“ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም” የሚለው ብሂል በዚህች አነስተኛ ቤት ውስጥ አይሠራም። ደሣሣዋ ቤት በጭስ ታፍናለች። ከውጭ ወደ ውስጥ ለሚዘልቅ እንግዳ የቤተሠቡን አንደኛውን አባል ከሌላኛው ፈጥኖ ለመለየት እጅጉን ይከብደዋል። እነርሱ ግና ተላምደውታል።
ከቤቱ በአንደኛው ጥግ ከምድጃው ላይ የሚታየው ሠፊ ብረት ምጣድ ሥራውን አልፈታም። የገብስ ቆሎ እየተቆላበት ነው። የእማ ትሁን ሁለት ሴት ልጆች የደረሰውን የገብስ ቆሎ ከጋለው ብረት ምጣድ ላይ ግፈው ለምሽት ገበያ ለማቅረብ ባዶ ሰሐኖቻቸውን ታቅፈው ከዳር ተቀምጠዋል።
ከወዲያ ማዶ ካለው የሣር ፍራሽ ባዶ ጡጦውን እንደ ጎረሰ መለ መላውን የተንጋለለው ሕጻን ለእማ ትሁን ፋታ ሰጥቷቸዋል። የዛሬ ዓመት ገደማ በሞት የተነጠቀችው የመጀመሪያ ልጃቸው ፍቅርተ ትታ የሄደችላቸው ቀሪ ሐብት ቢኖር ይኸው ሕጻን ነው።
ወይዘሮዋ አያት ለመሆን መብቃታቸውን እንደ ዕድል ቢቆጥሩትም መላ ቤተሠቡን የማስተዳደሩ ኃላፊነት በጫንቃቸው መውደቁን የሚቋቋሙት አልሆነላቸውም። ኑሮው ከብዷቸዋል – ይኼም ኑሮ፣ ይኼም ሕይወት ከተባለ።
ብረት ምጣዱን እንዳጋለው እሣት ኑሮውም የዚያኑ ያህል የሚፋጅ ሆኖባቸዋል። ኑሮን ለማሸነፍ የቤተሠቡ አባላት እንደየአቅማቸው ይታትራሉ – ግና አልሆነላቸውም። አንዱን ቀዳዳ ሲሸፍኑት ሌላው አፍጥጦ ይመጣል፣ ያኛውን ሲደፍኑት በሌላው ይፈሣል። ሕይወት በአዲስ አበባ – ቄራ እንዲህ እንደ ዋዛ የሚቀመስ አልሆነም። በተለይ…በተለይ ለወይዘሮ ትሁን ብጤዎች።
አሁን ላይ የኑሮው ውድነት መሽቶ በነጋ ቁጥር እያሻቀበ መሄዱ ነበር ሌላው ጣጣ። እንዲህም ሆኖ ወይዘሮ ትሁን እጅ አልሰጡም። “እጅ አልሰጥም” ብሏል ሐበሻ። ነገን በተስፋ ይኖሯታል። በዚህችው አነስተኛ ቤት ውስጥ ይህን…ይህን እያሰላሰልኩ በሐሳብ ብቻዬን ቆዘምኩ።
ጦርነት ማባሪያ አጥቶ በክርኑ ቁልቁል ይደቋቁሣት፣ ስደት፣ ረሐብ ብሎም በሽታ አንዴ የአይችይቪ/ኤድስ ሌላ ጊዜ የኮሮና ጦስ አልፋታት እያለ፤ የዜጎቿ መለያ እስኪመስል ዓለም ይጠቋቆምባት በነበረችው በዚህችው በእኛይቱ አገር ስንት ጉድ አይተናል፣ ስንት መከራ አሣልፈናል – ተነግሮ የማያልቅ።
እንዲያም ሆኖ ዛሬ ሌላ ቀን ነው። ለዓመታት ቋንጃችንን ጠፍሮና ማንቁርታችንን አንቆ ይዞ የኖረው ፈርጀ ብዙ መከራ በአንዲት ጀንበር ከላያችን ተሽቀንጥሮ ይወድቃል ብሎ አጉል ተስፋ የሚሰጥ ካለ ግብዝ ከመሆን ባለፈ የጤና አይመስለኝም።
ለዓመታት አብሮን የዘለቀው ይህ ስቃይ ኧረ እስከ ወዲያኛው ፈጽሞውኑ ሊላቀቀን አይቻለንም ብሎ ተስፋ ቆርጦ የሚደመድም ካለም እሱም “ጨለምተኛ” እንጂ ምን ሊባል ይቻላል።
