በእድሜያቸው ወጣት ቢሆኑም በሙያቸው የሀይማኖት መምህር በመሆናቸው በአንቱታ ልንጠራቸው ወደናል። ደራሲ ሲሆኑ፤ 13 የሚሆኑ መጽሐፍትን ለንባብ አብቅተዋል። ብዙዎችም ህማማትና ቃና ዘገሊላ በተሰኙት መጽሐፋቸው ያውቋቸዋል። መጽሐፍቱ በትግርኛ እና ኦሮሚኛ ቋንቋዎች ተተርጉመው የታተሙ በመሆናቸውም ብዙዎች ዘንድ ደርሰዋል። ከዚህም ባሻገር ተርጓሚ ናቸው። ተርጓሚነታቸውም በመጽሐፍት ብቻ ሳይሆን በፊልሞች ጭምር የሚታይ ነው።
በቅርቡ ደግሞ ወርሃዊ የንባብ ቀን በመወሰን ‹‹ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ›› በሚል ሰፊ ሀገራዊ ፕሮጀክት ነድፈው በመንቀሳቀስ የንባብ ክህሎት በአገሪቱ እንዲጎለብት የማድረግ ሥራም እየሰሩ ይገኛሉ። ከዚያ ባሻገር በአገር ጉዳይ ላይ፣ በእምነትና ባህል ጥልቅ ምስጢራዊ ትንታኔ ከሚሰጡ ምሁራን መካከልም ይጠቀሳሉ። የተለያዩ ሥልጠናዎችንም በዚህ ዙሪያ ይሰጣሉ። እናም ጊዜው ትንሳኤውን ከህማማቱ ጋር የምናይበት በመሆኑ ከአገር ትንሳኤ ጋር አሰናስለው እንዲያሳዩንና የህይወት ልምዳቸውን እንዲያጋሩን መምህር ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌን ለዛሬ የበዓልና የ‹‹ህይወት ገጽታ›› አምድ እንግዳ አድርገናቸዋል። መልካም ንባብ!
ብቸኛው ልጅ
ለእናትም ለአባትም ብቸኛ ልጅ ናቸው። በዚህም ቤት ውስጥ ተቀማጥለው እንዲያድጉ ሆነዋል። በተለይም እናታቸው እጅግ አድርጋ ትንከባከባቸዋለች። እርሳቸውም ቢሆኑ ከእርሳቸው ጋር ያላቸው ቀረቤታ እናትነት ብቻም አልነበረም። ጓደኛ ጭምር ሆነው ነው ያደጉት። ትምህርት ለቤተሰቡ ልዩ ትኩረት ስለሚሰጠውም ሌላ ሥራ ትዝ ሳይላቸው በእንክብካቤ እንዲያድጉ ሆነዋል። እድገታቸው ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ከእናታቸው ጋር ብቻ ስለነበር የእናትን ፍቅር በደንብ አይተው አድገዋል። እናት ሁሉ ነገር እንደሆነችም ተረድተዋል።
በባህሪያቸው ፈጣንና ቀልጣፋ ልጅ ሲሆኑ፤ እልኸኝነትም በውስጣቸው አለ። የፈለጉትን ሳያሳኩ ወደኋላ ማለት አይወዱም። ቀድሞ ያደገ ልጅ አይነት ስለነበሩም እስከ 10 ዓመታቸው ድረስ በጣም አስቸጋሪና ይህ ካልሆነልኝ የሚሉ ነበሩም። ብዙ ነገሮች እንዲደረግላቸውም ይፈልጋሉ። ነገር ግን እንዲያጠኑ ብቻ ስለሚፈለግ ቤተሰብን በምንም ነገር አግዘው አያውቁም። ነገር ግን እሳቸው ብዙ ነገር መሞከር ስለሚፈልጉ ከመስራት ያገዳቸው አልነበረም።
እንዲያውም በራሳቸው ፈቃድ አንድ ቀን ያደረጉት ነገር ዛሬ ድረስ ያስቃቸዋል። ነገሩ እንዲህ ነው። ሽንኩርት ምንም ላይ ሲገባ አይወዱም። ስለዚህ ዘይትና ውሃቸውን እንዲሁም ሌላ የሚጨማመሩ ነገሮችን ድስቱ ውስጥ ጨምረው ከፈላ በኋላ እንጀራ መጨመር ይጀምራሉ። ይሁንና የጨመሩት ውሃ ከመጠን ያለፈ ስለነበር በቀላሉ ፍርፍር መሆን አልቻለም። ከዚያ አንድ ዘዴ የሚሉትን ነገር ፈየዱ፤ በክዳኑ ብረትድስቱን ጥብቅ አድርገው በመያዝ አጠንፍፈፉት። እንጀራውም ደረቀና ወደ ምግብነት ለወጡት።
