አዲስ አበባ:- የአንድ አገር ሉዓላዊነት መርሆዎችን ጠንቅቆ የሚያውቀው የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትን የሚጋፉ ቅድመ ሁኔታዎችን በመደርደር ከምርጫ ታዛቢነት ራሱን ማግለሉ ፈጽሞ የማይጠበቅ ውሳኔ እንደሆነ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተፈራ አስታወቁ፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት ፤ የአውሮፓ ህብረት የአንድ አገር ሉዓላዊነት መርሆዎችንና የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን ጠንቅቆ ያውቃል ፡፡ ለተፈጻሚነቱም ተቆርቋሪ መሆን ይገባዋል፡፡
ምርጫን ለመታዘብ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የሚጥል፣ አድሎአዊነት የሰፈነበትና መርህን ያልተከተሉ ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጡ የሚያሳዝን ከስተት መሆኑን የገለጹትረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል፣መንግሥት በተለይ ከቴሌኮሙኒኬሽን ጋር ተያይዞ የአገርን ደህንነት የሚፈታትኑ መሳሪያዎች እንዳይገቡ መከልከሉ ተገቢና የትም አገር የሚደረግ ክልከላ ነው ብለዋል፡፡
‹‹የአገሪቱ መልካም ነገሮች አይጥማቸውም፣ ውሳኔውም ሚዛኑን የሳተ ነዉ›› ያሉት ፕ/ር ሳሙኤል፤ ህብረቱ ዓላማው እስከተሳካ ድረስ ጨቋኝ የነበሩ አፍሪካ መንግሥታትን ሲደግፍ ነበር፣ በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት በተደረጉ ምርጫዎችም በእነሱ ታዛቢነት ስር መንግሥት ኮሮጆን በመስረቅ መቶ በመቶ ሲያሸንፍ ያሉት ነገር እንዳልነበረ አመልክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ገለልተኛ ምርጫ ቦርድ አቋቁማ እየሰራች ባለችበት ሁኔታ ህብረቱ ስለምርጫው ገለልተኝነት አስቀድሞ መጠየቁ ያሳፍራል ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ፣ ይህ አይነቱ አሰራር በየትኛውም የአውሮፓ አገር ያልተለመደ ነው ብለዋል፡፡ የህብረቱ ውሳኔ በተጨባጭ ሲፈተሽ ሌላ የፖለቲካ ዓላማ ያነገበ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
ምርጫ በአውሮፓ ሲደርግ ለታዛቢነት እንደማይጋብዙ እያወቁ፣ ሲጋበዙ ግን ከቆሙት ዓላማ በተቃራኒ ችግር እንደሚፈጥሩ የጠቆሙት ፕ/ር ሳሙኤል፤ ዓላማቸው ግብ ካልመታ ስም ማጥፋትና የኢኮኖሚ ተጽእኖ በማድረግ እንደሚታወቁም አስታውቀዋል፡፡
እንደርሳቸው ገለጻ፤ የአፈጻጸም ችግር ቢኖርባትም ታዛቢ ከሚባሉት አንዳንድ አገር ቀድማ ያጸደቀቻቸውን ድንጋጌዎችና ስምምነቶችን ታከብራለች፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ኃይሎች ኢትዮጵያ ደካማ መንግሥት እንዲኖራትና በቅኝ ገዥ ፍላጎት ስር እንድትወድቅ ጠንክረው እየሰሩ ናቸው፡፡
የውጭ ኃይሎች፣ የቅኝ ገዥ አስተሳሰብ የሚቃወም፣ዴሞክራሲያዊና ጠንካራ መንግሥት በአፍሪካ እንዳይኖር በስውር የሚሸርቡት ሴራ ቀላል አይደለም፡፡ “ከዚህ በፊት ምርጫው በመራዘሙ ምክንያት ቅሬታ ሲያሰማ የነበረው ህብረት አሁን ምክንያት መደርደሩ እንዳለ ሆኖ አቋሙን ቀይሮ ወደ ታዛቢነት ይመለሳል” የሚል እምነት አለኝ ብለዋል፡፡
ከሁሉም በላይ ምርጫው ፍትሃዊና ተዓማኒ እንዲሆን የውስጥ አለመግባባቶችን በማጥበብ መፍታት ፣እንዲሁም ‹‹የአፍሪካን ጉዳይ በአፍሪካ›› እንደተባለው የአፍሪካ ህብረት ተዛቢዎች በስፋት የሚሳተፉበት ሁኔታ ማመቻችት እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል፡፡
ዋቅሹም ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ግንቦት 1 ቀን 2013 ዓ.ም