ለዘመናት ሲወርድ ሲዋረድ፤ ከአንደኛው ወደሌላኛው ሥርዓት በቅብብሎሽ ሲንከባለል የመጣን የኑሮ ፈተና ዳግም እንዳያገረሽ በመላ ይዞ ለተሻለ ቀጣይ ሕይወት የቤት ሥራዎችን በቅጡ እየከወኑ፣ መደላድሎችንም እያሠማመሩ መጓዝ ደግሞ የአባት ነው።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ በሁሉም መስክ ሊባል በሚችል ደረጃ ለውጥ መጥቷል። ለዕድገት ተስፋም መታየቱ እውነታ ነው። ይህንንም ‘ኧረ የለም’ ብሎ የሚሞግት ከተገኘም በሥልጣን ላይ ያለውን የለውጥ መንግሥት ‘ያሳጣልኛል’ ብሎ ካላሰበ በቀር በእጁ ላይ የሚቋጥረው ሚጢጥዬ ሐቅ እንኳን ያጣል ተብሎ አይገመትም።
እስቲ ጥቂት እንጠቃቅስ። ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መሥመሩን ይዟል። ብዙ ጋሬጣዎችን እያለፈ ቢሆንም የመጀመሪያው የውሃ ሙሌት በስኬት ተጠናቅቋል። ሁለተኛው ሙሌት በክረምቱ እውን ይሆናል። ዳመና ቋጥሮ ዝናብ በመጣል ተስፋ አሣይቷል። ትናንት ዓለም ሲሳለቅባት የነበረችው ይህች የጋራ አገራችን ወደብልፅግና ለመሸጋገር ቀበቶዋን አጠባብቃለች። በዚህ ረገድ ብዙ…ብዙ ማለት ይቻላል። ለጊዜው ባልፈውስ – እናም ቀደም ወዳነሣሁት የኑሮ ውድነቱ ልመለስ።
በርግጥም በኢትዮጵያ መሽቶ በነጋ፣ ነግቶ በመሸ ቁጥር የመሠረታዊ ዕቃዎች የመሸጫ ዋጋ መቆሚያ አጥቷል። ሁሌም ያለምክንያት እያሻቀበ ሲሄድ ታዝበናል። አሁንስ ሠማይ ሊነካ ምን ቀርቶታል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ጊዜያት የተከሠተው የምጣኔ ሀብት ቀውስ፣ ከእለት እለት የነዳጅ ዋጋ ከፍ ማለት፣ የአሜሪካ ዶላር የምንዛሪ ተመን በየጊዜው ማሻቀብ በምክንያትነት ሊጠቀሱ ይችላሉ። ጨርሶውኑ ከእነዚህ ጉዳዮች ጋር ተያያዥነት በሌላቸው ምርቶች ላይ የሚደረጉ የተጋነኑ የመሸጫ ዋጋ ጭማሪዎችም ራስ ምታት ሆነውብናል።
ታዲያ እነዚህ ጉዳዮች ተደማምረው የፈጠሯቸው ጫናዎች በተለይ …በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ፍዳቸውን እንዲያዩ እያስገደዷቸው መጥተዋል። ይኼም የየዕለቱ ነባራዊ እውነታ ነው።
ዜጎች በሚያገኟቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ድምጻቸውን እያሠሙ ናቸው። መንግሥት በጉዳዩ ላይ ጣልቃ ይገባ ዘንድ ይወተውታሉ፤ ይጠይቃሉ። በተፈጠረው ሠው ሰራሽ የኑሮ ውድነት ቅድሚያ ተጎጂ ለሆነውና በዝቅተኛ ገቢ ላይ ለሚገኘው የኅብረተሰብ ክፍል በአፋጣኝ ሊደርስለት ይገባል። በዚህ ሁሉም ይስማማል። የተከሰተውን የዋጋ ንረት መንስዔ መመርመር፣ በዘላቂነትም የመፍትሄ ርምጃዎችን መውሰድ ተገቢነቱ አያጠያይቅም። በሚፈለገው ደረጃም ባይሆን መልካም ጅምሮች ግን ይታያሉና ተጠናክረው ቢቀጥሉ።
