በጣሊያን የወረራ ዘመን ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማዋ ከታጠፈ፣ ሉዓላዊነቷ ከተደፈረ አምስት ዓመታት በኋላ ነፃነቷን ካስመለሰች እንሆ 80ኛ ዓመቷን አስቆጠረች። ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ንጉሰ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በአርበኞች ብርታትና መስዋዕትነት የጣሊያን ባንዲራ አውርደው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በታላቁ ቤተ-መንግሥት ሰቀሉ። ጣሊያን ከአድዋ ሽንፈት 40 ዓመታት በኋላ በዘመናዊ የጦር መሣሪያና በወታደራዊ ኃይል ይበልጥ ተደራጅቶ ኢትዮጵያን ከሦስት አቅጣጫዎች ወረረ። ከአድዋው ዘመቻ ያልተሻለ የጦር ትጥቅ የነበራት ኢትዮጵያም የጣሊያንን ጦር ተዋጋች።
የጊዜዎቹ ኃያላን እንግሊዝና ፈረንሳይ የጦር መሣሪያ በግዢ እንዳታገኝ ለጣሊያን ተደርበው ስላሴሩባት ኢትዮጵያ ብቻዋን ጦርነቱን በመጋፈጧ ድል ማግኘት አልቻለችም። የየግንባሮቹ የኢትዮጵያ የጦር አዛዦች ብዙዎቹ ሞተው ሠራዊቱም በአውሮፕላን ቦምብ ተደብድቦ ያለቀው አልቆ የቀረው ቀርቶ ጣሊያን ጊዜያዊ ድል አግኝታ አብይ አብይ ከተሞችን ብትቆጣጠርም ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ግን እምቢ ለነፃነቴ ፣ እምቢ ለአገሬ ብለው የሽምቅ ተዋጉ።
ንጉሰ ነገስቱም ስደት ሄደው በጊዜው ለነበረው የመንግሥታቱ ማኅበር /ሊግ ኦፍ ኔሽንስ/ አቤቱታ አቀረቡ። ይህ ደግሞ መልካም እድሎችን ሰጠ። ይህ ድል እንዴት ሆነ፤ ከዚህ ድልስ ምን እንማርና መሰል ነገሮችን በማንሳት ከጥንታዊ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ጋር አጠር ያለ ቆይታን አድርገን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡– ሚያዝያ 27 ጣሊያን ዳግም ባረገዘው ቂም ተመልሶ ቢመጣም ዳግመኛ ድል የተደረገበት የድል ቀን እንደሆነ ይታወቃል። ይህ ሁኔታ እንዴት ነበር የሆነው?
ልጅ ዳንኤል፡– በ1888 ዓ.ም የተደረገው የጣሊያንና የኢትዮጵያ ጦርነት በእነርሱ ብቻ የነበረ እንዳልሆነ የታሪክ ድርሳናት ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ። በዚህም ጣሊያን እንደ ምክንያት ሆነች እንጂ በጊዜው ከጎናቸው የነበሩ በርካታ ታላላቅ መንግስታት ነበሩ። አፍሪካን ለመቀራመትና ለመውረርም ነው ይህንን ያደረጉት። ይህ ጥንስሳቸውም ረጅም ርቀት የተጓዘ ነው። አንደኛና ዋነኛው ሰፊ ሀገር፣ ሀብት ያለበት፣ እንደ ልብ ሰራተኛ የሚገኝበት፣ አየሯ የተስማማ ሲባል የምትገኘው አፍሪካ በመሆኗ ከአውስትራሊያ፣ ከኒውዝላንድ፣ ከአሜሪካ ጭምር ቅርብ መሆኗ ሜዲትራንያንን ከአቋረጡ በኋላ አፍሪካ ይገባልና የበለጠ ለመጠቀም በቀጥታ ዘመቻቸውን ጀመሩ።
እያደገ የመጣውን ኢንዱስትሪያቸውን ከፍ የሚያደርግ የሰው ሀይልም የሚያገኙት ከአፍሪካ በመሆኑ ይህንን ለማሟላትም ሥራቸውን ያፋፍሙት ገቡ። ይህ በሚሆንበት ጊዜ የተጠቀሙት ጥበብ አፍሪካ ውስጥ ካሉ ታላላቅ ነገስታት፣ ባላባቶች ጋር መወዳጀት ነው። ይህንን ቁርኝት ደግሞ በሁለት መልኩ ይከውኑታል። ከቻሉ በገንዘብ ካልቻሉ ደግሞ በሀይል በመጠቀም የበታች በማድረግ ነው። ይህ ዘዴም ነው ኢትዮጵያ ላይ የተተገበረው። የውጫሌ ውል አንቀጽ 17ን መሰረት አድርገውም ነው ጦርነት ያወጁት።
