እድገቱ ደብረ ብርሀን ከተማ ነው።በሥራ ምክንያት ወደ ጎንደር፤ ከጎንደር ወደ ባህርዳር ከዚያም ወደ አዲስ አበባ ተዘዋውሯል።በአማራ ክልል የቴአተር ቡድን ውስጥ ለዘጠኝ ዓመታት በኃላፊነት ሰርቷል። ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በቋንቋና ሥነ ጽሁፍ ዲፕሎማ በማግኘት ወደ አዲስ አበባ አቅንቶ የቴአትሪካል አርት ትምህርቱን ተምሮ ተመርቋል።በወቅቱ ራስ ቴአትር ተቀጥሮ በተዋናይነት፣ በቴአትር ክፍል ኃላፊነት፣ በህዝብ ግንኙነትና ኪነ ጥበብ ልማት በመሳሰሉት ኃላፊነቶች አገልግሏል።
በባህልና ቱሪዝም የአሥሩም ክፍለ ከተሞች ዋና የሥራ ሂደት መሪ በመሆን አገልግሏል።ከዚያም በኢትዮጵያ ቋንቋና ሥነ ጽሁፍ የማስተርስ ዲግሪውን መያዝ ችሏል። በአሁኑ ወቅት በፎክሎር የትምህርት ዘርፍ የሦስተኛ ዲግሪውን ለመያዝ የመጨረሻ ምዕራፍ ብቻ ቀርቶታል። ደራሲና የባህል ትውፊት ጉዳዮች ተመራማሪው አንዱዓለም አባተ (የአፀደ ልጅ)
የግጥምና የቴአትርን ጨምሮ ያሳተማቸው መጽሐፍት ወደ 22 ይደርሳሉ።ከእነዚህ ውስጥ እንደ ፍቅርና መዳፍ፣ ንጉሥ ዘርዓያዕቆብ፣ የህሊና መንገድና መኤኒት መጻህፍት ይጠቀሳሉ።ከ200 በላይ የቴሌቪዥንና ከ200 በላይ አጫጭር የራዲዮ ድራማዎችን ጽፏል። አንዱዓለም አባተ (የአፀደ ልጅ) የኪነ ጥብበ መምህርም ነው።በአቢሲኒያ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በሌሎች ኮሌጆች ከማስተማርም ባሻገር በተጋባዥነት የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ሥልጠናዎችን ሰጥቷል።
ደራሲ አንዱዓለም፤ ከተለምዶ ወጣ ባለ መልኩ በመጠሪያ ስማቸው ላይ የእናታቸውን ስም ከሚያካትቱ ኢትዮጵያዊያን አንዱና ግንባር ቀደሙ ነው።የዚህ ምስጢሩ ሁለት ነገሮች መሆኑን የሚናገረው ደራሲው፤ አንድም አምጠን ካልወለድናቸው በቀር የእናቶቻችንን ውለታ መክፈል ስለማይቻለን እናትን ማስጠራት ተገቢም አስፈላጊም ነው ብሎ በማመኑ የእናቱን ስም ማስቀደሙን ይጠቅሳል።በሌላ በኩል በቤተሰባቸው “የመጽሐፍ” ጉዳይ የረጅም ዓመት ታሪክ ያለው በመሆኑና ከአያት ቅድመ አያቶቹ ጀምሮ ይጽፉ ስለነበሩ፤ ያም የመጣው በእናቱ በኩል ስለሆነ የእናቱን ስም ማስጠራት እንዳለበት አምኖ ያደረገው ስለመሆኑ ይገልጻል።
ባለ ትዳርና የሦስት ልጆች አባት የሆነው ደራሲ አንዷለም አባተ (የአፀደ ልጅ)፤ ባለፉት አምስት ዓመታት መገዘዝ መልቲ ሚዲያና የቴአትር ፕሮዳክሽን በማቋቋምና ሥራ አስኪያጅ በመሆን ከሥነ ጽሁፍ፣ ከቴአትርና ከፎክሎር ጋር የተገናኙ ምርምሮችና ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል።
