ኢትዮጵያ ሀገራችን በዘመኗ በርካታ አስቸጋሪ ጋሬጣዎች ገጥመዋታል። እንደ ቅርጫ ስጋ ሊቀራመቷት የተነሱ የውጪ ወራሪ ሀይሎች ከቀኝ ከግራ ተነስተውባታል። በቀኝ ተገዥነት ሊያንበረክኳት በተደጋጋሚ ጊዜ ወረዋታል። ከውስጥም ከውጪ የጠላት ሀይል ተፈታትኗታል። ሆኖም በታሪኳ ለአንዱም አልተንበረከከችም። ታሪክ የሚመሰክረውም በተግባር ያረጋገጥነውም የወረሯትን ሀይሎች፤ የተነሱባትን ጠላቶች ሁሉ ድል አድርጋ ዛሬም ድረስ የድል ብስሯቷን እያስታወሰችና እያከበረች እንዳለች ነው።
ይሁን እንጂ ዛሬም በእኛ ዘመን ሀገሪቷን ለማፍረስ፣ ህዝቧንም ለመበትን እና ዳር ድንበሯን ለመድፈር ብዙዎች ቋምጠዋል። ከውስጥና ከውጭ ሆነው ታግለዋል፤ አሁንም ከባድ የትግል ወቅት ላይ እንገኛለን። ይሄ የሀገርን ሉአላዊነት የማስከበር ትግል ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል፤ የሰዎችን ህይወት ሊያስገብር ይችላል። የኢኮኖሚ ድቀትን ሊያመጣ ይችል ይሆናል። ነገር ግን ሀገራችን ለማንም በምንም ምክንያት ልትንበረከክ አትችልም። የጀግንነት ታሪኳን ሊያጎድፍ የሚችል ሀይልም አይኖርም። ይልቁንም ዛሬም እንደትላንቱ በጀግኖች ልጆቿ ታሪክን ትደግማለች። ጠላቶቿን ታንበረክካለች። ለማንም ቀኝ እንዳልተገዛች ሁሉ አሁንም ለማንም በምንም መልኩ ሸብረክ አትልም፤ አትገዛም።
ቀደም ባሉት ዘመናት በሀገር ውስጥ በመሳፍንቱና በመኳንንቱ በኩል ቅራኔዎች ነበሩ። ጣሊያንም ይሄንን ቅራኔ መጠቀሚያ አድርጎ ኢትዮጵያውያኑን በዘር ከፋፍሎ አንዳንዱንም ባንዳና ቅጥረኛ አድርጎ ሀገሪቱን በቀኝ ለመያዝ እንደ መልካም አጋጣሚ አድርጎ ሊጠቀምበት አስቦ ነበር። ሆኖም ግን የኢትዮጵያውያን የሀገር ስሜት እንዳሰበው ሳይሆን ለሀገሩ ክብር ግንባር ደረቱን ለጥይት የሚሰጥ ሆኖ አገኘው።
በየዘመኑ ከሀገር መሪዎች፣ አስተዳዳሪዎች ጋር የሀሳብ እና የአስተሳሰብ ልዩነቶች፣ የጥቅም ግጭቶች ነበሩ። አሁንም ይሄን መሰል ልዩነቶች ይኖሩ ይሆናል። ይሁንና ልዩነቱ፣ አለመስማማቱና በአንድ ሆኖ አለመታየቱ በሀገር ሉአላዊነት ላይ ሲሆን መልኩ ይቀየራል። ለውጪ ወራሪ ሲሆን መልኩ፣ ቅርጹና አይነቱ ይለወጣል። ልዩነቱ ሁሉ ውበት ሆኖ በአንድነትና በእናት ሀገር ስሜት በቆራጥነት ቀፎው እንደተነካበት ንብ አንድ ሆኖ በጋራ ይቆማል። የውስጥ ልዩነቶቻችን ወደ ጎን ይቆየንና ለአንድ ሀገራችን በጋራ እንቆማለን የሚለው ወደፊት ይመጣል። ይሄ ዛሬ የተጀመረ ብቻ ሳይሆን እስካሁንም ልዩነታችንን ለማጥቂያ ሊጠቀሙበት ለከጀሉት ሁሉ የተሰጠ ምላሽ ነው። ጠላትን በተደጋጋሚ ጊዜ አሳፍረን የሸኘነው በዚህ መንገድ ነው።