ሰላም በነበረበት ጊዜም ቢሆን እነርሱ ሥራቸውን በሰላዮቻቸው አማካኝነት ሲሰሩ ቆይተዋል። ሰላዮቹ ከአንዱ ጠቅላይ ግዛት ወደ አንዱ እንደልባቸው ይንሸራሸሩ ስለነበርም ከባለስልጣኖቹ ጋር ወዳጅነት በመፍጠር፣ ስጦታ በማበርከት በተለይም የጦር መሳሪያ በመስጠት የነበረውን የፖለቲካ ሁኔታ በደንብ እንዲረዱ ሆነዋል። በዚያ ላይ አመጣጣቸው ከመነሻው ኢትዮጵያ እንደተዳከመች ስላዩ ነው። ሆኖም አንድ ነገር ረስተው ነበር። ይህም ኢትዮጵያዊያን በቋንቋ የተለያዩ ቢሆኑም በአገራቸው አለመደራደራቸውን ነው። በአንድ ጥሪ ወራኢሉ ላይ ተገናኝቶ በአንድ ቀን ድል እንዳደረገውም አላስታወሱም።
ለዚህ ድል መሰረቱ የአድዋ ድል መገኘትና የፈረንጆቹ እይታ ነው። በድሉ እኛ ከመፈንጠዝ አልፈን ጥቁር የሚባለውን ህዝብ ትችላለህ፤ ቀና ብለህ ሂድ ስንለው በተቃራኒው ፈረንጁ ግን አቀርቅሮ መሸነፍም እንዳለ ተመለከተ። ከፈረንጅ በላይ ማድረግ እንደምንችል በድሉ ብቻ ሳይሆን ተማራኪዎችን ሳይቀር በነጻነት ወደ አገራቸው የመለስን ህዝቦች ነን። ገለውናል፣ ወረውናል ብለንም አንገታቸውን በሰይፍ እንደሚጠብቁት አልቀላንም። ይልቁንም ሰብዓዊነትን የሚያከብር እንደኛ ማንም የለም የሚለውን አሳይተናል። ባህልና እምነታችንንም በአደባባይ ሰብከናል።
ጣሊያን በወቅቱ አውሮፓ ላይ ታላቅ መንግስት ካላቸው ተርታ የምትቀመጥ ናት። የምትተዳደረው በንጉስ ሲሆን፤ በጦር ሀይሏም ሀያል የምትባል አገር ነበረች። በኢንዱስትሪው ዘርፍም ከፍተኛው ደረጃ ላይ የምትቀመጥ ነች። ብዙ የአፍሪካ አገራትን የያዘችና የምታስተዳድርም ነበረች። ለአብነት እነ ቱኒዚያ፣ ሊቢያ፣ ሱማሌ ላንድንም ጭምር ተቆጣጥራ ነበር። ከዚያ ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ሞከረች። ይህ ደግሞ ምክንያቱ ሁለት ነው። የመጀመሪያው ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ መነሻ መሆኗን ማወቋ ሲሆን፤ ያንን የተቆጣጠረ አፍሪካንም ሆነ አውሮፓን መያዙ አጠያያቂ አይሆንም። እናም የወደፊት የፖለቲካ ፕሮግራማቸውን ይህንን አድርገው ለመያዝ ተንጠራሩ።
ከተሸነፉ በኋላ ከብዙ አገራት የተውጣጣ ዲፕሎማትን በማምጣት የዲፕሎማሲ ተልኳቸውን ከፈቱ። በፊት የማይፈልጓት አገራት ጭምር ታሪኳ በዓለም ሲናኝ ፈለጓት፤ ሁሉም ሊወሯት ተሰባሰቡባት። አሁን የሚታየው ኤንባሲ ሁሉ የተከፈተውና የተጀመረው በዚያን ጊዜ በሆነው ነው። አጼ ምኒልክ ብልጥ በመሆናቸውም ዳርዳሩንም ለማስጠበቅ ስለፈለጉ ከወንዝ በላይ ነበር የሰጧቸው። በወቅቱ ለስልጣኔ የነበረን ጉጉትም ከፍተኛ በመሆኑ ከእነርሱ እየተቀበልን መሄድና እዚያ ላይ ማተኮር ስንጀምር እነርሱ ቂማቸውን ለመወጣት ይሰሩ ነበር።
በበለጠ ወደ ክፍለ አገሩ በመሄድ ተራራውን፣ ወንዙን ማጥናት ቀጠሉበት። የህብረተሰቡን ቋንቋና ባህል እንዲሁም እምነት ጭምር መማሩን ተያያዙት። መጽሐፍቶቻችንን ሳይቀር ይመረምሯቸው ነበር። የባለስልጣኑን አመጣጥና ቤተሰቦቹንም በደንብ መርምረዋል። ማነው ሀይለኛ ማነው ደካማ የሚለውንም ለይተዋል። ይህ ደግሞ ለሚያስቡት መልካምም ሆነ መጥፎ ነገር የተሻለ እድል ሰጥቷቸዋል። ውስጥ አዋቂም አድርጓቸዋል።
አዲስ ዘመን፡– ለመሆኑ ለማሸነፋቸው ምክንያቱ ምንድን ነበር ይላሉ?
