በመንድር ውስጥ የሚኖር እድሜ ጠገብ ዛፍ አለ። ዛፉ ለብዙዎች ጥላ ሆኖ ያገለግላል። የአካባቢው ሰው ሸንጎ የሚቀመጠውም በዚሁ እድሜ ጠገብ ዛፍ ስር ነው። እድሜ ጠገብነቱ የአካባቢው ግርማ ሞገስ አድርጎታል። አንድ ቀን በዛፉ ስር ሸንጎ ሲደረግ ውሎ ማምሻው ላይ የዛፉ ቅርንጫፍ፣ ግንዱና ስሩ መነጋገር ይጀምራሉ። ጨዋታውን የጀመረው ሥሩ ነበር።
“ግንድና ቅርንጫፍ እንደምን አመሻችሁ፤ የዛሬው ሸንጎ ላይ የቀረበው ንትርክ በጣም አበሳጭቶኛል። ሁልጊዜም የሰዎችን ንትርክ እየሰማሁ መኖር በጣም ሰልችቶኛል። እናንተ እራሳችሁን ችላችሁ ያለ እኔ ደግሞ መቆም አትችሉም። እናንተን ጥዬ የትም መሄድ ባለመቻሌ ባዝንም እኔ ግን ከአከባቢው ለመጥፋት አስባለሁ፤ ራሴንም ችዬ ኑሮ እመሰርታለሁ፤ ከጭቅጭቅና ከንትርክ የጸዳ ኑሮን መኖር እፈልጋለሁ። ደግሞም እኔ ሥር፣ መሬት ውስጥ ስለምኖር ማንም ሳያየኝ ለብቻዬ ተደብቄ መኖር የምችልበት ቦታ ላይ ሄጆ ብኖር እችላለሁ” አላቸው።
ቅርንጫፍና ግንድ ከሥር የመጣላቸው መልእክት እጅግ አስደነገጣቸው። ለረጅም ዘመን በፍቅር ሲኖሩ ይህን የመሰለ የመለያየት ሃሳብ ገጥሟቸው አያውቅም ነበር። ግንድ ከሥር ቀበል አድርጎ “ወዳጄ ሥር ምን ሆነሃል እንዴት ይህን ያህል ዘመን አብረን ስንኖር መለያየትን ሳናስብ ኖረን እንዴት ዛሬ ከእኛ ተለይተህ የምትኖረው የተመቻቸ ኑሮ ታየህ?” ብሎ ይመልስለታል። ሥርም ምክንያት ብሎ ያቀረበው በዛፉ ስር የሚሰበሰበው ሸንጎ ከቀን ወደ ቀን ጭቅጭቅ የሞላበት መሆኑ ያስመረረው መሆኑን ይገልጻል። ቅርንጫፍ ቀጥሎ “እኔ ሲገባኝ ዋናው ምክንያቱ እርሱ አይመስለኝም፤ አንድ ቀን እንዲሁ ለእኔ ለብቻ አማረህ የነገርከኝ ነገር ነበር። እናንተን ሁሉ ተሸክሜ ያለሁት እኔ ነኝ፤ እኔ ባልኖር እናንተ መኖር አትችሉም ብለሃል ስለዚህ ዋናው ጉዳይ ለራስህ የሰጠኸው ትርጉም ነው።” አለው። ሥር በዚህ ጊዜ ደነገጠ። የውስጡ ሃሳብ ስለታወቀበት ተንተባተበ። በዚህ ሁኔታ ሁሉም በኀዘን ውስጥ ሆነው ዝም ተባባሉ።
ከቆይታ በኋላ ቅርንጫፍና ግንድ እርስ በርሳቸው መንሾካሾክ ቀጠሉ። ግንድ ለቅርንጫፍ ዝም ብሎ እኮ ነው ሥር የሚያስፈራራን። እኔ ከእነርሱ እሻላለሁ የማለቱን ሃሳብ ስለታወቀበት ተናዷል። ቅርንጫፍ ሚስጥሩን ባታውቀው ኖሮ እንዴት ልንሸወድ ነበር። ቅርንጫፍም ቀበል አድርጎ አይገርምህም ግንድ እኔም እኮ የገረመኝ እርሱ ነው። ሥር ከእኛ በተሻለ ሁኔታ በዛፍ ስር የሚሰበሰቡ ሰዎች የሚያወሩትን ስለሚያውቅ እኛ ላይ ክፉ ማሰብ አልነበረበትም። በድብቅ እኛ ላይ ከሚያደባ እኮ ችግሩን አቅርቦልን እንፈታለት ነበር። ግን በሂደት እኔ ብቻ ነኝ በሚል ትእቢት ራሱን ልዩ አድርጎ በማሰቡ ተሳሳተ። ሆሆሆ