የተወለዱት እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ በተለምዶ ቡልጋሪያ ማዞሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው። በስፍራው በጨዋታ ያሳለፉትን ጊዜ አያስታውሱትም። ምክንያቱም ማንበብ ከሁሉም ነገር የሚወዱት ነው። እናም ብዙ ጊዜ የሚያልፈው በጨዋታ ሳይሆን የተለያዩ የውጪና የአገር ውስጥ መጽሐፍትን በማንበብ ራሳቸውን ዘና ያደርጋሉ። ሌላው ዘና የሚያደርጋቸው ቴአትር ማየት ሲሆን፤ ከእናታቸው ጋር በመሆን በወቅቱ በአንጋፎቹ አርቲስቶች የተሰሩና አንቱታን ያተረፉ ቴአትሮችን በማየት ነው።
እንዲያውም ከዚህ ጋር ተያይዞ እርሳቸውም የቴአትር ሰው እንደሚሆኑ ያምኑ ነበር። በእርግጥ ከፍላጎት አንጻር የከተማ ልጅ በመሆናቸውና ሁሉም ልጅ በተለይም ጎበዝ የተባለ ‹‹ምን መሆን ትፈልጋለህ›› ሲባል ኢንጂነርና ዶክተር እንደሚለው እርሳቸውም ይህንን ያስቡ ነበር። ግን ህልማቸውና ጥልቅ ስሜታቸው የሚነግራቸው የሥነጽሁፍ ሰው መሆን ነውና ይህንን ለማድረግ ይታትራሉ። በቤት ውስጥ አረፍ ሲሉም የሚሞክሯቸው ግጥሞች፣ ቴአትሮች ጭምር እንደነበሩም ያስታውሳሉ።
የንባብ ህይወታቸው የተጀመረው በትልልቅ የራሽያ ልቦለዶች ሲሆን፤ ለዚህ ያበቃቸው ደግሞ የቤተሰባቸው አንባቢነት ነው። እናም የእነ ዶስትኦፍ ስኪን፣ ማግሲም ጎርኪ፣ ዳንኤላ ስቲል፣ አጋታ ክሪስቲን ልቦለዶች፣ ከአገር ውስጥ ደግሞ የእነ ከበደ ሚካኤል፣ ሀዲስ አለማየሁ፣ የእነ ስብሀት ገብረእግዚያብሔርና የመሳሰሉ የወቅቱ እውቅ ጸሐፊያን ድርሰቶችን በደንብ አንብበዋል። ከዚህ የተነሳ መጀመሪያ ያነበቡትም ቲሙርና ቡድኑ የተሰኘ የራሺያ ተረት እንደሆነም አይረሱትም።
እናታቸው ግብረሰናይ ድርጅት ውስጥ በመስራታቸው ምክንያት ብዙው የልጅነት ጊዜያቸው የሚያልፈው በልጆች ማቆያ ውስጥ ነበር። ይህ ደግሞ ከእናታቸው ጋር የሚገናኙበትን ጊዜ አሳጥሮታል። ይሁን እንጂ አንድ ልጃቸው ስለነበሩ እረፍት ጭምር እየወሰዱ ይንከባከቧቸዋል። መዋእለ ህጻናት ሲገቡ ግን ብዙ ከእርሳቸው ጋር የመገናኘት እድሉን አግኝተዋል። ጨዋታም ቢሆን በትንሹ የተጀመረው እዚህ አካባቢ ሲደርሱ ነው።
ወደ ድቁና ህይወታቸው ሲገባ ደግሞ ቡልጋሪያና ቄራ አካባቢ ያለ ልጅ ቤተክርስቲያን አካባቢ ብዙ ይታያል ተብሎ ባይታሰብም በሰንበት ትምህርት ቤት ህይወታቸው ጥሩ እንቅስቃሴ ላይ በመሆናቸው፤ ህልማቸውን የሚተገብሩበት ቦታ ስላገኙም ጎን ለጎን ትምህርቱን እንዲቀስሙት ሆነዋል። ዲቁናንም በሚገባ ከየኔታ ዘመንፈስ ተምረዋል። ‹‹ዲቁናው ለእኔ እንደመታደል የተሰጠች ትልቅ ገጸ በረከቴ ነው›› ይላሉ። ምክንያታቸውን ሲጠቅሱም ብዙ የከተማ ልጆች ይህ እድል የላቸውም። በዚያ ላይ እንደማንኛውም የአብነት ተማሪ ውሻ እየጮኸባቸው፣ በእመቤታችን ስም እየለመኑ በችግር ውስጥ ሆነው ያገኙት አይደለም። በከተማ ደረጃ ከእነርሱ እኩል ቀለሙን መቅሰም ስለቻሉና አሁንም በሙያው ማገልገል በመጀመራቸው ደስተኛ እንደሆኑም አጫውተውናል።