ልጅ ዳንኤል፡– ብዙ ነገሮች በማድረግ ነው። ለአብነት ከጣሊያን ወታደሮች ይማርኳቸው በነበሩ መሣሪያዎች ራሳቸውን እያደራጁ አብዛኛውን የገጠር ክፍል መቆጣጠራቸው አንዱ ነው። እንግሊዞች የጣሊያን ጠላት ሆነው ኢትዮጵያን መደገፍ ሲጀምሩም ወታደራዊ ድጋፍ ሰጥተው፤ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ሲረዷቸውም ተጠቀሙበት። በጄኔራል ካኒንግሂም የሚመራው የእንግሊዝ ጦር ከኬንያ ተነስቶ ከደቡብ አቅጣጫ ወደ መሀል ኢትዮጵያ ሲገሰግስ፤ በጄኔራል ፕላት የሚመራው ጦር ከሱዳን ተነስቶ ወደ አሥመራ፤ ከዚያም ከሰሜን አቅጣጫ ወደ መሐል ኢትዮጵያ ተንቀሳቀሰ። በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሚመራውና የአርበኞችና የእንግሊዝ አማካሪዎች የሚገኙበት ጌዲዮን ተብሎ የተሰየመው ጦር ደግሞ ከሱዳን ተነስቶ በኦሜድላ አልፎ በጐጃም በኩል ወደ መሐል አገር ገሠገሠ። ይህ በዘዴ እንዲመራ በማድረጋቸውም ነበር ለማሸነፋቸው ምስጢሩ።
ሌላው በመካከለኛ ኢትዮጵያ አርበኞች በጣሊያን ወታደሮች ላይ ጥቃታቸውን ማፋፋማቸው ነው። ጣሊያኖች ክፉኛ ተሸነፉ። በየቦታው ድል የመሆናቸው ዜና ተነገረ፤ ጣሊያኖች አዲስ አበባን ለቀው ፈረጠጡ። በዚህም ንጉሰ ነገስቱም ሚያዚያ 27 በአዲስ አበባ ታላቁ ቤተ-መንግሥት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ሰቀሉ። በአርበኞች ታላቅ ተጋድሎ፤ ኢትዮጵያ በዓለም ፊት በልጆቿ መስዋዕትነትና የደም ማኅተም ነፃነቷን አፀናች።
አዲስ ዘመን፡– ጣሊያኖችን ልዩ የሚያደ ርጋቸው ባህሪ ምንድነው?
ልጅ ዳንኤል፡– ጣሊያኖች እርስ በእርሳቸው ሀሳብ ይለዋወጣሉ። ይደጋገፋሉም። የእነርሱን የበላይነት እስካስጠበቁ ድረስ የሚደባበቁት ነገርም የለም። ምስጢርም ቢሆን ለራሳቸው ብቻ የሚፈልጉት ካልሆነ በስተቀር ያጋራሉ። የበላይነታቸው ከተጠበቀ ማንንም አይነኩም። ለበላይነታቸው ይሞታሉ። በዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ የገባውን ኬኒያ፣ ኡጋንዳ
ወይም ሌላ አገር ሊያዳክም ይችላል። እናም ዛሬ እንደሆነው በጋራ የመስራታቸው ሁኔታ የዛን ጊዜም አስተሳሰቡ ስለነበራቸው የተከፋፈሉትን ማንም መንካት እንደሌለበት ያውቃሉና ኢትዮጵያ የጣሊያን እንድትሆን በብዙ መንገድ ያግዛሉ። ይህንን ሲያደርጉ ደግሞ የነጭን የበላይነት አረጋግጠው ነው።
አዲስ ዘመን፡– ጣሊያኖች ይህ ድል ከመምጣቱ በፊት አዲስ አበባን የተቆጣጠሩት እንዴት ነበር?
