በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ተጋርዶ የነበረው ጥቁር ደመና ሲገፍ ብዙኋኑ በፈነጠቀለት ብርሃን የሀገሩን ትንሳኤና መጻኢ እድል አሻግሮ እየተመለከተ ተስፋውን አለምልሟል። ተስፋው ቢለመልም እንኳም የብርሃንና ጨለማው ትንቅንቅ ቀላል አልነበረም። የጨለማው ሃይል ብልጭ ያለውን ብርሃን ለማዳፈን ሲጥር የለውጥ ሃይሉም ብርሃኑን ለማስቀጠል ብርቱ ትግል እያደረገ ዛሬ ደርሰናል።
የሶስት ዓመታቱ የለውጥ ጉዞ አልጋ በአልጋ አልነበረም፤ በፈተና እና በተስፋ መካከል ስንት ውጣ ውረዶች አልፈዋል። በተለይ ጥቅማችን ተነካና እኛ ካልመራናት ኢትዮጵያ እንደሀገር መቀጠል አትችልም ሲሉ የነበሩ ሃይሎች በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ግጭቶችን እየፈጠሩ ሀገሪቱን ለማፈራረስ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም። አንዳንዴ በቀጥታ አንዳንዴ ደግሞ በእጅ አዙር በህዝብና በሀገር ላይ ግጭቶችን አቀጣጥለዋል። የህዝብን ስስ ስሜት በመነካካት ትርምስ መፍጠር ይቻላል በሚል ተራ ስሌት ታዋቂ ሰዎችን በመግደልና በማስገደል መንግስት ሚናውን አልተወጣም ለማስባል ጥረዋል። እነዚህ የግጭት ነጋዴዎች የሚለኩሷቸውን ግጭቶች እንዴ ሀይማኖታዊ ሌላ ጊዜ የብሄር ተኮር መልክ እያስያዙ በሚፈጥሯቸው ግጭቶች ንጹኋን እየተገደሉና እየተፈናቀሉ ስናይ ልባችን በሀዘን ተሰብሮ አልቅሰናል።
በተለያየ ጊዜ በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚደርሱት ግፎች በእኛ ሰዎች ዘንድ ዝብርቅርቅ አመለካከቶች እንድናንፀባርቅ ማድረጋቸው አልቀረም። አንዳንዶቻችን የፀረሰላም ሃይሎቹን ሴራና ተንኮል በውል ተረድተን ከመንግስት ጎን በመቆም ድርጊታቸውን እያወገዝን ቀሪ ጥፋታቸውን ለማክሸፍ እንሰራለን። አንዳንዶቻችን ደግሞ በተቀደደልን ቦይ በመፍሰስ ጣታችንን ወደ መንግስት እየጠቆምን ለአጥፊዎች አቅም እንፈጥራለን።
በየቦታው ተልእኮ ተሰጥቷቸው የንጹሃንን ህይወት ከሚቀጥፉትና ንብረት ከሚያወድሙት ጸረ ሰላም ሃይሎች ጀርባ እነማን እንዳሉ ማወቅ ያስፈልጋል። ይህን ምስጢር ምክንያታዊ መሆን ያስፈልጋል። ስለዚህ ህዝቤ ሆይ ከአጥፊዎቹ ሴራ እንንቃ።
በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ሆን ተብሎ በንጹሃን ላይ የሚደርሱት ጥቃቶች ለምን ዓላማ እንደሚፈፀሙ ማወቅ ይገባናል። የግድያዎቹ ዋና ዓላማ ሀገርን ለማፈራረስና መንግስት በህዝብ ዘንድ ያለውን አመኔታ እንዲያጣ ማድረግ መሆኑን ስንቶቻችን እንረዳ ይሆን? መንግስት ሀገር ማስተዳደር አልቻለም፤ ህዝቦቹን መጠበቅ አቅቶታል፤ የለውጥ አመራሩ ሀገር ማስተዳደር ከጀመረ ወዲህ ኢትዮጵያ ሠላም አጥታለች፤ በማለት ህዝብ በመንግስት ላይ አመኔታ እንዳይኖረውና እንዲያምጽ ለማድረግ ታስቦ የሚፈፀም ሴራ መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል። በቀደዱልን ቦይ ውስጥ ከመፍሰሳችን በፊት የከሃዲዎችን የተንኮል ሴራ ካለፈው ልምዳቸው መረዳት ይኖርብናል።
ብዙዎቹን ፈተናዎች አልፈን እዚህ ደረጃ ላይ ብንደርስም ሊነጋ ሲል ይጨልማል እንደሚባለው ዛሬም የኢትዮጵያ ጠላቶች ግብዓተ መሬታቸው እየተፈፀመ ባለበት በመጨረሻው ጊዜ በሚፈጥሩት ሴራ ህዝቦች በጥርጣሬ እንዲተያዩና በተጀመረው ለውጥ ላይ አመኔታ እንዳይኖራቸው የሚያደርጉ ስራዎችን እየሰሩ ይገኛል።
በስሜት ተነሳስተው የገቡበት የትጥቅ ትግል የትም እንደማያርሳቸው ሲረዱ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን በመፈፀም በህዝቦች መካከል ግጭት እየቀሰቀሱ መንግስት ማስተዳደር አይችልም በሚል ህዝብ ጥርጣሬ ላይ እንዲወድቅና በመንግስት ላይ እምነት እንዲያጣ መፍጨርጨራቸውን እናስተውል። በህዝብና በመንግስት መካከል ያለውን ሠላማዊ ግንኙነት ማሻከርን እንደ አንድ የትግል ስልት ቀርፀው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውንም እንረዳ።
