በሰሞነ ህመማት ላይ ሆነን የመድሃኒቱን የክርስቶስን ህማም ስናስብ፤ የስቅለቱ እለት የደረሰበትን መከራ ስናይ መንገላታቱ ፣መውደቅ መነሳቱ፣ ፍዳው፣ መከራው፣ የደሙም መፍሰስ፤ ረሀብ ጥማቱ ከፊታችን ድቅን ይላል። አሁን በኢትዮጵያ የሚታየው ግድያ፣ መፈናቀል፣ ግጭትና ድንጋይ መወራወር ኢትዮጵያ በሰሞነ ህማማት ውስጥ ያለች፤ የአርብ ስቅለት ላይ የደረሰች አይነት ሃሳበ ውስጤ ይመላለሳል።
እርስ በእርስ መወነጃጀል ፣መከደዳትና ሴራ መሸራረብ ባለባት ሀገር ውስጥ ሆኜ እንደ ይሁዳ በሰላሳ ዲናር ጌታውን የሸጠውን ያህል ህሊናቸውን አሳውረው ለሆድ ያደሩ፤ የሌላው ዋይታ የማይሰማበት ልጆቿን ሳይ ሀገሬ የስቅለቱ የሰቆቃው አርብ ላይ ናት ብል ማጋነን አይሆንም። ዶሮ ሳይጮህ ሶስቴ ትከደኛለህ እንደተባለው እንደ ደቀመዝሙሩ ይሁዳ ህዝባቸውንና አገራቸውን በከዱ ባንዳዎች መካከል መቆም ያማል።
አዳኙን፤ የዘላለም ህይወት ለጋሹን፤ መኖሪያ የሆነውን ፈጣሪ ላይ ፍፁም የጥላቻ ስሜት ሲያጸባርቁ፤ በተመሳሳይ ህዝቧን ሰብስባ ለማኖር ምንም ያልተሳናት ሀገር፤ በውስጧ ሞልቶ የተተረፈ ሀብት የታመቀባት ምድር ፤ ልጆቿ በድሎት ሊኖሩባት የሚችሉባት መሆኗን ዘንግተው እርስ በእርስ ዘር ለይተው እየተጣሉና ሲገዳደሉ ስታይ እውነትም ሀገሬ የሰቆቃው አርብ ላይ ናት እንድል ያደርገኛል።
ተወደደም ተጠላም ሀገሬ ሶስት ቀን ሶስት ሌሊት በመቃብር ውስጥ ብትሰነብትም ትንሳኤዋ አይቀርም።ከትንሳኤዋ በፊት መከፈል ያለበትን ዋጋ እየከፈለች ያለች ቢሆንም በሰሞነ ህመማት ታማ በሰቆቃ ውስጥ ተሰቃይታ አልቅሳ አንብታ እንባዋ ሊታበስ የአርቡ አመሻሽ የእንግልቱና የሰቆቃው ማብቀቂያ ላይ የቆመች ትመስለኛለች።
በፀሎተ ሀሙስ ጌታ ደቀ መዛሙርቱን ሰብስቦ በአንድ መአድ ሰብስቦ እንደመገባቸው ከእናት ምድሯ በረከት ልጆቿን ሰብስባ የመገበችበት ምሽት ነግቷል፤ የሚሸጠው ደቀመዝሙርም የሚከዳውም በየቦታው ተሰግስገዋል።ከእጇ እንዳልበሉና እንዳልጠጡ ሁሉ ጉንጯን ስመው ለጠላት አሳልፈው ሊሰጧት የተሰናዱበት ጊዜ ላይ ነን።ይህ መራር ፅዋ የሚጨለጥበት ወቅት ላይ ስለሆንን ሀገሬ ይች ፅዋ ካንቺ ብታልፍ እያልኩ እመኛለሁ። ከቅን ዜጎቿና ለአገራቸው እንደ ሻማ ቀልጠው ብርሃን ለመሆን ከተዘጋጁ የቁርጥ ቀን ልጆቿ ጋር ታልፈዋለች ብዬ አምናለሁ።
የንጹሃን መፈናቀል ፣ መገደል፣ መቸገርና መከራ ማየት ህምም ቢሆንም አገሬ ፈውስ እንደምታገኝ አምናለሁ፤ በጎ አሳቢ ዜጎቿ መከራዋን ያሳጥሩላታል ፤ የግጭቶችና የሴራዎች ደራሴና ተዋንያን የሆኑ እኩያንን ያስታግሱላታል። ጠላቶቿን አፋቸውን ያዝጉላታል፣ ሴራዎቿን ያከሽፉላታል ብዬ እተማመናለሁ።
ፈጣሪን ይሰቀል! ሰቀለው! ስቀለው! እያሉ እንደጮሁት መከራና ህማም ወደ ህይወታቸው የማይገባ እንደመሰላቸው እንደ አይሁዳውያኑ አንዱ ሲሞት የወገን ደም ሲፈስ ወደእኔ አይመጣም በሚል የተኙትን ያነቃላታል። የሰው መርገፍ የማያስደነግጣቸው የዘመናችን አይሁዳውያን ሀገራችን ላይ ሞልተው ሀገሬ እንደ ክርስቶስ የምትሰቀልበት መከራዋን የምታይበት እሷ ተሰቃይታ ለቀረው የተስፋ ብርሃን የምታመጣበት አርብ ላይ ናት ማለት ልክ አይሆን ይሆን ብዬ እጠይቃለሁ?
