ህወሓት የሰራው ሥራ ትግራይን በብዙ ውጣውረዶች ውስጥ ያሳለፈና አሁንም ድረስ ወደነበረችበት ሁኔታ እንዳትመለስ ያደረጋት እንደሆነ መናገር ለቀባሪው ማርዳት ቢሆንም ኮማንድ ፖስቱ ተቋቁሞ ምን አይነት ለውጦች እንዳሉ፤ ምን ፈተናዎች እየገጠሙ እንደሆነና ማን ምንን ማገዝ እንዳለበት መረጃ መስጠቱ ለነገ የሚባል አይደለም። ምክንያቱም የትግራይ ደህንነት የአገርም ደህንነት ነው። ትግራይ ላይ ሥራዎች ከተጀመሩ ሌሎች ቦታዎች ላይ መዋዕለ ንዋይና ድጋፍ ማድረግ ይቻላልና ነው። ስለዚህም ከኮማንድ ፖስቱ በፊትና በኋላ ያለው ነባራዊ ሁኔታን እንዲነግሩን የትግራይ ክልል ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ሌተናል ጀነራል ዮሐንስ ገብረመስቀልን አነጋግረን የሰጡንን ምላሽ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡– እርስዎ ኮማንድ ፖስቱን እንዲያስተባብሩ የተመደቡት በትግራይ የነበረውን ችግር መነሻ በማድረግ እንደሆነ ይታወቃል። ለመሆኑ ወደኃላፊነቱ ሲገቡ የትግራይ ሁኔታ ምን ይመስል ነበር ?
ሌተናል ጀነራል ዩሐንስ፡– የትግራይ ሁኔታ ሁሉም እንደሚያውቀው ብዙ ችግሮች የነበሩበት ነው። ችግሩ ሙሉ ለሙሉ ሳይፈታም ይኸው ስድስት ወራትን አስቆጥሯል። ኮማንድ ፖስቱ ወደ ስራ ሲገባም ግጭቱ አላለቀም ነበር። ስለዚህም ግጭቱን ለማሳጠር በተለይ በመከላከያና ሌሎች የጸጥታ ሀይላት ስራዎች ተከናውነዋል። መንግስትም በተለየ ኦፕሬሽን ትልቅ አቅሙን አሳይቷል።ይሁን እንጂ ግጭቱን መቋጨት አልተቻለም። አልቋል የሚያስብለው ላይም አልደረሰም። አሁንም በየአካባቢው መደበኛ ያልሆኑ ግጭቶች፣ መፈናቀሎች አሉ። ስለዚህ ኮማንድ ፖስቱ ከተቋቋመበት ጀምሮ እስካሁን ትግል ላይ ነው ያለው።
አዲስ ዘመን፡– እናንተ ከገባችሁ በኋላ ምን ለውጥ አመጣችሁ፤ ወቅታዊ ሁኔታውስ ምን ይመስላል?
ሌተናል ጀነራል ዩሐንስ፡– ግጭቱ መደበኛ መልክ በያዘበት ጊዜ ብዙ መሰረተ ልማቶች ወድመው ነበር። በተለይም መብራት ስልክና መንገድ ክፉኛ የተጎዱበት ጊዜ እንደነበር ይታወሳል። ክልሉ እንደ ክልልም ጨለማ ነበር ብሎ መውሰድ ይቻላል። የባንክ አገልግሎትና ስራ ጭምር ቆሟል። ሆኖም ኮማንድ ፖስቱ ከገባ በኋላ ብዙ ነገሮች እንዲስተካከሉ ተደርጓል። ለዚህም ማሳያው በዋና ዋና ከተሞች የተሰሩት ሥራዎች ናቸው። አዲሱ የብር ኖትን ቅየራ ሳይቀር ምንም ችግር እንዳያጋጥም አድርጎ መስራት መቻል ለውጥ ነው።