ከሰሞኑ በአማራ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረውን ጥቃት ተከትሎ በክልሉ የተቃውሞ ሰልፎች መደረጋቸው ይታወሳል። ሰልፉ ተገቢም፤ አስፈላጊም ነው። አማራ ክልል ብቻ ሳይሆን ሌሎች ክልሎችም ቢሆኑ አደባባይ ወጥተው ድርጊቱን ማውገዝ ይገባቸው ነበር። ምክንያቱም በንጹሃን አርሶ አደሮች ላይ የደረሰውን ጥቃት ለማውገዝ ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው።
በተወሰኑ ከተሞች በተካሄዱት ሰልፎች አንዳንድ ግለሰቦች ሲያንፀርቁ የነበሩትን ሃሳቦች ላደመጠ ሰው ሴረኞቹ እንደሀሳባቸው ሆነላቸው እንዴ የሚል ስጋት ያሳድራል። ትናንት ነፍሳቸውን ሰጥተው ኢትዮጵያን ከማፍያዎችና ከበዝባዦች ያላቀቁ መሪዎችን ዛሬ ስም እየሰጡ በአደባባይ ወጥቶ መኮነን ምናልባትም የፀረ ሠላም ሃይሉን ሴራ ካለመረዳት የሚመነጭ ሊሆን ይችላል። እንዲህ አይነቱ አስተሳሰብ አንድነታችንን ከመሸርሸርና በሴራው ወጥመድ እንድንያዝ ከማድረግ የዘለለ ትርጉም አይኖረውም። የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጥል ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ይታመናል። ኢትዮጵያን እንደሀገር ለማስቀጠል ግለሰብም ህዝብም መንግስትም የየራሳቸው ድርሻ አላቸውና።
በማንኛውም ጊዜ በስሌት ሳይሆን በስሜት የምንከፍተው ቀዳዳ ለሀገር አፍራሹ ቡድን ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጥርለትና ዋጋ እንዳያስከፍለን ልንጠነቀቅ ይገባል። አንድ ላይ ቆመን ለውጥ እንዳመጣን ሁሉ አሁንም አንድ ላይ ቆመን የኢትዮጵያን ጠላቶች መመከትና አሳፍሮ መመለስ ይኖርብናል።
ይህ ለውጥ ይዞ የሚመጣው መልካም ነገር እንዳለ ተስፋ የተጣለበት ነው። ነገር ግን መንግስት እረፍት አግኝቶ እንዳይሰራ፤ ህዝቡ የለውጡን ትሩፋት እንዳያገኝና አዲስ አየር እንዳይተነፍስ ይልቁንም መከራና ስቃዩን በማብዛት ተስፋ እንዲቆርጥ፤ የባሰ መጣ እያለ እንዲያማርር፤ የበፊቱ ይሻል ነበር እያለ እንዲያወድስ ፤ በፀረ ሠላም ሃይሎች ያልተደረገ ነገር የለም። የንጹኋን ሞትና መፈናቀልም ምስጢሩ ይኸው ነው።
ያለንበትን ወቅታዊ ሁኔታ መገንዘብና እንዲህ አይነት ጥቃቶች የሚፈጠሩት ለምንድነው? የሚለውን መመርመር ብልህነት ነው። ማነው የሚፈጽማቸው? ለምን አላማ ነው የሚፈፀሙት? የሚሉትን ጠይቀን ራሳችን መልስ መስጠት ይኖርብናል። ሁል ጊዜ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ማህበራዊ ቀውሶች ሲፈጠሩና እጃችንን ወደ መንግስት ስንጠቁም የሴረኞቹ ወጥመድ እየያዘን መሆኑን ማወቅ አለብን። ያለንበትን አስቸጋሪ ወቅት መሻገር የምንችለው መንግስት የህዝብን፤ ህዝብ የመንግስትን ችግር ሲረዳና ተናቦ መጓዝ ሲቻል ነው። ለውጡን ዳር ለማድረስ እያንዳንዳችን የሚጠበቅብንን አስተዋጽኦ ማበርከት ይኖርብናል።
በእናት ጡት ነካሾችና በውጭ ጠላቶቿ ቅንጅት የተወጠነው ኢትዮጵያን የማፈራረስ ሴራ የሚከሽፈው ህዝብ ሲነቃ ነው። ጠላት ህዝብ በመንግስት ላይ እንዲነሳና ሀገር እንድትተረማመስ ይፈልጋል። ህዝብ ጠላት በቆፈረለት ቦይ ከመፍሰሱ በፊት የሚያስከትለውን የከፋ አደጋ ማጤን ይኖርበታል።
እርግጥነው በማንነት ላይ ያነጣጠሩ የተለያዩ ጥቃቶች ሲፈፀሙ ማየት ስሜትን ይነካል፤ ያናድዳል፤ መንግስት ምን እየሰራ ነው? ሊያስብል ይችል ይሆናል። በየጊዜው ቦታቸውንና መልካቸውን እየቀያየሩ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ሁሉ መንግስት ሙሉ ለሙሉ ሊቆጣጠራቸው ይገባል ብሎ መፍረድም ተገቢ ላይሆን ይችላል። ያ ማለት ግን መንግስት ዜጎቹን የመጠበቅ ሃላፊነት የለበትም ማለት አይደለም። ሃላፊነቱን በአግባቡ ተወጥቷል አልተወጣም የሚለው ሊያከራክር ይችል ይሆናል። ስጋት ባለባቸው ቦታዎች ሁሉ የፀጥታ ሃይሉን ባያሰማራ ኖሮ ችግሩ ከዚህም በላይ ሊከፋ እንደሚችልም መገመት ያስፈልጋል።
ሜላት ኢያሱ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 30/2013