ፈጣሪ ለሰው ልጆች ምህረትና ድኅነት ለመስጠት ሲል ብዙ መከራና ስቃየን ተቀብሏል ። ተገርፏል፣ ተደብድቧል፣ተተፍቶበታል፣በመስቀል ላይ ተሰቅሏል፣ ሞቷል ፣ከሙታን ተለይቶም በትንሳኤው ብርሃን ተነስቷል። እነዚህን የክርስቶስ መከራዎች ሁሌም በሕይወት መስመራችን የምናስባቸው ናቸው ። በዚህ በሰሞነ ህማማት ደግሞ የማሰብ መጠናችን ከፍ ይላል። በከፍተኛ ኃዘንና ቁዘማ ውስጥ ሆነንም ስለሰው ልጆች የተቀበለውን መከራ እያሰብን ምህረትን እንዲልክልን የምንማጸንበት ጊዜም ነው። በሰሞነ ህማማት የምንተገብረው ሌላው ኃይማኖታዊ ግዴታ ደግሞ አምስቱን ቀናት ከመጨባበጥ፣ ከመሳሳምና ከመተቃቀፍ መራቅ ነው ። ይህ ወሳኝ ኃይማኖታዊ ግዴታ ደግሞ በተለይም አሁን ላለንበት ጊዜ እጅግ በጣም አስፈላጊና መሰረታዊ ሆኖ አግኝቸዋለሁ ።
አዎ ድሮ ድሮ ጓደኞቻችንን አቅፈን ሰላም ማለት ያስደስት ነበር ፤ ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ተቀራርበንና በአንድ ጠረጴዛ ከበንም እየተጫወትን እየሳቅን መብላት መጠጣቱም የሚናፈቅ የሚያስደስት ተግባር ነበር፤ ነገር ግን ዛሬ ላይ ይህ ሊሆን አልቻለም ። ምክንያቱ ደግሞ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ነው ።
ታዲያ ይህ ወረርሽኝ ትልቁ መከላከያው አለመጨባበጥ፣ አለመነካካት እንዲሁም ርቀትን መጠበቅ ነውና ከዚህ በኋላ በተለይም በሽታው ከአገራችን ሙልጭ ብሎ እስኪጠፋ ድረስ እያንዳንዷን የምናሳልፋትን ቀናት እንደ ህማማቱ ብናደርጋትስ ብዬ አሰብኩ።
ህማማት ምናልባት በዓመት አንድ ጊዜ መጥቶ ለአምስት ቀናት አለያይቶን ከዛም በትንሳኤው አስደስቶንና አስተቃቅፎን አብረን እንድንበላ፣ እንድንጠጣና እንድንደሰት የሚፈቅድ ነው ። ነገር ግን ኮቪድ 19 እንደዛ አይነት እድልን አይሰጥም፤ ላለፈው አንድ ዓመት ከእነዚህ ከለመድናቸው የእለት ተዕለት ተግባራቶቻችን እንድንርቅ ተገደናል፤ አሁንም ይህ ግዴታ አላበቃም፤ እንዲያውም የበለጠ ጠንቃቃ መሆንን እየጠየቀም ነው ። ታዲያ በሰሞነ ህማማቱን ለዛውም በዓመት አንዴ ለአምስት ቀናት ታማኝ ሆነን የምንተገብረውን ሕግ ለጤናችንና በሕይወት ለመኖር ስንል ብናስቀጥለውስ።
የአገሬ ሰው “ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ” ይላል አዎ ኮቮድ 19ን መጠንቀቅ የሚቻለው የሰሞነ ህማማቱን ሕግና ትዕዛዝ የኑሯችን አካል አድርገን መንቀሳቀስ ስንችል ብቻ ነው ። ታዲያ ከእኛ መኖር የሚበልጥ ነገር አለ እንዴ ? የለም እኮ ፤ዛሬ ይህንን መጥፎ ቀን ተሻግረን ነገን ማየት ከቻልን እንደ ድሯችን እንደ ባህል ወጋችን አብረን እንሆናለን ። ዛሬን ግን አልተፈቀደምና እንራራቅ ፣ አንጨባበጥ፣ አንሳሳም በተቻለ መጠን እራሳችንን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም እንጠብቅ ።
ሁሌም በየዓመቱ ህማማቱን በማሰብ ከመሳሳም ከመጨባበጥ ከመነካካት ውጭ ሆነን እናሳልፋለን ። ይህ ሁኔታ ሃይማኖታዊ በረከቱ ቀላል የሚባል አይደለም። ሃይማኖታዊ በረከትን ለማግኘት ግን እኛ በሕይወት መቆየት አለብን። ወገኖቼ ህማማትን የሕይወታችን አንድ አካል እንድናደርግ በዚህም ኮቪድን አሳፍረነው እራሳችንንም አገራችንንም ከከባድ ችግር ልንወጣ የምንችልበት ጊዜ ላይ ነን ።
