አዲስ አበባ፦ የኢትዮጵያውያን ዕድል በእኛው እንጂ በሌላ በማንም እጅ እንዳልሆነ ለዓለም ማሳየት እንደሚኖርብን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስታወቁ። የታላቁ የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅም ግዙፍ የብልጽግና ፋና እንደሚለኩስልን ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ 1442ኛውን ሂጅሪያ የኢድ አል ፈጥር በዓል አስመልክተው ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸው እንዳስታወቁት፣ ክፉውን ጊዜ እንደ ዒድ ሶላት ሰብሰብ ብለን ልንጋፈጠው፣ የአንድነታችንን ልክ አሳይተን ልናልፍ ይገባል። በኅብረታችን የሚገጥሙንን ፈተናዎች እንደ ምንሻገራቸው ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያውያን ዕድል በእኛው እንጂ በሌላ በማንም እጅ እንዳልሆነ ለዓለም ማሳየት ይኖርብናል።
በፍቅር እንጂ በኃይል እንደማንንበረከክ፣ ለእውነትና ፍትሕ እንጂ ለመደለያ እንደማንገዛ እና ሀገራዊ ክብርና ጥቅምን አሳልፈን እንደማንሰጥ ታሪካችን ምስክር ነው ያሉት ጠቅላ ሚኒስትሩ ፣ የማንንም ሐቅ የማንሻ ሕዝቦች፣ የፍቅር እጃችን ብሎ ለሚመጣው እንግዳ አክብረን ተቀባይ፣ ለሚሳደደው መሸሸጊያ ጥላ ስለመሆናችን ከነቢዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) እና ተከታዮቻቸው የተነገረልን የምስክርነት ቃል ከበቂ በላይ ነው ብለዋል።
በታሪካችን ውስጥ ያኖርነውን ደማቅ አሻራ ሁሌም ሲያንፀባርቅ ይኖራል። እኛ ሌላ ማንም አይደለንም። የእናት አባቶቻችን ልጆች ነን። ቀደምቶቻችን ያቆሙልንን መልካም ስምና ጀግንነት ለማጠንክር እንጂ ለመናድ አልመጣንም። ተገዳዳሪዎቻችን ምንም ያህል ቢለፉ ፀንተን ለመቆም መወሰን እንዳለብን አመልክተዋል።
የዘንድሮውን ዒድ አል ፈጥር የምናከብረው ሀገራችን ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ በርካታ ፈተናዎች እንደተደቀኑባት እያስታወስን ነው። መዋኛችን ድፍርስ፣ መንገዳችን እሾህ የበዛበት መሆኑን እናውቃለን። በመንገዳችን ላይ እንቅፋቶችን የሚያኖሩ፣ ወደኋላ የሚጎትቱ፣ ተስፋችንን ሳናይ በፊት ተሰብረን እንድንወድቅ መሠረታችንን የሚገዘግዙ ኃይሎች፣ ከውጭም ከሀገር ውስጥም በርትተው የመጡበት ፈታኝ ጊዜ ነው ብለዋል።
የእስልምና አስተምህሮ እንደሚገልፀው አንድ ሰው ለራሱ ጥቅም ብቻ ቢኖር ሕይወቱ ትርጉም አይኖረውም። የሚኖርበት ማኅበረሰብ ተርቦ እሱ ጠግቦ ቢውል፤ ጎረቤቶቹ ተረብሸው እሱ ሰላም ቢሆን፣ ሀገሩ ተቸግራ እሱ ቢደላው፣ በዙሪያው ርኩስ ተግባራት በዝተው ስለእሱ ብቻ ቅድስና የሚያስብ ከሆነ ከአላህ ፈጽሞ እዝነትን አያገኝም። የእሱ ፃድቅ መሆን ሕዝብና ሀገርን ካላፀደቀ፣ የእሱ ከፍ ማለት ሀገርና ወገንን ከፍ ካላደረገ፣ የእሱ ስኬት ሀገርንና ማኅበረሰብን ስኬታማ ካላደረገ አላህን ማገልገሉ ብቻ ጽድቅ አያስገኝለትም። ይልቁኑም ለራሱ ብቻ የኖረ ሰው ቀድሞውን ባይወለድ እንደሚሻለው የእምነቱ ሊቃውንት ያስቀመጡት እውነት እንደሆነ አመልክተዋል።
አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሁኔታም ለግላችን ሳይሆን ለጋራ ህልውናችን እንድናስብ የሚያስገድደን፣ ከግል ምቾታችን በላይ ለጋራ ደኅንነታችን እንድንተጋ በእጅጉ ግድ የሚልበት ጊዜ ነው። በህዳሴ ግድብ እና ከፊታችን ባለው ምርጫ ምክንያት ሀገራችን ፈተናዎቿ በዝተው አይተናል። እነዚህ ሁለቱን ማሳካት ለእኛ ቀላል የማይባል የስኬት በሮችን እንደሚከፍቱልን እናውቃለን። ምርጫውን በስኬት ማከናወን አዲስ የዴሞክራሲ ምዕራፍ እንደሚከፍትልን ግልጽ ነው። የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅም ግዙፍ የብልጽግና ፋና እንደሚለኩስልን ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ያውቃል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 5 ቀን 2013 ዓ.ም