው በህክምናው መስክ ብዙ የለፉና ብዙ ለውጥ ያመጡ መሆናቸውም ያስመሰግናቸዋል። ለአብነትም በህክምናው አለም ቆይታቸው በቀዶ ህክምና ብቻ ከ200ሺ በላይ ሰዎችን የዓይን ብርሀናቸው እንዲመለስ አድርገዋል።
ቀደም ሲል የዓይን ህክምና በአገር ውስጥ እንዳይሰጥ ብዙ ተግዳሮቶች ነበሩበት። በተለይም ቀዶ ህክምናውን ለማድረግ የሚያስችለው የግብዓት አቅርቦት ጉዳይ ዋጋው የናረና በቀላሉ የማይሸፈን እንዲሆን አድርጎት ቆይቷል። በዚህም እርሳቸው የህክምና ማህበረሰቡን የማሳመን ስራ በመስራት ነገሮች እንዲቀየሩና በቀላሉ በአገር ውስጥ የሚታከመው ሰው ህክምናውን እንዲያገኝ ማድረግ ችለዋል። በዚህም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቀላሉ የሚድነው በሽታቸው ጉዳት እንዳያደርስባቸው አድርገዋል።
የአገር አበርክቶ
ሬቲና የሚባለውን የአይን ክፍል በአገር ደረጃ በደንብ በህክምናው ዘርፍ እንዲሰራበት ካደረጉ ኢትዮጵያዊያን መካከል በመጀመሪያው ተርታ የሚቀመጡ ናቸው። ከዚህ ግን የሚልቀው በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ የአይን ህሙማን ብርሃናቸው የሚመለስበትን ሁኔታ ማመቻቸታቸው ነው። ከዚህ በተጓዳኝ በህክምናው ዘርፍም ቢሆን ከ20 ዓመት በላይ ብዙዎችን ማፍራት ችለዋል። የዓይን ህክምና ከአጋር አካላት ጋር በብዛት የሚሰራ በመሆኑም በተለይ ከውጪ አገር አጋዥ አካላት ጋር ብዙ ሰርተው አገራችን የምትጠቀምበትን ሁኔታም አመቻችተዋል።
የሬቲና ብቻ ሳይሆን የአይን ሞራ ግርዶሽ፣ የግላኮማና መሰል ቀዶህክምናዎች በዋናነት የሚሰሩና ብዙዎችን ብርሃናቸው እንዲመለስ ያደረጉ ናቸው። ከስኳርና ደም መፍሰስ ጋር ተያይዞ የሚመጡ የዓይን በሽታዎችንም ቢሆን በቀዶ ህክምና ፈውስ የሚሰጡም ናቸው።
የህይወት ፍልስፍና
ግልጽ መሆንና ለእውነት መስራት የሚረዳ ሰው እስኪገኝበት ድረስ ዋጋ ያስከፍላል ብለው ያምናሉ። በዚህም ሁልጊዜ እውነትን ተገን አድርገው መስራት ፍላጎታቸው ነው። ሰው ለሰው ከመድረስ የተሻለ እርዳታ የለም የሚል አቋም ያላቸውም ናቸው። በተለይም ባለሙያ የሆነ ሰው ባለው እውቀት ሰዎች ረክተው ሲሄዱ ማየት በአለ እድሜ ላይ መጨመር እንደሆነ ያስባሉ። በዚህም ዘወትር በህክምና አገልግሎታቸው ህሙማን ብርሀናቸው ሲመለስ ሲመለከቱ ውስጣቸው በሀሴት እንደሚሞላና አዲስ ተስፋን እንዳገኙ እንደሚሰማቸው ይናገራሉ።
በህይወታቸው ደስተኛ የሚሆኑት በተለይም ወጣቶችን አክመው ወደትምህርት ገበታቸው ሲመለሱ ማየት ነው። የህይወት ፍልስፍናቸውም ለሰው ያለን ሁሉ በማካፈል ሰውን ደስተኛ ማድረግ ራስን ዳግም ማኖር ነው የሚል ነው። ያለን መስጠት ባለ ላይ መጨመር ነው እምነታቸው ነው። በተለይም ሙያን ተገን አድርጎ የሚከናወን ተግባር አቅም ለእውቀት፣ ጭማሬ ለእውቅና፣ በረከት ለወደፊት ህይወትና ኑሮ ነው ባይ ናቸው። ስለዚህም ያለስስት ሙያቸውን ለተማሪያቸውም ሆነ ለታካሚያቸው መስጠት የህይወት ፍልስፍናቸው ነው።
የቀጣይ እቅድና ፍላጎት
