በአዲስ አበባም ሆነ በመላ ሀገሪቱ ለሚስታዋለው የዋጋ ግሽበት መንስኤ ምክንያቶች አንዱ የገበያ መረጃ እጥረት መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት የተሰሩ ጥናቶች ያሳያሉ:: ሸማቹ ስለ ገበያ ሁኔታ በቂ መረጃ ስለማይኖረው ነጋዴዎች የሚጠሩትን ዋጋ ከፍሎ የመግዛት ሁኔታ በሰፊ ይስታዋላል:: ይህንን ችግር ለመቅረፍ የከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ ጥረቶችን ቢያደርግም ችግሩ ሙሉ በሙሉ ሳይፈታ ዘልቋል:: የከተማ አስተዳደሩ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ የመረጃ እጥረት እና ከሌሎች ገበያ እና ግብይት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ችግር ሊያቃልል የሚችል ሶፍትዌር በማበልጸግ ላይ ይገኛል::
እየበለጸገ ያለው ሶፍትዌር የንግድና ገበያ ትንተና መረጃ ሲስተም ይሰኛል:: አዲሱ ሶፍት ዌር አዲስ የሚዘረጋው ሲስተም ሰው ባለበት ቦታ ሆኖ በድረገጽ ወይም በመንገድ ሲያልፍ ደግሞ በስክሪን የሸቀጦች ዋጋ ምን እንደሚመስል መረጃ እንዲኖረው የሚያስችል ነው:: የዕለቱ ፣ የትናንት ዋጋ ምን ይመስላል የሚለውን ለማየት ያስችላል::
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ሰርሞሎ በንግድ ስርዓት የሚስተዋሉ ችግሮችን ከመሰረታቸው ለመቅረፍ ባለፉት ዓመታት የተለያዩ ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል:: በኔትወርክ መሰረተ ልማት ዝርጋት፣ በሲስተም ማበልጸግ እና በሌሎች አቅም ግንባታ ረገድ ኤጀንሲው ውጤታማ ስራዎችን ሰርቷል:: በቅርቡ የተጀመረው የንግድ እና የገበያ ትንተና መረጃ ስርዓት ፕሮጀክት የከተማዋን የአገልግሎት አሰጣጥ ከፍ ወዳለ ደረጃ የማድረስ አቅም ያለው ነው::
ሲስተሙ ለንግድ ዘርፍ ከፍ ያለ ፋይዳ ይኖረዋል:: የንግድና የገበያ መረጃ ትንተና በማከናወን እንዲሁም ህብረተሰቡ በየወቅቱ ያለውን የገበያ ሁኔታ እንዲያውቅ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ከፍ ያለ ፋይዳ ይኖረዋል::
በአጠቃላይ 25 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ የሚሰራ እና በስምንት ወራት ለማጠናቀቅ የታቀደው ይህ ፕሮጀክት በከተማዋ አራት ቦታዎች በሚቀመጡ ትላልቅ ስክሪኖች አማካኝነት ወቅታዊ የገበያ መረጃዎችን ህብረተሰቡ አውቆ ኑሮ ውድነትን ለመቀነስ፤ ግልጽ፣ ተደራሽ እና ፍትሃዊ የንግድ ስርዓት እንዲኖር ያግዛል::
እስካሁን ባለው የፕሮጀክቱ ሂደትም የመረጃ ትንተና ስራዎች ተጀምሯል። ሲስተሙን የማበልጸግ ስራውና ለሲስተሙ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ወደ ሀገር ውስጥ እየገቡ ነው ::
ሲስተሙን ከኤጀንሲው በመውሰድ እያበለጸገ ያለው ድርጅት የፕሮጀክት ማናጀር አቶ ፋንታዬ መኮንን እንደተናገሩት፤ ፍትሃዊ ያልሆነ የንግድ ስርዓት በከተማዋ ውስጥ ችግር ሲፈጥር ቆይቷል:: አንዳንድ ሸቀጦች በከተማዋ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች በተለያዩ ዋጋዎች ነው የሚሸጡት:: ይህ የሚሆነው ከመረጃ ስርዓት ጉድለት ነው:: አዲስ የሚለማው ሲስተም ይህንን ችግር ለመቅረፍ ያስችላል:: ለገበያ መረጋጋት ወሳኝ ሚና ይኖረዋል:: ህጋዊ የንግድ ስርዓት እንዲዘረጋም ያደርጋል::