ሥር የግንድና ቅርንጫፍ ማንሾካሾክ እርሱን ማእከል ያደረገ እንደሆነ ልቦናው ነግሮታል። በሁኔታቸው አዝኖ አኮረፈ። እነርሱ በእኔ ላይ እንዲህ የሚንሾካሾኩ ከሆነ ቆይ የማደርገውን እኔ አውቃለሁ። እኔ ለእነርሱ እልነግርም፣ አላስደነግጣቸውም፤ ያልኩትን ሚስጥሬን ሁሉ ይዤ ዝም ነው የምለው። እኔ እንደሆንኩ አፈር ውስጥ ነው ያለሁት ምንም አልሆንም አለ። በዛፉ ስር እየተሰበሰበ የሚሞገተው ሸንጎ የሚነጋገረው ስለ ግዙፉ ዛፍ እጣ ፈንታ ነበር። አንዳንዶቹ የሸንጎው አባላት ዛፉ ተቆርጦ የሚወጣው መንገድ ይቅርብን ሲሉ፤ ሌሎች ደግሞ ለአከባቢያችን መሰረተ ልማት አስፈላጊ ስለሆነ የምንወደው ግዙፍ ዛፍ እንዲቆረጥ መወሰን አለብን የሚል ነው። ይህን ነገር የሠማው ሥር ነው። ግንድም ቅርንጫፍም አልሰሙም። በሥር ላይ ግንድም ቅርንጫፍም ባይንሾካሾኩ ኖሮ ሥር ሊነግራቸውና በጋራ ከመጥፋት የሚድኑበትን መንገድ ሊፈልግ አስቦ ነበር።
ሸንጎው የመጨረሻውን ስብሰባ ለማድረግ ተሰበሰበ። መስማማት ስላልተቻለ በድምጽ ብልጫ እንዲወሰን ተጠየቀ። በድምጽ አሰጣጡም ዛፉ ተቆርጦ መንገዱ ይሰራ የሚሉት አሸነፉ። በሸንጎው ያሉ ሦስት ዛፍ በመቁረጥ ገቢያቸውን በማግኘት የሚተዳደሩት የአካባቢው ነዋሪዎች ዛፉ መቆረጥ አለበት ከሚሉት መካከል ተሰለፉ። ግዙፉ ዛፍም እንዲቆረጥ፤ እኒህ ሦስት ዛፍ በመቁረጥ የሚተዳደሩትም ስራውን እንዲሰሩ ተወሰነላቸው።
ግንድና ቅርንጫፍ አሁንም ይንሾካሾካሉ። ሸንጎው ምን እያወራ እንዳለ ባያውቁም ሥር እንግዲህ ዛሬ እንደለመደው ሊያማርር ነው፤ የእርሱ ነገር በቃ ሸንጎ በቀረበ ቁጥር መነጫነጭ ሆኗል እያሉ አሙት። ሥርም ማንሾካሾካቸውን እየሰማ የሚጠብቅሽን አታውቂም እኔ እንደ ሆንኩ መሬቱ ውስጥ ስለምሆን ምንም አልሆንም ሲል ለራሱ ተናገረ።
በነጋታው ማለዳ ሦስቱ ዛፍ ቆራጮች ዛፉ ላይ ተሰማሩ። በእቅዳቸው መሰረት ቅርንጫፉን መቆራረጥ፣ ግንዱ ላይ መውጣት መውረድ፣ መጥረቢያቸውን ሥራ ላይ ማዋል ቀጠሉ። ቅርንጫፎቹ መጯጯህ ቀጠሉ፣ ግንድም እየሆነ ያለው ምንድን ነው? እረ አንድ ነገር እናድርግ፤ ምንድነው ነገሩ? እያለ ወከባ ውስጥ ገባ፤ ሥሩ ግን የሚያውቀውን ይዞ ይስቃል። ዛፉም ተቆርጦ አለቀ። ሥሩ ቀረ። የዛፉን ሥራስር ለተለየ ጉዳይ የፈለገው ነጋዴ ስለነበር የዛፉ ሥር እየተፈለገ ተበጣጠሰ። ሥሩ፣ ግንዱና ቅርንጫፉ አንድ ላይ ሆነው ግዙፉ ዛፍ ተብሎ የሚታወቀው ዛፍ ታሪክ ሆነ። በነበር የሚጠራ ታሪክ። ጥበብን መጥራት የተሳነው አሳዛኝ ዛፍ!