በመሰረተ ልማቱ ዙሪያ ጉዳቱ ከፍተኛ ቢሆንም የመንግስት ሀላፊነትና ፈቃደኝነት እጅግ የገዘፈ በመሆኑ መፍትሄ እየተሰጠ መምጣቱ ከነበረው ጉዳት አንጻርም ሲታይ ብዙ ርቀት ተሄዷል። ይህ ሁኔታ በመቶኛ ሲሰላ ለምሳሌ የባንክ አገልግሎት ተደራሽነቱ ከ80 በመቶ በላይ ፣ የመብራቱም እንዲሁ ደርሷል። ምክንያቱም መጀመሪያ አካባቢ ክልሉ ጨለማ ነበር። ዳግም በመስራትና ብዙ ወጪ በማውጣት በመብራት አገልግሎቱ ብዙኃኑ ተጠቃሚ እንዲሆን ተደርጓል። በተመሳሳይ ስልክም መብራትን እየተከተለ ስለሚሄድ መጠኑ ከዚህ አይተናነስም። ሰፊ ሽፋን አግኝቶ ግልጋሎት እየሰጠ ነው።
የግል ባንኮች ባይጀምሩም እንደ ንግድ ባንክ አይነቶቹ ከፍተኛ ሽፋን ሰጥተው እንዲሰሩም ሆነዋል። ለአብነትም አዲግራት፣ ማይጨው፣ አክሱም፣ አድዋና ሽሬ የመሳሰሉት ከተሞች ጥሩ አገልግሎት እያገኙ ናቸው። በክልሉ ብዙ ይቀራል የሚያስብለው ከመንገድ ጋር የተያያዘው ነው። ድልድዮች በጣም ፈርሰዋል፣ ቶሎ ለመጠገንም አስቸጋሪ ናቸው። ይሁንና ይህም ቢሆን መፍትሄ እንዲያገኝ በተቻለው ሁሉ ጥረት እየተደረገ ነው። በተለይ ክረምት ሳይገባ ወደ ስራ የሚገባበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ነባራዊ ሁኔታው ተጠንቶ ተጠናቋል። ከዚያ ጠንከር ያሉ ቡድኖች ስምሪት ተደርጎ ቢያንስ ክረምቱን ለመሻገር የሚያስችል ሁኔታ ይፈጠራል። ከክረምቱ በኋላም የተሻለውን ለመስራት ያስችላል። ወደ ነበረበት መመለስም የግድ ስለሚያስፈልግ ይኸው ይደረጋል።
ሌላው ችግር ማህበረሰቡ ጋር ያለው ሲሆን፤ ግጭቱ ኢ መደበኛ በመሆኑ እዚህም እዚያም ህዝቡ እንዳይረጋጋ አድርጓል። ከዚያም በላይ ብዙ ተፈናቃይ እንዲኖር ሆኗል። ለዚህ ደግሞ የሚያስፈልጉ ነገሮች እንዲበራከቱ አድርጓል። ለአብነት በዋናነት ሦስቱ ነገሮች የግዴታ ውዴታ የሚደረጉ ናቸው። እዚህም ምግብ ፣ መጠለያና መድሀኒት ሲሆኑ፤ ከእነዚህ ውስጥ አሁን በጣም እየፈተነ ያለው የመጠለያ ጉዳይ ነው። በተለይ ክረምት ሲገባ ትልቅ ስጋት ይሆንብናል ብዬ አስባለሁ። ሌሎቹ ላይ ግን መንግስት ቁርጠኛ ሆኖ እየተንቀሳቀሰ ስለሆነና ኮማንድ ፖስቱም በተጠናከረ ሁኔታ እየሰራ ስለሆነ ጥሩ ለውጦች መጥተዋል።
አዲስ ዘመን፡– ከተነሳው ችግር አንጻር የሰብአዊ ድጋፉ እንዴት ይገለጻል?
