ፍቅር
ባለፈው ሳምንት በዚህ የእንወራወር አምድ ‹‹ዜጎችን ከምርጫ ጥላቻ መታደግ ያስፈልጋል›› በሚል ርዕስ የቀረበ ጽሑፍ አንብቤአለሁ።ጽሑፉ በ6ኛው አገራዊ ምርጫ ዜጎች በምርጫው ድምጽ ለመስጠት የሚያስችላቸውን ካርድ በመውሰድ በኩል መቀዛቀዝ እንደሚታይባቸው በመግለጽ ለእዚህ ምክንያት ተድርጎ ያቀረበው ሀሳብ ወጣ ያለና ጥሩ እይታ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።መራጩ ሕዝብ ለዘመናት በተካሄዱ ምርጫዎች የተካደ መሆኑን ተከትሎ በአጠቃላይ ለምርጫ ያለው አመለካከት በጥርጣሬ የተሞላ መሆኑን ጸሐፊው ጠቁመዋል።በተጨማሪም አገሪቱ ጥሩ የምርጫ ታሪክ የሌላት መሆኗንም በመጥቀስ ይህም በመራጩ ላይ በሚገባ እንደሚንጸባረቅ ተመልክቷል።በዚህ የተነሳ ሕዝቡ የምርጫ ፎቢያ ወይም ጥላቻ እንዳደረበት በመጥቀስ ሕዝቡ በምርጫው በንቃት እንዲሳተፍ ለማድረግ በቅድሚያ አመለካከቱ ላይ መስራት ያስፈልጋል ተብሏል፡፡
እርግጥ ነው አገሪቱም ሕዝቧም ጥሩ የምርጫ ታሪክ የላቸውም።በምርጫ 1997 ትንሽም ቢሆን የምርጫ ጭላንጭል ታይቶ ነበር፤ ምርጫው ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲ የታየበት፣ሕዝቡም ሆነ ፓርቲዎች ጥሩ ቅስቀሳ ያደረጉበትና ሕዝብ የፈለገውን ፓርቲ በነጻነት የመረጠበት ነበር፤ በእርግጥም ያ የምርጫ ዘመን አገር ምርጫ ምርጫ ያወደችበት ነበር።
ያ ጭላንጭል ግን ከምርጫ በኋላ በተካሄደ የኮሮጆ ግልበጣ የቀደሙትን ዘመናት የምርጫ ታሪኮች ለመቀላቀል ተገዷል።ኢህአዴግ ያንን ሁሉ ድካም የምርጫው ዕለት ሌሊት ገደል ከቶት አደረ።ከዚያ በኋላ ብዙ ክፉ ነገር ሆነ፡፡
በዚያ ምርጫ ንቁ ተሳትፎ ያደረጉት በሙሉ የተረፋቸው በውድቅት ሌሊት ደዴሳ መጋዝ ነበር።ጎበዝ! ነጻውን ጋዜጣ ታነባለህ ተብለው ደዴሳ የተወረወሩ አውቃለሁ።በአጋጣሚ ሰልፍ ውስጥ የገባ መንገደኛ ከሰልፈኛው ጋር ተጠርጎ እንዲሁም የአእምሮ ህሙማን ደዴሳ ተወርውረዋል እኮ።ተማሪዎች በተለይ ቆይቶ ቆይቶ ሕይወታቸውን ሙሉ ለጤና መታወክ ሊዳርጋቸው በሚችል መልኩ ስስ አካላቸውን ተቀጥቅጠዋል፤ ታስረዋል።ከዚያ በኋላ የተካሄዱት ምርጫዎች የምር ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሌሉባቸው፣ የይስሙላ ወይም የተገዙ ፓርቲዎች ቂን ቂን ያሉባቸው ናቸው።እናም ይህን እውነታ የተመለከተ፣ በዚህ እውነታ ውስጥ የኖረ ዛሬ ምርጫ ላይ እግሩን ቢጎትት አይገርምም።በዚህ ውስጥ ያለፉ ሁሉ የማንትሴን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም፤ እዚያው በጠበላችሁ ሊሉ እንደሚችሉ ይታሰበኛል።
