የህግ ማክበር ጉዳይ ሲነሳ አብሮ የሚነሳው ህግን የማስከበር ጉዳይ ነው። ሁለቱም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ ናቸው። ነገር ግን ቀድሞ መምጣት ያለበት “ህግ ማክበር ወይስ ማስከበር” የሚለው ነገር ልክ እንደ “ዶሮው ወይስ እንቁላሉ?” አይነት አከራካሪ ጥያቄ ነው። ሰለጠኑ በሚባሉ ሃገሮች ዋና መለያቸው ህዝቡ መልካም ህግ አክባሪ፣ መንግስትም ጥሩ ህግ አስከባሪ መሆናቸው ነው።
በነገራችን ላይ “ማደግ ወይም አለማደግ” ሲባል በኢኮኖሚያችን ብቻ ሳይሆን በማህበራዊ መስተጋብራችንና በህግ አክባሪነትም ጭምር ነው። በኢኮኖሚ ያደገ ማህበረሰብ በማህበራዊ መስተጋብሩም ያደገና ህግ አክባሪነቱም የጎለበተ ሲሆን ይስተዋላል። በአንድ ወቅት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ሲናገሩ “የሚበላው ያጣ ህዝብ፣ መንግስትን ይበላል” ማለታቸው በኢኮኖሚ ካላደግን ህዝብ ህግ ማክበር ይሳነዋል የሚል አድምታ አለው፤ ስለሆነም ህግ አክባሪ ዜጋ ለመፍጠር በመጀመሪያ በኢኮኖሚ ማደግ ይኖርብናል ለማለት እንደሆነ ግልፅ ነው።
ብዙ ጊዜ አምባገነን መንግስት የሚፈጠረው ባለደጉ እና በማደግ ላይ ባሉ ሃገሮች ውስጥ መሆኑ የማይካድ ሃቅ ነው። ከዚህ ጋር አብሮ የሚነሳው አደጉ በምንላቸው ሃገሮች ለምሳሌ አሜሪካንን ብንመለከት መንግስት ለመመስረት የሚወዳደሩ ግለሰቦች በኢኮኖሚ አቅማቸው የበለፀጉ ናቸው። በድሃ ሃገራት ግን የሚስተዋለው በተቃራኒው ነው። በእኛ ሃገር ኢትዮጵያ የሚስተዋለው አንድ ሰው ሃብታም ለመሆን ወደ ከፍተኛው የመንግስት መዋቅር በጥረቱም ይሁን በአቋራጭ ብቅ ይላል። አመጣጡም ለመበልፀግ እስከሆነ ድረስ ህግ የማስከበር ጉዳይ አያስጨንቀውም። እንደያውም ሌሎችን በህግ በማሰር የራሱን ጥቅም እንዴት ያለገደብ ማጣጣም እንዳለበት ያሳስበዋል። ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታትም የታዬው ይኸው ለጥቅም ወደ መንበረ ስልጣኑ በማቅናት የሃገርን እና የህዝብን ሃብት መበዝበዝ ነበር።
በዚህም “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” የሚለውን አባባል ተረት ሳይሆን ልማድ ሆኖ በማህበረሰቡ ሰርፆ ቀርቷል። ተመልካችም አጥፊውን ወደ ህግ ከመውሰድ ይልቅ አይቶ እንዳላየ ያልፈዋል። በዚህም “ማንም አይጠይቀኝም” በሚል ስሜት ያለገደብ ይመዘብራል። ከሚገባው በላይ በልቶ ከጠገበ በኋላ የለየለት አምባገነን ሆኖ ይቀራል። በማህበረሰቡም ውስጥ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ሹመት ሃብታም እንደሚያደርግ እንጂ በህግ ተጠያቂ እንደሚያደርግ ሰው ሊገነዘበው አይችልም፤ ከዚህም ማህበረሰቡ ትምህርት ሊወስድ የሚችለው ህግ ከማክበር ይልቅ ህግን መተላለፍ እንደሚያዋጣ ሊሆን ይችላል።