ሌተናል ጀነራል ዩሐንስ፡– መንግስት 70 በመቶ እየሸፈነ በተቻለው ሁሉ ድጋፍ እያደረገ ነው። ይህንን ድጋፍ ግን የሚፈለገው ቦታ ላይ ለማድረስ ብዙ ችግሮች ይገጥሙታል። በዋናነት ማከማቻው አንድ መሆኑ ሁሉም ጋር በጊዜው እንዳይደርስ አድርጓል። ከዚያ በተጓዳኝ ብዙ ተፈናቃይ ያለባቸው ቦታዎች ላይ ለመድረስ ድልድዮች ከፍተኛ ጉዳት ስለደረሰባቸው እነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች ከድጋፉ በሚፈለገው ልክ እንዲጠቀሙ አልሆኑም። ይህ ደግሞ መንግስትን ጭምር ለአቅርቦቱ የሚከፍለውን መስዋዕትነት ዋጋ ያሳጣዋል። ያለውን ልዩ ትኩረትም ይቀንስበታል። የተፈናቃዩ ብዛት ብዙ በመሆኑም የሚጎዳው ሰው ከፍ እያለ ሊሄድ ይችላል። ስለሆነም ይህ እንዳይፈጠር ክረምቱን መቅደም ያስፈልጋልና ይህንን ለማድረግ እየተረባረብን እንገኛለን።
የድጋፉ አቅርቦት ፍላጎት ለተፈናቃዮች ብቻ ሳይሆን ለጠቅላላው ነዋሪ ነው። ስለዚህም በመሰረተ ልማት ችግር ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮችም ለነዋሪውም የሚደርስ ይሆናል። እናም ለሁለቱም አካላት አቅርቦቱን ለማቀላጠፍ ከመቀሌ በተጨማሪ ክምችት የሚደረግበት ማዕከል መክፈት እንደሚያስፈልግ መተማመን ላይ ተደርሷል። ለምሳሌ ሽሬ ላይ ብቻ 600 ሺህ ተፈናቃዮች አሉ። አክሱም አድዋና ሌሎችም ላይ ከዚህ ያልተናነሰ ተፈናቃይ ይኖራል። እነዚህ ላይ ለመድረስ ደግሞ ክረምቱን ለመቅደምና ሰብዓዊ ድጋፉን በቅርበት ለማቅረብ ተግባሩ በወቅቱ መከወን አለበት። በመሆኑም አክሱም ላይ ማዕከሉን ለመክፈት ጥረት እየተደረገ ነው።
የውጪ አገር ድጋፉን በተመለከተ ደግሞ የጀመሩ ቢኖሩም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። አሁን መንግስት እድልን ስለሰጠ ከገቡና ካገዙ መልካምነታችውን ሊያሳዩ ይችላሉ። በእርግጥ ይህ የሆነው በቢሮክራሲና መሰል ችግሮች ሳቢያ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ሰብዓዊነት ካላቸው ከዚህ በላይ እድል ሊሰጣቸው አይችልም። ተቆርቋሪነታቸውንም በተግባር ለማሳየት መትጋት ያለባቸው ወቅት ይህ ይመስለኛል። አሁን ባሉበት ቁጥቁጥ አካሄድ ግን የትም አይደርሱም። የሚጠበቀውና ተግባራዊ ምላሻቸውም አይዛመድላቸውም።
አዲስ ዘመን፡– የክልሉ ሲቪል አወቃቀር ቀበሌና ወረዳ ድረስ ወርዶ ተግባራዊ እንዲሆን ምን እየተሰራ ነው?
ሌተናል ጀነራል ዩሐንስ፡– ግጭቱ በታሰበው ጊዜ ባለማጠሩ ምክንያት መዋቅሩም በዚያው ልክ ጫና እየተፈጠረበት ይገኛል። ምክንያቱም መከላከያ በቦታው ሲኖር መረጋጋቱ ይታይና ጥሩ እንቅስቃሴ ይደረጋል። እርሱ በግዳጅ ወደ ሌላ ቦታ ሲዘዋወር መልሶ አለመረጋጋቱ ይፈጠራል። ኃላፊዎችም ተጋላጭነት ስለሚኖርባቸው ሥራዎችን በአግባቡ እንዳያከናውኑ አድርጓቸዋል። እስከመልቀቅ የሚደርሱም ይኖራሉ። ይህ ደግሞ በአመራር ደረጃ ጭምር የተረጋጋ ቆይታ እንዳይኖር አድርጓል።
ከእነርሱ ጋር ቋሚ የሆነ የጸጥታ ሀይል በሌለበት ቋሚ የሆነ አገልግሎት ለመስጠትም ያስቸግራል። መከላከያን በአንድ ቦታ ማቆየት ደግሞ ለሌሎቹ ሰላም መሆን ከባድ ፈተና ይሆናል። ኢ መደበኛ መልክ የያዘውን ግጭት ለማረጋጋት የሚቻለውም በመከላከያ ስለሆነ መንቀሳቀስ ግዴታ ይሆንበታል። እናም አሁን ያለው አወቃቀር በወረዳና በዞን ለመጠናከር ብዙ ይቀረዋል። ብዙ ሥራ መስራትንም ይጠይቃል። በዚህም ወረዳና ቀበሌ ላይ ያለው አወቃቀር ሥራውን በአግባቡ እንዲከውኑ አላስቻላቸውም።
ይህ ጉዳይ መፍትሄ በሚገባ ያስፈልገዋል። እናም የአካባቢ የጸጥታ ሀይል የሚባል ባይኖርም በአካባቢው ይህ እንዲፈጠር ለማድረግ ከፌደራል መንግስት ጋር በመነጋገር አንዳንድ ጥረቶች እየተደረጉ ነው። ይህ ግን ካልሆነ ክልሉ ጭምር ከፈተና የማይወጣበት ሁኔታ ይፈጠራል። ምክንያቱም አንዱ ለአንዱ ተመጋጋቢ ነው።
አዲስ ዘመን፡– በክልሉ ከፍተኛ የሆነ ሹም ሽረት ይታያል። ይህ የሆነውም ግልጽነት በጎደለው መልኩ እንደሆነ ይገለጻል። ለመሆኑ ምንጩ ምንድነው፤ አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታስ ምን ይመስላል?