ልጅ ዳንኤል፡– በወቅቱ ርዕዮት አለሙን ሊቀይር የሚችል ነገር በመፈጠሩና ብዙ ነገሮች መዳከማቸው ነው። ለአብነት ህዝብ እየተማረ፣ ስለአለም ሁኔታ እያወቀ፣ በኢኮኖሚውም እያደገ በመጣበት ጊዜ አዳዲስ የርዕዮት አለም ምልከታ ተፈጠረ። በተመሳሳይ የህዝብ ብዛት፣ የኢኮኖሚው መዋዠቅ፣ የኑሮ ውድነቱ፣ ሥራ አጥነቱ መበራከቱ የነበረውን መንግስት ለመገልበጥ እንዲነሳ አደረገው። ይህ ደግሞ ጣሊያኖች ከአገራቸው ውጪ ያለን ሀብት ወስዶ አገራቸውን ለማሳደግ ተጠቀሙበት።
በአርባ ዓመት ውስጥ አዲሱ ትውልድ በብዙ ነገሮች አገሩን ለውጧል። የካበተ ልምድ በእድገት ተለውጧልም። እናም ይህንን ለመውሰድ እኛ ያልደረስንበትን በማሳየት ኢትዮጵያን እንወራለን ብለው ተመልሰው ለመምጣታቸውም መንስኤ ነበር። በዚህም በ1928 ዓ.ም ኤርትራ ላይ ስለነበሩ ኢትዮጵያን ለመውረር በትግራይ ዋናውን ጦር በመያዝ ገቡ። በሱማሌ ላንድ በኩልም የመጡ ነበሩ። እነራስ ካሳ ፣ እነራስ ስዩም ተዋግተው ጦርነቱ የከፋ እንዳይሆን ቢያደርጉም አልተቻለም።
ጣሊያኖች አውሮፕላን ነበራቸው፤ በደቂቃ ከአምስት ሺህ በላይ ጥይት የሚተፋ መትረየስም እንዲሁ አላቸው። የሰለጠነ ወታደርም ይዘዋል። ኢትዮጵያን ግን ይህ የላቸውም። ብዙው አገሬን አላስደፍርም ብሎ በጀግንነት የወጣ ነው። ስለሆነም በዚህ ከቀጠሉ እንደሚያልቁ በማሰባቸውና የጣሊያንን ድል ማረጋገጥ እንደሚሆንባቸው ስለገመቱ ንጉሱ ሊግ ኦፍ ኔሽን ሄደው ቀደም ብለው በገቡበት መልኩ ለአለም መንግስታት አቤቱታ እንዲያቀርቡ ይደረግ ሲሉ ወሰኑ። ከእርሳቸው የበለጠ፣ ባለጉዳይም የበላይም የለምና ይህ መሆን አለበት ሲሉም ተስማሙ። ጦሩም ፊት ለፊት የሚያደርገውን መዋጋቱን ትቶ በሽምቅ ጦር የሚመጣውን ሀይል እንመክት፣ እናዳክመው ተባባሉም።
በዚያ ላይ የኢትዮጵያን አሰላለፍ በደንብ አድርገው ያውቁታል። በውትድርናው ደካማና ደካማ ያልሆነውን ስለለዩት የአለም መንግስታት አያግዟቸውምም። ንጉሱ እስከመጨረሻ ለመፋለምም ስለገቡ ቢሞቱ ጦሩ ይበተናል፤ ማንን ነው የምዋጋው ብሎም ከጣሊያን ወገን ይሰለፋል። ጣሊያን ኢትዮጵያን የመግዛት እድሉን ያገኛል የሚል ስጋት ነበረባቸውም።
በወቅቱ ኢትዮጵያዊያን ጀግኖች ሸሹና ተሸነፉም ተባሉ። ተዋጊዎቹ ግን ተሸነፍን አላሉም። የጦር ስልት ለወጥን ነው ያሉት። ይህ ደግሞ ትክክል ነው። ምክንያቱም ወይ መሞት ወይም ስልት ለውጦ መዋጋት የአማራጭ ጉዳይ ነው። ያም ስለሆነ ነበር አምስት ዓመታትን በጦርነት እንድንፋለም የሆነው።
ጣሊያን ሲገባ ሁሉም ዲፕሎማት እጁን ዘርግቶ በእንኳን ደህና መጣህልን ስሜት ነበር የተቀበለው። ለምን መጣህ፣ እንዴት መጣህ ያለው አልነበረም። ምክንያቱም ከላይ እንደተነሳው ፈረንጆች የነጭ የበላይነትን ሁል ጊዜ ማረጋገጥ ይፈልጋሉ።
አዲስ ዘመን፡– ጣሊያን ከአገር የተሰናበተው በየትኛው ትግል ነው። በአገር ውስጥ ታጋዮች ወይስ ንጉሱ ባደረጉት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት?