በቅርቡ ከደቡብ አፍሪካ የመጣ አንድ ወዳጄ እንደነገረኝ በፕሪቶሪያ ከተማ ሁሉም የመንግስትም ሆነ የግል ተቋማት በሙስና ውስጥ የተዘፈቁ እንደሆኑ ነው። በዚህም ሁሉም ሰው ባለው አቅም ጉቦ እየከፈለ ይስተናገዳል። የወዳጄ አገላለፅ እንደ ደቡብ አፍሪካ ባሉ ሃገራት “ሙስና ለሁሉም ከተፈቀደ ጥሩ፤ ለጥቂቶች ከሆነ ግን አደጋ አለው” ባይ ነው። እንደ ደቡብ አፍሪካ አገራት ያሉ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎችና ባለስልጣናት በሙስና የተዘፈቁት ከድህነት በመነጨ ነው የሚለው ለእኔ አይዋጥልኝም፤ ችግሩ ከድህነት ጋር የተያያዘ ቢሆን ኖሮ በአፍሪካ አደጋው የከፋ ይሆን ነበር።
እርግጥ ነው፤ አንድ ማህበረሰብ በማህበራዊ መስተጋብሩ ያልዳበረ ከሆነ በፖለቲካው ዘርፍ የሚያመጣው ውጤት የዳበረ ሊሆን አይችልም። የአንድ ማህበረሰብ የዕድገት ደረጃ የሚለካው ከዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ጀምሮ በየደረጃው ያለው የማህበረሰብ ክፍል በምግባሩ እና በሞራሉ ለውጥ ሲያመጣ ነው። ሁሉም ሰው ድሃ – ሃብታም፣ ሹመኛ – ምንደኛ ሳይል ለህግ ተገዥ ከሆነ በርግጥም ማህበረሰቡ አድጓል፣ ተመንድጓል ያስብላል።
በኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ስንቃኘው ማህበረሰቡ በተወሰነ መልኩ ህግን የመፍራት እንጂ የማክበር ዝንባሌ አይታይበትም። ለምሳሌ ሁሉም ሹፌሮች የትራፊክ ፖሊስ ባለበት አካባቢ የትራፊክን ህግ ይፈሩታል፤ ነገር ግን በአካባቢያቸው የትራፊክ ፖሊስ ከሌለ ህጉን ይተላለፉታል። በዚህም አደጋ ይከሰታል። በእግር ኳስም ዘርፍ ብንሄድ የመጫወቻ ህጎች ይታወቃሉ። አንድ ተጨዋች ህጉን ቢስት ዳኛው ካላዬ አጥፊው አይቀጣም፤ ይህ ባደጉት ሃገራት መፍትሄ ያገኘ ጉዳይ ቢሆንም፤ አጥፊው ራሱ ህጉን እንደሳተ ቢያውቅ እንኳ በራሱ ላይ አይመሰክርም። ይህም የሞራል ልዕልና የለውም ማለት ነው።
በሌላ አገልግሎት ዘርፍ ደግሞ ምሬትና ለቅሶ የሚያመጡ ተቋማት አሉ። ሁሉ ነገር በጉቦ የሚስተናገድበት አሰራር የተፈጠረ ይመስል፣ እንደ ገቢ፣ ሲኦሲ፣ መንጃ ፍቃድ ያሉ የምስክር ወረቀት መስጫ አገልግሎቶች ይህን ያህል ካላመጣህ አይሰጥህም የሚባልበት መኖሩን በመግለጸ ህብረተሰቡ በተለያዩ ጊዜ ብሶቱን ሲያሰማ ይስተዋላል። ይህን የተመለከተ ግለሰብ ወይም ማህበረሰብ ታዲያ “ተማር፣ ጥረህ ግረህ ብላ” ሲባል “ገንዘቤን ፎጭ አድርጌ አመጣዋለሁ” ይላል። ምን ያድርግ ታዲያ፣ በትክክለኛው መንገድም ህግን አክብሮ ቢሄድ እንኳን፣ ሌሎች በአቋራጭ ሲቀድሙት ያያል። ከእነዚህ ህገ ወጥ ሰዎች ምን ሊማር ይችላል? ያው ተያይዞ ገደል ማለት ነው።