ሌተናል ጀነራል ዩሐንስ፡– በግጭቱ ምክንያት የሚያሳዝነው ትግራይ ውስጥ የነበረ መዋቅር ፈራርሷል። ይህንን ለመመለስ ደግሞ ከዚህም ከዚያም የተሻለ አስተሳሰብ ያለውና ትግራይን ቢያንስ ከችግሯ ሊያወጣ የሚችል ሰው እየተሰባሰበ ነው። አካባቢውን ለማረጋጋት ነው ሰዎች በዞኑም፣ በከተማም ደረጃ እንዲቀመጡ የሆነው። በኪሳራ ውስጥ ሆኖ ስራ በሚሰራበት ጊዜ ደግሞ ይህ ሁኔታ መፈጠሩ አይቀሬ ነው። ምክንያቱም የተሻለውን ማንም በዓይን ሊያውቀው አይችልም። በሥራው እንጂ። ስለሆነም ህብረተሰቡን በምን መልኩ እያገለገለ ነው የሚለው ከእቅዱ ጀምሮ ይታያል። ተግባራዊነቱም በየጊዜው ይገመገማል። ይህ ደግሞ ሰዎች ወጣ ገባ እንዲሉ ያደርጋቸዋል። ሹም ሽረቱም የመጣው ከዚህ የተነሳ ነው።
ሥልጣን የሰጠው አካልና ስልጣን የተሰጠው ሰው መናበብ እስካልቻሉ ድረስም የሰጠው አካል ስልጣንህን በአግባቡ አልተጠቀምክም ብሎ የማንሳት መብት እንዳለው ግልጽ ነው። አሁንም እየሆነ ያለው ይህ ነው። በእርግጥ ኮማንድ ፖስቱ የማንሳትም፣ የማስቀመጥም ሀላፊነት የለውም። ስራው በአግባቡ መሰራቱን ብቻ ይገመግማል እንጂ። በዚህም እስካሁን እኔ በማውቀው ደረጃ ይህ ሹም ሽረት የተከናወነው ስራና የስራ ውጤትን መሰረት አድርጎ ነው።
ጊዜው 24 ሰዓት ስራን የሚጠይቅ ነው። ይህንን አላደርግም ያለ አመራር ደግሞ ቦታው ላይ ሊቀመጥ የሚችልበት ሁኔታ የለም። በተደላደለ ወንበር ላይ ተቀምጦ መስራትም አይቻልም። ምክንያቱም በትግራይ የደረሰው ኪሳራ ቀላል አይደለም። ስለሆነም በዚህ አካባቢ በአመራሩ ችግር የሚመጡ ችግሮች ሊታለፉ የሚችሉ አይሆኑም። በኪሳራ ላይ ኪሳራ መጨመር ስለማይቻል። በዚህ ጊዜ ቅድሚያ መሰጠት ያለበት ህብረተሰቡ እንጂ አመራሩ አይደለምና ይህ ይደረጋል።
ትግራይ መፈናቀል ያለበት፣ ረሀብና የጤና መታወክ ጭምር የሚታይበት ከሆነ ሰነባብቷል። ይህንን መፍታት የሚችል ጠንካራ አመራር ደግሞ በየቦታው ያስፈልጋል። ስለዚህም ይህንን ለማምጣት የሚሰራውን ከማይሰራው መለየት ግድ ነው። ማንም ሰው ከህዝብ በላይም አይሆንም። እናም የተሰጠን ተልዕኮ የማይወጣ ሁሉ ይሻራል። ስልጣን ሰጥቶ የሚጠብቅ አካል ካለም የሰው ክስረትን እየፈጠረ ስለሆነ እርሱም አይታለፍም። እናም አመራሩ ብቻ ሳይሆን ግለሰቦችም ከስልጣን መውረድ ብቻ ሳይሆን ይጠየቃሉ። ግን ይህንን የሚያደርገው ጊዜያዊ መስተዳደሩ ነው።
የኮማንድ ፖስቱ ስራ ከዚህ የተለየ ነው። በአካባቢው ያለው መከላከያና ሌሎች የጸጥታ አካላትን መቆጣጠር፤ ከመስተዳደሩ አመራሮችና ከመንግስት አካላት ጋር ስለ ሥራው ቀናነትና ቀጣይነት መወያየት እንዲሁም ተግባራዊነቱን መገምገም ነው። ዋና ስራውም ልማት፣ የህብረተሰብ ሰርቪስ አሰጣጥ፣ የሰላም ግንባታና እርዳታ እንጂ የግለሰቦች ጉዳይ አይደለም። ይሁንና የህዝብን ጥቅም የማያስከብር፣ አስተካክል ሲባል የማያርም ካለ እንደ አቅጣጫ በዛ ሊባል ይችላል። ሰዎቹ ተሳታፊም ስለሆኑ በእቅዳቸው መሰረት ተጠያቂ የሚሆኑበት ሁኔታ ይፈጠራል። ነገር ግን ኮማንድ ፖስቱ እንትናን አውርድ የሚልበት መብት አልተሰጠውም፤ አያደርግምም።
አዲስ ዘመን፡– የክልሉ ሲቪል አስተዳደርን በተመለከተ ምን አይነት ድጋፍ እያደረጋችሁ ነው፤ በተለይ ከጸጥታ፣ ከበጀት፣ ከሥራ እድል ፈጠራና መሰል ሥራዎች አንጻር?