ጥበብ፣
“የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው” የሚለው የጠቢቡ ሰለሞን ምሳሌ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ተጽፎ በስፋት ይታያል። ጥበብን ፈጣሪን በመፍራት ውስጥ መፈለግ እንደ ኢትዮጵያ ላለ ሃይማኖተኛ ህዝብ ውስጥ ትርጉሙ ብዙ ነው። ዛሬ ስለ ጥበብ ስናነሳ መነሻ ባደረግነው ታሪክ ውስጥ እናተኩራለን።
ሰሞነኛው የኢትዮጵያ ሁኔታ ዜጎችን በእጅጉ የሚያሳስብ እንደሆነ ለሁላችንም ግልጽ ይመስላል። አሜሪካ የወሰደችው የጉዞ ማእቀብ በማህበራዊ ሚዲያም በሌሎችም ሚዲያዎችም ሰፊ መወያያ ሆኗል። ለሚዲያዎች ቃላቸውን የሰጡ ኢትዮጵያውያን ያሉበትን ስጋት ሲያንጸባርቁ በተደጋጋሚ ከሚነሱ ቃላት መካከል አንዱ ጥበብ ሆኗል። ነገሮችን በጥበብ ለማለፍ መስራትን የሚመክሩትን አድምጠናል። ጥበብን ማሰብ የተገባ መሆኑን መስማት የምንችል ቢሆንም ጥበብን አስበን በተግባር ምን እንፈጽም የሚለው ግን ምላሽ ይፈልጋል። አሜሪካ ያለችውን ተቀብሎ መሄድ ነው ጥበብ? ወይንስ ያለንበትን ነባራዊ ሁኔታ መርምሮ ወደፊት መራመድ።
የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት እንደሆነ ለሚያምን ግለሰብ የጥበብ መጀመሪያ አሜሪካንን መፍራት ሆኖ ሊገለጽ አይችልም። እንደ ሀገር ልንከተል የሚገባውን ለመሪዎች ማስተዋል እንዲሆን ሁላችንም በጸሎት መሆን እንዳለብን ማሰቡ ተገቢ ነው። ከጸሎት ባሻገር እያንዳንዱ ዜጋ ጥበብን የተከተለ ኑሮን መኖርም ይገባዋል። ጥበብን አስበን ልንከተለው የሚገባውን ሃሳብ ከመነሻ ታሪካችን ውስጥ ሁለት ነጥቦችን አንስተን እንመልከት፤
1. የጋራ ህልውናን የመረዳት ጥበብ
የዛፉ አካልና ስጋዎች ማለትም ሥር፣ ግንድ እና ቅርንጫፍ ዛፍ የተሰኘ የጋራ ህልውና እንዳላቸው አልተረዱም። የጋራ ህልውናቸውን መረዳት ባለመቻላቸው በመካከላቸው የነበረው መለያየት ወደ መጥፊያቸው አደረሳቸው። በምናባችን የሳልነው የሥር፣ የግንድና ቅርንጫፍ የእርስ በርስ ግንኙነት የጋራ ህልውናን ከተናጥል ህልውና አንጻር መረዳት ቢቻል የተሻለ ይሆናል።
የጋራ ህልውናቸውን ማእከል ያደረገ እንቅስቃሴ ማድረግ ያልቻሉ ሀገራት በጥቂት ዓመታት ውስጥ በመሠረታዊነት ስፍራቸውን ሲለቁ ተመልክተናል። ያ እጣ ለእኛም እንዳይደርሰን ሁላችንም ለራሳችን የምንሰጠው ግላዊም ሆነ ቡድናዊ ቦታ እንዳለ ሆኖ ለጋራ ህልውና ስፍራን መስጠት ይገባል።
ጥበብ በጋራ ህልውና ውስጥ ስራዋን ትፈጽም ዘንድ ነገሮችን በአስተውሎት ማድረጉ ለሁሉም አዋጭ ነው። በብሄርና በእምነት እየተባላን ክቡሩን የሰውን ልጅ ህይወት አቅልለን ስንመላለስ እንዴት የጋራ ህልውናችንን ማስጠበቅ እንችላለን? ብለን መጠየቅ አለብን። ሁሉም የሰው ልጅ በፈጣሪ ፊት እኩል እንደሆነ ማመን አለብን። እምነታችን ይህ ከሆነ በጋራ ስንኖር እንዴት ሁላችንም በሰውነት የሚገባንን ቦታ አግኝተን እንኑር? የሚለውን ማሰብ አለብን። ሥሩም፣ ግንዱም ሆነ ቅርንጫፉ መኖራቸው ለዛፉ በሙላት መኖር የግድ መሆኑን መረዳት ይኖርብናል።