ፍላጎታቸው ህክምናው በሌሎች አለማት ላይ የደረሰውን ያህል ሆኖ በአገራችን ማየት የመጀመሪያው ነው። ለዚህ ደግሞ ትጋትና ትግስትን አስተባብሮ መያዝ እንደሚያስፈልግ ያምናሉና እርሱን በማድረግ ለስኬታቸው እንደሚሰሩ ነገርውናል። በተጨማሪ እርሳቸውም ሆኑ የሥራ ባልደረቦቻቸው የዓይን ህክምና ላይ የሚታየውን ችግር በቻሉት ሁሉ ለመቀነስ ተባብሮ መስራትን ልምድ እንዲያደርጉ የጀመሩትን እንቅስቃሴ አጠናክሮ መሥራት ቀጣይ እቅዳቸው መሆኑን አጫውተውናል።
ጓደኞቻቸው ስለእርሳቸው
ያየውን ማለፍ የማይወድ፣ ግትርና ለእውነት የቆመ ነው። በተለይም ያሰበውን ከግብ ሳያደርስ ወደኋላ ማለት የማይወድ ሥራ ወዳድ ባለሙያ ነው የሚል እምነት አለኝ። ስህተቱን በመሸፈን አያምንም ለማስተማር ይሞክርበታል እንጂ። በዚህ ደግሞ ማንም ሰው ከእርሱ ፊት ተሳስቶ አልተሳሳትኩም ማለት አይችልም። ከማስረጃ ጋር ጭምር የሚያቀርብና ለስኬታማነት የሚያበቃ ተግባር በሰዎች ላይ የሚሰራ ነው። በዚህም ብዙዎች ሊሸሹት ይችላሉ። ግን አንድም ቀን በዚህ ተጨንቆ የሚያውቅ አይመስለኝም። ምክንያቱም ይህ መለያ ባህሪው ነው። የተለመደ እውነታ ባሸት ተተካ ቢባል አይቻልም። ስለዚህም እርሱ ይህንን መላውን ይዞ የቀጠለና ለብዙዎች ትምህርት የሆነ ሰው ነው ይላሉ በቅርብ የሚያውቋቸው ዶክተር መሳፍንት አበበ።
መጀመሪያ ተማሪያቸው ከዚያ ደግሞ የሥራ አጋራቸው የሆኑት ዶክተር ዘላለም እሸቱ በበኩላቸው፤ በሁሉም መንገድ የማስተማር ብቃት ያላቸው፣ ተማሪን በጣም ተከታትለው ማሰራት የሚወዱ፣ አልችለውም የሚባል ነገር የሌለባቸው ናቸው ይሏቸዋል። ለዚህም በአብነት የሚያነሱት ኦብቲክ የሚባለውን መስክ የሚያስተምር ጠፍቶ አዲስ ተማሪዎች እስኪመረቁ ድረስ እርሳቸው በብቃት ማስተማራቸውን ነው።
በሌላ በኩል ሁሉን ነገር ጥንቅቅ አድርገው መስራት የሚችሉ፣ ሬቲናን የተመለከተ የዓይን ህክምና እንዲጀመር ፈር ቀዳጅ በመሆናቸው ለቀላሉ ህክምና ውጪ አገር ሄደው በትንሹ ክፍያ ከ300ሺ ብር በላይ የሚያወጡ ዜጎችን መታደግ የቻሉም መሆናቸውን ያነሳሉ። በተለይም ታዋቂው ፖለቲከኛ ሀይሉ ሻውል እስር ቤት በነበረበት ሰዓት የዓይን ችግር ገጥሞት ውጪ ካልሄደ መታከም አይችልም በመባሉ አደጋ ውስጥ ነበር። እርሳቸው ግን ከደቡብ አፍሪካ ጭምር እቃዎችን በማስመጣት ህክምናውን እንዲወስድ ያደረጉና አንድ ሰውም ቢሆን ዋጋ አለው ብለው የሚያምኑ የሰውም የአገርም ባለውለታ ናቸው ይሏቸዋል። ለሚፈልጉት አላማ ጽኑ አቋም ያላቸውም ናቸው። ምክንያቱም የሬቲናን ትምህርት ለመማር ሲሉ ብዙ የትምህርት እድሎችን አሳልፈዋል።
ዲስፕሊናቸው ለብዙዎች አርዓያ የሚሆን ነው። ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚሰሩበትን፣ ማህበራዊ ህይወታቸውን የሚያከናውኑበትንና ለቤተሰብ የሚሰጡትን ሰዓት በምንም መልኩ መቀነስ አይፈልጉም ይላሉ ስለእርሳቸው ሲያወሱ።
ቤተሰብ
ባለትዳርና የሦስት ወንድ ልጆች አባት ናቸው። ሁለቱ ትምህርት ጨርሰው በሥራ ላይ ይገኛሉ። አንዱ ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ነው። ባለቤታቸውን ያገኙዋት ሀረር ከተማ ላይ በሚሰሩበት ጊዜ ሲሆን፤ እርሷ የምትሰራበት ቦታ ላይ ደጋግመው በሚሄዱበት ጊዜ ነው ቀልባቸው ያረፈባት። ከዚያ ከልባቸው አልወጣም ስትል ለትዳር አጋራቸው ተመኟት። ውሃ አጣጬ ሁኝልኝ ሲሉም ጠየቋት። ትውውቃቸው ረዘም ያለ ስለነበርም እሷም አስባበት መልስ ሰጠቻቸው። ዛሬ ቤታቸው ሞቆ በፍቅር ጠግቧል። ልጆቻቸውም ቢሆኑ በደስታ እየኖሩ ይገኛሉ።