እነዚህ ዜጎች የምርጫ እንቅስቃሴን ሁሉ ባለፉት ዓመታት የምርጫ ሥራዎች ነው የሚተጐሙት። ቀጣዮቹን ምርጫዎች ቢጠራጠሩ፣ ቢፈርጁ አይፈረድባቸውም።መቶ በመቶ አሸናፊ እየተሆነ የተመጣበት ሁኔታ በቀጣይም የአገራችን ምርጫ ከዚህ አይወጣም ብለው አትድረሱብን፤ አንደርስባችሁም ቢሉም አላጠፉም።
ገዥው ፓርቲ በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች እየደለለ እና እያስገደደ ዜጎች በምርጫው ድምጽ እንዲሰጡ ሲያደርግ ነው የኖረው።ራሱ ተመልሶ እንደሚመጣ እየታወቀ ሕዝቡንና ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማታለል በሚል የአገር ሀብት በከንቱ እንዲወድም ተደርጓል።
ከእንደዚህ ዓይነቶቹ ምርጫዎች ምንም የተማርነው በሌለበት ሁኔታ፣ በዘንድሮው ምርጫ ዜጎች ከዚህ ዓይነቱ አመለካከት ይላቀቁ ዘንድ የረባ የግንዛቤ ሥራ ባልተከናወነበት ሁኔታ በምርጫው በንቃት ተሳተፍ ተብሎ ሲጠራ አቤት ለማለት አለመፍጠኑ አያስደንቅም።
እናም ያለፈው ሳምንት ጽሑፍ በዘንድሮው ምርጫ ሕዝቡ ካርድ ለመውሰድ ተቀዛቅዞ የነበረበት ሁኔታ ጥሩ የምርጫ ታሪክ ስለሌለውና ይህን ታሪክ ለመቀየር እየተከናወነ ስላለው ተግባርም በቂ ግንዛቤ ስለሌለው ነው ተብሎ መጻፉ ትክክል ነው።
እኔ ደግሞ በመራጮች በኩል ታይቶ ለነበረው መቀዛቀዝ ምክንያቱ የመራጩ ችግር ብቻ አይደለም እላለሁ።ችግሩ የምርጫ ቦርድም እንደሆነ ነው የሚሰማኝ።ቦርዱ ምዝገባው የተቀዛቀዘ መሆኑን በገለጸበት ወቅት ከ50 ሺህ የምርጫ ጣቢያዎች ግማሹ ብቻ መራጮችን እየመዘገቡ እንደነበረ ጠቁሟል።የምዝገባው ሂደት በዚሁ መልኩ በተካሄደበት ሁኔታ የሚጠበቀውን ያህል ሕዝብ ካርድ ለመውሰድ አልወጣም ብሎ ግንዛቤ መያዝ ትክክል አልነበረም።
ቦርዱ ቆይቶም ቢሆን የመራጮች ምዝገባ ሂደትን ገምግሞ ምዝገባው ችግር እንደነበረበት መለየቱ እንደ ጥሩ ነገር መውሰድ ይኖርበታል።ተቀዛቅዞ ለነበረው የመራጮች ምዝገባ ምክንያቱ መራጮች ብቻ አለመሆናቸውን ለማወቅ አስችሏል።ቦርዱም በራሱ ያልሰራው እንዳለ መመልከት አስችሏል።ከዚያ ግምገማ በኋላ በምዝገባው ላይ ለውጥ ማየት ተችሏል፡፡
ፓርቲዎቹም መራጩን ሕዝብ በምርጫው በንቃት እንዲሳተፍ የሚያስችል ሥራ ሰርተዋል የሚያሰኝ ሁኔታ የለኝም።ሰርተው ቢሆን ኖሮ እንደ ፓርቲዎቹ ብዛት በርካታ መራጮች በተመዘገቡ ነበር።
የሲቪል ማህበራት በምርጫ ያላቸው ገንቢ ሚና ከፍተኛ ቢሆንም፣ በመራጮች ምዝገባ በኩል አሻራቸው ብዙም አልታየም።ሕዝቡን ስለምርጫው አንቅተውት ቢሆን ኖሮ መራጮች እየተመዘገቡ ያሉበት ሁኔታ ባልተቀዛቀዘ ነበር።