በትዳር ውስጥ ባልና ሚስት በተናጥል ካላቸው ህይወት ባሻገር የጋራ ቤተሰባዊ ህልውናቸውን መገንዘብ አለባቸው። ይህ ሲሆን የጎደለው እንዲሞላ፤ የወደቀው እንዲነሳ፤ የላላው እንዲጠነክር እድልን ይሰጣል። በምንሰራበት ተቋምም ውስጥ ይሁን በጉርብትና ለጋራ ህይወታችን ልንሰጠው የሚገባውን መስጠት አለብን።
2. ችግርን በወቅቱ የመፍታት ጥበብ
ችግር አልባ ህይወትን ለመኖር የሚያስብ ሰው ምድር ፈጽሞውኑ ለእርሱ አትሆንም። ምድር ላይ በየትኛውም ጊዜ በየትኛውም ቦታ ችግር አለ። ችግርን መፍታት ደግሞ የግድ የሚል። የሚገጥመንን ማንኛውንም ችግር በመርህና በእውነት ውስጥ ሆኖ ለመፍታት መራመድ ጥበብን ይሻል። ችግር አልባ የሆኑ ዓመታት እንደሚመጡ ከመጠበቅ ችግርን በወቅቱ በመፍታት ጥበብ የማደግን ጊዜ መናፈቅ ይሻላል። በችግር ውስጥ ያለ ትዳርን ለማስማማት በሚደረግ ጥረት ውስጥ አስቸጋሪ የሚሆነው ነገር የችግሩ መነሻ ሳይሆን ችግሩ መሰንበቱና፤ ችግሩ በሰነበትበት ጊዜ ውስጥ የሚፈጥረው ቁስል ነው።
ችግርን በወቅቱ መፍታት እንደ ሀገር ያስፈልጋናል፤ እንደ ቤተሰብም እንዲሁ። ከትውልድ ትውልድ መልካም እሴቶች እንጂ ያደሩ ችግሮች ሊተላለፉ እንዳይገባ ማሰብ አለብን። ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አስተማሪዎች ምእመን ተኮር ወይንም የተወሰነ አካባቢ ተኮር ከሆነ አገልግሎታቸው ባሻገር ማህበረሰባዊና ሀገራዊ ጤንነትን ሊያመጡ የሚችሉ ችግር አፈታትን ባህል እንድናደርግ ሊያግዙ ይገባል። ኢትዮጵያ የወጣት ሀገር ነች ብንል ማጋነን አይሆንም። ወጣቶች ደግሞ ለለውጥ ዝግጁ የሆኑ ሃይሎች ናቸው። ለውጥ ደግሞ ተንከባሎ ከመጣ ቁርሾ መውጣት ስለሆነ፤ ወጣቶችን ማእከል አድርጎ ተንከባሎ የመጣን ችግር ለመፍታት መስራት ይኖርብናል።
ኢትዮጵያን ለመቀራመት ከዚህ በፊት የተደረጉ ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች የከሸፉበት ምክንያት ኢትዮጵያውያን በአንድነት በመቆማቸው ነው። በጊዜ ሂደት ግን ሳይዘጉ እየተሸጋገሩ የመጡ ቁርሾዎች ሌላ ቁርሾ እየፈጠሩ ዛሬ ላይ ደርሰናል። ዛሬ እንደ ሀገር የገባንባቸው ፈተናዎች ሥራቸውን ፈልገን ለመፍታት ስናስብ ችግሮቹ ዛሬ የተወለዱ ሳይሆን የዓመታት ድምር ውጤት እና ተዘዋዋሪዎች መሆናቸውን እንረዳለን።
ግንዱ፣ ቅርንጫፉን ሥሩ ችግራቸውን በወቅቱ ከመፍታት ይልቅ በመንሾካሾክ መፍትሄን ለመፈለግ የሄዱበት መንገድ መጨረሻቸውን ድንገት ሁሉም እንዲጠፉ ያደረገ ነው። ዝቅ በማለት ውስጥ መውጣት ይቻላልና፤ ችግራችንን ዛሬውኑ ለመፍታት ባህል እናድርግ። ከመነሻ ታሪካችን ተጨማሪ የጥበብ መንገድን ትምህርት እናገኛለን። ለዛሬ በብዙ ጥሞና በብዙ ማስተዋል እያንዳንዳችን ወደ ራሳችንን እንድንመለከት ለመጠየቅ ጥበብን በመጥራት እጋብዛለሁ። ጥበብን እንጥራት መንገዷም የድል ነው። መልካም ጥሪ።
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2013