ኢትዮጵያውያን ለወዳጆቻችን ፍጹም ታማኝ ፣ ለፍትህና እኩልነት የተባበርን የነፃነት አርበኞችን ያሰለጠንን ህዝቦች ነን። የተገፉና የተሰደዱ ፤ አምነውን የተጠጉንን ህዝቦች አክብረንና አቅፈን የያዝን፤ ዛሬም ሀገር እያላቸው በሀገራቸው ሰላም አጥተው የተሰደዱ ስደተኞችን ተቀብለን የምናስተናግድ ህዝቦች መሆናችን ለአንድ ጊዜም ሊዘነጋ አይገባም። ይሄም ሆኖ በየዘመኑ ጠላት ዓይኑን በሀገራችን ልማትና ዕድገት ላይ ማነጣጠሩ አልቀረም። እርስ በእርስ ሊያባሉን የሚሞክሩ ብዙ ናቸው። ሆኖም የሞከሩን ወድቀዋል፤ ሊጥሉን ሲገፉን ይበልጥ አንድ ሆነን ጠንክረን ቆመናል። ይሄ ጀግንነታችን ጥንካሬያችን መቼም አይፈረከስም። አሁንም ዳር ሆነው ሊቀራመቱን ላሰቡት ውስጥ ሆነው ለተባበሩት መልሳችን አንድ ነው። አንድ ሆነን ልዩነታችንን ለነገ አሳድረን ለእናት ሀገራችን እንቆማለን። እናት ሀገራችንን ከገባችበት ማጥ አውጥተን ወዳሰብነው የብልጽግና ማማ በዳግም ድል እናሻግራለን።
የማያውቁንም ሆነ አውቀውም የዘነጉን ወዳጅ ጠላቶቻችን ሊያስታውሱና ሊያውቁ የሚገባቸው ጉዳይ ቢኖር ኢትዮጵያ በታሪኳ ሁሉ የማትንበረከክ ሀገር መሆኗን ነው። ኢትዮጵያውያን ቀኝ ግዛትን ዛሬም ትላንትም የታገልን፤ ታግለን ያሸነፍን መቼም ለባርነት እጅ የማንሰጥ ህዝቦች ነን። ለነፃነትና እኩልነታችን ለሀገራችን ዳር ድንበር የሀያላኑ ጫና ቢበረታ፣ አስፈራውና አማላዩ ቢበዛ ዛሬም ነገም አንበረከክም። እስካሁን በየዘመናቱ ሁሉ ጫና ሊፈጥሩ የሻቱትን ሁሉ በአንድነት አሽቀንጥረን ጥለናል። በየትኛውም አቅጣጫ የመጣብንን ሀይል የምንመልሰው በተመሳሳይ መንገድ ነው። የዛሬው የአርበኞችን የድል በዓል ስናከበር በዚሁ የጀግንነት ስሜት መሆን አለበት።
በፍቅር በወዳጅነት ለቀረቡን ደግሞ እንግዳ አስተናጋጆች፣ የተቸገረ ረጂዎች የተሰደደ ተቀባይ ህዝቦች መሆናችንን የታሪክ መዛግብት እማኝ ምስክሮች ናቸው። በሀገራችን ላይ በጠላትነት ለመጣብን ደግሞ አራስ ነብር ነን። ኢትዮጵያዊነት ማለት ይሄ ነው። ጠላቶቻችን ከውስጥም ከውጪም እንደሚያስቡትና እንደሚገምቱት የውስጥ ሰላም ሲደፈርስ ሀገራችንን ለጠላት አሳልፈን የምንሰጥ ህዝቦች አይደለንም። ልዩነታችንን በይደር አቆይተን የእናት ሀገራችንን ዳር ድንበር እናስከብራለን። በአጠቃላይ በየጀግኖች እናት ኢትዮጵያን በታሪኳ ሁሉ ማንበርከክ አልተቻለም፤ አሁንም አይቻልም !
