ፀሀይ ወገግታዋን ተነጥቃና በጉም ተሸፍና ብቅ ብላለች። አይኑ ብርሀን ካየ እንቅልፍ የሚባል ነገር አይወስደውም ። ጭለማ ያስፈራዋል። እሱን ለመሸሽ በጊዜ መተኛትና ጭለማው ሲገፈፍ መንቃት ተላምዶታል። እንደ ለመደው ሰማይ ሲገለጥ ከእነቅልፉ እንደባነነ ለሰዓታት የተኛበት ፍራሹ ላይ እየተገላበጠ ቆየ ። የጠዋቱ ብርድ ከሞቀው ብርድ ልብሱ እንዳይላቀቅ አስፈርቶታል።
በቆርቆሮ ዙሪያዋን የተሰራቸውን በቀን ከሚያገኘው ቆጥቦ የተከራያት 2 ሜትር በ3 ሜትር የሆነችው ቤቱን የወረሰውን ቅዝቃዜ የተከላከለለት ብርድ ልብሱን ለቆ እንዳይወጣ ቢያስመኘውም፤ በረሀብ የተላወሰው አንጀቱ መልሶ ወደሚወደው እንቅልፍ ሊወስደው አልቻለም ። ረሀብና ጥማቱ መለየት ያልፈለገው ሙቀት ላይ እንዲቆይ ከቶም አልፈቀደለትም ።
ተኝቶ ምግብ የሚቀርብለት ተንጋሎ የሚበላበት የኑሮ ደረጃ ላይ አይደለምና የእለት ጉርሱን ለማግኘት ከቤት መውጣት ግድ ይለዋል ። በሀገራችን እየከፋ የመጣው ኮሮና ለእንደርሱ ያሉ የቀን ሰራተኞች ፈተና ሆኗል ። ተሯሩጦ ለምግብ ይሰራቸው የነበሩ ስራዎች ሁሉ እስከ አሰሪዎቻቸው ተቀዛቅዘውበታል ። በዚህ ሁለት ቀን ወጥቶ ከመግባት በቀር ይህ ነው የሚባል አንዲት ብር የሚያስገኝለት ስራ አልሰራም ።
በሚያውቁት ዘንድ ፍፁም ሥነ ምግባር የተላበሰ ሰው መሆኑና የሰጡትን ቃል የማይሰብር፣ ያመኑበት የማይከዳ፣ የዋሉለትን የማይረሳ ሰው መሆኑን አሳውቆታል ። ታማኝ መሆኑ በብዙዎች እንዲወደድ አድርታል ። በዚህ ሁሉ ስብዕናው ግን ኑሮው መለወጥ ሕይወቱ መስተካከል አልቻለም ። እንዲያውም የዘመኑ ሰው ተቃራኒ ሆኖ መገኘቱ ከብዙዎች ጋር ያራርቀዋል ። በፍጹም ውሸት መጥላቱ በውሸታሞች ያስተቸዋል ። ፍፁም ታማኝ መሆኑ በማይታመኑትና በአስመሳዮች እንዲነቀፍ አድርታል ። እርሱ ግን ገና ልጅ ሆኖ በመልካም ሥነ ምግባር ያነፀችው የእናቱን ቃል ፈፅሞ ማጠፍ አይሆንለትም ።
ለእድገቱ መሰረት የሆነችው እናቱ ጥሩ ስብዕናና ድህነት አውርሳው ነው በወጣትነቱ የሞተችበት ። ሲቸግረው የሚጠለልበት በመጥፎ ጊዜው የሚቀርበውና የሚያውቀው ወገን የለውም ። ዝም ብሎ የተገኘ ፍጡር አድርጎ ነው ራሱን አንዳንዴ የሚያስበው ። ራሱን ለመቻል ሌትተቀን ቢለፋም ለውጥ ግን ወደሱ ሊቀርብ ፈፅሞ አልቻለም ። አለ አይደል አንዳንዴ እድል የሚባል ነገር ። እድል ከእርሱ የራቀችው አይነት ሰው ነኝ ብሎ እስኪያስብ ድረስ ። መልካም ነገሮች ወደኔ የማይቀርቡኝ ነኝ ብሎ አመነ ።