በአሁኑ ጊዜ የተከበረ የተፈጥሮ ፀጋዋን፤ ውብ ሸማዋን፤ የሀገር ልብሷን አባይን፤ ትደምቀበት ዘንድ ልታስጠልፈው ብትነሳ የክርስቶስን ልብስ እንደገፈፉት የእሷን መጎናፀፊያ ገፈው እርቃኗን ሊያስቀሯት የሚታትሩት ብዙ ናቸው።ሆኖም እነዚህን ፈተናዎች አልፋ፣ የሴራ ድሮችን በጣጥሳ እንደ ክርስቶስ ትንሳኤ የምታበስርበት ጊዜ ሩቅ አይሆ ንም።
ለተራበና ለተጠማ መጋቢና አጠጭ ለሆነው ጌታ ተጠማሁ በላበት ወቅት ላይ የፈጠረውን ውሃ ከልክለው መራሩን ሀሞት እንዳስጎነጩት ሁሉ ሀገሬ የዳቦ ቅርጫት የሚያደርጋት የተፈጥሮ ፀጋ ባለቤት በሆነችበት ጊዜ በልጆቿ መቦጫጨቅ የተነሳ በረሃብ እጆቿን ወደ ውጭ ዘርግታለች።ሆኖም ችሮቿን አልፋ ልማቷን አልምታ የበለጸገች እንደምትሆን አልጠራጠርም።
ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ወደ መጠናቀቁ ምዕራፍ ላይ ነው።ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች እየተስፋፉ ናቸው።ገበሬው የዘመናዊ እርሻ ዘዴዎች ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ተስፋ ሰጪ ናቸው።አገሬ አሁን ያጋጠሟትን ፈተናዎችን አልፋ እነዚህ የልማት ስራዎችን ተጠናክረው ሲቀጥሉ ትበለጽጋለች፤ የህዝቦቿ ኑሮ ይሻሻላል።
አምላክን መስቀሉን አሸክመው ጉዞ ወደ ጎሎጎታ ተራራ ባዳረጉበት ወቅት፤ መውደቅ መነሳቱ፤ መንገላታቱ ይታወቃል።ሀገሬም በልጆቿ ህማም መከራ የወደቀች የተነሳችበት፤ የዜጎቿ ስደት የሰቆቃ፣ እንባ የፈሰሰበት የመከራ ዳገቷን ጫንቃዋ ላይ እጥፍ ድርብ የችግር ቀንበር ተሸክማ ደፋ ቀና ስለማለቷ አጠያየቂ ባይሆንም ትንሳኤዋ ተቃርቧል።
ሊነጋ ሲል ይጨልማል እንዲሉ በጥቅም አይናቸው የታወሩ ሀገራቸውን የከዱ ባንዳዎች ፣ በውስጥም በውጭም ያሉ ሃይሎች ቢያስቧትም እንባዋ መታበሱ አይቀርም። የመከራው የዋይታው የሰቆቃው አርብ ላይ ያለች ይመስለኛል።
በእንባ ተሸኝታ ገድለን ቀበርናት ብለው አታሞቸውን የሚደልቁት ደስታቸው ለአፍታ ሳየቆይ እንደ ክርስቶስ ትንሳኤ ሁሉ የሀገሬ ትንሳኤ በብረሃን ታጅቦ በታላቅ መነቃቃት ህዝቧን ባሳመነ መልኩ ፀብ ክርክር በራቀበት፤ መከባበር የሁል ጊዜ ቋሚ ቅርሷ የሚሆንበት ሁኔታ መፈጠሩ አይቀርም። ዘረኝነቱ ጎጠኝነቱ ከላይዋ ተጠራረጎ፤ ሁሉም ፊት ላይ የታየው ኀዘንና እንባ ተወግዶና ታብሶ ጥሩ ዘመን መምጣቱ አይቀርም።ለዚህ ትንሳኤ ግን ሁሉም ኢትዮጵያዊ እጅ ለእጅ ተያይዞ ሀገሬን ከተደቀነባት ፈተና ለማውጣት የበኩሉን ድርሻ መወጣት ይኖርበታል እላለሁ።
ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለ50 ሰው ጌጡ እንዲሉ አገራችን ከተደቀነባት የግጭት፣ የግድያ፣ አርስ በአርስ ድንጋይ ከመወራወር ፈተና ወጥታ ወደ ምቹው ጎዳና እንድታቀና ሁላችንም የበኩላችን እጡብ መደርደር ይገባናል።በተስፋና በቁዘማ የሚገነባ አገር የለም።ችግሮችን ለመፍታት ችግሮቹን የመጋፈጥና መፍትሄ የመስጠት ቁርጠኝነትና ተሳትፎ ይጠይቃል።ለዚህ ደግሞ ሁላችንንም ጥፋት የሚያጠፋውንና ኢትዮጵያን የጭን ቁስል የሆኑባትን ጸረ ልማትና ዴሞክራሲ ሃይሎች በጋራ መታገል ያስፈልጋል።
እንደ ይሁዳ አምላኩን ዶሮ ሳይጮህ ሶሰት ጊዜ እንደከዳው ደቀ መዝሙርና በኋላም በፀፀት ላለመሞት ዛሬ አገራችሁን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ እያደማችሁ ያላችሁ ኃይሎች ከድርጊታችሁ ብትቆጠቡ መልካም ነው።ሀገራቸውን ከማድማትና የእናት ጡት ነካሽ ከመሆን ይልቅ በስምምነት የማዕዱ ተካፋይ ብትሆኑ ይመረጣል።ይህን ባታደርጉም እንደ ሻማ ቀልጠው ለህዝብና ለአገር ብርሃን በሚሆኑ ውድ ልጆቿ ጋረጣዎችን አስወግዳ ትንሳኤዋን ታበስራለች።አምላክንም የኢትዮጵያ ትንሳኤ ይቀርብ ዘንድ የመከራ ቀኖቻችንን አሳጥርልን ብዬ አበቃሁ።
ብስለት
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 26/2013