ምድር ላይ እስካሁን ድረስ እንከን የለሽ የሚባል ፍጹማዊ የሕዝብ አስተዳደር ሥርዓት አልተፈጠረም። ምናልባት እንደዚያ ዓይነቱ ፍጹማዊ የአስተዳደር ሥርዓት የሚሆነው ፈጣሪ በሚያስተዳድረው በሰማያዊው ዓለም ይኖራል ብዬ አምናለሁ። ያም ሆኖ የሰው ልጆች ለዘመናት ባደረጉት ያለሰለሰ ጥረት ፍጹምም ባይሆን በአንጻራዊነት የተሻለ የሚባል የፖለቲካ ሥርዓት ማንበር ችለዋል።
ይህም ከዛሬ አንድ ሺህ ዓመት በፊት “ፖሊስ” ብለው በሚጠሯቸው ትንንሽ የከተማ መንግስታቶቻቸው በተለይም አቴናውያን እንደጀመሩት የሚነገረው “ዲሞክራሲ” በመባል የሚታወቀው የመንግስት አወቃቀርና የሕዝብ አስተዳደር ዘይቤ ነው። “ዲሞክራሲ”፡- “ዲሞ” = “ሕዝብ” እና “ክራሲያ” = “አስተዳደር” ከሚሉ ሁለት የግሪክ ስርወ ቃላት ጥምረት የተገኘ ቃል ነው “የሕዝብ አስተዳደር” የሚል አቻ የአማርኛ ትርጉም ይሰጠዋል።
እንደ ፖለቲካ ሥርዓት ተወስዶ ሲታይ ምንም እንኳን ዲሞክራሲም የራሱ የሆነ ህፀፅ ባይታጣውም በአንጻራዊነት የተሻለ ያስባለው ዋነኛው ሚስጥራዊ ምክንያት ስያሜውን ከፈጠሩት ሁለቱ ቃሎች መካከል “ሕዝብ” የምትለዋ ባለ ከባድ ሚዛን ቃል ናት። ምክንያቱም “አስተዳደር”ማ በአንድ ግለሰብ አራጊ ፈጣሪነት ወይንም በጥቂት ቡድኖች የበላይ ፈላጭ ቆራጭነት ብቻ ላይ የተመሠረተ “ንጉሳዊ” እና “አንባገነናዊ” አስተዳደርም አለ።
እናም አስተዳደር በዋነኝነት ሕዝብን የሚመለከት ጉዳይ በመሆኑ ዲሞክራሲ ደግሞ መሠረቱን ሕዝብ ላይ ያደረገ የአስተዳደር ስርዓት በመሆኑ ፍጹም እንኳን ባይሆን ከሌሎች የተሻለ እንዲሆን አድርጎታል። የሰው ልጅ ደግሞ በባህሪይው የተሻለውን በመምረጥ ህይወቱን የሚመራ ፍጡር በመሆኑ እስካሁን በዓለም ላይ ከተፈጠሩ የአስተዳደር ሥርዓቶች ሁሉ የበለጠ ዲሞክራሲ በብዙሃኑ ዘንድ ተቀባይነትን እንዲያገኝና በብዙ እጥፍ ከሚበልጡት ከአንጋፋዎቹም ሆነ ከዕድሜ እኩዮቹ የተሻለ አሁንም ድረስ በዓለም ላይ ተመራጭ ሥርዓት ሆኖ እንዲቀጥል አስችሎታል።
እንግዲህ በዚህ መንገድ የዲሞክራሲን አንጻራዊ የተሻለ ሥርዓትነት ሚስጥር በዚህ መንገድ ለማየትና ያየነውን ለማሳየት ሞክረናል። አሁን ደግሞ ዲሞክራሲ ካነሳነው ርዕስ ጋር በቀጥታ የተሳሰረባቸውን ቋጠሮዎች አንድ በአንድ እየፈታን፣ ከሃሳብነት አውጥተን ወደ መሬት አውርደን፣ ከነባራዊው እውነታ ጋር አገናኝተን በገሃዱ ዓለም ውስጥ ያለውን ተግባራዊ ግልጋሎት ከውጭ ቆመን ሳይሆን ከውስጡ ሆነን በግዙፍ ለመመልከት እንሞክራለን።
በአንጻራዊነት የተሻለ ሥርዓት እንዲባል ካደረጉትና ዲሞክራሲን ዲሞክራሲ እንዲሆን ካደረጉት ነገሮች መካከል አንዱና ዋነኛው ምርጫ ነው። ምርጫ ሲባል በፖለቲካዊና መንግስታዊ አወቃቀር ስርዓቱ ውስጥ ዜጎች በቀጥታ ወይም በውክልና መሪዎቻቸውን የሚመርጡበትና ሕዝብ በመረጠው አካል የሚተዳደርበት ሁኔታና አሠራር መኖር ማለት ነው። ምርጫ ሲባል በዜጎች ቀጥተኛና ንቁ ተሳትፎ የተመረጠ መንግስት ሃገርን የሚያስተዳድርበት ሥርዓት መኖር ማለት ነው።