ሌተናል ጀነራል ዩሐንስ፡– ከበጀት ጋር በተያያዘ በፌደራል መንግስት የተያዙ የልማት ስራዎች አሉ። ይህ ደግሞ የሚከናወነው የፌደራል መስሪያ ቤቶችን ያቀፈ አንድ ቦርድ ስላለ በእርሱ አማካኝነት ነው። ስለዚህም ይህ ቦርድ መልሶ ከመጠገን እስከ መስራት ድረስ ያሉ ተግባራትን ያከናውናል። እኛ ደግሞ እነርሱን በጸጥታ፣ በጥበቃ፣ በመረጃና የሚፈልጉትን ነገር በማቅረብ እናግዛለን።
ክልሉን በተመለከተ ደግሞ እርዳታና ደሞዝ የማድረስ ስራን ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን እንዲተገበር እናደርጋለን። በተለይም ደሞዝ አካባቢ ያለው የገንዘብ ዝውውርን በተመለከተ በሚገባ ጥበቃ እንዲደረግ ፤ የተፈለገው ቦታ ላይ በጊዜው እንዲደርስ ብዙ ተግባራት ይከናወናሉ። በተመሳሳይ የግል ድርጅቶችንም ቢሆን ሥራ እንዲጀምሩ ለማድረግ በሚፈልጉት ደረጃ የማገዝ ተግባርም ይከናወናል። ምክንያቱም እነርሱም መስራት ካልቻሉ የትግራይ ችግር በመንግስቱ ሰራተኛ ብቻ መቃለል ያዳግተዋል። እናም የማበረታታት ስራዎች ይሰራሉ። ሰራተኛው ደሞዝ ተከፋይ ብቻ ሳይሆን ሰራተኛም እንዲሆን ማድረግ ላይ ብዙ እገዛ ይደረጋልም። ጊዜያዊ አስተዳደሩን በመግፋት ተግባሩ ይከናወናል።
አዲስ ዘመን፡– አንዳንድ አለማቀፍ ተቋማት በትግራይ አካባቢ ረሀብን፣ አስገድዶ መድፈርና ሌሎች ተግባራትን እንደ ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ እየዋሉ ናቸው ይላሉ። በዚህ ላይ ምን አስተያየት አልዎት?