ልጅ ዳንኤል፡– እዚህ ላይ ሁለት ነገርን ማንሳት ያስፈልጋል። ንጉሰ ነገስቱ በአለም መንግስታት ስብሰባ ላይ የመጨረሻ ንግግራቸው ‹‹ ዛሬ እኛ ነን፤ ነገ ደግሞ እናንተ ናችሁ›› ብለው የተናገሩት አውሮፓን አጥለቅልቋል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ንጉሰ ነገስቱ ከጦርነቱ በፊት አውሮፓን ሄደው መጎብኘታቸውና ሲነግሱም ቢሆን የእንግሊዝ ልዑክ ሳይቀር መጥቶ የጎበኛቸው በመሆናቸው በብዙ አገራት ዘንድ ይታወቃሉና ነው። በተለያዩ ጊዜያት በሰሯቸው የዲፕሎማሲ ስራዎችም ብዙዎቹ ያደንቋቸዋል። በዚህም የጣሊያንና የኢትዮጵያ ጦርነት ሲነሳ የእርሳቸውን የዲፕሎማሲ ክብደት ያውቃሉና ጦርነቱ በእነርሱም እንደሚብስ ተረዱ። በዚህም የኢትዮጵያን ችግር ለመፍታት ንጉሰ ነገስቱን ወደ ኢትዮጵያ መመለስን አንዱ መፍትሄ ተደርጎ ተወሰደ።
እንግሊዞች ንጉሱን ደግፈው ወደ ኢትዮጵያ ሲያስገቡ የነበራቸው ሀሳብ ከነበሩት አርበኞች መካከል ደካማውን ፈልገው አገሩን ካረጋጉ በኋላ አገሩን ሊገዙ ነበር። ቦታውን እስከሚያዘጋጁ ድረስም ለረጅም ጊዜ ንጉሰ ነገስቱ አገራቸው ሳይገቡ ሱዳን ላይ አስቀምጠዋቸዋል። እንደውም ታኒጋን የተሰኘው የእንግሊዝ ወታደር አዲስ አበባ ገብቶ የእንግሊዝን ሰንደቅ ዓላማ አውለብልቦ ነበር። ይህ የሚያሳየው እንግሊዞችም በአንድ በኩል ንጉሱ አዲስ አበባ እንዲገቡ ይረባረባሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ሰንደቅ ዓላማቸውን ተክለው አገራችሁ የእኛ ነች በማለት መልዕክቱን ያስተላልፋሉ። ስለዚህም የተሸረበ ነገር እንዳለ ኢትዮጵያን ገባቸው።
በወቅቱ ይህንን ለማንም አልተነፈሱትም ከራሳቸው በስተቀር። ምክንያቱም እንግሊዝ ከአውሮፓው ሀያል እየሆነች መጥታለች። ለጀርመን እንኳን አልበገርም ያለች ነች። አፍሪካ ላይ ያለው ጦርም ቢሆን ጀርመንን ሳይቀር ያሸነፈ ነው። እናም ኢትዮጵያን ሊውጧት ሲሉም የኢትዮጵያ ጀግኖች አባቶች ከሱዳን ጀምሮ ያለውን ሁኔታ ይረዳሉና ከንጉሰ ነገስቱ ጋር በመሆን መፋለም ጀመሩ። በዚያ ላይ የእነርሱን ፖለቲካ የማይወዱ እንደ ጀነራል ዊንጌት አይነቶችም ስለነበሩ በጉዳዩ ላይ አጋዥ ሆነውላቸው አዲስ አበባ እንዲመጣ ሆነ።
ነገሮች እንዳይፋፋሙ ያደረጉት የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ናቸው። ምንም እንኳን እንግሊዞች የመጀመሪያውን በር ቢከፍቱም በዘዴ አይበገሬነ ታቸውን ያሳዩትም ጀግኖቻችን እንጂ ሌላው አጋዥ ኃይል አልነበረም። የእርስ በእርስ መቀያየም እንዳይኖርም አድርገው ነው በዲፕሎማሲያዊ መንገድ የተፋቱት። ስለዚህም ሁለቱም ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው ብሎ መውሰድ ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡– በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያ አርበኞችን ትግል እንዴት ይገልጹታል?
