አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን በማጠናከር አገርን ለማፍረስና የህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማስተጓጎል የሚሰሩ ኃሎችን ሴራ ማክሸፍ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ተሟጋቾች አቶ ሙሳ ሼኮና ወጣት ሱሌማን አብደላ ገለጹ፡፡
አቶ ሙሳ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ የፖለቲካና የሀሳብ ልዩነት የሰው ልጅ እስካለ ድረስ የሚኖር በመሆኑ ልዩነታችንን ወደ ጎን ትተን በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ተመሳሳይ አቋም መያዝ ይገባናል ፡፡
ኢትዮጵያውያን የሃይማኖት፣ የብሔርና የሀሳብ ልዩነትን ወደ ጎን በመተው ተደራጅተን የአገራችንን አንድነት መጠበቅና የታላቁ ህዳሴ ግድብን ለፍጻሜ ማድረስ ይገባናል ብለዋል፡፡
ግብጾች ኢትጵያን ሰላም መንሳት የጀመሩት ቀድመው አስበውበት ነው ያሉት አቶ ሙሳ፤ ያልሆነ ፕሮፖጋንዳ በመንዛት ጎረቤት አገራት በእኛ ላይ እንዲነሱና ኢትዮጵያ በሁለተኛው ውሃ ሙሌት ያላትን አቋም እንድትቀይር እጇን ለመጠምዘዝ ጥረቶች ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡
ግብጾች ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲና በወታደራዊ መስኮች ያላትን አቅም ዝቅ አድርጎ የማየት ችግር አለባቸው፣ በቀላሉም ማሸነፍ የሚችሉ ይመስላቸዋል፣ እውነታው ግን እነሱን ጨምሮ ብዙ አገሮች በቅኝ ግዛት ስር እያሉ ኢትዮጵያ ጠንካራ አገር እንደነበረች አስታውሰዋል፡፡
እንደ አቶ ሙሳ ገለጻ፤ ግብጻውያን በመካከላቸው ምንም አይነት ልዩነት ቢኖራቸው በአባይ ጉዳይ ያላቸው አቋም ተመሳሳይ ነው፡፡ እኛም ልዩነቶች ቢኖሩብንም አንድነታችንን በማጠናከር በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን ጫና መቋቋም ይገባናል፡፡
የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ተሟጋች ወጣት ሱሌማን አብደላ በበኩሉ፤ ግብጾች ኢትዮጵያ ውስጥ የሚከናወነውን ነገር በአንክሮ ሲከታተሉ መቆየታቸውን ጠቁሟል፡፡ በህዝቦች መካከልም ልዩነቶችን በማስፋት ግጭት ለመቀስቀስ መንቀሳቀሳቸውንም ገልጿል፡፡
በተለይ በቅርብ ዓመታት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች የተጠኑና በገንዘብ ጭምር የሚደገፉ መሆናቸውን ያመለከተው ወጣት ሱሌማን፤ ይህንን ማክሸፍ የሚቻለው ህዝቡ ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኝና አንድነቱን እንዲያጠናክር በማድረግ መሆኑን አመልክቷል፡፡
አብዛኞቹ ማህበራዊ አንቂዎች በክልላዊ አጀንዳዎችና በፖለቲካ ልዩነቶች ተወጥረው ያንኑ ሲያራግቡ እንደሚውሉ አመልክቷል፡፡ ማህበራዊ ሚዲያ የሚጠቀም እያንዳንዱ ግብጻዊ ግን ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ ስለአባይ መልዕክት ሳይለጥፉ፤ ምሁራንም ስለ አባይ ሳይናገሩ አይውሉም ብሏል፡፡
ብዙሃን መገናኛ እውነታን ለዓለም ማድረስ እንዳለባቸው የተናገረው ወጣት ሱሌማን፤ ህዝቡም ከመንግስት ጋር ልዩነት ቢኖረው እንኳን አንድነትን ማጠናከር ይገባዋል ብሏል፡፡ የአገር ሉአላዊነትን ለማስጠበቅ መንቀሳቀስ ይገባል እንጂ፤ በብሔርና በሃይማኖት በማጋጨት ኢትዮጵያን ሊያፈርሱ ለሚፈልጉ ኃይሎች በር መክፈት እንደማገባ አሳስቧል፡፡
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 1 ቀን 2013 ዓ.ም