ገና በለጋ እድሜ ላይ ሳሉ መንፈሳዊ መጽሔቶች ላይ ጭምር መጻፍ የጀመሩት ባለታሪካችን፤ ራሳቸውም በቤት ውስጥ ግጥሞችን በብዛት ይጽፋሉ። ከዚህ በተመሳሳይ ትምህርት ቤትና ሰንበት ትምህርት ቤትም እንዲሁ የተለያዩ መጣጥፎችን በራሳቸው ጽፈው ያቀርባሉ። እስከ ቴአትር ድረስ የጻፏቸውና ለእይታ የቀረቡ እንዳሉም አይረሳቸውም።
ድብልቁ ትምህርት
ኢትዮጵያን ጀሚኒ ትረስት የሚባል ግብረ ሰናይ ውስጥ ነው ከትምህርት ጋር የተተዋወቁት። ከዚያ 53 ቀበሌ የሚባል ሰንጋ ተራ አካባቢ የሚገኝ ትምህርት ቤት ገቡ። ትምህርት ቤቱ መዋእለ ህጻናት በመሆኑ ደረጃዎችን እስኪያልፉ ድረስ በዚያ ቆዩ። ቀጣዩ የትምህርት ጉዟቸው የሚወስደን ደግሞ አግአዚን ትምህርት ቤት ሲሆን፤ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ትምህርታቸውን ተከታትለውበታል። ከዚያ ሽመልስ ሀብቴ ተብሎ የሚጠራ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብተው ትምህርታቸውን መከታተል ጀመሩ።
ዘጠነኛና አስረኛ ክፍልን በዚህ ከተማሩ በኋላ አብዮት ቅርስ ወይም ጂሲኤ ተብሎ ወደሚጠራው ትምህርት ቤት ተዛወሩ። በዚህም 11ኛ እና 12ኛ ክፍልን መከታተል ችለዋል። በትምህርታቸው ጎበዝና የደረጃ ተማሪ በመሆናቸውም የዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤት አምጥተው ክፍለ አገር ተመደቡ። ይሁንና አንድ ልጃቸውን ከራሳቸው ማራቅ የማይፈልጉት እናት በግል እንዲማሩ አደረጓቸው።
በዚህም ቅድስተ ማሪያም ኮሌጅ በመግባት በማኔጅመንት የመጀመሪያ ድግሪያቸውን መማር ጀመሩ። ሆኖም ከዓመት በላይ አልቀጠለም። ምክንያቱም መሀል ላይ የሚወስዱት ኮሜሪሽያል ሎው የሚባለው ትምህርት መሰጣቸው። በዚያ ላይ ይህንን ትምህርት የሚሰጣቸው መምህር ‹‹አንተ የሚያዋጣህ ህግ መማር ነው›› ሲላቸው አላወላወሉም። ጊዜ ሳይፈጁም ህግ ለመማር ሮያል ኮሌጅን ተቀላቀሉ። ይሁንና ይህም ቢሆን ከዓመት በላይ የቀጠሉበት አልነበረም። ለዚህ ደግሞ ምክንያት የሆናቸው የቴአትር ትምህርት መጀመሩ ነው።
የቤተሰቡም ሆነ የእርሳቸው ፍላጎት ያለበት የትምህርት መስክ መጀመሩ ደግሞ ምንም ቢሆን ከመተው አያግዳቸውም ነበር። ስለዚህም ዓመት የተማሩትን ትምህርት አቁመው በቀጥታ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መልምሎ በሚሰጠው ትምህርት ውስጥ ገቡ። ትምህርቱን ተምረውም በሰርተፍኬት አጠናቀቁ። ከቴአትሩ በኋላ ግን የጀመሩዋቸውን ትምህርቶች ማጠናቀቅ እንዳለባቸው ስላመኑ በወቅቱ ያላሰቡትም ቢሆን የታሪክ ትምህርት ለማጥናት ስድስት ኪሎ ዩኒቨርስቲን ተቀላቀሉ። ነገር ግን ከሁለት ዓመት የትምህርት ቆይታ በኋላ የጋዜጠኝነት ትምህርት ለእርሳቸው የተሻለ እንደሆነ በማመን ታሪክ መማራቸውን ትተው ጋዜጠኝነቱን ጀመሩ። በመስኩም የመጀመሪያ ድግሪቸውን ይዘው ተመረቁ።