በከተማዋ የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም የከተማ አስተዳደሩ ችግሮች ውስብስብ፣ ስር የሰደዱና ተከማችተው የቆዩ ስለነበረ እስካሁን በመጣንበት መንገድ ችግሮቹን መፍታት እና ለውጥ ማምጣት አዳጋች ሆኗል። ስለዚህ የከተማ አስተዳደሩ አሰራሩን በቴክኖሎጂ የማዘመን፣ ዲጂታላይዝ የማድረግ፣ እንዲሁም ቴክኖሎጂውን ሊጠቀም የሚችል ብቃት ፣ ስነ ምግባር ያለው እና በእውቀቱ እና በክህሎቱ የዳበረ ባለሙያ የመፍጠር ስራ ወሳኝ መሆኑን የገለጹልን ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ሀላፊ ሀይሉ ሉሌ ናቸው::
የተለያዩ በቴክኖሎጂ የማዘመን ስራዎችን በመስራት አሁን ከተማዋ ካለችበት ሁኔታ አንድ እርምጃ ወደፊት መውሰድ ወሳኝ ነው ያሉት አቶ ሀይሉ፤ የንግድና ገበያ ሶፍት ዌሩ በጣም ወሳኝና አሁን ያለውን አገልግሎት ወደፊት ለመውሰድ የሚያስችል ነው ብለዋል ። በሀገሪቱም በከተማዋም የሚስታዋለው የፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣም እንደተጠበቀ ሆኖ ውድድሩ ላይ የተመሰረተ የገበያ ስርዓት የለም:: ይህንን ሁኔታ ለማዘመን ተደራሽ የሆነ መረጃ ለህብረተሰቡ፣ ለሸማቹ እና ለነጋዴው በማቅረብ አጠቃላይ የንግድ ስርዓቱን ለማዘመን የሚጠቅም የቴክኖሎጂ ግኝት ነው:: የቴክኖሎጂ ግኝቱ ተፈላጊውን ጥራት ይዞ በታሰበለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ የሁሉም ርብርብ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል::
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር ዓባይ እንዳሉት፤ ኢንዱስትሪ፣ መሰረተ ልማት እና የቴክኖሎጂ ልማቱ የከተማ አስተዳደሩ ልዩ ትኩረት የሚሰጣቸው ሶስት መሰረታዊ ነገሮች ናቸው:: የቴክኖሎጂ ማስፋፋት ትኩረት ከሚሰጠው ሶስቱ አንዱ ቢሆንም ቴክኖሎጂ ላይ ሰፊ ስራ አልተሰራም:: በብዙ ቦታዎች አገልግሎቶች ከሰው ንክኪ ነጻ የሆኑ እና በቴክኖሎጂ የተደገፉ አይደሉም:: ስለዚህ ብዙ ስራዎችን መስራት ይጠይቃል::
አዲስ የሚተገበረው ሶፍት ዌር የቅሬታ ምንጭ ከሆኑት አንዱ የሆነውን በንግድ ላይ የሚታዩ ችግሮችን በመቅረፍ ፍትሃዊ ንግድ ለማስፈን ከማስቻሉም ባሻገር ንግድን በቴክኖሎጂ ለማስደገፍ ያግዛል፤ ስርዓቱ ወደ ስራ ሲገባ በአንድ በኩል አገልግሎቱን ያፋጥናል፤በሌላ በኩል ሰው መረጃ አግኝቶ ወደ ልማት እንዲንቀሳቀስ እድል ይፈጥራል ብለዋል::
አዲስ የሶፍት ዌር ልማት ስትራቴጂ ተግባራዊ እያደረገ ነው:: በንግድ ዘርፍ የሚስታዋሉ የህብረተሰቡን ቅሬታዎችና ብልሹ አሰራሮችን ይቀርፋል:: ህጋዊ የንግድ ስርዓት እንዲዘረጋና የአሰራር ግድፈቶች እንዲታረሙ እገዛ ያደርጋል ሲሉ ተናግረዋል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 4/2013