አንድ የማይናወጥ አቋሙን ግን ራሱ ይወደዋል። የእሱ የመኖር ትርጓሜው ያለው እሱው ውስጥ ይመስለዋል። በልቶ ከሚጠግብ ይልቅ የሚያበረታው፤ለብሶ ከማጌጥ ይልቅ የሚዋብበት ታማኝነቱን ይወደዋል። የሰው ያለውን ወደ ራሱ ፈጽሞ ማስጠጋት አይፈልግም ። በመልካምነቱ ያገኘው ምንም ቢሆንም ምንም ሆኖ ይህችን ምድር እስኪሰናበት ለእኔ ስብዕና የሚመጥነው መልካምነት ነው የሚለውን መርሁን ግን ዘንግቶት አያውቅም ።
የግዱን ከመኝታው ላይ ተነስቶ ፊቱን ውሀ አስነክቶ ከቤቱ ወጣ ። በረሀብ የተጣበቀ አንጀቱ አንዳች መፍትሄ ቢያገኝ ዞር ዞር ማለቱ ሳይሻለው አይቀርም ። እየተንገዳገደ ከቤቱ ወደ ዋናው መንገድ የሚያስኬደውን መንገድ ይዞ ሩቅ ተጓዘ ። ከ15 ደቂቃ የእግር ጉዞ በኋላ አንድ አጥር ተደግፎ በተቀመጠ ጠፍጣፋ ድንጋይ ላይ አረፍ አለ።
ከተቀመጠበት ቀና ሲል ከፊት ለፊቱ በስሎ የተንዠረገገ ሙዝ ተመለከተ። አጠገቡ አንድም ሰው የሚተላለፍ የለም ። በረሀብ የተጣበቀ አንጀቱ በዚህ ሙዝ ጊዜያዊ ፈውስ እንደሚያገኝ ጉልበቱም እንደሚበረታ ያውቀዋል። ግን ከማንነቱ ጋ የተጋባውን ታማኝነት ማጉደል አልፈለገም። እንዳይተው ሞት ወደሱ የቀረበ መሰለው። እንደው በደመ ነፍስ የሆነ ስሜቱ አስገድዶት ተነስቶ በደከመ አረማመድ ወደ ሙዙ ማሳ አጥሩ ተጠጋ ።
ከአጥሩ ውጪ ዥርግግ ብሎ ከተንጠለጠለውና ከበሰለው የሙዝ ፍሬ እጁ የያዘለትን ያህል ገንጥሎ መጀመሪያ ወደነበረበት ተመለሰ ። እንዴት እንደላጠውና በምን ፍጥነት በልቶ እንደጨረሰ ሳይገባው የተወሰኑ የሙዝ ልጣጮች እግሩ ስር ተገኙ ። ከደቂቃዎች በኋላ ረሀቡ ሲወገድና የደከመው ጉልበቱ ሲመለስ ተሰማው ። ቅድም በረሀብ ስሜት ረሀብ ባደከመው ህሊና ያረገው ያስቆጨው ጀመር ፡ “ስለምን ያልተፈቀደልኝን ነካሁ፤ እንዴትስ ደፍሬ ታማኝነቴን አጎደልኩ” ብሎ ራሱን ክፉኛ ወቀሰ ።
ስላደረገው ነገር ጸጸት ተሰማው ። ከረሀቡ ሲመለስ ትክክለኛ ማንነቱን ማጉደፉ ታወቀው ። ተቆጨ ፤ማድረግ የሌለበትን በማድረጉ በራሱ ተናደደ ። የሙዙ ማሳ ባለቤት ይቅርታ በመጠየቅ ኃጥያት ያለውን ተግባሩን ለማንፃት አስቦ ባለቤቱ ይገኝበታል ወደተባለው ቦታ ርቆ ተጓዘ ። በብዙ ጥረት የሙዝ ማሳው ባለቤት አግኝቶ አናገረው ። ፈፅሞ የሰውን ንብረት ነክቶ እንደማያውቅና በረሀብ ተሸንፎ ከእርሳቸው ማሳ ሙዝ ያለፍቃድ ረሀቡን ለማስታገስ እንደበላና ይቅርታን ሊጠይቅ መምጣቱን ነገረው ።