ከዚህ በኋላ ግን ትምህርታቸው አልቀጠለም። ይሁንና የተለያዩ ሥልጠናዎችን ወስደዋል። ማስተማር፣ ማሰልጠን ላይም ስለሚሳተፉ ሁልጊዜ እየተማሩና እውቀታቸውን እያጎለበቱ ይገኛሉ። በተለይ ግን በንባብ የሚገኝ እውቀት ምንም የማይተካው እንደሆነ ይናገራሉ። የጽሁፍ ስራውም ቢሆን ሁልጊዜ የሚማሩበት ስራቸው እንደሆነ ያስረዳሉ። ግን አሁንም ቢሆን የመማር ፍላጎት እንዳላቸውና የጀመሯቸውን የትምህርት መስኮች እንደሚያጠናቅቁ አጫውተውናል።
መምህሩ ደራሲ
አብዛኛው መጸሐፋቸው መንፈሳዊ ይዘት ያለው ሲሆን፤ ለወጣቱ፣ ለቤተሰብ፣ ለህይወትና ለኑሮ ትምህርት ሰጪ ይዘቶች አላቸው። ከዘጠኝ ዓመት በፊት በአንድ መጽሐፍ ያዩትን ውጤት ተመልክተውም ነው ሁለት፣ ሦስት እያሉ የቀጠሉት። በየዓመቱ ስራቸውን ለንባብ ወደ ማብቃቱም የገቡት። ስድስት ያህሉ ወደ ትግሪኛ አራት ያህሉ ደግሞ ወደ ኦሮሚኛ ተተርጉመው ብዙዎች እንዲያነቡት ሆኗልም። አሁን አጠቃላይ 13 መጽሐፍትን ለንባብ ያበቁ ሲሆን፤ ብዙዎቹ ወቅቱን ጠብቀው በየጊዜው የሚነበቡና የሚደጋገሙም ናቸው።
‹‹መጽሐፍ ከመናገር በላይ ሀይል ያለው ነው። እንቢ ያሉትን ሳይቀር ብቻቸውን እንዲያሰላስሉ እድል ይሰጣል። ትውልድ ከዘመኑ ጋር እንዲዋሀድና በእውቀቱ አለም እንዲዋኝም ያግዛል። ከዚያ ባሻገር ሰዎችን ያለገደብ ደርሶ መምራት ያስችላልም። በመንገር የማይረዱትን በማንበብ እንዲረዱት የማድረጊያ ዘዴም ነው። የፈለጉትን ሀሳብ ማሳመኛም እንደእርሱ የለም። እናም የንባብ ባህላችን ቢዳብር ኖሮ ይህንን ሁሉ ከእነርሱ ማግኘት ይቻል ነበር›› ይላሉ።
ኢትዮጵያ ጥልቅ ሥነጽሁፍ ያለባት አገር ነች። አባቶቻችን ማተሚያ ቤት ሳይኖር አንድ መጽሐፍ ለመጻፍ አንድ ሺህ ፍየል ታርዶ ቆዳው ብራና ሆኖ፤ ቀለም ተበጥብጦና ከአቀረቀሩበት ሳይነሱ ጽፈው ነው ለዛሬ ያበቁት። አፍሪካ አገር ውስጥ የትም የሌለና የሚያኮራ ልምድም ያለባት ናት። በመንገድ ላይ ጭምር ማንበብ የሚወዱ መሆናችንን ኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ ማንሳት በቂ የሆነባት ነበረች። ነገር ግን ዘመናዊው የማንበብ ልምዳችን ይህንን ነገራችንን እየሸረሸረው ይገኛል።
ይሁን እንጂ ይህ እየታየ ዝም መባል የለበትም የሚሉት እንግዳችን፤ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ይምጣ ከተባለ መጀመሪያ መሰራት ያለበት የሚያነቡ ሰዎች መፍጠር ላይ ነው ይላሉ። አንባቢ ትውልድ መፍጠር በእውቀት የሚሰራ ሀይልን መገንባት ያስፈልጋል። ራዕይና ማመዛዘን የሚችሉ ወጣቶችም እንዲኖሩን ደግሞ ሁላችንም አሻራችንን ማሳረፍና ታሪክን መመለስ ግዴታችን ነው ባይ ናቸው።