ማህበራቱ ከምርጫ 97 ወዲህ ባሉት ምርጫዎች ላይ ብዙም እንዳልታዩ ይታወቃል።ምክንያቱም በምርጫ 97 ዴሞክራሲያዊነት ላይ የተጫወቱት ሚና ኢህአዴግን ማስቆጣቱ ነው።ይህን ተከትሎ በኢህአዴግ መራሹ መንግሥት ተደቁሰዋል።የውሾን ነገር ያነሳ ተብለው ባለፉት ዓመታት የምርጫን ነገር ሳያነሱ ቆይተዋል።ሕግ በማሻሻል ጭምር ነበር ሽባ የተደረጉት።
የለውጡ መንግሥት ቅድሚያ ሰጥቶ እንዲሻሻሉ ከሰራቸው ሥራዎች መካከል የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ማቋቋሚያ አዋጅን ማሻሻል ይገኝበታል።ይህ ምርጫ የማህበራቱ ሚና እንዲጎለብት የሚያስችል ነው።በዚህም በዘንድሮው ምርጫ ሚናቸው ከፍተኛ እንደሚሆን ይጠበቃል።እስከ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ጥሩ ቁመና ላይ አይደሉም።የመራጮች ምዝገባ የሚጠበቀውን ያህል ብቻ ሳይሆን በእጅጉ መቀዛቀዝ ለታየበት ሁኔታ ከተጠያቂዎቹ መካከል እነዚሁ የሲቪክ ማህበራት ይጠቀሳሉ ።
በርካታ ወገኖች ትናንት ጥሎባቸው ያለፈው አሻራ አላላውስ ብሏቸው ይታያሉ።ትናንት ዛሬአቸውንና ነገአቸውን ቀፍድዶ ይዞባቸዋል።ይህ ደግሞ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ይንጸባረቃል።የትናንቱ ምርጫ ጥሎባቸው ያለፈው መጥፎ ጠባሳ የዛሬውንና የነገውን እየፈሩና እየተጠራጠሩ እንዲመለከቱ አላደረጋቸውም ማለት አይቻልም።
ይህ ሁኔታ መቀየር አለበት።ሁሉም ክፉኛ ከተቸከለበት ትናንት ራሱን ማላቀቅ ይኖርበታል።እርግጥ ነው ትናንት ለዛሬም ለነገም መሠረት ነው።ከዚያ ባለፈ ግን ዛሬንም ነገንም ተከቶ ሊቆም አይችልም።ከትናንት መውሰድ የሚገባውን በመውሰድ ዛሬንና ነገን እንደዛሬና ነገ መኖር ያስፈልጋል።
ያለፉትን ዘመናት የምርጫ ታሪክ መቀየር በሚያስችለን ወሳኝ ወቅት ላይ እናገኛለን።ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫችንን በዛሬና በነገ ላይ ቆመን እናስፈጽም። መንግሥት የምርጫውን ታሪክ ለመቀየር ቁርጠኛ መሆኑን በተደጋጋሚ አረጋግጧል።በዚህች አገር ከዚህ በኋላ ስልጣን የሚያዘው በምርጫ እና በምርጫ ብቻ ነው እያለ አስረግጦ እያስገነዘበ ነው።ይህን ለማድረግ የሚያስችሉ ሁኔታዎችም መሬት ላይ ይታያሉ።መረጃዎቹን ተጠቅሞ ራስን ለምርጫው በማዘጋጀት የታሪኩ ተጋሪ መሆን ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 19/2013