ነገር ግን የሚደረገው ምርጫ ምን ዓይነት ምርጫ ነው? ይህ ነው የዲሞክራሲያዊ ስርዓት አጥንትና ደም ሆኖ የሚያገለግለው ዋነኛው የዲሞክራሲ መገለጫ የሆነው ምርጫን የሚመለከተው ወሳኝ ጥያቄ። በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ የሚደረገው ምርጫ በህግ በተደነገገ በተወሰነ ጊዜያት ልዩነት ወቅቱን ጠብቆ የሚካሄድ፣ ሁሉም ዕድሜያቸው ለመምረጥ የደረሱ ዜጎች በምልዓት የሚሳተፉበት፣ ከማናቸውም ዓይነት የአስፈጻሚው አካልም ጣልቃ ገብነት ነጻ የሆነ፣ ፍትሐዊ የሆነ ምርጫ ነው። ዓላማውም ዜጎችን የስልጣን ባለቤት ማድረግ ነው። ስልጣን ብቻ ሳይሆን ተጠያቂነት ያለው መንግስት መመስረት ነው። ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ዲሞክራሲያዊ መንግስትን ብቻ ሳይሆን ዲሞክራሲያዊ ሕብረተሰብም የሚፈጠረበት ሥርዓት መሆኑ ይታወቃል። ዲሞክራሲያዊ ህብረተሰብ ማለት መብትና ግዴታቸውን ለይተው የሚያውቁ፣ ለነጻነታቸው የሚከራከሩ፣ በሃገራቸው ሁለንተናዊ ጉዳይና በመንግስት አሰራር ላይ በንቃት የሚሳተፉ ጠያቂና ያገባኛል የሚሉ ዜጎችን ያቀፈ ሕብረተሰብ ነው።
ከዚህ አኳያ በእኛም አገር በቅርቡ የሚካሄደው ስድስተኛው ሃገራዊ ምርጫም እነዚህን የዲሞክራሲ ትሩፋቶች ለዜጎች ማቋደስን ዓላማው ያደረገ ሊሆን ይገባዋል። ምርጫውን በመጠቀም ሃገራችንን ለረጅም ዘመናት ወደ ኋላ ሲጎትታት የኖረውን በተንኮልና በሴራ ላይ የተተበተበውን፣ በኃይልና በጠብ-መንጃ ላይ የተመሰረተውን የስልጣን ሽግግርና አውዳሚ የፖለቲካ ባህል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መለወጥ ይገባል። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ሃገራችን የብዙ ሺህ ዓመታት የዳበረ ሥጋዊ መንፈሳዊ ሃብት ባለቤት፣ ከሁሉም በፊት የነቃች፣ የሰው ዘር መገኛና የሰው ልጆች ስልጣኔ መነሻ እርሾን የጣለች አኩሪ ታሪክ ያላት ታላቅ ሃገር ብትሆንም ቀድማ ወደፊት መጓዝ ያልቻለች መሆኗ ማስረጃ የማያሻው እና ማንም ሊያስተባብለው የማይችለው የኢትዮጵያውን ሁሉ መራራ ሃቅ ነው።
እንዲያውም የቀደምትነቷን ያህል በጀመረችበት ፍጥነት መጓዝ ቢያቅጣት እንኳን የያዘችውን አስጠብቃ መቀጠል አቅቷት በብዙ መልኩ ከነበረችበት ተንሸራታ ጀማሪ ኋላቀሪ ሃገር መሆኗን የአሁኑ ታሪካችን ቁልጭ አድርጎ እያሳየን ነው። በመሆኑም የቀዳሚ ኋላቀ ርነታችንን መሰረታዊ መንስኤ በጥልቀት በመርመርና ወደፊት እንድንጓዝ የኋልዮሽ አስሮ ጠፍንጎ የያዘን ዋነኛ ችግራችን ምን እንደሆነ ማወቅና ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ በማበጀት ከወደቅንበት ተነስተን ታላቋ ሃገራችን እንደጅማሬዋ ከፊት ቀድማ የምትገኝበትን ብልሃት መዘየድ ተገቢ ነው።
ለዚህም በቅድሚያ የችግሩን መንስኤ ለይተን ማወቅ ይጠበቅብናል። ከዚህ አኳያ ለመሆኑ ታላቋን ሃገር ኢትዮጵያን በጀመረችው ፍጥነት ወደፊት እንዳትጓዝ፤ ባለችበት ቆማ እንድትቀርና ይባስ ብሎ በየጊዜው ወደ ኋላ እየተንሸራተተች ቀድሞ ኋላ ቀሪ እንድትሆን ያደረጓት ችግሮች ምንድናቸው? ብለን የጠየቅን እንደሆን በርካታ ምክንያቶችን እናገኝ ይሆናል።