እርሳቸው ይህንን ታሳቢ በማድረግ ወርሀዊ የንባብ ቀን በመሰየም ሥራ ጀምረዋል። ሰባተኛ ወር ላይ እንደደረሱ አጫውተውናል። “አሁን ላይ በብሔር ተነድቶ የተባለው ላይ የሚሳተፍ ወጣት የመጣው ማገናዘብ፣ ራዕይ ኖሮት መንቀሳቀስ ባለመቻሉ ነው። ማሰብና ወደውስጥ ማየት እንዲጀምር ደግሞ ማንበብ እንዲችል ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው ነው። ከዚያ ለኢትዮጵያ ማንነት ዋጋ መስጠት ይጀመራል” ይላሉ።
የሥራ ዓለም
በቅጥር ደረጃ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማህበረ ቅዱሳን አልወጡም። ጅማሬያቸውም ፍጻሜያቸውም በቅጥር የመስራት ሁኔታ በዚህ ቤት ነው። በዚህም ሥራን የጀመሩት የሐመር መጽሔት ሪፖርተር በመሆን ነበር። ከዚያ ከፍተኛ ሪፖርተር ሆነው ማገልገል ቀጠሉ። ራዲዮኑ በስፋት መስራት ሲጀምር ደግሞ ቦታቸውን ቀይረው በአለም አቀፍ ደረጃ በሚደመጠው የሬዲዮ አዘጋጅነት ውስጥ ገቡ። ቴሌቪዥኑ ሲጀመር ደግሞ ከመሰረቱ ጀምሮ በሃላፊነት ቦታ ላይ ተቀምጠው አገልግለዋል።
የራዲዮ ክፍሉም ቢሆን ሃላፊ ነበሩ። በእነዚህም በአጠቃላይ አምስት ዓመት ያህል አሳልፈዋል። ከዚያ ብዙ ጉዞዎች ያደርጉ ስለነበረና ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት ምቹ ሁኔታ ስላልነበራቸው በተቋሙ መቆየት አልቻሉም። በዚህም ሥራውን አቋርጠው በግላቸው ወደመስራቱ ገቡ። አሁን የሙሉ ጊዜ ጸሐፊ፣ መምህርና አሰልጣኝ ናቸው። በዚህ ደግሞ በዓመት ውስጥ ወደ 23 አገራትን የማየት እድሉን አግኝተዋል። እንዲያውም ለዘጠኝ ወር ያህል ማለትም ኮቪድ እስኪገባ ድረስ በአገር ውስጥ ሳይሆን በውጪው አለም በመዘዋወር ነበር እነዚህን ሥራዎቻቸውን የሚያከናውኑት።
ትንሳኤና የሰው ልጅ
ትንሳኤ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣውና የሚታሰበው ሞት ነው። ምክንያቱም ያልሞተ አይነሳም የሚሉት ዲያቆን ሄኖክ፤ ስለትንሳኤና ሞት እንዲሁም ሰው በስፋት ያብራራሉ። መጀመሪያ ከትንሳኤና ሞት ይነሳሉ። ትንሳኤ ሲታሰብ የክርስቶስን መከራ፣ ስቃይና ግርፋትን መጥቀስ ግድ ነው። ክርስቶስ በአራት አቅጣጫ ባለው መስቀል ላይ ሲሰቀል ደቡብ፣ ምስራቅ፣ ምዕራብ ሰሜን እንዳለ በተግባር ነግሮናል። እጆቹን ዘርግቶ የመሰቀሉን ጉዳይም ሁሉንም በፍቅር ማቀፍ እንደሚያስፈልግ ሰብኮልናል። ሌላው ኢየሱስ ናዝራዊ የአይሁድ ንጉስ የሚለው ከመስቀሉ ላይ የተጻፈው የቋንቋ ልዩነት የሌለበት መሆኑም ዛሬ በቋንቋ ለምንከፋፈለው ሰዎች ልዩ ትምህርት የሰጠ ነው። ስለዚህም በፈጣሪ የሚያምን የቋንቋና የብሔር ልዩነት አይኖረውም፤ እርሱ የሁሉም እነርሱም የእርሱ ናቸው።
ስለ ሰው ልጅና ትንሳኤ ሲያነሱ ደግሞ እንዲህ ይላሉ። የሰውን ልጅ የህይወት ጉዞም ጥንቅቅ አድርጎ ያሳያል። የሰው ልጅ መከራን በተስፋ መሻገር ከቻለ ትንሳኤ ላይ እንደሚገኝ የሚያስረዳ ነው። ለዚህም በርካታ ምሳሌዎችን ማንሳት ይቻላል። አንዱ ማሳያው እንቅልፍ ነው። እንቅልፍ የሰውን ልጅ ከትናንት መጥፎ ማንነቱ ያሳርፈዋል፤ አዲስ ሀሳብ የሚያይበትን ዓይንም ይሰጠዋል። ምክንያቱም ሲነቃ ታድሶ ይነሳል። እንቅልፍ ትናንት የተከፋንበትን ነገ ሌላ ቀን ነው እንድንል ያደርገናል፤ መጽናናትና ራዕይ ኖሮን ወደፊት እንድንገሰግስ ያደርገናልም። ስለዚህ ትንሳኤ አዲስ እንደሚያደርገን ሁሉ እንቅልፍም አዲስ መሆኛ ነው።
