አዲስ አበባ፦ በታላቁ የረመዳን ወር ከአንድነታችን የሚቀዳው መደጋገፍ፣ መተሳሰብ እና መረዳዳት ኢትዮጵያዊ መሰረቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጥሪ ቀረቡ
አቶ ደመቀ መኮንን ለ1442ኛ ጊዜ ለሚከበረው የኢድ አልፈጥር በዓል አስመልክቶ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ፣ ታላቁ የረመዳን ፆም በአማኞቹ ዘንድ ልዩ ሃይማኖታዊ ትርጉም ያለው ነው ብለዋል ።
በአንድ ወር የፆም ፀሎት ጊዜ ከዕምነቱ ውጭ ያሉ ወገኖቻችንን ጋር አንድነታችንን ይበልጥ ለማጥበቅ መልካም አጋጣሚ የፈጠረ ነበር ያሉት አቶ ደመቀ፣ መልካም አጋጣሚዎችን ተከትሎ በተለያዩ ጊዜያት በተዘጋጁ የኢፍጠር መርሃ ግብሮች ላይ ልዩነቶቻችን ሳይገድቡን ማዕድ የተጋራንባቸው መድረኮች የአብሮነታችን ውሃ ልክ ትክክለኛ ማሳያዎች ነበሩ ብለዋል።
በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር ተሰባስበን አንድነታችንን ይበልጥ የሚያጠብቁ እና የሚያደምቁ መርሃ-ግብሮችን አገራዊ መሠረት እና ይዘት እንዲኖራቸው የበለጠ መሥራት እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።
”ባሳለፍናቸው ጊዜያት በዜጎቻችን ላይ ያጋጠሙ አሳዛኝ ጥፋቶች እንዳይደገሙ እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ ከውስጥ እና ከውጭ ከገጠመን ፈተና በጥበብ ለመሻገር በፅናት መረባረብ ይኖርብናል” ያሉት አቶ ደመቀ ፣ አገራችን ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በተለየ የዜጎቿ ደህንነት እንዲጠበቅ፣ አንድነታቸው እንዲጠናከር እና እንዲደምቅ የሻተችበት ወቅት ላይ እንገኛለንም ብለዋል።
ይህ ታሪካዊ የለውጥ ጉዞ በልዩነቶቻችን ላይ ቆሞ ከመሳሳብ ይልቅ፤ አንድነታችንን በሚያፀኑ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ተጎጂ ወገኖችን የመደገፍና ዘላቂ ሰላም እውን የማድረግ ቀዳሚ ኃላፊነታችን ለመወጣት መንቀሳቀስ ይኖርብናል። በታላቁ የረመዳን ወር ከአንድነታችን የሚቀዳው መደጋገፍ፣ መተሳሰብ እና መረዳዳት ኢትዮጵያዊ መሰረቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ በአቅርበዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 5 ቀን 2013 ዓ.ም