ኢትዮጵያን ባለችበት እያስረገጠ አንዳንዴም የኋልዮሽ እያስጓዘ ከዓለም ቀድማ ከጀመረችው የመሪነት ጉዞ አሰናክሎ አድርቆ ያሰቀራት ክፉ ጠላት የስልጣኔና የዕድገቷ አቀንጭራ ግን አንድ ነው። እርሱም በመንግስትና በሕዝብ አስተዳደር ሥርዓቷ ውስጥ ሰርፆ የገነገነው፣ ሁል ጊዜ የማያድገውና ከዓለም ኋላ ቀርቶ ኋላ የሚያስቀረው ቆሞ ቀሩ የፖለቲካ ባህሏ ነው። በእኔ ዕምነት ከጥንት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ከብሉይ እስከ ሐዲስ ታላቂቷ ሃገር ታላቅ መሆን በሚገባት ደረጃ ታላቅ እንዳትሆንና በተነሳችበት ልክ ወደፊት እንዳትጓዝ ከኋላ ሆኖ ሲጎትታት የኖረው የኢትዮጵያ ዋነኛው ችግር በሴራ፣ በጥላቻና በመጠላለፍ ላይ የተመሰረተው ይኸው ኋላ ቀሩ የፖለቲካ ባህላችን ነው።
ምርጫውን እንደ መልካም ዕድል በመጠቀም ለዘመናት አስሮ ከያዘን ከዚህ ጎታች ኋላ ቀር የፖለቲካ ባህላችን ቆርጦ የመውጣት ኃላፊነቱ ግን ለአንድ ወገን ብቻ የሚተው ሳይሆን የሁላችንም ነው። መንግስት ምርጫውን ነጻና ፍትሐዊ የማድረግ ኃላፊነት አለበት። የተለያዩ ማህበራዊ ቡድኖችን ፍላጎቶችና አስተሳሰቦች በመወከል ስልጣን ለመያዝ በምርጫው የሚወዳደሩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲደረግ መታገልና በምርጫው መሳተፍ ይጠበቅባቸዋል።
በተጨማሪም ፓርቲዎች የህብረተሰቡን መሰረታዊ ችግሮች ነቅሶ በማውጣት የፖሊሲ ሃሳቦችን በማፍለቅና ነባር ፖሊሲዎችም የሚሻሻሉበትን መንገድ በመፍጠር፣ የዜጎችን የተሳትፎ ደረጃ በማሳደግ መሪዎች የሚፈጠሩበትን መድረክ ማመቻቸት፣ የመንግስት ተጠያቂነትና መልካም አስተዳደር እንዲጎለብትና ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ባህል እንዲዳብርና ዲሞክራሲያዊ መንግስት እንዲቋቋም ማድረግም ይጠበቅባቸዋል።
ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎችንና ህዝባዊ ማህበራትን በተሻለ ቅንጅትና ስልት እንዲደራጁ በማድረግና የማደራጀት ነጻነት እንዲኖር በማድረግ የህብረተሰቡን የፖለቲካ ተሳትፎ ማሳደግና የመራጩን ህዝብ ቁጥር እንዲጨምር በማድረግ ዲሞክራሲንና ዲሞክራሲያዊ ህብረተሰብን በመገንባት ረገድ ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ ይገባል። ዜጎች በወቅቱ የምርጫ ካርዳቸውን ወስደው ይበጀኛል የሚሉትን ተወካያቸውን በመምረጥ በተቀናጀ የጋራ ኃላፊነት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን አምጦ ለመውለድ በሚደረገው ጥረት በባለቤትና በያገባኛል ባይነት በንቃት መሳተፍ ይገባቸዋል።
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 27/2013