ሌላው የትንሳኤ ምሳሌ መሞትና መነሳት በባህላችንም ውስጥ የምናሳየው መሆኑ ነው። ለአብነት ቀብረን ስንመለስ የምንመገበው ንፍሮ ከስንዴ የተዘጋጀ ነው። ይህ ምሳሌነቱ ስንዴ አንዷ ፍሬ የትም ላይ ብትወድቅ ምቹ ሁኔታን ካገኘች መልሳ ትበቅላለች። ከተጣለችበት ትነሳለች። የሰውም ልጅ ሞቶ አይቀርም፣ ይነሳል የሚለውን ይነግረናል። ስለዚህ መነሳትና መሞት ለክርስቶስ ብቻ ሳይሆን ለሰውም ልጅ እንደሆነ በእነዚህ ነገሮች መረዳት ይቻላል። እናም አማኝ ነን ብለን የምናደርገው ከክርስቶስ ፍቅርና ህግ የማንወጣባቸው ብዙ ነገሮች ተቀምጠዋልና ትንሳኤና ሞትን እያሰብን መንቀሳቀስ እንደሚገባን ይመክራሉ።
ክርስቶስ ከወንድማችሁ ለአንዱ ከአደረጋችሁ ለእኔ እንዳደረጋችሁ አድርጌ እቆጥረዋለሁ ቢልም እኛ ግን ወንድማችንን ተነስተን ስንገለው ክርስቶስን እንደገደልነው አናገናዝብም። ስለዚህም ዛሬ ወንድሞቻችን ላይ የምናደርገው ክፉ ነገር ክርስቶስ ላይ እንዳደረግነው ማሰብ ይገባናል። ትንሳኤውን ስናስብ ዘመን ለይቶን እንጂ አርብ ላይ ብንሆን ኖሮ ምን ልናደርግ እንደምንችል ከዚህ ድርጊታችን መማር የዛሬ ሥራችን መሆን አለበት።
ይህ ካልሆነ ግን ከሰቃዮቹ፤ ምራቅ ከሚተፉት አለያም ስቀለው ከሚሉት ወገን መሆናችንም አይቀርም። እናም አሁን ማሰብ ያለብን ተሰቃየ፣ ተገደለ፣ ተገረፈ፣ ሞተ አይደለም። ይህ ዳግም መሆን አይችልም። ክርስትናችንም በዚህ የሚገለጽ አይሆንም። እርሱ ሞትን ድል አድርጎ መነሳቱ እንደምን ነው ብሎ መመርመር ይገባል። በትንሳኤው ራሳችንን አንስተን ሌሎችን ማንሳት ይጠበቅብናል። አጠገባችን ያለውን ወንድማችንን መደገፍና ከእድሉ ተካፋይ መሆንም ግዴታችን ነው።
ህማማት ላለችው ኢትዮጵያ ማሪያምን የመሰሉ ትንሳኤ አብሳሪ ያስፈልጓታል። ስለሆነም በየአቅጣጫው ያለውን ረሀብ፣ ችግር፣ መፈናቀልና ሞት በእኛ ቆም ብሎ ማሰብ መፍታት ያስፈልጋል። በኢትዮጵያ ስቃይና ህማም ውስጥ የእኛን ሚና ማወቅም ይገባል። ቆመን እየሳቅንባት ወይስ ወደ ፈጣሪ እያለቀስን እንባዋን እያበስን ነው የሚለውን ማረጋገጥም ይገባናል።
አማኝነትና ተግባር
ከነብስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደሆነ ሁሉ ከሥራ የተለየ እምነትም እንዲሁ የሞተ ነው ይላል መጽሐፍ ቅዱስ። ስለዚህም እንደ አገር መጀመሪያ 98 በመቶ አማኝ ነን ወይ የሚለውን መመለስ ተገቢ ነው። ምክንያቱም በእምነት ብቻ መዳን አይቻልም። እምነት ከስራ ጋር መዋሀድ አለበት። በአማኝነት ከሆነ ሰይጣንም ያምናል፣ ይንቀጠቀጣልም። ነገር ግን ምግባሩና ተግባሩ የተለየ ነው። አሁንም አማኝነት በተግባር እግዜአብሔር የለም ባይ በአፉ ግን እግዜአብሔርን አምላኪ ሰው ሞልቷል። ይህ ደግሞ ለመታወቂያ ያህል ብቻ ነው የተቀበልነው። ኑሯችንም ሆነ ፍላጎታችን አማኝነትን በስም ብቻ ተሸክመን የምንዘዋወር ነን ይላሉ።