ልጅ ዳንኤል፡– እያንዳንዱን ኖሬ ባላሳይም አባቴ ያደረጉት ብቻ አርበኞቹ ምን ያህል ተጋድሎ እንዳደረጉ የሚያሳይ ነው። ምክንያቱም በቅርቤ ከአለው መነሳት ስላለብኝ ነው። ከእርሳቸው በላይም ያደረጉ እንዳሉ ግን ታሳቢ ይደረግ። እናም ወደ ምላሹ ስገባ አባቴ 150 የሚሆኑ ጣሊያኖችን በቤታችን እንዲኖሩ አድርጓቸዋል። እነዚህ ጣሊያኖች ደግሞ ባህሉን ጭምር እንዲኖሩት ተደርገው ነው ያደጉት። የእርሳቸው ወታደሮች ጭምር ወደ ከተማ ሲሄዱ ይጠብቋቸው ነበር። ምክንያቱም እንግሊዞች መጥተው በቅኝ ግዛት ይወስዷቸዋልና ነው።
ሁሉ ነገር በሰፈነበት ወቅት ንጉሱ የጣሊያን ጦር ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን አትንኩ ብለው ሲያውጁ ፣ ባንዳዎቹን ምህረት ሲያደርጉ እንግሊዞች ግን ጣሊያኖችን በቅኝ ግዛት እየወሰዱ ይጠቀሙባቸው ነበር። የእኛ መንግስት ግን ይቅርታ ስላደረገላቸው እንዲቀሩ አደረጓቸው። ለምን ቢባል መብራቱን፣ ስልኩን፣ መንገዱን የሚሰሩ እነርሱ ስለሆኑ ነው። እናም አባቶቻችን ከዚህ ጥቃት ጭምር የሚያድኑ ነበሩ። እንደውም በአንድ አጋጣሚ ከአባቴ ጋር ከሚኖሩ ጣሊያኖች ውስጥ አንዱን ሊወስዱት ሲሉ ደጃዝማች መስፍን ይደርሳሉ። ልትወስደው አትችልም ተባብለው ኮሎኔሉ በጥፊ የተመታበት ጊዜ እንደነበርም ሰምቻለሁ።
በውትድርናው ማዕረግ አባቴ ሻለቃ ሲሆኑ፤ የእንግሊዙ ወታደር ግን ኮሎኔል ነው። መበላለጥ በመካከላቸው አለ። ነገር ግን የሚያሸንፈው ባለአገር ነውና አሸንፈው ጣሊያኑን የራሳቸው አድርገዋል። ይሁን እንጂ ፈረንጅ እልኸኛ በመሆኑ ተከሰሱ። ከዚያ እንዳይቀርቡ ጠፉ። ስለዚህም በብዙ አርበኞች ቤት ጣሊያኖችን መሸሸግ የተለመደ ነበር። ስለዚህም እኛ ኢትዮጵያዊያን ጠላት የነበረውን ጣሊያንን ሳይቀር አቅፈን ከእንግሊዞች የታደግን ነን። በትዕዛዝም ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም ጥቅሙ የገባው ለአገር ያለውን ጥቅም አይቶ ያልገባው ደግሞ በትዕዛዙ መሰረት ለማድረግ ሲል ከውኖታል። ይህ ደግሞ ከጦርነቱ በኋላ የወደመውንና የፈራረሰውን እንዲገነባና ሥራ እንዲጀምር አድርገንበታል።
አዲስ ዘመን፡– በዚያ ጦርነት ምን አጣን ?