የምርት አቅርቦቱ ከፍላጎት ጋር እስኪጣጣም፣ ጤናማ የገበያ ውድድር እስኪፈጠር ብሎም ሸማቹ መብቱን መጠየቅ ከሚችልበት ደረጃ ላይ እስከሚደርስ ቁጥጥር ማድረግ ተገቢ ይሆናል እላለሁ።
ይህ ከሆነም መንግሥት ሠፊ የሕዝብ ይሁንታንና ድጋፍን ያገኛል። “ጎሽ፣ አበጀህም” ይባልለታል። በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ባለው የኅብረተሰብ ክፍል ውስጥ መልካም ስሜትንም ይፈጥራል። ቅጥ ያጣና መረን የለቀቀ ሕገ ወጥነትን “ሃይ” ማለቱ ተገቢነት አለውና። ከመጠን ባለፈ ስግብግብነት የዋጋ ንረትን ማባባስ አይገባም። ዜጎች በኑሮ ውድነቱ ትከሻቸው ጎብጦ፣ አንገታቸውን እንዲደፉ፤ ሞራላቸው እንዲላሽቅ ብሎም በጥቂቶች እግር ሥር እንዲንበረከኩ መፍቀድ በዚህች አገር መታሰብ የለበትም። ሁሉም ከአገሪቱ ብልፅግና በፍትሐዊነትና በእኩልነት ተጠቃሚ ይሆን ዘንድ የፀና አቋም ሊኖረን ይገባል።
መላ ሕዝብ ላለፉት ረዥም ዘመናት የሠላም፣ የዴሞክራሲና የልማት እጦት ረሃብተኛና ጥማተኛ ሆኖ ኖሯል። ይህን ሊያስታግስ፣ ጥማቱን ሊያረካ፣ ይፈልጋል። ውጤቶቹን ሊያጣጥም፣ ትሩፋቶቹን ሊቋደስ ይሻል። ከዚህ ማዕድ ላይ መነቀልን አይመርጥም። እምነትና ተስፋ ጥሏል።
ከዚያች ጠባብ ክፍል ከተቀመጥኩበት በርጩማ ላይ ሆኜ ወደ ኋላዬ ተንጠራራሁ። እማ ትሁን እንደ ጎረቤቶቻቸው ተነሳስተውና የሚሰማሩበትን የሥራ መስክ ለይተው አውቀው ምናልባትም በተለያዩ የብድር አገልግሎቶች ተጠቃሚ ቢሆኑ ይመረጣል። እርሣቸውና መሰሎቻቸው በዚህ ዕድል ተጠቃሚ ሣይሆኑ እስካሁን ስንቱን አሣልፈው ይሆን? ምናልባት ድፍረቱን አጥተው አሊያም እውቀቱ ጠፍቷቸው ቀርተው ይሆን? አሁንም ቢሆን ጊዜው አልረፈደም። እኔም በምክርና ሐሳብ አበረታታኋቸው። ከደረሱ ሁለት ልጆቻቸው ጋር ሆነው አዋጭ የሥራ ዕድሎችን ፈትሸው የብድር አገልግሎቱ ተጠቃሚ በመሆን ኑሯቸውን እንዲለውጡ ምክሬን ለገስኳቸው። በዚህ አይነት መንገድ ሰርተው የተለወጡ ስለመኖራቸውም ምሳሌ እየጠቀስኩ አቅጣጫውን አመለክትኳቸው።
ዓይኖቻቸውን ከምድጃው ውስጥ ከሚንቀለቀለው እሣት ላይ ተክለው ቀሩ። ካቀረቀሩበት እንደተመለሱ ሁለቱንም እጆቻቸውን አቆላልፈው ይዘው አንገታቸውን ላይ ታች ነቀነቁ። አዎ! ሕይወት መለወጥ ትችላለች – በውስጣቸው ለራሳቸው ቃል ገቡ።
ጋሻው ጫኔ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 21/2013