በእርግጥ ሰሞነ ህማማቱ የሚመለከተው የክርስትና እምነት ተከታዮችን ብቻ ቢሆንም መልካም ነገርን ግን ወደ ሌሎችም የሃይማኖት ተከታዮች እንዲሁም ወደመላው የአገሪቱ ሕዝብ ማጋባት ችግር የለውም። ስለዚህ እንደ አገርና እንደ ሕዝብ ይህ መጥፎ ቀን እስኪያልፍ ሁሉንም ቀናት፣ ሳምንታት እንደ ሰሞነ ህማማቱ ከመጨባበጥ ከመተቃቀፍና ከመሳሳም አንርቅም ።
ብዙዎች ለራሳቸውና ለአገራቸው ብዙ መስራትና ቤተሰባቸውን ማስተዳደር በሚችሉበት ጊዜ እያጣናቸው ነው፤ በእድሜ የገፉ አዛውንቶችም ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው እንዳያስታምሟቸው የሚያደርግ በሽታ ነው። ብቻቸውን ከሞት ጋር ታግለው እንዲያልፉ እየተገደዱ ነው ። ታዲያ ይህንን ሁኔታ ለማምለጥ ምነው ሁሉም ቀናት ህማማት ቢሆኑ አያስብልም ወይ?።
አንዳንድ ጊዜ ከጤና ባለሙያዎችም ሆነ በዘርፉ ካሉ አካላት የሚነገሩ ነገሮች እኛን የሚመለከቱ የማይመስለን ብዙዎች ነን፤ ካልደረሰብኝ አላምንም እያልን ከበሽታ ከስቃይ ጋር ለመጋፈጥ እራሳችንን ያዘጋጀንም አንጠፋም ፤ ነገር ግን በሽታው ጎብኝቷቸው የፈጣሪን ምህረት አግኝተው የተረፉ ሰዎች ሲናገሩ እንደሚሰማው አብዛኞቻችን እንዳቀለልነው ሳይሆን ብዙ ስቃይ ያለው ከዛም ከሞት ጋር የሚያፋጥጥ ዘመድ አዝማድ ቤተሰብ የሚያርቅ ነው ።
ታዲያ መጠንቀቅ ስንችል ለምን እንሰቃይ ወገኖቼ “ቀን እስኪያልፍ ያለፋል” ነውና በተቻለ መጠን እራስን መጠበቅ፤ ልንከተላቸው የሚገቡ የጤና መጠበቂያዎችን በአግባቡ መተግበር ፣አታድርጉ ከተባሉት ነገሮችም መራቅ እድሜን ለማርዘም መንገዱ ሆኗልና ሁሌም እራሳችንንና ሌሎችን ለመጠበቅ አንቦዝን እላለሁ ።
የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ (ማስክን) ለራስ ጤና ብለን ሳይሆን በመንገድ ላይ ላሉ ፖሊሶች የምናደርግ፣ እኛን በሽታ አይነካንም ብለን በዘፈቀደ ሰው ላይ የምንጠመጠም ፣ የምንጨባበጥ ተቃቅፈን ሰላምታ ስንለዋወጥ የምንውል ሰዎች ለራሳችን ማሰብ ካልፈለግን ለሌሎች ሰዎች እንጨነቅ ። ምናልባት በትንሽ ጥንቃቄ ትልቁን መከራ ማለፍ ስንችል ይህ ሁሉ የበዛ መዘናጋትና እኔን አይነካኝም የሚል እብሪት ከምን የመነጨ ይሆን? ወገኖቼ ከሞቱ አሟሟቱ የሚያስብል እግዚአብሔር ይማርህ ተብሎ የማያጠያይቅ ሰው ከሰው የሚያፈራራ ፣ቤተሰብ ውሃ ሳያጠጣ ሳይዳብስ፣ የማጽናኛ ቃልን ሳይናገር የሚረዳህን የጤና ባለሙያ መልክ ሳታየው በብዙ ስቃይና መከራ ከማለፍ ሁሉንም ቀናት እንደ ሰሞነ ህማማቱ ማድረጉ ሳይሻል አይቀርም ባይ ነኝ።
በአሁን ጊዜ በሽታው እየተስፋፋ ነው ። አገራችን በበሽታው የሞቱም ሆነ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ነው ። እንዲሁም በሩቅ ስንሰማ የነበረው ነገር ሁሉ የእያንዳንዳችንን ቤት እያንኳኳ ነው ። ከዚህ ነገር ማምለጥ የሚቻልበት ብቸኛ መንገድ ደግሞ ራስን መጠበቅ በአግባቡ የህክምና ባለሙያዎችን ምክር ሰምቶ መተግበር ሲቻል መሆኑን ተደጋግሞ እየተነገረን ይገኛል ። እራሳችንን ከምንጠብቅበት መንገድ አንዱ ሁልጊዜ በሰሞነ ህማማቱ የተከለከሉትን ተግባራቶች መፈጸም ስንችል ብቻ ነው ።
ወገኖቼ በተቻለ መጠን እራሳችንን ጠብቀን የነገዋን ጸሐይ እንያት፤ በቸልተኝነት ለሚያልፍ ዝናብ አንመታ፤ አገርንም ከፍተኛ የሆነ ችግር ውስጥ አናስገባ ። ሁሌም ሰሞነ ህማማቱን የተከለከሉ ተግባራትን ኮሮና እስኪጠፋ ድረስ ተግባራዊ እናድርግ ። የከርሞ ሰው ይበለን።
በእምነት
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 22/2013