ልጅ ዳንኤል፡– የካቲት 12 ላይ ብዙ ህዝብ ያለቀው በዚህ ጦርነት ምክንያት ነው። በሀብት ደረጃ የእኛ ሊሆን የሚገባውን ጣሊያን ያመጣው ንብረትን እንግሊዞች ወደ ማላዊና ኬኒያ ወስደውታል። በምኒልክ ግቢ የነበሩትን ብዙ እቃዎችም ወስደዋል። በተለይ ወንበሮች፣ ስዕሎች፣ ጌጣጌጦችን፣ መጽሐፍት ሳይቀሩ ቅርሶች ተዘርፈዋል።
አዲስ ዘመን፡– የድል በዓሉ ብዙ ጊዜ የሚታየው በአዲስ አበባ ሲከበር ነው። ምክንያቱ ምን ይሆን ?
ልጅ ዳንኤል፡– በዓሉ የሚታወቀው የአርበኞች በዓል ተብሎ ነው። ይህ ግን ትክክል አይደለም። መባል ያለበት የድል በዓል ነው። ምክንያቱም አርበኞች ምክንያቶች፣ ደማቸውን ያፈሰሱት ናቸው። በዓሉ ደግሞ ድል የተገኘበት ነው። ድሉን ያስገኙት ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ ነው። በደርግ ጊዜ አርበኛ የሚባለው በሙሉ በጊዜው የተሾመ፣ የተሸለመ፣ ንብረት ያፈራ፣ ንብረት የተሰጠው ወይም ከፊውዳል ስርዓቱ ጋር ተዋልዶ የመጣ መሆን ነው።
የኮሚኒስት ርዕዮት አለም ሲመጣ ያንን በሙሉ የአገር ጠላት ተብሎ ተፈረጀ። ስለዚህ የዛሬ 50 ዓመት ጀምሮ በዓሎቹ እስከወረዳ ድረስ መከበራቸው ቀረና አሁን የምንጠቀምበት ጊዜ ላይ ደረስን። አከባበሩም በአዲስ አበባ ላይ ብቻ ተወሰነ። ሐውልቱን ሳይቀር ደርግ ማፍረስ ቢችል ኖሮ ያፈርሰው ነበር። ጊዜ ስላላገኘ አላደረገውም። ልክ እንደመጽሐፍቶቻችን በየሰፈሩ ያወድመው ነበር።
አዲስ ዘመን፡– ይህ በዓል ሲታሰብ ኢትዮጵያን ምንን ሊያስታውሱ ይገባል ይላሉ?
ልጅ ዳንኤል፡– አገራችን አሁን በበርካታ ችግሮች ውስጥ ትገኛለች። አንዴ በግጭቱ አንዴ በበሽታውም እየተዋከበች ነው። ብዙዎችም እየሞቱ ይገኛሉ። ሌላው ውጥረት ውስጥ የከተታት የህዳሴው ግድብ ጉዳይ ነው። ከውጪው አካል ብዙ ጫና እያረፈባት ነው። ከሱዳንና ግብጽ ጋር ያለው ጭቅጭቅም ቢሆን በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ምክንያቱም የአባይን ውሃ ግብጾች የሚፈልጉት ከራሳቸው አልፈው ሊነግዱበት ነው። ይህንን ለማሳካት ብዙ የአሜሪካ ዶላር አዲስ አበባ ውስጥ ይበትናሉ። ይህ ባለበት ሁኔታ ደግሞ አንዳንድ 10ና 20 ሺህ ዶላር ቢሰጠው ለማበጣበጥ ወደኋላ የማይል ሃይል አይጠፋም።
እጁ ላይ ያለውን እንጂ ሩቅ ሄዶ አገሩ ላይ የሚከሰተውንም አያስታውልም። ይህ የሆነው ደግሞ ለ50 ዓመት ያህል ትምህርት ቤቶቻችን ሲያስተምሩ የቆዩት ታሪክን ማጠልሸት እንጂ ታሪክን መገንባት ላይ አልነበረም። በደርግ ጊዜ ስለአገር ታሪክ የተማሩትም ቢሆን ቀይና ነጭ ሽብር ተብሎ አለቁ። አዲሱ ትውልድም የተማረው ታሪክ ታችነትን ነው። ስለሆነም ኢትዮጵያን ለማንሳት አስቸጋሪ በመሆኑ ዛሬ አወቅን የምንለው ማስተማር ይገባናል። የጀግኖች አርበኞችን ታሪክ እየነገሩ እነርሱን እንዲኖሯቸው ማድረግም ያስፈልጋል።