በአንዱ ዓለም አባተ (የአፀደ ልጅ) የሚመራው መገዘዝ መልቲ ሚዲያና የቴአትር ፕሮዳክሽን፤ በዋናነት በቴአትር ዘርፍ ላይ የተለያዩ ሥራዎችን ይሰራል።ለአብነትም ከወልዲያ፣ ደብረ ብርሀን፣ ጎንደር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የበዓል ፕሮግራሞችንና ሌሎች ኪነ ጥባባዊ መድረኮችን በማዘጋጀት ሰርቷል። በተለይ በደብረ ብርሀን ህዝቡ ታሪኩንና ባህሉን እንዲያወቅ ከኪነ ጥበብ ጋር የቀረበ ቁርኝት እንዲኖረው የተወሰኑ አንጋፋና ታዋቂ ሰዎች በመውሰድ ልምድ እንዲሰጡ አድርጓል። ለረጅም ጊዜ የቆየ የሥነ ጽሁፍ ምሽቶችንም አካሂዷል። በቴሌቪዥንና በራዲዮም ልዩ ልዩ የበዓል ፕሮግራሞችን መስራት ችሏል። ወጣቶች የሥነ ጽሁፍ ሥራቸውን እንዲያወጡ እገዛ አድርጓል። አስፈላጊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መልቲ ሚዲያው የራሱን እገዛ እያደረገ ይገኛል።
የወደፊት ትልም
በአሁን ወቅት አንድም በኮቪድ በሌላ መልኩ ባለመረጋጋት ረጅም ጊዜ ከመቆየታችን የተነሳ ኪነ ጥበቡ የተዳከመበት ጊዜ መሆኑን የሚናገረው አንዱዓለም፤ ለወደፊት በርካታ ስራዎችን ለመሥራት እንቅስቃሴ ላይ መሆኑን ይገልጻል።“አገሪቷ ሠላም ሆና 2014 ዓ.ም ላይ በበርካታ ሥራዎች እንመጣለን ብለን ነው የምናስበው” በማለት፤ ለዚህም ዝግጅቶችን እያደረገ መሆኑንና የተቋረጡ የሥነ ጽሁፍ መድረኮችን እንደሚያስቀጥል፤ ሥነ ጽሁፍን የተመለከቱ አጫጭር ሥልጠናዎችንም አጠናክሮ እንደሚያስኬድ ነው የሚናገረው።
የእረፍት ውሎ
“ብዙም እረፍት የለኝም።አረፍኩ ከተባለ ሥራ በመቀየር ነው የማርፈው። የእረፍት ጊዜን የማሳልፍበት ነው ቢባል ግን ከምንም በላይ ረጅም መንገድ ጉዞ ማድረግ ያስደስተኛል። ማታም ሆነ ጠዋት በእግር እጓዛለሁ።በዚያ መጓዝ ውስጥ ሀሳቦችን አፈልቃለሁ። ከዚያ ውጭ ለራሴ የሰጠሁት የእረፍት ጊዜ የለኝም። አብዛኛውን ጊዜ በሥራ ስለማሳልፍና ጉዳዮቼ ብዙ ስለሆኑ ቀኑ አይበቃኝም። የእረፍት ጊዜ ለማግኘት መወጣት ያሉብኝን ጉዳዮች ነው የማከናውነው።አስቀድሜ ፕሮግራም በማውጣት ከእኔ ጋር ያለውን መስተጋብር በማስታረቅ ነው የምኖረው።
ሣምንቶችን በአብዛኛው በሰዓት በተገደበ ሁኔታ ነው ሥራ የማከናውንባቸው። ከዚህ የምትተርፈኝን ነገር ከልጆች ጋር ጉዞ የማደርግባት ናት። በተለይ ዘወትር እሁድ ጠዋት ቤተክርስቲያን እንሄዳለን። ይህ የእረፍት ጊዜዬ ነው። ማታ ላይ ደግሞ ልጆችን ይዤ የእግር መንገድ ጉዞ እናደርጋለን። በምናደርገው የጉዞ ፕሮግራም ውስጥ እየተጫወትን፣ እየዘፈንን እየተሳሳቅን ተረት እያወራን እንቆቅልሽ እየተጠያየቅን እንሄዳለን። ይኼንን ነው እንደ እረፍት አድርጌ የማሳልፈው” ሲል የእረፍት ውሎውን በአጭሩ አስቃኝቶናል።