ሌተናል ጀነራል ዩሐንስ፡– ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት ወደ መጠለያ የመጣ የሰው ብዛት ብዙ ነው። እስካሁን በጊዜው የሚፈልጉት ነገር እንዲደርስላቸው ጥረት እየተደረገ ነው። ከዚህ በኋላም ከባድ እንዳይሆን እንሰራለን እንጂ የሌሎችን ንግግር የምንሰማበት አካሄድ አይኖረንም። አሁን ከጊዜው ጋር እየተሯሯጥን ነው። በተለይም ክረምት ከገባ የሚደርሰው ችግር ከባድ ስለሚሆን ያንን ለመቅደም ነው ትኩረታችን። ከምግብ ጋር የተያያዘው በጥሩ ሁኔታ እየሄደም መሆኑን አይተው እንዲመሰክሩም እድሉ ተሰጥቷቸዋል። የዚያን ጊዜ ሀሳባቸውን ያነሳሉ የሚል እምነት አለኝ።
ከጤና ጋር በተያያዘም እንዲሁ እንቅስቃሴዎቹ መልካም ቢሆኑም የሚቀረው ነገር አለ። ምክንያቱም የወደመው ንብረትን ቶሎ መተካቱ አይደለም ለታዳጊ አገራት ለሀያላኑም ስለማይቻል። ስለዚህም ጤና አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያስችሉ ጤና ጣቢያዎች በቂ ስላልሆኑ አስፈላጊውን አገልግሎት ለመስጠት ሞባይል ክሊኒክ ከፍቶ እየተሰራም ይገኛል። ይህም የመንግስትን ጥረት ከወቀሳ እንደሚያድነው ማሳያ ይመስለኛል። በእርግጥ አንዳንድ ሆስፒታሎች የገቡና ህክምና እየወሰዱ ያሉ ሰዎች አስገድዶ መድፈር ደርሶባቸዋል ተብሏል። ይህም ቢሆን ሁሉም ላይ መድረስ ስለማይቻል የተከሰተ ነው።
ረሀብ ወደ መጠለያ ያልመጣውን መንካቱ አይቀሬ ነው። በዚያ ላይ ወደ ሁለት ሚሊዬን የሚጠጋ ሰው በሴፍትኔት የሚደገፍ ነው። ስለዚህም በቂ ነገር መዳረሱ ላይ ክፍተት ሊፈጥር ይችላል። እኛም በጊዜው ያልደረስንበት አካባቢም መራቡ አይቀርም። ስለዚህም ይህንን ጉዳይ በሂደት ማየት ይገባል እንጂ በረሀብ ተቀጡ መባል ይኖርበታል የሚል እምነት የለኝም። አሁን ግን ሁሉንም ገብተው በማየት ይረዱታል ብዬ አስባለሁ።
ጦርነት ካለ እንኳን ርሀብ ሞት አይጠፋም። የጦርነት አስከፊ ገጽታም ይህ ነገሩ ነው። ሁሉም ችግር ህብረተሰቡ ላይ የሚደራረብበትም ነው። ከጉዳት ውጪ የሚያስተናግድ ማህበረሰብም አይኖርም። ስለሆነም መጥፎ አጋጣሚ ሆኖ ተከስቷል። የወሰደውም ጊዜ ቀላል አይደለም። ህብረተሰቡም በችግር ውስጥ ተዘፍቋል። ህይወቱን ለማዳንም እየተፈናቀለ ከአንዱ ቦታ ወደሌላው ይጓዛል። ስለዚህ ማን ምን አለ የሚለውን ትቶ ለመፍትሄው መረባረብ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡– የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንና የተባበሩት መንግስታት በክልሉ ሁኔታ ላይ በጋራ ለመስራት ተስማምተው ነበር። መንግስትም ፈቅዷል። ከጸጥታና መሰል ነገሮች አንጻር እንዴት እየደገፋችኋቸው ነው ?
ሌተናል ጀነራል ዩሐንስ፡– እስካሁን እገዛ ፈልገው የመጡበት ሁኔታ የለም። ነገር ግን በድጋፍ ደረጃ ከእኛ የሚፈልጉት ነገር ካለ ዝግጁ እንደሆንን አንድ አድቫንስ ቲም አግኝቼ አሳውቄያለሁ። እንደ ክልል ሰብአዊ መብት ላይ የሚሰሩ አካላት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እያደረጉ መሆኑም በሚያወጡት ሪፖርት ይታያል። ይሁንና በቅንጅት የሚሰራው አካል ሥራ የጀመረ አይመስለኝም። ምክንያቱም ሥራውን ለመጀመር የሚጠብቁት ነገር እንዳለና ዝግጅት ላይ እንደሆኑ ገልጸውልናል። ስለሆነም በእኛ በኩል አስፈላጊውን ድጋፍ የምናደርግ ይሆናል። ከእነርሱም ጋር ተነጋግረናል።
አዲስ ዘመን፡– የትግራይ ህዝብ ከስነልቦና አንጻር አሁን ያለበት ሁኔታ እንዴት ይታያል፤ በተለይ ግጭቱ ካስከተለበት ችግር አንጻር አሁን በምን ሁኔታ ላይ ነው ያለው?