ለዚህ ዋናው መፍትሄ የሚሆነው የማህበረሰብ ዕድገት ለውጥ (Social Development) መምጣት ሲችል ነው። ይህ የሚሆነው ደግሞ ህግ አስከባሪው በትክክል ሚናውን መወጣት ሲችል፣ ተገቢ ባልሆነ ጥቅማጥቅም ሳይደለል ሙያው የሚፈቅደውን ስነምግባር ተላብሶ መስራት ሲጀምር ይሆናል። በተጨማሪም ህብረተሰቡ አጥፊዎችን አይቶ ከማለፍ ይልቅ ባጠፋው ጥፋት ልክ ማውገዝና ለፍትህ ማቅረብ ሲጀምር እንደሆነ የሌሎች ሃገራት ተሞክሮ ያሳያል።
አሁን በሃገራችን እየተስተዋለ ያለው ህገወጥነት መነሻው የህብረተሰብ ንቃተ ህሊና በሚጠበቀው ደረጃ አለማደጉ ነው። ህገወጥ የሚሰራ ሰው ላይ ርምጃ ይወሰድበታል ሲባል ከስህተቱ ከመታረም ይልቅ በእልክ ተነሳስቶ ወደ ጥፋት የሚገባው ይበልጣል። ይህ ስህተት ነው፤ ኋላቀርነትም ነው። ህግ ማክበር በየትኛውም እምነት የሚሰበክ የሞራል ትምህርት ነው። ታዲያ የችግሩ ተጠያቂ የሚሆነው ማን ነው?
በእርግጥ ሰዎች ህግ ጥሰዋል ተብለው የባህሪ እርምት እንዲወስዱ ወደ ማረሚያ ቤት ሲወርዱ ልናይ እንችላለን። በማረሚያ ቤት የቆዩትም ታራሚዎች ፍርዳቸውን ጨርሰው ሲወጡ የተወሰኑት ባህሪያቸውን አርመው ወደ ህብረተሰቡ ሲቀላቀሉ አንዳንዱ ደግሞ ከማረሚያ ቤት ከወጣ በኋላም ተመሳሳይ ጥፋት ሲሰራ ይታያል።
በሃገራችን ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሃገርን ለማፍረስ የርስ በርስ ግጭት ለመቀስቀስ ሲዳክሩ የነበሩ በአቅም የፈረጠሙና አይነኬ የተባሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ተይዘው ለፍትህ መቅረብ መቻላቸው አንድ ትልቅ ማህበራዊ ዕድገት ነው። ማንም ሰው ከህግ በላይ መሆን የለበትም። ህግ አስፈፃሚው አካል ህግ የማክበርና የማስከበር የሞራል ልዕልና ሲኖረው ህግ ይከበራል።
ዋናው ጉዳይ የህግ ማስከበር እሳቤ በላይኛው እርከን ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ወደታችም ወርዶ በማህበረሰቡ ላይ እንግልት የሚፈጥሩ፣ ሁከትና ዝርፊያ የሚፈፅሙ፣ በተዋረድ በሙስና የተዘፈቁ አካላትን በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ሁሉም የበኩሉን ሚና እየተወጣ ሲሄድ ትልቅ ማህበረሰባዊ እድገት ልናመጣ እንችላለን። በመሆኑም ለሃገራችን ሁለንተናዊ እድገት መንግስት ያወጣውን ህግ ልናከብረው ይገባል!
ፈላስፋው
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 29/2013