አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ሙስሊምና ክርስቲያን የመተሳሰብና የመከባበር እንጂ የመቃረን ታሪክ እንደሌላቸው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ኡለማ ምክር ቤት አባልና የሰላምና እርቅ ዘርፍ ኃላፊ ሼህ መሐመድ ሲራጅ ገለፁ።
ሼህ መሐመድ ሲራጅ 1442ኛውን የኢድ አልፈጥር በዓል መሰረት በማድረግ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለፁት ፤ ኢትዮጵያውያን አብሮነት እንጂ መለያየት ባህርያቸው አይደለም። ስልጣን ፈላጊ ሰዎች አልፎ አልፎ ሊያቆሳስሉን ይሞክራሉ። ሆኖም ይህንን የአብሮነት ማንነት የሚፈታተኑ የክፉ ጥሪ አድራጊዎችን አደብ ገዝታችሁ ቁጭ በሉ ማለት ያስፈልጋል።
በኢትዮጵያ የእስልምናና የክርስትና ውህደት ከቤት ይጀምራል ያሉት ሼህ መሀመድ፣ በርካታ ሙስሊምና ክርስቲያን ኢትዮጵያውያን በጋብቻ ጭምር ተሳስረው በአንድ ጣራ ስር በፍቅር እንደሚኖሩ አመልክተዋል።
እኔ “ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ነኝ፤ እኔ ኢትዮጵያዊ ክርስቲያን ነኝ” የሚል ሰው የፋሲካና የኢድን በዓል አከባበር ከሕዝቡ አኗኗር ጋር ያለውን ዝምድና ብቻ አይቶ መቃቃሩን ያጠፋል፤ፋሲካ ለክርስቲያኑ ቢሆንም ሙስሊም ጎረቤት ያለው ሁሉ አብሮ የሚያከብረው በዓል ነው። ኢድም ቢሆን እንዲሁ ክርስቲያን ጎረቤት፣ ቤተሰብ ያለው በአንድነት እንኳን አደረሰህ እየተባባለ የሚያከብረው በዓል እንደሆነ አስተውቀዋል።
በበዓል ወቅት አንዱ ለሌላው ደስታን መመኘት በራሱ አንድነትን ከመፈለግ የተለየ አይደለም ያሉት ሼህ መሐመድ፤ ኢትዮጵያዊ “በእምነት ተኮራርፎም ተለያይቶም አይታወቅም። የአብሮነት ባህልን ከፍ እያደረጉ ይሄዳሉ እንጂ” ብለዋል።
አልፎ አልፎ የሚፈጠሩ ችግሮች ከሌሎች የምንወስደውን ባለማወቃችን፣ መተጋገዝ ባለመቻላችን፣ በምክክር ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ ተቃራኒውን በማየታችን ነው ያሉት ሼህ መሐመድ፣ ኢትዮጵያዊ ያልሆነ ሙስሊም መጥቶ የአንተ ወገን ነኝና ተከተለኝ ሲለን ከመከተላችን በፊት እኔ ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ነኝ ማለት አለብን ብለዋል።
እንደ ሼህ መሐመድ ገለጻ፤ ማንነታችንን በአገራችን መግለጽ ከምንም በላይ ከችግሮች ያድነናል። ይሁንና ይህንን ስናደርግ አይታይም። በአገር ጥቅም ዙሪያ እምነትን ተታኮ የመጣ አማኝ ማስተናገድ ተገቢነት የለውም። እነርሱ በብዙ ነገር ሊሸረሽሩን ይፈልጋሉ። ግን መረታት የለብንም።
አንድነታችንን የሚሸረሽረው በዋናነት በመልካም ጎኑ ከመረዳት አሉታዊውን ማየት መፈለጋችን ነው የሚሉት ሼህ መሐመድ፤ መጥፎ ጎኖችን ነጸብራቅ እያደረጉ መልካሙን እየቀበሩ ያሉት ደግሞ አቅማቸውን ለማጎልበት ሃይማኖትን ወይም ብሔርን ተገን አድርገው የሚሰሩ አካላት እንደሆኑ ጠቁመዋል።