“በአብዛኛው ሥራዬ እረፍቴ ነው” የሚለው ደራሲው፤ ሥራው በአብዛኛው ማንበብና መጻፍ ስለመሆኑ ገልጾ፤ አንዳንዴ የጻፈውን አርትኦት ለመስጠት ከተማ ሊቀይር እንደሚችል ይናገራል።እንደ ናዝሬት፣ ሀዋሳ፣ ባህርዳርና ደብረ ብርሀን ወዳሉ ከተሞች ለዚሁ ዓላማ ሊሄድ እንደሚችልም ይጠቅሳል። ይህም ለእርሱ እንደ እረፍት የሚታይ ነው። “የአርትኦት ሥራ እንድሰራ ከመጣና ከሰዎቹ ጋር በክፍያ ከተስማማሁ አርትኦቱ 15 ቀናት እንዲፈጅ አላደርግም።ለሁለት ቀናት ወደ አንድ ቦታ ሄጄ አይኔ ጥሩ ነገር እያየ የተወሰነ ሥራ ሰርቼ ተራራም ጫካም ካለ በተገኘው ሥፍራ በመሆን እሰራለሁ። ውሃም ካለ፤ ውሃ ዳር በመቀመጥ አሳልፋለሁ። ጣና ላይ ጥሩ ጊዜ ስላሳለፍኩ ውሃ ዳር መቀመጥ ያስደስተኛል። ውሃ ዳር መመሰጥ ማሰላሰልም እንዲሁ ያስደስተኛል።በተገኘው አጋጣሚ ወጣ ብዬ እንዲህ የማድረግ ልማድ አለኝ” ይላል ደራሲው።
ደራሲ አንዱዓለም ይህንንም አበክሮ ይናገራል። “ሥራዬን እደሰትበታለሁ። አንዳንድ ሰው ቢሮ እንደማይገባ ሲያስብ ይደሰታል። እረፍቴ ነው ብሎ ያስባል። እኔ ደግሞ ቢሮዬ ጭንቅላቴ ስለሆነ እረፍቴ በልቤ ውስጥ ስለሆነ ሁልጊዜ ሥራ፤ ሁል ጊዜ እረፍቴ ነው። የሚወዱትን ሥራ መስራት ለዚህ ነው የሚያግዘው። ሥራዬ እረፍቴና መዝናኛዬ ስለሆነ ያሳርፈኛል። ጭንቀት የለብኝም።ብዙ እንቅልፍ የለኝም።በቀን ከአራት ሰዓታት በላይ እንቅልፍ አላውቅም።”
መልዕክት
ደራሲው እንደሚለው፤ አሁን ጥሩ ዘመን ላይ ነን።ምክንያቱም ዘመኑ ሁለተኛው የኢትዮጵያ ሚሊኒየም የውሃ ዘመን ነው። የመድኃኒት ዓመትም ነው። በብዙ ችግሮችና መከራዎች ውስጥ አልፍን የምንወጣበት የበራ ዓመት ነው። በዚህ ውስጥ በተቻለ መጠን ልባም መሆን፣ በጽናት መጓዝ፣ ማስተዋል፣ ያስፈልጋል።
እንደ አገር ሲታሰብ ከፊታችን ያለው ምርጫና የውሃ ሙሌቱ የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ ላይ የሚያሳድሩት አሻራ ትልቅ ነው። ስለዚህ ጠንክረን፣ ተጋግዘንና ተቻችለን ይኼንን ቀን በማለፍ ለልጅ ልጆቻችን የሚተርፍ መልካም ሥምና ተግባር ትቶ ማለፍ ግድ ይላል። ምክንያቱም ይኼን ጊዜ ካጣናው መልሰን ለማግኘት ሌሎች መቶና ሺህ ዓመታትን ሊጠይቅ ይችላል።
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2013