ሌተናል ጀነራል ዩሐንስ፡– የስነ ልቦና ጫናው ላይ መስራት ቢኖርብንም ከዚህ የሚቀድም የመብላትና የመኖር ጉዳይ አለና እዚያ ላይ ነው እየተረባረብን የምንገኘው። ህይወቱን ታደግን ማለት የስነ ልቦና ጫናውንም በዚያው ልክ ቀነስን ነው። ምክንያቱም በህይወቱ የሚገጥሙት እያንዳንዱ ችግር የሥነ ልቦና ጫናውን ከፍ ያደርገዋል። አለንልህ ሲባል ደግሞ በመጠኑም ቢሆን መረጋጋትን ይሰጠዋልና እርሱም ወደመፍትሄ እንዲሄድ ያግዘዋል።
የሥነልቦና ሀኪም መድቦ መስራቱም መጀመሪያ ያለበትን ችግር እየፈቱ ከሄዱ በኋላ የሚደረግ ነው። አሁን በባለሙያ እየደገፍን ነው፤ ብዙ ባለሙያዎችም አሉን ብዬ መናገር አልችልም። ሰውም ቢሆን የስነልቦና ህክምና ያስፈልገዋል። ምክንያቱም ብዙ የተፈናቀለ፣ ቤተሰቡን ያጣ እንዲሁም ሀብት ንብረቱ የወደመበት አለ። ይህንን የሚያክም ባለሙያ ደግሞ የለም። ሰብዓዊ ድጋፉ በደንብ ከደረሰ በኋላም ይህ ነገር በሚገባ ይሰራበታል ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡– ኮማንድ ፖስቱ የትግራይን መረጋጋት ከማምጣት አንጻር ምን ሊሰራ አቅዷል ?
ሌተናል ጀነራል ዩሐንስ፡– በዋናነት ትግራይን ሊያረጋጉ የሚችሉት አራት ጉዳዮች ናቸው። እነዚህም የክልሉን የጸጥታ አቅም መፍጠርና የሰላም ግንባታውን ማፋጠን ላይ የመጀመሪያው ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ይሆናል። ከላይ እንደተጠቆመው በወረዳና ዞን አካባቢ ያለው ማህበረሰብ ተረጋግቶ እንዲኖር ከተፈለገ ይህ ስራ ቀድሞ መከወን ያለበት ጉዳይ ነው። መከላከያው ብቻም ጸጥታውን በሙሉ ሊያስጠብቅ አይችልም። እናም ክፍተቶችን ለመድፈን ጠንከር ያሉ ስራዎችን ለመስራት ታስቧል። ግጭቱ ኢ መደበኛ መልክ በመያዙ ከእርሱ ጋር የሚስማማ ስትራቴጂ መከተል ላይ ይሰራል። መቋጫ እንዲያገኝም ለማድረግ የኮማንድ ፖስቱ ሥራ ብቻ የሚፈታው ስላልሆነ የፌደራል መንግስቱን ጨምሮ የሌሎች ርብርብንም ይጠይቃልና በተቻለው ሁሉ ይሰራል።
ሌላው በሁለተኛ ደረጃ ታቅዶ እየተሰራበት ያለውና ወደፊትም በቋሚነት መፍትሄ እስኪያገኝ የሚከናወነው የተፈናቀለውን ህዝብ ወደ ነበረበት የመመለስና ከ90 በመቶ በላይ አርሶአደር በመሆኑ ወደ እርሻው ተመልሶ የሚሰራበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው። ይህ ካልሆነ ግን ከባድ ችግር ውስጥ ይገባል። መስሪያ ጊዜው ደግሞ አሁን ነውና ያንን የማድረጉ ጉዳይ አስቸኳይ ሥራን ይጠይቃልና ኮማንድ ፖስቱ ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን ይህንን ያደርጋል።
ሦስተኛው የመሰረተ ልማቱ ጉዳይ ሲሆን፤ አሁን በርካታ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ይገኛሉ። ብዙዎቹም ወደነበሩበት እየተመለሱ ነው። አንዳንድ ድልድዮች ከፍተኛ ጉዳት ስለደረሰባቸው ቶሎ ለመጠገን ቢያስቸግሩም። እነዚህም ቢሆኑ ክረምቱ ሳይገባ መፍትሄ እንዲያገኙ ለማድረግ እየተሰራ ነው። ሆኖም ሁሉም በመንገድና በሌሎች መሰረተ ልማቶች እንዳይቸገሩ ለማድረግ ብዙ ስራ ይጠይቃል። ስለሆነም የኮማንድ ፖስቱ የቀጣይ ስራ የሚሆነው መሰረተ ልማቶቹ ወደ ነበሩበት ተመልሰው ሁሉንም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ ነው።
አራተኛው ሰብዓዊ እርዳታው ለሁሉም በጊዜው እንዲደርስ ማድረግ ላይ ሲሆን፤ ለዚህ ደግሞ ተጨማሪ ማዕከላት ተከፍተው ስርጭቱን የተሳለጠ ማድረግ ላይ ይሰራል። በተለይ በአሁኑ ወቅት መቀሌ ላይ ብቻ ማከፋፈያ ያለ ስለሆነ በቅርብ ርቀት መድረስ አስቸጋሪ ሆኗል። እናም አክሱምና መሰል አዋሳኝ ቦታዎች ላይ ማከማቻዎችን በመክፈት ድጋፉ የሚደርስበት ሁኔታን ማመቻቸት እንዲሁም የጤና ግልጋሎቱ በሚፈለገው መጠን እንዲጓዝ ማድረግ ሌላው እቅድ ነው።
አዲስ ዘመን፡– በቀጣይስ በክልሉ ያለው አለመረጋጋት ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኝ ማን ምን ይስራ ?