ስብከታችንም አሉታዊ መሆኑ አንዱ ተጽዕኖ ፈጣሪ ጉዳይ ነው የሚሉት ሼህ መሐመድ፤ ወጣት ችኩል ነው፤ ሁሉንም መንካትና ማየት ይፈልጋል። ጥሩ አድርገን ካልሳልነው ደግሞ ልማት፣ ጉልበት፣ የአገር ሀብት የሆነውን ወጣት እናጣዋለን። ይህ ሆነ ማለት ደግሞ ሰዎች ጧሪ ቀባሪ ያጣሉ፤ አገር ሰላሟ ይደፈርሳል፤ ተተኪ ትውልድንም በቀና አዕምሮ ማውጣት ይከብዳል ብለዋል።
ሼህ መሐመድ እንደገለጹት፤ በሃገራችን ከትውልድ ግንባታ ጋር በተያያዘ የሆነ ቦታ ላይ ያመለጠን ነገር አለ። ይህንን ደግሞ በማስተማር፤ በጥናት መመለስ ያስፈልጋል። ስለዚህም ወላጆች ከልጆቻቸው የጀመረ ሥራ መስራት አለባቸው። የሃይማኖት አባቶችም የሃይማኖት አስተምሯቸውን በሚገባ በአርአያነት ማስተማር አለባቸው። በትምህርት ቤት የሚሰጠውን ትምህርትም አስመልክቶ መንግስት በሚገባ ሊፈትሸው ያስፈልጋል።
እምነት በአለባበስ ሊለይ ይችላል እንጂ በተግባር አንድ ነው የሚሉት ሼህ መሃመድ፤ ዋና መሰረቱ መልካም ማድረግ፤ መልካሙን ሁሉ ማሰብና በዚያ መኖር ነው ብለዋል። አንድ ሰው አማኝ ነው አይደለም የሚያስብለውም ሥራው እንጂ ንግግሩ ወይም አለባበሱ እንዳልሆነ አስታውቀዋል።
ሼህ መሐመድ እንደተናገሩት፤ ሰዎች በእምነት ከኖሩ መደጋገፋቸውን ማንም ሊሸረሽረውና ሊነካው አይችልም። በብዙዎቹ የአገራችን ክፍሎች የሚታየውም ይኸው ነው። ሙስሊሙ ክርስቲያኑን ይጠብቃል፤ ክርስቲያኑም እንዲሁ ሙስሊሙ እንዳይነካበት ይከላከላል። ነገር ግን የሚታየው አሉታዊው ስለሆነ ይህንን ለማንሳት አልተቻለም።
ደካማ ሰዎች ድክመታቸውን የሚጠግኑት ብሔርን ወይም ሃይማኖትን ተገን በማድረግ ነው። አሁን እየታየ ያለውም ችግር የደካሞች ሰለባ መሆናችን ያመጣው ነው። ጥሩ ሰዎች የሚያስቀይማቸው ነገር ካለ በግልጽ ይናገራሉ። ለአቅም ማጎልበቻ ብሔራቸውንም ሆነ ሃይማኖታቸውን መጠቀሚያ እንደማያደርጉ አመልክተዋል።
ጥሩ ሰዎች መጥፎ ታሪክ አላስመዘግብም የሚሉ ብቻ ሳይሆኑ፤ የሚያስተሳስር የእምነት ስርዓቱን የሚጠብቅ ተግባር የሚከውኑም ናቸው የሚሉት ሼህ መሐመድ፤ ወገኖቼን በማቁሰል፣ በማድማት፣ ህይወታቸውን በመቅጠፍ ፤ ሀብታቸውን በመዝረፍ ታሪኬን አልቀብርም የሚሉም በመሆናቸው መጥፎ ተግባር ላይ አይሳተፉም ብለዋል። ጥሩ ሰዎች በፈጣሪ እንጂ በማንም መከለልም አይፈልጉም። አቅምና ጉልበታቸው እርሱና ሥራቸው ነው። ስለዚህም የመጥፎ ተግባር ከዋኞቹ አማኞች ሳይሆኑ ከዚያ ውጪ የሆኑ ናቸው ብለዋል።
አሁን ያለውን መፈናቀል፣ ሕይወት መጥፋት በብሔርና በሀይማኖት ተገን እንጂ በትክክል በህዝቡ ዘንድ ያለ እንዳልሆነ በማመን በአንድነት ለችግሩ መፍትሄ መስጠትም ከእያንዳንዱ ዜጋ እንደሚጠበቅ አሳስበዋል፡፡
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ግንቦት 5 ቀን 2013 ዓ.ም