በትኛውም እምነት አንዲትን አራስ በተኛችበት ግደል አይልም፤ አስከሬን ጎትት ብሎ የሚመክር እምነትም የለም፤ የሚሉት ዲያቆን ሄኖክ፤ እምነቱ የፈጠረው ነው ብሎ መውቀስ አይቻልም። ከዚያ ይልቅ ከእምነቱ ጋር የተጣበቅንበትን ምስጢር ራሳችን መመርመር ያስፈልጋል። እምነቱ ጠላትህ ቢርበው፣ ቢጠማው የሚፈልገውን አድርግለት ይላል እንጂ ግደለው አይልም። እናም ይህንን እንመርምረው ሀሳባቸው ነው።
ኢትዮጵያ በእምነትና በባህል
ከበዓላት አከባበር ጀምሮ ያለው ሂደትና ሁኔታ ኢትዮጵያ ባህሏና ሀይማኖቷ ተለይተው እንዳይታዩ ሆነው የተዛመዱ ናቸው። ለዚህ ደግሞ አማኝነታችን ምንጩ መጸሐፍ ቅዱሳዊ መሆኑ ነው። አለም ሁሉ ለእግዚአብሔር እኩል ቢሆንም ኢትዮጵያ ለየት ያለች ነች የሚባልበት መሰረታዊ ምክንያት አለ። ከእነዚህ መካከል ደግሞ ሰላምታ አንዱ ነው። በየትኛው አገር ያለ ሰላምታ እግዚአብሔርን የሚጠራ አይደለም። ኢትዮጵያ ግን እንደምን አደርክ ሲባል እግዚአብሔር ይመስገን ምግቡ ነው። ቢያገኝም ቢያጣም እግዚአብሔር ይመስገን ይላል። ሌላው ጋር ግን የግል ጥሬ አመጣው ነው የሚባለው።
ሌላው ኢትዮጵያ ሁሉን ነገር የምታሸንፈው በፀሎት የሆነባት አገር ነች። ይህ ደግሞ በኮቪድ ብቻ ማየት ይቻላል። ብዙ የከፋ ነገር እንዳይደርስብን ሆነናል። ምክንያቱም ሀያል ነን የሚሉ ዛሬ ድረስ ምን ላይ እንዳሉ ማየት ቀላል ነው። እነርሱ ጋር ቴክኖሎጂውም ሆነ ጥንቃቄው ብዙ ነው። ግን ሰዎቻቸው ስቃይ ላይ ናቸው። የእኛ አማኝነታችን ከሰው ወዳድነታችን ጋር ባለመቀናጀቱ እያመጣን ያለነው ብቻ ነው እየጎዳን የሚገኘው። ምክንያቱም አማኝ ነን፤ ግን በክርስቶስ ያገኘነውን ወንድማችንን እንገለዋለን። ፈጣሪ የሰጠንንም እድል በዚህ እያጣነው እንገኛለን።
አሁን እየሆነብን ያለው እምነታችን ምን ጠቀመ ሊያስብል የሚችል ፈተና እንደሆነ የሚያነሱት ባለታሪካችን፤ በየቦታው ሰው ተገደለ እንደሚባለው ሰው ለሰው ሞተ የሚለውን አናሳይም፤ ቤታቸው ሸሽገው ከችግር የታደጉትም በስፋት ሲወሳ አይታይም። ጀግንነትን ከሰው መግደል ጋር እንጂ እንዳይሞቱ ከማድረግ አንጻር የተወሰደው መሰዋዕትነት አይደለም። እናም ይህንን በእምነቱ አስተምሮ መመከትና እምነቱን ከፈተና ማላቀቅ ያስፈልጋል። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን አሁን ካለችበት ህማማት ይታደጋታል።
ከልምዳችን መዛነፍ አንጻር ግን ክርስቶስ ሲነሳ እኛ መሞት እንጀምራለን። አሁን ሁላችንም አደብ እየገዛን ያለነው ጾም ላይ ስለሆንን ነው። ሲፈታና 50 ቀን ፋሲካ ሲበላ ግን የተለየ ተግባራችን ይታያል። ይህ የሚያሳየን ደግሞ እያንዳንዱን ሥራችንን ከልምድ ጋር እንጂ ከባህል ወይም ከእምነታችን ጋር አያይዘነው ስላልተጓዝን ነው። እናም ትንሳኤያችን የተሳካ እንዲሆን ሞትና ህመማችን እንዳይበረታ በመደጋገፍ ጊዜው ይለፍልን። እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይወዳታል ይጠብቃታል የምንለው በምክንያት ነው።