ሌተናል ጀነራል ዩሐንስ፡– ችግሩ የተከሰተው ትግራይ ላይ ቢሆንም ጉዳቱ ግን የአገር ጭምር ነው። ስለዚህም መፍትሄውም እንደ አገር የሚመጣ መሆን አለበት። ከእኛ ራቅ ያለ ነው የሚባልም አይደለም። አንድ አገር ፣ አንድ ህዝብ ነንና ነግ በኔን አስቦ መረባረብ የውዴታ ግዴታም ነው። ጦርነት በአንድ ጫፍ ይጀምራል። መድረሻውና ማብቂያው ግን አይታወቅም። እናም እጣው የማን እንደሆነ ማሰብ ተገቢ ነው። እንዳይደርስብኝ የሚባል ነገር የለም። ስለዚህም ሁሉም ለሰላምና ለሰላም ሲል ብቻ የሚጥለው ጠጠር መኖር አለበት።
ግጭቱን ማራዘም የሚፈልጉ ሀይላት አሉ። ወጣቱን የሚያስበረግጉም እንዲሁ አሉ። እነርሱ ግን ከእሳቱ የራቁና በእኛ መጠቀም የሚፈልጉ ናቸው። በዚህም ወጣቱን ያለ እድሜው ህይወቱን ይቀጩታል። ስለዚህም ወጣቱም ሆነ ማህበረሰቡ ተጠቃሚ አይሆንምና መንቃት አለበት። ለሰላም ተብሎ የሚከፈል ዋጋን መክፈል እንጂ አንዱ በአንዱ ላይ የሚፎክርበት ጊዜ አይደለም። ምክንያቱም ማንም አሸናፊ የሚሆንበት ወቅት ላይ አይደለንም። ስለዚህም እዚህ ላይ መለያየት አያስፈልግም። እንደ ልብ በሚረጭ ፕሮፓጋንዳ እስካሁን የተወናበድኩት ይበቃኛል ብሎ ቆም ብሎ ማሰብም ይገባል።
ከአሁን በኋላ በትናንቱ ሳይሆን በዛሬው ሥራችን በነገው ተስፋችን እንደምንኖር ልንረዳ ይገባል። ስለዚህም በትናንት መኖርን ሁሉም ሰው ትቶ ዛሬን እየኖረ ነገን ብሩህ እያደረገ መጓዝ ያስፈልገዋል። ለጋራ ጥቅም፣ ለጋራ ደህንነት አብሮ መቆምም ተገቢ ነው። ለዚህ ደግሞ ሚዲያውም ጭምር ማገዝ አለበት። ለሰላም ምርኮኛ መሆንም ይጠበቅበታል። ምክንያቱም ለሰላም መማረክ ጀግና መሆን ነውና። ለሰላም የምንከፍለው ዋጋም ብዙ ነገራችንን የሚያስከብርልን አገራችንን የሚያስጠብቅልን ይሆናል። ጦርነትን ፈጣሪም አጥፊም ሰዎች ናቸውና ልዩነታችንን በሚያስተናግድ መልኩ ጦርነቱን ማጥፋት ላይም መረባረብ አለብን። ሁላችንም የሰላም ሐዋርያ ሆነንም በተግባር ለአገራችን ደህንነት እንስራ እላለሁ።
አዲስ ዘመን፡– ስለሰጡን ማብራሪያ እጅግ እናመሰግናለን።
ሌተናል ጀነራል ዩሐንስ፡– እኔም አመሰግና ለሁ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 29/2013