ከ27 ዓመታት በላይ በትዳር ኖረዋል። በመካከላቸው መጋጨትን የሚያስቡበትን ሁኔታ አይተው አያውቁም። ነገር ግን እንኳን ባልና ሚስት እግርም ከእግር መጋጨቱ አይቀርምና ይህ ነገር ሲፈጠር አንዱ ተሸናፊ ሆኖ ነገሩን ያረግበዋል። በዚህም ልጆቻቸው ጭምር ፍቅርን እንጂ ጸብንና ጥላቻን እያዩ እንዳያድጉ ሆነዋል። እንደውም ለሌሎች ጭምር ቤተሰቦቻቸውን ምሳሌ እንደሚያደርጉ ይናገራሉ።
መልዕክት
ከእኔ ቢወሰድ የምለው ምንም ነገር የለም። ይሁንና አንድ ነገር ልምድ ቢሆን ሳልል አላልፍም። ይህም ራስንም ሆነ አገርን መውደድ በሚል ደረጃ ሊፈረጅ ይችላል፤ አገሩ ላይ መስራትን ሰው የመጀመሪያው ምርጫው ቢያደርግ የሚለው ነው። ምክንያቱም በጣም ጥቂት ሰዎች በሚመረቁበት በእዚያ ጊዜ ከተመረቅነው 90 ውስጥ ከ60 በላይ ያለው በውጪ አገር እየኖረ ውጪውን እያገለገለ ይገኛል። ሀገር ግን ሁልጊዜ ሰው አጥታ ትኖራለች። በለፋችበት ልክም እንዳትጠቀም ሆናለች። በእርግጥ ምክንያቱ ብዙ ሊሆን ይችላል። ሆኖም እንደ እኔ እምነት እንደአገር የሚጠቅም ምንም አለ ብዬ አላምንምና ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው ሰሪና ለአገራቸው አገልጋይ ቢሆኑ ያሸንፋሉ፤ ይበለጽጋሉ፤ ከራሳቸው አልፈው አለምን ጭምር ማኖር ይችላሉ። ስለዚህም አገር ወዳድን ዜጋን ለመፍጠር ለአገሬ በአገሬ የሚል መርህን የሚከተል ትውልድ ማፍራት ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ ዛሬ ለአገሬ በአገሬ የሚል ትውልድን ትፈልጋለችና እዚህ ላይ መስራት ይገባልም ይላሉ።
ኢትዮጵያዊያን እንደሚባለው ብቻ ሳይሆን በተግባር ጭምር ተሳክቶልንም ሆነ ሳይሳካልን አቅፈው መያዝ የሚችሉ ናቸው። በሄድንበት ሁሉ በተለይም ለህክምና ባለሙያዎች የሚሰጡት ክብርና ግምት የበለጠ እንድንሰራ እንጂ እንድንሸማቀቅ የሚያደርግ አይደለም። ይህንን የመጠቀምና ለህሙማኑ የመድረሱ ሀላፊነት የእኛ ድርሻ ነው። ስለዚህም ሀኪሙ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የሙያ መስክ ላይ ያለ ኢትዮጵያዊ ለእንስፍስፉና ትሁቱ ዜጋ አገልጋይነቱን ማሳየት አለበት ሌላው መልዕክታቸው ነው።
ወደኋላ ተመልሰን የተሳሳትነውን መቀየር ባንችልም ወደፊቱ ብዙ በጎ ነገር ያሰራናል። ስለሆነም አሁን ካለንበት ጀምረን እስከምንኖርበት የመጨረሻዋ ሰዓት እኛንም፣ ስማችንንም አገራችንንም የሚቀይር ነገር ለመስራት እንታትር። ሁልጊዜም የራሳችንን ደስታ ስንፈጥር የሌሎችንም እናስብ። የዚህ ጊዜ በእኛ ደስታ ውስጥ እነርሱ ይኖራሉ፤ የደስታቸውን ምንጭም ያያሉ። በተለይም ለስኬት መንገድ የሚሆናቸውን ስንቅ እንዲይዙ እናደርጋቸዋለን። ስለዚህም ደስታችን የሌሎች ደስታና መንገድ መቀየሻ እንዲሆን እንጣር። ወቅቱ ስኬቶቻችንን የሚቀሙንን ሁለት ስህተቶች ማለትም ሥራን አለመጀመርና ጀምሮ አለመጨረስን የምናርምበት በመሆኑ እንጠቀምበት ምክራቸው ነው።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኔ 13/2013