ወቅቱ ቴክኖሎጂ የሰፋበት በመሆኑም ዘመኑን የዋጀ ተግባር መከወን ከሁሉም ዜጋ ይጠበቃል። ለአገሩ የሚሆነውን ሁሉ በተግባር ማሳየትም አለበት። አሁን ያለው እንደ አድዋ አይነት የበዓል አከባበር የኢትዮጵያ ህዝብ ውስጥ የገባ ነው። ታሪኩንም እየተረዳ የሄደበት ጊዜ ሆኗል። እናም ከዚህ በበለጠ ታሪክ ሰሚ ብቻ ሳይሆን ታሪክ ሰሪም ለመሆንም መታተር ያስፈልጋል። የአድዋ በዓል ከጀግናውና ከመንግስት እጅ ወጥቶ ህዝቡ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ መጠቀሙም በእጁ ላይ ነው።
ማንነትን ማወቅ የሚቻለው የነበረን ታሪክ በአግባቡ ማወቅ ሲቻል ነው። ኢትዮጵያ እንድትበጣበጥ ያልታሰበበት ጊዜ የለም። ግን ታሪክ አዋቂና ማንነታቸውን የለዩ ኢትዮጵያን በመኖራቸው ነው መቆም የቻለው። እናም ማንም አካባቢ ለሚፈጠረው ችግር እኛም አለንበት ባይን ዛሬም ልናነግበው ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡– በመጨረሻ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ?
ልጅ ዳንኤል፡– ከታሪካችን እንደምንረዳው የፈረንጅ ትምህርት ባይኖረንም ፈረንጆች የሚቀኑብን ብዙ ታሪክ ያለን ነን። ትምህርት፣ ባህል፣ ታሪክ ይቀናሉም። እንዴት ይህንን ያህል ቋንቋ ያለው ሰው በአንድነት አብሮ ይኖራል የሚለውም ያስገርማቸዋል። በዚህም አሁንም ሊለዩን ይፈልጋሉ። ነገር ግን መቼም አይቻላቸውም። አሁን ልዩነታችን እየሰፋ ነው ቢባልም መቼም በአገራችን አንደራደርም። ልጆቻችንም አይለያዩም። አንሸነፍላቸውምም። ቂምና በቀሉን ትቶም ሁሌም አንድነቱን ስለሚያጠነክርም ነው ኢትዮጵያኑን ከአፍሪካውያን የሚለየው።
ኢትዮጵያዊያን የሌላው አገር ህዝብ አንድ እንዲሆን የምንፈልግም ነን። ስለዚህ ይህንን እያሰብንም መንቀሳቀስ አለብን። አገሪቱ ከድህነት እስካልተላቀቀች ድረስ ሁልጊዜም አለመረጋጋት ይኖራል። በመሆኑም ከድህነት ለመውጣት መጣርም ያስፈልጋል። እኔ እበልጣለሁ እኔ እበልጣለሁ ባይነቱ የጥቂቶች ነውና ላለመታለል መሞከር አለብንም። ምሁር ሳይሆኑ ምሁር ነኝ የሚሉትንም መጠንቀቅ አለብን። ችግር ሰው ሰራሽ እንጂ አብሮ የተወለደ አይደለም፤ የውስጥ በሽታም አይደለም። ይህ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ተላልቀን ነበር። ይህንን ማሰብም ያስፈልጋል።
በውስጥ ያለብንን አለመግባባት ገመድ በመጎተት ማስፋት አያስፈልግም። ከዚያ ይልቅ በመወያየትና በመግባባት መፍታት የሁልጊዜ ስራችን መሆን አለበት። ያንን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ ቤተሰብ ልጁ ላይ ሲሰራ ነው። ህብረተሰቡም በተለያዩ መንገዶች ታዳጊውን ማስተማር አለበት። ትምህርት ቤቶችና የተለያዩ ተቋማትም እንዲሁ መስራት ይኖርባቸዋል። በኢትዮጵያዊ ስሜት መንቀሳቀስና የተለያዩ ንቅናቄዎችንም ማድረግ ከምንም በላይ ያስፈልጋልም።
አዲስ ዘመን፡– ስለሰጡን ማብራሪያ እጅግ እናመሰግናለን።
ልጅ ዳንኤል፡– እኔም አመሰግናለሁ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 27/2013