እኛ ኮቪድ ሆነን ባናስቸግር ኖሮ በአምናው ሥራችን ብቻ አለምን ማስደመም እንችል ነበር። ሞት አጠገባችን አይደርስምም። ሆኖም በራስ ከማመካኘት ይልቅ በሌላው ላይ ጣት መጠቆሙን ስለምናስበልጥ እዚያ እየተገደለ አይደለም እንጂ ለምን ሞተ አንልም። ይህ ደግሞ ድርጊቱን እንዳናወግዝ፤ ባለንበት እንድንጓዝ ያደርገናል። እኔን አይነካኝም መርሀችን ይሆናል። ነገ እሞታለሁን ትቶም ቀብር ላይ ቆሞ ጭምር እቅድ ማቀድም ይጀመራል። እናም ዛሬ ካልነቃን እኛም አገራችንም ትንሳኤን አናይም።
እንደ አገርም እንደ ግለሰብም ብዙ እድል ተሰጥቶናል። ከአቅም በላይ እንድንፈተንም አላደረገንም። ነገር ግን ካለመጠቀማችን አንጻር አሁንም ብዙ ነገሮች እያመለጡን ይገኛሉ። ለአብነት በነጻ የመተንፈስ ሁኔታችን ጭምር እየተገደበ መጥቷል። በሺህዎች ብር ከሌለን የለንም። የምንተነፍሰውን አየር በመሳሪያ ተደርጎ እየተሸጠልንም ነው። ታዲያ መቼ ልንማር ነው ሲሉ ይጠይቁና ብዙዎች ህማማት ላይ ናቸውና ይህንን የምናይበት ዓይን ይኑረን በማለት ይመክራሉ።
መልዕክት
‹‹ሰዎች ከዛሬ ነገ ይሻላል ብሎ ማሰብን ከእኔ ቢወስዱ እላለሁ። እንዲህ ሆነን አንቀርም የሚል እምነትም ተስፋም አለኝ።›› የሚሉት እንግዳችን፤ እግዚአብሄር ሁሉንም ሰው ያለ ልዩነት የሰጠው ስጦታ ጊዜ ነው። ለድሀውም ለሀብታሙም 24 ሰዓት ተሰጥቶታል። ልዩነቱ ጊዜውን በአግባቡ የመጠቀምና ያለመጠቀም ነውና የምንማርበት ጊዜ እጎናችን አለ። ያንን መጠቀሙ ደግሞ በጊዜው መሆን አለበት። የራስን ሩጫ ከጊዜው እኩል መሮጥ ይገባል። መወዳደርም ከራስ ጋር እንጂ ከሰው ጋር መሆን የለበትም። ራስን መብለጥን የመሰለ ስጦታ የለምና ይህንን እናድርግ የመጀመሪያው ምክረ ሀሳባቸው ነው።
ሌላው ያነሱት ይህ ትንሳኤ የኢትዮጵያ ትንሳኤ እንዲሆን ሰዎች የሚያደርጉት ነገር እንኳን ባይኖር እነርሱ አረም ከመሆን ራሳቸውን መቆጠብ አለባቸው የሚለው ነው። የግለሰቦች መነሳት ኢትዮጵያን ያነሳታል። እናም ብንችል መፍትሄ አመንጪ ካልቻልን ደግሞ ችግር ላለመሆን እንተባበር። ኢትዮጵያ መስቀል ላይ በመሆኗም መስቀሏን ለመሸከም ምን እያደረኩ ነው እንበል ይላሉ።
መርጦ የተወለደ ክርስቶስ ብቻ ነው። የሰው ልጅ ግን ከዚህ ዘር ተብሎ አልተወለደም። እናም ይህንን ምልከታችንን በሚገባ መመልከትና ለራሳችን ትንሳኤን ማወጅ ያስፈልገናልም ሌላው ሀሳባቸው ነው። ከአፋችን የሚወጣውን ቃል ብርሃን ይሁን፣ ምድር ታብቅል፣ ሰዎች በሰላም በፍቅር ትንሳኤውን ይዩ፣ አገር ሰላም ይሁን ብሎ የሚሰብክና የሚያኖር እንጂ የምናሳምምበት፣ መስቀል ላይ የምናውልበት አናድርገው። በትንሳኤው እንፈውስበትም የመጨረሻ መልዕክታቸው ነው። ሠላም!!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24/2013