የሙዝ ማሳው ባለቤት ከዚያ ማሳው ብዙዎች ያለፍቃዱ ያሻቸውን ያህል ከመብላት አልፎ ብዙ ጊዜ እየዘረፉ እንደሚወስዱ ያውቃል። ይህ ወጣት ደግሞ ረሀቡን ለማስታገስ በበላው ጥቂት ፍሬ ሙዝ ይቅርታ እየጠየቀው ነው ። ይቅርታ ሊጠይቀው የመጣውን ወጣት ማንነትና ምንነት ከጠየቀውና በጥሞና እየተመለከተው ከቆየ በኋላ አንድ ነገር አለው ። “ወጣቱ፤ ይቅር የምልህ አንድ ነገር ካደረክ ብቻ ነው ፤ካልሆነ አላደርግልህም አለው።” ስላደረገው ነገር ይቅርታ በብርቱ የሚፈልገው ወጣት ስለጉዳዩ ምንነት ጠየቀ።
ባለ ሙዝ ማሳው እንዲህ አለ ። “ልጄ አካል ጉዳተኛ ናት መናገር አትችልም፤ እግርም የላትም ። ማግባት ትፈልጋለች፤ እስዋን ካገባሃት ነው ይቅርታ የማደርግልህ” አለው ። ይሄኔ ወጣቱ ተሸበረ ። የሰውን እንዳይነካ እየነገረች ያሳደገችው እናቱ በፍፁም በታማኝነቱ እንዲዘልቅ ቃል ያስገባችው ወላጅ እናቱን ቃል ለማክበር እስከ ዛሬ ድረስ ጥሮ ዛሬ ሊወድቅ ነው ። ስላደረገው ዕምነት ማጉደል ይቅርታ ለመጠየቅ ቢሞክርም የበለጠ ከባድ ነገር ገጠመው፤ ተጨነቀ፤ ብዙ አሰበ፤ አወጣ አወረደ። ይቅርታ ማግኘቱን በብርቱ ፈልጓል ፤ነገር ግን ማግኘት አልቻለም። ይቅርታውን ለማግኘት አድርግ የተባለው ግን ከበደው ። በጭንቀቱ መሀል እንዲሁ በደመ ነፍስ “ይቅርታዎች በጣም ስለምፈልግ እሺ” የሚል ቃል ተነፈሰ ።
ሰውየው ማመን አቃተው ፤በፈገግታ ተሞልቶ ወደ ዋናው ቤቱ ይዞት ሄደ ። ገና ግቢ ሲገቡ እጅግ የተዋበች ወጣት ልጅ በረንዳ ላይ ቁጭ ብላ ተመለከተ ። ልጅትዋ አባትዋን ስታይ እየተፍለቀለቀች ቀርባ “አባዬ! እንኳን በደህና መጣህ፤ ምሳ ደርሷል ፤ስንጠብቅህ ነበር ። ብላ እንግዳውን ወጣት ሰላምታ ሰጥታ ተቀበለቻቸው ።
ሰውየው ወጣቱን ከምሳ ግብዣ በኋላ ይዘውት ወደተዋበው ማረፊያ ክፍላቸው ወስደውት ። “ልጄ ታማኝነትህ ደንቆኛል ። በዚህ ዘመን እውነተኛ ሰው መሆንህ እንድወድህ አድርኛል ። ልዛመድህም ፈልጌያለሁ።
አካል ጎደሎ ናት ያልኩህ አውቄ ነው። ልጄ የቅድምዋ ምንም ያልጎደላት ውብዋና ቆንጆ ነች። የአንተ ታማኝነትና መልካምነት አስገርሞኝ ብዙዎች ሲጠይቁኝ የከለከልኳቸውን ልጄን እንድታገባት እፈልጋለሁ፤ በረሀብ ምክንያት እምነትህን አጉድለህበት የነበረው የሙዝ ማሳም ከአሁን ጀምሮ የአንተ እንዲሆን ወስኛለሁ ። ከዛሬ ጀምሮ አንተ ልጄ ነህ ።” ሲሉት የወጣቱ አይኖች በእንባ ተሞልተው ነበር። ተፈፀመ።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 22/2013